Friday, May 17, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

ካለፈው የቀጠለ

በምን ተስኖት ቤት ዐድረው ከወጡት ሰዎች መካከል በሌላ አቅጣጫ የሄዱትም እንደዚሁ በተመሳሳይና በሌሎች የወቅቱ ሁኔታ በፈጠራቸው ነጥቦች ላይ ይከራከሩ ነበር፡፡ ሐሳባቸውን በውይይት እያጠነከሩና እየተስማሙ መጥተው በመጨረሻ በአንዳንድ ነጥብ ላይ ለመግባባት አልቻሉም፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ ያስቸገሯቸውንና አልታረቅ ያሏቸውን ነጥቦች በሚከተለው ሁኔታ አጠቃለሏቸው፡፡

 1. ምን ተስኖት በሰይጣን መንፈስ እንደሚሠራ እናውቃን፤ ከጥንቈላ፣ ከሟርት፣ ከአስማተኛነት ጋር የእግዚአብሔር መንፈስ ግንኙነት የለውምና፥ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን ክብር፣ አምልኮት፣ ስግደትና ዝማሬ የሚቀበለው በምን ተስኖት ያደረ ራሱን የእግዚአብሔር ተገዳዳሪ ያደረገው ሰይጣን ነው፡፡ ታዲያ ሰይጣን በምን ተስኖት ቤት ሲመለክ የሚያድርበትን ዕለት በየወሩ ለሚካኤልና ለገብርኤል መታሰቢያ በሚከበሩ በዓላት ለምን አደረገው?


   2.   በስለትና በስጦታ የሚገባለትን መባ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር የሚካፈልበት ምክንያትስ ምንድር ነው?
  3.  ምን ተስኖት በየወሩ በሚጠነቍልበት ዕለት በሚካኤልና በገብርኤል ስም ግብዣ ያደርጋል፡፡ ታዲያ ምን ተስኖት የሚጠነቍልበትንና የሚመለክበትን ርኩስ መንፈስ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ምን አገናኛው?
  4.  እኛ በምድር ሚካኤልና ገብርኤል እያልን የምንጠራቸው በእግዚአብሔር ፊት በአገልግሎት ከሚቆሙት ሚካኤልና ገብርኤል የተለዩ ራሳቸውን በቅዱሳት መላእክት ስም እያስጠሩ በማስመስል የሚያታልሉ መናፍስት (ሰይጣናት) ይሆኑን?
  5.  እኛ ሚካኤልና ገብርኤል እያልን የምንጠራቸው እውነተኞቹ ሚካኤልና ገብርኤል ቢሆኑ ኖሩ ለቅድስና ተቃራኒ የሆኑትን ዝሙትን፣ ስካርን፣ ሌብነትን፣ ነፍሰ ገዳይነትን፣ በስለት እንዴት ይቀበሉ ነበር? ጥንቈላን፣ ሟርትን፣ አስማተኛነትን በሚሠራ ሰውስ በማደር ራሳቸውን ለማስከብር እንዴት ይፈልጉ ነበር?
  6.    በነጥቦቹ ላይ በተነጋገሩ መጠን ይበልጥ ሌሎች ጥያቄዎች እየተወለዱ የውይይታቸውም ዙር (ክበብ) እየሰፋ የጥያቄዎቹን ትክክለኛ መልስ ከእግዚአብሔር ቃል ለማግኘት ከዐቅማቸው በላይ ሆኖ ስላስቸገራቸው ከቍርስ በኋላ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ዘንድ ሄዶ ለመረዳት ወስነው ወደ ቤታቸው አመሩ፡፡

*********

ከቤተ ክርስቲያን መልስ ረፋዱ ላይ ቄስ  በሻህ ውረድ እንደ ተቈጡ እያጕረመረሙ ሲሄዱ ርምጃቸውንና አቅጣጫቸውን እንኳ መቈጣጠር ተስኖአቸው ነበር፡፡ የሾለ ድንጋይ ግራ እግራቸውን አነቀፋቸው፡፡ የሰውነታቸው ሚዛን አጋደለና ቍልቍለቱን አንደርድሮ ባፍጢማቸው  ደፋቸው፡፡ እመር ብለው ከመሬት ተነሡ፤ ዙሪያ ገባውን ቃኘት ቃኘት አደረጉ፡፡ ሰው እንዳላያቸው ሲያረጋግጡ አቧራውን ከጢማቸውና ከልብሳቸው ላይ አራገፉ፡፡ ጥምጥማቸው ባለመውደቁም ተገረሙ፡፡ ከመሬት ብድግ ባደረጉት አንድ ድንጋይ ወርውረው ያነቀፋቸውን ድንጋይ መቱት፡፡ ሆኖም በልባቸው “እንቅፋቱ ለሚያጋጥመኝ ጥሩ መስተንግዶ ጠቋሚ ነበረ” አሉና የመልካም አጋጣሚ ዕድላቸውን መምታታቸው አላስደሰታቸውም፡፡

