Monday, June 8, 2015

መሠረተ እምነት

ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ
ክርስቶስ እርሱን ወክለው የሚያገለግሉ ካህናትን ሾሟልን?
ከነቅዐ ጥበብ
ባለፈው ዕትም በዚሁ ዐምድ ላይ በወጣው ጽሑፍ ውስጥ ከተነሡት ነጥቦች መካከል አንዱ፥ “ክርስቶስን የሚተካ ሌላ መካከለኛ አለን?” የሚል ነበር (ገጽ 6)። መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገንና የአበውን ምስክርነት ጠቅሰን ክርስቶስን የሚተካ ሌላ መካከለኛ እንደሌለ ለማሳየት ሞክረናል። ቀደም ብለንም የክርስቶስን መካከለኛነት በሌሎች መካከለኞች የተኩ ወገኖች፥ መካከለኞቻቸው ያደረጓቸው ያንቀላፉ ቅዱሳንንና ቅዱሳን መላእክትን መሆኑን ተመልክተናል። የክርስቶስን መካከለኛነት ባንቀላፉ ቅዱሳን ብቻ ሳይሆን በሕይወት ባሉ “ካህናትየተኩበትም ሁኔታ አለ። ይኸውም የክርስቶስ ክህነት በውክልና ለሐዋርያት እንደ ተሰጠና “ሐዋርያትም የእርሱን መሥዋዕት በማቅረብ የእርሱን የክህነት ሥልጣን ወክሎ በመሥራት የማዳን ጸጋውን ለብዙዎች እንዳዳረሱ፥ “ይህንን ሥራ በመቀጠል ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ከመስበክ ጋር ሲወርድ ሲዋረድ በመጣላት የክርስቶስ የክህነት ሥልጣን መሠረት የምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ጸጋ በክርስቶስ ስም ላመኑት ሁሉ ለማዳረስ ትጥራለች።” በማለት ይህንና ይህን የመሰለ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ውጪ የሆነ ትምህርት ያስተላልፋሉ (ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር፣ ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፣ 1996፣ 233)።

ይኸው መጽሐፍ “ሥልጣነ ክህነት ለተመረጡት ብቻ ይሰጣል” በሚል ንኡስ ርእስ ሥር ያሰፈረው ሐተታ እንዲህ ብሏል። እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ፥ “በዐዲስ ኪዳንም ሥልጣነ ክህነት ለተመረጡት ብቻ እንጂ ለአማኞች ሁሉ እንደማይሰጥና ለተመረጡት ብቻ እንጂ አማኞች ለሆኑት ሁሉ ለወንዶችም ለሴቶችም አይሰጥም። እንዲያማ ካልሆነ ክርስቶስ ከብዙዎች መካከል ለምን ዐሥራ ሁለቱን ከዚያም ሰባውን ደቀ መዛሙርት ብቻ መረጠ? ሐዋርያው ጳውሎስም የክህነት ሹመት ከመሰጠቱ በፊት በጥንቃቄ እንዲሆን በማሰብ መልካም ጠባያቸውንና አኗኗራቸውን በማስመልከት መመረጥና መሾም ስለሚገባቸው ካህናት መመሪያ አዘጋጅቷል (1ኛ ጢሞ. 3፥1-13፤ ቲቶ 1፥6-9)። በዚህም ምክንያት ፈጥኖ እጆቹን በመጫን ካህናትን እንዳይሾም ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል (1ኛ ጢሞ. 5፥22)” (ገጽ 260፡261)። በዚህ ዕትም በጒዳዩ ላይ አተኲረን የክርስቶስን ብቸኛ መካከለኛነት እናስረዳለን።

በቅድሚያ “ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር፣” የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ብዙ የወንጌል እውነት የተገለጠበት መጽሐፍ በመሆኑ፣ ለአዘጋጁ ያለንን አድናቆት መግለጽ እንወዳለን። የኖረውን ትውፊት በትውፊትነቱ ብቻ ከማቅረብ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አስደግፈው ለማቅረብ በሚያደርጉት ጥረት ግን፥ በሌላ አቅጣጫ የገለጹትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የሚያፈርሱት ሆኖ ይታያል። ለዚህም ከላይ የተጠቀሰው አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

