ደጁ ለጌታ ይከፈት
ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ በክቡር ደሙ የዋጃት
የብቻው ገንዘቡ ናት። እንደ ተጻፈውም፣ “አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት” (ኤፌ. 1፥23)። የቤተ ክርስቲያን መሠረት ክርስቶስ ነው፤ ማእከሏም ክርስቶስ ነው፤ ራሷም ክርስቶስ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን
የሚያሰኛት ቅሉ ክርስቶስን መሠረቷ፣ ማእከሏና ራሷ ማድረጓ ነው፤ ያለ ክርስቶስ ከሆነች ግን “ቤተ ክርስቲያን ነኝ” ማለቷ መንፈሳዊ
ትርጕም ያጣል። ብዙ ነገር አለኝ ብትል እንኳ ያለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባዶ ስብስብ ትሆናለች። ክርስቶስን ኹለንተናዋ ያላደረገች
ቤተ ክርስቲያን እንዴት ምስኪን ናት!
በምድር ላይ የምትገኘው ቤተ
ክርስቲያን፣ ራሷንና ጌታዋን ክርስቶስን ከውስጧ አስወጥታ በራሷ ነገር ልትሞላና እርሱን በአፍኣ (በደጅ) ልታቆመው ትችላለች። በራእየ
ዮሐንስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ትልቅ ስሕተት ፈጽማ ነበር። ለዚህ
ነው ጌታ፣ “እነሆ
በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም
ከእኔ ጋር ይበላል” ሲል ለቤተ ክርስቲያኒቱ የክፈችልኝ መልእክት ያስተላለፈው (ራእ. 3፥20)።
የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ጌታዋን
ከውስጧ አውጥታ በደጅ እንዲቆም ለምን አደረገች? ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልአክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተላለፈው የንስሓ መልእክት
ውስጥ እንደ ዘረዘረው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእኔ ጌታ አያስፈልገኝም ባይ ሳትሆን አልቀረችም። ጌታ ከውስጧ ወጥቶ በደጅ እንዲቆም
ያደረገውም ዋና ነገር ይህ እንደ ሆነ መገመት አያስቸግርም። ጌታ እንደ ተመለከታት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤
አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም” ባይ ነበረች፤ ይሁን እንጂ፦ ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውር፣ የተራቈተችም መሆንዋን አላወቀችም ነበር
(ቍጥር 17)። ባለጠጋ ሳትሆን ባለጠጋ
ነኝ፤ ብዙ የጐደላት ነገር እያለ አንዳች አያስፈልገኝም ማለቷና ጌታን በደጅ ማቆሟ የቤተ ክርስቲያኒቱ ውድቀት ከፍ ያለ መሆኑን
ያሳያል። አፍቃሪዋ ጌታ ግን ወደ እርሷ ለመግባት በደጅ ቆሞ እያንኳኳ ነበር። ለእርሷ ያልታወቃት ጕስቍልናዋ፣ ምስኪንነቷና ድኽነቷ
እንዲወገድና በብልጽግና እንዲተካ “በእሳት የነጠረውን ወርቅ”፣ የለበሰች ሲመስላት ኀፍረቷ እንዳይገለጥ “ነጭ ልብስን”፣ የምታይ
ሲመስላት ለታወሩት ዐይኖቿ የምትኳለውን ኵል ከእርሱ እንድትገዛ መክሯታል (ቍጥር 18)። ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልአክ “ከእኔ እንድትገዛ
እመክርሃለሁ” ነው ያለው፤ ይህም የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚፈታውና ጕድለቷ የሚሟላው ከጌታ ዘንድ ብቻ መሆኑን ያሳያል።
እንደ ሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ጌታን ከውስጧ ያወጣችውና በአፍኣ
ያቆመችው፣ የእርሱን ስፍራም በሌሎችና በምድራዊ ጕዳዮች ያስያዘች፣ ያለች ሲመስላት የሌለች፣ ባለጠጋ እንደ ሆነች የምታስብ፣ ነገር
ግን የተጐሳቈለች፣ ዐይናማ ነኝ ስትል ማየት የተሳናት ቤተ ክርስቲያን መፍትሔዋን ከሌላ ዘንድ ብትፈልግ ችግሯን ማባባስ እንጂ መፍትሔ
አታመጣም። መፍትሔው ሳታመነታና ሳትዘገይ “አታስፈልገኝም” ብላ በአፍኣ ያቆመችውን ጌታዋን አሁኑኑ ይቅርታ ጠይቃ ደጇን ከፍታለት
ግባ ማለት ይገባታል። በተሰጣት ዕድል ተጠቅማ ደጇን ካልከፈተችለት ግን ፍጻሜዋ የከፋ ይሆናል። “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ
ሥራህን ዐውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ፥ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ
ልተፋህ ነው” የሚል ብርቱ ማስጠንቀቂያ ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መሰጠቱን መዘንጋት የለብንም (ቍጥር 15-16)።
በማሕልየ መሓልይ ውስጥ እንደምናነበው፣
ውዷ በደጅ ቆሞ “እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ
ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ” ሲላት በጊዜው፣ “እኔ ተኝቻለሁ፤ ልቤ ግን ነቅቷል” የምትለው ሙሽራዪቱ
የውዷ ቃል መሆኑን ብታውቅም ተነሥታ ላለመክፈት ምክንያቶቿን በመደርደር፣ “ቀሚሴን አወለቅሁ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ እንዴት
አሳድፈዋለሁ?” እያለች ጊዜያቶችን አሳለፈች። ለራሷ ምቾት እንጂ በጠልና በሌሊት ነጠብጣብ ለራሰው ውዷ ቅድሚያ አልሰጠችውም። እርሱም
እንዳልከፈተችለት ባየ ጊዜ ማንኳኳቱን ትቶ ፈቀቅ አለ። ዘግይታ ግን ተነሣችና ከፈተችለት፤ ይሁን እንጂ ውዷን አላገኘችውም። ብትጠራውም
አልመለሰላትም። እርሱን ፍለጋ በሌሊት ብትወጣም የተረፋት በከተማዪቱ ጠባቂዎች መደብደብ፣ መቍሰልና የዐይነ ርግብ መሸፈኛዋን መነጠቅ
ሆነ። ከዚያ የጠፋውን ውዷን የማፈላለጉን ሥራ ቀጠለች (ማሕ. 5፥2-8)። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው ውዷ ለክርስቶስ ደጇን መክፈት አለባት። ካልከፈተችለት ውዷ ፈቀቅ ሊል ይችላል።
ያለእርሱ የምታደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴዋ ሁሉ ከንቱ፣ ምድራዊና እዚሁ ምድር ላይ ቀሪ ነው የሚሆነው።
ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ምክንያት
ውዷን ክርስቶስን ከውስጧ አውጥታ በደጅ አቁማዋለች። የራሷን ዝናና ጥንታዊነት ስትተርክ፣ “እኔ ከሁሉ ቀዳሚ ነኝ፤ ሁሉ አለኝ፤
አንዳች አያስፈልግኝም” ስትል፣ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእርሱን ብቸኛ ቤዛነት መስበክ ትታ ሌሎችን ቤዛዎች አድርጋ ስትሰብክ፣ እስትንፋሰ
እግዚአብሔር የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መመሪያዋ ማድረግ ሲገባት፣ እርሱን ቸል ብላ ሌሎች ድርሳናትን መመሪያዋ ስታደርግ፣ በእርሷ
ዘንድ ስፍራ ያላገኘው ጌታ ከውስጧ ወጥቷል። በደጅ ቆሞም እንድትከፍትለትና እንዲገባ እያንኳኳ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን፣
በማሕልየ መሓልይ ላይ እንደ ተጠቀሰችው ሙሽሪት፣ ለሚያንኳኳው ጌታ ላለመክፈት፦ ጥንታዊነቴ፣ ታሪኬ፣ ትውፊቴ፣ አስተምህሮዬ፣ ሥርዐቴ፣
ባህሌ፣ ልማዴ፣ ወዘተ. እያለች ውዷን ላለማስገባት በደጅ አቁማው እያንገራገረች ትገኛለች። ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ሁሉ ዕሴቶች
ባለቤት ብትሆንም፣ ዕሴቶቹን ለጌታ ክብር ካላዋለቻቸውና የእርሱን አዳኝነት ላልሰሙት ለማሰማት ካልተጠቀመችባቸው ጥቅም የላቸውም፤
እዚሁ በምድር ላይ ቀሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ጌታ ዛሬም ከውስጧ አውጥታ በደጅ ያቆመችውን ቤተ ክርስቲያን፣ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤
ማንም ድምፄን ቢሰማ፥ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” ሲል የፍቅር ድምፁን እያሰማት ይገኛል (ራእ. 3፥20)።
እኛም የክርስቶስ ሙሽራ የሆንሽ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የክርስቶስ ብቻ እንጂ የሌሎች ልትሆኚ አይገባሽም። በአፍኣ ቆሞ ለሚያንኳኳውና ከአንቺ ጋር እራት ለመብላት ለሚፈልገው ለውድሽ ለክርስቶስ ደጁን ክፈቺለትና ወደ አንቺ ይግባ ማለት እንወዳለን። የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ደጁን ለጌታ የዘጉበትንም ሁሉ ከዘማሪ ዳዊት ጋር በመተባበር፣ “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” እንላቸዋለን። “ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?” ሲሉ ቢጠይቁን መልሳችን ይህ ነው፤ “እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኀያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኀያል። … የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።” ስለዚህ “እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” (መዝ. 23/24፥7-10)።
እኛም የክርስቶስ ሙሽራ የሆንሽ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የክርስቶስ ብቻ እንጂ የሌሎች ልትሆኚ አይገባሽም። በአፍኣ ቆሞ ለሚያንኳኳውና ከአንቺ ጋር እራት ለመብላት ለሚፈልገው ለውድሽ ለክርስቶስ ደጁን ክፈቺለትና ወደ አንቺ ይግባ ማለት እንወዳለን። የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ደጁን ለጌታ የዘጉበትንም ሁሉ ከዘማሪ ዳዊት ጋር በመተባበር፣ “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” እንላቸዋለን። “ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?” ሲሉ ቢጠይቁን መልሳችን ይህ ነው፤ “እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኀያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኀያል። … የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።” ስለዚህ “እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” (መዝ. 23/24፥7-10)።
(በጮራ ቍጥር 45 ላይ የቀረበ)