በረጅም ከዘራቸው መሬትን እየደቁ የኰበለለች ሚስታቸው እንደምትመለስላቸው ከምን ተስኖት የተሰጣቸውን ተስፋ በማስታወስ ፈገግ እያሉ ርምጃቸውን ቀጠሉ፡፡ “ጤና ይስጥልኝ” አላቸው ድንገተኛ ድምፅ ከወደ ኋላቸው፡፡ ዞር ብለው አዩትና “እግዚአብሔር ይመስገን! እንደ ምን አረፈድክ፤ ወዴት ትሄዳለህ?” አሉ ቄሱ የዲያቆኑ አቅጣጫ ቢለወጥባቸው፡፡ “አለቃ ነቅዐ ጥበብ ዘንድ ለመሄድ ዐስቤ ነው መምሩ!?” አለ ዲያቆን ምስግና፡፡ “ለምን?” “የአንዳንድ ጥየቄዎቻችንን መልስ አለቃ አብራርተው ስለሚያስረዱን እኔና ጓደኞቼ ብዙ ጊዜ እርሳቸው ዘንድ እንደሄዳለን፡፡”

“እኔ እንኳ” አሉ መምሬ በሻህ ውረድ፥ “እኔ እንኳ ያን ወዳጄን የንስሓ ልጄን ታውቀው የለ! ምን ተስኖትን፥ ዛሬ ገብርኤል አይደል፥ ሁሉንም ጋብዟል፡፡ እንዲያውም በነገራችን ላይ ዐብረን ብንሄድ፥ አለቃ ዘንድ ነገም ተነገ ወዲያም ትሄዳለህ፤ ግድ የለህም ዐብረን እንሂድ፤ አንተም ቀድሰሃል እኮ! እንሂድ፡፡ ጓደኛ እንደ መሆናቸው መጠን ስለሚያከብራቸው ትእዛዛቸውን ላለመጋፋት “እርስዎ ካሉ እ … ሺ” አለና በመንፈስ ሳይሆን በአካል ተከተላቸው፡፡

ቍልቍለቱን እንዳገባደዱ “መምሩ!” አለ ዲያቆን ምስግና ሆድ ሆዱን ሲበላው የቈየውን ነገር ለማንሣት ፈልጎ፡፡ “ይህ ምን ተስኖት ጠንቋይ አይደለም እንዴ! መሪ ጌታ ንዋይም ጋኔን ይጐትታሉ፤ መልክአ ሳጥናኤል ይደግማሉ ይባላል፡፡ ሁለቱም የእርስዎ የንስሓ ልጆች ናቸው ማለት ነው፤ ምን ተስኖት ዛሬ አስቀድሷል፤ መሪ ጌታም በማሕሌት ሲያገልግሉ ዐድረዋል” አላቸው ሲፈራ ሲተባ፥ ሐሳቡን ማያያዝ እያቃተው፡፡

“ልክ ነህ ሁለቱም ዐዋቂዎች ናቸው፤ የተናገሩት ከመሬት ጠብ አይልም፡፡ በዚያ ላይ ጠንካራ ክርስቲያኖች፥ የቤተ ክርስቲያንም አገልጋዮች፥ ሲያበሉ፥ ሲያጠጡ ቤታቸው ቤተ አብርሃም ነው” አሉ ቄሱ ለዲያቆኑ፡፡

በንግግራቸው ብዙ ያዘነው ምስግና ለዘብና ጠነን ባለ ድምፅ “መ-ም-ሩ”  አለ፤ “መምሩ እነኛ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ ወጣቶች እመንደራችን እየመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ፡፡ እኔና ጓደኞቼ እግር ሲያደርሰን ትምህርቱን ተከታትለናል፤ ታዲያ አንድ ሎሌ ለሁለት ጌቶች አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡ የእግዚአብሔርንና የሰይጣንን ጽዋ በአንድነት መጠጣትም አይፈቀድም የሚል ቃል ከመጽሐፉ አንብበውልናል” ሲል፤ ቄሱ ከአፉ ነጠቁትና “ሞኝ ነህ ልበል? በአንድነት! ማን በአንድነት አለህ? በየተራ እንጠጣዋለን እንጂ! ቂ-ቂ-ቂ-ቂ-ቂ-”

ዲያቆኑ ስለ ርሳቸው ዐፈረና ከበስተ ኋላቸው ቀና ብሎ እያያቸው ዝም አለ፡፡ “ልጄ ሁሉም እግዚአብሔር የገለጠው ጥበብ ነው፤ አትታለል፡፡ የአስኳላና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያልኸኝን ግን ዐውቄአቸዋለሁ፡፡ ትናንት በመንገድ ላይ ሁለቱን አግኝቻቸው ነበር፡፡ ዐይነ ውሃቸው ነግሮኛል፤ የደብረ ታቦሩ ደምፀ ቃለ አብ ልጆች ናቸው፡፡ አንደኛውን በዚህ በከዘራ ልዠልጠው ነበር፡፡ የአለቃ ነቅዐ ጥበብ ልጅ እንዲያው ጥልቅ ብሎ አስመለጠኝ፡፡ የእነርሱን ጕዳይ ከእድር ዳኞች፣ ከደብተራ ምን ተስኖት ደመቀና ከመሪጌታ ንዋይ ሲሞን ጋር ተነጋግረንበታል፡፡ መቀበሪያም አያገኙም፡፡ እነርሱን ብምር ነፍሴን አይማራት” እያሉ ከጠበቀው በላይ ምርር ብለው ተናገሩ፡፡ ሊቀ ካህናት ቀያፋን መሰሉት ለዲያቆኑ፡፡ ወዲያው በአፋቸው ውስጥ የተጠራቀመውን ምራቃችን ለመዋጥ ፈለጉና የመረራቸው ይመስል ተፉት፤ ጢቅ፡፡

ዲያቆን ምስግና በልቡ ጦር የተሰካበት ያህል ሕመም ተሰማውና በጣም ዐዘነ፡፡ ከቄሱ ለመለየት ምክንያት ቢያጋጥመው እየተመኘና እያሰላሰለ ቢከተላቸውም ያለ መተዋወቅን የሚያህል ዝምታ በመካከላቸው ሰፍኖ ነበር፡፡ ቄስ በሻህ ውረድና ቄስ ታችበሌ ቄስ ዝቁም ከደብተራ ምን ተስኖትና ከመሪጌታ ንዋይ ሲሞን ጋር በመዶለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮችን ለማሳደድ መወሰናቸውን ዲያቆን ምስግና ይበልጥ ተረዳ፡፡ ወዲያውም ከቄሱ ጋር የተወያዩባቸውን ጕዳዮች ነጥብ በነጥቡ በልቡ ከለሳቸው፤ ሲጠቃልልም፡-

“ሃይማኖታችን ክርስትና ሊባል ይችላል ወይ? ወይስ ከክፉ መናፍሰት ጋር ቍርኝት ያለው በስመ ክርስትና የተቋቋመ የማስመሰያ ድርጅት ነው? እንዲህ ካልሆነ የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የሟርተኞች፣ የጋኔን ጐታቾች መጠለያና የአምልኮ ባዕድ ፈጻሚዎች መጠራቀሚያ እንዴት ሆነ?”

“ሃይማኖታችን እንደ ስሙ እውነተኛ ክርስትና ቢሆን ኖሮ፥ ከርኩሳን መናፍስት ጋር የተወራረሱትን እያቀፈ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ኢየሱስ ጌታ ነው የሚሉትን ባላሳደደ ነበር (1ቆሮ. 12፥1-3፤ 1ዮሐ. 3፥10-15)”

“ማኅበራችን ክርስቲያናዊ ድርጅት ከሆነች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ የሃይማኖት መመሪያዬ ነው ለምን አላለችም? ወይስ “አትግደል”፣ “አታምልክ”፣ የተባለው ሕግ ከእኛ መጽሐፍ ቅዱስ ወጥቷልን”
“የክርስቲያናዊ ሕይወት መስፈርት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስና የሐዋርያቱ ትምህርትና ሕይወት ነውና ክርስቲያን ለእምነቱ ይሰደዳል፤ ይገደላል እንጂ እንዲያሳድድና እንዲገድል አልታዘዘም፡፡ የኛ ማኅበር በዚህ መስፈርት ስትለካም ኢ-ክርስቲያናዊት ትመስላለች (ዮሐ. 15፥18-20)”

“የለም! የተሳተፍሁባት ማኅበር አሁን ባለችበት ሁኔታ በክርስትና ስም ልትጠራ አይገባትም፡፡ የለም! አሕዛብን በዝሙቷና በአስማቷ የምታስት፥ በኢየሱስ ምስክሮች ደም የሰከረች ባቢሎንን መሰለችኝ (ራእ. 17፥5-6)፡፡ ዐብሬ እንዳልጠፋ ከርሷ መለየት አለብኝ” (2ቆሮ. 6፥17፤ ራእ. 18፥4)፡፡

እያለ በተመስጦ ከራሱ ጋር ያወራ በነበረበት ሰዓት፥ ቄስ በሻህ ውረድም በደብተራ ምን ተስኖት ቤት ስለሚጠብቃቸው መስተንግዶ፥ በቍርስና በምሳ ላይ ስለሚቀርበው የምግብና የመጠጥ ዐይነት ራሳቸው ለራሳቸው እያወሩ ምራቃቸውን ዐሥር ጊዜ ይወጡ ነበር፡፡ እንደዚህ የሚበላና የሚጠጣበትን ባህለ ሃይማኖት ለመለወጥ በተሐድሶ መርሐ ግብር የተሰለፉትንም ተራገሙ፡፡

ሁለቱም በተለያየ መንፈስ በተለያየ ባሕር ጠልቀው እያዋኙ ሳለ፥ ከደብረ ስኂን መድኀኔ ዓለም፥ ደብረ ዘይት ዐማኑኤልና ከደብረ ሣህል ኢየሱስ ከሚመጡት ሦስት ዲያቆናትና ሦስት ቀሳውስት ጋር በመንገዱ መስቀለኛ ላይ ተገናኙ፡፡ ወደ ምን ተስኖት ቤት ለመሄድ የሚጐዳኟቸው መስሎአቸው ነበር፡፡ እንደ ተገናኙም ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ዲያቆናቱና ቀሳውስቱ ወደ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ቤት በመሄድ ላይ መሆናቸውን በመናገራቸው ዲያቆን ምስግናም በባከነው ጕልበትና ጊዜ ሳይጸጸት ከመሰሎቹ ጋር ወዲያ ተጐዳኘ፡፡ ሰባቱም ልኡካን ቄስ በሻህ ውረድን ተሰናብተው ጕዞአቸውን ወደ አለቃ ቤት አቀኑ፡፡ ቄሱም ብቻቸውን ወደ ምን ተስኖት ቤት ለመውረድ ቍልቍለቱን ተያያዙት፡፡

ቄስ በሻህ ውረድ በመጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮች ላያ ያሰሙትን ዛቻ ዲያቆን ምስግና ለጓደኞቹ ሲያጫውታቸው፥ ከዳዊት መዝሙር 2፥1-2 ያለውን በቃላቸው እያነበቡ ተወያዩበትና ተጽናኑ፡፡ በዜማም “እግዚአብሔር ኀያል ወጽኑዕ፤ እግዚአብሔር ኀያል በውስተ ጸብእ - እግዚአብሔር ነው፤ ብርቱና ኀያል፤ እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኀያል” እያሉ አምላካቸውን ወደሱት፡፡ የመንገዱም ርዝመትና ወጣ ገባ መሆን ሳይታወቃቸው አለቃ ቤት ደረሱ፡፡

የአለቃ ነቅዐ ጥበብ እልፍኝ በሰው ብዘት ተጨናንቋል፡፡ ከበር እሰከ በር ዙሪያውን ለመቀመጫ የተሠራው መደብ ለሰዎቹ ባለመብቃቱ የተለቀለቀው ወለል ጭምር ለሰው መቀመጫ ውሏል፡፡ ከጸሎት በኋላ ዲያቆን ምስግና ድግድጋቱን እያስተካከለ፥ ከምን ተስኖት ቤትና ከቤተ ክርስቲያን መልስ ሕዝቡ በቡድን በቡድን ሆነው ያነሡትን ጥያቄ እርስ በርስም በመወያየት የደረሱበትን ነጥብ፥ በቂ መልስ አልተገኘለትም ያሉትንም በመልክ - በመልኩ አቀናብሮ ካስረዳ በኋላ ተቀመጠ፡፡ ዲያቆን ምስግናን ስለ ርቱዕ አንደበቱ አለቃም ሆኑ ሕዝቡ በአድናቆት ተመለከቱት፡፡ አለቃም ጕረሮአቸውን ካጠሩ በኋላ ጥያቄውን በመድገም እያወሱ ተራ በተራ መልሱን አከታትለው ሰጡ፡፡

አንደኛ - “ከአምላክ በቀር ለሌላ እንዲሰገድ ታዞአልን? ለተባለው በሰዎች እንጂ በእግዚአብሔር አልታዘዘም፡፡ በሰዎች የታዘዘውን እንቀበል ካላችሁ፥ ለመሆኑ ያልተሰገደለት ነገር ይገኛልን? ስለ ኢ ክርስቲያናዊ አምልኮቶች አንናገርም፡፡ ምን አግዶን? በስመ ክርስቲያናዊ ክበባችን ከሆነ ሰዉ፣ እንስሳው፣ ወንዙ፣ ተራራው፣ ኵሬው፣ ዋሻው፣ ድንጋዩ፣ ቅርጻ ቅርጹ፣ ምስሉ፣ ቂጣው፣ ጠላው፣ መሶቡ፣ … ተዘርዝሮ የማያልቀው ብዙ ነገር እየተሰገደለት ነው፡፡ እንዲህ እንዲሆን በእግዚአብሔር ቃል ተደንግጎአልን? የምትሉ ከሆነ፥ አሁንም መልሱ የለም፤ አልታዘዘም የሚል ነው፡፡ ከእኔ በቀር ለሌላ አትስገድ ከማለት ተነሥቶ በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ካለው በውሃ ውስጥም ካለው፡-

- ለማናቸውም ምሳሌ አትሥራላቸው፤
- አትስገድላቸው፤
- አታምልካቸው፤
ስለሚል ምስል እንዳንሠራላቸው፥ ለእነርሱም ሆነ ለምስላቸው እንዳንሰግድ፥ እነርሱንም ሆነ ምስላቸውን እንዳናመልክ ተከለከለ እንጂ አምልኮት ብቻ አልተከለከለም ዘፀአት 20፥4-5 ተመልከቱ” አሉ አለቃ፡፡

“በመቀጠልም በኦሪት ዘዳግም 4፥15-19፡፡ ለዚህ አንቀጽ እንደ ማብራሪያ የተጻፈ ስላለ ይነበብ” አሉ፡፡ ልጃችው ልዕልት አነበበች፡፡ የቃሉን መደጋገፍና ተብራርቶ መቅረቡን አስተውሉ፡፡
1. በምድር ያሉትን የወንድን፣ የሴትን፣ የእንስሳትን የአዕዋፍን ምስል እንዳንሠራ (የማሚቴንም የወልዴንም ቢሆን)፤
2. በባሕር ያሉትንም የማናቸውንም ምሳሌ እንዳንቀርጽ፤
3. በሰማይ ያሉትን የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና (የሰማይ ሰራዊትን) ምስል እንዳንሠራ፤
4. ለእነዚህ ሁሉ እንዳንሰግድ፥ እንዳናመልክም ተከልክሏል፡፡

“የሰማይ ሠራዊት” በማለት የጠራቸውም ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህማ በስማቸው ተለይተው በግልጥ ተጠርተዋል፡፡ የሰማይ ሰራዊት በማለት የገለጸው ነገደ መላእክትን አጠቃሎ መሆኑ ይታመናል፡፡ “ኵሉ ሰራዊተ ሰማያት ይበሉ ብፅዕት አንቲ - የሰማይ ሰራዊት የተባሉት ሊቃነ መላእክትና ጭፍሮቻቸው ብፅዕት ናት እያሉ ያመሰግኑሻል እየተባለ ውዳሴ ተደርሶበታል፡፡” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕን ይመልከቱ) አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ፡፡

“ለማጠቃለልም ከፀሐይ፣ ከጨረቃና ከከዋክበት ሌላ በተጨማሪ የሰማይ ሰራዊት ለተባሉ መናፍስት ሁሉ፡-
ሀ. ምስል እንዳይሠራላቸው፣
ለ. እንዳይሰገድላቸው፣
ሐ. እንዳይመለኩ፣
በእግዚአብሔር ሕግ ተደንግጎአልና በበር የወጣችዋን አምልኮ ባዕድ በመስኮት ለማስገባት የአክብሮት ስግደት፣ የጸጋ ስግደት እየተባለች ከሰይጣን የመጣችን ፈሊጥ በዚያው በመስኮት ወርውሯት፡፡” በማለት የአንደኛውን ጥያቄ ምላሽ ደመደሙ፡፡

ዲያቆን ምስግና ተነሣና “ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን፥ በታቦት የስርየት መክደኛ ላይ ምስላቸው ስለ ተሠራው ሁለት ኪሩቤል ጕዳይ ቢነግሩን፥ ከዚህስ ጋር ግንኙት አላቸውን?” ብሎ ጠየቀና ተቀመጠ፡፡

አለቃ መነጽራቸውን እያስተካከሉ “መልካም” አሉ፡፡ “መልካም፣ በእግዚአብሔር ቃል ተመዝግቦ የተላለፈልንን እናንተም እንድታስተውሉት ኦሪት ዘፀ. 25፥17-22፤ 26፥1፤ 37፥7-9፤ 2ዜና. 3፥7፡10-14ን አንብቡ” አሉ፡፡ ሁለት ሰዎች በየተራ ተከፋፍለው አነበቡ፡፡ አለቃም ማብራሪያ ሰጡበት፡፡ “ሁለት ኪሩቤል በታቦቱ ክዳን ላይ እንዲቀረጹ፥ በመጋረጃዎቹም ላይ እንዲለጠፉ ሙሴ በእግዚአብሔር ታዘዘ፡፡ ምስያቸውም የተሰጠው ከእግዚአብሔር ነው (ዘፀ. 25፥40፤ ዕብ. 8፥5)፡፡

በዚያው መሠረትም ሙሴ ሁሉን አከናወነ፡፡ በታቦቱ የስርየት ክዳን ላይ የተቀረጹት ኪሩቤል ራሶቻቸውን ዘንበል ያደረጉት እግዚአብሔር በዚያ ላይ ሆኜ አነጋግራችኋለሁ ወዳለው ወደ ስርየት ክዳኑ ሲሆን፥ በክንፎቻቸውም ይሸፍኑ የተባለው ይህንኑ የስርየት ክዳን ነበረ (ዘፀ. 25፥20-22)፡፡ በቅድስተ ቅዱሳን ወይም በመጋረጃ ላይ የነበሩት የኪሩቤል ምስያዎችም ወደ ቤቱ ያመለክቱ እንደ ነበረ ተገልጾአል (2ዜና. 3፥13)፡፡ ይህ አቋማቸው ለሚያስተውል ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ትኲረቱም ሆነ ስግደት ለእነርሱ እንደማይገባ እያስገነዘቡ፥ የሰዎች ትኵረት እነርሱ ወደሚያመለክቱት ወደ መቅደሱ ባለቤት እንዲሆን ያስተምሩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ ማከል የምፈልጋቸው ሁለት ዐበይት ጕዳዮች አሉ፡፡

እነሱም፡-
1ኛ. ምስሎቹ ሁለት ከመሆናቸው በቀር እነማን መሆናቸው በሰዎች እንዳይታወቅ ስም የለሾች ነበሩ፡፡
2ኛ. ቤተ መቅደሱ በባቢሎናውያን በተቃጠለበት ጊዜ የኪሩቤል ምስልም ዐብሮ ስለ ተቃጠለ፥ የተቀረጸው የኪሩቤል መልክ ምን ይመስል እንደ ነበረ አይታወቅም፡፡ ዛሬ በይመስላል ከአረማውያን የመላእክት አምልኮ በተወሰደ ግምት ሰዎች የመላእክትን ሥዕል ይስላሉ እንጂ፥ ያ በእግዚአብሔር እየተነገረው ሙሴ የሠራው የኪሩቤል መልክ ፈጽሞ አይታወቅም” ሲሉ አጠቃለሉ፡፡

ሁለተኛው ጥያቄ “እ-እ-እ ምን ነበር? እ-እ አዎን ደብተራ ምን ተስኖት ደመቀ ጠንቋይም ነው፤ የቤተ ክርስቲያንም አገልጋይ ነው፡፡ መሪጌታ ንዋይ ሲሞን የወጣላቸው ማሕሌታይ ናቸው ቢባልም በዚያው የወጣላቸው አስማተኛ ሰይጣን ጐታችም ናቸው፡፡ በዚህ ራሳቸውም ይኰሩበታል፡፡ እነቄስ በሻህ ውረድም ደብተራ ምን ተስኖት ላሠራውና ለተከለው ደብረ ፋይድ ገብርኤል አገልጋዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ እንዴት የመንፈስ አንድነት ሊኖራቸው ቻለ? በተጨማሪ፥ “ኢየሱስ ብቻ ጌታም አዳኝም ነው” የሚሉትን ለማሳደድ እንዴት በአንድ ግንባር ለመሰለፍ ተስማሙ? የሚል ነበር ጥያቄያችሁ አይደለም?” አሉና ለማረጋገጥ ዞር ዞር እያሉ ሲመለከቱ “አዎን አዎን አሉ” ሁሉም ባንድ ላይ በማከታተለም፡፡

“አዬ የዋሆች! ሰይጣን ክርስቲያን መሰል ድርጅት እንዳያቋቁም መቼ ታገደ? የሚታወቀው ከፍሬው ነው እንጂ ድርጅቱ ከሚጠራበት ስያሜ የማን መሆኑ መቼ ይታወቅና!! አይታወቅም፡፡ አንዱ ክርስቲያን ነኝ እያለ የኪሩቤል ሥዕል ነው ብሎ ስም ቢያወጣለትና ጕልበቱን ቢያንበረክክለት፤ ሌላው በዚሁ ስመ ክርስትና እየተጠራ ከሞቱ ዘመዶቹ፥ ወገኖቹ ወይም ከሰው ዝርያዎች የአንዱን ስም እየጠራ ቢሰግደለት፥ መሥዋዕት ቢሠዋለት ቍርባን ቢያቀርብለት፤ ሌላው ሦስተኛ ወገን ደግሞ ስመ ሃይማኖቱን ሌላ አድርጎ የተጠረበ ዕንጨት፥ ወይም የቆመ ዛፍ ቢያመልክ፥ እንዲሁም ሌላው አራተኛ ወገን ሆኖ የአውሬ መልክ ቀርጾ ቢያመልክ፥ ወይም ሌላው ራሱን እንደ ዐምስተኛ ቡድን አድርጎ የሰይጣንን ስም እየጠራ በቀጥታ ሰይጣንን ቢያመልክ ሁሉም እንደ ዐምስተኛው ቡድን ያመለኩት ያው ሰይጣንን ነው እንጂ ሌላን አይደለም፡፡

የኪሩብ ምስል፥ ወይም የሰው መልክ የያዘው ምስል፥ የአውሬው ምስል፥ ወይም የተጠረበ ዕንጨት፥ ወይም የቆመ ዛፍ በራሱ ለራሱ አምልኮቱን፣ ስግደቱን፣ መሥዋዕቱን፣ ውዳሴውንና ጸሎቱን አይቀበለውም፡፡ ሁሉንም የሚቀበል የእግዚአብሔር ያልሆነውን ሁሉ ለመቀበል ራሱን በእነዚህ ውስጥ የሰወረው ሰይጣን ነው፡፡ ስለዚህ በየትም ሆነ በየት ቢሰለፉ ያሰለፋቸው አንድ መንፈስ ስለ ሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ድኅነት ፍጹምና በቂ እንደ ሆነ የሚመሰክረውን ቃሉን በአንድነት ይቃወማሉ፡፡ የቃሉን እውነት መሆን የሚያረጋግጠውን መንፈስ ቅዱስን እኩል ይጠላሉ፡፡ በመንፈሱና በቃሉ ተመርተው “ኢየሱስ ጌታዬና አዳኜ ነው፤ ሌላ ጌታና አዳኝ የለኝም” የሚሉትን አማኞች በተናጠልም በተባበረ ግንባርም ያሳድዳሉ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ እናት በልጇ ላይ ምራት በአማቷ ላይ በጠላትነት እንዲነሡ የሚያደርጋቸው በሁሉም ውስጥ ሠርጾ ያለው ያ በፀረ ክርስቶስነት የታወቀው ሰይጣን ነውና በአንድነት መቆማቸው አያደንቅም፡፡”
    
አለቃ መጽራቸውንም ለማስተካከል አድማጮቻቸውም እየተከተሏቸው እንደ ሆነ ለማረጋገጥ ንግግራቸውን ቆም አደረጉ፤ አየር ሳቡናም ቀጠሉ፤ “የእግዚአብሔርን ስም በመጥራታቸው ብቻ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው አይምሰላችሁ፡፡ የጠራውን ሰው ማዳን የሚችለው የእግዚአብሔር ስምኮ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ም. 10፥4-13 ግልጽ አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔርንማ ሌላው ይቅርና ኢየሱስ ክርስቶስን የካዱ ደቀ መዛሙቱንም ያሳደዱ አይሁድ ያምኑት የለምን? የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪካዊነትማ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ይቀበለው፥ ሰይጣንስ ማንነቱን ያውቅ የለምን? (ማቴ. 8፥28-29፤ ሐ.ሥ. 19፥13-15)፡፡ ሰው በማያድነው በማናቸውም አስካሁን በተፈጠረ ገናም በሚፈጠር ሃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ ቢገባ ሰይጣን ተቃውሞ የለውም፤ ያው ከእርሱ ክበብ ውጪ አልሄደምና፡፡ ሰው ወደ የትኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት ባይገባም ቤዛው ሆኖ ያዳነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነት ሲቀበል ብቻ ነው ሰይጣን በጠላትነት የሚነሣበት” አሉ፡፡

“ሦስተኛው ጥያቄችሁ” አሉና ቀጠሉ፤ “ሦስተኛው ጥያቄአችሁ ከሁለተኛው ጋር ይቀራረባል፡፡ ቢሆንም እንደ አቀራረቡ ለይተን መልስ እንስጥበት፡፡ ከመላእክት ለአንዱ መሥዋዕት ብንሠዋለት ይቀበለዋልን? ተብሏል፡፡ ለአንድ የእግዚአብሔር መልአክ ብንዘምር ብንሰግድ መሥዋዕትና ቍርባን ብነሰጠው ያ የእግዚአብሔር መልአክ ከሆነ አይቀበለውም፤ ቢቀበል ደግሞ እንደ ሳጥናኤል ከክብሩ ይወድቃል፤ ከወደቀም የሳጥናኤል ጭፍራ ይሆናል፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔር መላእክት ናቸው ለሚባሉት የሚሰጠውን ስግደት፣ ውዳሴ፣ መሥዋዕት፣ አምልኮት ማን ይቀበለዋል? ተብሎ ቢጠየቅ አግባብነት አለው፡፡ የብርሃን መላእክትን ተመስለው ይህን ሁሉ የሚቀበሉት ሰይጣናት ናቸው ብለን እንደ እግዚአብሔር ቃል በርግጠኛነት ጥያቄውን እንመልሳለን፡፡ ድርሳን በመድረስና ዝናቸውን በማስፋፋት እነርሱን የሚያገለግሉትም ሁሉ ሐሰተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸው ይላል ጳውሎስ (2ቆሮ. 11፥13-15)፡፡

“ከዚህም ጋር አያይዘን እንድንመለከተው ይገባል የምለው ነጥብ አለ፡፡ እርሱም” አሉ አለቃ “እርሱም ወደ ሞቱ ሰዎች ነፍሳት የምናሳርገው ጸሎት ወይም መሥዋዕት ለሞቱት ሰዎች ነፍሳት እንደማይደርስ ካሁን ቀደም የነገኳችሁን ማስታወስ ነው፡፡ ይህ የሙታን ሳቢነት ድግምት ሳሙኤልን የመሰለ ሰው እንዲቀርብ ማድረግ ቢችልም፥ ነፍሱ ወደ ሥጋው እንዳልተመለሰችና ሳሙኤል እንዳልተነሣ የተረጋገጠ ነው፡፡ 1000 ሰዎች በአንድ ጊዜ በተለያየ ስፍራ እንደ ሳሙኤል ያለ አንድ የሞተ ሰውን በድግምት ቢጠሩ ያን አንድ ሰው የመሰሉ መናፍስት በሁሉም ቦታ ተሰማርተው ለእያንዳንዱ የሙታን ነፍስ ሳቢ የተጠራሁት እኔ ነኝ ማለት ይችላሉ፡፡ ስለዚህም” አሉ አለቃ መነጽራቸውን ከፍና ዝቅ እያደረጉ በማስተካከል “ስለዚህም፡-

1.     የብርሃን መልአክን መስሎ የምናቀርብለትን ጸሎትና መሥዋዕት የሚቀበለው ሰይጣን ነውና በተዘዋዋሪ ሰይጣን አምላኪ እንዳንሆን፥ መናፍስት የሆኑትን ሁሉ በጸሎት ከመጥራት፥ ከመላእክትም አምልኮት ራሳችንን እንጠብቅ (ዘሌ. 19፥31፤ ዘዳ. 18፥10-11፤ ቈላ. 2፥18)፡፡
2.    ለሞቱ ሰዎች ነፍሳት የምናቀርበው ጥሪ ወደ ሟቾቹ ነፍሳት ስለማይደርስ የተጠራሁት እኔ ነኝ ብሎ የሚመጣውም ራሱን በአምላክ ደረጃ የሚያስቀምጥ “አማልክትን /ኤሎሂምን/ ይመስላሉ” የሚያሰኝ ሰይጣን ስለ ሆነ በሞኝነት ከርኩሳን መናፍስት ጋር እንዳንቈራኝ እንጠንቀቅ” (ዘዳ. 18፥11፤ 1ሳሙ. 28፥8-20) አሉና ወደ አራተኛው ጥያቄ መልስ ተሸጋገሩ፡፡

“አራተኛው ጥያቄም” አሉ፤ በመቀጠልም “በመጽሐፈ ኢዮብ 2፥2 እና በሚቀጥሉት ቍጥሮች እንደሚነበበው ሰይጣን እንዳሻው ዘዋሪ ከሆነ የብርሃን መላእክትማ ከሰይጣን በተሻለ ነጻነት እየተዘዋወሩ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሳይጠብቁ በጸሎት የሚጠሯቸውን ሰዎች ለመርዳት እንዴት አይችሉም? እያሉ በሕርመተ መላእክት (በመላእክት አምልኮ) የተጠመዱ ሰዎች ጥያቄ ማቅረባቸው ተወስቷል፡፡ መቼም “ዐይነ ልቦናው ላልበራለት ሰው ሜዳውና ገደሉ አይለይለትም” እንደ ተባለው ሆነና ነው እንጂ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ይህን ያህል የሚዛመድ ጕዳይ ተገኝቶ አይደለም፡፡ ሰይጣን እኮ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ክልል የወጣ አንድ አባት እንደ ገለጹት “ወሮበላ፥ በፈቀዱ ዐዳሪ” ሆኗል፡፡ ቅዱሳን መላእክት ግን ሁሉ ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክበብ ውስጥ ይኖራሉ እንጂ እንዳሻቸው የሚንቀዋለሉ ዘዋሪዎች አይደሉም፡፡ ይህም ከሰይጣን ጋር ዐብረው በወደቁና ባልወደቁ መላእክት መካከል ያለ ቋሚ ልዩነት ነው (መዝ. 102/103፥20-21፤ ዕብ. 2፥14)፡፡ በፈቃዱ ክበብ ውስጥ ሆነው ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ ያገለግሉታልም (ዳን. 7፥10፤ ራእ. 5፥11-12)፡፡

“ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንድ ቃል አውጥተው ካላይና ከታች ከሚገኘው ሐሳብ ጋር ያለውን ዝምድና አፍርሰው ስሕተት በማስተማር ላይ ካሉ ሰዎች መካከል በመዝሙረ ዳዊት 32/33፥7 ላይ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል” የሚለውን ይጠቅሱና “በሚፈሩት” የሚለው ቃል መልአኩ እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል ማለቱ ሳይሆን፥ መልአኩ የሚሰፍረውና የሚያድነው ራሱን በሚፈሩት ዙሪያ ነው እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል፤ እየተከታተላችሁኝ ነው?” በማለት አለቃ መልስ ሳይጠብቁ ቀጠሉ፡፡

“እየተከታተላችሁኝ ነው? እንዲዚህ የሚሉ ሰዎች በዚሁ መዝሙረ ዳዊት 32/33 ከፍ ብለው ቍጥር 6 ላይ ቢመለከቱ “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎም ቍጥር ስምንትን ቢያነቡ የችግረኛውን ጩኸት ሰምቶ የሚያድነውን የእግዚአብሔን ቸርነት እንዲቀምሱና እንዲታመኑበት ዘማሪው ሰዎችን ሲጋብዝ በተረዱ ነበር፡፡ በማከታተልም በቍጥር 9 “የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና እግዚአብሔርን ፍሩት” ይላል፡፡

“ ‘እንዲህ በማለቱም ሊፈራ የሚገባው መልአኩን ሄደን እኔን በሚፈራኝ በዚያ ሰው አጠገብ ሆነህ ጠብቀው እርዳው’ በማለት ትእዛዝ የሚሰጥ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህም ዘማሪው ዳዊት በቍጥር 11 ላይ ‘ልጆቼ ኑ እግዚአብሔርን መፍራት ላስተምራችሁ’ ይላል (መልአኩን መፍራት ላስተምራችሁ አይልም)፡፡ በፈቃዱ ዐዳሪና እንደ ሰይጣን የሚንቀዋለል መልአክ እግዚአብሔር ከቶ የለውም፡፡ አለ ካለችሁም ሰይጣን በሉት እንጂ መልአከ እግዚአብሔር አትበሉት፡፡ መልአክ የሚባላውም እንደ ቃሉ የሚላክ፥ የሚላላክ፥ የእግዚአብሔር ተላላኪ፥ ሲጠራው አቤት፥ ሲልከው ወዴት፥ የሚል ምን ጊዜም በእግዚአብሔር ፈቃድ ክበብ ውስጥ የሚኖር ሲሆን ብቻ ነው” አሉና በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ግንባራቸውንም ቋጠር ፈታ አደረጉት፡፡

ጥቂትም በትካዜ ተዋጡና እንደ ገና ተነፈሱ፤ ከዚያ “ስለ እነዚህ ዐይነት ሰዎች ሳስብ በጣም አዝንላቸዋለሁ፡፡ ሰይጣን እንኳ “እስመ ጽሑፍ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይዕቀቡከ፤ - ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስላንተ ያዝዛል” ተብሎ ተጽፎአልና (ሉቃ. 4፥10) አለ እንጂ መላእክት ሳይታዘዙ ወደ አንተ እየገሰገሱ ይመጣሉ አላለም፡፡ የምትሏቸው ሰዎች ግን የሰይጣንን ያህል እንኳ ቃለ እግዚአብሔርን ማስተዋልና መጥቀስ እንዴት ተሳናቸው? እውነትን መቀበል ባለ መፍቀዳቸው ምክንያት (ኤር. 8፥8-10፤ ሮሜ 1፥19-25) ከሰይጣን በባሰ መጠን የማስተዋላቸውን ጸጋ የተገፈፉ ይመስለኝና እደነግጣለሁ፡፡
“ወዳጆቼ እንዲዚህ ካለ የአእምሮ ድቀት እግዚአብሔር ይጠብቀን” በማለት አሳሰቡና የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት ዘጉ፡፡

በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment