Thursday, January 16, 2014

የመዳን ትምህርት

Read IN PDF
የመዳን ትምህርት ማጠቃለያ

 ከናሁ ሠናይ
ካለፈው የቀጠለ

በጥበቡ ሰማያትን የፈጠረ፥ በኀይሉም ምድርን ያጸና፥ የፈቀደውንም ሁሉ በባሕርያዊ ቃሉ ያደረገ፤ ምንም የማይሳነው ልዑል እግዚአብሔር፥ ኀጢአተኛውን የሰው ዘር ለማዳን አንድ መንገድ ብቻ ማዘጋጀቱን (ዮሐ. 14፥6) ባለፈው ዕትም አንብበናል፤ ሌላ አማራጭ የሌለው ብቸኛው መንገድም፥ የሚታመኑበትን ሁሉ ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በኀጢአተኛ ሰው ምትክ እንዲሞት መደረጉን፡፡ ኀጢአተኛን ለማዳን ከዚህ በስተቀር ሌላ መንገድ ስላልተዘጋጀ፥ ስለሌለም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ባንተ ምትክ ተሰቅሏል፤ ሞቷል፤ ተነሥቷል፤ የምሥራች! በሚለው የስብከት ሞኝነት የሚታመኑትን ሁሉ ከኀጢአትና በኀጢአት ምክንያት ከመጣ ቍጣ እንዲድኑ በእግዚአብሔር የመወሰኑ ርግጠኛነት በቃሉ ተደግፎ ቀርቦ አንብበናል (1ጢሞ. 1፥15)፡፡ በዛሬውም ዕትም በእግዚአብሔር ጸጋ ሰውን ስለሚያድነው ሕያው እምነትና በእምነት ለሚገኘው መዳን ምንጩ ስለ ሆነው ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ዐጭር መግቢያ እንዲሁም ከቍ. 1 እስከ 7 በወጡት ጮራ መጽሔቶች በዚህ ርእስ ሥር በተከታታይ የቀረበውን ትምህርት ከተከታተሉት መካከል እማሆይ ማርያማዊትና ወይዘሪት ልዕልት ነቅዐ-ጥበብ እንደ ማጠቃለያ ያቀረቧቸውን መግለጫዎች እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

ሕያው እምነትና ዐዲስ ፍጥረት
የተሰበከላቸውን የወንጌሉን ቃል ይቀበሉ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር ልባቸውን የከፈተላቸውና (ሐ.ሥ. 16፥14) ቃሉን በእምነት ከልባቸው ጋር ያዋሐደላቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው ሞት እኔ ኀጢአተኛው ልሞተው ይገባኝ የነበረ ሞት ነው፤ ትንሣኤውም በኀጢአት ምክንያት ምዉት የነበርኩ እኔ ሕያው እሆን ዘንድ፥ ዛሬ የመንፈስ ትንሣኤን ያገኘሁበት፤ በመጨረሻው ቀንም የሥጋ ትንሣኤ የሚሰጠኝን ሕያው ተስፋ የጨበጥሁበት አለኝታዬ ነው” በማለት ሲያምኑ፥ እምነታቸው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሞቱና የትንሣኤው ተባባሪ ያደርጋቸዋል (ሮሜ 6፥1-8)፡፡ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃንም ለመዛወራቸው የሚያረጋግጥ ለውጥ ይታይባቸዋል (ቈላ. 1፥13-14)፡፡ ከዚህ የተነሣ ከሞት ወዲህ ማዶ ያለ የትንሣኤን ሕይወት እየኖሩ ነው ማለት ይቻላል (ሮሜ 8፥9-11)፡፡


እንዲህ ያለው ሕያው እምነት ቀድሞ ለኀጢአት ሕያዋን ለቅድስና ግን ምዉታን የነበሩትን ክርስቲያኖች ለውጦ፥ ለኀጢአት ምዉታን፥ ለቅድስና ግን ሕያዋን አድርጓቸዋል፡፡ እገሊት ተለውጣለች፤ እንቶኔ ዐዲስ ፍጥረት ሆኗል የሚባለውም ከዚህ እውነታ በመነሣት ነው (ሮሜ 6፥5-11፤ 2ቆሮ. 5፥17)፡፡

በሌላም በኩል ኀጢአታቸው፥ ቤዛቸው በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲያርፍ፥ በለውጡ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስና ለእነርሱ መጐናጸፊያ እንደ ሆነላቸው፥ መንፈስ ቅዱስ ለመንፈሳቸው ይመሰክርላቸዋልና የልውውጡ መሠረትና ጉልላት ምን ያህል የጸናና የተጠናቀቀ መሆኑን ክርስቲያኖች ይረዳሉ (ዮሐ. 17፥19)፡፡ ዓለም የሌላት ዕረፍትና ሰላም፥ ነጻነትና ሐሤት በዝቶ የሚትረፈረፍላቸውም ከዚህ የተነሣ ነው (ዮሐ. 10፥10፤ 14፥27)፡፡ በዐዲስ ተፈጥሮአቸው የሚታይባቸው ፍሬያማው የአገልግሎት እንቅስቃሴም ለሕያው እምነታቸው ጕልሕ ማስረጃ ይሆናል (ሮሜ 12፥1-2)፡፡

አንዳንድ ሰዎች ይህን ዐይነቱን ሕያው እምነት ሳያውቁት፥ ሳይረዱት፥ ሳይቀበሉት፥ ሳያጣጥሙት፥ ሳይኖሩበት፥ “እምነትንማ ጋኔንም ይዞታል፤ ግን አይድንም፡፡ ጋኔን የማይድነውም እምነት በማጣቱ ሳይሆን ምግባር ስለማይኖረው ነው” ይላሉ ምግባር የሚሉትም የኦሪትን ሕግ እንደ ሆነ አክለው ያስረዳሉ፡፡ እንደ ማስረጃ አድርገው ከአባባላቸው ጋር የማይስማማውን (ያዕ. 2፥18-26) ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡

ያዕቆብ “ሥራ” እያለ የጠራው እሱን የኦሪትን ሕግ ነውን? የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የኛ ሞትና ትንሣኤ ነው በማለት የሚታመኑ ክርስቲያኖችን የጌታ ሞትና ትንሣኤ ተካፋዮችና ዐዲስ ፍጥረት የሚያደርጋቸው እምነት ዐይነት በአጋንንት ዘንድ አለ ብሎ ያዕቆብ እውን ተናግሮአልን? እነዚህን ጥያቄዎች በእግዚአብሔር ቃል መመርመርና መልሳቸውን መስጠት አስፈላጊም ተገቢም ነው፡፡

ሥራ ደኅንነትን ያስገኛልን?
ሥራ ደኅንነትን ያስገኛል የሚሉ ሰዎች ስብከታቸው በዐይነቱም ሆነ በይዘቱ የሐሰተኞች ወንድሞችን (ቢጽ ሐሳውያን) ትምህርት (ገላ. 2፥4 ይመስላል)፡፡ በሐዋርያት ዘመን ከፈሪሳውያን መካከል “ክርስቲያን ሆነናል” ያሉ ሰዎች ከክርስቲያኖች ጋር ከተደባለቁ በኋላ፥ “ካልተገረዛችሁ፥ በሙሴ በኩል የተሰጠውንም ሕግ ካልጠበቃችሁ በስተቀር ኢየሱስ ክርስቶስን በማመናችሁ ብቻ ልትድኑ አትችሉም” በማለት ወደ ክርስቲያኖች ልብ ጥርጥርን ዘሩ (ሐ.ሥ. 15፥5)፡፡

በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ጕዳዩን የመረመሩት ሐዋርያት፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ምእመናን ሰው የሚድነው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ ሆነ አረጋግጠው (ሐ.ሥ 15፥11) ሥራ (ምግባረ ኦሪት) ደኅንነትን ያስገኛል እያሉ የሚያስተምሩት ሰዎችም ከጌታ ሐዋርያት ያልተላኩ መሆናቸውን አጋልጠው፥ “ትገረዙና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል” የሚሉት ሰዎች ትምህርት የምእመናንን ልብ ለማወክና ለማናወጥ እንደ ሆነ አስገነዘቡ (ሐ.ሥ. 15፥24)፡፡

ጳውሎስም በተለያየ ስፍራ ለነበሩ ክርስቲያኖች ጸጋና ሕግ እርስ በርስ ተቃራኒ እንደ ሆኑ ገልጾ፥ በሥራ የሚጸደቅ ቢሆን ኖሮ ጽድቁ ለሕግ ሥራ እንደ ተገቢ ክፍያ (ዋጋ) በተቈጠረና፥ በሥራ የጸደቀውን ሰው እንዲመካበት ባስቻለው ነበር፡፡ እንዲሁም በሕግ የሚጸድቅ ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለትን ባስከተለ ነበር እያለ ከተበ (ሮሜ 4፥4፤ 11፥6፤ ገላ. 2፥15-21፤ ኤፌ. 2፥4-9)፡፡ የጳውሎስ ክታብ፥ “ሕግ በሙሴ በኩል ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተሰጠ” ከሚለው ከወንጌለ ዮሐንስ ጋር ይመሳሰላል (ዮሐ. 1፥17)፡፡ በሕግ ውስጥ ያሉ በጸጋ ውስጥ አይደሉም፡፡ በጸጋ ውስጥ ያሉ ደግሞ በሕግ ውስጥ አይደሉም፤ ሕግ በሰው ላይ ያመጣው ሞትን፥ ጸጋ ያመጣው ግን ጽድቅን ነው (ሮሜ 5፥16-17)፡፡

ያዕቆብስ ቢሆን “ሥራ (ምግባር)” እያለ የጠራው ምግባረ ኦሪትን ነውን ቢባል - መልሱ “አይደለም” ነው፡፡ ፍቅር፥ ቸርነት፥ በጎነት በሐዲስ ኪዳን ላይ የበቀለው የሕያው እምነት ፍሬዎች ናቸው እንጂ ከዐሠርቱ ትእዛዛት መካከል አይደሉም፡፡ ለችግረኞች እንድንቸር የማያደርግ እምነትም ፍሬ አልቦ ነውና ሕያው ነው ማለት አይቻልም ነው የያዕቆብ አስተምህሮ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለተቀበሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ይሰጣቸው ዘንድ በነፍሳቸው ላይ የታተመባቸውና የተቀቡት መንፈስ ቅዱስ (2ቆሮ. 1፥21-22፤ 1ዮሐ. 2፥20-27)፡፡ በውስጣቸው ሆኖና እነርሱን መሣሪያ አድርጎ የሚያፈራቸው ፍቅር፥ ቸርነት፥ በጎነት የመንፈስ ፍሬዎች ተብለዋል (ገላ. 5፥2-3)፡፡

በእግዚአብሔር ጸጋ በእምነት የዳነ፥ የጸደቀ ክርስቲያን ቀድሞ ከሥጋና ከደም በመወለድ ወርሶት የነበረውን ፍጥረታዊነት በመሻር፥ በዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጅ ያደረገው ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የራሱን ባሕርይ በውስጡ ስለሚያስተላልፍለት መልካም ሥራዎች በክርስቲያኑ ኑሮ ይታያሉ፡፡ ስለሆነም የመልካም ሥራዎች ባለቤት መንፈስ ቅዱስ እንጂ፥ መንፈስ ቅዱስ በመሣሪያነት የተገለገለበት ክርስቲያኑ አለመሆኑን “የመንፈስ ፍሬ” የሚለው ስያሜ ይገልጻል፡፡ በመሠረቱም የዳነ፥ የጸደቀ፥ ዐዲስ ፍጥረት የሆነ ክርስቲያን የመልካም ሥራዎች መፍለቂያ የመሆኑ ምክንያትም ዐዲስ ፍጥረት ከሆነበት ባሕርይ የተነሣ እንደሆነ ይታወቃል (ኤፌ. 2፥8-10)፡፡ አስደናቂ ነገር እዚህ አለ፡፡ ዐዲስ ፍጥረት የሆነው ክርስቲያን እጸድቅበታለሁ፥ የማይለውና የማይመካበት መልካም ሥራ (የመንፈስ ፍሬ) ሲታይበት (ሉቃ. 17፥10) በሥራዬ እጸድቃለሁ ባዩን የአፍ ክርስቲያን ሕይወት የመንፈስ ፍሬ ምክነት ያጠቃዋል፡፡ ምክንያቱም በሥራዬ እጸድቃለሁ ባዩ የመንፈስ ፍሬን ሊያፈራ ይችልበት በነበረው ዳግም ልደት መሰል ሥርዐት ከሥርዐተ ክርስትና እንጂ ከመንፈስ ስላልተወለደ ነው፡፡ ከሥርዐት ለሥርዐት መወለድ ፍጥረታዊን ሰው መንፈስ አያደርገውም፤ ከመንፈስ ሲወለድ እንጂ (ዮሐ. 3፥5-8)፡፡

እንግዲህ ከማያፈራ ዛፍ የተወለደ፥ በዚህም ላይ በሽታ ያጠቃው ተክል ፍሬን ይሰጥ ዘንድ አስቀድሞ
1.  ከበሽታው እንዲፈወስ
2. እንዲጸድቅ
3. ፍሬን በመስጠት ዕውቅ ከሆነ ተክል ጋር እንዲዳቀል፥ (እንደ ገና እንዲወለድ) መደረግ አለበት (ሮሜ 11፥17-24)፡፡ ከዚያ በኋላ የሚጠበቀውን ፍሬ ማፍራቱ ባሕርያዊ ግዴታው ይሆናል፡፡ ያዕቆብም “ሥራ” በማለት የሚገልጸው ይህን ዐይነቱን የመንፈስ ፍሬ እንጂ ሕገ ኦሪትን እንዳልሆነ ከንባቡ መረዳት ይቻላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በፈራጅነቱ በሚገለጽበት ጊዜ ሕግን ሁሉ በፈጸመበት በቅዱስ ሕይወቱ ቤዛነት፥ ዋጋዋ ሙሉ በሙሉ ከተከፈለ በኋላ “የተዘጋች ፋይል - ዴድ ፋል” ከሆነችው ኦሪት ሕግጋት መካከል አንዱን አንቀጽ እንኳ ለመፋረጃ አይጠቅሰውም፡፡ የመንፈስ ፍሬን አለማፍራቱ ለመዳኑ ምልክት ነውና የመንፈስ ፍሬን በማያፈራው ላይ ብቻ እንደሚፈርድ ወንጌሉ ያረጋግጣል (ማቴ. 7፥15-20፤ 25፥31-46 እንይ)፡፡

የጋኔን እምነት እንዴት ያለ ነው?
እምነት ብቻውን የሚያድን ከሆነ አጋንንትም ያምናሉና ለምን አይድኑም? ይላሉ፤ የጋኔን እምነት አድናቂዎች፡፡ አጋንንት የማይድኑት እምነት በማጣታቸው ምክንያት እንዳልሆነ፥ ነገር ግን ከእምነት ጋር መጣመር የሚገባው ሥራ ስለማይኖራቸው እንደማይድኑ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ የጋኔን እምነት አድናቂዎች እግዚአብሔርንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምኑት በአጋንንነት እምነት መጠን መሆኑን ወይም ከአጋንንት ዕውቀት የሚበልጥ እምነት እንዳልሠረጸባቸው በሚያቀርቡት ሐተታ ጠቋሚነት ይታወቃሉ፡፡

አጋንንት መልካቸውን፥ ስማቸውንና ጾታቸውን በመለዋወጥ በብዙ አማልክት ስሞች በቆሙ ሕንጻዎች፥ በተቀረፁ ምስሎች፥ በተሣሉ ሥዕሎች … ውስጥ ራሳቸውን ሰውረው አረማውያን እንዲያመልኳቸው ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም ለራሳቸው አንድ እግዚአብሔር ብቻ እንዳለ ያውቃሉ፥ ያምናሉም፡፡ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ ተወዳዳሪና ተቃዋሚ እያደረጉ ከሰው ልጆች መካከል በዘመናት ውስጥ ሐሰተኞች ክርስቶሶችን አስነሥተዋል፥ ለራሳቸው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያውቃሉ፥ ያምናሉም፡፡ ይህም በሚታይ መልኩ የጴጥሮስን እምነት ይመስላል (ያዕ. 2፥19፤ ማር. 1፥24፤ 3፥11)፡፡ እስከዚህ ድረስ የተነገረው ሁሉ እውነት ቢሆንም ሁሉን በሚያውቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የጴጥሮስ እምነትና ምስክርነት ከሰማዩ አባቴ እንጂ ከሥጋና ከደም አልተገለጠም ተብሎ ሲወደስ፥ የጋኔን እምነትና ምስክርነት ግን “ውጣ ሂድ” አስባለው፡፡

እንደ ወንጌላውያን አጻጻፍ የቅደም ተከተል ተራቸውን ስናይ፥ ከጴጥሮስ በፊት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የተናገሩት አጋንንት ነበሩ ለምሳሌ፡-

የአጋንንት ምስክርነት የተጻፈበት ስፍራ           የጴጥሮስ ምስክርነት የተጻፈበት ስፍራ
ማቴ. 8፥28-29                                           ማቴ. 16፥16-19
ማር. 1፥23፡29    
ማር. 3፥11
ማር. 5፥1-7                                              ማር. 8፥29
ሉቃ. 4፥33-35
ሉቃ. 8፥28-29

የሁለቱ እምነት ልዩነት ከምኑ ላይ ነው? ቢባል፥ በጋኔን እምነት ቁም ነገር ሆኖ የሚሠራበት የታወቀውንና ሊካድ የማይችለውን እውነት ከጭንቅ የተነሣ እውነቱን መናገር፥ ነገር ግን በእውነት ላይ አለመቆምና አለመኖር ሲሆን፤ በጴጥሮስ ዘንድ ግን እምነት የሆነውና የተባለው፥ እውነት የሆነውን በእውነትነቱ ማወቅና መቀበል፥ የራስ ምርጫንም በዚሁ እውነት ላይ ማሳረፍና በእርሱም መኖር፥ ለሌሎችም ይህንኑ እውነት በቃልና በሕይወት መመስከር ማለት ነው፡፡

“ዱባና ቅል፥ አበቃቀላቸው እየቅል” ይባላል፥ ፍሬያቸውም እንጂ እየቅል ነው፡፡  የጋኔንና የጴጥሮስም እምነት እንዲሁ አበቃቀላቸውም፥ ፍሬያቸውም አንድ አይደለም፡፡ ጋኔን “ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ” ይላል፤ ጴጥሮስ ግን  “አንተን ትቼ ወዴት እሄዳለሁ? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ!” ይላል፡፡ የጋኔን ውሳኔ ከኢየሱስ መገለል፥ የጴጥሮስ ውሳኔ በኢየሱስ መጣበቅና በእርሱ መኖር፤ የጋኔን ምርጫ እሪያ፥ የጴጥሮስ ምርጫ ኢየሱስ፡፡ የሁለቱም እምነቶች በዐላማቸው፥ በጕዟቸውና በግባቸው አይገናኙም (ማር. 5፥7-13፤ ዮሐ. 6፥66-69)፡፡ አዳናቂዎችን ማግኘቱ ይገርማል እንጂ የጋኔን እምነት ይኸው ነው፤ ምዉት ነው፡፡

ምዉት እምነት ምንድን ነው
ምዉት እምነት እውነትን በእውነትነቱ ከማወቅ ያላላፈ የጋኔን እምነት ሲሆን፥ እውነትን አምኖ መቀበል፥ በተቀበሉት እውነት መጠቀምና በእርሱም መኖር የሌለበት፥ እንዲያውም በአኗኗር እውነትን መካድና መቃወም የሚታይበት ሕይወት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሁለት የታመሙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሄዱ፡፡ ሐኪሙ ምርመራ ካደረገላቸው በኋላ፥ በሽታቸው የሳንባ ነቀርሳ መሆኑን ለሁለቱም ነገራቸው፡፡ ሐኪሙ በዚህ ሳይወሰን በሽታቸውን የሚያጠፋላቸውና የሚፈውሳቸው መድኀኒት ምንና ምን እንደ ሆነ ዘርዝሮ ለየግላቸው በደብዳቤ አስታወቃቸው፡፡

አንደኛው በሽተኛ መድኀኒቱን በታዘዘው መሠረት ገዛና ተጠቀመበት፤ በመጨረሻም ተፈወሰ፤ ዳነ፡፡ ሁለተኛው ግን በሽታውን ከማወቅ፥ የመድኀኒቱን ፈዋሽነት ከመስማትና ማዘዣውን በቤቱ ከማስቀመጥ በቀር መድኀኒቱን ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይፈወሳልን? አይፈወስም፡፡ ይህ ምስኪን በሽተኛ ፈዋሹ መድኀኒት ምን እንደሆነ ከተረዳና በጓደኛው ጤንነት ላይ የተከሠተውን አስገራሚ የጤና ለውጥ ከተመለከተ በኋላ እንኳ የታዘዘለትን መድኀኒት በመውሰድ ፈንታ፡-
1.  የሀገር ባህል መድኀኒት ለመፈለግ ከቦታ ወደ ቦታ ይንከራተታል፡፡
2. በነቢያትና በሐዋርያት፥ በጻድቃንና በሰማዕታት፥ በመላእክትም ስም ራሳቸውን የሰየሙ መናፍስትን በሚስቡ ደጋሚዎች፥ ጠንቋዮች፥ የመናፍስቱ ስም የተጻፈበትን ክታብ በውድ ዋጋ እየገዛ ያነግታል፡፡
3. ከቤተ ክርስቲያን ዐውድ በሚገዙ ጉዝጓዝ፥ ዕጣንና ሰንደል ወዘተ. የሚታጀበውን የቡና መንፈስ ይማለላል፡፡
4. በመናፍስት ስም በተሰየሙ በዓላት ዶሮ፥ በግ … በመሠዋት፥ ደም በማፍሰስና በመርጨት፥ የቂጣ ቍርስራሽና ቆሎም በመበተን ይማጸናል፡፡

አሁንም ገና ስላልተፈወሰ አለ የተባለውን መድኀኒት ሁሉ ይቀማምሳል፤ ስለ መድኀኒት ዐዋቂ ሲወራ ጆሮውን ያቆማል፤ በማስታወሻው ላይም የመድኀኒተኛውን ስም፥ የሚገኝበትን ቦታ ይመዘግባል፡፡ ጧትና ማታ የሚያገኘው ጓደኛው በተፈወሰበት መድኀኒት ለመፈወስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አሁንም ከነበሽታው ይገኛል፡፡

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለው መዳናቸውን ጋኔን ያውቃል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኀኒት መሆኑንም ያምናል፡፡ ዳሩ ግን አዳኝነቱን የሚያውቀውን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊቀበልና ሊድን ምንጊዜም ፈቃደኛ አይሆንም፡፡ የማይድነውም መድኀኒቱን ስለማይቀበልና ስለማይጠቀምበት ነው እንጂ ጋኔን ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን ያምናል፡፡ በመቀበል በመድኀኒትነቱ ለመዳን ግን አዳኝነቱን አይፈልግም፡፡

እንደዚሁም የሚታመኑበትንና የሚቀበሉትን ሁሉ ከኀጢአት ስለሚያድናቸው “ኢየሱስ” ተብሎ የተሰየመውን የእግዚአብሔር ልጅ (ማቴ. 1፥21) በመቀበል መዳንና መጽደቅ የእግዚአብሔር ልጅም የመሆንን መብት መጐናጸፍ ሲችሉ፥ ብዙ ሰዎች እምነታቸው የጋኔን ያህል ብቻ በመሆኑ የተዘጋጀላቸውን ሳይቀበሉ ይቀራሉ፡፡ የሚገርመው የጋኔን ያህል ኢየሱስን ማወቃቸውን ይኰሩበታል፡፡ ወደ መቀበል ደረጃ ደርሰው በመድኀኒትነቱ ስላልዳኑ ከላይ ታሪኩ እንደ ተመዘገበለት ሰው እርሱን ትተው የማያድኑ መድኀኒቶች ፍለጋ ከአገር ወደ አገር ይንከራተታሉ፡፡ መንፈሳዊ ዕረፍት፥ ሰላምና ሐሤት የሚገኘው ኢየሱስን ተቀብሎ በመዳን ነበረ፤ እነርሱ ግን ከሚሞክሯቸው መድኀኒቶች ሁሉ የፈለጉትን ለማግኘት ባለመቻላቸው ወደ መበሳጨት ከዚያም በዕፆችና በአልኮል ራስን ወደ ማደንዘዝ ይሸጋገራሉ፡፡ ሁኔታው ቢያሳዝንም፤ የምርጫ ጉዳይ ነው!! የማያድን፥ ምዉት እምነት የጋኔን እምነት ያላቸው ሰዎች ዕድል ፈንታ ይኸው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ እማሆይ ኤልሳቤጥ በአለቃ ደምፀ ቃለ አብ ቤት ለተሰበሰቡት ምእመናን የሰበኩትን ከዚህ ቀጥሎ አቅርበነዋል፡፡
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment