Sunday, August 16, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን - ክፍል አንድ

መንደርደሪያ
ታላቁ ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ” በተባለውና መሠረታውያን የኾኑ የክርስትና ትምህርቶችን በእግዚአብሔር ቃል መሠረትና የጥንት አበውን ምስክርነት በመጥቀስ ባዘጋጁት መጽሐፋቸው መቅድም ላይ፥ መጽሐፉ የተጻፈበትን ምክንያት ካተቱ በኋላ እንዲህ ብለው ነበር፤
… ይህን ሁሉ ማተታችን መምህራኑ የማያውቁት ኾነው እነርሱን ለማስተማር አይደለም። ነገር ግን የዚህን ሐሳብና ምስጢር ቃለ መጻሕፍትን መመገብ የሚያዘወትሩ ሊቃውንት እያወቁት ሳለ፥ ብዛት ያላቸው መሃይምናን አያውቁትም። አያውቁምና መምህራን ለማነጽ ጠቃሚ መኾኑን ተረድተው የሚደግፉትን፥ ‘ለሕዝበ ክርስቲያንም ይረባል’ ሲሉ የሚያቅዱትን ጥልቅ አስተያየት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያልጸና የመሃይምናኑ አእምሮ እንደማይደርስበት የታወቀ ቢኾንም (፩ቆሮ. ፪፥፲፩)፥መሃይምናኑ ራሳቸው ስለ ሃይማኖት ያላቸው ዕውቀት ዝቅተኛ መኾኑን መዝነው ስፍራውን ይለቅቁላቸው ዘንድ ተገቢ በሚኾንበት ፈንታ፥ ሊቃውንቱን በመናፍቃን ስም ቀብተው ‘አብዝኆ መጻሕፍት ያዘነግዕ ልበ።’  የሚል የአረማዊውን የፊስጦስን ቃል እየጠቀሱ (የሐዋ ፳፮፥፳፬) ወዲያውኑ እንደ ተለመደው በሠለስቱ ምእት ሊቃውንት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊፈርዱባቸው እንዳይቸኵሉና በዚሁ አስገራሚ አኳኋን የቤተ ክርስቲያንዋ መሻሻል ዕድል እንዳይሰበር አሥጊ መኾኑን ብቻ ለማሳሰብ ነው። (መሠረት 1951፣ ገጽ 15 አጽንዖት የግል)
በርግጥም አለቃ ያሉት የደረሰ ይመስላል። ዛሬ ትልቁ ችግር መሃይምናኑ የሊቃውንቱን ስፍራ መንጠቃቸውና በእነርሱ ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊቃውንቱን “መናፍቅ” የሚል ስም ቀብተው ለመፍረድ መቸኰላቸው ነው። ይህም እርሳቸው እንዳሉት የቤተ ክርስቲያንን መሻሻል ወደ ኋላ የሚጐትት እንዳይኾን ያሠጋል። በዚህ አጋጣሚ ሌላውን ቀድሞ መናፍቅ ማለት አማኝ ለመኾን ማረጋገጫ እንዳልኾነ፥ በዚህ መንገድ መናፍቅ በመባልም መናፍቅ መኾን እንደሌለ መግለጥ እንወዳለን።  

ለዚህ ጽሑፍ መነሻው ያረጋል አበጋዝ የተባለ ዲያቆን “መድሎተ ጽድቅ” በሚል ርእስ የጻፈውና አሳትሞ መጋቢት 2007 ዓ.ም. ለገበያ ያቀረበው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ተሐድሶኣዊ አገልግሎት ላይ ያተኰሩትን፦ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን፥ “ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት”ን፥ የተቀበረ መክሊት”ን፥ “የለውጥ ያለህ!!!”ን እና ሌሎችንም የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች በመተቸት የተዘጋጀ ነው። ጸሓፊው በእነዚህ ሥራዎች ላይ ትችት ለማቅረብ ሲነሣ፥ ዝም ብሎ እንዳልተነሣና እነዚህ ሥራዎች በሕዝቡ ውስጥ ያሳደሩት ተጽዕኖ ቀላል አለ መኾኑን ስለ ተገነዘበ እንደ ኾነ እንረዳለን። እርሱ ግን፥ የተቻቸው መጽሔትና መጻሕፍት ውጤት እንዳልተገኘባቸው አስመስሎ ቢጽፍም፥ እውነታው እንደዚያ እንዳልኾነና እርሱንም ይህን መጽሐፍ እንዲጽፍ ግድ እንዳለው መካድ አይቻልም። ጽሑፎቻችንን ተችቶ ሲጽፍ፥ በአንድ በኩል እኛ ተሐድሶ ያስፈልጋቸዋል ብለን የገለጥናቸውን ትምህርቶች በመደገፍ፥ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ኾነ በማኅበሩ ውስጥ ለመናገር የማይደፍራቸውን እውነቶች፥ እነዚህን የጽሑፍ ሥራዎች ተተግኖና ‘ቤተ ክርስቲያን የማትለውን ትላለች ይላሉ’ የሚል ምክንያት በመስጠት በነጻነት ለመግለጥ ሰፊ ዕድል እንዳገኘ ተገንዝበናል።
መጽሐፉን ስንመለከተው በአንድ በኩል ዛሬ አብዛኛው ሰው የማያውቀውንና የማያምነውን፥ ብዙዎች የቤተ ክርስቲያን ልጆችም “መናፍቅ”፥ “ተሐድሶ” እየተባሉ የተወገዙበትንና ዛሬም የሚወገዙበትን እውነት የኾነውን ትምህርት እውነተኛነት አጽድቆ የጻፈበት ኹኔታ ስለሚታይ፥ ይህን ገጽታውን እንደ ተሐድሶኣዊ ዐቋም ወስደንለታል። በአንጻሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውንና ከጊዜ በኋላ የተፈጠሩ የስሕተት ትምህርቶችንና ልምምዶችን በግድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ የታገለበት ኹኔታም ስለሚስተዋል፥ ያን ዐቋሙን ፀረ ተሐድሶኣዊና ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ መኾኑን ተረድተናል። በዚህ ምላሻዊ ጽሑፍ እነዚህን የተለያዩ ዐቋሞች በየፈርጁ ለማቅረብና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን። 

ስለ መጽሐፉ ርእስ
የመጽሐፉ ርእስ “መድሎተ ጽድቅ” ነው። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ “መድሎተ አሚን” የሚል፥ ካቶሊካዊውን ጽሑፍ በመተቸት ለጻፉት መጽሐፍ የሰጡትን ርእስ ያስታውሳል። ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው “መድሎት” በሚል ርእስ የእርሳቸውንም የሌሎችንም ጥንካሬና ድክመት ያሳዩበትን ፖለቲካዊ መጽሐፍ ጽፈዋል። ዲ/ን ያረጋልም ለመጽሐፉ የሰጠው ከእነዚህ መጻሕፍት ጋር ተቀራራቢ የኾነ “መድሎተ ጽድቅ” የሚል ርእስ ነው። ርእሱ “መድሎተ ጽድቅ” ይባል እንጂ ይዘቱ ሲታይ ግን እንደ ስሙ ኾኖ አይገኝም፤ ራስን ትክክለኛ ሌላውን የተሳሳተ፥ ራስን ጻድቅ ሌላውን ኃጥእ፥ ራስን አማኝ ሌላውን መናፍቅ፥ ወዘተ. አድርጎ የሚያቀርብና ሚዛናዊነት የጐደለው ሥራ በመኾኑ፥ በእኛ እይታ ጽሑፉ “መድሎተ ጽድቅ” ለመባል የሚበቃ አይደለም።
ዲ/ን ያረጋል ለመተቸት ከደፈራቸው መጻሕፍት መካከል “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ” የተባለውን መጽሐፍ አለቃ መሠረት ያሳተሙት በ1951 ዓ.ም. ነው። ጸሓፊው አባል የኾነበት ማኅበር ከጳጉሜን 5/1985 ጀምሮ የሚያሳትመውን ጋዜጣ “ስምዐ ጽድቅ” ብሎ ነው የሰየመው። “ስምዐ ጽድቅ” በመባል ግን ስምዐ ጽድቅ መኾን አይቻል ይኾናል። ከዚህ ቀደም አቶ ብርሃኑ ደቦጭ የተባሉ ምሁር በአራተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ስለ ጋዜጣዋ (ስምዐ ጽድቅ) በሰጡት አስተያየት፡- “ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንደ ስሟ እውነትን በመናገር ረገድ ብዙም የተዋጣላት አይደለችም።” ካሉ በኋላ፥ የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመት ውጤቶች፡- “የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮ የኾነው ወንጌልን ገሸሽ ያደረጉና የወንጌሉ ዐቢይ መልእክት እውነት፥ መንገድ እና ሕይወት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሚገባ የማይገልጽ ነው” በሚል አስተያየታቸውን ማጠናከራቸውን ፍቅር ለይኩን የተባሉ ጸሓፊ ጥናቱን በዳሰሱበት ጽሑፋቸው ላይ ገልጠዋል (abaselama.org)። በዚህ የምሁሩ መለኪያ እንኳ “ስምዐ ጽድቅ” መባል የሚገባው የአለቃ መሠረት መጽሐፍ መኾኑን ማስተባበል አይቻልም።
የስያሜዎቹ መቀራረብ እንዳለ ይኹንና “መድሎተ ጽድቅ” የተባለው መጽሐፍ በርግጥ የጽድቅ ሚዛን ለመኾን ብቁ ነወይ? ስሙስ አይበዛበትም ወይ? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መነሣታቸው አይቀርም። ወደ ፊት መኾን አለ መኾኑን ግን የዲያቆኑን “መድሎተ ጽድቅ”፥ መድሎተ ጽድቅ በኾነው መጽሐፍ ቅዱስ ስንፈትሸውና ስንመረምረው የምናውቀው ይኾናል።
ሚዛኑ ምንድን ነው?
በ“መድሎተ ጽድቅ” መጽሐፍ በሽፋኑ የፊት ገጽ ላይ የሚታየው ሥዕልና በውስጥ ገጽ ስለ ሽፋኑ ሥዕል የተሰጠው መግለጫ እንደሚያሳየው፥ ጸሓፊው የተቻቸውን መጻሕፍት ለመመዘን የሞከረው ማንኛውም ክርስቲያናዊ ትምህርት ሊመዘንበት በሚገባው በመጽሐፍ ቅዱስ አለ መኾኑ፥ መጻሕፍቱን ያለ ሚዛን ለመመዘን የሚሞክር መዛኝ ያሰኘዋል። ርግጥ፥ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ምንም ሊነጻጸርና ሊወዳደር በማይችል መልኩ አክብራና አልቃ የምታምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው” (2007፣ ገጽ 38) በማለት፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ የሰጠውን ታላቅ ቦታ ለማሳየት ሞክሯል። በመጽሐፉ ውስጥም በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ጽፏል። ይኹን እንጂ እንታደስ የሚል መልእክት ያዘሉ ጽሑፎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ሳይኾን በዮሐንስ አፈ ወርቅ መጽሐፍ ለመመዘን መሞከሩ፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ የሰጠውን ቦታ ትልቅነት ከልብ ያልሰጠ አስመስሎታል።
በሽፋኑ ሥዕል ላይ የሚመዛዘኑ ተሐድሶኣውያን መጽሔትና መጻሕፍት እና የዮሐንስ አፈ ወርቅ የተባለ መጽሐፍ በሚዛን ላይ ተቀምጠዋል። ሚዛኑ ምን እንደ ኾነ ግን አልነገረንም። በሌላ በኩል ግን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውንና በእኛ ጽሑፎች የተገለጠውን ትምህርት፥ “በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት … በመቀጠልም በቀደምት አበው ትምህርት እንዲመዘኑ” እንደሚያደርግ ጽፏልና፥ ኹለት ሚዛኖች እንዳሉት ግልጥ አድርጓል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 17)። በክርስትና ትምህርት ግን ኹለት ሚዛን የለም፤ ሚዛኑ ሊኾን የሚገባው አንድ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል የኾነው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በሌላ ዐላማ ካልኾነ በቀርም ተሐድሶኣውያኑ ጽሑፎችም ኾኑ የዮሐንስ አፈ ወርቅ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመዘኑ እንጂ፥ እርስ በርሳቸው የሚመዛዘኑ አይደሉም።
ዲ/ን ያረጋል አንዱና ብቸኛው የክርስትና ሚዛን መጽሐፍ ቅዱስ አልበቃው ብሎ፥ የቀደምት አበውን ትምህርት ተጨማሪ ሚዛን ያደረገው ለምን ይኾን? መልሱ ቀላል ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸውንና ከጊዜ በኋላ የገቡትን እንግዳ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የሚደግፉልኝ እነርሱ ናቸው ብሎ ስለሚያምን ነው። በዚህም አዋልድ መጻሕፍት የሚሉትን ኹሉ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠምዘዝና የማይደግፈውን በግድ እንዲደግፍ በማስጨነቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማስመሰል ነው። ነገር ግን በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው ስለ ተዝካርና ዝክር የተጻፈው? የትኛውስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው ስለ ምንኩስና የሚናገረው? ቅዱሳት መካናትን ስለ መሳለም የተጻፈውስ በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው? እነዚህና የመሳሰሉት ትምህርቶች በአዋልድ መጻሕፍት (የሊቃውንት መጻሕፍትም ቍጥሩ ከአዋልድ መኾኑን ልብ ይሏል) እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ አይታወቁም። እርሱ ግን እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱት ልምምዶች በግድ መጽሐፍ ቅዱሳውያን ናቸው እያለ ነው።     
ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር የእግዚአብሔር ቃል የሚባል ሌላ መጽሐፍ ፈጽሞ የለም። ዮሐንስ አፈ ወርቅና ሌሎቹም አበው መጽሐፍ ቅዱስን አብራሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ልዩ ልዩ ክርስቲያናውያን ትምህርቶችን ቀረጹ፤ አስተማሩ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው መጽሐፍ አልጻፉም። የእነርሱም ምስክርነት ‘የእኛ ጽሑፎች የእግዚአብሔር ቃላት ናቸው’ የሚል አይደለም። ይልቁንም የእግዚአብሔር ቃል የኾነውን መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብና እርሱ የሚለውን ብቻ እንድንሰማ ነው የመከሩን፤ ለዚህም የሚከተሉትን ምስክሮች እንጠራለን።   
·        “የሚበልጠውም ትእዛዝ በኦሪት፥ በነቢያት፥ በወንጌል በሐዋርያት ቃል እናምን ዘንድ ነው። ንጉሥ ሆይ! … ለነፍስህ መድኀኒት ይኾኑህ ዘንድ እግዚአብሔር ሊገልጽልህ የወደዳቸው መጻሕፍት እሊህ ናቸው።” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ 89፡90)።
·        “ይደልወነ ናፅምዕ ቃላተ መለኮት ከመ ኢይባዕ ቃል ነኪር ውስተ አልባቢነ - ልዩ (ባዕድ) ቃል ወደ ልባችን እንዳይገባ ቃላተ መለኮትን (መጽሐፍ ቅዱስን) ማድመጥ ይገባናል።” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ 1987፣ ገጽ 92)።

ዲ/ን ያረጋል ግን ይህን ላይቀበል ይችላል። ለእርሱ መጽሐፍ ቅዱስና ከሐዋርያት ዘመን በኋላ የተነሡ እንደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ያሉ አበው የጻፏቸው መጻሕፍት እኩል ናቸው፤ ከላይ እንደ ጠቀስነው ሚዛን ያደረጋቸው መጽሐፍ ቅዱስንና የቀደምት አበው ጽሑፎችን ነውና።
በቅድሚያ በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎች አበው የተጻፉ መጻሕፍት መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። ደጋግመን እንዳልነው የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ትምህርት ብቸኛ ምንጭ ነው። በእርሱ ላይ መጨመርም ኾነ ከእርሱ ላይ መቀነስ፥ መልእክቱን ማዛባት፥ ተገቢ ባልኾነና ለራስ ሐሳብ ደጋፊ አድርጎ መተርጐም፥ ወዘተ. ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ በኋላ የተነሡ አበው የጻፉትም ኾነ ያስተማሩት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ነው እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የኾነ ዐዲስ መገለጥ አላመጡም። ቢያመጡም ማንም እንደማይቀበላቸው ስለሚያውቁ፥ የትኛውንም ዐይነት ክርስቲያናዊ ትምህርት ያስተምሩ፥ ትምህርታቸውንም ያስደግፉ የነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። ይህም ለመጽሐፍ ቅዱስ የሰጡትን ሥልጣናዊ ስፍራና የእነርሱ ጽሑፎችም ቦታ የት እንደ ኾነ በግልጥ ለይቶ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪ ማንኛውም ክርስቲያናዊ ትምህርት ሊመዘን የሚገባው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መኾኑን ያስገነዝባል።
እነዚህ አበው ለመጀመሪያው ምእት ዓመት ክርስትና ቅርቦች በመኾናቸው፥ መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ ስለ ጻፉና ስላስተማሩ ብቻ፥ ትምህርታቸው ምንም ስሕተት የሌለበትና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚታይ ነው ማለት ግን ፈጽሞ ስሕተት ነው። ጽሑፎቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝነው እንጂ “እነርሱ አይሳሳቱም” ተብለው በደፈናው እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሥልጣን የምንሰጣቸው አይደለም። ስለዚህ ትምህርታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሊመዘንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መኾን አለ መኾኑ ሊረጋገጥ የሚችል፥ የሚገባውም ነው። ጕዳዩን በዚህ መንገድ መረዳት ካልቻልን ለእነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስን ያኽል ሥልጣን መስጠት ይኾናል። ይህም ፈጽሞ ሊኾን የማይገባ፥ እነርሱም ያላሉትና እኛ በፈቃዳችን ለእነርሱ የምንሰጣቸው የተሳሳተ ቦታ ነው የሚኾነው። በእኛና በዲ/ን ያረጋል መካከል የልዩነታችን መሠረት ይህ ነው።
በጽሑፎቻችን ውስጥ ከቀደምት አበው ጽሑፎች ስንጠቅስ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል ባለ ሥልጣን ናቸው ብለን፥ ወይም ሰዎችን የማማለያ ስልት አድርገን አለ መኾኑ ግን በቅድሚያ ሊታወቅ ይገባል። ደግሞም ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውንና ሲመሰክሩት እየተወገዙበት ያለውን እውነት ከየትም አላመጡትም፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ እነዚህም አበው ይህን እውነት ይጋሩታል ለማለት ነው። በተጨማሪም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘናቸው እንደ ተጠበቀ ኾኖ፥ በብዙ ኹኔታ ዛሬ ለቆምንበት ክርስቲያናዊ ትምህርትና ሕይወት ብዙ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በመቀበል ነው። ይኹን እንጂ በምንም መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ዐይነት ሥልጣን አላቸው ማለት ግን ፈጽሞ አይደለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንጂ የዮሐንስ አፈ ወርቅም ኾነ የሌሎቹ አበው ጽሑፎች፥ ለክርስትና ትምህርት አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ትምህርት ሚዛን ግን አይደሉም።
የምላሹ አቀራረብ
ለ“መድሎተ ጽድቅ” ምላሽ ስንሰጥ መጽሐፉ የአንድ ግለሰብ ሥራ እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክል ነው በሚል እንዳልኾነ በቅድሚያ መግለጥ ያስፈልጋል። በዋናነት የምናተኵረውም በእኛ ጽሑፎች፥ ማለትም በ“ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”፥ በ”ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት”፥ በ “የተቀበረ መክሊት” እና በ “የለውጥ ያለህ!!!” ላይ የቀረበውን ትችት መሠረት በማድረግ ይኾናል። ይህም ሲኾን፥ በየርእሱና ንኡስ ርእሱ ላይ በተነሣው ጭብጥ ላይና ተዛብተው በተጠቀሱ የጽሑፎቹ ጥቅሶች ላይ እናተኵራለን። የተተቹት ጽሑፎቻችን በሚዛናዊ መንገድ መተቸት አለመተቸታቸውን እንመረምራለን። በየርእሱ የተነሡትን ጭብጦች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እየፈተሽን እርሱ ያቀረበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር ትክክል መኾን አለ መኾኑን እንገመግማለን። በግምገማችን ጸሓፊው እውነትን ለመሸፋፈን የተጠቀመበትን ስልቱን በማስረጃ አስደግፈን ወደ ብርሃን እናወጣለን። በየአርእስቱ የእኛን ጽሑፎች ተተግኖ የገለጣቸውንና ከእኛ ጋር የተጋራቸውን መጽሐፍ ቅዱሳውያን እውነቶችም እንጠቍማለን። እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎቹ ጽሑፎች ላይ ባቀረበው ሒስ ውስጥ ማብራሪያ መስጠት ካስፈለገ ልንሰጥ እንችላለን።         
በዚህ የመጀመሪያው ክፍል ምላሻችን፥ በ“መድሎተ ጽድቅ” መቅድም ላይና “‘ጮራ’ መጽሔት እና ‘ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ’ መጽሐፍ” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ያነሣቸውን ዋና ዋና ጕዳዮች እንመለከታለን።

ጥቂት ስለ አለቃ መሠረት
ዲ/ን ያረጋል ከመጽሐፉ መቅድም አንሥቶ አለቃ መሠረትን “እርሱ” እያለ በመጥራት፥ በኢትዮጵያ ፕሮቴስታንቲዝምን ለማስፋፋት ከሚስዮናውያን ተምረው “ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ፕሮቴስታንቲዝምን በፈሊጥ ለዘብ አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል በማለት ይከሳል (2007፣ 13)። ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ስሕተቶች አስተካክላ እንድትታደስ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት አበው ትምህርቶች በመጠቃቀስ ያቀረቡበትን መንገድም፥ “መሠረት ስብሐት ለአብ ይህን አስመሳይ ተንኰሉን ‘ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ’ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል” በማለት ቃላተ ፅርፈትን በመጠቀም ጭምር ይተቻል (2007፣ 14)።  
በመቀጠልም፥ “‘ጮራ’ መጽሔት እና ‘ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ’ መጽሐፍ” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር፥ የሚከተለውን ጽፏል፤ “መሠረት … ለትምህርት በተለያየ ቦታ በተዘዋወረበት ወቅት የኢትዮጵያን የክርስትና ትምህርት በፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ለመለወጥ ዐልመው ወደ ሀገራችን ከመጡት የአውሮፓ የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ከነ ዳቪድ ስቶክስ (የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር መሥራች) እና ከመሳሰሉት ሚስዮናውያን ጋር ‘የስብከት ዘዴ ለመማር’ በሚል ሰበብ ተወዳጀ። ቀስ በቀስም የሚስዮናውያኑን ፍልስፍናና አስተምህሮ ተቀብሎ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመለወጥ ብዙ ደክሟል። - ባይሳካለትም።
“… የስሕተት (የተሐድሶ) ትምህርቱን በ1950ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች (በሸዋ፣ በጎንደር፣ በጐጃም) ለማስፋፋት ሞክሮ የተለየ እምነትና አስተምህሮ ያለው መኾኑ እየታወቀበት ከኹሉም የተባረረ ሲኾን፥ በኋላም በእነ ሚስተር ዳቪድ እስቶክስ ጠቋሚነትና ስለ ‘ዘመናዊ አስተሳሰቡ’ በሰጡት ምስክርነት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሴሚነሪ ሲጀመር እንዲገባ ተፈልጎ ከፍተኛ ትምህርት ቤቱ ከተከፈተ ከኹለት ዓመታት በኋላ ለስብከት ከሄደበት ቦታ ወደ ዐዲስ አበባ ተመልሶ ወደ ሴሚነሪ ገብቶ ነበር። ኾኖም ግን በዚህ ትምህርት ቤትም ያው የተለመደውን ፕሮቴስታንታዊ የኾነውን የሚስዮናውያኑን ትምህርት ማስፋፋት ሲሞክር ተደርሶበት፥ ከዚያም በቅዱስ ፓትርያርኩ ትእዛዝ ተባርሮ ወጥቷል። በመቀጠልም ወዳስተማሩትና በእምነት ወደሚመስሉት ወደ ሚስዮናውያን ዘንድ በመጠጋት በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ቦታዎች፤ በተለይም እነርሱ በኋላ በአዲስ አበባ ባቋቋሙት ሴሚነሪ እስከ ኅልፈተ ሕይወቱ ሲያገለግል ቈይቷል።” (2007፣ 23)        
አለቃ መሠረት በብዙዎች ዘንድ በዕውቀታቸው፥ በሥራዎቻቸውና በኑሯቸውም የታወቁና የተመሰከረላቸው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ናቸው። ሊቁ በዲያቆኑ “አንተ” ቢባሉም፥ በሊቃውንቱ ዘንድ ግን እጅግ የተከበሩና “አንቱ” የተባሉ ሰው ነበሩ። ይህ የያረጋል ክብርን ማዋረድ የእርሳቸውን ታላቅ ሰብእና ለማቃለልና ለማራከስ ኾን ተብሎ የተሰነዘረ ቢኾንም፥ በዚህ ራሱን ያስገምታል እንጂ ተቀባይነትን አያገኝም፤ የእርሳቸውንም ማንነት ሊለውጠው አይችልም። ድርጊቱ ኢትያጵያዊ ባህላችን የማይፈቅደው ሲኾን፥ በእግዚአብሔር ቃልም የተከለከለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፥ “… ወአክብር ገጸ አረጋዊ ወፍራህ እግዚአብሔርሃ አምላክከ፥ እስመ አነ እግዚአብሔር አምላክክሙ። - … ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” (ዘሌ. 19፥32) ይላል።
ይህ የዲ/ኑ ድርጊት፥ ከዚህ ቀደም ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና ሐመር መጽሔት 10ኛ ዓመት በዓላቸውን የካቲት 20/1996 ዓ.ም. ባከበሩበት ወቅት፥ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣን፥ “ደካማና ፈሪ ብለው ስለ ኰነኑትና ስለ ዘለፉት”፥ እንዲሁም በወቅቱ የነበረው ዐዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን ጸሓፊ፥ “በቤተ ክርስቲያኒቱ እየታተሙ ከሚወጡት ዕትሞች በማኅበረ ቅዱሳን እየታተሙ የሚወጡት ዕትሞች የተሻሉ መኾናቸውን ደፍረው ስለ መሰከሩ” አንጋፋውና በጊዜው ፷ ዓመት የሞላው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፥ በማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ “የ፷ ዓመቱ አዛውንት በ፲ ዓመቱ ሕፃን ተዘለፈ” በሚል የጻፈበትን ርእሰ ጽሑፍ ያስታውሰናል (1996፣ ገጽ 1፡5)።
ዲ/ን ያረጋል የአለቃ መሠረትን ሰብእና ለማራከስ የሞከረው በተለይ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን  በመጥቀስ ነው። ሌሎች የታወቁ ሥራዎቻቸውን ግን ለመጥቅሰም ኾነ መኖራቸውን እንኳ ለማስታወቅ አልሞከረም፤ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ግን የሚከተሉትን መጻሕፍት ጽፈው አሳትመዋል፤ ለኅትመት አዘጋጅተዋል፤ በማዘጋጀትም ላይ ነበሩ።
ያሳተሟቸው፡-
·        “ሥላሴ በተዋሕዶ”፥
·        “ትውፊታዊ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ - በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐቋም”፥
·        “ሥረ ብዙ”፥
·        “ቃለ እግዚአብሔር ነበረ”
·        “አርዮሳውያን”
ለኅትመት ተዘጋጅተው የነበሩት፡-  
·        “ተፈንዎ በኢቡዓዴ (ተልእኮ ባለ መለየት)”
·        “ማእከላይ በተዋሕዶ”
·        “ሕይወተ ክርስትና በተዋሕዶ”
·        “ኀሠሣ ተመርሖ ልቡናዊ (የመጽሐፍና የልቡና መስማማት)
·        “ጽጌ ደንጐላ (የሱፍ አበባ (ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን))”
በመዘጋጀት ላይ የነበሩ መጻሕፍት፡-
·        “ከግእዝ መጽሐፍ ቅዱስና ከአበው ሊቃውንት መጻሕፍት የተገኙ አንድ መቶ ሠላሳ ኹለት የቅኔ መንገዶች (ጐዳናዎች) ዐመልና ስልት”
·        “ሥነ ጽሑፋችንና አወራረዱ”
·        “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአስተዋፅኦ”
·        “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባህልና የሥነ ሥርዐት አፈጻጸም”
·        “ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ያድናል”

እርሱ ግን “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን ብቻ ሲተች፥ በእነዚህ ታላላቅ መጻሕፍቶቻቸው ላይ ግን አስተያየት አልሰጠም፤ መኖራቸውንም እንኳ አልጠቈመም። ይኹን እንጂ ብዙዎች “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን ጨምሮ በእነዚህ መጻሕፍት የሚደመሙና በየ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው በዋቢነት የሚጠቅሷቸው፥ ትልቅ ምስክርነትም የሚሰጧቸው ናቸው። ለምሳሌ፦ አለቃ መሠረት በትውፊታዊ ሐሰበ ዘመንና ታሪኩ መጽሐፋቸው ላይ መጽሐፉን አንብበው ላበረታቷቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የወሮታ ምስጋና ያቀረቡላቸው ሲኾን፥ እነርሱም ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ዘከፋ ሀገረ ስብከት፥ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፥ ንቡረ እድ ድሜጥሮስ ገብረ ማርያም ናቸው። “ትውፊታዊ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ” ከታተመ ከ1981 ዓ.ም. ወዲህ ስለ ኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር፥ ስለ ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ ወዘተ. የጻፉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኹሉ ማለት ይቻላል፥ መጽሐፉን በዋቢነት ሳይጠቀሙበትና ሳይጠቅሱት  ጽፈዋል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ፦
·        መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ እና ሊቀ ሥዩማን አስረስ ራደ (1999፥ ገጽ 17)፥ “ክርስቶስ ዘሀሎ ወይሄሉ” በተሰኘ መጽሔት ላይ “የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር” በሚል ርእስ ለጻፉት ጽሑፍ፥
·        ሊቀ ኅሩያን ጌታቸው ጓዴ (1999፣ ገጽ 16) “ቃሉ ይናገር” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ባሳተማቸው መጽሔቶች ቍጥር 1፥ 2 እና 4 ላይ በቅደም ተከተል፥ “የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር”፥ “በዘመን አቈጣጠር የጊዜ መስፈርታትና አዕዋዳት” እና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር ያለው ቦታ” በሚሉ አርእስት ለጻፏቸው ጽሑፎች፥
·        መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ እና ዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ (2000፣ ገጽ 38ቃሉ ይናገር” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ባሳተመው  መጽሔት ቍጥር 4 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስና ሥነ ምግባር” በሚል ርእስ ለጻፉት ጽሑፍ፥
·        ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ (2003፣ ገጽ 30) “በመስቀሉ ገነትን ከፈተ” በተሰኘውና ለመስቀል ደመራ በዓል በተዘጋጀው ልዩ መጽሔት ላይ ለጻፉት ጽሑፍ፥
·        “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም. (2000)” በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ክፍል 2 ገጽ 87 ላይ “ትው.ሐ ዘመን ገጽ 147” ተብሎ ተጠቅሷል።
·        አለቃ ያሬድ ፈንታ (2005) “ባሕረ ሐሳብ፥ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምስጢር” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፥
ተጠቅመዉበታል፤ በዋቢነትም ጠቅሰዉታል።
ከነዚህም በተጨማሪ ስለዚህ መጽሐፍ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ፥ “ባሕረ ሐሳብ፥ የዘመን ቈጠራ ቅርሳችን ከታሪክ ማስታወሻ ጋራ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል። “የግእዝና የአማርኛ የብራና መጻሕፍትን ስመለከት ስለ ባሕረ ሐሳብ የተጻፉት መጻሕፍትም በውስጣቸው ያለው ቋንቋው ሳይቀር ኹሉም ያንኑ መምህራኑ የሚያስተምሩትን ነው። በዚያ ላይ አራት የታተሙ መጻሕፍት አንብቤያለሁ። እነዚህ መጻሕፍትም ካንዱ አቶ መሠረት ስብሐተ ለአብ ካሳተሙት በቀር ሌሎቹ አንዱ ከሌላው በአንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች ይለያዩ እንደ ኾነ ነው እንጂ ኹሉም ያቀረቡልን ያንኑ ያልታተሙት መጻሕፍት የያዙትንና መምህራኑ የሚያስተምሩትን ነው፤ ተጨማሪ ማብራሪያ የለባቸውም።” (2006፣ ገጽ 13)። ስለ ኾነም፥ “የባሕረ ሐሳብ ዕውቀቱን ሊያሰፋ የሚፈልግ ከላይ ከጠቀስኳቸው መጻሕፍት በተጨማሪ አቶ መሠረት ስብሐት ለአብ በመካነ ኢየሱስ ሴሚነሪ ድጐማ ትውፊታዊ ኀሳበ ዘመንና ታሪኩ በሚል ርእስ በ1981 ዓ.ም. ሆንግ ኮንግ ያሳተሙትን … ቢያጠና ይጠቀማል።” ብለዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 17)።    
ዶ/ር ፈቃደ አዘዘም “የሥነ ቃል መምሪያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፥ አኹን፥ አኹን በአገራችንና በሌሎችም ሀገሮች ቋንቋዎች በፍጥነት እየገባና እየተለመደ የመጣውን “ፎክሎር”ን፥ ቀደም ሲል ትውፊት ብለው ይጠሩት እንደ ነበረና ይህም የኾነው፥ “‘በመሠረት ስብሐት ለአብ ተጽፎ በታተመው ትውፊታዊ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ - በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐቋም’ (1981) በተባለ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበውን የትውፊትን ፍቺ በመመርኰዝና” የራሳቸውን ሐሳብ በመጨመር በቃሉ ለመገልገል ወስነው የነበረ መኾኑን ጽፈዋል (1991፣ ገጽ 11)።
“ከትውፊታዊ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ” በተጨማሪ ከሌሎች የአለቃ መጻሕፍት ውስጥ የሚጠቅሱ አሉ። ይልቁንም ትንሣኤየተሰኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሔት በሐምሌ 1972 ዕትሙ ከስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ ላይ እና ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአስተዋፅኦ ላይ “ሰላማ ካሣቴ ብርሃን” በሚል ርእስ ጽሑፍ አውጥቷል (ምንጩን ግን በአኅጽሮት ስ.ጽ.ብ. ብሎ ነው የጠቀሰው ገጽ 8-9፡12)።
ዲ/ን ያረጋል “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ንና ጸሓፊውን አለቃ መሠረትን ለመተቸት መነሣቱን ስናስብ፥ እንዲህ ለማድረግ የሚያስፈልገው ድፍረት እንጂ ዕውቀት አለ መኾኑን ተገንዝበናል። እርሱ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን ለምን አጥላልቶ ጠቀሰው? እውን በዚያ መጽሐፍ ላይ ኑፋቄ ስላለ ነውን? ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖረው ይኾን? ያን በስፍራው የምናየው ይኾናል። መጽሐፉ በዚያ ዘመን አነጋገር ብሔራዊቷ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውንና የምታስተምረውን ትምህርት በሦስት ክፍላትና በአርባ ስድስት አናቅጽ የሚዘረዝር፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን የሚያስይዝና በጥንት አበው ትምህርትም የሚያጐላምስ፥ ቤተ ክርስቲያን ከልማድ ወጥታ በእግዚአብሔር ቃል እንድትመራ ለማድረግ መሠረተ እምነቷንና ትምህርቷን እንድትፈትሽና በቃሉ ላይ እንድትመሠርት የሚቀስቀስ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉም ለብዙ ዓመታት በሊቃውንቱ ዘንድ የሚደነቅና የሚነበብ መጽሐፍ እንደ ነበረና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ካለው ከኦርቶዶክስ ትምህርት ውጪ እንዳልኾነም ይታወቃል።
ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ የተጻፈበት ዘመን (1951 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያን ጳጳሳት መመራቷ አብቅቶ፥ የራሷን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ የሾመችበትና ኹኔታውም “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መታደስ” ተብሎ በአደባባይ በቃልም በመጻፍም የተነገረበት ዘመን ነው። የአለቃ መሠረት ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን በዚህ መንገድ በግብጻውያን ከመመራት ወጥታ ራሷን በመቻል ተሐድሶ እንዳደረገች ኹሉ፥ የራሷን ሲኖዶስ ወደ ማቋቋም የምትገባው ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነቷንና አስተምህሮዋን በመጽሐፍ ቅዱስ እንድትፈትሽና ተሐድሶ ማድረግ ባለባት ጕዳይ ላይ ተሐድሶን እንድታደርግ ለማነሣሣት ነው። አለቃ መሠረት ስምዐ ጽድቅን፥ “ … ለመጻፍ ያነሣሣኝ ምክንያት ... ነጻነት ያገኘችው ቤተ ክርስቲያናችን በብሔራዊ አንድነት ቀዋሚውን ሃይማኖት ሳይሆን፤ ያለ ሐሳብ የገባውን ልማድ እንድታሻሽልና ጥንታዊውን የሃይማኖት መሠረት ግልጽ አድረጋ በማስተማር እንድትታደስ ነው። … ግን ደግም ስለ ቤተ ክርስቲያን መታደስ ስንናገር በአኹኑ ጊዜ በብዙዎች ዘንድ መታደስ የተባለው ኀይለ ቃል በሃይማኖት ላይ ዐዲስ ነገር ወይም ዐዲስ ሐሳብ እንደ ማምጣት ስለሚገመት፥ አንዳንዶቹም በቅርታ መንፈስ እየ ተመለከቱት ስለሚታይ፤ ይህን ለማወቅ አስቸጋሪ ያልነበረውን ነገር እስቲ እንነጋገርበት!” በሚል ነው (መሠረት 1951፣ ገጽ 9፡11)። የተሐድሶን ምንነት በቅጡ ያልተረዳውና በየገጹ ሁሉ ተሐድሶን “ዐዲስ ሃይማኖት” አድርጎ ለማቅረብ የሚጥረው የ“መድሎተ ጽድቅ” ፀሓፊ ግን በዚህ ደስ አልተሰኘም። ስለዚህ አለ ስማቸው ስም ሰጥቶ፥ ሥራቸውን አክፍቶ ጻፈ። 
አለቃ መሠረት በሥራዎቻቸው ኹሉ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዋ እንድታደርግ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይቃረኑ ትምህርቶቿን፥ ሥርዐቷን፥ ትውፊቷንና ባህሏን ጠብቃ እንድትጓዝ ከልብ የሚሹ፥ ቤተ ክርስቲያኗን የሚወዱና ተሐድሶዋን የሚናፍቁ አባት እንደ ነበሩ ከማንም በላይ ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ። ዲ/ን ያረጋል እንዳለው ዐላማቸው ቀስ በቀስ ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት ማድረግ ግን ፈጽሞ አልነበረም፤ እንዲህ ቢኾን ኖሮ፥ “ሥላሴ በተዋሕዶ”ን ባልጻፉ ነበር፤ “ትውፊታዊ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ” ን ባላዘጋጁም ነበር። ያልታተመውን “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአስተዋፅኦ” ንና ሌሎችንም መጻሕፍት በማዘጋጀት ባልደከሙ ነበር። ከላይ የተዘረዘሩትን፥ የታተሙትንና በዝግጅት ላይ የነበሩትን የአለቃ መሠረትን መጻሕፍት ስሞች ስንመለከት እንኳ፥ ዲያቆኑ ከልቡ አንቅቶ እንደ ጻፈው አንድም ፕሮቴስታንቲዝምን ለማስፋፋትና ኦርቶዶክስን ለማዳከም የተጻፈ መጽሐፍ እንደሌለ መገንዘብ እንችላለን። ምክንያቱም ፕሮቴስታንቲዝምን የሚያቀነቅን ሰው በእነዚህ ርእሰ ጕዳዮች የተጻፉትን መጻሕፍት ኹሉ ቀድሞም አለ መጻፍ እንጂ በትጋት አዘጋጅቶ ማሳተምና ለሕዝብ ማሠራጨት አያስፈልገውም። ስለዚህ የያረጋል ትችትና ነቀፋ መሠረተ ቢስ መኾኑን ከአለቃ ማንነትና ከሥራዎቻቸው መገንዘብ ይቻላል።
ያረጋል የአለቃ መሠረትን ታሪክ በተሳሳተ መንገድ ማቅረብ ብቻ ሳይኾን፥ የጊዜ ቅደም ተከተሉን በማዛባት ጭምር ነው የጻፈው። እርሳቸው በሰዋስው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሊማሩ ገብተው የነበረ ቢኾንም፥ ብዙም ሳይቈዩ “መጽሐፍ ቅዱስን ለተማሪዎች ታስተምራለህ” በሚል ክስ ተወንጅለው ከዚያ መባረራቸውን መስክረዋል። ይኸውም “እዚያው ገብተው እየተማሩ ሳለ ክርክር ተነሣ፥ በትምህርት ቤቱ ዲያሬክተር በአባ ቀለመ ወርቅም ተቃውሞ ደረሰባቸውና ከትምህርት ቤቱ ወጡ።” በጊዜው አባ ቀለመ ወርቅ በተመሳሳይ ምክንያት ብዙ ተማሪዎችን ማባረራቸውንና በዚሁ ምክንያት ብዙም ሳይቈዩ ከሥራቸው ላይ መነሣታቸውም ታውቋል (ጮራ ቍጥር 14፣ ገጽ 15፣ ሥላሴ በተዋሕዶ የአቶ መሠረት ስብሐት ለአብ ዐጭር የሕይወት ታሪክ)። ልብ እንበል! አለቃ የተባረሩት፥ “መጽሐፍ ቅዱስን ለተማሪዎች ታስተምራለህ” ተብለው ነው። ያረጋል ግን፥ “በዚህ ትምህርት ቤትም ያው የተለመደውን ፕሮቴስታንታዊ የኾነውን የሚስዮናውያኑን ትምህርት ማስፋፋት ሲሞክር ተደርሶበት” ነው ይላል (ያረጋል/ዲ/ን 2007፣ ገጽ 23)። መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ለያረጋል “የስሕተት (የተሐድሶ)” ወይም “ፕሮቴስታንታዊ” ትምህርት ነው ማለት ነው።
አለቃ ከ1950ዎቹ በኋላ ሳይኾን ከዚያ በፊት ነው በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ሲማሩ፥ ሲመራመሩና ወንጌልን ሲሰብኩ ያሳለፉት። ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጰውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የወጡትም ከ1950 ዓ.ም. በፊት ነው እንጂ ያረጋል ዘመኑን አዛብቶ እንዳቀረበው በኋላ አይደለም። ከዚያ እንደ ወጡ፥ “ቄስ ጊዳዳ፥ የሚማሩ ሰዎች ከእኛ ዘንድ ስላሉ መጥተህ አስተምርልን በማለት፥ ወደ ቤቴል ማኅበረ ምእመናን ጠሯቸው። በቤቴልና በአሜሪካን ሚሽን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ ለ7 ዓመታት ያኽል ቈዩ።” (ሥላሴ በተዋሕዶ፣ የአቶ መሠረት ስብሐት ለአብ ዐጭር የሕይወት ታሪክ)። በ1965 ዓ.ም. በመካነ ኢየሱስ ሴሚነሪ የማስተማር ተግባራቸውን ትተው፥ ራሳቸውን ችለው፥“እያረስኩ ወንጌልን እስብካለሁ፤ የድርሰቱንም ሥራ በአንጽንዖት አካሂዳለሁ” ብለው ወደዚያ ያቀኑ ቢኾንም፥ በጊዜው የነበሩ የመካነ ኢየሱስ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፥ “አንተ እንደ አንድ የወንጌል አስተማሪ ኾነህ ከምትሰማራ ይልቅ፥ ለዚህ ሥራ ሊሰማሩ የሚሠለጥኑ ብዙ ቀሳውስትንና ወንጌላውያንን በማሠልጠን ሥራ የምታደርገው ተሳትፎ የበለጠ ጠቃሚነት አለው በሚል ምክር ወደ ማስተማር ሥራዬ መለሱኝ” ሲሉ፥ ከጮራ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጠዋል (ጮራ ቍጥር 14፣ ገጽ 13)።  
በመካነ ኢየሱስ ሰሚነሪየም በመምህርነት በቈዩባቸው ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜ ተማሪዎች፥ “የሕዝባቸውን መሠረት እንዲያውቁ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋፅኦ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባህልና እምነት፥ የዐማርኛ ሰዋስው፥ ግእዝና የመሳሰሉትን ከማስተማራቸው በላይ፥ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ለሚመጡ የኢትዮጵያ ጥናት ሊቃውንት ከሰፊ ዕውቀታቸው ሲያካፍሉ ቈይተዋል። ከዕውቀታቸው ሰፊነትና ጥልቅነት የተነሣ አንዳንዶች አቶ መሠረት ‘የቁም መዝገበ ቃላት ናቸው’ እያሉ ይናገሩ ነበር።” (መሠረት 1988፣ የአቶ መሠረት ስብሐት ለአብ ዐጭር የሕይወት ታሪክ)። ይህም የሚያሳየው አለቃ መሠረት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን ጥልቅ ፍቅርና ተሐድሶዋን የሚመኙ መኾናቸውን እንጂ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ሌላ ማንነት ወይም ወደ ፕሮቴስታንትነት የመለወጥ አጀንዳ ያልነበራቸው መኾኑን ነው። እንግዲህ ለሰው ከሥራው በቀር ማን ይመሰክራል?
ዲ/ን ያረጋል በአንድ ወገን ሚስዮናውያኑን እነ ዳዊት እስቶክስን፥ “የኢትዮጵያን የክርስትና ትምህርት በፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ለመለወጥ ዐልመው ወደ ሀገራችን” የመጡ የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን አድርጎ ያቀርባቸዋል። በሌላ ወገን ደግሞ አለቃ መሠረት ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የተደረገው በዳዊት እስቶክስ “ጠቋሚነትና ስለ ‘ዘመናዊ አስተሳሰቡ’ በሰጡት ምስክርነት” ነው ይላል። እርሱ እንደሚለው ሚስዮናውያኑ ዐላማቸው የኢትዮጵያን የክርስትና ትምህርት ወደ ፕሮቴስታንትነት መለወጥ ከኾነ፥ ትምህርት ቤቱ እነርሱንም ኾነ ምስክርነታቸውን እንዴት ተቀበለ? እንዴትስ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሴሚነሪ ከእነርሱ ጋር በስምምነት ሊሠራ ቻለ? የሚሉት ጥያቄዎች ይነሣሉ። በርግጥ ያረጋል አለቃ መሠረት ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሴሚነሪ እንዲገቡ፥ ዳዊት እስቶክስ ምስክርነት መስጠታቸውን አልካደም። ኾኖም ምስክርነቱ የተሰጠው በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትና በሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር መካከል በነበረው ስምምነት መሠረት መኾኑን መግለጥ ግን አልፈለገም። እርሱ መግለጥ ባይፈልግም፥ “በሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበርና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት ትምህርት ቤቱ የሚስተር እስቶክስን ተማሪዎች ይቀበል ነበር።” (መሠረት 1988፣ የአቶ መሠረት ስብሐት ለአብ ዐጭር የሕይወት ታሪክ)። ወደ ፊት በስፍራው እንደምንመለከተው የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በነበረው ስምምነት መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱን በመደገፍና በመርዳት ዐብሮ ሲሠራ ቈይቷል። ከዚህ አንጻር የአለቃ መሠረት “የስብከት ዘዴ” ለመማር በሚል ከዳዊት እስቶክስ ጋር መወዳጀት የሚያስደነቅ አይደለም።          
 ይቀጥላል……


ዋቢ ጽሑፎች
ሃይማኖተ አበው (1986) ዐዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
መሠረት ስብሐት ለአብ (1951) ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ። ዐዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።
                 (1988) ሥላሴ በተዋሕዶ። ዐዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት።
ማኅበረ ቅዱሳን (2003) የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ፡፡ አዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያተገለጸ፡፡
ማንሰል፣ ኮ. (2003) ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ። ዐዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ድርጅት።
ምስክረ ብርሃን (ነሐሴ) 1964። 
                 (ጥቅምት) 1964።
ስምዐ ጽድቅ (መጋቢት) 1995 ዓ.ም.።
ቃሉ ይናገር (ቍጥር 1፣ 2፣ 3፣ 4) (1999) ወሩ እና ቀኑ ያልተጠቀሰ።
በመስቀሉ ገነትን ከፈተ (2003) መስከረም 16።
ተግሣጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ። (1987) ዐዲስ አበባ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት።
ትንሣኤ (ሐምሌ) 1972።
ክርስቶስ ዘሀሎ ወይሄሉ (1999) ሚያዝያ (ቀኑ ያልተጠቀሰ)።
ዜና ቤተ ክርስቲያን (1996) መጋቢትና ሚያዝያ (ቀኑ ያልተጠቀሰ)።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.። (2000)፣ አዲስ አበባ፣ ሜጋ ማተሚያ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር።
ያሬድ ካሳ (ሊቀ ሊቃውንት) (1993) ሕያው ስም። (ማተሚያ ቤቱና ቦታው ያልተጠቀሰ)።
ያሬድ ፈንታ (አለቃ)(2005) ባሕረ ሐሳብ፥ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምስጢር። ዐዲስ አበባ፣ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃላ. የተ. የግ. ማኅበር። 
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (ነጋድራስ) (2002) ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች። ዐዲስ አበባ፣ አአዩ ማተሚያ ቤት።
ጌታቸው ኀይሌ (ጌታቸው ኀይሌ)፥ “ባሕረ ሐሳብ፥ የዘመን ቈጠራ ቅርሳችን ከታሪክ ማስታወሻ ጋራ”
ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን (1993) ጥቅምት፡፡
ጮራ (አልቦ ወርኅ ወዓመተ ምሕረት)።
ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) (1991) የሥነ ቃል መምሪያ። ዐዲስ አበባ፣ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት።
Benson, Doris. The Most Valuable Thing: The Word at work in Ethiopia. n.d.
www.abaselama.org. 18 September 2012. Document. 14 may 2015.
www.tehadeso.com. 12 January 2012. Document. 14 may 2015.


2 comments:

  1. ልቦና ይስጣችሁ መጽሐፉን ሲጽፈው በእናንተ ጽሑፎች ምክያት የሚመጣውን ክርስትና መሰል ክህደት ሌላውን እንዳያደናግር ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ለእናንተም ጭምር ነው፡፡ ምናልባት የጻፈው ነገር እውነት ሊሆን ስለሚችል በቀና ልቦና አንብቡት፡፡ ፍርድ እንደሁ አይቀርም፡፡

    John 6፡54 Whoso eateth my flesh, and drinketh my blood, hath eternal life; and I will raise him up at the last day.

    ReplyDelete
  2. ጭራሽ ሥጋ ወደሙን ካዳችሁ! እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ!
    ሉተር እንኳ አልካደውም

    ReplyDelete