Monday, September 23, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


አለቃ ነቅዐ ጥበብና አገልግሎታቸው

አለቃ ነቅዐ ጥበብ በመካከል ካለችው ከአሮጌዋ አትሮንስ ፊት ለፊት ተቀምጠዋል፡፡ አለቃ ደምፀ ቃለ አብ በስተቀኛቸው የኔታ ማኅተመ ሥላሴም በስተግራ አጐዛና ሰሌን በተነጠፈበት መደብ ላይ ጕብ ብለዋል፡፡ ቀሳውስት፥ ዲያቆናትና ምእመናን የአለቃን እልፍኝ አጨናንቀዋታል፡፡ ከጥማት ለመርካት በምንጭ ዙሪያ የተሰለፉ ዋልያዎችን ሁኔታ የሚያስታውስ ትዕይነት ነበር (መዝ. 41/42፥1)፡፡

በጉባኤው የተገኙ ዐዳዲስ ታዋቂ ዕድምተኞችም ነበሩ - መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን፥ አጋፋሪ ዕንባቆም ኀይለ ልዑልና ተማሪ የማነ ብርሃን፡፡ የሁሉም ዐይኖች በመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞንና በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ላይ በየተራ ያርፉ ነበር፡፡አለቃ ደምፀ ቃለ አብ ጉባኤውን በጸሎት እንዲከፍቱ ስለ ተጋበዙ ብድግ አሉ፡፡ በካበቸው ስር ከለበሱት ባለዘርፍ ኩታቸው አንደኛውን ጠርዝ አመቻችተው በካባቸው ላይ ጣል አደረጉት፤ ማደግደጋቸው ነበር፡፡

በቅድስናው ለከበረው ብቻውን በክብር ከፍ ከፍ ላለው የእስራኤል ቅዱስ ውዳሴንና ምስጋናን መሠዋት ጀመሩ፡፡ የእምነት አባቶችን የአብርሃምን፥ የይሥሐቅንና የያዕቆብን አምላክ ስም ባረኩ፡፡ “ብቻውን ተኣምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ የከበረው ስሙ ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይሙላ፤ ይሁን ይሁን፡፤” (መዝ. 71/72፥18-19) እያሉ፥ በመቀጠል ይህን ያህል ሕዝብ በፉጨት ጠርቶ በቃሉ ዙሪያ በማከማቸቱ ጌታን አመሰገኑ፡፡ በፊቱ የፈሰሰውም የጉባኤው አባላት ልብ እንደሚቃጠል ቍርባን ሆኖ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዲያርግና እንዲቀበለው ማለዱ፡፡ በማያያዝም የክብር መንፈስ እንዲወርድ፥ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ራሱን ለውርደት አሳልፎ የሰጠውንና አሁን በኀይል ቀኝ ሆኖ የሚመሰገነውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በጉባኤው መካከል ከፍ ከፍ እንዲያደርገው፥ መሲሓዊ አዳኝነቱንና ጌትነቱን ለእያንዳንዱ ሰው ነፍስ እንዲያውጅም ተማጸኑ፡፡

በአለቃ ጸሎት ከሥጋና ደም ተለይተው የተነሣሡትና ወደ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ወደሚገኝበት ሉዓላዊ ስፍራ የደረሱት የጉባኤው አባላት ነፍሳት በክብር መንፈስ ነዲድ እሳት እየተቃጠሉ፥ እየቀለጡና እየነደዱ በኅብረት በሚያሳርጉትና መልካም መዐዛ ባለው የጸሎታቸው ዕጣን ጢስ ውስጥ ራሳቸው ተዋሕደው አንድነታቸው እንደ ተደበላለቀ የሽቱ ቅታር (የተቀመመ ሽቱ) በመንፈስ ሲትጐለጐል ጉባኤውን ከማወዱ ሌላ የምድርን መሠረትና የሰማያትን አዕማድ ያናወጠ መሰለ፡፡

አለቃ ደምፀ ቃለ አብ ጸሎታቸውን በመቀጠል፥ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩ ብርሃን እንዳይበራላቸው የሰዎችን ልብ ለማጨለም የሸመቀውንና ለውጊያ የተሰለፈውን የሰይጣንን መንፈስ ተቃወሙ፡፡ ጕልበት ሁሉ በሚንበረከክለት፥ አንደበት ሁሉ በሚገዛለት፥ በእምነት የጠራውን ሁሉ የማዳን ኀይል ባለው፥ እንዲሁም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉ ፍጥረታትና ኀይላት ሁሉ በሚርዱለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና ሥልጣን ርኩሳን መናፍስት ከአካባቢው እንዲወገዱ አዘዙ፡፡ ገናም ጸሎታቸውን በመቀጠል ላይ እንዳሉ ተሰምቶ የማያውቅ የኀይለኛ ጩኸት ድምፅ ከጉባኤ መካከል ተሰማ፡፡ “ወይኔ ሳተናው! ተቃጠልኩ፥ ነደድኩ” አለናም ድል መነሣቱን ለጉባኤው አበሠረ፡፡ አለቃም ተሸናፊውን መንፈስ ጸጥ እንዲል በእግዚአብሔርም አርያማዊ እሳት እየተቃጠለ እንዲቈይ በጌታ ስም አዘዙ፡፡

በጉባኤው መካከል አንድ አረጋዊ ወድቀው በመንፈራገጥና በማጓራት ላይ በነበሩበት ጊዜ፥ ጉባኤው በጸጥታና በመንፈስ ጸሎቱን እንዲቀጥል አለቃ ደምፀ አሳሰቡ፡፡ በአረጋዊው ያለ መንፈስ በምጥና በጻዕር እየተጨነቀም ቢሆን ጸጥ አለ፡፡ ምስግናና ልዕልት በመረዳዳት አረጋዊውን አመቻችተው በጉባኤው መካከል አጋደሟቸው፡፡ ጉባኤው ግን ባለ መረበሽ ከአለቃ ጋር በአንድ መንፈስ ይጸልይ ነበር፡፡ አለቃም እግዚአብሔርን ማመስገን ቀጠሉ፡፡

“እስመ አንተ ውእቱ ዘወሀብከነ ሥልጣነ ከመ ንኪድ ከይሴ ወአቃርብተ ወዲበ ኵሉ ኀይለ ጸላኢ … ከመ ንፍታህ ዘኢይትፈታሕ - እባቡንና ጊንጡን እንድንረግጥ በጠላትም ሁሉ ላይ እድንጫማ … ሊፈታ የማይችለውን ቋጠሮ እንድንፈታ ሥልጣንን የሰጠኸን አንተ ነህና፥ አንተ ነህኮ …” በማለት ጌታን አከበሩ፡፡

መንፈሱ አሁንም እየተሸበረና እየተቃጠለ ስለ ነበረ፥ “ተቃጠልኩ፥ ልውጣ ይፈቀድልኝ ወይኔ ሳተናው! ተዋረድኩ” አለ፡፡ በቅድሚያ እንዴት ወደ መሪ ጌታ ንዋይ እንደ ገባ በዝርዝር እንዲናገር በጸሎት ላይ እንዳሉ አለቃ መንፈሱን አዘዙት፡፡ ጉባኤውም በጸሎት ላይ እንዲቈይ አሳሰቡ፡፡ መንፈሱም ታዘዘ፥ እንዲህም ሲል ቀጠለ “ዘርዐ ያዕቆብ ስምዖን በጓደኞቹ ንዋይ ሲሞን ከመባሉ በፊት ወጣት በነበረበት ጊዜ ዜማ ሊማር ወደ ቤተ ሳይዳ መጣ፡፡ በጥረቱ ትምህርትን ለመቅሠም የማይወድ ስለ ነበር፥ በአቋራጭ የብዙ ዕውቀት ባለቤትና በዐጭር ጊዜ ሹምም ሀብታምም የመሆን ብርቱ ፍላጎት ያደረበት ወጣት ነበር፡፡ የመምህሩን ጫማ ከሳመና ከተዋወቀ በኋላ የበርጤሜዎስ ባልደረባ ሆኖ እንዲማር ተፈቀደለት፡፡

በርጤሜዎስ ይህ ቀረው የማይባል ማሕሌታይ ነበረ፡፡ መምህሩም ይወዱታል፤ ያመሰግኑታል፤ ያከብሩታል፡፡ ዐዲስ ተማሪ ሲመጣ በፊታቸው ሞገስ ያገኘ ከሆነ ለበርጤሜዎስ በባልደረባነት ይሰጡታል፡፡ ዘርዐ ያዕቆብም በርጤሜዎስን እየመራ፥ ልብሱን እያጠበ፥ ምግቡንም እያዘጋጀ ያገለግለው ጀመር፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ ታዋቂ ሰው ከመሆን ምኞቱ ሌላ የሰውን ልብ በጨዋታና በአገልግሎት ወደ እርሱ የማዘንበል ችሎታ አለው፡፡ ከወደ ትምህርቱ ግን በገፍ የማይጐርስ ሲሆን፥ የጐረሰውንም አላምጦና አጣጥሞ የመዋጥ ችሎታ አልነበረውም፡፡ የቀለም ትምህርቱን ቶሎ የማይዝ፥ በትግልና በብዙ ጥረት የያዘውንም ቶሎ የሚረሳ ቢሆንበት በርጤሜዎስ ተጨነቀለት፡፡

አንድ ቀን በሰሙነ ኤጲፋኒያ (አስተርእዮ) ተማሪዎች በየክብረ በዓሉ ለመገኘት በሩቅም በቅርብም ተበትነው ስለ ነበረ፥ በትምህርት ቤታቸው ዘርዐ ያዕቆብና በርጤሜዎስ ብቻ ከጥቂት በሽተኛና ደካማ ተማሪዎች ጋር ቀሩ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በርጤሜዎስን፥ “የኔታ! አስተርእዮ ምን ማለት ነው?” “አስተርእዮ ማለት ማሳየት መግለጥ ማሳወቅ፥ ምስጢሩን ማፍታታትና ማስረዳት ማለት ሲሆን፤ ወቅቱ ዘመነ አስተርእዮ የመባሉ ምክንያት በያዝናቸው ሰሙናት የሁለት ዐበይት ምስጢራቶች ክሥተት ስለሚታሰብ ነው፡፡

አንደኛ በወንጌላት ውስጥ ከእድገቱ ጀምሮ እስከ ጥምቀቱ ድረስ ስላለው የረዥም ጊዜ ማለት የ30 ዓመታት አኗኗሩ ብዙ ያልተተረከለት፥ በቤተ ሰቡ ውስጥ እንደ ማንኛውም ልጅ እያገለገለ የቈየው የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲጠመቅ ማንነቱ ይፋ ወጥቷል፡፡ ለምሳሌ፡- የኤልሳቤጥ ልጅ ዮሐንስ ኢየሱስን የዝምድናውን ያህል ያውቀው የነበረ ቢሆንም፥ የማንነቱን ውስጠ ምስጢር አልተረዳም ነበር፡፡ “ወአንሰ ኢያአምሮ ወባሕቱ ዘፈነወኒ ከመ አጥምቅ በማይ ውእቱ ይቤለኒ ዲበ ዘርኢከ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ ወይነብር ዲቤሁ፤ ውእቱኬ ዘያጠምቅ በመንፈስ ቅዱስ፡፡ ወለልየ ርኢኩ ወአነ ሰማዕቱ ከመ ዝንቱ ውእቱ ወልዱ ለእግዚአብሔር፡፡ - እኔም አላውቀውም ነበር፤ ዳሩ ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ፡፡ እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ፡፡” (ዮሐ. 1፥33-35) ለማለት በቅቷል፡፡

“ሁለተኛ፡- የናዝሬቱ ኢየሱስ በነቢያት የተነገረለትና የተጠበቀው መሲሕና አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ለመመስከርና ለማስተዋወቅ በዮርዳኖስ አብና መንፈስ ቅዱስ በአንድ ላይ ስለ ተገለጡ የሥላሴ (ሦስትነት) ምስጢር ገሃድ ሆኗል፡፡ ስለዚህም ይህ መታሰቢያ ጊዜ አስተርእዮ ሊባል በቅቷል” አለው፡፡ በርጤሜዎስ እንዲህ የቃሉን ምስጢር ከመሠረታዊ መነሻው በመጀመር ተንትኖ ሲያስረዳው ዘርዐ ያዕቆብ ቀና፡፡ እርሱም ቢሳካለትና የጀመረውን የዜማ ትምህርት ቢያጠናቅቅ ቅኔንና ትርጓሜ መጻሕፍትን አጣጥሞ ለማወቅ ጊዜ መውሰድ እንደማይኖርበት ወሰነ፡፡ ግን እንዴት? ርቀቱን ጥቂት ለማየት ሞከረና በፍጥነት አቋረጠ፡፡ “የለም! አቋራጭ መንገድ መገኘት አለበት” አለ፡፡ “ግን እንዴት?” እንዴት ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለብኝ እንዴ! የለም መልስ የመስጠት ግዴታ አይኖርብኝም” “ይኖርብሃል እንጂ!” “የለም አይኖርብኝም!” የሚሉት ክርክሮች በውስጡ እየተመላለሱ ሲያስተጋቡ “ዘርዐ ያዕቆብ!” ተባለ “አቤት የኔታ”
“እስኪ ወደ ዐረህ እንውረድ”
“እሺ የኔታ፡፡”

ዘርዐ ያዕቆብ በርጤሜዎስን እየመራ ወደ ዐረህ ወረዱ “ትልቁ ዕፀ ከርዴን ካለበት ቦታ ስንደርስ ንገረኝ” ብሎ ስለ ነበረ “ይኸው ደረስን” አለው፡፡
“በአካባቢው ሰው ስላለመኖሩ ርግጠኛ ነህን?” ሲል ጠየቀው በርጤሜዎስ፡፡
“አዎን ከወፎች በስተቀር ምንም ማንም የለም የኔታ”
“ይኸውልህ እዚህ ዛፍ ላይ ተቀጥላ አለ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ ተቀጥላ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃለህ? በዕፅ ከርከዴን ላይ ቢበቅልም ቅርንጫፍነቱ ለከርከዴን አይደለም፤ በምንም አይመሳሰሉም፤ ባዕድ ነው፥ ይታይሃል?” አለ በርጤሜዎስ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ አንጋጠጠ፤ በዐይኑ ቃኘ፤ ዛፉን እየዞረ ፈለገ ፈላለገ፤ በአንዳንድ  ቅርንጫፍ ላይ ዐይኑ ዐረፈ፡፡
“አዎን አየሁት፤ ያ … ውና ሩቅ ነው፤ እዛፉ ላይ ርቆ ያልወጣ ሰው አይደርስበትም፡፡” አለ ዘርዐ ያዕቆብ እንዳንጋጠጠ፡፡
“አየህ ዘርዐ ያዕቆብ! ልብ አድርግ፤ ለሰው አይነገርም፡፡ አንተ በቅንነት ብዙ አገልግለኸኛል፤ ትምህርቱ ደግሞ ከብዶሃል፤ አዝኜልሃለሁ፡፡ ዋጋህንም ለመክፈል ስል ሆሳዕና (መድኀኒት) ላደርግልህ ዐስቤአለሁ፤ መወጣጫውን ፈልግና እዛፉ ላይ ውጣ ከተቀጥላው አንዱን ቅርንጫፍ ገንጥለኸው አምጣ” አለ በርጤሜዎስ በኵራት መንፈስ፡፡

የዘርዐ ያዕቆብ ልብ በደስታ መታ፤ ቸኮለ፣ በሌላ ጊዜ ለሌላ ጕዳይ ቢሆን ዛፉ ላይ  መውጣት ዕርሙ ነበር ይፈራል፤ አባቱም የሞተው ለሞፈር ትሆናለች ያላትን መለሎ ዕንጨት ገደል ላይ ከበቀለ ዛፍ ሲቈርጥ በሙሉ ኀይሉ የቆመበት የዛፉ አንደኛ ክንፍ በመገንጠሉ እንደ ሆነ በልጅነቱ ተነግሮት ስለ ነበር አሁን ከሚያየው ዛፍ ላይ ለመውጣት ባልሞከረ ነበር፡፡ ግን እንዴት እንደ ወጣው ሳያውቀው እንደ ጕሬዛ ከአንዱ ቅንጫፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገረ ተቀጥላው ዘንድ ሲደረስ ስለት ሊነካው አይገባም ተብሎ ተነግሮት ነበርና አንደኛውን ዐይኑ ያረፈበትን ተቀጥላ በእጁ ታግሎ ገነጠለው፡፡ ወደ መሬት ሊወረውረው እጁን እንደ ዘረጋ “ይረክሳልና ከመሬት ላይ ሳትጥል እንደ ጨበጥህ አምጣ” የተባለውን አስታወሰ፡፡ በአንድ እጁ ተቀጥላውን እንደ ጨበጠ፥ ላለመውደቅም በሁለተኛው እጁ እየተረዳ እንደ ምንም ብሎ ከዛፉ ወረደ፡፡ “ይኸው የኔታ” አለ፡፡
“በል ትክል ደንጊያ ፈልግ፤ ትክል ደንጊያ ማለት ይገባሃል! በሰው ያልተተከለ፥ በተፈጥሮው ከመሬት ጋር የተያያዘ ዐለት ማለት ነው” በርጤሜዎስ አዘዘው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በአካባቢው እየተዘዋወረ በዐይኑ እየቃኘ ፈለገና “ያውና እዚያ” አለ፡፡ በእጁ እያመለከተ፥ በርጤሜዎስ ያይለት ይመስል፡፡

በርጤሜዎስ ከዐለቱ ላይ ወጣ፤ ዘርዐ ያዕቆብም እንደ ታዘዘው በዐለቱ ላይ በበርጤሜዎስ እግር ሥር ተቀመጠ፡፡ በርጤሜዎስም ድግምቱን ተያያዘው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በድግምቱ የሚያገኘው ውጤት ምን እንደሚሆን ለማወቅ ወደ ርሱም ለመድረስ በመጓጓትና በማሰላሰል ፈዞ ከቈየ በኋላ፥ ከድግምቱ አንዳንድ ቃል፥ “ዲያብሎስ ሰይጣን፥ ብርያል፥ ቤልሆር” የሚለው እየተወረወረ በጆሮው ሲገባ አነቃው፡፡ ሰውነቱን ሰቀጠጠው፥ አእምሮው ተረበሸ፤ የደም ሥሮቹ ተወጣጠሩ፤ ጸሎቱ ምን ያህል ጊዜ እንደ ወሰደ ለዘርዐ ያዕቆብ ሳይታወቀው በርጤሜዎስ “አሜን” ሲል ብቻ ቀጣዩን ለማወቅ ተዘጋጀ፡፡ “እንካ ይህን ዕንጨት! ዕንጨቱን አኝከው፤ ውሃውንም ምጠጠው፤ ቅጠሉን ግን በእጅህ እያሸህ ጭመቀውና በጭማቂው ውሃ ከራስ ፀጕርህ ጀምሮ እስከ እግር ጥፍርህ ድረስ ያለውን ገላህን ቀባው” አለ በርጤሜዎስ፡፡ እንደ ተባለውም ዘርዐ ያዕቆብ ፈጸመ፡፡ ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ የዘርዐ ያዕቆብ አእምሮውና ልቡ ተለወጡ፡፡ ቀድሞ ያልሰማውንና ያላጠናውን መልክአ ሳጥናኤልንና ሌሎች ብዙ መልካ መልኮችን እንዳጠናቸው ያህል በቃሉ ደገማቸው፡፡ የሳጥናኤልና የዘርዐ ያዕቆብ መወራረስ እንደዚህ ተፈትኖ ዐለፈ፡፡

“እንግዲህ” አለ በርጤሜዎስ “እንግዲህ የጕዳዩ ምስጢርነት ተጠብቆ ይቀመጥ!! አንተ ምን ጊዜም መልክአ ሳጥናኤልን ሳትደግም ከቤት አትውጣ፤ ተወራርሰሃል፡፡ ከዚህ በኋላ እንኳ የተማርከውን ያልተማርከውን ሁሉ ከፈለግህ ታውቀዋለህ፡፡ ሁሉንም ነገር በውስጥህ ተሰውሮ የሚሠራው ከአንተ ጋር የተወራረሰው ሳጥናኤል ነው፡፡ እርሱ ጌታህ ነው፤ ታዘዘው፡፡ እርሱም ይታዘዝሃል፡፡ የባላጋራህን ቤት እንዲያቃጥልልህ ብትጠይቀው ይሠራልሃል፡፡ ግደልልኝ ያልኸውን ይገድልልሃል፡፡ አንተም ታዲያ እርሱ የሚልህን ሁሉ መፈጸም አለብህ” አለና ጸጥ አለ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብም ንግግሩን ሁሉ ቢያዳምጠውም በርጤሜዎስ ሲጨርስ እንኳ ልቡ አልተመለሰለትም፡፡ ግን የት እንደሄደበት አላወቀም፡፡

ከሰመመኑ ሲነቃም፥ “እስካሁን ስደግመው የነበረውን መልካ መልኩን ሁሉ መተው አለብኝ እንዴ?” ጠየቀ ዘርዐ ያዕቆብ፡፡ “መተው?” አለ በርጤሜዎስ “የምን መተው! እኔ መች ተውሁ! በሁሉም መልክ የምትጠራው ያው ሳጥናኤልን እኮ ነው፡፡ ሞኝ! ኋላ አንተ ጠራኻቸውና ጊዮርጊስም ሚካኤልም ሊመጡልህ ነው? በል ሞኝ አትሁን” አለና አጽናናው፡፡

የነገሩ ደርዝና ፈርጅ በግልጽ አልታይህ ብሎት እንደ ተደባላለቀበት ዘርዐ ያዕቆብ በርጤሜዎስን እየመራ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ ጋደም እንደለ ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ለረጅም ሰዓት ተወሰደ፡፡ ሲነቃ ጊዜው መሽቷል፡፡ እራት ቢጤ በላልተው እንደ ጨረሱ “እስኪ እንግዲህ ትምህርትህን ቀጽል” አለው፡፡ ከዚያም በርጤሜዎስ አዜመ፤ ዘርዐ ያዕቆብ ያለ ምንም ችግር በርጤሜዎስ ያዜመውን ሁሉ መልሶ አዜመው፤ ርክርኩንና ለበርጤሜዎስ ዜማ ልዩ መታወቂያ የሆነውን የድምፁ አሻራ (ቅላጼ) እንኳ አላስቀረም፡፡ አስተማሪው ቀጠለ፤ ተማሪው ተከተለ፤ አስተማሪው ሄደ፤ ተማሪው እንደ አስተማሪው ሄደ፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረው ልዩነት አንደኛው ቀድሞ ማዜሙ፥ ሁለተኛው ተከትሎ ማዜሙ ብቻ ነበር፡፡

ውድቅት ሌሊት ሆነ፡፡ “እስኪ የተማርኸውን ከልሰው” አለና በርጤሜዎስ ጋደም አለ፤ በተራው አንቀላፋ፡፡ ዘርዐ ዕቆብ የተመራውን ሁሉ ያለ ምንም እንከን ከለሰው፤ አልተደነጋገረውም፤ አልተሳሳተም፡፡ ወፎች ሲንጫጩ ዘርዐ ያዕቆብ ደገፍ እንዳለ በተራው አንቀላፋ፡፡ ቀትር ሲሆን ከእንቅልፉ ነቃና ያዘጋጀውን ምሳ ከአስተማሪው ጋር ተመገበ፡፡ “አሁን ትምህርትህን ቀጽል” አዘዘ በርጤሜዎስ፤ ተማሪው ተዘገጃጀ፡፡ በርጤሜዎስ አዜመ፤ ዘርዐ ያዕቆብ እንደ ተማሪ ሆኖ አዜመ፤ አልተሳሳተም፡፡ አስተማሪው ቀጠለ፤ ተማሪው ደገመ፡፡ አስተማሪው ቀጥሎ አዜመ፤ ተማሪውም ያንኑ አዜመው፡፡ ሲመሽ አቋረጡና ዕረፍት አደረጉ፡፡ እራት ከበሉ በኋላ  አንተ የተማርከውን መከለሱን ቀጥል” አለና በርጤሜዎስ ጸሎቱን ከደጋገመ በኋላ ተኛ፡፡ እንቅልፍ ግን አልወሰደውም፡፡ ተማሪውን ያዳምጥ ነበር፤ ዘርዐ ያዕቆብ የተማረውን ሳይሳሳት ወጣው፡፡ “ይህ ነው በርጤሜዎስ ወልደ ጤሜዎስ!” እያለ በልቡ ፎከረ፤ መሰል የቀለም ልጁን በመንፈሱ እያየው፡፡

አስተማሪውና ተማሪው ጥቂት ወራት በዚህ ሁኔታ እንዳሳለፉ ዘርዐ ያዕቆብ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የታወቀ ሁለተኛ በርጤሜዎስ ሆነ፡፡ አንድ ቀን መምህር እንግዳሸት ጸሎት ሲያደርሱ እንደ ዋሽንት ያለ ድምፅ እየተንቈረቈረ ወደ ጆሮዋቸው ደረሰ፡፡ ድግምታቸውን ቆም አደረጉና ማን፥ ምን እያለ እንደ ሆነ ለማድመጥ ሞከሩ፡፡ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ አንዱ ተማሪ ዝማሬ እየቀጸለ መሆኑን ከድምፁ ጥራት በስተቀር የጕረሮው ዐመል የርሳቸው እንደ ሆነ አረጋገጡ፡፡ በርጤሜዎስ መሰላቸው፡፡ አንዱን ተማሪ ሲያልፍ ጠሩና “ማነው ዝማሬ የሚቀጽለው?” አሉና ጠየቁ፡፡ “አይዋ ዘርዐ ያዕቆብ” ሲል መለሰ ተማሪው፡፡ “የቱ ነው ዘርዐ ያዕቆብ? አይዋ በርጤሜዎስን የሚመራ መልከ መልካሙ ተማሪ” አላቸው፡፡ መቼ ወደ ትምህርት ቤታቸው እንደ ገባ እንኳ ማስታወስ አቃታቸው፡፡ የሚያስታውሱት ቢሆን መልኩን ለማየት ጓጉ፡፡ “ቅጸላውን ሲጨርስ ከኔ ዘንድ እንዲመጣ ንገረው” አሉትና ብዙ ለማውራት ምኞት ያደረበትን ተማሪ በማሰናበት የድግምት ጸሎታቸውን ቀጠሉ፡፡

መምህር እንግዳሸት ድግምቱን ጨርሰው ጐበብ አድርገው በዘረጓቸው የሁሉት እጆቻቸው መዳፎች ላይ “ትፍ ትፍ” በማለት መዳፎቻቸውን እርስ በርሳቸው ካፋተጉና ምራቃቸውን ካዳረሱ በኋላ ፊታቸውን አባበሱት፡፡ በበርጩማቸው ላይ ዐረፍ እንዳሉ ለግላጋ ወጣት በጫማቸው ላይ ተደፋ፡፡ መምህር እንግዳሸት እግራቸውን ቀረብ እያደረጉለት የአፍ ዐመል ሆኖባቸው “ተው፥ ተው እንጂ፥ ተው” አሉ፡፡ ወጣቱ ግን በሁለት እጆቹ መሬቱን ተደግፎና ዐንገቱንም አስግጎ ሁለቱንም ጫማዎቻቸውን ከሳመ በኋላ አቀርቅሮ ቆመ፡፡ “ማነህ አንተ?”
“ዘርዐ ያዕቆብ ነኝ”
“መቼ ነው እኛ ዘንድ የመጣኸው?”
“አንድ ዓመት ዐልፎኛል”
“በፊት ከማን ዘንድ ትማር ነበር?”
“እኔ እዚሁ ነው ሰላም ለኪ ያልኩት”
“ወይ ግሩም!” አሉ በልባቸው፡፡ በርጤሜዎስ አብነት አቅምሶታል ተብሎ በብዙ ተማሪዎቻቸው የተነገራቸው ሐሜት ስለዚህ ተማሪ መሆኑን ተረዱና ዝም አሉ፡፡ “በል መልካም ለዚህ ነው የጠራሁህ” በማለት አሰናበቱት፡፡

ዘርዐ ያዕቆብ በሚቀጥሉት ቅርብ ወራት ውስጥ ቅኔንና ትርጓሜ መጻሕፍትን በየተራ ለመማር እዚያው ደብር ወዳሉ ሌሎች መምህራን ለመዛወር ወሰነ፡፡ በዚያው ሰሞን የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል ሊከበር ተቃርቦ ነበር፡፡ በመስቀል ላይ ሰዎችን ለማዳን በሰዎች ቦታ ተተክቶ የተቀበለው መከራ በታላቅ ሥነ ሥርዐት ይታሰብ ስለ ነበረ በቤተ ሳይዳ መድኀኔ ዓለም አንቱ የተባሉ መምህራን ሁሉ በሥርዐተ ማኅሌቱ ላይ ተገኝተው ነበር ዘግይተው ወደ ቅኔ ማኅሌት (የማኅሌት አገልግሎት የሚሰጥበት ክፍል) የገቡት አለቃ ደምፀ ቃለ አብና የኔታ ማኅተመ ሥላሴ ነበሩ፡፡ ሁለቱም በመምህር እንግዳሸት በስተቀኝ ቦታ ተሰጣቸው፡፡ ወዲያው ዲያቆኑ ለበዓሉ የተመረጠውን ምስባክ ከሰበከና ቄሱ ወንጌል ካነበበ በኋላ ዲያቆኑ ከቅድስት ወደ ቅኔ ማሕሌት ገባ፤ መስቀሉን ለመሪ ጌታው አስረከበ፡፡ መሪ ጌታውም እጅ ነስተው ከተቀበሉ በኋላ መስቀሉን ለአለቃ ደምፀ አስተላለፉ፡፡

አለቃ ደምፀም እጅ ነሥተው መስቀሉን ከተቀበሉ በኋላ እስመ ለዓለሙን መቃኘት ጀመሩ፡፡ “ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ፤ ወበስምከ ነኀሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ፤ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ፡፡ ካዕበ ይቤ ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፍርሁክ ከመ ያምስጡ እም ገጸ ቅስት፡፡ ወይድኅኑ ፍቁራኒከ፡፡ ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም፤ ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት በዓለ እግዚእነ፡፡  - ባንተ ጠላቶቻችንን ሁሉ እንወጋቸዋለን፡፡ የተሰለፉብንንም በስምህ እናጐሳቍላቸዋለን ሲል ዳዊት የአብ ቃል በሥጋ ስለ ተሰቀለበት መስቀል በትንቢት መንፈስ ተናገረ፡፡ እንደ ገናም የሚፈሩህ ከጦርነት ያመልጡ ዘንድ፥ አንተም የምትወዳቸውና የሚወዱህ ይድኑ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው ሲል ይኸው ዳዊት ተናገረ፡፡ (መዝ. 59/60፥4)፡፡

“እንግዲህ እኛም ዛሬ በዚች በጌታ በዓል ደስ እያለን፤ በዓላችንን እናድርግ” አሉና ቀጥለው አንገርጋሪውን መሩ፡፡ ዝማሜውንና ጽፍዐቱን አጠናቀው ወደ ንኡስ መረግድ ከዚያም ወደ ዐቢይ መረግድ እየተሸጋገሩ አለቃ ደምፀና የኔታ ማኅተመ ሥላሴ በተመስጦ ያገለግሉ ነበር፡፡ ለጓደኞቻቸውም በአየር ላይ የሚንሳፈፉ መሰሉ፡፡ የልባቸውን ሐሤት በሚገልጽ ፈገግታ ፊታቸው የተሞላ ሆኖ ሳለ፥ ከዐይኖቻቸው አንዳንድ እንክብል ውሃ ዱብ ዱብ ይል ነበር፡፡ “ብከ ንወግኦሙ ለኵሎሙ ፀርነ” ይላሉ “ወንሕነኒ ንፈሣሕ ዮም ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት በዓለ እግዚእነ” ይሉና መልሰው ይላሉ፡፡ “ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም… “ እንደ ገና “ ብከ ንወግዖሙ … ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም…”

“እንዴ! ከሥርዐቱና ከይትበሀሉ ውጪ፥ መልሰው እያሉ ስንት ጊዜ ሊመረግዱት ነው?” አለ አንዱ ደብተራ ለጓደኛው ቀስ ብሎ፡፡ “እግዚአብሔርን ለማመስገን የቍጥር ወሰን አያስፈልገውም፡፡ ማሕሌተ ገንቦውን ስንደልቀውና ስናሸበሽብበት እንውላለን፡፡ ማሕሌተ ገንቦአችን ያለ ቍጥር ማሕሌተ እግዚአብሔርን ግን በቍጥር ይሁን ብሎ የደነገገ ማን ነው?” ጠየቀ ጓደኛው፡፡ ሌላው ደብተራ ጣልቃ በመግባት “12 ጊዜ እግዚኦ መሐረነ እንበል ይባል የለም እንዴ?” አለ፡፡ አራተኛው ደብተራ ተቈጣና “ከአእምሮ ከለብዎ (ከማስተዋል) ውጪ ነው ንግግራችሁ፡፡ እግዚኦ መሐረነን (አቤቱ ማረንን) 11 ጊዜ ወይም 13 ጊዜ መጸለይ ኵነኔ የለበትም” አለና ሥቆ አሣቃቸው፡፡

በርጤሜዎስ ግን አጀማመሩ ስላላስደሰተው ቀደም ብሎ ዘርዐ ያዕቆብን ይዞ ከቅኔ ማሕሌት ወጥተው ወደ ትምህርት ቤት፥ ከዚያም ዕፀ ከርከዴናቸው ወዳለበት ዐረህ ሔዱ፣ መሸጉ፡፡ ዘግይቶም ሌሎች ሁሉት ደብተሮች እያጓሩ ከቅኔ ማሕሌት ወጡ፡፡ አብዛኞቹም አንድ ባንድ እየተሰረቁ ነጐዱ፤ እንኳ ቅኔ ማሕሌቱ አካባቢው ታወከ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ዜና ልደት የምሥራቅ ጠቢባን ባበሠሩ ጊዜ ኢየሩሳሌም የታወከችውን ያህል ቅኔ ማሕሌቱ ተተረማመሰ፡፡ አግዐዝያኑ (ነጻዎቹ) መዘምራን እነ አለቃን ተከትለው አሁንም “ብከ ንወግኦሙ” ይላሉ በመረግድ፡፡ ከዚያ በማለዘብ፡፡ የዚያን ዕለት ማሕሌተ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ የተለየ ሆነበት፡፡ እነዚያ ከመናፍስት ማለት ከእኛ ጋር የተቈራኙ ቀሳውስት፥ ዲያቆናትና መዘምራን ሁሉ አለቃ ደምፀ ቃለ አብና የኔታ ማኅተመ ሥላሴ በሚገኙበት አገልግሎት ምን ጊዜም ላለመሳተፍ ወሰኑ፡፡” አለና የወደቀው መንፈስ ቀጠለ፡፡

“አንድ ቀን ጧት ዘርዐ ያዕቆብ ውዳሴውን መልካ መልኩን ደጋገመ፡፡ ወዲያው አንድ ድምፅ ተሰማው፡፡ በስሙም ጠራው፡፡ “ዘርