Wednesday, September 4, 2013

የዘመን ምስክር


በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


አለቃ ታየ ገብረ ማርያም (1853 - 1916 ዓ.ም.)
አይሁድ መሲሑን ይጠባበቁ የነበሩ ሕዝብ ናቸው፤ መሲሑ ሲመጣ ግን አልተቀበሉትም፡፡ የመሲሑን ደቀ መዛሙርትም አሳድደዋል፡፡ እነርሱን መስሎ የሚኖረውን ሰው እውነተኛ አይሁዳዊ ሲሉ፥ ዐዲስና እንግዳ ትምህርትን ሳያመጣ በመጽሐፋቸው የተገለጠውንና እነርሱ ያላስተዋሉትን እውነት የሚያምነውንና የሚኖረውን የመሲሑን ተከታይ ደግሞ መናፍቅ እያሉ ሲኰንኑ ኖረዋል፡፡

ሳውል፥ በጊዜው በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር በነበረው በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረ ሊቅ እንደ መሆኑ በዚያው ሥርዐት ሲኖር እጅግ የተከበረ ሰው ነበረ (ፊል. 3፥5-6)፡፡ ክርስቶስ ከተገለጠለትና በወንጌል አምኖ የእርሱው አገልጋይ ከሆነ በኋላ ግን፥ የቀድሞ ክብሩን ዐጥቶ አሳዳጁ ሲሰደድና ሲንገላታ፥ አለሥራውም ክፉ ስም ሲወጣለት ነበር፡፡ ቀድሞ ያከበሩት ወገኖች፥ “ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው” (ሐ.ሥ. 24፥1-9) ሲሉ በሐሰት ከሰዉታል፡፡ እርሱም ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፥ “በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፡፡ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ ” (ቊጥር 10-21) ብሏል፡፡


በአገራችንም ብዙ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት ከማስተዋላቸውና በእርሱ መመራት ከመጀመራቸው በፊት ሊቅነታቸውን በተረዳላቸው ማኅበረ ሰብ መካከል ሲከበሩ ኖረዋል፡፡ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘወር ባሉና መመሪያችን ሊሆን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው ብለው በተነሡ ጊዜ ግን፥ የተሰጣቸው ክብር ተገፏል፤ አለ ስማቸውም ሌላ ስም ተሰጥቷቸዋል፤ በሌሎችም እንዲጠሉና እንዲዋረዱ ተደርጓል፡፡ ይህ ዕጣ ከደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት መካከልም አንዱ አለቃ ታየ ናቸው፡፡
  
አለቃ ታየ ማናቸው?

የካቲት 25 ቀን 1961 ዓ.ም. ለንባብ የበቃው ዐዲስ ዘመን ጋዜጣ “ምን ሠርተው ታወቁ?” ለተሰኘው ዓምዱ የመረጣቸው ዕውቅ ሰው አለቃ ታየ ነበሩ፡፡ ስለ እርሳቸው ከሰጠው ምስክርነትም እንዲህ የሚለው ይጠቀሳል “እንደ ዛሬው ኤ.ቢ.ሲ.ዲ. የቈጠረው በመቶ ሺህ ሳይቈጠር፥ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰርና ዶክተር ሳይገኝ፥ አለቃ ታየ የዐሥራ ዘጠነኛው ዘመን ኢትዮጵያዊ ምሁር ነበሩ፡፡ ሙያቸውና ችሎታቸው በአንድ መሥመር ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በአንደበታቸው የሚመስጡና ልብን የሚማርኩ የክርስቲያን ሃይማኖት ሰባኪ፣ የሚራቀቁ ደራሲ፣ የሚመራመሩ ታሪክ ጸሓፊ፣ ስለ ኅሊና ነጻነት ተከራካሪ፣ ከውጭ አገር ተበትነው የነበሩትን የኢትዮጵያ መጻሕፍት ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ በቤተ መንግሥት የተከበሩትን ያህል በወኅኒ ቤት ማቀዋል፡፡ የተወደዱትን ያህል ብዙ ጠላቶችም ተነሥተውባቸዋል፡፡”  

እኒህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ዕውቅ የቋንቋ ሊቅና የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሓፊ፥  ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን እድገትና መሻሻል ልዩ ቅንአት የነበራቸው ታላቅ ሰው የተወለዱት በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በኅዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም. ነው፡፡ የትውልድ ስፍራቸውም በቀድሞው በጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ከምከም ወረዳ፥ ግምጃር ሚካኤል በተባለ ጎጥ ነው፡፡ በ5 ዓመታቸው ወደ ቤተ ክህነት ትምህርት ቤት እንደ ተላኩና በ7 ዓመታቸውም ማንበብና መጻፍ እንደ ቻሉ ይነገራል፡፡

የ18 ዓመት ወጣት ሳሉ ወደሚኖሩበት መንደር የገባው ወረርሽኝ ወላጅ እናታቸውን ጨምሮ ዘመዶቻቸውን ሁሉ ፈጀባቸው፡፡ በእናታቸው ሞት ላይ የአባታቸው በአካባቢው አለመኖር ሐዘናቸውን መሪር ስላደረገው፥  አባታቸውን ፍለጋ ወደ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ለመሄድ ሞክረው ሳይሳካላቸው በመቅረቱ፥ የእናታቸው ወንድም ወደሚገኙበት ወደ ትግራይ አቀኑ፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ እንዳደረጉት አጎታቸውንም ስላላገኟቸው፥ የጉዞአቸውን አቅጣጫ ወደ ኢየሩሳሌም አዞሩ፡፡ ጒዟቸው በምፅዋ በኩል ነበረና፥ በዚያ እምኲሉ በተባለው ስፍራ የስዊድን ወንጌላውያን ሚስዮን ትምህርት ቤት መኖሩን ስላወቁ ጎራ አሉ፡፡ የመማር ዕድል እንዲሰጣቸው ቢጠይቁ፥ እዚያ ከሚማሩት ወንዶች ልጆች በዕድሜም በዕውቀትም ከፍ ያሉ በመሆናቸው ጥያቄያቸው ለጊዜው ምላሽ ሳያገኝ ጥቂት ወራት ተቈጠሩ፡፡ በመጨረሻ ግን እንዲማሩ ተፈቀደላቸው፡፡

በትምህርት ቤቱ በነበራቸው ቈይታ ወደ እውነተኛው መንገድ ለመድረስ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸውና፥ ወደዚያው የሚመራቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር፡፡ የአገራቸው መንፈሳውያን ትውፊቶች ምርኮኛ ስለ ነበሩና ሰፊ ዕውቀትም ስላካበቱ፥ ብዙ ጊዜያቸውን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የቤተ ክርስቲያናቸውን አስተምህሮና ልምምድ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ይመረምሩ ነበር፡፡ ይህ ዝንባሌያቸው ከምዕራባውያን ትምህርት ይልቅ ለምሥራቃውያን ትምህርት የበለጠ ትኲረት ይሰጡ እንደ ነበር ተግባራዊ ምስክር ነው፡፡ ወደ ተጠቀሰው ትምህርት ቤት በተማሪነት ይግቡ እንጂ፥ ሚስዮናውያኑን በሥነ ጽሑፍ አገልግሎት ያግዙ ነበር፡፡         

ከዚህ በኋላ ቅኔ ለመማርና በታላላቅ ገዳማት ውስጥ የሚገኙ መንፈሳውያን መጻሕፍትን ለማጥናት ወደ ትውልድ ስፍራቸው ወደ በጌምድር ተመለሱ፡፡ ከትምህርታቸውና ከጥናታቸው ጎን ለጎን የተሸከሙትን የወንጌል ዘር በአገራቸው ሰዎች ልብ ላይ ለመዝራት ጒጒት የነበራቸው ቢሆንም፥ ዘሩ የወደቀበት ምድር የሚያበቅልና የሚያፈራ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ ፊታቸውን ወደ ቅኔ ትምህርታቸውና በሃይማኖት ትምህርት ውሳኔዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክና መሰል ዘርፎች ላይ ለሚያደርጉት ጥልቅ ምርምር የሚረዷቸውን ታላላቅ የታሪካዊ ሰነዶች ስብስቦችን ወደ መፈለግ መለሱ፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም “አለቃ” የሚለውን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡

ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1877 ዓ.ም. ወደ ምፅዋ እምኲሉ ሚስዮን ትምህርት ቤት ተመለሱና በአስተማሪነት፣ በተርጓሚነትና በሰባኪነት ማገልገል ጀመሩ፡፡ የድርሰት ሥራ የጀመሩትም በዚህ ወቅት እንደ ነበረ ይታመናል፡፡ በ1886 ዓ.ም. ከጣና በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው የትውልድ ስፍራቸው ወደ ይፋግ ተመልሰው ትዳር መሠረቱ፡፡ የስብከተ ወንጌል ሥራቸውንም ቀጠሉ፡፡ በየሰንበቱና በየሃይማኖታውያን በዓላቱ ለሚሰበሰበው ሕዝብ፥ ስለ መዳንና ሰለ መመለስ (ንስሓ ስለ መግባት) ይሰብኩ ነበር፡፡ በሥርዐተ ቀብር ላይም ስለ ሞት፣ ስለ ትንሣኤ፣ ስለ ፍርድና ስለ ዘላለም ሕይወት በማስተማር የመዳንን መንገድ ያስረዱ ነበር፡፡  በየዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ እየተገኙም በበዓሉ ታሪክ ላይ ተመሥርተው ወንጌልን ይሰብኩ፥ ከአንዳንድ ታዋቂ የጎንደር ሊቃውንት ጋርም በነገረ መለኮት ዙሪያ ክርክር ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አገልግሎታቸው ተወዳጅነትን ስላገኙ፥ በጊዜው ከፊል በጌምድርን ይገዙ የነበሩት ራስ መንገሻ አቲከም አቀረቧቸው፡፡ ለአገር የሚጠቅም ሥራ ሊሠሩ የሚችሉ ሊቅ መሆናቸውን ሲረዱም በ1891 ዓ.ም. ወደ ዐፄ ምኒልክ ላኳቸው፡፡

በጊዜው ዐፄ ምኒልክ የራስ መንገሻ ዮሐንስን መሸፈት ተከትሎ በራስ መኰንን የሚመራ ጦር ወደ ትግራይ ልከው ሁኔታውን በቅርብ ለመከታተል ወሎ ውስጥ ደነባ በተባለ ስፍራ ነበሩ፡፡ አለቃ ታየም ወደዚያው ሄደው ከዐፄ ምኒልክ ጋር ተዋወቁ፡፡ በ1889 ዓ.ም. አሳትመዉት የነበረውን “መጽሐፈ ሰዋስው” የተሰኘ መጽሐፋቸውንም አበረከቱላቸው፡፡ ዐፄ ምኒልክም በሥራቸው መደሰታቸውን በመገለጽ ካበረታቷቸው በኋላ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ሄደው እንዲቈዩ አዘዟቸው፡፡

ለአገር ምን አበረከቱ?
ለአገር አስተዋፅኦ ማበርከት የሚቻለው አገርን መውደድ ሲቻል መሆኑ ምንም አያጠያይቅም፡፡ አለቃ ታየ አገር ወዳድ ለመሆናቸው አንዱ ምስክር፥ በውጭ አገር ሳሉ የሌሎች አገሮች መንግሥታት ወደ ሠለጠኑ አገሮች አንዳንድ ሰዎቻቸውን እየላኩ ሲያስተምሩ አይተው፥ “ለአገሬ መንግሥት ቅንአት እንደ እሳት በላኝ፤ ምንኮ አደርጋለሁ! ዐዝኜ ወደ መቃብር እወርዳለሁ” በማለት ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የገለጹባቸው ቃላት ናቸው፡፡ ከቃል ባለፈ ለአገራቸው እድገትና ብልጽግና ያፈለቋቸው ጠቃሚ ሐሳቦችና የሠሯቸው ሥራዎችም ይመሰክራሉ፡፡ ተመልካቾችም ስለ እርሳቸው የሰጧቸው አስተያየቶች ሌሎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡

ወደ ሠሯቸው ሥራዎች ከማለፋችን በፊት፥ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስለ አለቃ ታየ የሰጡትን ምስክርነት እንጥቀስ፡፡ ምስክርነቱ በዚያ ዘመን ወደ ውጭ አገር ተሰደው ወይም ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ቀሥመው አገራቸውን ለመጥቀም የሚፈለጉ ኢትዮጵያውያን፥ ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ መናፍቅና የሌላ መንግሥት ሰላይ እየተባሉ ይፈጸምባቸው የነበረውን ግፍ የሚያስታውስ ነው፡፡ በዚህ መንገድ በርካቶች የተንገላቱ መሆናቸውን ነጋድራስ ጠቅሰው፥ “የሚከተሉት የሁለት ሰዎች ስም ግን እንዲወሱ የግድ ነው፡፡ እነርሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታዬ ናቸው፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ፥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አርጎ መንግሥቱን የሚወድ ሰው አላየሁም፡፡ ይህ ደግነታቸው ግን እስከ ዛሬ ድረስ አልታወቀላቸውም ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል የነርሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጁን አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቈርጣልና” በማለት መስክረዋል፡፡

አለቃ ታየ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ዐፄ ምኒልክን ከተዋወቁ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በወንጌል ማስተማርና በጽሑፍ ሥራ ተጠምደው ነበር፡፡ ከጀርመን መንግሥት ተልከው የመጡ ሰዎች፥ ከኢትዮጵያ የተወሰዱና በዚያ የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ጥንታውያን መጻሕፍት መኖራቸውን በጠቈሟቸው መሠረት፥ አለቃ ታየ ከሰዎቹ ጋር ወደ ጀርመን ሄደው የተባሉትን መጻሕፍት እንዲመረምሩ ከዐፄ ምኒልክ በመጋቢት 9 ቀን 1897 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ትእዛዝ ደረሳቸው፡፡ ከሰዎቹ ጋር ወደ ጀርመን ሄደውም የተሰጣቸውን አገራዊ ተልእኮ በትጋት ፈጽመዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ከብዙ በጥቂቱ ከዐማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ፥ የታተሙ የ140 መጻሕፍትን ዝርዝር፥ እንዲሁም በፓሪስ ከተማ የታተሙና ያልታተሙ ያሏቸውን የ10 መጻሕፍት ዝርዝር ለዐፄ ምኒልክ በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡

በውጭ አገር ቈይታቸው ሥራቸው መጻሕፍትን ማሰባሰብ ብቻ አልነበረም፤ በጀርመን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዐማርኛንና ግእዝን አስተምረዋል፡፡ በተጨማሪም ለዐፄ ምኒልክ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ ለኢትዮጵያ እድገት ማነቆ የሆኑትን ችግሮች በመጠቈም ንጉሠ ነገሥቱ ማሻሻያና ለውጥ እንዲያደርጉ አሳስበዋቸዋል፡፡ አለቃ በውጪ አገር ቈይታቸው በአውሮፓውያን ሥልጣኔ መመሰጣቸውንና ለአገራቸው መቅናታቸውን እንዲህ ሲሉ ጽፈዉላቸዋል፡፡ “የአዳምን ልጆች ዓለሙንም ሁሉ የፈጠረ አድልዎ የሌለበት አንድ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ላንዱ ወገን ሕዝብ ሙሉ ላንዱ ወገን ጐደሎ ልብ አልፈጠረም፡፡ በፍጥረቱ የአዳምን ልጆች ሁሉ አስተካክሎ እንደ ፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ እንዲህ ከሆነ ስለ ምን የአውሮፓና የእስያ ሰዎች፥ ከአፍሪቃ ክፍልም ጥቂቶች ብልሃተኞች ሲሆኑ፥ እኛ ሐበሾች ከሌሎች አሕዛብ ተለይተን፥  ሁሉ በፊት አባቶቻችን ሕገ ኦሪትን የተቀበሉ፥ ከ308 ዓመት በኋላም በክርስቶስ ያመኑ ልጆች ስንሆን በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጥበብ ወደ ፊት የማንገፋበት ምክንያቱ ምን ይሆን?” የሚል ጠያቂ ቢኖር ምላሾቹ የሚከተሉት ናቸው ይላሉ፡፡
“1ኛ. ሕዝቡ ሁሉ ባይማርና የወንጌልን ስብከት በብዙው ባይሰማ፣ እውነተኛ ዕውቀትና አፍቅሮ ቢጽ (የባልንጀራ ፍቅር)፣ ትሕትና ቢጠፋ ነው፡፡
“2ኛ. በአገራችን ጥቂት ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በመከበር ፈንታ ስለሚሰደቡና ስለሚዋረዱ፣ ስለሚጠቁ የሚያውቁትን ጠቃሚ የጥበብ ሥራ ትተው በቦዘን መኖርን መረጡ፡፡ በመመስገን ፈንታ የሚሰደበው ሥራ፦ መጽሐፍ ቢማሩ ኰቸሮ ለቃሚ፣ ደብተራ፥ ጽሕፈት ቢማሩ ጠንቋይ፣ አስማተኛ፥ ብርና ወርቅ ሲሠሩ አንጥረኛ፣ ብረት ቢሠራ ቀጥቃጭ፣ ቡዳ፥ … እየተባለ ለየሥራው ሁሉ ስም እየተሰጠ ስለሚሰደብ፥ የጥበብ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀዘቀዘ ጠፋ፡፡ ስለዚህ ጒዳይ ጃንሆይ አስበዉበት እንደዚህ ያለው ስድብ ሁሉ ባዋጅ እንዲከለከል፥ የጥበብ ሥራ የሚሠሩት እንዲከበሩ ቢያደርጉ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ልጁን እንዲያስተምር ቢደረግ ልዩ ልዩ ዐይነት ጥበባትን የሚያስተምሩ መምህራን ከውጭ አገር ቢያስመጡ፣ የመጽሐፍ ማተሚያ ከአውሮጳ ቢያስወስዱና ጥቅም የሚገኝባቸው መጻሕፍቶች ሁሉ እየታተሙ ለሕዝብ እንዲታደል ቢሆን፡፡ በሌላ መንግሥት ስምና መልክ የተቀረጸ ገንዘብ ከመገበያየት በጃንሆይ መልክና ስም የተቀረጸበት ገንዘብ እንዲወጣ ቢያደርጉ፥ ነጻ መንግሥትም ራሱን የቻለ የተሟላ ይሆናል” ሲሉ አጅግ ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን ሰጥተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ዐፄ ምኒልክ የትምህርትን አስፈላጊነትና የሥራን ክቡርነት የተመለከተውን ዐዋጅ አወጡ፡፡
      
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከታቸው እነዚህ ነገሮች ብዙም ላያስደንቁን ይችላሉ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን የዚያን ዘመን ሁኔታ በመገምገም አለቃ ታየ የሰጧቸውን ምክሮች ስንመዝን ግን፥ እርሳቸው ምን ያህል አስተዋይ፣ ለአገርና ለወገን ዐሳቢና ተቈርቋሪ፣ ወደ ሥልጣኔ የሚወስደውን ጐዳና ቀድመው የተረዱ ሊቅ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡

አለቃ ታየ በጀርመን ሳሉ አንድ ጀርመናዊ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከኋላ ቀርነት የተነሣ፥ በሕዝቡ ላይ ይደርስ የነበረውን ችግር ብቻ በፊልም ቀርጾ ለሕዝብ በአደባባይ ሲያሳይ አይተው፥ “አንተ ክፉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለህን በዘረኛነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻ ለማንጸባረቅ ስትል፥ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መልካሙን ባህልና ማኅበራዊ ኑሮ አንዲት ስንኳ በፊልምህ ሳትቀርጽ ክፉውን ብቻ ታሳያለህን?” ሲሉ እንደ ገሠጹትና በዚህ መነሻነት የፊልም አንሺው ባለበት ሰፊ ውይይት እንደ ተደረገ የታሪክ ሰነዶች ይጠቊማሉ፡፡

አለቃ ታየ በውጪ ቈይታቸው ከጀርመን በተጨማሪ ስዊድንን፣ ቱርክን፣ ኢጣሊያን፣ ግሪክን፣ እስክንድርያን ጐብኝተዋል፡፡ ታላቅ ሰውነታቸውን በማድነቅም የጀርመን፣ የግሪክና የኢጣሊያ መንግሥታት የተለያየ ኒሻኖችን ሸልመዋቸዋል፡፡ ተልእኮአቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ፥ በፈጸሙት አኲሪ ተግባር በመደሰት ዐፄ ምኒልክ ሦስተኛውን የኢትዮጵያን የክብር ኮከብ ኒሻን በመሸለም፥ ርስትና ጒልት ሰጥተው ወደ ትውልድ ስፍራቸው እንዲሄዱና አስቀድሞ ጀምረዉት የነበረውን የኢትዮጵያን ታሪክ የመጻፍ ሥራ እንዲፈጽሙ አዘዟቸው፡፡       
   
ለቤተ ክርስቲያን መሻሻል ምን ሠሩ?
ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው አለቃ ታየ በእምኩሉ ሚስዮን ትምህርት ቤት ያገኙት ዋና ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን የበላይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርትና ልምምድ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን እየመረመሩ ሊጸና የሚገባው እንዲጸና፣ ሊሻሻል የሚገባው እንዲሻሻል፣ ሊለወጥ የሚገባው እንዲለወጥና ሊወገድ የሚገባው እንዲወገድ በቃልም በጽሑፍም ብዙ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በተለይም በጽሑፍ ያሰፈሯቸው የለውጥ ሐሳቦች፥ ወደ ሰው ትምህርትና ልማድ የተንሸራተተው ክርስትና ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱ እንዲመለስ የሚያሳስብ ነው፡፡

አለቃ ታየ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው እንደ መሆናቸው ለጥናትና ምርምር የሚረዱ ታሪክ ነክና ልዩ ልዩ ግጥሞችን ደርሰዋል፡፡ ሃይማኖታውያን የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ ከሚጠቀሱት መካከል፦ መዝገበ ቃላት የሚባለውና 400 ገጾች ያሉት በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያቀረቡትን ምሁራዊ ሂስ የያዘ ያልታተመ መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ መዝሙረ ክርስቶስ፣ መልክአ መድኀኔ ዓለም፣ መልክአ ኢየሱስ፣ ምክሐ ምእመናን የተሰኙት መጻሕፍት ግን በአንድ ላይ ሆነው በ1913 ዓ.ም. ታትመዋል፡፡

መዝገበ ቃላት የተሰኘው መጽሐፋቸው፥ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉ የበላይ መሆኑንና እንዴት ባለ ጥንቃቄ መነበብ እንዳለበት ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማሙ አዋልድ መጻሕፍትንና ስሕተቶቻቸውን በምሁራዊና በማስረጃ በተደገፈ አቀራረብ ይተቻል፡፡ ከተቻቸው መጻሕፍት መካከል፦ ሲኖዶስ፣ ፍትሐ ነገሥት፣ መጽሐፈ ግንዘት፣ ገድላት፣ ድርሳናትና ተኣምር ይገኙባቸዋል፡፡ አቀራረቡ በተስእሎ ወተሰጥዎ (በጥያቄና ምላሽ) መልክ ሲሆን፥ በጥያቄ መልክ የሚያቀርቡት የአዋልድ መጻሕፍትን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና በአዋልድ መጻሕፍት የተላለፈው ትምህርት ትክክል ነው የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች ነው፡፡ ሐሳቦቹ በጥቅሶችና በማብራሪያዎች የተደገፉ ስለ ሆነ፥ ለጊዜው እውነት ይመስላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመልሱ ላይ ስሕተት መሆናቸውን በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባላቸው የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ጥቅሶች ያፈርሱታል፡፡ ይህ መጽሐፍ የያዛቸው ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስና የጥንት አበው ድርሳናት ጥቅሶች፥ የተቀመጡት በግእዝ ነው፡፡ መጽሐፉ ቢታተምና ቢሠራጭ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልና የብዙዎችን ዐይን እንደሚገለጥ ይታመናል፡፡
              
አለቃ ታየ የግጥም ተሰጥኦ ስለ ነበራቸው፥ ብዙ ነገሮችን ይገልጹ የነበረው በግጥም እንደ ነበረ ከሥራዎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ደብዳቤ እንኳ በግጥም ይጽፉ ነበር፡፡ መንፈሳውያን የሆኑትና መዝሙረ ክርስቶስ፣ መልክአ መድኀኔ ዓለም፣ መልክአ ኢየሱስ፣ ምክሐ ምእመናን የተባሉት ድርሰቶቻቸው በግእዝ በግጥም የቀረቡ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በይዘታቸው የለውጥ ሐሳብን ያዘሉ፣ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ማእከል ያደረጉና እርሱን ብቻ የሚማጸኑ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ መዝሙረ ክርስቶስ የተሰኘው ድርሰት የግእዙን መዝሙረ ዳዊት መሠረት ያደረገና በ150ው መዝሙር፣ በመሓልየ ማሕልይና በነቢያት ጸሎት የመጀመሪያ ስንኝ ተጀምሮ ለክርስቶስ ውዳሴ የሚቀርብበት ባለ 5 ስንኝ መዝሙር ነው፡፡ መልክአ መድኀኔ ዓለም፣ መልክአ ኢየሱስ፣ ምክሐ ምእመናን የተሰኙት መጻሕፍትም በግእዝ ቋንቋ የተደረሱ ሲሆን እያንዳንዳቸው ባለ 5 ስንኝ የሆኑ ግጥሞችን የያዙ ድርሰቶች ናቸው፡፡

አለቃ ታየ በቃልም ቢሆን ይሰጡ የነበረው ትምህርት፥ ክርስትናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን እንዳይለቅ የሚረዳ እንደ ነበረ፥ ከሚከተለው አቀራረባቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዐፄ ምኒልክ በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ማስተማርና መስበክ እንደ ቀጠሉ፥ በይፋግና በዙሪያው ባሉ ታላላቅ አድባራት ታዋቂ እየሆኑ በመምጣታቸው፥ በዐበይት በዓላት የእርሳቸውን ስብከት ለመስማት ብዙ ሕዝብ ይሰበሰብ ነበር፡፡ አንድ ቀን በሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ተጘኝተው ሳለ፥ መልክአ ሥላሴ የተባለውን የግእዝ መጽሐፍ አወጡና፥ በዚያ ለተሰበሰቡት ሁሉ በማሳየት፥ መጽሐፉን ማን እንደ ደረሰው ጠየቋቸው፡፡ ሁሉም በመስማማት የተከበሩ ኢትዮጵያውያን ጥንታውያን ሊቃውንት እንደ ደረሱት ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አለቃ ከመጽሐፉ ውስጥ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ደሙን ስለ ኀጢአት ስርየት እንዴት እንዳፈሰሰና በእግዚአብሔር ፊት እንዴት እንዳጸደቀን የሚናገረውን ክፍል አነበቡ፡፡ ከዚያም እርሳቸው የሚሰብኩት ወንጌል ዘመን አመጣሽ (እንግዳ) ትምህርት ሳይሆን፥ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተቀበለችውና የምታስተምረው ትምህርት መሆኑን አስረዷቸው፡፡ ብዙዎችም ተደስተው ነበር፡፡ ይህ አቀራረባቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ምኲራብ እየተገኘ እነርሱ ከሚቀበሏቸው ቅዱሳት መጻሕፍት በመነሣት እርሱ የሚሰብከው ኢየሱስ ይመጣል የተባለው መሲሕ መሆኑን ያስረዳቸው ከነበረው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል (ሐ.ሥ. 17፥2)፡፡

አለቃ ታየና የጽሑፍ ሥራዎቻቸው
አለቃ ታየ ምንም እንኳ በመንፈሳዊ ጒዳይ ስማቸው ቢገንም በሥነ ጽሑፉ ዓለም አያሌ ድርሰቶችን ያበረከቱ ሰው መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ ጽሑፎቻቸው ሃይማኖታዊ አሻራ ያረፈባቸውና መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ቢሆኑም፥ ለጥናትና ለምርምር የሚረዱ የታሪክና የግጥም መጻሕፍትንም አበርክተዋል፡፡ ከጽሑፍ ሥራዎቻቸው መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
·       መጽሐፈ ሰዋስው፣
·       መጽሐፈ መነጽር፣
·       የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣
·       የኢትዮጵያ ታሪክ (በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወራሾች እጅ አለ ተብሎ የሚታመንና ሳይጨርሱት የቀረ መጽሐፋቸው ነው)፣
·       መዝገበ ቃላት፣
·       የመንግሥት ሕይወት፣
·       መዝሙረ ክርስቶስ፣
·       መልክአ መድኀኔ ዓለም፣
·       መልክአ ኢየሱስ፣
·       ምክሐ ምእመናን፣
·       ትርጓሜ ዳዊት ከነታሪኩ፣
·       ምስጢረ ሥላሴ፣
·       አምስቱ አዕማድ፣
·       መጽሐፈ ምክር፣
መጽሐፈ ምክር የተሰኘው 91 ግጥሞችን የያዘ መድበል ሲሆን፥ በውስጡ የተካተተው እያንዳንዱ ግጥም፥ ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችንና ሥነ ምግባራዊ ጥያቄዎችን ይዟል፡፡ በተለይ አስተምህሮኣዊ ጒዳዮች የተዳሰሱበት ክፍል፥ ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና የመጨረሻው ፍርድ ድረስ ስላለው ሁኔታ ጠቃሚ ሐሳቦችን አስፍሯል፡፡ ይህን የግጥም መድበል ለዐፄ ምኒልክ፣ ለራስ ሚካኤልና ለልጅ ኢያሱ አበርክተው ነበር፡፡ ሲያበረክቱም በመንግሥታቸው ውስጥ ለወንጌል ተገቢውን የክብር ስፍራ እንዲሰጡ በትሕትና ጠይቀዋል፡፡ የአለቃ ታየ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ የጽሑፍ ሥራዎቻቸው የኅትመት ብርሃን ያላዩና በተለያዩ ቦታዎችና ግለ ሰቦች እጅ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

አለቃ ታየን የገጠማቸው ተቃውሞ
በክርስቶስ የተሰበከውና ከዘመናችን የደረሰው ወንጌል እስከ መጨረሻው የተሰበከው ተቀባይነትን በማግኘት አይደለም፡፡ በብዙ መከራና ስደት እንደ ተሰበከና እዚህ እንደ ደረሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ በየዘመናቱም ወንጌልን ለመስበክ  የተነሡ ሁሉ ወንጌልን የሰበኩት በብዙ መከራና ችግር ውስጥ ዐልፈው ነው፡፡ የወንጌል ባሕርዩ ይህ ስለ ሆነ፥ አለቃ ታየም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተንሸራቶ በሰው ትምህርትና ልማድ በተጠላለፈ ማኅበረሰብ መካከል ወንጌልን ለመስበክ በተነሡ ጊዜ የተወደዱበት ጊዜ ቢኖርም፥ ልዩ ልዩ ተቃውሞ፣ እንግልትና እስርም ደርሶባቸዋል፡፡

አለቃ ታየ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ተዋውቀው ወደ ትውልድ ስፍራቸው ከተመለሱ በኋላ፥ በሚስዮን ትምህርት ቤት ተምረዋል በሚል አንዳንድ የቤተ ክህነት ሰዎች ይቃወሟቸው ስለ ነበር ከዐፄ ምኒልክ የመከላከያ ደብዳቤ አጽፈው ነበር፡፡ በደብዳቤው የተመለከተው የአለቃ ታየ ሃይማኖት ስለ ተመረመረና ችግር ስለሌለበት በሃይማኖት ነገር ማንም አንዳች እንዳይናገራቸው የሚያዝ ነበር፡፡ በዚህም እስከ ተወሰነ ጊዜ በነጻነት አገልግሎታቸውን ማከናወን ችለው የነበረ ሲሆን በብዙዎች ዘንድም ተወደው ነበር።

ዐፄ ምኒልክ ከወሎ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ አለቃም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴን ባልደረባ ተቀበሉ፡፡ ይኸውም ወደ ዐፄ ምኒልክ እንዲያቀርቧቸው ነው፡፡ እርሳቸው ግን ሳያቀርቧቸው ከ6 ወራት በላይ ሆነ፡፡ አለቃ ታየ በዚህ ወቅት ብዙ ጊዜአቸውን ያሳልፉ የነበረው፥ የክርስቶስን ወንጌል ይወዱ ከነበሩ ብዙ ወገኖች ጋር ነበር፡፡ ከእነርሱ ጋር የነበራቸው ውይይት በቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ዘንድ ስለ ተሰማ፥ አለቃ ታየ የተቃውሞ ትምህርት ያስተምራሉ በሚል ተከሰው በጳጳሱ ፊት ቀረቡ፡፡ ስለ ተከሰሱበት ነገር ራሳቸውን መከላለከል ሲጀምሩ፥ ጳጳሱ በቊጣ አቋርጠዋቸው፥ “አንተ አህያ ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ሲሉ ዘለፏቸው፡፡ እርሳቸውም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሾሙት ግብጻዊው ጳጳስ በክርስቲያናዊ እምነታቸው ላይ እንዲቀልዱ ባለመፍቀድ፥ “በርግጥ እኛን የማይረቡ አህዮች ያሰኘን እኮ በቤተ ክህነታችን ላይ እንደ እርስዎ ያሉትን ባዕዳን በመሾማችን ነው” ሲሉ መለሱ፡፡ ጳጳሱም ተቈጥተው አለቃን እስር ቤት እንዲወረውሯቸው አዘዙ፡፡ አለቃም በቊጣ፥ “ንጉሠ ነገሥቱ በአገሩ ሳለ እርስዎ እኔን የማሳሰር ሥልጣን የለዎትም” የሚል ምላሽ ሲሰጡ ከጳጳሱ ጋር የነበሩት ታላላቅ የቤተ ክህነት ሰዎች አለቃ ታየ ባልተለመደ ሁኔታ ለጳጳሱ እንዲህ ያለ ምላሽ በመስጠታቸው ደንግጠው ክሱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡

በማግሥቱ ጳጳሱ ወደ ቤተ መንግሥት በመሄድ በዐፄ ምኒልክ ፊት የአለቃ ታየን ስም አክፍተው በመናገር ዐፄ ምኒልክ እንዲያሳስሯቸው አሳሰቡ፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ እንዲያውም ንጉሠ ነገሥቱ አለቃ ታየን ከዚህ ቀደም እንደሚያውቋቸውና ትምህርተ ሃይማኖታቸው ጤናማ መሆኑን በመመስከር፥ “ስለ ሃይማኖቱ በእኔ ፊት ለምን አልመመሩትም?” ሲሉ አቡኑን ጠይቀዋቸዋል፡፡ በዚህም አለቃ ታየ ከእርሳቸው ይልቅ በዐፄ ምኒልክ ዘንድ ቦታ እንዳላቸው አቡኑ ተገንዝበዋል፡፡ ዐፄ ምኒልክም ጳጳሱ የፈለጉትን ከማደረግ ይልቅ እርሳቸው በአለቃ ታየ ላይ ስላደረሱት እንግልት ቅሬታቸውን ገልጸዉላቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በአለቃ ላይ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር እንዲደርስ ምክንያት እንዳይሆኑም ነግረዋቸዋል፡፡ ባልደረባ ሆነው የተሰጧቸው ጸሓፌ ትእዛዝንም ገሥጸዋቸዋል፡፡

ጳጳሱና የቤተ ክህነቱ ታላላቅ ሹማምት ቤተ መንግሥቱን ለቀው ከሄዱ በኋላ፥ ለአለቃ ታየ መልእክት ልከው፥ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ከሰጧቸው በኋላ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኘው በቀር ሌላ ነገር እንዳያስተምሩ በመጽሐፍ ቅዱስ አማሏቸው፡፡       

አለቃ ታየ ዐፄ ምኒልክ በዘመናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይወዷቸውና ከሳሾቻቸውን ይከላከሉላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከታመሙና እየደከሙ ከመጡ በኋላ በአለቃ ታየ ደስ ያልተሰኙ ሁሉ፥ የተለያየ ችግር ለማምጣት ተንቀሳቅሰዋል፡፡

አለቃ ከውጭ አገር ተመልሰው ከመጡ በኋላ በ1907 (እ.አ.አ.) ዐፄ ምኒልክ መሬት ሰጥተው ወደ ትውልድ ስፍራቸው በመመለስ በዚያ ገዥ የነበሩት የደጃዝማች መሸሻ ረዳት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ደጃዝማቹ በዚህ አልተደሰቱምና ተቀናቃኝ ሆነው ተነሡባቸው፡፡ ብዙም ሳይቈይ ዐፄ ምኒልክ ስለ ታመሙና በሽታቸውም እየጸና ስለ ሄደ፥ የአለቃ ታየ ሕጋዊ ከለላ እየላላ መጣ፡፡ በተለይ ንግሥት ዘውዲቱ ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ ከፍተኛ ችግር አጋጥሟቸው ነበር፡፡

ደጃዝማች መሸሻ ለአለቃ ከተሰጣቸው መሬት ግማሹን በኀይል ከነጠቋቸው በኋላ፥ የቀረውንም ለመጠቅለል በአለቃ ላይ ስሕተት ይፈልጉባቸው ነበር፡፡ ከዚያ “አለቃ ታየ ሃይማኖቱ የንስጥሮስ ነው፡፡ ይህንም ለሕዝቡ ያስተምራል” ሲሉ ከሰሷቸው፡፡ የበጌምድር ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስም፥ አለቃ ታየ ዐርፈው እንዲቀመጡ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ጻፉላቸው፡፡ አለቃ ታየ ግን ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ መሆኑን በመግለጽ ደጃዝማች መሸሻ የፈጸሙባቸውን ግፍ ሁሉ በዝርዝር አስረዱ፡፡ ንጉሡም የተወሰደባቸው መሬት እንዲመለስላቸው ፈረዱላቸው፡፡

በዚህ ደስ ያልተሰኙት ደጃዝማች መሸሻ፥ “አለቃ ታየ ሃይማኖቱ ፀረ ማርያም ነውና አገር መግዛት አይገባውም፤ ፀረ ማርያም አይደለሁም ካለ ሥዕለ ማርያም ይምጣለትና ይስገድ” ሲሉ አመለከቱ፡፡ አለቃ ታየም በቀረበላቸው ሐሳብ ባለመስማማት፥ “ከግብጽ ምድር  ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች ካለው በውሃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ላንተ አታድርግ፤  አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ … እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” (ዘፀ. 20፥1-6) ብሏልና ለሥዕል አልሰግድም አሉ፡፡ በኋላ በዚሁ ምክንያት ከታሰሩ በኋላም ይህንኑ ጽኑ ዐቋማቸውን በሚከተሉት ስንኞች አጠንክረዋል፡፡
"እንኳን በእግር ብረት ቢያገቡኝ በግንድ
ከቶ ምንም ቢሆን እውነቱን እውነቱን አልክድ
መጨመር ነው እንጂ ከሳት ላይ ባሩድ
የተሰወረውም እንዲሆን ገሃድ
እኔ ለአምላክ እንጂ ለሥዕል አልሰግድ
አንገቴ ቢቈረጥ በሰይፍ በካራ
አልሰግድም ለሥዕል ለሰው እጅ ሥራ"

ከላይ የተጠቀሰውን በአደባባይ የሰጡትን ምስክርነት ተከትሎ የተሰበሰበው ሕዝብ በአለቃ ታየ ላይ መደንፋት ጀመረ፡፡ ንጉሥ ወልደ ጎዮርጊስም በነገሩ የተበሳጩ ቢሆንም ጉዳዩ ሃይማኖት ነክ በመሆኑ፥ አለቃ ታየ ታስረው ወደ አዲስ አበባ እንዲላኩ አደረጉ፡፡

አዲስ አበባ ላይ በግራዝማች መሸሻ በኩል እንዲከራከሩ የተመረጡት አለቃ ፈለቀ የተባሉ ሰው ሲሆኑ፥ በግብጻዊው የኢትዮጵያ ጳጳስ በአቡነ ማቴዎስ ፊት ቀርበው አለቃ ታየን እንዲህ ሲሉ ከሰሷቸው፦
1.     ለሥዕልና ለመስቀል አልሰግድም ብሏል፤
2.    ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ አያማልዱም ብሏል፤
3.    ሰው ከሞተ በኋላ ስለሱ የሚደረገው ምጽዋትና ዝክር አያጸድቀውም፤
4.   በልማድ የሚጾም ጾም ዋጋ ቢስ ነው፤
5.    ቅዳሜንና አሑድን አላከብርም ብሏል የሚሉ ነበሩ፡፡

በነዚህ ነጥቦች ላይ በጉባኤ ከፍ ያለ ክርክር  የተደረገ ቢሆንም፥ አለቃ ታየን ለመርታት የሚያስችል በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ስላልተገኘ፥ ለወደፊቱ አለቃ ታየ እንዲህ ያለ ትምህርት ለሕዝብ እንዳያስተምሩ ተገሥጸው ተለቀቁ፡፡ ይሁን እንጂ በውሳኔው የተበሳጩ ካህናት በጊዜው የዐፄ ምኒልክ ባለ ሙሉ እንደ ራሴ ለነበሩት ለራስ ተሰማ አመልክተው አለቃ ታየን ያለ ሕግ አስይዘው በወኅኒ አኖሯቸው፡፡

በወኅኒ ሳሉ ከገጠሟቸው ግጥሞች መካከል የሚከተሉት ስንኞች ይገኙባቸዋል፡፡
“አያችሁት ብዬ ጥበቡን የአምላክ፣
እኔ ክስ ፈርቼ እንዳልታወክ፣
አጥብቄ ብተኛ እንቅልፍ ያለ ልክ፣
ከሳሽ አስነሥቶ ወንጌሉን ሲሰብክ፣
የኔ ወኅኒ መግባት በጣም ደስ ብሎኛል፣
አምላኬ በኔ ስም ተመስግኖልኛል፡፡
እንኳን መጣህልን ሰው ሁሉ ይለኛል፡፡
ለወንጌሉ ስብከት ጊዜ አጋጥሞኛል፡፡”

በወኅኒ ጥቂት ከቈዩ በኋላ በቁም እስር እንዲቈዩ ተደረገ፡፡ ኀይሉ ከበደ በመመረቂያ ጽሑፉ ላይ እንዳሰፈረው፥ "በ1904 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ፍጹም ዐርነት ከአገኙ በኋላ እስከ 1909 ዓ.ም. ድረስ ከመንግሥት ምንም ዐይነት ድጋፍ ሳያገኙ ተቀመጡ፡፡ ከመጋቢት 1 ቀን በ1909 ዓ.ም. በመታሰራቸው ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የታሪክ መጻፍ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ከመንግሥት ደመወዝ እንዲከፈላቸው ታዞ ታሪኩን መጻፍ ቀጠሉ፡፡ በኋላ በ1912 ዓ.ም. ለመንግሥት አማካሪነት ተመርጠው ይሠሩ ነበር" ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡ ብዙ ሊቃውንትም በስውር ከጨለመ በኋላ እየመጡ ከአለቃ ይማሩ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ አገራቸውንና ሕዝባቸውን እያገለገሉ ሳሉ ታመው ነሐሴ 15 ቀን 1916 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም መከራና ሥቃይ በሞት ተለዩ፡፡ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ብዙ መከራና እንግልት ያደረሱባቸው ወገኖች በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቀብር ቦታ በመንፈጋቸው፥ ዐፄ ምኒልክ ለውጪ ሰዎች በሰጡትና ከከተማው ወጣ ባለው ስፍራ በሚገኘው መካነ መቃብር ነው የተፈጸመው፡፡     

የአለቃ ታየ ነገር በዚህ አላበቃም፡፡ ከተቀበሩ በኋላ ምድር ሬሳቸውን አልቀበል ብላ አስቸገረች ተብሎ ይወራ ነበር፡፡ ይህን የሰማ አለቃን በሚገባ የሚያውቅ አንድ ሰው፥ በምን ምክንያት ነው እንዲህ የሆነው ብሎ ቢጠይቅ፥ ምድር እንኳ የኀጢአታቸውን ብዛት ስትመሰክር ነው አሉት፡፡ እርሱም ተሳስታችኋል፤ (ምድር እንዲህ አታደርግም እንጂ) ምድር እንዲህ ካደረገች ምክንያቷ፥ "ታየን ያህል ታላቅ ሊቅ እኔ ልሸከመውና ሥጋውንም ልበላ አልችልም ብላ ነው" ብሎ መለሰ ይባላል፡፡ 

አለቃ ባለፉ ጊዜ እኅታቸው ላቀች አላምነህ ከገጠሙላቸው የሙሾ ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚሉት ይገኛሉ፡፡
"አንገቴ ቢቈረጥ በሰይፍ በካራ፣
አልሰግድም ለሥዕል ለሰው እጅ ሥራ፣
ይህንን ቢናገር በቈራጥነት፣
አቡንና ዕጨጌ ብዙ ካህናት፣
በዚህ ምክንያት ነው የፈረዱበት፣
ይዘው የከተቱት ከጨለማ ቤት
አትብሉ ስላለ የሙታን ንብረት፣
ከወኅኒ ቤት አስረው የዘጉበት ሣንቃ፣
ብሎ ተናግሮ ነው የወንጌል ቃል ይብቃ፡፡"

እናስተውል!
የክርስትና መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ክርስትና የመሥራቹን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንና የደቀ መዛሙርቱን አርኣያ ይከተላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የነበሩና ከዚህ እውነተኛ መሠረታቸው ወደ ሰው ትምህርት፣ ባህል፣ ሥርዐት፣ ልማድና ወግ የተንሸራተቱ አብያተ ክርስቲያናት ግን፥ ቅድሚያ የሚሰጡት የእግዚአብሔር ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን፥ ለሰው ትምህርት፣ ሥርዐትና ወግ ነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የክርስቶስን ሳይሆን የክርስቶስ ተቃዋሚዎች የነበሩትን፦ የአይሁድን፣ የካህናት አለቆችን፣ የጸሐፍትንና የፈሪሳውያንን ምሳሌነት ይከተላሉ፡፡

ክርስትና የሚሰደዱለት ሕይወት ነው እንጂ የሚያሳድዱበት ሃይማኖት አይደለም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ስለ ጽድቅ ይሰደዳል እንጂ ስለ ሰው ወግና ልማድ አያሳድድም፡፡ ስለ እግዚአብሔር እውነት ይገፋል እንጂ ስለ ሰው ሥርዐት አይገፋም፡፡ ስለ ወንጌል ይንገላታል እንጂ ስለ ሰው ትምህርት አያንገላታም፡፡ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ይሞታል እንጂ ስለ ኀላፊ ክብርና ስለ ጠፊ ጥቅም አይገድልም፤ ክርስትና መሰደድ እንጂ ማሳደድ ባሕርዩ አይደለምና፡፡ ጌታ የተናገረውም ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፤ “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ፡፡ ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስላይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል፡፡ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል ዐስቡ፡፡ እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ፡፡ ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል፡፡  እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ስለ ኀጢአታቸው ምክንያት የላቸውም” (ዮሐ. 15፥18-22)፡፡

በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” (2ጢሞ. 3፥12)፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወደ ሰው ትምህርት፣ ባህል፣ ሥርዐት፣ ልማድና ወግ የተንሸራተቱ ወገኖች ግን እንዲህ አይደሉም፡፡ አርኣያዎቻቸው ክርስቶስንና ተከታዮቹን እንዳሳደዱ ሁሉ፥ እነርሱም ከባህላዊና ልማዳዊ ክርስትና ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና ዘወር ያሉትን ክርስቲያኖች፥ ፀረ ማርያም፣ መናፍቅ፣ ወዘተ. የሚሉ ስሞችን ለጥፈው ያሳድዳሉ፡፡ እንዲህ በማድረጋቸውም እግዚአብሔር ይደሰታል ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህን የሚያደርጉት እግዚአብሔርን ስላላወቁ መሆኑን ቅዱስ ወንጌል ይመሰክርባቸዋል (ዮሐ.16፥1-4)፡፡ ማሳደድ ለእነርሱ ትልቅ የቀናተኛነት መገለጫ ነው፡፡ የቀድሞው ሳውል ሰለ ነበረው ቅናት ታላቅነት ሲገልጥ፥ “ስለ ቅናት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ” (ፊል. 3፥6) ብሏል፡፡ በእግዚአብሔር ስም ተሰልፌአለሁ ብሎ እግዚአብሔርን መቃወም ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

ጌታና ደቀ መዛሙርቱ የተሰደዱት ክርስቲያን ባልሆኑ ወገኖች ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባለው ዘመን ግን ክርስቲያኖችን እያሳደዱ ያሉት ፀረ ክርስትና ዐቋም ያላቸው ወገኖች ብቻ አይደሉም፤ ክርስቲያን ነን የሚሉ ወገኖችም አሳዳጅ ሆነው ተሰልፈዋል፤ የክርስትና መርሕ እንዲህ አይደለምና፥ ክርስቲያን ነኝ የሚል ክርስቲያንን ማሳደዱ እንዴት አሳዛኝ ነው!!

ዋቢ መጻሕፍት

ገብረ ዮሐንስ ገብረ ማርያም (1994) አጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፡፡ (ስፍራውና ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ)፡፡
ኀይሉ ከበደ (1997) የአለቃ ታየ የሕይወት ታሪክ፡፡  አዲስ አበባ፡፡
ሰሎሞንና (1956) ደማቆቹ ፀሓያት፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment