Sunday, August 16, 2015

ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ላይ በዚህ ዐምድ በተከታታይ የወጡትን ጽሑፎች አስመልክተው፣ የተለያዩ አንባብያን የስልክ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል። ከአንባብያኑ መካከል አንዳንዶቹ የክርስቶስን መካከለኛነት ላለመቀበልና ለሌሎች ቅዱሳን ለመስጠት አለን ያሉትን ማስረጃ በማቅረብ ጭምር ለመከራከር ሞክረዋል። ለክርክራቸው እንዲረዳቸውም፣ “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ. 5፥16) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የጠቀሱ ሲሆን፣ በመጨረሻም፣ “አሁን እርሱ መካከለኛ መሆኑ ቀርቷል፤ አሁን አምላክ ነው” ሲሉ ደምድመዋል። ክርስቶስን ከመካከለኛነቱ ስፍራ አንሥተውም፣ “አሁን መካከለኛው ሥጋ ወደሙ ነው” ሲሉም አክለዋል። ስለ ሥጋ ወደሙ የተባለውን ለቀጣዩ ዕትም እናቈየውና በጥቅሱ ላይ የተላለፈውንና ክርስቶስ አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም የሚለውን አውጣኪያዊ ትምህርት በመመርመር የክርስቶስን መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስንና የአበውን ምስክርነት በመጥቀስ ወደ ማሳየት እንለፍ።
ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ብቻ ነበረ እንጂ አሁን ወደ ክብሩ ከገባ በኋላ መካከለኛ አይደለም’ የሚሉት በትምህርተ ሥጋዌ ላይ በቂ ዕውቀት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ተምረዋል የሚባሉትም ጭምር እንደ ሆኑ ይታወቃል። በተለይም የተማሩት ክፍሎች እንዳልተማሩቱ አፋቸውን ሞልተው አሁን አምላክ ብቻ ነው እንጂ ሰውም አይደለም አይሉም፤ ክርስቶስ ዛሬም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን እናምናለን ይላሉ። ክርስቶስ አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ ግብረ አምላክን (የአምላክን ሥራ) እንጂ ግብረ ትስብእትን (የሰውነትን ሥራ) አይፈጽምም ስለሚሉ ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእትን ያስተባብላሉ። ለምሳሌ፣ … ነቢረ የማን (በአብ ቀኝ መቀመጥ) ክርስቶስ ግብረ ትስብእት ከፈጸመ በኋላ እንደ ገና የሰውነትን ሥራ የማይሠራ፥ ነገር ግን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በክብር መለኮታዊ ሥራውን እየሠራ የሚኖር መሆኑን የሚያስረዳ ቃል ነው”[1] ያሉ ይገኛሉ። አባባሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ እስኪቀመጥ ድረስ መለኮት ሥራውን ለትስብእት ትቶ ትስብእት ብቻ ይሠራ ነበር፤ ትስብእት ደግሞ አሁን በተራው የሥራ ጊዜውን ስለ ፈጸመ ሥራውን ለመለኮት ተወ ያሰኛል። እንዲህ ከሆነም ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ግብረ ትስብእትን ብቻ እንጂ ግብረ መለኮትን አይፈጽምም ነበር የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። ቅዱሳት መጻሕፍትና በእነርሱ ላይ የተመሠረቱ የአበው ምስክርነቶች ግን የሚነግሩን ከዚህ የተለየ እውነት ነው።

“አንሶሰወ ከመ ሰብእ እንዘ ይገብር ከመ እግዚአብሔር። ርኅበ በፈቃዱ ከመ እጓለ እመ ሕያው ወአጽገቦሙ ለርኁባን ብዙኃን አሕዛብ እም ኅዳጥ ኅብስት ከመ ከሃሊ። ጸምአ ከመ ዘይመውት ወረሰዮ ለማይ ወይነ ከመ ማሕየዌ ኵሉ። ኖመ ከመ ውሉድ ዘሥጋ ነቅሐ ወገሠጾሙ ለነፋሳት ከመ ፈጣሪ። ደክመ ወአዕረፈ ከመ ትሑት ወሖረ ዲበ ማይ ከመ ልዑል። ወኰርዕዎ ርእሶ ከመ ገብር ወአግዐዘነ እም አርዑተ ኀጢአት ከመ እግዚአ ኵሉ።”
ትርጓሜ፥ “እንደ እግዚአብሔር እየሠራ እንደ ሰው ተመላለሰ። ሰው እንደ መሆኑ በፈቃዱ ተራበ፤ ከሃሊ እንደ መሆኑ የተራቡ ብዙ አሕዛብን ከጥቂት እንጀራ አጠገባቸው። የሚሞት እንደ መሆኑ ተጠማ፤ ሁሉን የሚያድን እንደ መሆኑ ውሃውን ወይን አደረገው። እንደ ሥጋ ልጆች ተኛ፤ ፈጣሪ እንደ መሆኑ ነቅቶ ነፋሳትን ገሠጻቸው። ትሑት እንደ መሆኑ ደክሞ ዐረፈ፤ ልዑል እንደ መሆኑ በባሕር ላይ ሄደ። እንደ ተገዢ ራሱን መቱት፤ የሁሉ ጌታ እንደ መሆኑ ከኀጢአት ቀንበር ነጻ አደረገን።”[2] 
በዚህ ቃለ ቅዳሴ ውስጥ አንዱ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ በሰውነቱ የተከናወነውንና ያከናወነውን ግብረ ትስብእትን፣ በአምላክነቱም የሠራውን ሥራ (ግብረ መለኮትን) በንጽጽር እንመለከታለን።
·        መራብ የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 4፥2፤ 21፥18)፤ - በጥቂት እንጀራ ብዙዎችን ማጥገብና ዐሥራ ሁለት መሶብ ተረፍ ማስነሣት ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 6፥10-13)።
·        መጠማት የሰውነት ግብር ነው (ዮሐ. 4፥7፤ 19፥28)፤ - ውሃውን ወደ ወይን መለወጥ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 2፥7-11)።
·        ማንቀላፋት የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 8፥24፤ ሉቃ. 8፥23)፤ - ነፋሱንና ባሕሩን መገሠጽና ጸጥ ማድረግ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 8፥26-27፤ ሉቃ. 8፥24-25)።
·        መድከምና ማረፍ ግብረ ትስብእት ነው (ዮሐ. 4፥6)፤ - በባሕር ላይ መሄድ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 14፥25-26)።
·        ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዘንግ መመታት) ግብረ ትስብእት ነው (ማቴ. 27፥29-30)። - ሰውን ከኀጢአት ማዳን ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (1ጢሞ. 1፥15፤ ዕብ. 2፥14-15)።
ክርስቶስ አሁን ያለው በክብር እንጂ በዚህ ምድር በነበረበት ሁኔታ አይደለምና በዚህ ምድር በሰውነቱ የተቀበለው ግብረ ትስብእት ማለትም፦ መራብ፣ መጠማት፣ መድከም፣ ማረፍ፣ ማንቀላፋት፣ ወዘተ. አሁን የለበትም። ይሁን እንጂ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ አንድ ጊዜ በፈጸመውና ለዘላለም በሚያገለግለው የአድኅኖት ሥራው አሁን በክብር ባለበት ሁኔታ፣ በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡትና ከመጡም በኋላ ጠላት የሆነው ሰይጣንና ኀጢአት ለሚከሷቸው ሁሉ ዋስትናቸውና መታረቂያቸው ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ መሆኑን መካድ አይቻልም። የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳውያን ጥቅሶች ይህን ያስረዳሉ፤
·        እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ 8፥33-34)።
·        “ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ” (1ዮሐ. 2፥1-2)።
በክብር የሆነውና ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ የሚያከናውነው ግብረ ትስብእት ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር የሚያያዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያት ያለፈ በድካማችንም ሊራራልን የሚችል ታላቅ ሊቀ ካህናት ነው (ዕብ. 4፥14-15)። “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ጌታ ሊቀ ካህናት የሆነው በሰውነቱ ነው (ዕብ. 5፥1)። ስለዚህም በሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚከናወነው የሊቀ ካህናትነቱ ተልእኮ ግብረ ትስብእት ነው። እርሱ “በሥጋው ወራት (በዚህ ምድር ሳለ) ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ … ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብ. 5፥7፡9-10)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ጸሎትንና ምልጃን እንዳቀረበና እንደ ተሰማለትም ተገልጿል። ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ደግሞ በሊቀ ካህናትነቱ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራውን ፈጽሞ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል (ማር. 16፥19፤ ሐ.ሥ. 2፥33፤ 7፥55-56፤ ሮሜ 8፥34፤ ቈላ. 3፥1፤ ዕብ. 10፥12፤ 1ጴጥ. 3፥22)። በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠውም በዚህ ምድር ሳለ ይፈጽም የነበረውን ግብረ ትስብእትን የማይፈጽም ሆኖ፣ ነገር ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእት እየፈጸመ ነው። የዕብራውያኑ ጸሓፊ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት” (ዕብ. 8፥1-2)። ልብ እንበል! በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ሊቀ ካህናት፣ በዚያው ሁኔታ በሰማይ ያለችውና በእግዚአብሔር የተተከለችው የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው። ወደዚያች የገባውም፣ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት አሁን ይታይልን ዘንድ ነው (ዕብ. 6፥20፤ 9፥24፡28)። ይህም በክብሩ ሆኖ ግብረ ትስብእትን እንደሚፈጽም ያመለክታል።
ከዚህ ቀደም በተከታታይ ለማስገንዘብ እንደ ሞከርነው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃ (ዮሐ. 17፥9፡20-21) እና አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት (ዕብ. 10፥12፡14) ለዘላለም መካከለኛችን ነው። ይህም ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በሰማይ ምልጃና መሥዋዕት ያቀርባል ማለት ሳይሆን፣ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ዛሬም አስታራቂያችንና መታረቂያችን እርሱው ብቻ ነው ማለት ነው። ዛሬ አንድ ኀጢአተኛ ሰው የወንጌልን ቃል ሰምቶ፣ በክርስቶስ አዳኝነት ቢያምንና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቢጸልይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቀውና የኀጢአቱን ስርየት የሚቀበለው፣ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት (በደሙ) አማካይነት ነው። በክርስቶስ ያመነውና በልዩ ልዩ ምክንያት በኀጢአት የወደቀ ክርስቲያንም ንስሓ ሲገባ ስርየተ ኀጢአትን የሚቀበለው በዚሁ መንገድ ነው። በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡት ለዘላለም የመዳን ምክንያት ሆነላቸው ተብሎ የተነገረውም ስለዚህ ነው (ዕብ. 5፥9-10፤ 7፥25)።
ክርስቶስን አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም፤ ወይም የአምላክነቱ ግብር እንጂ የሰውነቱ ግብር ቀርቷል ማለት ያስፈለገው ታዲያ ለምን ይሆን? ብለን መጠየቅ ይገባናል። የምናገኘው ምላሽም ከሁለቱ ውጪ እንደማይሆን እንገምታለን። የመጀመሪያው ‘ክርስቶስ አሁንም መካከለኛ ነው ካልን የሰውነቱን ግብር መግለጻችን ነውና እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል’ ከሚል ሥጋት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ‘ክርስቶስን አሁንም መካከለኛ ካደረግነው እኛ መካከለኛ ያደረግናቸው ቅዱሳን ምን ሊሆኑ ነው?’ የሚል ይመስላል።
ትምህርተ ተዋሕዶ ምን ይላል?[3]
“ክርስቶስ አሁን መካከለኛ አይደለም” የሚለው ኑፋቄ ምንጩ የአውጣኪ ትምህርት መሆኑ ይታወቃል። አውጣኪ በአንዱ በክርስቶስ የቃልና ሥጋ መደባለቅ (ቱስሕት)፣ የሰውነት ወደ አምላክነት መለወጥ (ውላጤ) ወይም መለዋወጥ (ሚጠት) ተከናውኗል ብሎ የተነሣ መናፍቅ ሲሆን፣ እርሱም ትምህርቱም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተወግዘው ከተለዩ ብዙ ምእት ዓመታት ተቈጥረዋል። በእርሱ የኑፋቄ ትምህርት አንጻር ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትምህርተ ተዋሕዶን አምልተውና አስፍተው አስተምረዋል።
የተዋሕዶ ትምህርት “አንቀጸ ተዋሕዶ” እንደሚባል ሊቃውንቱ ያስረዳሉ። ተዋሕዶ ሊገኝ የቻለውም አንቀጸ ተከፍሎን መነሻ በማድረግ ነው ሲሉ ያክላሉ። እንደ ሊቃውንቱ ማብራሪያ የአንቀጸ ተከፍሎ ትምህርት የሚያመለክተው ከተዋሕዶ በፊት የነበረውን የሥግው ቃልን ባሕርያውያን ምንጮችን ነው። ይኸውም ከሁለት ባሕርያተ ልደታት፣ ማለትም ቃል እም ቅድመ ዓለም ከአብ መገኘቱን፣ ትስብእትም ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም አብራክ መገኘቱን (መከፈሉን) ነው። በጥቅሉ የሁለቱም ምንጭና ተረክቦ (መገኘት) የሚታሰበብትን ጊዜ ያሳያል። አንቀጸ ተከፍሎን ፊልክስ ሰማዕት እንደሚከተለው አብራርቷል፤ “ወካዕበ ይቤ ንጠይቅ ክፍላተ ፪ቱ ህላዌያት ወስመ ፪ቱሂ ክፉል በኵሉ ጊዜ በምግባር ወበነገር ዘውእቶሙ መለኮት ወትስብእት። ወሶበ ንቤ ከመዝ ኢይምሰልክሙ ዘንከፍሎ እም ድኅረ ፩ዱ ከዊን ወዳእሙ ናጤይቅ ህላዌ መለኮት ወህላዌ ትስብእት ወዓዲ ነአምር እስመ ቃል አኮ ዘተመይጠ እም ህላዌ መለኮቱ ለከዊነ ትስብእት ሶበ ኀደረ ላዕሌነ። - ዳግመኛ [ቅድመ ተዋሕዶ የነበረ] የሁለቱን ባሕርያት (የመለኮትንና የትስብእትን) ልዩነት፣ የሁለቱም ስም በጊዜው ሁሉ በሥራ በአነጋገር ልዩ እንደ ነበረ እንወቅ፤ እነዚህም መለኮትና ትስብእት ናቸው። እንደዚህም ባልን ጊዜ ከተዋሕዶ በኋላ የምንለየው አይምሰላችሁ፤ የመለኮትን ባሕርይ የትስብእትን ባሕርይ እናስረዳለን እንጂ፤ ዳግመኛም ቃል ባሕርያችንን በተዋሐደ ጊዜ ከመለኮቱ ባሕርይ ሥጋ ወደ መሆን እንዳልተለወጠ እናውቃለን።” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 131)።
“በዚህ መሠረት የአንቀጸ ተዋሕዶ ትምህርት በአንቀጸ ተከፍሎ መሠረት ከጥንት ተለያይተው ከኖሩ ከሁለቱ … የአንዱን የዐማኑኤልን ህላዌ ቅውም አድርጎ የሚያሳይ የምስጢረ ተሠግዎ ወይም የምስጢረ ተዋሕዶ ትምህርት ነው።”[4] ስለዚህ በተከፍሎ የነበሩት ከተወሐዱ በኋላ አንዱን ከሌላው መለየትና እየብቻቸው ማድረግ አይቻልም። ቄርሎስ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ኢትፍልጥ ሊተ እም ድኅረ ትድምርት እስመ ዘፈለጠ እንተ ባሕቲቶ ብእሴ ወእንተ ባሕቲቶ አምላከ ቃለ ክልኤተ ይሬስዮ ለዐማኑኤል። - ከተዋሕዶ በኋላ አትለይብኝ፤ ከተዋሕዶ በኋላ ብቻውን ሰው፥ ብቻውን አምላክ ቃል የሚል ሰው ቢኖር ዐማኑኤልን ሁለት ያደርገዋል።”[5]
የአንጾኪያው ባስልዮስም፣ “አይትከፈል ኀበ ክልኤቱ ህላዌያት እም ድኅረ ተዋሕዶ እስመ ለምንታዌ አእተታ ተዋሕዶ፤ ወተዋሕዶኒ ያግሕሥ ኵነኔሁ ለምንታዌ እስመ ውእቱ ተዋሕዶ አካላዊ ዘኢይትከፈል። - ከተዋሕዶ በኋላ ወደ ሁለት ህላዌያት አይከፈልም፤ ተዋሕዶ መንታነትን አስወግዷልና፤ የመንታነትንም ፍርድ አርቋል። እርሱ የማይከፈል አካላዊ ተዋሕዶ ሆኖአል” ብሏል (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 422)።   
ከእነዚህ ምስክርነቶች ስለ ወልድ ከትስብእትና ከተዋሕዶ በፊት ስለ ነበረው አቋም በአንቀጸ ተከፍሎ ሊነገር እንደሚገባና ከተዋሕዶ ወዲህ ስላለው አቋሙ ደግሞ በአንቀጸ ተዋሕዶ ሊነገር እንደሚገባ እንረዳለን። ምስጢረ ተዋሕዶ የተከናወነው በተለመደውና በሚታወቀው የውሕደት ሕግ ሳይሆን በሕገ ተዐቅቦ ነው። “ተዐቅቦ ማለት በቀላል አገላለጽ መጠበቂያ ማለት ነው። ለምሳሌ መጠበቂያ ያለው ነገር ከተፈለገ፣ ለጊዜው የጠመንጃ ሁኔታ ሊታወስ ይቻላል። ጠመንጃው ጥይት ጐርሶአል እንበል። ነገር ግን በአስፈላጊው ሁኔታና ጊዜ ምላጩ ተስቦ እስኪተኰስበት ድረስ መጠበቂያ ይደረግበታል። መጠበቂያም ስላለው፣ ምላጩን ወይም ቃታውን ሲስቡ፣ ጥይቱ አይተኰስም፤ አይባርቅም። ለዚያውም (ለተኳሹም) ለሌላውም ሰው ጕዳት አያስከትልበትም። መጠበቂያው እንዳይተኰስ ጠብቆታልና። እንግዲህ የመጠበቂያው መኖር በአስፈላጊነቱ መጠን ጠቀመ ማለት ነው።”[6] በምስጢረ ተዋሕዶ ላይ ሕገ ተዐቅቦ ያስፈለገውም ቃልና ሥጋ እንዲጠባበቁ ለማድረግ ነው። “ተዐቅቦ ተራርቀው ይኖሩ የነበሩትን ባዕል፣ ምሉእና ፍጹም የሆነ አካለ ቃልን እና ድኻ፣ ውሱንና ትሑት የሆነ አዳማዊ ትስብእትን አገናዝቦ የሚገኝ” የምስጢረ ተዋሕዶ መጠበቂያ ነው።  
ምስጢረ ተዋሕዶ የተመሠረተው “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ ዐደረ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ነው (ዮሐ. 1፥14)። እንደ ሊቃውንቱ ማብራሪያ በጥቅሱ ውስጥ የምናገኛቸው “ኮነ” እና “ኀደረ” (ሆነ እና ዐደረ) የሚሉት ቃላት ተዋሕዶንና ተዐቅቦን በኅብረት ይዘዋቸዋል። አንዱ ለብቻው ተነጥሎ ማለትም “ኮነ” ለብቻው “ኀደረ”ም ለብቻው የተዋሕዶን ምስጢር ለመጠበቅ አያስችሉም። ስለዚህ ኮነ እና ኀደረ በአንድነት ምስጢረ ተዋሕዶን የሚጠብቁ ቍልፍ ቃላት ናቸው ማለት ነው። ቃላቱ ለተዐቅቦ ሕግ የተወሰኑት ሁለቱን ነጣጥለው በመጠቀም የተዋሕዶን ምስጢር ያፋለሱትን የንስጥሮስንና የአውጣኪን የተሳሳተ ትምህርት ለማረም መሆኑን ከሊቃውንቱ ማብራሪያ እንገነዘባለን።
ንስጥሮስ ምስጢረ ተዋሕዶን ለመግለጽ ኮነን ትቶ ኀደረን ነው የወሰደው። ስለዚህ “ ‘በአንዱ ክርስቶስ ሁለት ህላዌያት አሉ’ እስከ ማለት ደረሰና ውስጣዊ መለያየትን (ቡዓዴን) እና መከፋፈልን (ፍልጠትን) በምስጢረ ተዋሕዶ ላይ አመጣ። ለዚህም የኮነን እውነተኛ ትርጕም ወይም ፍቺ የያዘና ከኀደረ ጋር የሚያገናኝ መጠበቂያ እንዲኖር አስፈለገ። እነሆም ‘ዘእንበለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ዘእንበለ ፍልጠት (ያለመፈራረቅ/ያለመከፈል)፣ በኢተላፅቆ (ያለመነባበር)’ የሚሉ መጠበቂያዎች፣ የኮነን ምስጢር ይዘው “ኀደረ” ያለውን እንዲጠብቁ ተደረገና የሥግው ቃል ተዋሕዶ ተጠነቀቀ። ለዚህ ለንስጥሮስ ንጥል ሐሳብ ተዐቅቦ ባይደረግበት ለተዋሕዶ ትምህርት አደገኛ ይሆናል። የመጻሕፍት አተረጓጐምም ይጥበረበርበታል።”[7]      
ከንስጥሮስ በተቃራኒ አውጣኪም እንዲሁ ምስጢረ ተዋሕዶን የሚያጠፋ ትምህርት አስተማረ። “በአንዱ ክርስቶስ ቱስሕት (መደበላለቅ)፣ ውላጤ (የሰውነት መለወጥ)፣ ሚጠት (መለዋወጥ) እንዳለበት፣ ሰውነቱ ወደ አምላክነቱ እንደ ተለወጠ ተናገረ። አውጣኪ ኀደረን በመተው የኮነን ፍቺ በተሳሳተ አተረጓጐም ተመለከተና ኮነን ‘ተለወጠ’ በሚል ቃል ተርጕሞ ተሳሳተበት። እንደርሱ ዐሳብ ቢሆን የተዋሕዶን ምስጢር ተዋሕዶንም ደመሰሰበት። ለዚህም መጠበቂያ ልጓም አስፈለገ። እነሆም ‘ዘእንበለ ቱስሕት (ያለመደበላለቅ)፣ ዘእንበለ ውላጤ (ያለመለወጥ)፣ ዘእንበለ ሚጠት ያለመለዋወጥ/ያለመመላለስ)’ የሚሉ ቃላት የኀደረን ምስጢር ይዘው የኮነን ፍቺ ወደ ሌላ እንዳይሄድ፣ ይኸውም በመለወጥ እንዳይተረጐም ይጠብቁ ዘንድ ተደረገ። በዚህም ተዐቅቦ የሥግው ቃል ተዋሕዶ ተጠነቀቀ፤ ታወቀ። ይህ ተዐቅቦ ባይኖር የአውጣኪን ግንጥል ዐሳብ ለተከተለ ሰው የተዋሕዶ እምነቱንና በቅዱሳት መጻሕፍት ያለው የአተረጓጐሙን መንገድ ያቃውስበታል።”[8]
በአጠቃላይ ምስጢረ ተዋሕዶን “የምንጠብቀው በእነዚህ ሕጋውያን የውሳኔ ቃላት መጠበቂያዎች /ሕገ ተዐቅቦ/ ነው። ተዋሕዶ ባለበት ሁሉ ተዐቅቦም ዐብሮት ይገኛል።” ስለዚህ በተዐቅቦ በሆነው ተዋሕዶ አንዱ ክርስቶስ ያለመለያየት፣ ያለመፈራረቅ/ ያለመከፈል፣ ያለመነባበር፣ ያለመደበላለቅ፣ ያለመለወጥ፣ ያለመለዋወጥ ወይም ያለመመላለስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑ ከትምህርተ ንስጥሮስና ከትምህርተ አውጣኪ የተለየ የተዋሕዶ ትምህርት ነው።
ምስጢረ ተዐቅቦን በተመለከተ ቄርሎስ፣ “ኢይደልወነ ንፍልጦ ለ፩ዱ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ውእቱ ብእሲ በዐቅሙ ወለእመኒ ነአምሮሙ ለ፪ቱ ህላዌያት በዘዘዚኣሆሙ ወነዐቅቦሙ ዘእንበለ ቱስሕት በበይናቲሆሙ ንብል እንከ ፩ዱ ውእቱ ክመ ኢየሱስ ክርስቶስ። - በዐቅሙ እንደ ዕሩቅ ብእሲ አድርገን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስ ልንለየው አይገባንም፤ ሁለቱን ባሕርያት በየገንዘባቸው ብናውቃቸውም ያለመቀላቀል በየራሳቸው ብንጠብቃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መቸም መች አንድ ነው እንላለን” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 338)።
ዛሬ ትምህርተ አውጣኪን በፊት ለፊቱ ሳይሆን በጀርባው ዞረው የሚያስፋፉት ክፍሎች፣ ምንም እንኳ ክርስቶስ ዛሬም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው ማለታቸው ባይቀርም (በተለይ ሊቃውንቱ)፣ የሰውነቱ ግብር ግን ቀርቷል እንደሚሉ ከላይ ተመልክተናል። ከዚህ የተነሣ “እርሱ አሁን አምላክ ነው” የሚልና ሰው መሆኑንና የሰውነቱን ግብር የሚያደበዝዝ አውጣኪያዊ ትምህርት እየተስፋፋ ይገኛል።
ትምህርተ አውጣኪ የተስፋፋበት ሌላው መንገድ
ትምህርተ አውጣኪ እየተስፋፋ ባለበት መንደር ውስጥ እግዚአብሔር አብን፣ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት” ብሎ መጥራት እንደ ኑፋቄ ይቈጠራል። በዚህ ፈንታ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” ነው የሚባለው። እግዚአብሔር አብ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባቱም አምላኩም ነው። ይህን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ ሐዋርያት፣ ከእነርሱ በኋላ የተነሡ አባቶችም መስክረዉታል። የሚከተሉትን መጽሐፍ ቅዱሳውያን ምስክርነቶችን እንመልከት፤
·         “በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም፥ አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው” (ማቴ. 27፥46)።
·        “ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት” (ዮሐ. 20፥17)።
·        “ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና” (ራእ. 3፥2)።
·        ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዐምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን ዐዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ ዐዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ” (ራእ. 3፥12)።
·        “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (2ቆሮ. 1፥3)።
·        “ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል” (2ቆሮ. 11፥31)።
·        “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (ኤፌ. 1፥3)።
·        “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ ዕድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (1ጴጥ. 1፥3)።
·        “ለወደደን ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኀይል ይሁን፤ አሜን” (ራእ. 1፥5፡6)።

ግሪኩን ሳይሆን ግእዙን መሠረት ያደረገው የሁለት ሺሁ ዓ.ም. ዕትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ፣ በወንጌላትና በራእየ ዮሐንስ ውስጥ ጌታ ከተናገረው በቀር፣ ሐዋርያት የጻፏቸውን እነዚህን ክፍሎች “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” በማለት ነው ያስቀመጠው። ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ እና ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ እግዚአብሔር አብን “አምላኬ” ብሎ የጠራባቸውን ክፍሎች ግእዙም “አምላኪየ” ስለሚል፣ ዐማርኛውም “አምላኬ” የሚለውን አለወጠውም።
·        “በዘጠኝ ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ፥ ‘ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ። ይኸውም፥ ‘አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?’ ማለት ነው” (ማቴ. 27፥46 የሁለት ሺህ ዓ.ም. ዕትም)።
·        “ጌታችን ኢየሱስም፥ ‘አትንኪኝ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄጂና፣ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው’ አላት” (ዮሐ. 20፥17 የሁለት ሺህ ዓ.ም. ዕትም)።
·        “እንግዲህ ተግተህ ሊሞቱ የደረሱትን አጽናናቸው፤ በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም” (ራእ. 3፥2 የሁለት ሺህ ዓ.ም. ዕትም)።
·        “ድል የነሣውን በአምላኬ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ” (ራእ. 3፥12 የሁለት ሺህ ዓ.ም. ዕትም)።
ከሐዋርያት በኋላ የተነሡ አበውም ይህን ትምህርት ተቀብለው ለእኛ አስተላልፈውልናል። ኤጲፋንዮስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አብን አባቴና አምላኬ ማለቱን ጠቅሶ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “እግዚአብሔር አብ ውእቱ አቡሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በህላዌ መለኮቱ … እግዚአብሔር አብ አምላኩ ለወልድ ውእቱ በእንተ ትስብእቱ። - እግዚአብሔር አብ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርየ መለኮቱ አባቱ ነው። ... ሰው ስለ ሆነ ለወልድ እግዚአብሔር አብ አምላኩ ነው።” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 177)።
ዮሐንስ አፈ ወርቅም እንዲሁ ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር አብን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ማለቱን፣ ጌታችን ራሱም አብን አባቴ እና አምላኬ ማለቱን ጠቅሶ ይህን ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል። “ይቤ ወአፍቅሮተክሙ ኵሎ ቅዱሳነ አኮ ለእለ ይነብሩ ምስሌሁ ባሕቲቱ አላ ለኵሉ ይቤ ኢያንተጉ አእኵቶቶ  በእንቲኣክሙ ወእዜከረክሙ በጸሎትየ ከመ አምላኩ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አበ ስብሐት የሀብክሙ መንፈሰ ጥበብ። ናሁ ውእቱ ሰመዮ ለአብ አምላኮ ለክርስቶስ ቦኑ የሐጽጽ ክርስቶስ ወልድ ስብሐተ እም አቡሁ ሐሰ ወአልቦ መኑሂ እቡድ ዘይትሀበል፣ … ወባሕቱ ውእቱሰ አዖቀ በዝንቱ እስመ ክርስቶስ ኮነ ዘበአማን ሰብአ ከማሁ ዓዲ ሶበ ተንሥአ ከሠተ ትሥጉቶ ዘነሥኦ እም ዝንቱ ፩ዱ ልሕኵት ወእም ቅድመ ዕርገቱ ኀበ አብ ዘኢተፈልጠ እምኔሁ ግሙራ ይቤ ለአርዳኢሁ አምላኪየ ወአምላክክሙ ከመ ሶበ ሰምዑ ዘንተ ኢየኀልዩ እስመ ትስብእት ባሕቲቱ ተናገረ ዘንተ ዳእሙ ለሊሁ እግዚአብሔር ቃል ዘኮነ ሰብአ አኀዘ ወይቤ አዐርግ ኀበ አቡየ ወእም ድኅረዝ ይቤ አምላኪየ።  
ትርጓሜ፦ “ምእመናንን ሁሉ መውደዳችሁን አለ። በኤፌሶን ከእርሱ ጋር ያሉትን ብቻ አይደለም፤ በሃይማኖት ለሚመስላቸው ሁሉ አለ እንጂ። ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ማመስገን አልተውሁም አለ፤ የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት (በግእዙ መሠረት አምላክ መባል ነበረበት ‘ከመ አምላኩ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ’ ነውና ያለው) እግዚአብሔር አብ ዕውቀት የሚሆን ሀብትን ይሰጣችሁ ዘንድም በምጸልየው ጸሎት አስባችኋለሁ አለ። እነሆ እርሱ ጳውሎስ አብን አምላኩ ለክርስቶስ (የክርስቶስ አምላክ) አለው። በውኑ ወልድ ክርስቶስ በክብር ከአባቱ ያንሳልን? ከአብ አያንስም፤ ደፍሮ ይህን የሚናገር ማንም ሰነፍ የለም። … ነገር ግን እርሱ በዚህ ክርስቶስ በእውነት ሰው የሆነ እንደ ሆነ አስረዳ። ዳግመኛም በተነሣ ጊዜ ከዚህ ከአዳም ባሕርይ ሰው መሆኑን አስረዳ፤ ፈጽሞ ከእርሱ ወደ አልተለየው ወደ አብም ከማረጉ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ አምላኬ አምላካችሁ አለ፤ ይህን በሰሙ ጊዜ ይህን የተናገረ ሥጋ ብቻ እንዳይመስላቸው ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ አቡየ (አባቴ) ብሎ ከዚያ በኋላ አምላኪየ (አምላኬ) አለ” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 248)።
ዛሬም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው ካልን፣ ከትሣኤና ከዕርገት በኋላም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑ እንዳልተለወጠ ከተረዳን፣ እርሱ እግዚአብሔር አብን አባቴ እና አምላኬ ብሎ መጥራቱ፣ ሐዋርያትም “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት” ብለው እግዚአብሔር አብን መጥራታቸው ተገቢ እንጂ ስሕተት አይደለም። እርሱም ሐዋርያትም ይህን ያሉት ደግሞ ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል። እግዚአብሔር አብ፣ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ አምላኩ ነው። ከተዋሕዶ በፊት ቃል ከዘላለም በነበረው ባሕርያዊ ልደት ወይም በአምላክነቱ ደግሞ እግዚአብሔር አብ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አብን አምላኬ ሲል፣ ሐዋርያትም አብን አምላኩ ሲሉ የምንገነዘበው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን ነው። ደግሞም አባቴ ሲልና አባቱ ሲሉ የምንረዳው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆኑን ነው። ስለዚህ አምላኬ እና አምላኩ የሚሉት ሰው መሆኑን ሲያጠይቁ፣ አባቴ እና አባቱ የሚሉት ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከሉንና አምላክ መሆኑን ያመለክታሉ (ዮሐ. 5፥17-18)። ይህን እውነት መቀበል እንጂ ይህን እውነት ማሻሻል አይቻልም፤ “ከእግዜር ወዲያ ፈጣሪ ከባለቤቱ በላይ መስካሪ” ማን ሊመጣ!
ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅም በድርሳኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብን አምላኬ ያለበትን ምክንያት ራሱን ጌታችን ኢየሱስን ተናጋሪ አድርጎ በዚህ መልክ አቅርቦታል። “ይብል እስመ አነ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ ወአነ ፩ዱ ውእቱ አነ እብል ዘንተ ወዝክተሂ እስመ ተወከፍኩ ኵሎ ዘእጓለ እመ ሕያው ዘአልቦቱ ኀጢአት ይብል አንሰ ነሣእኩ ዘበአማን ትስብእተ ወከመዝ ጸዋዕክዎ ለአቡየ አምላኪየ ዘከመ ይደሉ ለሥርዐተ ትስብእት ዘረሰይክዎ ፩ደ ምስሌየ።”
ትርጓሜ፦ “እኔ ሰው የሆንኩ አምላክ ነኝና፣ እኔም አንድ ነኝና ይህንም ያንም እኔ እላለሁ ይላል። የሰውን ባሕርይ ገንዘብ አድርጌአለሁና፤ ኀጢአት የሌለበት እርሱ እኔ ነፍስን ሥጋን በእውነት ተዋሕጄአለሁና ከእኔ ጋር አንድ ላደረግሁት ለሥጋ ሥርዐት እንደሚገባ እንዲህ አባቴን አምላኪየ ብዬ ጠራሁት” አለ ይለናል (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 248)።
ይህን ነጥብ ያነሣነውና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት” የሚለውና የክርስቶስ ማንነት መግለጫ የሆነውን ሐረግ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” በሚለው መተካቱን የተቃወምነው በከንቱ አይደለም። እግዚአብሔር አብን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ብቻ ብሎ መጥራት፣ ኢየሱስ ዛሬ አምላክ ብቻ ነው እንጂ ሰው አይደለም የሚል ፍቺ ስለሚሰጥና ትምህርቱም ወደ አውጣኪ ትምህርት ስለሚሄድ ነው። ትምህርቱ ወደዚህ መንደር ያደረሳቸው ክፍሎችም፣ “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” የሚለውን ጥቅስ በተዛባ መንገድ በመጥቀሳቸውና ክርስቶስ አሁን አምላክ ብቻ ነው በማለታቸው ሥጋታችን ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዉልናል።  
ጥቅሱ ምን ይላል?
“ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ. 5፥16)። ጥቅሱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ሌላ ሐሳብ ይዞ ላነበበውና ላይ ላዩን ለተመለከተው ሰው፣ ‘ክርስቶስ አሁን ያለው በሥጋ አይደለም በአምላክነት ብቻ ነው የሚገኘው’ የሚል ይመስላል። እንዲህ ማሰብ ግን ስሕተት ነው። ጥቅሱ ክርስቲያኖችንም ክርስቶስንም የተመለከተ ሐሳብ አለው።
“ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም” የሚለው የሚያመለክተው ክርስቶስን ሳይሆን በክርስቶስ የሆነውን (ያመነውን) ክርስቲያን ነው። ቍጥር 14 እና 15 ላይ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” እንዲሁም ቍጥር 17 ላይ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን ዐዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም ዐዲስ ሆኖአል” የሚሉት ሐሳቦችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። በእነዚህ ቍጥሮች የተገለጸው ሐሳብ ክርስቶስ የሞተበትን ዐላማ፣ ማለትም ምእመናን ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው ለክርስቶስ ይኖሩ ዘንድ እንደ ሞተ ይናገራል። ሰው በእርሱ ሲያምንም የቀደመው በኀጢአት የመመላለስ ኑሮው እንደሚለወጥና ዐዲስ ፍጥረት እንደሚሆን ያስረዳል። ይሁን እንጂ ክፍሉ በክርስቶስ ስለሚገኘው ዐዲስ ሕይወት እንጂ ሰው ሥጋ መሆኑ ቀርቶ ወደ ሌላ ማንነት ስለ መለወጡ የሚናገር አይደለም። በእነዚህ ቍጥሮች መካከል የሚገኘውን ቍጥር 16ን ለብቻው ነጥሎ በመምዘዝና በዐውዱ መሠረት ሳይሆን በራስ መንገድ ለመፍታት መሞከር፣ የራስን ስሕተት ለጊዜው ለመሸፈን ካልሆነ በቀር ለሌላ አይረዳም።
“ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” የሚለው ንባብ የሚያመለክተው ክርስቶስ አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ያለው በዚህ ምድር በነበረበት ሁኔታ አለመሆኑን ይጠቍማል። ርግጥ ነው፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ ኀጢአት የሌለበትና ኀጢአትን ያልሠራ ፍጹም ሰው ነው። ከትንሣኤው በኋላ በእርሱ ዘንድ ዐዲስ የሆነው ነገር ታዲያ ምንድን ነው? እንደ ቀድሞው የሆነውን ግብረ ትስብእትን ማለትም፦ መብላት፣ መጠጣት፣ መድከም፣ ማንቀላፋት፣ በማያስፈልገውና ሕማምና ሞት በማያገኘው መንፈሳዊ አካል ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ ነው፤ እንዲህ ማለት ግን ሰውነቱ ቀርቷል ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ያለው ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ነው።
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት ክርስቶስ ኢየሱስ በለበሰውና በትንሣኤ በተለወጠው ሥጋ እንዳረገ ተመልሶ በዚሁ ሥጋ ይመጣል (ሐ.ሥ. 1፥11)። “የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ በእርሱ ያመንን ሁላችንም ወደ ፊት እርሱ የለበሰውን ያን መንፈሳዊ አካል እንለብሳለን (1ቆሮ. 15፥46)። “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኀኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” (ፊል. 3፥18-21)።  
ያለ ዐውዱ “ክርስቶስ ከትንሣኤና ከዕርገት በኋላ ሰው መሆኑ ቀርቷል” ለማለትና መካከለኛነቱን ለማስተባበል የተጠቀሰው ጥቅስ መልእክት እስካሁን የተመለከትነውን ይመስላል። ጥቅሱ በክብር የሆነውን የክርስቶስን መካከለኛነትም ሆነ ሰው መሆኑን ይመሰክራል እንጂ አያስተባብልም።

ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 45 ላይ የቀረበ


[1] የኢኦተቤክ መሠረተ ሃይማኖትና የካህናት ተልእኮ 1982፣ ገጽ 28
[2] መጽሐፈ ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ 1984 ገጽ 73
[3] በዚህ ነጥብ ሥር ለተነሣው ሐሳብ የተሰጠው ማብራሪያ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስተዋፅኦ” የተሰኘውን የአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብን ያልታተመ ጽሑፍ መሠረት ያደረገ ነው።
[4] መሠረት ስብሐት ለአብ የቤተክርስቲያን ታሪክ አስተዋፅኦ ገጽ 51 ያልታተመ
[5] ዝኒ ከማሁ
[6] ዝኒ ከማሁ
[7] ዝኒ ከማሁ
[8] ዝኒ ከማሁ

No comments:

Post a Comment