Sunday, January 17, 2016

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ
በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምኢ እዝነኪ”
“በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ” (መዝ. 44/45፥9-10)

ይህን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በሚያነብብ በአብዛኛው ሰው አእምሮ ውስጥ በቶሎ የምትከሠተው ድንግል ማርያም ናት። ይህ የሆነው ጥቅሱ ስለ እርሷ የተነገረ ስለ ሆነ ግን አይደለም። ስለ እርሷ የተነገረ ነው ተብሎ ስለ ተወሰደ፥ በተደጋጋሚ ከእርሷ ጋር ተያይዞ ስለ ተነገረ፥ በየወሩ በ21 ለበዓለ ማርያም የሚዜም ምስባክ ስለ ሆነ ነው ስለ እርሷ የተነገረ ያህል እየተሰማን የመጣው። ቅድስት ድንግል ማርያምን ንግሥተ ሰማይ ወምድር ብለው የሚያምኑ ክፍሎች፥ ሐሳባቸውን በዚህ ጥቅስ ለማስደገፍ ይሞክራሉ። እርሷን በንጉሥ እግዚአብሔር ቀኝ እንደ ተቀመጠች ንግሥትም ይቈጥሯታል።

ቃሉ ስለ ማን እንደ ተነገረ ከመጽሐፉ ተነሥተን እንመልክት። ጥቅሱ ለሚገኝበት ለዚህ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የዐማርኛው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ “ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ባሳተመችው የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም “ለመዘምራን አለቃ በመለከቶች የቆሬ ልጆች ትምህርት የፍቅር መዝሙር” በማለት ይህንኑ ርእስ ነው ያስቀመጠው።

Monday, January 4, 2016

ሐሰትን እውነት ለማድረግ መታገል ማንን ለመጥቀም?

መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተላኩ ቅዱሳን ሰዎች የጻፉትና ምንም ማሻሻያ ሳናደርግ የምንቀበለው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምናምነውን፣ የምንቀበለውንና የምንታዘዘውን ወይም የምንኖርበትን እውነት የያዘ ብቸኛ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የክርስትና ትምህርትና ሥርዐት ምንጭና መመዘኛ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከነቢያትና ከሐዋርያት የተቀበለችውና የተመሠረተችበት እውነት መጽሐፍ ቅዱስ በመኾኑም፣ እንደ ዐይን ብሌን ልትጠብቀው ይገባል፡፡

እንዲህ የተባለው በከንቱ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዘመን እየ ራቀች በሄደች መጠን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም ከእዚያ ውጪ የኾኑ የተለያዩ ትምህርቶችን፣ ሥርዐቶችንና ልምምዶችን አዳብራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርትና ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ከሌለው ትምህርትና ልምምድ ጋር እየተዛነቀ በሄደ ቍጥር ትምህርቷ ድብልቅ እየ ኾነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ እየ ደበዘዘ እና ሌላ መልክ እየ ያዘ መሄዱ አልቀረም፡፡ በኋላ የተገኘው ድብልቅ ትምህርት፣ መሠረቷ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ስፍራ እያስለቀቀው መጥቷል፡፡ ይባስ ብሎም መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርት ለቤተ ክርስቲያን ባይተዋር፣ ድብልቁና እንግዳው ትምህርት ደግሞ ባለቤት እየ ኾኑ ነው፡፡