የጋብቻ ትምህርት
የእግዚአብሔር
ሥራ ምን ጊዜም መልካም ነው
የሰው ባሕርይ ከቤተ ሰቡ የተወረሱ ድክመቶችን የሚያንጸባርቀው በሁለት ተቃራኒ
መንገዶች ሊሆን ይችላል፡፡ የአባቶች ድክመቶች ምናልባት ባለማወቅ የሚደጋገሙና የበለጠ እየተባባሱ የሚሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ወይንም በራሳቸው ውሳኔ ወደ ሰፋ ልዩነት የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ በሚፈልጉ ተከታይ ትውልዶች ግልጽ ተቃውሞ ይገጥማቸው ይሆናል፡፡
አብርሃም ልጅ ስላልወለደ ተጨንቆ በአንድ ወቅት አባ ወራነቱን ትቶ የሣራን አስተሳሰብ
በመከተል ድክመቱን ሲገልጥ፥ ልጁ ይሥሐቅ ከሚስቱ ከርብቃ ጋር ስለ ልጆቻቸው የሚጸናና የሚዘወተር አለመግባባትን ለመቈጣጠር
ባለመቻሉ የባሰውን ድክመት አሳየ፡፡ የይሥሐቅ ታናሽ ልጅ ያዕቆብ ግን በወላጆቹ የተለመደ ድክመት እንዳይደገም በሌላ አቅጣጫ ሲሄድ
በዚህ ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡
የእልከኛ ብላቴና
ዐሳብ
የታናሽ ልጁ የያዕቆብ ባሕርይ ግን በሁለተኛ መንገድ የሚታይ ነው፡፡ ያዕቆብ በራሱ
ፍላጎት ተነሣሥቶ የራሱን ሚስት ለማግባት ብልጠት ያለው ሰው ስለ ነበረ፥ ከመጀመሪያ ጀምሮ ተንኰለኛና ሚስቱን በራሱ ቍጥጥር
ሥር ለማድረግ የቻለ ሰው ነበረ፡፡ የእግዚአብሔርን ጥበቃና እንክብካቤ በተመለከተም ለያዕቆብ የነበረው አመለካከት፥ በመታዘዝ
ጸጥ ብሎ ወደ መሠዊያው ቦታ መሥዋዕት ለመሆንና በኋላም በአባቱ በአብርሃምና በሎሌው በኤሊዔዘር ወደ ተዘጋጀችለት ሚስት ምርጫ
ካዘነበለው ከአባቱ ከይሥሐቅ ብዙ የማይመሳሰል ነበር፡፡ ያዕቆብ በልጅነቱ ወቅት የነበረውን ሁኔታና በተለይም በአባቱና በእናቱ
መካከል የነበረውን አለመግባባት ተገንዝቦ፥ ሊሆን ያለው ነገር እንደሚመጣ በመወሰን ሁኔታዎችን በተለየ መንገድ ፈጽሞ እውነተኛ
የቤተ ሰብ መሪ መሆን ይፈልግ ነበር፡፡ ያዕቆብ የቃል ኪዳን በረከትን ከታላቅ ወንድሙ ከዔሳው “ከሰረቀ” በኋላ በዚህ ሁኔታ
ውስጥ የሠራች የእግዚአብሔር እጅ በይሥሐቅ ዘንድ ስትታወቅና ስትረጋገጥ፥ ዔሳው ያዕቆብን ሊገድለው በመወሰኑና ከሥርዐት ውጪ
ከአሕዛብ ሚስት በማግባት በወላጆቹ ላይ የዐመፀ በመሆኑ ነው፡፡ የእነዚህ ሁኔታዎች አጠቃላይ ቅንጅት ሎሌ ከመላክ ይልቅ ወደ
ካራን ሄዶ በዚያ ከሚገኘው ቤተ ሰባቸው መካከል ሚስት ለመፈለግ ያዕቆብን ራሱን እንዲልክ ገፋፋው፡፡ ይህንም ያደረገው ይሥሐቅ
ምናልባት ከራሱ የሕይወት ልምድ በመነሣት ለልጁ ለያዕቆብም የሚያስፈልገውን ተረድቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ያዕቆብም በሕይወቱ ውስጥ
እግዚአብሔር ከነበረው ዐላማ አንጻር የእግዚአብሔር ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ በግል ሕይወቱ ውስጥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዴት
በጥልቀት እንደሚሠራና ምን ያህል እንደሚከተለው ጥቂት በማሰብ ጕዞውን ጀመረ፡፡ ያዕቆብ ራሱ ቤቴል (የእግዚአብሔር ቤት) ብሎ
በጠራው ቦታ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው የመጀመሪያ ግንኙነት ለእግዚአብሔር ቅን ታዛዥነትን ከማሳየት ይልቅ ከእግዚአብሔር
ጋር ለመስማማት በመነጋገር ብቻ አከተመ፡፡ ይህን አስተማማኝ ስሜት ይዞ ያዕቆብ ካራን አጠገብ በምትገኘው መስጴጦምያ (ሶርያ)
ደረሰ፡፡ እዚያም አጐቱን ላባን የሚያውቁ እረኞችን በአንድ ጕድጓድ አጠገብ አገኘ፡፡ በእረኛነት ላይ ከነበረችዋ ከላባ ልጅ
ከራሔል ጋር እረኞች አስተዋወቁት፡፡ ያዕቆብም ለማግባት የሚፈልጋት ሚስቱ እንደ ሆነች በማወቅ ራሔልን ወደዳት፤ ሚስት ትሆነውም
ዘንድ ራሔልን እንዲሰጡት በባላ ቤት ውስጥ ሰባት ዓመት ለማገልገል ተስማማ፡፡
የአሰቃቂ ጋብቻ ማስጠንቀቂያ
ከዚህ በኋላ የታየው ከቍጥጥር ውጪ የሆነ የያዕቆብ የራሱ የግል ባሕርይ በመሆን
በዘፍጥረት ም. 29-31 ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ጠቃሚ ትምህርቶችን ልንማር እንችላለን፡፡
ያዕቆብ የራሱን የማታለል ፍሬ ሲለቅምና በዐጸፋውም በራሔል ፈንታ ታላቅዋን ልጁን
ልያን በሚስትነት በሰጠው በላባ ሲታለል፥ ለምርጫው የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመሻት ረገድ ያደረገው ጥረት የለም፡፡
የእግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ላይ የመወሰን ሥልጣንና ለሰው ልጅ የሚያደርገውን እንክብካቤ አምኖ በመቀበል መንፈስና በንስሓ
አልቀረበም፡፡ ምናልባት ክርስቲያኖች የኑሮ ጓደኛቸው ማን መሆን እንደሚገባው በማወቅ በኩል ጠንከር ያለ አቋም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በዚህ ግላዊ ፍላጎት ላይ እግዚአብሔር
ለራሱ ዐላማ ሲል በጊዜያቱ ሊወስን ይችላል፡፡ የበረከት መንገድ ጋብቻ ሁለቱ ተጋቢዎች ለእግዚአብሔር መንግሥት ዐላማ ተባብረው እንዲያገለግሉ
እንጂ፥ እንዲሁ የግል ፍላጎትን ብቻ ለማርካት እንዳልሆነና በእግዚአብሔር እንደ ተመሠረተ በቅንነት ተረድቶ ለእግዚአብሔር እጅ መታዘዝ
ነው፡፡ እግዚአብሔር ተጋቢዎችን በጋብቻ ሕይወታቸው ወቅት መምራት ሲጀምር፥ አንደኛው በሌላው ተደሳች ለመሆን የሚበቃ ፍቅርን እግዚአብሔር ራሱ በመካከላቸው መፍጠር ይችላል፡፡ አንደኛቸውን
ለአንዱ የሰጠ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን ተጋቢዎች እየተረዱት የሚሄዱ በመሆናቸው በመካከላቸው ያለው ፍቅር እያደገ ይሄዳል፡፡
ያዕቆብ ልያንና እንዲሁም ራሔልን ለማግባት ሲወተውት በዘፍጥረት 2፥24 አንድ ሰው
ከሚስቱ ጋር ፈጥኖ ለመጣመርና ከእርስዋም ጋር አንድ አካል ለመሆን እናትና አባቱን መተው አለበት ከሚለው በእግዚአብሔር
ከተደነገገው የመጀመሪያ ሥርዐት ወጣ፡፡ የያዕቆብ የሕይወት ታሪክ በአብዛኛው በሁለቱ እኅትማሞች መካከል የነበረ የምቀኛነትና
የውጥረት ታሪክ ነው፡፡ ምክንያቱም እኅትማሞቹ እያንዳንዳቸው ልጅ በመውለድ፥ አንዳንድ ጊዜም በአሕዛብ ልማድና የማታለል ዘዴዎች
በመጠቀም፥ ሚስትነታቸው በያዕቆብ ዘንድ እንዲታወቅላቸው ለያዕቆብ ፍቅር ለመወዳደር ሙከራ አድርገዋልና፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ
የታየው የአባታቸው የላባ የዘወትር ጣልቃ ገብነትም ቤተ ሰቡን በማቋቋምና በማደራጀት በኩል ለያዕቆብ ትልቅ እንቅፋት ነበረ፡፡
እግዚአብሔር ለጋብቻ ከደነገገው ሥርዐት መውጣት ወደ ችግርና አለመስማማት ያመራል፡፡
አስደናቂው የእግዚአብሔር ዐላማ
የያዕቆብ ባሕርይና ስሕተቶቹ የእግዚአብሔርን የፍቅር ዐላማ አላሸነፉትም፡፡ ቤት ውስጥ
ትርምስ ወይም የአጠቃላይ ሥርዐት ጥፋት የያዕቆብ የእልከኛነት ባሕርይ አሳዛኝ ውጤት ነበረ፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ሁሉ
እግዚአብሔር የራሱን ዐማዎች በማሳካት ላይ ነበረ፡፡ ከዚህ ከተመሰቃቀለ (ሥርዐት ካጣ) ቤተ ሰባዊ ሕይወት ውስጥ ለሕዝቡና
ለእስራኤል መሪዎች መሆን የሚገባቸውን ሰዎች አስገኘ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ የቤተ ልሔም ሽማግሌዎች ከሩት ጋር በተጋቡበት ጊዜ
ለቦኤዝ፥ “እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባዋን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ
ያድርጋት” (ሩት 4፥11) በማለት ተናገሩት፡፡ ለያዕቆብ ወደ ንስሓ ለመምጣትና እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ብዙ ዓመታት
ፈጅቶበታል፡፡ ሆኖም ሐዲስ ኪዳን በዕብራውያን 11፥21 ላይ ስለ እርሱ የሚነግረን የመጨረሻ ታሪኩ፥ ለእግዚአብሔር
በመታዘዛቸው የዮሴፍን ልጆች የባረከ፥ “በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ የሰገደ” የእምነት ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በያዕቆብ
የጋብቻና የቤተ ሰብ ሕይወት ማዕበል ውስጥ ሁሉ እግዚአብሔር በታማኝነት ያዕቆብን ጠበቀው፤ በመጨረሻም እርሱ የሚፈልገውን ዐይነት
ሰው አደረገው፡፡
መደምደሚያ
ከኀጢአት ኀይልና ከጥፋት ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ የዳንን ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን፥
በቀን ተቀን ሕይወታችን ውስጥ የዳኑ ሰዎች የሚኖሩትን ሕይወት ለመኖር መማር ይኖርብናል፡፡ “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም
መቀደሳችሁ ነውና፡፡” (1ተሰ. 4፥3) ሁላችንም የእግዚአብሔር ሥነ ሥርዐት ከሚያስፈልገው ከአሮጌው ሕይወታችን የተወሰኑ
የድክመት ባሕርያትን በጋብቻችን ላይ እናመጣለን፡፡ እግዚአብሔርም እንድንቀደስ ያለውን የራሱን ፈቃድ በአንድ ወይም በሌላ
መንገድ ለመፈጸም ጋብቻችንን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ነገሮች ሁሉ ተዛብተው ተስፋ በመቍረጥ ላይ መሆናችን ቢሰማንም እንኳ፥
የያዕቆብ የጋብቻ ሕይወት መልእክት “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዐሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ
እናውቃለን፡፡” (ሮሜ 8፥28) በሚለው ቃል ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ምንም ዐይነት ችግር ያጋጥመን፥ ወደ እግዚአብሔር በንስሓ
ከቀረብንና ነገሮችን ሁሉ እንዲያቀናልን በእርሱ ላይ ከታመን ለያዕቆብ እንዳደረገው እግዚአብሔር እውነተኛ የአምልኮ ሰዎች ወደ
መሆን ደረጃ ያመጣናል፡፡ የሐዋርያው ጳውሎስ አባባል በሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለመታመን አነቃቂያችንም
የሚያሳስበንም ይሁን “የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ፤ የሚጠራችሁ የታመነ ነው እርሱም ደግሞ ያደርገዋል” (1ተሰ. 5፥23-24)፡፡
በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment