Saturday, December 21, 2013

ጋብቻ


የጋብቻ ትምህርት

“እግዚአብሔር መረጠ” (1ቆሮ. 1፥27)

“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡” (ገላ. 4፥4) በአብርሃምና በሣራ፥ በይሥሐቅና በርብቃ፥ እንዲሁም በያዕቆብና በሚስቶቹ የጋብቻ ሕይወት ጥናታችን ውስጥ ግንኙታነቸው፥ ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንደ ክርስቲያንነታችን ልንገነዘባቸው የቻልን የተለያዩ ትምህርቶች እንደ ነበሩ እናስታውሳለን፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ውድ ልጁን በሕፃንነቱም ሆነ በወጣትነቱ ወቅት ሊያስተናግድ የሚችል ቤት ለመሥራት ምን ዐይነት ቤተ ሰብ መረጠ? እግዚአብሔር ለዚህ ታላቅ ነገር በሚመርጣቸው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እርሱን የሚያስደስቱ መልካም ባሕርያትን በርግጥ እናያለን፡፡ በዚህም የክርስቲያናዊ ጋብቻ ጥናታችንን መሆን በሚገባው መጠን ልናዳብረው እንችላለን፡፡

ፍሬ በአንድ ዕለት አይበስልም

ከጋብቻ ችግሮች ሁሉ የገንዘብ ዕጦት ዋናው እንደ ሆነ የሚታመን ቢሆን እግዚአብሔር ለልጁ እናት እንድትሆንለት ሀብታም ሴትን ወይም ባለጸጋ አሳዳጊ አባትን እንዳልመረጠ ልብ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም ዮሴፍ፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልንን?” በማለት ናትናኤል “በእውነት የእስራኤል ሰው” (ዮሐ. 1፥46) የተነገረላት የተናቀችዋ የናዝሬት ከተማ ኗሪ የሆነ ተራ ሠራተኛ ወይም ዕንጨት ጠራቢ ሰው ነበረና ነው፡፡ ማርያምም እንደ ዮሴፍ ሁሉ በናዝሬት ከተማ ትኖር የነበረች የዓለምን ነገር ገና ያልተገነዘበች ድንግል ነበረች፡፡ ልጇ የሚወለድበት ጊዜ ሲቀርብ ማርያምም ሆነች ዮሴፍ በራሱ ቅድመ አያቶች ከተማ በቤተ ልሔም በነበሩበት ጊዜም እንኳ ተመልሰው የሚገበቡት የራሳቸው የሆነ ንብረት ወይም ሀብት የነበረው የታወቀ ዘመድ አልነበራቸውም፡፡ ሕፃኑ የተወለደው በግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሕፃኑን በቤተ መቅደስ ውስጥ ለጌታ ለመስጠት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ መሥዋዕት ይዘው የሄዱት “ሁለት የዋልያ ወይም ሁለት የዕርግብ ጫጩቶችን” ነበር፡፡ እንደዚህ ዐይነቱ ስጦታ የጠቦት መሥዋዕት ማቅረብ የማይችሉ እጅግ የደኸዩ ሰዎች የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደነበር በሕግ መጽሐፍ ተጠቅሷል (ዘሌ. 12፥8)፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሰብአ ሰገል ጕብኝት ቀጥሎ በዚያን ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ከነበረው ከሄሮድስ የጭካኔ ሥራ ለማምለጥ ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብጽ እንዲሄዱ ተነገራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ምናልባት ለችግራቸው ይሆናቸው ዘንድ የወርቅ ስጦታዎችን፥ ዕጣንና ከርቤ በእግዚአብሔር ርዳታ ሳያገኙ አልቀሩም፡፡ ለዚህ በተለየ መንገድ ለተመረጠ የኑሮ ጉድኝት በገንዘብ ችግር ምክንያት መጠለያ መጥፋቱ እግዚአብሔር፥ “የዚህን ዓለም ብልጽግና” አለመምረጡን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን ያደረገው ምናልባት ሁለቱ ዮሴፍና ማርያም ለሚያስፈልጋቸውና ለሚያጋጥማቸው ችግር ሁሉ በትሕትና መንፈስ በእርሱ ላይ ተደግፈው እንዲኖሩ በመፈለጉ ነው፡፡ “ገንዘብ ስለሌለን በኑሮአችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መታዘዝ አንችልም” በሚል ሐሳብ የሚፈተኑ ክርስቲያን ባለትዳሮች ካሉ ከዚህ ቤተ ሰብ አኗኗር ይማሩ፡፡

Tuesday, December 10, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት

መጽሐፈ ባሮክ
ካለፈው የቀጠለ

መግቢያ
ባሮክ የነቢዩን የኤርምያስን ቃል እየሰማ ይጽፍ የነበረ ወይም በዐጭር ቃል ኤርምያስንና የቃሉን ባለቤት እግዚአብሔርን በጸሓፊነት ያገለገለ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነበረ ይታወቃል (ኤር. 36፥1-8፤ 27፥32)፡፡

በኤርምያስ አንደበት እንደ ተነገረው የእግዚአብሔር ቃል፥ ናቡከደነፆር ያዘመተው የከለዳውያን ጦር ሠራዊት ምድረ ይሁዳን ከወረረ፥ የኢየሩሳሌምን ከተማ ከነቅጥሯ ከደመሰሰ፥ የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ከወሰደና ቤተ መቅደሱን ካቃጠለ በኋላ፥ የሕዝብ አለቆችንና ባለሙያዎችን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፡፡ የደረሰውን ጥፋት አስቀድሞ በመተንበዩ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ተግዞ የነበረውን ኤርምያስንም በነጻነት በፈለገው ስፍራ እንዲኖር ፈቀደለት (ኤር. 38፥17-18፤ 39፥11-14፤ 40፥1-6)፡፡

Tuesday, December 3, 2013

መሠረተ እምነት

ኢየሱስ ክርስቶስ ዐዲስ ኪዳን መካከለኛ
በጮራ ቊጥር 40 ላይ፡-
·        ኢየሱስ አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ?
·        1ዮሐ. 2፥1-2 ስለ ማን ይናገራል?
·        የኢየሱስ ጠበቃነት በምድራዊ ጥብቅና ይመዘናልን?
·        ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ መካከለኛነቱን አስቀርቶታልን?
·        ቅዱሳን መካከለኞች አይደሉምን?  
በሚሉ ዐምስት ንኡሳን አርእስት ሥር የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማስረጃዎችን በማቅረብ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በዚህ ዕትም ደግሞ የዕብራውያንን መልእክት መሠረት በማድረግ የክርስቶስን መካከለኛነት እንመለከታለን። በቅድሚያ ግን ለዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ለሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላና ምሳሌ ስለ ሆኑት የብሉይ ኪዳን መካከለኞች ስለ ነበሩት ሊቃነ ካህናት መሠረታውያን ነገሮችን እንዳስሳለን። ከዚህ በፊት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 23 በስፋት መጻፉን ለአንባብያን መጠቈም እንወዳለን።

የካህናት ሹመትና አገልግሎት በብሉይ ኪዳን
የዕብራውያን መልእክት “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤” (ዕብ. 5፥1) በማለት፥ ስለ ሊቀ ካህናት ማንነት፣ ሊያሟላ ስለሚገባው መስፈርትና ስለሚሰጠው አገልግሎት የሚናገር ቃል እናነባለን። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚሾመው፡-
·        ከሰው ተመርጦ መሆኑን፣
·        ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ መሆኑን እና
·        ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ ስለ ሰው የሚሾም መሆኑን
እንገነዘባለን። ጥቅሱ ስለ ብሉይ ኪዳን ካህናት ማንነት፣ ስለሚሾሙበት ምክንያትና ስለሚወክሉት ወገን ይናገራል ማለት ነው። “ከሰው ተመርጦ” የሚለው፥ ሊቀ ካህናት የሚሆነው የመላእክት ወገን ሳይሆን የሰው ወገን መሆኑን ሲያስረዳ፥ መራጩም አካል ሌላ [እግዚአብሔር] እንጂ ካህኑ ራሱን በራሱ ሊመርጥ ወይም ሊሾም እንደማይችል ያመለክታል። “እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም” (ቊጥር 4)።