Friday, August 16, 2013

የመዳን ትምህርት





“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል?”
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ (ሮሜ 7፥24-25)

ከናሁ ሠናይ 
ካለፈው የቀጠለ

ሰውን የማዳን ሥራ በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጀምሮ በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተጠናቀቀ ካለፈው ዕትም ያነበብነውን እናስታውሳለን፡፡ ሰውን የማዳን ሥራን ከኀጢአተኛው የሰው ዘር የተወለደ ማንኛውም ሰው ሊያከናውነው አይችል የነበረ መሆኑን፥ በመላክትም እንኳ ሊሠራ የማይችል እንደ ነበረ ካነበብነው ተረድተን እዚህ ደርሰናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ነፍሱን ለማዳን ቤዛ የመስጠት ግዴታ ያለበትና ያላገኘ መሆኑን ሲያመለክት፥ ሰው ዓለምን ሁሉ ቢገዛ ከሚገዛው ዓለም ሁሉም ለነፍሱ ቤዛ የሚሆንለት ማግኘት ካልቻለ፥ ዓለምን በመግዛቱ ምን ተጠቀመ? አለ፡፡ ዓለም ሁሉ ሲባልም የምናውቀውንና የማናውቀውን ዓለም ሁሉ ቢገዛም፥ ከሚገዛው ዓለም ሁሉም ለነፍሱ ቤዛ የሚሆን ማግኘት ካልቻለ ገሃነመ እሳት መውረድ አልቀረለትምና፥ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ የማድረጉና ያለማድረጉ ውጤት ነፍሱን በሚመለከት ልዩነት እንደሌለው አመስጥሮ አስረዳ፡፡

በእግዚአብሔር የተመን ሠንጠረዥ የሰው ዋጋ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንዲሆን መወሰኑን ስንገነዘብ፥ በአንድ ወገን እግዚአብሔር ለፈጠረው ሰው የሰጠውንና የመደበውን የክብር ደረጃ ያሳውቀናል፡፡ በሌላ ወገንም እግዚአብሔር ልጁን ቤዛ ሰጥቶ ሰውን ከሚያድን በቀር፥ ሁሉን ማድረግ በሚችለውና ምንም ምን በማይሳነው በእግዚአብሔር ጥበብና ችሎታ ሰው የሚድንበት ሌላ መንገድ እንዳልተገኘ ያረጋግጥልናል፡፡ ይህን የሚያህል ከማስተዋል በላይ የሆነ ውለታ የተደረገለትም ሰው ፈንታው ማመስገንና ስጦታውን መቀበል ብቻ ይሆናል፡፡ የዚህን መንፈሳዊ ምስጢር ጥልቀትና ምጥቀት የተረዳው ሐዋርያው ጳውሎስ የሚሰጠን ትምህርትም ይህንኑ በይበልጥ ያብራራልናል፡፡

አንደኛ፡- እግዚአብሔር ሰውን በመውደዱ ቤዛ ይሆንለት ዘንድ አንድያ ልጁን ሰጠለት የሚለውን የምሥራች ቃል (ዮሐ. 3፥16) ሐዋርያው አጕልቶ ሲሰብክ አንድያ ልጁን ተለዋጭ እስኪያደርግለት ድረስ በእግዚአብሔር የተወደደው ሰው ለመወደድ በሚያበቃ ደረጃ ላይ ባልተገኘበትና ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖ በተመዘገበበት ሰዓትና ሁኔታ እንደ ነበረ ያስተምረናል (ሮሜ 5፥8)፡፡ የሰው መወደድ እንኳ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ እንጂ ለመወደድ ባደረገው ዝግጅት እንዳልሆነ ግልጽ አድርጐልናል፡፡ ለመወደድ አለመዘጋጀቱም ከመወደድ አላስቀረውም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን!!

ጳውሎስ ከራሱ ሕይወት አንጻር ይህን ተረዳ፡፡ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን የሰጠለት መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡ ኀጢአቱንም በልጁ ላይ እንደ ጫነለትና በምትኩም ልጁ እንደ ተቀጣለት አልተረዳም ነበር፡፡ በልጁም ሞት ከገዛቸውና አምነው እንዲድኑ ከጠራቸው መካከል አንዱ ይሆን ዘንድ ገና በእናቱ ማሕፀን በነበረበት ጊዜ መመረጡን አላስተዋለውም ነበር (ገላ. 1፥15-16)፡፡ እንዲያውም ይህን ዐይነቱን የምሥራች ሊያበሥሩ የተሰማሩትን ቅዱሳን ያሳድድ ነበር (ሐ.ሥ. 22፥3-5)፡፡ ጳውሎስ የተባለው ሳውል ይህን የመሰለውን ሁሉ እያደረገ ሳለ፥ በጥላቻ በማይለወጠው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር የተወደደና በዘረጋውም የዘላለማዊ ሕይወት ዕቅዱ የታቀፈ እንደ ነበረ የተረዳው እጅግ በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ “ካልፈለግህ ይቅር” የሚለው ውሳኔ ሳይተላለፍበት “ምንም ቢሆን አንተ የኔ ነህ” ብሎ በመንገድ ላይ የያዘው የራሱም ምርኮኛ ያደረገው የእግዚአብሔር ፍቅር በነፍሱና በመንፈሱ ጠልቆ፥ ጅማቶቹንና አጥንቶቹንም ዐልፎና ዘልቆ እየገባ ያስገርመውና ለምስጋና ያነሣሣው ነበር (1ጢሞ. 1፥12-17)፡፡

ሁለተኛ፡- ሐዋርያው በጥሩ ቋንቋ የሚገልጸው ሌላም ጕዳይ አለ፡፡ እያንዳንዱ ኀጢአተኛ በምንም ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የነበረና በየትኛውም መንገድ የተጠራ ቢሆን፥ ጥሪውንም ተቀብሎ ካመነ በኋላ በምንም ዐይነት አገልግሎት ላይ ያለ ምእመን ቢሆን፥ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የከፈለው ዋጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡ ብዙ የማወቅ ዕድል የተሰጠህ አንተ ምእመን ያንተን ዕድል ያላገኘውን ወንድም ታሳዝናለህን? አንተ የምታሳዝናቸው ወንድምና እኅት ኢየሱስ በምትካቸው የሞተላቸው ናቸውኮ! ይላል (ሮሜ 14፥15፤ 1ቆሮ. 8፥11)፡፡

በእግዚአብሔር የተከፈለው የእያንዳንዱ ሰው ዋጋ የንጉሥም፥ የጳጳስም፥ የአናጕንስጢስም … ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፥ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልዑልና ክቡር ደረጃ የምንረዳ ከሆነ (ማቴ. 21፥34-37፤ ማር. 12፥6) እርሱ ዋጋው ሆኖ የተሰጠለት ሰው ደረጃ ታየን፥ ታወቀን ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ሰውን ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስን በተለዋጭነት ከመስጠት በቀር ሌላ የማዳኛ መንገድ እግዚአብሔር አላገኘም፡፡ እግዚአብሔር ያላገኘውንም ሰው ሊያገኝ አይቻለውም፡፡ ለማንም ስለማይቻለውም ከእግዚአብሔር ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሊኖረንና ወንጌሉን ልንቀበል ይገባል፡፡ በአንዳንድ ቦታ ይህን ወንጌል በማናናቅ የሰውን ነፍስ ለማዳን የሚከፈለው፥ ከጐመን ዋጋ ያነሰ እንደ ሆነ በማስመሰል በእልህ እየተሰበከ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ ይቅር ይበለን፡፡ ለአንድ ድኻ ዐሥር ሳንቲም መስጠት ዋጋ አለው፡፡ እግዚአብሔር ለሰጪው ዋጋውን አያስቀርበትም፤ ብዙ ዕጥፍ አድርጎ ይከፍለዋል እንጂ (ዕብ. 6፥10)፡፡ ይህን ማለት ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት የጠየቀውን ሰውን የማዳን የዋጋ ተመንን እንኳ ዐሥር ሳንቲም ይቅርና ዓለምን ሁሉ መስጠት ቢቻል ያሟላል ማለት እንዳይደለ ልንዘነጋ አይገባም፡፡

የጽድቅንና የዋጋን ወይም የእምነትንና የምግባርን ትርጕምና ውጤት መረዳት ለአንዳንዶች ችግር የሆነባቸውን ያህል፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጕም አጣርተው ለተረዱ ንዑዳን አባቶች ችግር አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመውን ቤዛነት አምኖ መቀበል እንደሚያጸድቅ፥ ባጸደቀን በክርስቶስ ኢየሱስ ስም የምናደርገው መልካም ሥራ ዋጋ ለማግኘት ብለን ባንሠራውም የእምነታችን ሕያውነት መግለጫ ፍሬ ሆኖ ዋጋ እንደሚያሰጠን አበጥረውና አንጠርጥረው አስተምረዋል፡፡ የትምህርታቸው ምስጢር ግልጽ ነው፤ አንድ ዛፍ ከጸደቀ በኋላ ፍሬን ያፈራል እንጂ ለመጽደቅ አያፈራም፡፡ የብዙዎች ችግር ግን ለጋሪውና ለፈረሱ ተገቢ ቦታቸውን አለመስጠትና በተገቢው ሁኔታ አለማገናኘት ነው፡፡ (እምነት መጽደቂያ፥ ምግባር የእምነት መግለጫ ነው ይላል ለምስካየ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 40ኛው ዓመት መታሰቢያ የወጣ መጽሔት ገጽ 8)፡፡

የእግዚአብሔር ባለጠግነቱ ጥበቡ ዕውቀቱ የሰው አእምሮ ተመራምሮ ምንጩን፥ መጠኑን፥ መድረሻውን … ሊደርስበት አይችልም (ሮሜ 11፥33)፡፡ የወደደውን ሁሉ እንደ ወደደው ማድረግ የሚችል እንደ ሆነ፥ ሐሳቡም በማንም በምንም እንደማይከለከል በቃሉ ተረጋግጧል (ኢዮ. 42፥2)፡፡

ሰውን ለማዳን ግን አንድ መንገድ ብቻ ነበረው፡፡ ያም አንድያ ልጁ በሥጋ ተገልጾ ሰው ከሆነ በኋላ፥ የሰውን ኀጢአት እንዲሸከምና በሰው ቦታ ተተክቶ ሰው በኀጢአቱ ሊቀበል የሚገባውን ቅጣት እንዲቀጣና የኀጢአትን ዕዳ እንዲከፍል ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ የሁላችንንም ኀጢአት እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አኖረበት ይላል ቃሉ፡፡ ስለ አንተ፥ ስላንቺ፥ በግል የማውቀው የለኝም፡፡ ዳሩ ግን እንደኔ ከኀጢአተኛው የአዳም ዘር መወለዳችሁንና መድኅኑ እንደሚያስፈልጋችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለ ራሴ ከሆነ ግን ከዚህ የበለጠ ብዙ ዐውቃለሁ፡፡ ከረሳሁት፥ ላስታውሰው፤ ካለፍኩት በአምላኬ ዐይን ርኵሰት ሆኖ ሳለ፥ እንደ ጽድቅ ቈጥሬ በሰው ፊት ከተመጻደቅሁበት ኀጢአት በቀር (ኢሳ. 64፥6) ኀጢአትነቱን እያወቅሁ ያመረትኩት ኀጢአት ስፍር ቍጥር የለውም ብዬ አምናለሁ፡፡

ዳሩ ግን በኀጢአት እየኖርኩ በነበረበት ጊዜ እንኳ ኀጢአት ይቀፈኝ ይዘገንነኝ፥ ሰላምም ይነሣኝ ነበረ፡፡ በሕግ የተደነገገውን ድንበር ሁሉ በሐሳብና በቃል በሥራም የተላለፍኩ በመሆኔ ለኀጢአቴ የምሰጠው ምክንያት አልነበረኝም፡፡ እንግዲህ ከአዳም ውድቀት ጅምሮ እንደኔ ባሉ ኀጢአተኞች የተመረተው የኀጢአት ብዛት ምድርን አርክሷታል ማለት ይገባል (መዝ. 105/106፥35-40)፡፡ ይህን ሁሉ ኀጢአት ነው እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ አካል ላይ ያሳረፈው፤ ከዚህ የተነሣ ኀጢአት የማያውቀውን ጻድቁንና ቅዱሱን ስለኛ ኀጢአት አደረገው (2ቆሮ. 5፥21)፡፡

እንደዚህ የሚቀፈውንና የሚያጸይፈውን የኛን የኀጢአት ርኵሰት የተሸከመው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና በሥጋ መሠቃየት ሳይጀምር ነፍሱ ሞትን በሚያህል ትካዜ ውስጥ ሰጥማ ነበር (ማር. 14፥32-34፤ ዮሐ. 12፥27)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእኛን ኀጢአት በበሽታ መስሎ ሲያቀርበው “ራስ ሁሉ ለሕመም፥ ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል፡፡ ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፣ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፤ አልተጠገነም፤ በዘይትም አልለዘበም” ይላል (ኢሳ. 1፥5-6)፡፡ በሌላም ስፍራ ጕረሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም ርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸውም ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ በዐይኖቻቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፡፡” (መዝ. 13/14፥3-6)፡፡

እንደ ገናም እንዲህ ይላል “ዐመፃ ሁሉ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት፥ የሞላባቸው ናቸው፡፡ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኮልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፡፡ የሚያንሾካሽኩ፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን የሚፈላልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል አፍራሾች፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት የለሾች ናቸው፡፡” (ሮሜ 1፥28-31)፡፡

በቃላት ተዘርዝረው የማይጨረሱትን የኀጢአት ርኵሰቶች ሁሉ አጠቃሎ እግዚአብሔር በልጁ ላይ አኖረ፡፡ የኀጢአት ዋጋ ይከፈልና ሰው ይድን ዘንድም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአእምሮው እየተጨነቀና በሥጋው እየተሠቃየ ተቀበለው፡፡ ስለ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፤ “ተጨነቀ፥ ተሠቃየ፥ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ እርሱ ስለ በደላችን ደቀቀ፤ ስለ ሕግ ተላላፊነታችን ቈሰለ፤ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፡፡” (ኢሳ. 53፥3-10)፡፡

ሰው የሚድንበት አማራጭ የሆነ ሌላ መንገድ ቢያገኝ ኖሮ፥ እግዚአብሔር በልጁ ላይ የኀጢአትን ዝፍት በመጫን እንደ ኀጢአተኛ ሆኖ ይቀጣ ዘንድ እንዲጨነቅ፥ እንዲሠቃይ፥ እንዲዋረድ፥ እንዲተፋበት ለምን አሳልፎ ይሰጠው ነበር?

ወንድሜና እኅቴ! እንደኔ ኀጢአተኞች መሆናችሁን የምታምኑ ከሆነ የኀጢአታችን ዕዳ እንዴት እንደ ተከፈለ ትረዱ ዘንድ ወደዚያች ዕለተ ዐርብ መለስ በሉና ከጌቴሴማኒ እስከ ቀራንዮ በመንፈስ በመጓዝ የሆነውን ሁሉ በመንፈስ ቃኙት፡፡

ወንድሜ ሆይ! ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የአይሁድና የሮማውያን ጭፍሮች ሲይዙት፥ ሲያዳፉት፥ በጥፊ ሲመቱት ይታይሃልን? ከተቆላለፈው የእሾኽ ሐረግ የተሠራውን ቆብ በራሱ ላይ እየደፉ ለክብረ ንግሥህ የሚገባ አክሊል እነሆ! ብለው ሲያሾፉበት፤ የእሾኽ አክሊሉን በዘንግ እየጨፈጨፉና ፊቱን በጥፊ እየመቱ የመታህን እስኪ ተናገር በማለት ሲቀልዱበት ትመለከታለህን? በአክሊሉ ከነበሩት እሾኾች ስንቶቹ በራሱና በግምባሩ ጠልቀውና ተሰብረው በዚያ እንደ ቀሩ ባይጻፍም፥ ደሙ በፊቱ ላይ ሲንዠረዠር ተመልክተኸው ታውቃለህን? ልብሱን አውልቀው በልቡ ሲያስተኙት፥ ሲገርፉት፥ የጀርባው ቆዳ እየተቀደደ ሥጋውም እየተቈራረጠ ሲወድቅ ደሙም ከሰውነቱ ተርፎ የተኛበትን መሬት ሲያለብሰው ይታይሃልን? ከራሱ በሚወርደው ደም ፊቱ የተሸነፈነውን፥ ጀርባው ተቦዳድሶ በአጥንት የቀረውን ኢየሱስን የሚሰቀልበትን ግንድ አሸክመው ወደ ቀራንዮ ኰረብታ ጭፍሮች ሲወስዱት፥ የሚሰማው ድካምና ሥቃይ ይሰማሃልን? በጕዞው ሲወድቅ ሲነሣ ይታይሃልን? በዚህ ሁሉ ሥቃይ ውስጥ ያለፈውን ኢየሱስን በዕንጨት ላይ ሰቅለው እጆቹንና እግሮቹን በዚያን ጊዜው ቀጥቃጭ ቀጥቅጦ በሠራው ወፍራም ምስማር ሲቸነክሩት፥ ከንፈሮቹና ምላሱ ሐሞትና ከርቤ በተደባለቁበት ሆምጣጤ ሲኰማተሩ በመንፈስ አይተሃልን? በመስቀል ላይ ሆኖ ያችን የፃዕር ጊዜ እንኳ ለግሉ እንዳያውላት የካህናት አለቆችና ጭፍሮቻቸው መንገደኞች ሳይቀሩ እየዘበቱና እያሽሟጠጡ፥ ያም እንደ ዕረፍት ተቈጥሮ ዕረፍት ሲነሡት የነበረበትን ሁኔታ ታስታውሳለህን? ተፈጸመ ብሎ ነፍሱን ሲሰጥና አንዱ ጭፍራ ጐኑን በጦር ሲወጋው ይታይሃልን?

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል ላይ ሥጋውን ለማውረድ ከዕንጨቱ ጋር ከተዋደደው ምስማር ጋር ሲታገሉ፥ ምስማሩ የቦደሰውንና የተነደሉትን እጆቹንና እግሮቹን የመንፈስ ዐይኖችህ አይተው ያውቃሉን? እኔ ልዘረዝረው አልችልም፡፡ በመስቀል ላይ በተቸነከረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተጻፈውን የሥቃያት ፊደል ታላቁ መምህር ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እጅህን ይዞ ቢያስቈጥርህ ይሻላል፡፡

ምናልባት አንተ ያየኸው፥ የከሳውን፥ የገረጣውን፥ የተጐሳቆለውን፥ ደሙ ፈስሶ ያለቀበትን፥ ውበቱ ሁሉ የተወሰደበትን፥ እውነተኛ የኀጢአትህ መሥዋዕት ሆኖ በመስቀል ላይ የተሠዋውን የእግዚአብሔር በግ ሳይሆን፥ ለቀልድ፥ ወይም ፎቶ ለመነሣት በዕንጨት ላይ የወጣ የሚመስለውን እንቦቀቅላ ጎረምሳ ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱን ጠላት እንደ ሣለው ቍጠረውና አስወግደው፡፡ ላንተ ግን በእግዚአብሔር መንፈስና በቃሉ ሰዓሊነት በመስቀል ላይ የተሳለውን እውነተኛውን ኢየሱስን የምታይበትን መንፈሳዊ ዐይን ጌታ ያብራልህ! አሜን፡፡

እንግዲህ ልዑልና ቅዱስ እግዚአብሔር እኛን ወደደ፤ ቢወደንም የኀጢአታችን ዋጋ ካልተከፈለ በቀር ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊኖረን ስለማይችል፥ የኀጢአታችንም ዋጋ መከፈል ያለበት ከዚህ በላይ በተጻፈው መንገድ ብቻ ሆኖ በመገኘቱ እንጂ እግዚአብሔር በሚወደው አንድያ ልጁ ሥቃይ ተደሳች ሆኖ አይደለም፡፡ እንኳ በአንድያ ልጁ ላይ በማንም ሰው ላይ ቢሆን ሥቃይ እንዲደርስ አይፈቅድም (ሕዝ. 33፥11)፡፡


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በሌላ በማንም ቢሆን ሊሠራ የማይችለውንና በሌላ በምንም መንገድ ቢሆን ሊገኝ አይችል የነበረውን የሰውን ደኅንነት ያስገኘልን በዚህ ሁኔታ፥ ማለት ራሱን ተለዋጫችን በማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛን ለማዳን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የደረሰውንና የተፈጸመበትን ሁሉ፥ ሰው እንዴት የራሱ ገንዘብ አድርጎ ሊጠቀምበት ይችላል? የሚለውን በቀጣዩ ክፍል እንመለከታለን፡፡

በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment