Monday, January 4, 2016

ሐሰትን እውነት ለማድረግ መታገል ማንን ለመጥቀም?

መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተላኩ ቅዱሳን ሰዎች የጻፉትና ምንም ማሻሻያ ሳናደርግ የምንቀበለው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምናምነውን፣ የምንቀበለውንና የምንታዘዘውን ወይም የምንኖርበትን እውነት የያዘ ብቸኛ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የክርስትና ትምህርትና ሥርዐት ምንጭና መመዘኛ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከነቢያትና ከሐዋርያት የተቀበለችውና የተመሠረተችበት እውነት መጽሐፍ ቅዱስ በመኾኑም፣ እንደ ዐይን ብሌን ልትጠብቀው ይገባል፡፡

እንዲህ የተባለው በከንቱ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዘመን እየ ራቀች በሄደች መጠን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም ከእዚያ ውጪ የኾኑ የተለያዩ ትምህርቶችን፣ ሥርዐቶችንና ልምምዶችን አዳብራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርትና ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ከሌለው ትምህርትና ልምምድ ጋር እየተዛነቀ በሄደ ቍጥር ትምህርቷ ድብልቅ እየ ኾነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ እየ ደበዘዘ እና ሌላ መልክ እየ ያዘ መሄዱ አልቀረም፡፡ በኋላ የተገኘው ድብልቅ ትምህርት፣ መሠረቷ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ስፍራ እያስለቀቀው መጥቷል፡፡ ይባስ ብሎም መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርት ለቤተ ክርስቲያን ባይተዋር፣ ድብልቁና እንግዳው ትምህርት ደግሞ ባለቤት እየ ኾኑ ነው፡፡

እምነታችን በእውነተኛው አምላክ ማንነት፣ ባሕርይ እና ግብር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እውነተኛው እምነት በሰው አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ሳይኾን መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው እውነት ላይ የቆመ ነው፡፡ እውነተኛው እምነት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ብሎ ማመን፣ ከሥላሴ አንዱ አካል ወልድ ሰው ኾኖ መምጣቱን፣ በእርሱ ዓለሙ መዳኑንና ከእርሱ በቀር ዓለም የሚድንበት ሌላ አማራጭ መንገድ የሌለ መኾኑን፣ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ተልእኮውን ፈጽሞ ወደ ሰማይ ካረገና በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ፣ አብ በሰጠው ተስፋ መሠረት መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ጸጋውን በመስጠትና የክርስቶስን አዳኝነት ለሰዎች በመግለጥ ቤተ ክርስቲያን እንድትመሠረት፣ ቤተ ክርስቲያንም ወንጌልን በመስበክ ሰዎችን በክርስቶስ አዳኝነት እንዲያምኑ፣ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲጠመቁና ክርስቶስ ያዘዘውን ኹሉ እያስተማረች ደቀ መዛሙርት እንዲኾኑ፣ ጌታ ዳግም እስኪመጣ ድረስ የተሰጣትን ተልእኮ እንድትፈጽም ማድረጉንና እስከ ፍጻሜ ዘመንም ይኸው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሚቀጥል ማመንና በዚሁ እምነት መሠረት መመላለስ ነው፡፡ ይህን እምነት የተቀበለና በዚህ እምነት መሠረት የሚኖር ክርስቲያን ነው፡፡ ይህን እምነት የሚበርዝና የሚከልስ፣ በዚህ እምነት ላይ ባዕድ ነገር የሚጨምርና ከእውነተኛው እምነት ውጪ የሚመላለስ ደግሞ መናፍቅ  ኾኖ ነበር የሚቈጠረው፡፡ በሐዋርያትና ከእነርሱ በኋላ በተነሡ አበው ዘመናት አማኙና መናፍቁ የሚለዩበት የእምነት መሠረት ይህ ነበር፡፡

በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ይህ መለኪያና መመዘኛ ተለውጧል፡፡ ዛሬ አንድ ክርስቲያን በእውነተኛ እምነት ውስጥ ለመኖሩ ማረጋገጫው ከላይ በተገለጠው እምነት መሠረት ማመኑና መኖሩ አይደለም፤ ወይም ከዚያ ውጭ የኾነውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውን ትምህርት አልቀበልም ማለቱ አይደለም፡፡ ይህ እንዲያውም “መናፍቅ” የሚያሰኝና ከሞላ ጐደል “እንደ ስሕተት ትምህርት” ወይም “እንደ ኑፋቄ” የሚቈጠር ኾኗል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው አማኝ እያሰኘ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው ትምህርት ላይ በተጨመሩና በሂደት ዳብረው የመጽሐፍ ቅዱስን ስፍራ በነጠቁ መጤ ትምህርቶች መሠረት ማመንና በዚያው መሠረት መኖር ነው (ዕድሜ ጠገብ ቢኾንም እንኳ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ የቆመ ትምህርት ሁሉ መጤ ነው)። ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ስትገፋውና ይህን ይተኩልኛል ያለቻቸውን ሌሎች ትምህርቶች መመዘኛዋ ስታደርግ ከማየት የበለጠ ውድቀት ከወዴት ይገኛል?

ከኹሉም የሚያሳዝነው ደግሞ፣ በለስ ቀንቷቸው የመጽሐፍ ቅዱስን የትምህርት ስፍራ የነጠቁትን እንግዳ ትምህርቶች ወደ መጡበት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ደግሞ ወደ ቦታው በመመለስ ተሐድሶ ማድረግ ሲገባ፣ እየ ተሠራ ያለው ከዚህ በተቃራኒው መኾኑ ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ ብቻ መመሥረትና ከዚያ ውጪ የሆኑ ሌሎች ትምህርቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘን ሲገባቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በሌሎች ትምህርቶች ለመመዘን እየ ደፈሩ ነው፡፡ የስሕተት ትምህርቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ከመመርመርና እንዲወገዱ ከማድረግ ይልቅ፣ ለስሕተት ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሽፋን እየ ሰጧቸው ይገኛሉ ሐሰትን በእውነት ከማስወገድ ይልቅ፣ ሐሰትን እውነት ለማድረግ እየ ተጉ ነው፡፡ ነገር ግን ሐሰትን ሐሰት ብሎ ከማስወገድ ይልቅ ሐሰትን እውነት ለማስመሰል የሚደረገው ጥረት ምን ለማግኘት ነው? ማንንስ ለማስደሰት ይኾን?

በጮራ ቍጥር 47 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment