Monday, February 16, 2015

ርእሰ አንቀጽ

ያንን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ትጠፋለች

በዘመናት ውስጥ ራሱን ያለ ምስክር ያልተወ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በቀድሞ ዘመን በተለያየ የመገለጽ ስልት በተለያየም ጐዳና ተናገረ ይላል የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ፡፡ በየዘመኑ በምሳሌ፥ በሕግ፥ በክህነት፥ በመሥዋዕት፥ በመቅደስ፥ በትንቢት፥ በተስፋ ቃል ተናግሮ ነበር፡፡ በአባቶች፥ በመሳፍንት፥ በነገሥታት፥ በካህናት፥ በነቢያት በኩል ተናግሮ ነበር፡፡ ተናግሮት የነበረውም ሁሉ ሊፈጸም ከነበረው ዕቅዱ አንዲት የውጣ እንደማትወድቅ የሚያመለክት ጥላ ነበር፡፡ ከጥላው በስተኋላ ሊገለጥ ያለው አካል ባይኖር ኖሮ ለጥላው መገለጥ ስፍራ ባልተገኘ ነበር፡፡ ስለዚህ ጥላውን ያስገኘ የአካሉ መኖር ነበር ማለት ነው፡፡

ከበስተኋላ እየመጣና እየቀረበ ላለው የአካል መገለጥ ግምት ያልሰጠ ሞኝ ወይም እብሪተኛ ሰው ይኖርን? ጥላውን እንደ አካል ቈጥሮና በጥላ ፍጹምነት አለ ብሎ የረካ ሰውስ ይገኛልን? ሆኖም ጥላው ከበስተኋላ አካል እንዳለው በመረዳት አካሉን የጠበቁ ሁሉ ብፁዓን የሚያሰኛቸውን ርካታ እንደሚያገኙ አይጠረጠርም፡፡ 
ሰዎች ጠበቁም አልጠበቁም እግዚአብሔር በወደደው ሰዓትና በወሰነው ጊዜ በአሮጌው የኪዳን ዘመን ውስጥ ጥላውን ያሳየ አካል እንዲገለጽ አደረገና ዐዲስ ኪዳን ተተካ፡፡ ምእመናንም ጥላ በሆነ ሥርዐት የሚያመልኩበት ሁኔታ አበቃ፡፡ በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዐዲስ ቃል ኪዳን (ውል) የተፈረመበት ዐዲስ ዘመን ገባ፡፡

ያን አሮጌ ኪዳን ከእግዚአብሔር ተቀብሎና ከሕዝቡ ጋር አስተዋውቆ የነበረው ሙሴም፥ “እንደኔ ያለ ነቢይ ከመካከላችሁ እግዚአብሔር ያስነሣልና እርሱን ስሙት፤ እርሱን የማትሰማ ነፍስ ትጠፋለችና” በማለት በቅድሚያ ያሰማው ተስፋና ማስጠንቀቂያ ያለበት ዐዋጅ ከተፈጸመ ዓመታት ተቈጠሩ፡፡ ታዲያ ነቢዩን ለማትሰማ ነፍስ ከመጥፋት በቀር የተጠበቀላት ሌላ ዕድል እንዳልተዘጋጀ ግልጽ ነው፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በኤርምያስ አንደበት በቅድሚያ ውራጅ ያደረገው ኪዳን የሚገዛበት ዘመን ሲጠናቀቅ (ዕብ. 8፥8-13) እግዚአብሔር በልጁ በኩል በመጨረሻው ዘመን ከተናገረ በኋላ ሌላ ሦስተኛ ኪዳን የሚያቆምበት ክፍተት ከቶ አልተወም፡፡ በልጁ በኩል በመጨረሻ ጊዜ ያቆመው ዐዲስ ኪዳን ከፍጹምነት በላይ የሆነ ፍጹምነትን የተሞላ ሙሉ አካል የሆነ የመጨረሻው ኪዳን ነውና፡፡
 
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ስለ መጨረሻው ኪዳን በምሳሌ ያስተማረውን ሦስቱም ወንጌላውያን ጽፈውታል፡፡ ቅጥር የቀጠረለትን፥ መጥመቂያ የማሰለትንና ግንብ የገነባለትን የወይን አትክልት ቦታውን ለገበሬዎቹ ያኰናተረ ከበርቴ የመከር ወራት ሲደርስ ከሰብሉ ድርሻውን እንዲልኩለት ባሮቹን በመደጋገም ወደ ገበሬዎቹ ላከ፡፡ በተለያየ ጊዜ ተልከው የሄዱትን ባሮች ገበሬዎቹ አልታዘዙአቸውም፡፡ ከባሮቹ የተደበደቡ፥ የተወገሩ፥ የተገደሉ ነበሩ፡፡ ከበርቴው በመጨረሻ (ከሁሉ በኋላ) የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ገበሬዎቹ ላከ፡፡ እርሱንም ገደሉት፡፡ ከበርቴውም ከልጁ በኋላ ሌላ የሚልከው አልነበረውምና፥ ልጁን ባልተቀበሉት ላይ ቅጣት ሊወስን ተዘጋጀ፡፡

ምሳሌውን በጥሞና ያደመጡ ፈሪሳውያን እንኳ፥ ምንም ምሳሌው ስለ እነርሱ እንደ ተነገረ ቢያውቁም፥ ከበርቴው ገበሬዎቹን ምን ማድረግ እንዳለበት አስተያየታቸውን ጌታ ሲጠይቃቸው፥ ለገበሬዎቹ ሌላ አንድ ዕድል ሊሞክርላቸው ይገባል አላሉም፡፡ የሚወደውን አንድዬ ልጁን ከብዙ ባሮቹ በኋላ ልኳልና ሌላ የሚልከው እንዳልነበረው ፈሪሳውያን ከምሳሌው ተረድተዉታል፡፡ ስለዚህ ልጁን ተቀብለው እንደሚገባቸው ያላስተናገዱትን ገበሬዎች ከበርቴው ሊያጠፋቸው ይገባል በማለት አስተያየት ሰጡ (ማቴ 21፥33-46፤ ማር. 12፥1-12፤ ሉቃ. 20፥9-19)፡፡

በእግዚአብሔርም ዘንድ ውሳኔው ይኸው ነው፡፡ ልጁን የተቀበሉትና በስሙ ያመኑት አይፈረድባቸውም፡፡ ያልተቀበሉትና ያላመኑት ግን ካሁን ጀምሮ ተኰንነዋል (ዮሐ. 3፥18)፡፡ ሌላ ሦስተኛ ዕድል አልተዘጋጀም፡፡ ሦስተኛ ቃል ኪዳንም የለም፡፡ ሰው ሁሉ እንደመሰለውና እንደሚመኘው ብዙ ቃል ኪዳን በፈጠራ ቢጽፍም፤ እግዚአብሔር በኪዳኑ ላይ ካልፈረመበት ምን ሊፈይድ ይችላል? ቃል ኪዳን ማለት እኮ በኹለት ተዋዋዮች መካከል የሚፈረም ስምምነት ነው!! (ኤር. 31፥31)፡፡

ያንን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ሁሉ ትጠፋለች እንጂ ሌላ ዕድል የላትም፤ - የላትም፥ - የላትም (ዘዳ. 18፥15-19፤ ሐ.ሥ. 3፥22፡23)፡፡ ሌላ ዕድል የላትምና፤ ከሁሉ በኋላ እግዚአብሔር የሚወደውን አንድዬ ልጁን ልኮታልና፤ እርሱን ትስማ (ማቴ. 17፥5)፡፡

በጮራ ቍጥር 9 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment