Wednesday, August 21, 2013

የመዳን ትምህርት



ካለፈው የቀጠለ
ድሩም ማጉም ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን ደኅንነት
ሰው እንዴት የራሱ ሊያደርገው ይችላል?

ከላይ እንዳነበብነው ይህ ቀረው የማይባለውን ሰውን የማዳን ሥራ፥ እግዚአብሔር ከፍ ባለ መለኮታዊ ጥበብ ዐቅዶት በነበረው መሠረት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አጠናቆታል፡፡ ዛሬ ሰውን ለማዳን የሚታቀድም ሆነ የሚደረግ አንድም ነገር አልተተወም፡፡ አሁን የሚቀር ቢኖር በሰው ደረጃ መፈጸም የሚገባው የተፈጸመውን “በእምነት መቀበል” ብቻ ነው፡፡ ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ዮሐንስ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ የተጠናቀቀውን የሰውን ደኅንነት በወንጌሉ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ በመስጠት ከጻፈ በኋላ የሰው ድርሻም ምን መሆን እንዳለበት ሳይገልጽልን አላለፈም፡፡

ወንጌላዊው፥ መዳንን የሚፈልግ ሰው ወደ ቅድስት ሀገር ይሂድና የታሪክ ቦታዎችን ይጐብኝ፤ ወይም ወርቅ ብር ይክፈልና ይግዛ፤ ወይም ሰባት ዓመት በራሱ ይቁምና ይጸልይ፤ ወይም በአንዱ በረሓ ውስጥ ገብቶ በረኃብና በጥም ራሱን ይግደል፤ ወይም …  አላለም፡፡ እንደዚህማ ባለ መንገድ የሰው ነፍስ ልትድን ብትችል ኖሮ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ተለዋጭ ሆኖ ይሞት ዘንድ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ያስተማረውን መሠረት በማድረግ ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ ጽፎ ያስተላለፈልን ትምህርት የሚለው እንዲህ ነው፡፡

1.  ሙሴ በምድረ በዳ የናስ እባብን እንደ ሰቀለ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል በማለት በእግዚአብሔር በኩል ስለ ሰው ሊሠራ የታቀደውንና እንደ ታቀደውም የተሠራውን ከገለጸ በኋላ፥ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ለምን ተገባው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሆን ዘንድ በሰው በኩል መደረግ የሚገባውን የሰውን ድርሻ ለማመልከት፥ በሙሴ የናስ እባብ ምሳሌ በተሰቀለው የሚያምን የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ነው ይለናል (ዮሐ. 3፥14-15)፡፡

የናሱን እባብ ሙሉ ታሪክ እንድናስታውሰውም ኦሪት ዘኍልቍ 21፥8 እና 9ን እንድናነብ ያነሣሣናል፡፡ የእስራኤል ልጆች በመርዛማው እባብ በተነደፉ ጊዜ፥ በመርዙ ከመሠቃየት ከመጯጯህና በጻዕር ወደ ሞት ከመነዳት በቀር፥ በዚያን ጊዜ ሊያደርጉት የቻሉት ነገር አልነበረም፡፡ ምስጋና የሚገባው እግዚአብሔር ግን ጊዜያዊና ሥጋዊ ከሆነ በሽታቸው ይልቅ፥ የማይለካ ክብደት ካለው የኀጢአት በሽታ የሚፈወሱበትን መድኀኒትን ለማዘጋጀት የወሰነውን ዕቅዱን እንዴት እንደሚያጠናቅቀውና ሰው እንዴት እንደሚጠቀምበት ተነቦና ተስተውሎ የማያልቅ የዕድሜ ልክ ልምምድን የሚያስተምር መግለጫ በሁለት ቍጥሮች አስፍሮ አስተላለፈልን፡፡ ለሙሴ በተነገረው ትእዛዝ መሠረት በእባብ መርዝ የተጐዳው እስራኤላዊ ሁሉ ይድን ዘንድ፥ ሰውን ያልነደፈውና ጐጂ መርዝም በባሕርዩ የሌለበት የናስ እባብ በዕጨት ላይ መቸንከርና መሰቀል ነበረበት፡፡ በመርዛማው እባብ የተነደፉት ሰዎች ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝና ለመዳን ከፈለጉ፥ የናሱን እባብ ከማየት የበለጠ ነገር እንዲሠሩ አልተጠየቁም፡፡ ቢጠየቁም ኖሮ በሥቃይና በሞት አፋፍ ላይ ሆነው በነበሩበት ጊዜ ሊሠሩ የሚችሉት ነገር ሊኖር ባልቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚችሉትን ብቻ ይሠሩ ዘንድ ድርሻ ሆኖ የተሰጣቸው የእግዚአብሔርን ቃል አምነው ታዘዙ፤ እስራኤላውያን ሁሉ የናሱን እባብ አዩ፤ ዳኑም፡፡ በዚህም ምክንያት አስደናቂ ተኣምር የሆነ ለውጥ ተከናወነ፡፡

ሀ. ተናዳፊው እባብ በሰውነታቸው ውስጥ የረጨው መርዝ ተወሰደላቸው፡፡
ለ. መታመም፥ ሥቃይና ሞት ቀረላቸው፡፡
ሐ. ሰፈሩን ያደባለቀውና ያናወጠው ዋይታና መተራመስ ቀረና የሐሤት፥ የዝማሬና የሰላም መንፈስ ሰፈነ፡፡
መ. ነዳፊው እባብ ተገደለ የሚል ቃል ባይኖርም ከዚ በኋላ ያ እባብ እስራኤላውያንን አላጠቃም፡፡
ሠ. በእባብ ምክንያት ታግዶ የቈየውንና ወደ በረከት ሙላት ይደረግ የነበረውን ጕዞ ጤናማው ሕዝብ ቀጠለ፡፡

ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል ምሳሌ ሆኖ በእግዚአብሔር ቃል የተላለፈው የናስ እባብ መሰቀል ነው፡፡ እርሱ በምሳሌነት የሚያመለክተው የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል የሚሰጠውን ጥቅም ወደ መገንዘብ ስንመጣ የሚከተለው ሁሉ ለአማኝ መሰጠቱን እናስተውላለን፡፡

ዲያብሎስና ሰይጣን፥ ታላቁ ዘንዶ፥ የቀደመው እባብ እያለ የእግዚአብሔር ቃል በሚጠራው መርዘኛ መንፈስ የተነደፈው የሰው ዘር ሁሉ፥ ኀጢአትን ተከትሎ በመጣው ሞት አፋፍ ላይ ሆኖ በራሱ ጥረት ሊያደርግ የሚችለው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በባሕርዩ የኀጢአት መርዝ የሌለበት፥ ምንም ጕዳት ያላደረሰው ንጹሕና ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ማንንም እንዳልበደለው የናስ እባብ በመስቀል ላይ ተቸነከረ፡፡ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ያገኛል እንጂ አይጠፋም በሚለው መለኮታዊ ዐዋጅ በመተማመን፥ ኀጢአታችንን ተሸክሞ የተሰቀለውን ኢየሱስን በእምነት በዐይነ ልቡና (በመንፈስ ዐይን) የሚመለከት ሁሉ ይድናል፡፡ ይድናልን የሚናገረው ሰው አይደለም፤ ተናጋሪው እግዚአብሔር ነውና ቃሉ በፍጹም እውነት ነው (1ቆሮ. 15፥3፤ 1ጢሞ. 1፥15)፡፡ ደካማው ኀጢአተኛ ሰው ከዐቅሙ በላይ እንዲያደርግ አልተጠየቀም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው የተፈጸመውን በእምነት እንዲቀበል ብቻ ስለሆነ ለዚህ ጥሪ እንዲታዘዝ በወንጌል እየተጋበዘ ነው፡፡

2.  ይኸው ወንጌላዊ፥ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወደደ” ካለ በኋላ፥ አሁንም ቤዛ መስጠት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት መልሱን ሰጠ፡፡ ቤዛ ይሆን ዘንድ ዐልፎ በተሰጠው አንድያ ልጁ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ነው ይለናል (ዮሐ. 3፥16)፡፡

አሁንም በዚህ ጥቅስ የሰው ድርሻ ሆኖ የቀረበው በተፈጸመው የእግዚአብሔር ሥራ ማመን ብቻ ነበረ፡፡ ቃሉን የሚሰማ ሰው ራሱን  ለማዳን ከእንግዲህ ወዲያ የሚሠራው ግዳጅ እንደ ወደቀበት ሆኖ አይሰማውም፡፡ በኀጢአትህ ምክንያት ባንተ ላይ ሊያርፍ የነበረው የእግዚአብሔር ፍርድ፥ ባንተ ላይ ማረፉና መፈጸሙ ቀረና ቤዛ ሆኖ በተሰጠልህ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ዐረፈ፤ በእርሱም ላይ ተፈጸመ ተብሎ ሲሰበክለት በኔ በኀጢአተኛው ላይ ማረፍ ይገባው የነበረ ፍርድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ዐርፎአል የምሥራች ተብሎ ተነገረኝ፡፡ እንግዲህ እኔ ምን ማድረግ ይገባኛል? ቢል ያንተ ድርሻ በእግዚአብሔር ውሳኔ መስማማት ብቻ ነው ይባላል፡፡ አይ! ኀጢአቴን እንደ ተሸከምኩ እቈያለሁ፤ በኀጢአት ላይ ያለውን ቍርጠኛውን የእግዚአብሔርን ፍርድ እኔው እቀበላለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በኔ ቦታ ተተክቶ መቀጣቱን አልስማማበትም የማለት መብት ማንም እንዳለው የታወቀ ነው፡፡

የምሥራቹን ቃል የሚሰማ ሁሉ በእምነት የመቀበልና ያለመቀበል ቀላል ውሳኔ የሚያደርግበት ምርጫ በፊቱ ተቀምጧል፡፡
አንደኛ፥ የምሥራቹን በእምነት የሚቀበል ሁሉ “ይድናል አይጠፋም” የሚል ማረጋገጫ ወይም ዋስትና ታትሞበታልና፤ “የዘላለም ሕይወት አለው” የዘላለም ሕይወት የሚኖረው መቼ ነው? እንዳይባል “አለው” የሚለው አንቀጽ አሁን ካመነበት ቅጽበት ጀምሮ የዘላለም ሕይወት ባለቤት እንደ ሆነ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን (ቀዳሚና ተከታይ የሌለውን) የኔ ቤዛ ይሆንልኝ ዘንድ ሰጥቷልና፥ የኔ ተለዋጭ በመሆኑ ስለኔ ሆኖና፥ በኔ ቦታ ተተክቶ ኀጢአቴንና ኀጢአቴ ያስፈረደብኝን ቅጣት ተቀብሎልኛልና እኔ በኀጢአቴ አልጠየቅም ማለት የእግዚአብሔርን እውነት መቀበልና በውሳኔውም መስማማት ስለ ሆነ የተሻለ ምርጫና ውሳኔ ነው (ሮሜ 3፥21-26፤ 2ቆሮ. 5፥14)፡፡

ሁለተኛ፥ አልቀበልም ላለ ደግሞ በቃሉ የተናገረው እውነት “አሁን ተፈርዶበታል፡፡ - ወድአ ተኰነነ” የሚል ነውና፥ ለሚቀበል አሁን የዘላለም ሕይወት ባለቤት የመሆን መብት እንደሚኖረው ሁሉ፥ ለማይቀበልም ያለመቀበል ውሳኔ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የተፈረደበት ሆኗል (ዮሐ. 3፥18-36)፡፡ በእምነት በመቀበልና ባለመቀበል መካከል የሆነ በሦስተኛነት ለምርጫ የቀረበ መንገድ የለም፤ አልተዘጋጀምም፡፡

የእስራኤል ልጆች የተሰቀለውን የናስ እባብ “እዩና ዳኑ” ሲባሉ አዩና ዳኑ እንጂ፥ ‘ቈይ ሙሴ! ጥያቄ አለኝ! የነደፈኝ መርዛሙ እባብ ሳይሰቀል ወይም የእባብ መርዝ የተሠራጨበት የእኔ ሰውነት ሳይበጣ፥ ሳይቈረጥ፥ ሳይቸነከር፥ መርዝ የሌለበት በተፈጥሮው እባብ ያልሆነ የናስ እባብ በመሰቀሉና በመቸንከሩ፥ እኔም እርሱን በማየቴ እንዴት ልፈወስ እችላለሁ? ለምን ትቀልድብኛለህ? እኔ እኮ አእምሮ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ይህን የሞኝነት ነገር እውነት ነው ብዬ እንዴት እቀበላለሁ? ባይሆን አንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነህና ብትዳስሰኝ እንኳ ይሻላል’ የሚል እስራኤላዊ ቢኖር ኖሮ ከመሞት በቀር ሌላ ዕድል ባልኖረው ነበር፡፡ ምንም ሞኝነት ቢመስል ከተፈጥሮ እባብ መርዝና መርዙ ካስከተለው ሞት ለመዳን የፈለገ እስራኤላዊ የተሰቀለውን የናስ እባብ ማየት ብቻ ይጠበቅበት ነበር፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ዕቅድና ውሳኔ ምንም ኀጢአት በሌለበት፥ ነገር ግን በእኛ ኀጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በተሰቀለው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት አማካይነት በእኛ ሰውነት ውስጥ ያለ አስኰናኝ ኀጢአት እንዲቀጣ ተደረገ፡፡ “ወሶበ ተስእኖ ለሕገ ኦሪት ላዕለ ሞት በእንተ ድካመ ሥጋ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ በአምሳለ ነፍስተ ኀጢአት ወኰነና ለይእቲ ኀጢአት በነፍስቱ፡፡ - በሥጋ መድከም ምክንያት የኦሪት ሕግ በሞት ላይ መሠልጠን (ድል አድራጊ መሆን) በተሳነው ጊዜ፥ እግዚአብሔር  ልጁን በኃጢአተኛ ሰውነት ምሳሌ ላከውና በሰውነቱ ኀጢአትን ቀጣ” (ሮሜ 8፥3-4)፡፡ በኀጢአተኛው ሰው ምሳሌ ኀጢአት የሌለበትን በመቅጣት እውነተኛውን (አማናዊውን) ኀጢአተኛ ማዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ከጥበብ ሁሉ የላቀ ጥበብ ነው፡፡ ነገር ግን ለሥጋዊ ሰው ማለት በአእምሮ ለሚመራ በመንፈስ ማስተዋል ለማይችለው ከዚህ የባሰ ሞኝነት ያለ አይመስለው ይሆናል (ማቴ. 16፥17፤ 1ቆሮ. 2፥14)፡፡

ለሚታዘዙለት ሁሉ የስብከትን ሞኝነት ይዞ ወደ ደካማው ሰው ልብ ውስጥ የሚገባው የእግዚአብሔር ቃል የሚሠራውና የሚያስከትለው ለውጥ እንዴት እንደ ሆነ፥ የሰው አእምሮ ሊቀበለውም ሆነ ሊደርስበት የማይችል ቢሆንም፥ ውጤቱ ሊካድ የማይቻል ሐቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አብርሃምና ሣራ ሰውነታቸው በእርጅና ምክንያት የሟሸሸና የሟረጠ በሆነበት ጊዜ ለከርሞ ወንድ ልጅ ይኖራችኋል ተብሎ ከእግዚአብሔር የተነገራቸው ቃል ለእነርሱ ለራሳቸው፥ ለሚሰማውም ሁሉ የሚያሥቅ ቢሆንም፥ ለተፈጥሮ ሕግ ተስማሚና አመቺ ባይሆንም፥ ሞኝነት በሚመስለው ቃለ እግዚአብሔር ሲታመኑ፥ የሞተው ሰውነታቸው ትንሣኤንና የተሐድሶን ለውጥ አገኘ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የተፈጥሮ ሕግ ተሻረ፤ የምጸት ሣቅ ከደስታ በመነጨ ሣቅ ተተካ፤ ሣቅ በሣቅ የሆነው ይሥሐቅ ተወልዶአልና (ዘፍ. 17፥15-17፤ 18፥11-15፤ 21፥1-6፤ ሮሜ 4፥19-21፤ ዕብ. 11፥11-12)፡፡

በጌታ ወዳጆች የሆናችሁ ወንድሞችና እኅቶች አምላካችን እግዚአብሔር ራሱን ዐላማውንና ዕቅዱን በአብዛኛው የሚገልጽበት መንገድ፥ የሰው አእምሮ በማይጠብቀው፥ ባልተለመደ፥ በተናቀ፥ ግምት በማይሰጠው ኢ ምንት ነገር እንደ ሆነ ተረድቶ ለማድነቅ፥ ለማመስገንም፥ የሚከተሉትን አራት ምሳሌዎች በልባችን ጽሌ (ጽላት) ላይ እንጣፋቸው፡፡

1.    ከዲያብሎስ ቤተ ሙከራ የመነጨውንና ዓለምን ያጥለቀለቀውን በጥበብ ስም የሚሠራበትን አሁንም የሰው አእምሮኣዊ መሣሪያ የሆነውን ብልጠት፥ እግዚአብሔር ያከሸፈውና ከንቱ ያደረገው፥ ማንም ሰው ይህንስ ከሞኝነት ፍጹም ሞኝነት ነው ብሎ በሚቈጥረው፥ እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ራሱን ሊከላከልበት ባለው መብቱ እንኳ ባልተጠቀመ በኢየሱስ ክርስቶስ ይውህና (ሞኝነት) አይደለምን? (ማቴ. 27፥12፤ ኢሳ. 53፥7)፡፡ ሳይሞት ቆዳውን በሚሸልተው ሰው ፊት ዝም ብሎ የሚቆም በግ አላጋጠመኝም፤ ከየዋሁ የእግዚአብሔር በግ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር (ማቴ. 11፥29)፡፡ ይህ ይውህና (ሞኝነት) ግን የሰይጣንን ጥበብ መንግሎ የጣለ የእግዚአብሔር ጥበብ የመሆኑ ጕዳይ ያስደንቀኛል (1ቆሮ. 1፥21-25)፡፡

2.   ከዲያብሎስ ቤተ ሙከራ (ልቡና) መንጭቶ ዓለምን ያጥለቀለቃትን እኔ ከማን አንሳለሁ፤ እበልጣለሁ እንጂ የሚለውን ጀብደኛ ትዕቢትና በተፈጥሮ ከተሰጠ ክልል ውጭ ለማለፍ የሚደረግን የመንጠራራት ዕብሪተኛ ክብር (ሉቃ. 4፥5-6) እግዚአብሔር አክሽፎታል፤ ከንቱም አድርጎታል፡፡ ከንቱ ለማድረግ የተጠቀመበት መሣሪያ ግን ያስደንቃል፡፡ ከሌላ ከማንም ባልተቀበለውና የራሱ ባሕርያዊ ገንዘብ በሆነው መለኮታዊ ክብር መኖርን በመተው፥ የተፈጠረ ሰው የሚንቀውን መደብ የባሪያን መልክ (አርኣያ ገብርን) ገንዘብ አደረገ እስኪባል ድረስ (ማር. 10፥45) ለፍጡራን ከተሰጠ ክልል በታች እንኳ በፈቃዱ በወረደውና ራሱን ባዶ ባደረገው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ትሕትና (ውርደት) የዲያብሎስን ትዕቢተኛ ክብር ደመሰሰው (መዝ. 21/22፥1-8፤ ኢሳ. 52፥14፤ 53፥3)፡፡

ዲያብሎስም ሆነ አዳምና ሔዋን በተፈጥሮ ከተሰጣቸው፥ ለባሕርያዊ ተፈጥሮኣቸው ተስማሚ ከሆነ ክበብ በማለፍ ለባሕርያቸው ወደማይስማማና ወደማይገባ ልዕልና ለመውጣት ሲፈልጉ (ዘፍ. 3፥4-5)፥ ይህን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ (1ዮሐ. 3፥8) ባሕርያዊ በሆነ ኀይሉ ወይም በፈጠራቸው መሣሪያዎቹ በመብረቅና በነጐድጓድ አልተጠቀመም፡፡ ነገር ግን ከባሕርያዊ የልዕልናው ክበብ ወደማይገባው የውርደት ዐዘቅት በፈቃዱ ወረደ፡፡ የጲላጦስ፥ የሄሮድስና የአይሁድ ጭፍሮች መቀለጃ ሆነ፤ ተተፋበት ተሰደበ፡፡ ይህን ሁሉ በይገባኛል አሜንታ መቀበሉ ግን የዲያብሎስንና ከእርሱም ወደ ዓለም ሁሉ የተዛመተውን ትዕቢት አፈራረሰ (ሉቃ. 23፥11፤ ፊል. 2፥5-8)፡፡

3.   ከዲያብሎስ ልቡና መንጭቶና ወደ ዓለም ገብቶ እየተገበረ ያለው በተፈጥሮ ከተሰጠ ውሱን ክበበ ኀይል በመውጣት ሁሉን እችላለሁ የሚያሰኘውን ዲያብሎስ ሠራሽ ጀብደኛነት፥ እግዚአብሔር ድል ያደረገውና ያፈራረሰው ኤልሻዳይ እንደ መሆኑ መጠን በቃልነቱ ከዊን “ይሁን” እያለ ሁሉን በትእዛዝ የሠራበትን ክሂሎቱን (ሁሉን ቻይነቱን) በፈቃዱ ትቶ ለሚጸፉት ጕንጮቹን፥ ለሚገርፉት ጀርባውን፥ ለሚተፉበትም ፊቱን፥ ለሚቸነክሩት እጆቹንና እግሮቹን … ለተቃውሞ በሰጠ በኢየሱስ ክርስቶስ ድካም (ምንም ለማድረግ ያለመቻል) አይደለምን? (ኢሳ. 50፥6፤ ማቴ. 26፥67፤ 27፥30)፡፡ አዬ ድካም! የኢየሱስ ክርስቶስ ድካም! የተቀጠቀጠ ሸምበቆን የሚሰብርበት፥ የሚጤስን ክር የሚያጠፋበት ዐቅም ያልታየበት ኢየሱስ ክርስቶስ! (ኢሳ. 42፥2-3) ግን ሊጠቀምበት ቢፈልግ በድካም በተሸፈነው ኢየሱስ ክርስቶስ ኢ ውሱን የሆነ የኀይል ሙላት ነበር፤ አሁንም አለ (ኢሳ. 9፥6፤ ማቴ. 8፥26፤ 17፥18፤ ዮሐ. 18፥4-8)፡፡

4.   ዲያብሎስ አንድም አስተዋፅኦ ባላደረገበት ሥርዐተ ተፈጥሮ ውስጥ፥ ዓለም ሁሉ የኔ ናት በማለት የራሱ ባልሆነ ብልጥግና በድፍረትና በማስመሰል ራሱን የሚያስተዋውቅበትን ባለጠጋ ነኝ ባይነትን (ማቴ. 4፥8-9) እግዚአብሔር የሻረው እንዴት ነው? ብልጥግናው በፈጠራቸው ዓለማትና በውስጣቸው ባሉ በተፈጠሩ ሕያዋንና ግዑዛን ፍጥረታት ብቻ ሳይወሰንና አንዳች በማይጐድለው ባሕርያዊ የመለኮቱ ሙላት ሆኖ ሳለ፥ በፈቃዱ ከመለኮታዊና ባሕርያዊ የሀብቱ ክልል ራሱን በማግለል ከድኾችና ምስኪኖች ሁሉ ይልቅ ድኻና ምስኪን ሆኖ በተቈጠረ በኢየሱስ ክርስቶስ ወሰን የለሽ ድኽነት የሻረውና ያስወገደው አይደለምን? (2ቆሮ. 8፥9)፡፡

በሥዕል እንደሚታየውና በፈጠራ ድርሰቶች እንደሚነበበው ከወርቅና ከሐር ከተሸመኑ መጋረጃዎች ግቢ ከኖረ፥ የወርቅ ጫማ ከተጫማ፥ ከብርና ከወርቅ በተሠሩ የቤት ዕቃዎች ከተጠቀመ ቤተ ሰብ አልተወለደም፤ በመጨረሻው ድኽነት ኑሮ ውስጥ ከነበረች ድንግል ተወልዶ ያደገና የኖረ ነበር እንጂ (ሉቃ. 2፥7፤ 22፥24፤ ዘኍ. 12፥8)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ የተመዘገበ፥ የኔ ነው የሚለውም ምድራዊ ሀብት ከቶ አልነበረውም (ማቴ. 8፥19-20፤ ሉቃ. 9፥57-58)፡፡ በመጨረሻው ሰዓት እጀ ጠባቡና መደረቢያው (ጋቢው) እንኳ የእርሱ አልሆኑም፤ እነርሱም ተወሰዱበትና ራቍቱን በመስቀል ላይ ዋለ (መዝ. 21/22፥16-18፤ ማቴ. 27፥35፤ ማር. 15፥24፤ ሉቃ. 23፥34፤ ዮሐ. 19፥23-24)፡፡ ሞኝነት፥ ውርደት፥ ድካም፥ ድኽነት በሆነው መንገድ እግዚአብሔር ተጠቀመና ሰውን አዳነ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ሲል ያላደረገው ምን አለ?

ማጠቃለያ፡- የሚያምንበት ሁሉ እንዲድን እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን የሰው ቤዛ ይሆን ዘንድ ሰጠ፡፡ እንዲሁም የሚያምንበት ሁሉ እንዲድን እንጂ እንዳይጠፋ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በሙሴ የናስ እባብ ምሳሌ ይሰቀል ዘንድ ተገባው፡፡ ለመዳን የፈለገ ሰው ድርሻ የተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ የእርሱ ተለዋጭና ምትክ ሆኖ እንደ ተቀጣ ማመን ብቻ ሆኖ በወንጌል ተበሠረ፡፡ አዎን ለመዳን ከማመን የበለጠ ወይም ያነሰ እንዲያደርግ ማንም አልተጠየቀም፡፡

እስራኤላውያን የናስ እባብ በተሰቀለ እኛ እንዴት እንድናለን እንዳላሉ ሁሉ፥ የሐዲስ ኪዳን ምእመናንም ቅዱሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ እኔ ኀጢአተኛው እንዴት እድናለሁ? እንዳይል በሙሴ የናስ እባብ የተደረገውን ተኣምር ያስታውስ ዘንድ በማስረጃነት ተጠቅሶ ቀርቦለታል፡፡ ባለንባት ምድር በጠራራ ፀሓይ ሰው ሁሉ እያየ በሙሴ የናስ እባብ የተደረገውን የተኣምር ታሪክ ማመን ካቃተው ሰማያዊው ምስጢርማ ቢነገረው እንዴት ይገባዋል? የምሳሌውን ትርጕም ማስተዋል ካልቻለ ምሳሌው የሚገልጸውን ምስጢር ማስተዋል አይችልም (ማቴ. 13፥13-16፤ ዮሐ. 3፥11-12)፡፡

የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን በማመን የሰው ኀጢአት ወደ ተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወሰድ፥ በለውጡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅና ቅድስና ወደ አማኙ እንደሚተላለፍ ለአእምሮአችን ሞኝነት ሆኖ ቢታየንም በጥበቡ ሰማያትን የፈጠረ፥ በኀይሉም ምድርን ያጸና እግዚአብሔር በልጄ በኢየሱስ ክርስቶስ የገለጽኩት፤

-   ይህ ሞኝነት የጠቢባንን ጥበብ የሻርኩበት ጥበቤ ነው፡፡
-   ይህ ውርድት የትዕቢተኞችን ክብር ያዋረድኩበት ክብሬ ነው፡፡
-   ይህ ድካም የኀያላንን ጀብደኝነት ያሸነፍኩበት ኀይሌ ነው፡፡
ይህ ድኽነት የባለጠጎችን በራስ መተማመን የደመሰስኩበት ብልጽግናዬ ነው ብሎ እነዚህ ሁሉ ተሟልተውና ተማክለው፥ ተቀርጸውና ተሥለው ቤዛችን ሊሆን በተሰቀለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲነበቡ አደረገ፡፡ በዚህ የስብከት ሞኝነት ማመንና መዳንን ሰው ሁሉ እንዲቀበል ይጋበዛል፡፡

(በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment