Thursday, January 2, 2014

መሠረተ እምነት

Read IN PDf

(ከነቅዐ ጥበብ)

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ለተሰኘበት ኩነቱና ወልድ ለተሰኘበት ልደቱ ተስማሚ በሆነው በመልእክተኛነት (ተፈናዊነት) እና በታዛዥነት ሥራ መደብ ተገልጾ አባቶችንና የእስራኤልን ሕዝብ በሥጋ ወደሚገለጽበት ጊዜና ስፍራ እስኪያደርሳቸው ድረስ በመንገድ መሪነትና በጠቅላይ ጦር አዛዥነት ሲሠራ (ዘፀ. 23፥20፤ 33፥14-16፤ ኢያ. 5፥13-15፤ 1ሳሙ. 17፥45) የመልአከ እግዚአብሔርን ምስያ፥ አርኪ ውሃን በማፍለቅ የዐለትን ምስያ በመንሣት (ገንዘብ በማድረግ 1ቆሮ. 10፥4) መርቷቸው የነበረ መሆኑን ባለፉት ዕትሞች (ጮራ ቍጥር 6 እና 7 አንብበናል፡፡

ከዚህም ጋር በማያያዝ በእስራኤል ሕዝብ መሪነት የተገለጸው መልአክ ፍጡር መልአክ ሊቀበለው የማይገባውን ስግደትን፥ አምልኮትን፥ ውዳሴን፥ የመቀበል መብት ያለው ኤል፥ (አምላክ - መለክ) ይሆዋ፤ (የነበረ ያለና የሚኖር) ኤልሻዳይ፥ (ሁሉን የሚችል የሚሳነው የሌለ) የሆነ መለኮታዊ ባለ ሥልጣንነቱን የሚያስጨብጡ ጥቅሶችን ማንበባችንን እናስታውሳለን (ዘፍ. 17፥1፤ 28፥1-4፤ 35፥9-15፤ ዘፀ. 3፥13-15፤ 6፥2-8)፡፡ ዛሬም በመቀጠል ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ቃልና ጥበብ የሆነበትንና የተባለበትን ኩነቱንና የባሕርያዊ ግብሩን መግለጫ በጥቂቱ እንመረምራለን፡፡


ወልድ የአብ ባሕርያዊ ቃል
አርዮሳውያን ስለ ወልድ ቃል መሆን ሊያስተምሩን ሲጀምሩ፥ ወልድ አብ የሚናገርበት ባሕርያዊ ቃሉና ዓለምን የፈጠረበት ባሕርያዊ ጥበቡ እንዳልሆነ በድፍረት ይናገራሉ፡፡ በሹመት ቃለ ዐፄ (ቀላጤ) ሆኖ የተሾመ ፍጡር መልአክም ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም እነርሱ ይላሉ እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱስ አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስስ ባሕርያዊ ጥበቡና ቃሉ፥ ሐሳቡ (ኅሊናሁ) ዕውቀቱ፥ ማስተዋሉ፥ ችሎታው… እንደሆነ ያስተምረናል፡፡

የሚታየውና የማይታየው ሁሉ የተፈጠረበት ባሕርያዊ ቃል
ይሆዋ ሁሉን የፈጠረው በቃሉ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ፥ ስለ ቃሉ ማንነትና ህላዌው (አኗኗሩ) ዝርዝር መግለጫ ያቀርብልናል፡፡ “ቃል አስቀድሞ ወይም በመጀመሪያ ነበረ” በማለት ለህላዌው ጅማሬ እንደሌለው ያስተምረናል፡፡ “አስቀድሞ ወይም በመጀመሪያ” የሚለውንም ቃል በኦሪት ዘፍጥረት 1፥1 እናገኘዋለን፡፡ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል፡፡ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን መፍጠር የጀመረበትን ጊዜ “መጀመሪያ” ይለዋል፡፡ ይህ የጊዜ መግለጫ ይሆዋ፥ ፍጥረትን መፍጠር እንደጀመረ ከማስረዳቱ በቀር መቼውንም ቢሆን፥ ይሆዋ መኖር የጀመረበት ጊዜ ነው ተብሎ ጤነኛ አእምሮ ባለው ሰው ዘንድ ታስቦ አያውቅም፡፡ እግዚአብሔር የሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ የሚመሰክር ግልጽና ቋሚ ማስረጃ ነውና (ኢሳ. 41፥4)፡፡

ይሆዋ “የነበረ ያለና የሚኖር” በሚል ስም ራሱን ማስተዋወቁ፥ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፥ እርሱስ በማን ተፈጠረ? የሚለውን ጥያቄ ሊያስነሳ ይችል የነበረውን የተጠራጣሪውን ሰው ልብ ያነጻል፤ ያንጻልም (ዘፀ. 3፥13-16)፡፡ ስለዚህ በጊዜ ሊገለጽ ከማይችል፥ መነሻ ከሌለው ከዘላለም ጀምሮ በፈጣሪነት፥ በአምላክነት፥ በሁሉን ቻይነት፥ በጌትነት … የኖረ ይሆዋ በወደደ ጊዜ፥ ባቀደው ሰዓት ሰማይንና ምድርን በመጀመሪያ ፈጠረ፡፡ “መጀመሪያ” የሚለውም ቃል ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር መፍጠር መጀመሩን ለማመልከት ገባ እንጂ የፈጣሪን መኖር ጅማሬ የሚያመለክት አገባብ የለውም፡፡

እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በመፍጠር ጀመረ፡፡ ሰማይና ምድርም የተፈጠሩት በእግዚአብሔር ቃል ነበረ፡፡ “ይሁን” እያለ በመናገር እያንዳንዱን ፍጥረት ፈጠረ፤ አስገኘ፡፡ “ሁሉ በእርሱ (በቃል) ሆነ እንጂ ያለእርሱ የሆነ የለም፡፡” (መዝ. (33)፥6፤ 144፥4፤ ዮሐ. 1፥3)፡፡

ይሆዋ ሁሉን የፈጠረበት ቃልም “ወልድ” እንደ ሆነ፥ እርሱም በሥጋ እንደ ተገለጸ መጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ ማስረጃ ይሰጣል (ዮሐ. 1፥14፤ 1ዮሐ. 1፥2፤ 4፥9)፡፡ ሰማያትና ምድር፥ በውስጣቸውም ያሉ ፍጥረታት ሁሉ የተፈጠሩበት ቃል የአብ ባሕርያዊ ቃል ነው፡፡ አርዮስና ተከታዮቹ ግን እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረበት ቃል አንድ ቀን የፈለሰፈው የፍጥረት ማምረቻ መሣሪያ እንደ ሆነ አስመስለው አቀረቡ፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳችን፥ “እግዚአብሔርም ይሁን አለ፥ ሆነም” ይለናል (ዘፍ. 1፥3-24)፡፡ “አለ” ማለት ተናገረ፤ ትእዛዝ ከአፉ ወጣ፥ እንዲሆን የፈለገው ይሆን ዘንድ በባሕርያዊ ማናገሪያ ቃሉ አዘዘና አደረገ ማለት ነው፡፡ እርሱ “ይሁን አለ ሆነም” ተናግሮአልና ሆኑ፤ እርሱ አዘዘ ጸኑም (መዝ. (33)፥9) ማለትም የመፍጠሪያ መሣሪያ ሠራ ከማለት፥ ወይም በፈለሰፈው የማምረቻ መሣሪያ ማምረት ቀጠለ ከማለት ጋር በፍጹም የተራራቀ ነው፡፡

አርዮሳዊ ሆይ! “እርሱ አዘዘ፤ እነርሱም ተፈጠሩ” በማለት ይሆዋ እያዘዘ ፍጥረታትን ወደ መኖር ያመጣበትን ንግግር ያፈለቀውን መናገሪያ ቃሉን የተፈጠረ ማምረቻ መሣሪያ ነው ብትለን፥ አንተ ሰይጣን እግዚአብሔር ይገሥጽህ! እንልሃለን፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ እንደ ምሳሌው ለባዊ፥ ነባቢ፥ ሕያው አድርጎ ሠርቶናልና፥ ፍጥረታትን የፈጠረበት ቃሉ ከይሆዋነቱ ክልል ውጪ የሆነ አንድ ቀን የተፈጠረ ነው ብትለን አንቀበልህም፡፡ ፍጥረትን ያስገኘው ትእዛዝ የወጣው ከአፉ፤ ከመናገሪያ ቃሉ ነውና፤ ቃሉም በእኔነቱ ክልል ያለ የይሆዋነቱ ምልዐት ነውና ተሳስተህ፥ አታሳስት፡፡

ይሆዋ ያለ ባሕርያዊ ቃል አልኖረም
ይሆዋ ቃልን መናገር የማይችል፤ ቃል የለሽ (ኢነባቢ) አልነበረም፤ እንደዚህ የሆነበት ጊዜ ፈጽሞ የለም፡፡ በሚናገርበት ባሕርያዊ ቃሉ ፍጥረታትን ፈጠረ እንጂ ከባሕርየ መለኮቱ ክልል ውጪ በሆነ ማምረቻ እንዳልፈጠረ ከላይ ተመልክተናል፡፡ ወልድም ቃለ እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር ከዘላለም እንደ ነበረ ሁሉ ነባቢ የሆነበት (የተሰኘበት) ቃሉም በመጀመሪያ በእርሱ ዘንድ ነበረ (ዮሐ. 1፥1)፡፡

ይሆዋ ለባዊ፥ ነባቢና ሕያው ነው፡፡ ያስባል፤ ያውቃል፤ ያቅዳል፤ ያስተውላል፣ ይሠራል፡፡ የዚህንም እውነት በእኛና በፍጥረተ ዓለም መፈጠርና መኖር ይበልጥ እንረዳዋለን፡፡ ቀና ብለን ሰማይን፥ ጎንበስ ብለን ምድርን፤ ተዟዙረን አካባቢያችንን ከቃኘን በኋላ የምንደርስበት የዕውቀት ጭብጥ አለ፡፡ ይህን ሁሉ የፈጠረ ይሆዋ፦ አንደኛ፥ ሁሉን ቻይ እንደ ሆነ፥ ሁለተኛ፥ በዕቅድ እንደሚሠራ በተፈጠረው ፍጥረት ላይ በፊደል ሳይሆን በመንፈስ የተጻፈውን እናነባለን፡፡ የእያንዳንዱም ዕለት ድምፅ የለሽ ንግግር ስለዚህ ብዙ ያስተምረናል (መዝ. (19)፥1-6፤ 147፥8-18፤ ሮሜ 1፥20)፡፡ ይሆዋም የሚያስብበት፥ የሚያሰላስልበት፥ የሚያቅድበት፥ የሚሠራበት ቃሉ፥ ዕውቀቱ፥ ማስተዋሉ፥ ችሎታው፥ … በይሆዋነቱ ክልል የነበረ፥ ያለና የሚኖር ነው፡፡ “እኔ እግዚአብሔር… ነኝ” እያለ በዘመናት ውስጥ ራሱን በቃሉ ሲገልጥና ሲያስተዋውቅ ኖሯልና (ዘዳ. 32፥39-40፤ ኢሳ. 43፥11-13፤ 44፥6)፡፡

ስለሆነም እኔ የሚልበትን ቃል አንድ ቀን ከአንድ ስፍራ አላገኘውም፤ ወይም ከፍጥረታት እንደ አንዱ ከፈጠረው በኋላ መናገሪያ ቃል በማድረግ አልሾመውም፡፡ ቃሉ ራሱ ይሆዋ ነውና (ዮሐ. 1፥1)፡፡ ይሆዋም ያስባል፥ ያቅዳል፥ … ማለትን ጕልሕና ተአማኒ የሚያደርገው ሐሳቡ፥ ዕቅዱ፥ ቃል መሆኑና በቃል የመገለጡ ማስረጃ ነው፡፡ ለማንኛውም ሕያውና ጤነኛ ሰው የቃል ባለቤትነት ትርጉም ያለው ሆኖ የሚገኘው መጀመሪያ ለራሱ ለቃሉ ባለቤት፥ ሁለተኛ ሐሳቡ ለሚነገረውና ለሚያደምጠው ሌላ ሰው ይሆናል፡፡

ይህስ እንዴት ነው ቢባል፥ አንድ ሕያውና ጤነኛ ህልው ቢያስብ፥ ቢያሰላስል፤ ዕቅድ ቢያወጣ፤ ፕላን ቢነድፍ፥ ሥዕል ቢሥል … የሕያውነቱ ክፍል በሆነ ቃሉ፥ ዕውቀቱ፥ ጥበቡ፥ ችሎታው እንደ ሆነ አያጠራጥርም፡፡ የሚያስብበት፥ የሚያሰላስልበት፥ ዕቅድ ያወጣበት፥ ፕላን የነደፈበት፥ ሥዕል የሣለበት፥ … ጥበብ፥ ችሎታ … በቃል አማካይነት ከአፉ ባይወጣም በልቡ የሚኖር ቃል ነው፡፡ ይህ ሰው መጀመሪያውኑ ሊሠራ ያሰበው የቃል ቅርፅና ትርጉም ያለው ስለሆነ ለራሱ ይረዳው ነበር፡፡ ከሠራው በኋላም ሥራውን ያየው ሰው ቃል ባይተነፍስም አንብቦ ይረዳለታል፥ ሥራው የቃል ትርጉም ያለው ጥበብ ነውና፡፡

አዎን፥ ጤነኛ ሰው፥ ሕልምን ቢያልም እንኳ በቃል ቅርፅ ነፍሱ ተረድታው ነበርና ከነቃ በኋላ ሕልሙ ተቀርፆ በነበረበትና ለራሱ በተረዳበት ቃሉ ሕልሙን ሊናገርና ሊያስረዳ ይችላል፡፡ ሥዕልም ሆነ ፕላን፥ ሌላም ሐሳብ ቢሆን ገና በሐሳብ፥ በጥናት፥ በዕቅድ ደረጃ በልቡ (በአእምሮው) ያለውን በአእምሮው (በልቡ) እንዳለው አድርጎ ሊቀርፀው ወይም እንደ ፈለገው በሥራ ሊተረጕመው ይቻለዋል፡፡ የተሣለውን፥ የተነደፈውንም ሆነ የተቀረፀውን፥ ወይም በሥራ የተተረጐመውን በማየት ተመልካች ሊያነበውና ትርጉሙን ሊረዳው ይችላል፡፡

እንግዲህ ይሆዋ ዐሰበ፥ ዐቀደ፥ ሠራ፥ ተናገረ ቢባል፥ ሐሳቡ፥ ዕቅዱ፥ ዕውቀቱ፥ ጥበቡ፥ ማስተዋሉ … ትርጉም ያለው ባሕርዩ የሆነ ችሎታው እንደ ሆነ መናገራችን ነው፡፡ ከዚህ የተነሣም የይሆዋ ሐሳቡ፥ ዕውቀቱ፥ ጥበቡ፥ ማስተዋሉ ትልቅ ነው፤ አይመረመርም፤ ተብሎ የሚገለጸው እኮ የቃል ትርጉም ስላለው ነው! የተዘበራረቀ፥ የተምታታ፥ ትርጉም የሌለው ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የማይታይ ሐሳቡ፥ ዕቅዱ፥ ዕውቀቱ፥ ጥበቡ፥ ማስተዋሉ … ምን ያኽል ጥልቅና ከምርምር በላይ ሆኖ ሳለ መጠኑ በሚታየው ሥራውና ፍጥረቱ ይታወቃል፥ ይነበባልም (ኢሳ. 40፥26፤ ሮሜ 1፥20-21)፡፡

ወልድ የይሆዋ ጥበብ የሆነው እንዴት ነው?

እንደ አርዮስ አመለካከት ሐሳብ፥ ዕቅድ፥ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ጥበብ ማለት የሚታይ፥ ሥራ (ፍጥረት) ማለት ነው፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ የይሆዋ ሐሳብ፥ ዕቅድ፥ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ጥበብ … እየተባለ በከፍተኛ አድናቆት የሚጠራው

1.      የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታትን፣
2.     እነዚህንም የሚመራበትንና የሚቈጣጠርበትን ኹለንተናዊና ክልላዊ ሕገ ተፈጥሮ፣
3.     ቅንብራዊና ሥነ ሥርዐታዊ እንቅስቃሴን መሠረት በማድረግ ፍጥረታት ለተፈጠሩበት ዐላማ የመሳሰለውን ሁሉ የፈለሰፈበትንና ወደ መኖር ያመጣበትን ባሕርያዊ ጥበቡን እንደ ሆነ እናስተውላለን፡፡

ለምሳሌ አንድ ተመራማሪ በሐሳቡ፥ አወጣ፥ አወረደ፥ ዐቀደ፥ በሞዴል አስተካከለ፤ ከዚያም መኪና ፈለሰፈ፥ ሠራና አሳየ፡፡ እንደ አርዮስ ያለ ሰው ጥበብ የሚለው የተፈለሰፈውን መኪና ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጥበብ የሚለው ፈልሳፊው መኪናውን ለመሥራት የበቃበትን የባሕርይ ገንዘቡ የሆነውንና በእኔነቱ ክልል ያለውን ሐሳቡን፥ ዕቅዱን፥ ችሎታውን ነው፡፡

ይሆዋ በጥበቡ፥ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋሉም ሰማያትን አጸና፥ በዕውቀቱ የተሠሩ ቀላያት ደመናትን፥ ደመናት ጠልን እንዲያንጠባጥቡ አደረገ (ምሳ. 3፥19-20)፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር ጥበብ፥ ማስተዋል ማለትም፥ ምድር፥ ሰማያት፥ ቀላያት፥ ደመናት አይደሉም፡፡ እነዚህን የሠራባቸው ባሕርያዊ ችሎታው እንጂ ምድር፥ ሰማያት፥ ቀላያት፥ ደመናትን የመሳሰሉት ፍጥረታትማ የሚያልፉ፥ የሚጠፉ፥ የጥበቡ የሥራ ውጤቶች ናቸው፤ በእኔነቱ ክበብ ያሉ የባሕርያቱ ምልአቶች ግን አይደሉም (ኤር. 10፥10-12)፡፡

እንደዚህም ስለ ሆነ የይሆዋ ጥበቡ፥ ዕውቀቱ፥ ማስተዋሉ፥ ችሎታው ጥልቅ ነው፤ አይመረመርም ሲባል (ሮሜ 11፥34-35) የፈጠራቸውን ፍጥረታት ማለቱ አይደለም፡፡ እነዚህንማ ሰው የችሎታውን ያኽል ይመረምራቸዋል፡፡ የማይመረመረው ፍጥረታትን የፈጠረበት፥ በእኔነቱ ክልል ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ፥ ማስተዋል፥ ዕውቀት፥ ችሎታ ነው (ኢሳ. 40፥12-26፤ ሮሜ 16፥27)፡፡ ከዚህም የተነሣ የባሕርይ ዕቅዱ፥ ሐሳቡ ጥበቡ ያስገኛቸው ፍጥረታት የፈጣሪያቸውን ጥበበኛነት በማመልከት እንድናደንቅ እንድንወድስ እንድንዘምር ያነሣሡናል፡፡ በእያንዳንዱም ፍጥረት ውስጥ የፈጣሪ ጥበብ ይታያልና (ኢዮ. 9፥1-10፤ መዝ. 8፥1-9፤ 139፥1-18)፡፡ የይሆዋ ጥበብማ በተፈጠሩት ፍጥረታት አይወሰንም፡፡ በመፍጠር ለተገለጸውና ላልተገለጸው ባሕርያዊ ለሆነው ሐሳቡ፥ ዕውቀቱ፥ ጥበቡ፥ ማስተዋሉ ወሰንና ድንበር የለውም፡፡ ቢሆንም ይሆዋ በባሕርዩ ካለው ከማይወሰነው ከማይሰፈረውና ከማይቈጠረው ጥበባዊ ምስጢር … በወሰነው ጊዜ ልንረዳው በምንችለው አቅማችን መጠን ጥቂት ብልጭታ ይገልጽልናል (ሮሜ 8፥28-30፤ 16፥25-26፤ 1ቆሮ. 2፥6-16፤ ኤፌ. 1፥8-10፤ 3፥1-12፤ ቈላ. 1፥24-29)፡፡

እንግዲያውስ የይሆዋ ሐሳብ፥ ዕቅድ፥ ጥበብ፥ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ችሎታ … እኛ ያወቅነው ፍጥረት እንዳይደለ፥ ነገር ግን በይሆዋነቱ የመለኮት ክልል (በእኔነቱ) ያለ የማይወሰነው የማሰብ፥ የማቀድ፥ የመፍጠር የተፈጠረውንም ፍጥረት የማስተዳደር ችሎታው እንደ ሆነ እናስተውላለን፡፡

ይህም ዓለምን በመፍጠር፥ በማስተዳደርና ሰውንም በማዳን የተገለጸው የይሆዋ ሐሳብ (ኅሊናሁ ለአብ) ዕቅዱ (ምክሩ)፥ ዕውቀቱ፥ ማስተዋሉ (አእምሮቱ) ኀይሉ፥ ጥበቡ፥ ቃሉ፥ የማኑ፥ እደ መዝራእቱ፥ እየተባለ የተነገረለት ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ሳሙ. 2፥3፤ መዝ.(104)፥24፤ (118)፥15፤16፤ (139)፥5፤9፤10፤ ኢሳ. 14፥24-27፤ ኤር. 10፥12)፡፡ በእርሱም የተፈጠረውን የጥበብ ውጤት ፈጣሪ በሆነው በይሆዋ ዘንድ ካለው በፍጥረት ከተገለጸው ባሕርያዊ ጥበቡ ለይተን የምናይበትን ማስተዋል ይስጠን፡፡

በሰው ደረጃ እንኳ ብናስተያየው፥ የሰው ሐሳብ፥ ዕውቀት፥ ጥበብ፥ ማስተዋል፥ ዕቅድ የነፍሱ ባሕርያዊ ችሎታ እንደ መሆኑ መጠን የነፍሱ ለባዊትነት፥ ነባቢትነትና፥ ሕያዊትነት የቆመበት፥ የጸናበትና የሚታወቅበት እኔነቷ ነው እንጂ፥ ነፍስማ አንድ ቀን የፈጠረችው ፍጥረቷ ነው ልንል አንችልም፡፡ በዚህ በእኔነቷ ዐስባ አውጥታ አውርዳ ተጠብባ የፈለሰፈችው የሥራ ውጤቷ ሲሆን ብቻ ፍጥረቷ ነው ሊባል ይችላል፡፡

የይሆዋ ጥበብ ዕውቀት … ከሰው ችሎታ በላቀና በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለይ ይታወቃል፡፡ ሰው ያሰበውን ደጋግሞ ቢያስብበት ወይም ያሰበውን በሥራ ላይ ሲያውለው በሂደት ስሕተት ስለሚያገኝበት ሊያርመው፥ ሊያሻሽለው፥ ሊለውጠው ይችላል፡፡ የይሆዋ ዕውቀት፥ ችሎታ፥ ጥበብ … ፍጹም ነው፡፡ ገና ሲያስብ፥ ሲያቅድ … መጀመሪያውንና መጨረሻውን ያውቀዋል፡፡ የሁሉም ነገር ጅማሬውም፥ ፍጻሜውም እርሱ ነውና (መዝ. (33)፥10-11፤ ኢሳ. 46፥10፤ ማቴ. 25፥34፤ ኤፌ. 1፥4-5)፡፡ እንዲህ ስለ ሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ የመፍጠሪያ ቀን የተፈጠረውን ፍጥረት ሲገመግም፥ “እነሆ መልካም ሆነ” በማለት ሁሉ እንደ ወደደው እንዳቀደው የሠመረ ሆኖ እንደ ተገኘ ይነግረናል (ዘፍ. 1፥4፡10፡12፡18፡21፡25፡31)፡፡

ከዕውቀቱ ፍጹምነትና ከጥበቡ ምሉእነት፥ ከኀይሉም ታላቅነት የተነሣ ትእዛዝ ከአፉ ሲወጣ፥ ፍጥረት እንዲሆን በወደደው ፍጹምነት መጠን በአንድ ቅጽበት ስለሚፈጠር አስቀድሞ መንደፍን፥ ማሻሻልን፥ ማረምን፥ ማስተካከልን፥ በሞዴል የጥናቱን ውጤት መገምገምን፥ በሂደትና በአኗኗር በአጠቃቀም የሚያጋጥም ለውጥ ቢኖር ማረምን የሚጠይቅ መውጣት መውረድ በይሆዋ ዘንድ የለም፡፡ ስለዚህም “ይሁን” ባለ ጊዜ ወደ መሆን የመጣው ዓለም ብቻ አልነበረም፡፡ ከፍጥረተ ዓለም እያንዳንዱ ንኡስ ፍጥረት የሚመስለው ሁሉ ጭምር የሚተዳደርበት ሕገ ተፈጥሮ በዚያው ዓለም በተፈጠረበት ትእዛዝ ከዓለም ጋር ዐብሮ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም ዓለምና ሕገ ተፈጥሮ የሚደመደምበት ድንበር በአንድነት ያኔውኑ ተደንግገዋልና የጥበቡን የዕውቀቱን የማስተዋሉን የክሂሎቱን ፍጹምነት በመጠኑ ያስነብበናል (መዝ. 148፥6)፡፡ እንግዲህ ይህ ጥበብ፥ ችሎታ … በእኔነቱ ክልል የታቀፈ የይሆዋ ባሕርያዊ ገንዘብ እንጂ ፈጥሮ ያገኘው አይደለም፡፡
የባሕርያዊ ጥበብ ፈጠራ፡- ጥበብ፥ ስልት፥ ዘዴ፥ ብልሃት፥ መላ፥ መንገድ
ሰው የእግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ በተፈጠረበት ነፍሱ ለባዊ፥ ነባቢ፥ ሕያው እንደሆነ በዚህ ክፍል ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ለባዊትነት፥ ነባቢትነት፥ ሕያዊትነት ለሰው ነፍስ በባሕርያዊ ግብር መግለጫነት ቢያገለግልም፤ ለነፍስ ኩነቷ ማለት የህሉናዋ አመክንዮ፥ የህላዌዋ መታወቂያ፥ የከዊኖቷ ባሕርያዊና አካላዊ ዳር ድንበር ይኸው ለባዊትነቷ፥ ነባቢትነቷና፥ ሕያዊትነቷ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አይደለችም (ኢዮ. 32፥8፤ 33፥4)፡፡

የሰው ነፍስ ፈጣሪዋን (አዃኟን) የመሰለችበት አኀዝም (ቍጥርም) ይኸው የኩነቷ ሥሉስነት ሲሆን፥ ኩነቶችዋ የተዋቀሩበት የአካሏ ረቂቅነትም (መንፈስነትም) መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔር አስመስሏታል፡፡ የእነዚህም ድምር ውጤት፥ “በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር” በማለት ለተናገረበት ዕቅዱ ሥሙር መሆን ማረጋገጫና ማስረጃ አድርጓታል (ዘፍ. 1፥26-27)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስም የዚህን ምንጭ ምንነት ሲናገር፥ ይሆዋ ሰው አድርጎ ሊፈጥረው ባዘጋጀው ከዐፈር በሠራው አካላዊ ቀርጽ አፍንጫ ውስጥ የራሱን የሕይወት እስትንፋስ እፍ በማለት እንዳስተላለፈለት ይናገራል፡፤ መለኮታዊውም የሕይወት አስትንፋስ ከዐፈር የተሠራውን አካላዊ ቅርፅ ይሆዋ እንዳሰበውና እንደወደደው ያለ ሕያው ፍጡር (ሕያው ነፍስ) ይሆን ዘንድ እንዳስቻለው ያስተምረናል (ዘፍ. 2፥7፤ ኢዮ. 33፥4-6፤ 34፥14-15)፡፡

የነፍስ ባሕርያዊ ጥበብ፥ ሐሳብ፥ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ክሂሎት ኩነቷ በሆነው ቃል (ነባቢነቷ) ተቀርጾ፥ ተቀምሮና በልብ ኩነቷ (በለባዊትነቷ) መዝገብ ሞልቶ ተቀምጧል (ሉቃ. 6፥45)፡፡ ሰው የምንም ዐይነት ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆን በነፍሱ ልብ መሆን (ለባዊትነት) የሚያስበው፥ የሚያቅደው፥ የሚወስነው ለራሱ በሚረዳውና ለሌላውም ማስረዳት በሚችለው በነፍሱ ቃል መሆን (ነባቢትነት) ነው፡፡ ስላልተናገረ አላሰበም፤ በነፍሱም ቃል የለውም፥ ነባቢ አይደለም አይባልም፤ ቢፈልግ ያሰበውን በወደደ ጊዜ ይናገረዋልና፡፡ በሥጋው ዲዳ እንኳ ቢሆን በነፍሱ ነባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚሥለው ሥዕል፥ የሚቀርጸው ቅርጽ፥ የሚሠራው ሥራ … በነፍሱ ልብ መሆን የተከማቸ የነፍሱ ንባብ ቃል፥ ጥበብ ነውና፡፡

ሰው ከነፍሱ ባሕርይ ምንጭ መሆን የተነሣ በልቡ (በነፍሱ ለባዊትነት) የሚስበውንና፥ በቃሉ (በነፍሱ ነባቢትነት) ተቀርጾና ተቀምሮ የሚገኘውን ሐሳቡን ዕቅዱን፥ ጥበቡን፥ ማስተዋሉን፥ ችሎታውን በሥራ የሚገልጽበት ዘዴ ስልት መንገድ ብልሃት፥ መላ ብዙውን ጊዜ ጥበብ ዕውቀት ይባላል፡፡ ስሙን የወሰደው ብልሃቱን፥ መላውን፥ ዘዴውን፥ ስልቱን፥ መንገዱን ከፈጠረው ከነፍስ ባሕርያዊ ጥበብ ነው፡፡

ምስጢሩን ለማየት ሲሞከር በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲህ ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ የሰው ነፍስ በሦስቱ ኩነቶችዋ ያላት ባህርያዊ ሐሳብ፥ እቅድ፥ ጥበብ፥ እውቀት፥ ችሎታ፥ ራሷ የሆነችው ነው እንጂ የፈጠረችው ወይም የምትፈጥረው አይደለም፡፡ የሆነችባቸውን ኩነቶች በሥራ የምትገልጽበት ዘዴ ስልት መንገድ ምንም በስሙ ፈጣሪው የሆነውን የነፍስን ባሕርያዊ ጥበብ ስያሜ በመውሰድ “ጥበብ” ተብሎ ቢጠራም ነፍስ የራሷ ኩነቶች በሆኑ ለባዊትነት፥ ነባቢትነትና ሕያዊትነት የምትፈጥረው አእምሮኣዊ ፈጠራ የባሕርያዊ ጥበብ ነጸብራቅ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡

ይህን ማብራሪያ እንደ ያዝን፥ ወደ ይሆዋ ባሕርያዊ ጥበብ ብንመለስ ንጽጽሩ ማብራሪያውን ይበልጥ ያጐላልናል፡፡ ወልድ በይሆዋ ልብ መሆን ያለና የሚኖር ባሕርያዊ ጥበብ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ክሂሎት ቃል ነው፡፡ በጥበቡ ሰማያትን ያጸና፥ በማስተዋሉም ምድርን የፈጠረ ይሆዋ በሰማይና በምድር ያሉ ፍጥረታትን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ በምናነበው መላ፥ ብልሃት፥ ዘዴ፥ ስልት መንገድ ለመፍጠር ባይወሰንና ይህን ዘዴ ስልት መንገድ ሳይከተል በሌላ የአፈጣጠር ዘዴ ቢፈጥር ኖሮ የሚከለክለው ባልነበረ፡፡ ባሕርያዊ ጥበቡ ግን ራሱ የሆነው ኩነት ስለሆነ አይለወጥም (ሚል. 3፥6፤ ዘኍ. 23፥19)፡፡ በጥበቡ የሚፈጥረውን የአፈጣጠር ዘዴ ስልት መንገድ ግን የጥበቡ ነጸብራቅ የአእምሮውና የክሂሎቱ ፈጠራ ስለ ሆነ እንዳሻው ይለውጠዋል፡፡

ለምሳሌ፦ ይሆዋ በመጀመሪያ ሰማያትንና በጨለማና በውሃ የተሸፈነች ባዶ ምድርን ፈጠረ፡፡ በዚሁ ቀን ብርሃንን ፈጥሮ ቀንና ሌሊትን ለየ፡፡ በሁለተኛውም ቀን ጥልቅ የሆነውንና ምድርን ሸፍኗት የነበረውን ውሃ ከሁለት ከፈለና ጠፈርን ፈጥሮ በውሃና በውሃ መካከል የሚኖር ሰማይ ብሎ ጠራው፡፡ ቀጥሎም ምድርን የሸፈናትን ተራራውን ውሃ እንዲሰበሰብና የብስ እንዲገለጽ አደረገ፡፡ እንግዲህ ከዚህ የፍጥረት ታሪክ ምን እንረዳለን፡፡ ይሆዋ ሰማያትንና ምድርን ለመፍጠር ያሰበበት፥ ያቀደበት፥ የወሰነበትና፥ የፈጠረበት ጥበብ የባሕርዩ ሲሆን ለመፍጠር የተጠቀመበት ዘዴ የባሕርያዊ ጥበቡ ነጸብራቅ ወይም የዕውቀቱና የችሎቱ ፈጠራ ነው፡፡ ቢፈልግ ኖሮ በሁለተኛው ቀን የሠራውን በዚያው በመጀመሪያ ቀን በአንድ ጊዜ ትእዛዙ እንዲፈጠሩ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ጥበቡ፥ ችሎታው፥ ባሕርያዊ ሲሆን፥ ያፈጣጠሩ ዘዴ፥ ስልት መንገድ ግን የችሎታው ነጸብራቅና ፈጠራ ነው፡፡

ሌላውንም የአፈጣጠሩን ዘዴ፥ አንድ በአንድ ብናየው የሚያስረዳን ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ሰባት ቀን የወሰደውን የፍጥረት ታሪክ ቢፈልግ ኖሮ በአንድ ቀን በአንድ ቅጽበት ማጠቃለል ይችል ነበር፡፡ ይህም አንደኛው ዘዴ በሆነ ነበር፡፡ ባሕርያዊ ጥበቡ፥ ችሎታው ግን መቼውንም ባሕርያዊ ነውና ኩነቱም ነውና አይለዋወጥም፡፡ ጥበቡን፥ ችሎታውን፥ ዕውቀቱን፥ ማስተዋሉን፥ ውሳኔውን፥ ዕቅዱን ተግባራዊ የሚያደርግበት ዘዴ ግን እንደ ወደደ የሚፈጥረው የችሎታው ፈጠራ፤ የዕውቀቱ ነጸብራቅ ነው፡፡ ይህም ማለት ዘዴው፥ ስልቱ፥ መንገዱ ባሕርያዊ እና ኩነቱም አይደለም ማለት ነው፡፡ አርዮስም ሆነ ተከታዮቹ ሊያስተውሉ ያልቻሉት ምስጢር አንዱ ይህ ነበር፡፡ በይሆዋ የሥላሴነት ክበብ ወልድ የኩነት ቃል፥ ጥበብ፥ ዕውቀት፥ ማስተዋል፥ ክሂሎት፥ ሲሆን፥ እርሱም አካላዊ ነው፡፡ ይሆዋ ጥበቡ፥ ዕውቀቱ፥ ማስተዋሉ፥ ክሂሎቱ በሆነው ወልድ ዓለማትን የፈጠረበት ዘዴ፥ መላ፥ ስልት፥ መንገድ፥ ብልሃት ምንም ጥበብ ተብሎ ቢጠራ ኢአካላዊ ነው፤ ቋሚ አይደለም፡፡ የጥበቡ ፈጠራ ስለ ሆነ አሁን እንዲዚህ ሠርቶ እንደ ሆነ ሌላ ጊዜ እንደዚያ አድርጎ ይሠራል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ አርዮስ በይሆዋ ሥላሴነት ክበብ ያለ ቃል፥ ጥበብ፥ አእምሮ ወልድ መሆኑን ማስተዋል እንደ ተሳነው ሁሉ ፍጥረታትን በሥራ ላይ ለማዋል የተጠቀመበትን የአእምሮውን፥ የክሂሎቱን ፈጠራ የጥበቡን ነጸብራቅ ምንነትም ማስተዋል አልቻለም ነበር፡፡ የይሆዋን ባሕርያዊና አካላዊ ጥበብ፥ አእምሮ፥ ቃል፥ ችሎታ የሆነውን ወልድንና በእርሱ ጥበብ መሆን ዓለማትን ለመፍጠር የተጠቀመበትን ፈጠራ፥ ዘዴ (ጥበብ) አላወቃቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱንም ማለት አካላዊ ጥበቡን ወልድንና ጥበብ ተብሎ የተጠራውን የጥበቡ ፈጠራ የሆነውን ዘዴውን፥ ስልቱን፥ መንገዱን “ጥበብ ተብሎ በመጠራቱ ብቻ አደባለቃቸውና በአንድ ዐይነት ትርጉም ተረዳቸው፡፡”

እስኪ አንድ ምሳሌ እናክልበት፡፡ እግዚአብሔርም “ብርሃን ይሁን አለ፥  ብርሃንም ሆነ” ሲል የሚገልጸው በመጀመሪያ ደረጃ የእግዚአብሔርን መናገሪያ ቃል ባሕርያዊ ጥበብ፥ ባሕርያዊ ዕውቀት የሆነውን ወልድን ያመለክተናል፡፡ እርሱም የይሆዋነቱ ምልአት የእኔነቱ መግለጫ ባሕርያዊ ቃል ጥበብ ነው፡፡ በእርሱ ዓለማትን ፈጠረ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከሰማይና ከምድር ቀጥሎ ብርሃንን ለመፍጠር የተጠቀመበት የባሕርያዊ ጥበቡ የአፈጣጠር ዘዴ ይታየናል፡፡ ይህ የተፈጠረው ብርሃን አካላዊ ሆኖ በመዓልት የሚያበራ፥ በሌሊት ላይ የማይሠለጥን እንዲሆን የተጠቀመበትን ብልሃት፥ መላ፥ ዘዴ፥ ስልት፥ መንገድ፥ ራሱ ጥበብ ነው፤ ሆኖም የባሕርያዊ ጥበቡ ፈጠራ ነው፡፡ ቢፈልግ ኖሮ በመጀመሪያ ከመፍጠር በመጨረሻ ቢፈጥረው የራሱ ምርጫ ነበር፡፡ ዘዴው ፈጠራ ስለ ሆነ ሊለውጠው በቻለ፡፡ ዓለማትን የፈጠረበትንና ዘዴውንም የፈጠረበትን ባሕርያዊ ጥበቡን፥ ቃሉን ወልድን ሊለውጠው አይችልም፡፡ በእኔነቱ ክልል ያለ የይሆዋነቱ ምልአት ነውና፡፡ ባይናገርበትም ባይፈጥርበትም የይሆዋነቱ ምልአት እንደ ሆነ ይኖራል፡፡

በምሳሌ 8፥9 ጥበብ የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ ስትል፥ በባሕርያዊና አካላዊ ጥበቡ ዓለማትን ለመፍጠር የተጠቀመበትን የባሕርያዊ ጥበቡ ፈጠራ የሆነውን የአፈጣጠር ዘዴ፥ ስልት፥ መንገድ እንጂ ባሕርያዊ ጥበቡን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ የራሱን ለባዊነት፥ የራሱን ነባቢነት፥ የራሱን ሕያውነት መፍጠር ከቶ አይችልምና፡፡

የባሕርያዊ ሐሳብ፥ የዕውቀት፥ የጥበብ ፈጠራዎች ከአንዱ ባለቅኔ ወደ ሌላው የሚተላለፉባቸው ብዙ የዐይነት ስልቶች ዘዴዎች መንገዶች አሉ፡፡ የማይናገረው እንደሚናገር፥ የማይንቀሳቀሰው እንዲሚንቀሳቀስ፤ ሕይወት የሌለው እንዳለው ሆኖ ይቀርባል፡፡ የተፈጠረው እንደ ፈጣሪ፤ ሐሳብ እንደ አካል ሆኖም ይነገራል፡፡ ወንዱ እንደ ሴት፤ የጾታ መደብ ለሌለውም ጾታ ተመድቦለት ብዙ ጊዜ ይጻፋል፤ ይደረሳል፡፡ በምሳሌ 8 እና 9 በኢዮብ 28፥12-28 ላይም የሚገኘው ይኸው ነው፡፡ ይህም የአእምሮና የክሂሎት ነጸብራቅ፥ የጥበብ ፈጠራ የሆነ መላ፥ ዘዴ፥ መንገድ፥ ስልት ነው፡፡ መላ ፍጠር፤ ዘዴ ፈልግ፤ ሌላ መንገድ ቀይስ፤ ስልት ተጠቀም የሚባለው ዐይነት ነው፡፡

(በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment