Tuesday, November 22, 2011

በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮች መካከል የተደረገ ክርክር (1)

READ PDF
                                                                            ረቡዕ ኅዳር 13 2004
በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮችና አባላት መካከል እየተካረረ የመጣውን ውዝግብ ተከትሎ የአጋዓዝያን ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና ሊቃውንት ሁለቱን ወገኖች ፊት ለፊት ለማነጋገርና ችግሮችን ለመፍታት ጉባኤ ጠርተው ነበር። በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ይምርሐነ ክርስቶስና ብፁዕ አቡነ ፍሬምናጦስ፣ ከሊቃውንትም አለቃ ነቅዐ ጥበብና መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እም አእላፍ፥ የኮሌጁ ደቀ መዛሙርትና የማኅበሩ አንዳንድ ተወካዮች፥ እንደዚሁም ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ ሁሉ የጉባኤው ታዳሚዎች ነበሩ። 

ብፁዕ አቡነ ፍሬምናጦስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ፥ የመድረክ መሪ ሆነው የተሠየሙት መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እም አእላፍ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቅደም ተከተል በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰበሰው ታዳሚ አብራሩ። በዚሁ መሠረት የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች በየተመደበላቸው ስፍራ ላይ ሆነው ቅሬታቸውን በመደማመጥ ተራ በተራ እንዲያሰሙና በመጀመሪያው ዙር ሁለቱም ወገኖች ሐሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ በሁለተኛው ዙር አንደኛው ወገን ለቀረበበት ጥያቄ ወይም ክስ፥ ወይም ለተሰነዘረበት ትችት በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጥ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚኖርም አስረዱ። በመጨረሻም ከጉባኤው ታዳሚዎች አስተያየት ከተሰጠ በኋላ፥  ከሊቃውንት ደግሞ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ሐሳብ ሰጥተው ጉባኤው ወደ መፍትሔ ሐሳብ እንደሚያመራ፥ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ይምርሐነ ክርስቶስ ቃለ ምእዳን አሰምተውና ጸሎት አድርገው መርሐ ግብሩ እንደሚጠናቀቅ የጉባኤውን አካሄድ አስታወቁ። 

 የመጀመሪያውን የመናገር ዕድል ያገኘው የማኅበረ ቀናዕያን ወገን ሲሆን፥ ተወካዩ ዲያቆን በለው ዘርዐ ያዕቆብ ለታዳሚው ሰላምታ ካቀረበ በኋላ በደቂቀ እስጢፋኖስ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ላይ ማኅበረ ቀናዕያን ያለውን ቅሬታና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጋርጠዋል ያለውን አደጋ ማብራራት ጀመረ።

“እናት ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ በልዩ ልዩ ፈተናና ችግር ያለፈች ሲሆን፥ እርሷን ለማፈራረስ ከውጭ ዐላውያን ነገሥታት፣ ከውስጥ ደግሞ ቦርቧሪዎች መናፍቃን ያልሸረቡት ሤራ አልነበረም። ቤተ ክርስቲያናችን ግን ይህን ሁሉ በእግዚአብሔር ኀይልና በልጆቿ ተጋድሎ ድል እየነሣች እዚህ ደርሳለች። ዛሬ የተጋረጠባት ፈተና ዐዲስ ባይሆንም፥ በውስጧ ሠርገው የገቡ መናፍቃን ብዙዎችን እየበከሉና ከቻሉ ቤተ ክርስቲያናችንን ሙሉ በሙሉ በቊጥጥራቸው ሥር አውለው ሊወርሱ፥ ካልሆነላቸውም ሊካፈሉ ባለ በሌለ ኀይላቸው እየተንቀሳቀሱ ነው። ዋና ዐላማቸውም ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ወደ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ማንሸራተት ነው። በስብከታቸው ላይ የእመቤታችንንና የቅዱሳንን ስም አያወሱም፤ ሁል ጊዜ ኢየሱስ፥ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚሉት። ዝማሬያቸው ያሬዳዊ ለዛ የሌለውና ወደ ዘፈን ያጋደለ ነው፤ አንዳንዱ ዝማሬማ በቀጥታ ከዘፈን ዜማ የተወሰደ ነው። በአጠቃላይ መናፍቃኑ ለማደናገር እኛ ኦርቶዶክሶች ነን ይበሉ እንጂ፥ አስተምህሮአቸው የሚቀርበው ለኦርቶዶክስ ሳይሆን ለፕሮቴስታንት ነው። ማኅበራችን ይህን አስመልክቶ ባደረገው ጥናት በመቶኛ (በፐርሰነት) ሲያሰላው፥ የእነርሱ አስተምህሮ ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ ጋር መቶ በመቶ ሲመሳሰል፥ ከኦርቶዶክስ አስተምህሮ ጋር ግን መቶ በመቶ ይለያያል። ይህን አንገብጋቢ ጕዳይ ቤተ ክርስቲያናችን ቸል ብትለውም፥ ማኅበራችን ግን በንቃት እየተከታተለና መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያን ለመመንጠርና ከውስጥ ጠራርጎ ለማስወጣት በጠረጠራቸው ሰዎች ላይ መረጃ እየሰበሰበ፥ ክትትል እያደረገም ይገኛል። 

“መናፍቃኑ ለያዙት የጥፋት ተልእኮ ብዙ ስልቶችን እየተጠቀሙ ያለ ሲሆን፥ ከስልቶቻቸውም አንዱ መንፈሳውያን ኮሌጆቻችንን በኑፋቄ ትምህርቶቻቸው መበከልና ከዚያ ተመርቀው በአገልግሎት ላይ የሚሰማሩ አገልጋዮችን የምንፍቅናና የቅሰጣ ትምህርታቸው አስተላላፊዎች የማድረግ ስልት ነው። በዚህ ረገድ ብዙዎቹ ኮሌጆቻችን በመናፍቃን እየተወረሱ ናቸው። ስለዚህ ምእመናን ሆይ! አባቶች ያወረሱንን ሃይማኖት ጠብቀን ማቈየትና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብንና ከእኛ ጋር ልትነሡ ይገባል።” አለና በተሰጠው ዕድል ሊናገር የወደደውን ተናግሮ ሲጨርስ፥ ከወደ ኋላ ጥቂት እጆች ሲያጨበጭቡ ተሰማ፤ በአዳራሹ ተሰብስቦ የነበረው ታዳሚ “ዞረህ ተመልከት” ተብሎ የታዘዘ ይመስል ወደሚጨበጨብበት አቅጣጫ ዞረ። … ጭብጨባው ወዲያው ቆመ።

የመድረኩ መሪ መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እም አእላፍ፥ “ከማኅበረ ቀናዕያን ወገን የመጀመሪያው ተናጋሪ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፤ እግዚአብሔር ይስጥልን። የሚቀጥሉት ተናጋሪ ከደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዝሙር በቃሉ ታመነ ናቸው” አሉና ለተናጋሪው ጊዜውን አስረከቡ።

ደቀ መዝሙር በቃሉም ለታዳሚው የከበረ ሰላምታውን ካቀረበ በኋላ የመጀመሪያ ሐሳቡን መናገር ቀጠለ። “የራስን ጉዳይ ትቶ ስለ ሌሎች ብቻ መናገር የራስን ችግር ለመሸፈን፥ ወይም ነገሮችን ከምሕዋራቸው ለማስወጣትና አቅጣጫ ለማስለወጥ የሚደረግ ጥረት እንጂ ራስን መግለጽ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ሌሎችን በመኰነን መጽደቅ፥ ሌሎችን በማርከስ መቀደስ፥ የሌሎችን ስም በማጕደፍ የራስን ስም ማንጻት አይቻልም። ዲያቆን በለው አሁን የተናገረው እርሱ ስለሚወክለው ማኅበር ትክክለኛ ማንነት፥ ማኅበሩን ስላጋጠመው ችግር፥ ከእኛ ጋር ሆድና ጀርባ ስለ ሆነበት ጕዳይና ተያያዥ ስለ ሆኑ ነገሮች አይደለም። እኛና እነርሱ ውዝግብ ውስጥ የገባንበትን ጉዳይ ከመግለጽ ይልቅ፥ የእኛን ጕዳይ ከል አልብሶ በመካከላችን ያለውን ውዝግብ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ችግርና ቤተ ክርስቲያቱን ትልቅ አደጋ ላይ የጣለ ሃይማኖታዊ ሕጸጽ አስመስሎ ነው ያቀረበው። ይህም ጀሌና ደጀን ለማፍራትና እውነትን በሐሰት ለመለወጥ የሚደረግ ኢመንፈሳዊ አካሄድ ነው። እኔ በዚህ መንገድ መሄድና ጕዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ መውሰድ አልፈልግም። እኛንና ማኅበረ ቀናዕያንን ያጋጨውን መሠረታዊ ሐቅ መርምሮ እውነቱን ወደ መግለጥ ነው የምገባው።” ብሎ በአዳራሹ የተሰበሰበውን ጉባኤ፥ ዲያቆን በለው ሊነዳ ከፈለገበት አቅጣጫ ለመመለስ ጥረት አደረገ።

ቀጠለና፥ “እኔ እንደሚገባኝ ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐት የደረጀችና ከራሷ ተርፋ ለሌሎችም ምሳሌ የምትሆን ቤተ ክርስቲያን ነች። አሁን፥ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ግን ይህን ክብሯን የሚቀንስ ሆኗል።  ቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት ያለባት ቤተ ክርስቲያን ስትሆን፥ በአንድ ማኅበር ትመራ በሚለው የማኅበረ ቀናዕያን አካሄድ ሥርዐቷ እየላላና እየተደፈረ መጥቷል ማለት ይቻላል። ሕግና ሥርዐት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ በዘመነ መሳፍንት እንደ ነበረው የእስራኤል ልጆች አኗኗር ሁሉም በሕግና በሥርዐት ሳይሆን በዐይኑ ፊት መልካም መስሎ የታየውን ወደ ማድረግ መሸጋገር ይሆናል (መሳ. 17፥6፤ 21፥25)። ይህም ፍጹም ሥርዐት አልበኛነትን ያሰፍናል።

“ሁላችንም የአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ነን፤ ይህን መብት ማንም አልሰጠንም፤ ማንም ሊወስድብን አይችልም። ከማኅበሩ ጋር እያወዛገበን ያለው ዋናው ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን የሥልጣን መዋቅር ባልጠበቀ ሁኔታ፥ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያን እኔ በቀየስሁላት መንገድ ትሂድ ማለቱ ነው። ይኸው የማኅበሩ ድፍረት ወደ እኛም ተሸጋግሮ ኮሌጁን ለመቈጣጠርና ኢመጽፍ ቅዱሳዊ የባልቴቶች ተረቱን በኮሌጃችን ውስጥ ለመንዛት ዕቅድ ይዞ መንቀሳቀሱን ደርሰንበታል። ሁላችሁም እንደምታስተውሉት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐተ ትምህርት ቀርጻ መንፈሳውያን ኮሌጆችን የከፈተችውና ልጆቿ ገብተን እንድንማር ዕድል የሰጠችን፥ ለምእመናን ትክክለኛውን ትምህርተ ወንጌል እያስተማርን ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመንግሥተ ሰማያት እንድናበቃው፣ በሥጋዊ ኑሮውም ወደ ተሻለ ደረጃ ይደርስ ዘንድ በመንፈሳዊ ዕውቀት እንድናበረታው ነው እንጂ፥ ባለበት እንዲረግጥ አይደለም። እንዲህ ስንልም ካሁን ቀደም ያልነበረ ዐዲስ ሃይማኖት እንፈልስፍ ማለታችን አይደለም፤ እምነታችንና ሥርዐታችን በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ይሁን፤ ጌታ ከአብ ተቀብሎ የሰጠውና (ዮሐ. 8፥26) ለሐዋርያት ያስተላለፈውን ትምህርተ ወንጌል መሠረት አድርገው አበው ያስተማሩት ትምህርትና ያቈዩልን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዐት ብቻ ይምራን፤ ከዚህ ውጪ ያለው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት እንደየሁኔታው፡- መስተካከል ያለበት ይስተካከል፤ መሻሻል ያለበት ይሻሻል፤ መወገድ ያለበት ይወገድ ነው የምንለው። ከዚህ ውጪ ማኅበረ ቀናዕያን እኛን የሚከስበት ነጥብ የለውም። ቢያገላብጠን የሚያገኘው እርሱ ‘ኑፋቄ’ የሚል ስም የሰጠውን ወንጌልን ነው።

“በመቀጠል ዲያቆን በለው ባቀረበብንን ትችት ላይ ምላሽ ወደ መስጠት እሸጋገራለሁ” ሲል የመድረኩ መሪ መጋቤ ወንጌል ኅሩይ አቋረጡትና “መምህር በቃሉ፥ ዲያቆን በለው ላቀረበው ሐሳብ ምላሽ የሚሰጠው በሁለተኛው ዙር በተመደበልህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ነውና የመጀመሪያ ሐሳብህን ብትቋጭ የተሻለ ነው” ሲሉ በአካሄዱ ላይ ማስተካካያ ሰጡ፤ መምህር በቃሉም የመጀመሪያ ሐሳቡን መጨረሱን ገልጾ ንግግሩን አቆመ።

በመርሐ ግብሩ መሠረት በመድረክ መሪው ግብዣ ዲያቆን በለው፥ መምህር በቃሉ ላቀረበው የመነሻ ሐሳብ ምላሽ ለመስጠት መድረኩን ተረከበና ንግግሩን ቀጠለ። “መቼም አባቶቻችን እንደሚተርቱት ‘የጦጣን ልጅ በዛፍ የመናፍቅን ልጅ በአፍ’ የሚችላቸው የለም፤ ከመምህር በቃሉም የምንረዳው ይህንኑ ነው። ማኅበረ ቀናዕያን ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን የሚቀኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ያሰባሰበ ማኅበር መሆኑን ስሙም (‘እስመ ስሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ’ እንዲል)፥ በሰው ሁሉ ፊት የተገለጠው እንቅስቃሴውም ምስክር ነው። ማኅበሩን ያስነሣውም ለቤተ ክርስቲያናችን ግድ የሚለው እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ እርሱ ይህን ማኅበር ባያስነሣ ኖሮ ይህች ቤተ ክርስቲያን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ፕሮቴስታንትነት መለወጧ አይቀርም ነበር። በእኛ ትግል ግን ይኸው እስካሁን አለች፤ ወደ ፊትም ትቀጥላለች።” ሲል ብዙው ታዳሚ በተቀመጠበት አጕተመተመ፤ ጥቂት እጆች ግን የዲያቆን በለውን ንግግር በጭብጨባ አጀቡት።

ዲያቆን በለው ቀጠለ፤ “ከመንፈሳውያን ኮሌጆች ተማሪዎች ጋር እያጋጨን ያለው የቤተ ክርስቲያናችን ጕዳይ እንጂ ሌላ ተራ የእርስ በርስ ሽኩቻ አይደለም። እኛ አባቶቻችን በብዙ ተጋድሎ ያቈዩልን ማንኛውም ትምህርትና ሥርዐት ምንም እንከን የሌለው ስለ ሆነ ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዳለ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ አለበት ብለን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። አስተዳደራዊ ተሐድሶ እንደሚያስፈልግ ግን እኛም እናምናለን። ይሁን እንጂ እነርሱ፥ … ይኸው በዚህ ጉባኤ እንኳ መምህር በቃሉ አፉን ሞልቶ አባቶቻችን ያቈዩልን ትምህርትና ሥርዐት የሚስተካከል፣ የሚሻሻልና የሚወገድ ነገር እንዳለበት አድርጎ ነው የተናገረው። ከመንፈሳውያን ኮሌጆች የሚወጡ ደቀ መዛሙርት እየሰበኩ ያለው ስለ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ የእመቤታችንን፣ የቅዱሳን መላእክትን፣ የጻድቃንንና የሰማዕታትን ስም ተሳስተው እንኳ ሲጠቅሱ አይሰማም። ምድራችንን እየበከሉ ያሉ ዝማሬዎቻቸውም ያሬዳዊ ላህይ (ለዛ) የሌላቸው ዘፈኖች እንጂ መዝሙሮች አይደሉም። ወደ ዓለም እየተሳበ ላለው ወጣቱ ትውልድ ጆሮ ግን ተስማሚ ስለ ሆኑ ብዙ አድማጭ እያተረፉ ነው። ይህን የቤተ ክርስቲያናችንን የኖረ ትምህርትና ሥርዐት የሚንድ ተግባር ዝም ብለን ማለፍ ስለማንችል ነው ምእመናንን ወደ ማስጠንቀቅ የዞርነው። መምህር በቃሉ ሌላ ገጽታ ሊሰጠው የሞከረው በእኛና በእነርሱ መካከል ያለው መሠረታዊ ችግርም ይኸው ነው፤ እኛ ሌሎችን በመኰነን ራሳችንን ማጽደቅ የምንፈልግ ግብዞች አይደለንም።
                                             ይቀጥላል

6 comments:

  1. would you please tell me that the organization "mahbere bekur" is there?because i was trying to distribute some Chora books during 1984-1988.I was very interested in the renewal of the nowadays orthodox church.But all is according to the will of God.But it is better to work like this with his grace.bertu....try at least form some orthodox church which resembles the true church of Christ. my email is hababate16@gmail.com

    ReplyDelete
  2. Abet kentu dikam! yekidusan Amlak Egzi'abher benante adro kidist betekiristianin lemafres yemmidekmewun diablosin hulem be kena'iyan lijochu lay adro ras rasun yiketekitalina be kentu atidkemu!

    ReplyDelete

  3. For the reason that the admin of this web site is working, no question very quickly it will be famous, due to its quality contents. netflix login

    ReplyDelete
  4. This info is worth everyone's attention. Where can I find out more?

    ReplyDelete
  5. Thank you for another magnificent post. The place else may just anybody get that
    type of info in such a perfect method of writing? I have a
    presentation next week, and I'm on the look for such information.

    ReplyDelete
  6. Howdy would you mind letting me know which webhost you're using?
    I've loaded your blog in 3 completely different browsers
    and I must say this blog loads a lot faster then most.
    Can you recommend a good internet hosting provider
    at a fair price? Cheers, I appreciate it!

    ReplyDelete