Saturday, November 26, 2011

በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮች መካከል የተደረገ ክርክር (2)

           READ PDF                                                
 ቅዳሜ ኅዳር 16 2004       
                                ክፍል ሁለት 

“ሌላው የነመምህር በቃሉ የማደናገሪያ ስልት ከአባቶች ትምህርት የሚስማማቸውን ብቻ ከፍሎ በመጥቀስና ሌላውን በመተው የእኛ ትምህርት የአባቶች ነው ለማለትና ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት ወደ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ለማንሸራተት መሞከራቸው ነው። እኛ እያልን ያለነው አንዱን ጠቅሶ ሌላውን መተው ትክክለኛ አያሰኝምና ከአባቶች ከጠቀሳችሁ ሁሉንም መጥቀስና ስለ ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን ስለ እመቤታችን፣ ስለ መላእክት፣ ስለ ቅዱሳን አስተምሩ፤ ትክክለኛውን አስተምህሮአችንን ወደ ፕሮቴስታንቶች አስተምህሮ አታንሸራቱ ነው። ይህ ደግሞ ወንጌል እንጂ ከወንጌል የሚቃረን አይደለም” አለና ንግግሩን አጠናቀቀ።

ቀጣዩ ተረኛ ተናጋሪ መምህር በቃሉ እንዲናገር ከመድረክ መሪው ሲጋበዝ ለመናገር ጕረሮውን በእህህህታ ሞርዶ ለጥቂት ሰኮንዶች በዐይኖቹ ታዳሚዎቹን ከቃኘ በኋላ ቀጠለ። “እኔ ለዲያቆን በለው ጽርፈት (ስድብ) የተሞላበት ንግግር ምላሽ ከመስጠቴ በፊት፥ በለውን ጨምሮ ሁላችንም በየልባችን ምላሽ የምንሰጥባቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ማኅበረ ቀናዕያን የተቋቋመበት ዐላማ አሁን ዲያቆን በለው የዘረዘረውን ለማድረግ ነው ወይ? እንዲህ እንዲያደርግ ሥልጣን የሰጠው አካልስ ማነው? እንዲህ የማድረግስ ሕጋዊ መብት አለው ወይ? ማኅበሩ ራሱን የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ፖሊስና ጠበቃ በማድረግ፥ እኔ ከሌለሁ ቤተ ክርስቲያን አትኖርም ማለቱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነውን የክርስቶስን ስፍራ መንጠቅ አይሆንም ወይ? … እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉም ለራሱ እንዲመልስ በትሕትና አሳስባለሁ።

“የማኅበረ ቀናዕያን አባላት የሚታወቁት ወንጌልን በመስበክ አይደለም፤ ለወንጌል አገልጋዮች መናፍቅ የሚል ቅፅል ስም በማውጣት ነው እንጂ። ምናልባት እነርሱ እኛን ያናደዱ መስሏቸው ዘወትር እንዲህ ቢሉ ቅር አይለንም። እኛ የእነርሱን ጽርፈት ሳይሆን በጽርፈታቸው አንጻር ጌታችን የተናገረልንን ቃል ነው የምናስበው። “ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፣ ሲለዩአችሁም፣ ሲነቅፉአችሁም፣ ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ ብፁዓን ናችሁ” (ሉቃ. 6፥22) ልብ በሉ! ‘ስለ ሰው ልጅ … ስማችሁን እንደ ክፉ ሲያወጡ’ ነው ያለው። እነ ዲያቆን በለው የእነርሱ አባል ያልሆነውንና ከእነርሱ በተጻራሪ የቆመ የመሰላቸውን ሰው ሁሉ በሌላቸው ሥልጣን ወይም ባልተቀበሉት የቤተ ክርስቲያን ውክልና ከሜዳ ተነሥተው መናፍቅ ማለት ልማዳቸው ብቻ ሳይሆን የእምነት ዐቋማቸውም እየሆነ መጥቷል። መናፍቅ የሚለው ስም እንዲህ እንደ ዛሬው ማንም እየተነሣ ሌላውን የሚጸርፍበት ተራ ስድብ ከመሆኑ በፊት፥ ቤተ ክርስቲያን ከትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቷ ላፈነገጠና ተመክሮና አልመለስ ብሎ በተሳሳተ ዐቋሙ ለጸና ሰው፥ ጕዳዩን በቅዱስ ሲኖዶስ መርምራ በተገቢው መንገድ የምትሰጠው ስያሜ ነበር። አንድን ሰው በተገቢው መንገድ መናፍቅ ለማለት ሥልጣን ያላት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት ማለት ነው። ከእርሷ ውጪ ሌሎች ማኅበራትና ግለ ሰቦች፥ ቤተ ክርስቲያን በተገቢው መንገድ መናፍቅ ያላለችውን ሰው፥ እነርሱም ሆኑ ሌሎች ግለ ሰቦች መናፍቅ ቢሉት እንደ ተራ ስድብ ነው የሚቈጠረው፤ ያ ሰው ተሰደበ እንጂ ተወገዘ አይባልም።” ሲል ንግግሩን የታዳሚው ጭብጨባ አቋረጠው።

“ሌላው የቀረበብን መሠረተ ቢስ ክስ የኦርቶዶክስን ትምህርት ወደ ፕሮቴስታንት ትምህርት ማንሸራተት ይዛችኋል የሚል ነው። እውን ማኅበረ ቀናዕያን እንዲህ ብሎ ለመናገር እርሱ ማነው? የኦርቶዶክስ ትምህርት መዛኝ ያደረገውስ ማነው? አባላቱ እንደ ተሰጥኦ ተቀባይ በጆሮ ጠገብነት ወይም በድምጫ በቃረሙት ውጥንቅጥ ትምህርትና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሳይማሩ ለይስሙላ በተሸከሙት ማዕርግ ለኦርቶዶክስ አብነታዊ ትምህርት ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም፤ ነገረ ሥራቸው ሁሉ ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንደ ተባለችዋ ልጅ ያለ ነው። ለመሆኑ የኦርቶዶክስ ትምህርት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለምን? የአበው ትምህርት ምንጩስ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለምን?

“ወገኖቼ፥ ከማኅበረ ቀናዕያን ጋር የሚያለያየን መሠረታዊ ነገር ሁለታችንም የምንመራባቸው መጻሕፍት መለያየታቸው ነው። የእነርሱ ዋና መመሪያ አዋልድ መጻሕፍት ሲሆኑ፥ የእኛ ደግሞ በዋናነት መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ለተጻፉ የአበው ትምህርቶችም ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጣለን። በአዋልድ መጻሕፍት የተጻፉት ብዙዎቹ ነገሮች ክርስትናን ወደ ተረት የሚያንሸራትቱ መሆናቸው የክርስትናን ትምህርት በሚገባ ከተረዳ ሰው የተሰወረ አይደለም። ገድላትና ድርሳናት በአብዛኛው ገጽታቸው የክርስቶስን አዳኝነት በቅዱሳን መላእክትና ሰዎች አዳኝነት የሚሸፍኑ ልቦለድ ድርሰቶች በመሆናቸው ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ናቸው። የእኛ ጥረት ደግሞ በአዋልድ ስብከት ወደ ተረት የተንሸራተተውን ትምህርት ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱ መመለስ ነው። ይህ ነው እንግዲህ ክፉ ስም በማውጣት በተካኑት ማኅበረ ቀናዕያን ዘንድ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት እየተባለ የተብጠለጠለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መመራት ክርስቲያን ማሰኘቱ ቀርቶ ፕሮቴስታንት ካሰኘ እንግዲህ ምን ይባላል?

“ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአበው ትምህርት የሚስማማቸውን ጠቅሰው የማይስማማቸውን ያልፉታል፤ ወይም ሥራቸው “ከፍሎ መጥቀስ” ነው ተብለናል። ዲያቆን በለው በዚህ አነጋገሩ፥ ከአፉ ሊለየው የማይፈልገውን “መናፍቅ” የሚለውን ቃለ ጽርፈት በውስጠ ወይራ ንግግር ሊጠቀምበት ሞክሯል። መናፍቅ ማለት ከፍሎ አማኝ ማለት ስለ ሆነ፥ ከፍሎ ጠቃሽ ለማለት የቃጠውም “መናፍቅ” ለማለት ፈልጎ ይመስለኛል። እነርሱ መናፍቅ ካላሉ ስብከታቸውም ሆነ ትምህርታቸው የሚጣፍጥላቸው አይመስላቸውም፤ ስለዚህ ቃሉን የስብከታቸው ቅመም አድርገው ይጠቀሙበታል።

“አንድ መታወቅ ያለበት መሠረታዊ ጕዳይ አለ። የክርስትና ትምህርት ምንጩና መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ማኅበረ ቀናዕያን መወለዱ ቀርቶ በእንጀራ አባት ደረጃ እንኳ ሳይዛመዷቸው አባቶቻችን እያሉ የሚጠሯቸው የጥንታውያን አበው ትምህርት ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አበው እኮ ዐዲስ መገለጥ አላመጡም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን እውነት ነው ለማብራራት የሞከሩት። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ትምህርቶቻቸው የሚቀርቡት ለእኛ እንጂ አዋልድን መመሪያቸው ላደረጉት ለማኅበረ ቀናዕያን አይደለም።

“የማኅበረ ቀናዕያን አባላት ከአበው ትምህርቶች ሲጠቅሱ ብዙ ጊዜ አበው በግልጽ ቃላት ያስቀመጡትን እውነት፥ እነርሱ በአተረጓጐም ስልታቸው አደብዝዘውና አጠይመው ለትምህርታቸው በሚስማማ መንገድ ነው የሚያቀርቡት። በተጨማሪም አበው ወይም በአበው ስም ሌሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ የደረሷቸውንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጣሉትን ድርሰቶች እንደ ትክክለኛ ትምህርት ይጠቅሷቸዋል። እኛ እነርሱን ባለመጥቀሳችንም ከፍሎ ጠቃሾች ይሉናል። በመሠረቱ እኛ አበውን የምንጠቅሰው የምናስተምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በእነርሱም ዘንድ የታወቀና ተቀባይነትን ያገኘ ጥንታዊ ትምህርት መሆኑን ለማሳየት እንጂ፥ የእነርሱ ማብራሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስለሚበልጥ አለመሆኑ መታወቅ አለበት።” አንዳንድ የማኅበረ ቀናዕያን አባላት ዐልፎ ዐልፎ ከሚያሰሙት ሹክሹክታ በቀር ታዳሚው ሁሉ በትኵረት ማድመጡን እንደ ቀጠለ ነው። ብዙው አድማጭ ጆሮውን እንደ ሰጠው የተረዳው መምህር በቃሉ ወደ ሌላው ነጥብ ተሸጋገረ።

“ይገርማል!” አለ ሐዘኔታ በተሞላመበት ድምፀት። “ይገርማል! … ሌላው የቀረበብን ክስ መጽሐፍ ቅዱስን ዐውቃለሁ የሚል ሰው ሊያቀርበው የማይገባ ክስ ነው። ቅድም ዲያቆን በለው በድፍረት፥ ኢየሱስን ብቻ ይሰብካሉ ሲል ነው በፊታችሁ የከሰሰን። ኢየሱስ በመሰበኩ ሊበሳጭ የሚገባው ከጨለማው ግዛቱ ወደሚደነቀው ብርሃን ብዙዎች እየፈለሱበት ያለው ሰይጣን እንጂ፥ ኢየሱስ የሞተላቸው ሰዎች መሆን አይገባቸውም ነበር። ግን ምን ያደርጋል አለመታደል ሆኖ፥ የዚህ ዓለም አምላክ ዐሳባቸውን ያሳወረባቸው ሰዎችም፥ የኢየሱስ የአዳኝነት ዜና ሲነገር ጆሯቸውን ያሳክካቸዋል። እሺ! ወንጌል ምንድን ነው? በወንጌል ሊሰበክ የሚገባውስ ማነው?

“ወንጌል ሌላ ሳይሆን ስለ ኢየሱስ ክርቶስ የሚናገር የእርሱ የአዳኝነት ዜና ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ ወንጌል ከዳዊት ዘር በሥጋ ስለ ተወለደው፥ ከሙታን ተለይቶ ስለ ተነሣውና በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር የምሥራች ቃል ነው ይላል (ሮሜ 1፥1-4፤ 10፥16)። ስለ ሆነም በወንጌል የሚሰበከው የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ እንጂ ሌላ ፍጡር መልአክም ሆነ ሰው አይደለም።” ሲል ታዳሚው ቆመና የተሰበሰበበትን ስፍራ በማያቋርጥ እልልታና ጭብጨባ አናጋው። እልልታውና ጭብጨባው ጋብ እንዳለ፥ መምህር በቃሉ ምላሹን መስጠት ቀጠለ። “አሁንም ይኸው እውነተኛ ሐዋርያ ብፁዕ ጳውሎስ ራሳችንን ሳይሆን የተሰቀለውን የክርስቶስን ጌትነት እንሰብካለን በማለት ሊሰበክ የሚገባው እርሱ ብቻ መሆኑን አመልክቷል (1ቆሮ. 1፥22-23፤ 2ቆሮ. 4፥5)። በርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰብከው አዳኝ እርሱ ብቻ እኮ ነው!! ተሰቅሎ ያዳነንና ከአብ ጋር ያስታረቀን እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ሊሰበክ የሚገባውም የእርሱ አዳኝነት ብቻ ነው።

“መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የስብከታችን ማእከል የተሰቀለው ኢየሱስ ብቻ መሆኑ ለድርድር የሚቀርብ ጕዳይ አይደለም። ሆኖም በዚህ ውስጥ ስለ እመቤታችን፣ ስለ መላእክት፣ ስለ ጻድቃንና ስለ ሰማዕታት ማውሳታችን አይቀርም፤ ይህም አንዳንዶች እንደሚደርጉት የእነ በለውን ክስና ትችት ፈርተን፥ በአዋልድ መጻሕፍት ስብከት መሠረት ለቅዱሳን መላእክትና ሰዎች ያልተሰጣቸውን ክብርና ሥልጣን ሰጥተንና በአምላክ ስፍራ አስቀምጠን እነርሱን ለማምለክ አይደለም። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እነርሱ ከተጻፈው በመነሣት ለእግዚአብሔር ያሳዩትን ፍቅርና መታዘዝ፣ ስለ ስሙ የተቀበሉትን መከራ በማውሳት እኛም እንደ እነርሱ ባለ ሕይወት እንድንመላለስ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ በዚህም ውስጥ ቢሆን የስብከታችን ማእከል አይለወጥም፤ የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነው። ” ንግግሩን ሌላ ጭብጨባና እልልታ አቋረጠው።

“በመጨረሻ ላነሣ የምፈልገው” አለ፤ “በመጨረሻ ላነሣ የምፈልገው በዝማሬዎቻችን ላይ የቀረበውን ትችት ነው። ሁሉን ዐዋቂ ነኝ የሚለው የማኅበረ ቀናዕያን ተወካይ ዲያቆን በለው እዚህ ላይ ራሱን የያሬድ ዜማ ሊቅ፥ እኛን ደግሞ የዓለማዊ ዘፈን አቀንቃኝ አድርጎ አቅርቧል። መቼም በጉባኤ ትምህርት ሳይውሉ በቅልውጥና በድምጫ ዕውቀት ከዚህ በላይ መናገር አይቻልም። በለው ስለ ያሬድ ዜማ ቢያውቅ ኖሮ እንዲህ ባላለም ነበር፤ ቅዱስ ያሬድ ያዜመባቸው ሦስቱ የዜማ ስልቶች፡- ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ ለሁሉም ዜማዎች መሠረት መሆናቸውንና ከእነርሱ ውጪ የሆነ ዜማ እንደሌለ ድጓው ይመሰክራል፤ እንዲህ በማለት፥ ‘… ኢየዓዱ እንስሳ ወሰብእ እምነ ሠላስ ዜማሁ፤ - የሰውም ሆነ የእንስሳ ዜማ ከሦስቱ ያሬድ የዜማ ስልቶች ውጪ አይሆንም’ (ድጓ ገጽ 289፣ 2ኛ ዓምድ)። በዚህ ስንኝ መሠረት ከያሬድ ዜማ ውጪ የሆነ የዜማ ስልት የለም ማለት ነው። በርግጥ እንዲህ ብሎ ለመደምደም የመስኩን ሊቃውንት ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ በመሆኑ ጕዳዩን ለእነርሱ ልተውና፥ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት የተመረጠና የተለየ ዜማ አለ ወይ? የሚል አንድ ጥያቄ ላንሣ።

“መቼም ይህ ጥያቄ ለዲያቆን በለው ቢቀርብ፥ ያሬዳዊ ዜማ ብቻ ብሎ እንደሚመልስ ምንም ጥርጥር የለውም” ሲል ጉባኤው ሣቅ በሣቅ ሆነ። ሣቁ ተግ እንዳለ፥ “ርግጥ እኛ ኢትዮጵያውን የያሬድ ዜማ ስለ ተሰጠን በዚህ ዜማ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። ሆኖም የያሬድ ዜማ ቀለል ያለና ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያጠናው የሚችለው ባለመሆኑና በሊቃውንቱ ዘንድ ብቻ ተወስኖ በመኖሩ፥ ምእመናን የዜማው አድማጮች እንጂ ተሳታፊዎች አይደሉም። ይህን ክፍተት ለመሙላት በቀላሉ የሚጠኑና ማንኛውም ምእመን አምላኩን በዜማ እንዲያመሰግን የሚያደርጉ ዝማሬዎች በዐማርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች መውጣታቸው ሊመሰገን እንጂ ሊኰነን የሚገባው ተግባር አይደለም። የዝማሬዎቹ ግጥሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ያላቸውና ከቃሉ ጋር የማይቃረኑ፥ ለእግዚአብሔር ብቻም ክብርን የሚሰጡ መሆን ያለባቸው መሆኑ ከቶም ሊያከራክር አይገባም። ከዚህ በቀር የትኛው ዝማሬ ነው መልካም ዝማሬ? የሚለውን የሚወስነው ግን አድማጩ ሕዝብ እንጂ እኛ አይደለንም። ሕዝቡ የትኛው ዝማሬ መንፈሱን እንደሚያነቃቃውና እንደሚባርከው፥ እግዚአብሔርንም እንደሚያስመልከው፤ የትኛው ዝማሬ ደግሞ በመንፈሱ አንዳች ነገር ጠብ እንደማያደርግለት ለይቶ ያውቀዋል።

“እኔ አንድ ጥርጣሬ አለኝ” ሲል፥ የሁሉም ሰው ትኵረት ይበልጥ ወደ መምህር በቃሉ ተሳበ። “እኔ አንድ ጥርጣሬ አለኝ፤ ዲያቆን በለውና መሰሎቹ ዝማሬዎቻችንን ሲተቹ ለያሬዳዊ ዜማ ቀንተው አይመስለኝም። ምናልባት ሕዝበ ክርስቲያኑ የእነርሱን ማርያም ወረደች አሸዋ ላሸዋ ዐይነት ዝማሬዎች ቸል እያለ በመምጣቱና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ወዳላቸውና የአምልኮ ጥማቱን ወደሚያረኩለት ዝማሬዎች በማዘንበሉ፥ የእነርሱ ዝማሬዎች ከገበያ ውጪ መሆናቸው ስላሳሰባቸው ይሆናል። መቼም ገበያ ተኰር ‘አገልጋዮች’ ስለ ንግዳቸው እንጂ ስለ ሕዝቡ ደንታ የላቸውም። የገበያቸውን መቀዛቀዝ የሃይማኖት ችግር አስመስለው ማቅረባቸው፥ የብር ሠሪውን የድሜጥሮስን ነገር ነው የሚያስታውሰኝ።

“ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን በነበረው አገልግሎት ብዙዎች ንስሓ እየገቡ ወደ ወንጌል ስለ መጡና ከእነዚህም መካከል አያሌ አስማተኞችም ይገኙ ስለ ነበር፥ በአምልኮተ ጣዖት መንደር ሁከት በሆነ ጊዜ በጣዖት ንግድ የሚተዳደረው ድሜጥሮስ፥ የሕዝቡ ሕይወት አሳዝኖት ሳይሆን የገቢው መቀዝቀዝ አሳስቦት ሰዉን ሁሉ ለማሳደም ሞክሮ ነበር። ቅስቀሳውም፡- ‘ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ይህም ጳውሎስ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደለም ብሎ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንዳስረዳና እንዳሳተ አይታችኋል፤ ሰምታችሁማል። ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፤ እስያ ሁሉ፥ ዓለሙም ሁሉ የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቈጠር እንጂ፥ ታላቅነቷም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል’ (ሐ.ሥ. 19፥25-27) የሚል ነበር። በዚህ ንግግሩ ውስጥ ሌላው ሁሉ ሽፋን ሲሆን፥ እርሱ ማስተላለፍ የፈለገው ዋና ነገር ‘ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።’ የሚለው ነው። እነ በለው በዝማሬዎቻችን ላይ እየሠነዘሩ ያሉት ትችትስ ከዚህ ውጪ ነው ትላላችሁ? … ስላዳመጣችሁኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ” አለና መምህር በቃሉ ንግግሩን ደመደመ።
ይቀጥላል

3 comments:

  1. please come up with part 3

    ReplyDelete
  2. ጥንት ቤተክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረ አሰራር እንደዚህ ነበር ችግርን ለመፍታት ደስ የሚል ነው።ክፍል 3 እንፈልጋለን አባቶች ያለ መፍትሔ አልተውም

    ReplyDelete
  3. ጥንት ቤተክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረ አሰራር እንደዚህ ደስ በሚል ነበር ። ክፍል 3 የታል አባቶች ያለ መፍትሄ አልተውንም መፍትሄ እንፈልጋለን ይህን አይነት ችግር በየቤተክርስቲያናችን ያለ ነው

    ReplyDelete