በብሉይ ኪዳን ክህነት ለማን ተሰጠ?
እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣውን አጠቃላዩን ሕዝበ እስራኤል፥ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” ሲል ተናግሯቸው ነበር (ዘፀ. 19፥5-6)። በኋላም አሮንንና ልጆቹን ካህናት ሆነው በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ያገለግሉት ዘንድ ለያቸው (ዘፀ. 28፥1፤ ዘሌ. 8-9)። ሕዝቡ የካህናት መንግሥት ቢሆኑም፥ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግሉ የተመረጡት ግን አሮንና ልጆቹ ነበሩ።

ለአሮን የተሰጠው ክህነት የጥላው አገልግሎት ክህነት ነበረ። ያገለግል የነበረውም ብዙ ጒድለቶች የነበሩበትን የጥላውን አገልግሎት ነበረ። ከጕድለቶቹም ዋና ዋናዎቹ፥
~        ለኀጢአተኛው ሰው ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት የእንስሳ መሥዋዕት ስለ ነበረ (ለሰው ምትክ ሆኖ ይቀርብ የነበረው እንስሳ መሆኑ) በዕሴት የማይመጥን ነበር (ዕብ. 10፥1-4)።
~        መሥዋዕቱ ይቀርብ የነበረው በምድራዊቱና የሰው እጅ በሠራት መቅደስ ውስጥ ነበረ (ዕብ. 8፥3-5፤ 9፥1-5)።
~        መሥዋዕት አቅራቢው ካህን ስለ ራሱ ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የሚጠበቅበት ኀጢአተኛ ነበረ (ዕብ. 5፥1-3፤ 9፥6-7)።
እነዚህ ጒድለቶች የነበሩበት የብሉይ ኪዳኑ የክህነት አገልግሎት ወደ ፊት በሚገለጠውና ምንም እንከንና ጒድለት በሌለው በሐዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት እንደሚተካ ግልጽ ነበር። እነዚህ ጒድለት የነበረባቸው መሥዋዕቱ፥ ቤተ መቅደሱና ሊቀ ካህናቱ፥ ለሚመጣው አካልና አማናዊ ነገር ጥላዎችና ምሳሌዎች ነበሩ። በሐዲስ ኪዳን ግን የእንስሳቱ መሥዋዕት በክርስቶስ መሥዋዕትነት፥ ምድራዊቱ ቤተ መቅደስ በሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ፥ የአሮን ክህነት በክርስቶስ ክህነት ተተክተዋል።

በሐዲስ ኪዳን ክህነት ለማን ተሰጠ?
ሐዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ እንደ መሆኑ፥ በብሉይ ኪዳን ጥላና ምሳሌ የሆኑ ነገሮች ሁሉ አማናዊነትንና ፍጻሜን ያገኙበት ኪዳን ነው። እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ተብሎ ትንቢት የተነገረለት ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከአሮን በሚበልጥና እንደ መልከ ጼዴቅ በሆነ ክህነት ሊቀ ካህናት በመሆኑ፥ ለኦሪቱ ክህነት ፍጻሜን ሰጥቷል። የኦሪት ሥርዐተ ክህነት ላይመለስ በክርስቶስ ተተክቷል ማለት ነው። ስለ ሆነም፥
~        የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህነት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ አንድን መሥዋዕት፥ ራሱን ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል። መሥዋዕቱ ፍጹም፥ ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃና ኀጢአትን ሁሉ ሊያስወግድ የሚችል ስለ ሆነ መደጋገም አላስፈለገውም (ዕብ. 10፥12፤ 1ዮሐ. 2፥2)።
~        የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ያገለገለው በሰው እጅ በተሠራው መቅደስ ውስጥ ሳይሆን በሰማይ ባለችውና የሰው እጅ ባልሠራት እግዚአብሔር በተከላት መቅደስ ውስጥ ነው (ዕብ. 8፥2፤ 9፥24)።
~        የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ስለ ሆነ እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ክህነቱ በሞት አይሻርምና የሚተካው ወይም እርሱን ወክሎ የሚሠራ ሌላ ሊቀ ካህናት የለም (ዕብ. 7፥24-25)።

በክርስቶስ የሊቀ ካህናትነት አገልግሎት እግዚአብሔርና ሰው በፍጹምነት ስለ ታረቁ፥ አሁን ያለው አገልግሎት ኀጢአተኞች ሁሉ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ባቀረበላቸው አንድና ፍጹም መሥዋዕት አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃቸውን ማወጅና የምሥራቹን ቃል ያልሰሙና ያላስተዋሉ ይህን ዐውቀው፥ አምነውና ተቀብለው ኀጢአታቸውን ለሊቀ ካህናታቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ እየተናዘዙ ስርየትን እንዲቀበሉ ማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው ሐዋርያትና ከእነርሱም በኋላ በየዘመናቱ የተነሡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናንም በአጠቃላይ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ባኖረው የማስታረቅ ቃል አማካይነት ለሰው ልጆች ሁሉ ይህን የምሥራች እየተናገሩ፥ ኀጢአተኞችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ጥሪ ያቀርባሉ (2ቆሮ. 5፥18-20፤ 1ጴጥ. 2፥9)። አሁን ያለው አገልግሎት ይኸው ብቻ ነው። ከዚህ በቀር በክርስቶስ ያልተጠናቀቀ፥ ወይም የጐደለና የቀረ ነገር ኖሮ ኀጢአትን የሚያስተሰርዩ ሌሎች ካህናት አላስፈለጉም፤ አልተሾሙምም። በሰማያዊቱ መቅደስ ውስጥ የቀረበ ፍጹምና ታላቅ መሥዋዕት እያለም፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ምድራዊ ቤተ መቅደስም ሆነ በዚያ የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት የለም። እነዚህ ነገሮች በሐዲስ ኪዳን እንዳሉ ማሰብና ሰዎች በሠሯቸው ሌሎች ምድራውያን ሥርዐቶች መዳን እንደሚገኝ መስበክ፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ለመዳናችን የሠራውን ፍጹምና ታላቅ ሥራ መናቅና ማቃለል ነው የሚሆነው።

ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን ብቸኛ ሊቀ ካህናት ነው። እርሱ የአሮንን ክህነት አስቀርቷል። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን የሚተካም ሆነ የሚወክል ሌላ ሥጋ ለባሽ ካህን አላስፈለገንምና አልተሾመልንም። ለምን ቢባል፥ እርሱ ጌታችን ስለ ኀጢአታችን ሞቶ የነበረ ቢሆንም ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል፤ ሕያውም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በንጽጽር ሲያብራራ “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” ይላል (ዕብ. 7፥23-25)። ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ላይ ሌሎች ካህናት አሉ ብሎ ማሰብና ማመን፥ የቀደመውን ወደሚመስል “ክህነት” ለመመለስ መሞከር ይሆናል።

ሐዲስ ኪዳን ከአማኞች የተለዩ ካህናት እንዳሉ ይናገራልን?
“በሐዲስ ኪዳን ከአማኞች የተለዩ ካህናት አሉን?” የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። ምክንያቱም የ“ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር” ጸሓፊና ሌሎችም፥ ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን የክህነት አገልግሎት ወክለውና ተክተው የሚሠሩና ከምእመናን የተለየ ክህነት ያላቸው ካህናት አሉ የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህን ትምህርታቸውን የሚደግፍ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይኖርም፥ ስለ ሌሎች ጒዳዮች የተነገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ሐሳባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ለማሳየት ይሞክራሉ። ለምሳሌ፥ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በመጽሐፋቸው ያሰፈሩትንና ከላይ የጠቀስነውን እዚህ ላይ ብንመለከተው ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። “በዐዲስ ኪዳንም ሥልጣነ ክህነት ለተመረጡት ብቻ እንጂ ለአማኞች ሁሉ ለሁሉ እንደማይሰጥና ለተመረጡት ብቻ እንጂ አማኞች ለሆኑት ሁሉ ለወንዶችም ለሴቶችም አይሰጥም። እንዲያማ ካልሆነ ክርስቶስ ከብዙዎች መካከል ለምን ዐሥራ ሁለቱን ከዚያም ሰባውን ደቀ መዛሙርት ብቻ መረጠ? ሐዋርያው ጳውሎስም የክህነት ሹመት ከመሰጠቱ በፊት በጥንቃቄ እንዲሆን በማሰብ መልካም ጠባያቸውንና አኗኗራቸውን በማስመልከት መመረጥና መሾም ስለሚገባቸው ካህናት መመሪያ አዘጋጅቷል (1ኛ ጢሞ. 3፥1-13፤ ቲቶ 1፥6-9)። በዚህም ምክንያት ፈጥኖ እጆቹን በመጫን ካህናትን እንዳይሾም ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል (1ኛ ጢሞ. 5፥22)።” (ገጽ 260፡261)።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እና ለቲቶ በጻፋቸው መልእክቶች ውስጥ ያሰፈረውን ሐሳብ ከመልእክቶቹ ጥቂቱን በመጥቀስ እንመልከት። ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት ውስጥ፥ “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?” ብሏል (1ጢሞ. 3፥1-5)።

ለቲቶ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፤ “ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኰራ፥ የማይቈጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር፥ ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅሥ ይችል ዘንድ፥ እንደ ተማረው በታመነ ቃል ይጽና።”  (ቲቶ 1፥5-9)።

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ካህናት፥ ስለ ክህነት አገልግሎት አይናገሩም። ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች፥ ቤተ ክርስቲያንን ስለ መመገብና ስለ ማስተዳደር ይናገራሉ ነው የሚናገሩት። ይኸውም ኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት ለአገልግሎት ስለሚሾሙበት መስፈርትና ቤተ ክርስቲያንን ስለ መመገባቸውና ስለ ማገልገላቸው እንጂ፥ እነርሱ ክርስቶስን በመወከል ካህናት ሆነው መሥዋዕት በማቅረብ በክህነት ስለሚያገለግሉት የክህነት አገልግሎት አይደለም። በክፍሎቹም ውስጥ ኤጲስ ቆጶሳት፥ ሽማግሌዎች (ቀሳውስት)፥ ዲያቆናት፥ የተባሉ መሪዎችና አገልጋዮች፤ ቤተ ክርስቲያንን ማደራጀት፥ ማስተዳደር፥ መመገብ የሚሉ አገልግሎቶች እንጂ፥ ክህነት፥ ካህናት፥ መሥዋዕት የሚል አንድም ቃል ወይም ሐሳብ የለም። ክፍሎቹ የሚናገሩት ቤተ ክርስቲያንን ስለ መመገብና ስለ መምራት እንጂ፥ በክህነት ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስን ወክሎ መሥዋዕት ስለ ማቅረብ አይደለም የተባለው ለዚህ ነው።

የ“ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር” ጸሓፊ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ሹመት እንደ ክህነት በመቊጠር፥ “በሐዲስ ኪዳንም ሥልጣነ ክህነት ለተመረጡት ብቻ እንጂ አማኞች ለሆኑት ሁሉ ለወንዶችም ለሴቶችም አይሰጥም” (ገጽ 261) በማለት ዛሬም እንደ ኦሪቱ ዐይነት ያሉ ካህናት እንዳሉ አስመስለው ጽፈዋል። የኦሪት ሊቃነ ካህናትን ዛሬ “ካህናት” እየተባሉ ከሚጠሩ ቀሳውስት ጋር ማነጻጸር ከተጀመረ፥ ቤተ መቅደሱና መሥዋዕቱም ወደ ንጽጽር መግባታቸው አይቀርም። ይህ ንጽጽሮሽና በሐዲስ ኪዳን ሥልጣነ ክህነት በተወሰኑ ሰዎች እጅ ነው የሚገኘው የሚለው ሐሳብ፥ በትውፊት ሲሠራበት የቈየውን አሠራር ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠጋት ታስቦ የተደረገ እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ግን ይታወቃል። ምክንያቱም፥
·        ክህነትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነጻጸሩት አሮን እና ኢየሱስ ናቸው እንጂ አሮንና ተከታዮቹ የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናትና ሐዋርያት አይደሉም (ዕብ. 5፥1-10፤ 7፥1-28)።
·        የብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስና ጌታ ያገለገለባት ሰማያዊት ቅድስተ ቅዱሳን እንጂ፥ የኦሪቱ መቅደስ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር አልተነጻጸሩም (ዕብ. 8፥1-2፤ 9፥1-8፡11-12፡24)።
·        የብሉይ ኪዳን የእንስሳት መሥዋዕቶች ጌታ በሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ጋር ካቀረበው ክቡር ደሙ ጋር እንጂ በኅብስትና በወይን ከተሰጠው ከጌታ ሥጋና ደም ጋር አልተነጻጸሩም (ዕብ. 9፥9-13፡25-26፤ 10፥1-14)።

ታዲያ የኦሪት ካህናትን ከሐዋርያትና በእነርሱ እግር ከተተኩት የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች፥ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ጋር በክህነት አገልግሎት ማመሳሰል ከምን የመጣ ነው? ቢባል፥ ነገሩ ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውና በትውፊት ሲሠራበት የኖረውንና ቀሳውስትን የተለዩ ካህናት ብሎ የመቊጠርን ልማድ የተከተለ ነው ከማለት በቀር ሌላ ምላሽ የሚገኝለት አይመስልም። ኀጢአተኛውን ሰው ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን በራሱ ስለ ፈጸመና የቀረ አንዳች ነገር ስለሌለ፥ የክህነት አገልግሎቱን በውክልና ለሌሎች አልሰጠም። እርሱም እንኳ ከዚህ በኋላ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ እንደሌለበት ተጽፏል (ዕብ. 7፥27፤ 9፥26፤ 10፥12፡14፡18፡26)፤ ስለዚህ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት በእርሱ በኩል አምነው የሚመጡትን ያድናቸዋል (ዕብ. 5፥9-10)።

የሐዲስ ኪዳን ካህናት የሚያቀርቡት መሥዋዕት ምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ነው። እርሱ የጠራቸውና የመረጣቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና መጋቢዎች ምእመናንም ሁሉ ደግሞ ካህናት ይባላሉ (1ጴጥ. 2፥9፤ ራእ. 1፥6)። ስለ ኀጢአት የቀረበውን አንድና ፍጹም መሥዋዕት አንድ ጊዜ ያቀረበው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ፥ ይህን መሥዋዕት እርሱም ደግሞ አያቀርብም፤ ሌሎች እንዲያቀርቡም ውክልና አልሰጠም። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በመሠዋት አንድ ጊዜ ካቀረበው ፍጹም መሥዋዕት ሌላም፥ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አለ ብሎ የሚያምንና የሚያስተምር ቢኖር የክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት አልጠቀመም፤ መሥዋዕቱም በቂ አይደለም ማለቱ ነው።      

የ“ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር” ጸሓፊ የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ሹመት እንደ ክህነት በመቊጠር፥ ዛሬ እየሰጡ ያለውን መቅደሳዊ አገልግሎትም ከኦሪቱ የደብተራ ኦሪት የክህነት አገልግሎት ጋር በማመሳሰል፥ “ካህናተ ኦሪት የእንስሳት መሥዋዕትን ያቀርቡ ነበር። ካህናተ ወንጌል ግን እጅግ የላቀውንና የተቀደሰውን የጌታን ሥጋና ደም መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሆነዋል” (ገጽ 259) ሲሉ ጽፈዋል። ይህን ንጽጽር ላይ ላዩን ለተመለከተው የሚያስኬድ ይመስላል። ከላይ እንደ አየነው በማደሪያው ድንኳን መሥዋዕተ ኦሪትን ይሠዉ የነበሩት ሊቃነ ካህናት የሚነጻጸሩት ከክርስቶስ ጋር እንጂ ከሐዋርያት ጋር ባለመሆኑ ትምህርቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ይታወቃል።

የሐዲስ ኪዳን ካህናት የተባሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ መጋቢዎችና ምእመናን በአጠቃላይ ይነጻጸሩ ከተባለም፥ ሊነጻጸሩ የሚችሉት በኦሪት፥ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” (ዘፀ. 19፥5-6) ከተባሉት ሕዝበ እስራኤል ጋር ነው። ምክንያቱም በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ለክርስቲያኖች (አገልጋዮችና ምእመናን) ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቃል ተነግሮላቸዋል፤ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤” (1ጴጥ. 2፥9)። እዚህ ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ራሱን “የንጉሥ ካህናት” ካላቸው ምእመናነ ወንጌል መካከል አላካተተምና ጥቅሱ “የተለየ ክህነት አላቸው” ብለው የተናገሩላቸውን ሐዋርያትን አይጨምርም የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ሐዋርያው ዮሐንስ በራእዩ፥ “ለወደደን ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኀይል ይሁን፤ አሜን።” በማለት፥ እርሱን ጨምሮ በክርስቶስ ደም ከኀጢአታቸው የታጠቡ ሁሉ ካህናት መሆናቸውን ጽፏል (1፥5-6)።

ስለ ሐዲስ ኪዳን ካህናት፥ “እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።” ተብሎ ተጽፏል (1ጴጥ. 2፥5)። ከዚህም ካህናተ ወንጌል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት እንዳለ እንረዳለን። መሥዋዕቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ እንደ የ“ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ምግባር” ጸሓፊ አመለካከትም ሥጋ ወደሙም  ሳይሆን፥ “መንፈሳዊ መሥዋዕት” ተብሏል።

መንፈሳዊ የተባለው መሥዋዕት ልዩ ልዩ ነው። እነዚህ መሥዋዕቶች ከኦሪቱ የእንስሳት መሥዋዕት የተለዩና ከእነርሱ ጋር ሲነጻጸሩ በእጅጉ በእግዚአብሔር የተወደዱ መሆናቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቀረበው ንጽጽር መረዳት እንችላለን፤
~       ሚቃጠልና ከሚታረድ መሥዋዕት ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት (1ሳሙ. 15፥22)
~       ከሚቃጠለው መሥዋዕት ይልቅ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ (መዝ. 51፥16-17)
~       ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ (ምሳ. 21፥3)፥
~       ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ (ሆሴ. 6፥6)፥
~       መሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ማቴ. 9፥13)፥
እግዚአብሔር እንደሚወድና መንፈሳዊው መሥዋዕት ከሚቃጠል መሥዋዕት እንደሚበልጥ በተደጋጋሚ ተናግሯል። መንፈሳዊ መሥዋዕት የተባሉትም የሚከተሉት ናቸው።
~        ሁለንተናን ሕያው መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብ (ሮሜ 12፥1-2፤ ኤፌ. 5፥2)።
~        ወንጌልን ላልሰሙትና ላላመኑት መመስከርና በክርስቶስ እንዲያምኑ፥ እንዲድኑና ለክርስቶስም ሕያዋን መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ እንደካህን ማገልገል (ሮሜ 15፥15-16፤ 1ጴጥ. 2፥9-10)
~        የምስጋናን መሥዋዕት ማቅረብ (መዝ. 50፥14፡23፤ 54፥6፤ 107፥21-22፤ ዕብ. 13፥15)።
~        መልካም ማድረግና ካለው ነገር ላይ ለሌሎች ማካፈል (ምሳ. 21፥3፤ ፊል. 4፥18፤ ዕብ. 13፥15)።
~        ቃሉን የማድመጥና የመታዘዝ መሥዋዕት (1ሳሙ. 15፥22) (ጮራ ቊጥር 23 ገጽ 47ን ይመልከቱ)

በሐዲስ ኪዳን ካህናት የሚቀርቡት መንፈሳውያን መሥዋዕቶች ከላይ የተዘረዘሩት ናቸው። ከእነዚህና ከመሳሰሉት በቀር ስለ ስርየተ ኀጢአት የሚቀርቡ ሌሎች መሥዋዕቶች የሉም። ሥጋ ወደሙ በትውፊታዊው አስተምህሮ “መሥዋዕት” ተብሎ ቢጠራም፥ ስያሜው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፤ መሥዋዕት ነው መባሉም አመክንዮኣዊ አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርብ ሊሰቀል ኀሙስ ማታ፥ በኅብስትና በወይን ሥጋውንና ደሙን እንዲቀበሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷል፤ እንዲህ በማለት፥ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋውንም አንሥቶ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ “ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የዐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴ 26፥26-28)። ከዚሁ ጋር አያይዞ፥ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል (ሉቃ. 22፥19፤ 1ቆሮ. 11፥24)። ከዚህ ውጪ ሥጋ ወደሙን (ኅብስትና ወይኑን) መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አላቀረበውም። ለእግዚአብሔር ያቀረበው ራሱን ነው (ኤፌ. 5፥2፤ ዕብ. 7፥27፤ 9፥12፡28)። እኛን ለማዳን አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ለማሰብና መታሰቢያውን ለማድረግ፥ ቤተ ክርስቲያን ምስጢረ ቊርባንን በመፈጸም የክርስቶስን መታሰቢያ ስታደርግ ኖራለች፤ ጌታ እስኪመጣ ድረስም መታሰቢያውን ታደርጋለች (ሐ.ሥ. 2፥46፤ 1ቆሮ. 10፥16-17፤ 11፥20-34)። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ይህን ምስጢር በማዘጋጀታቸውና ለምእመናን በማቅረባቸው ከኦሪት የበለጠ መሥዋዕት አቀረቡ አያሰኛቸውም።
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 44 የቀረበ

No comments:

Post a Comment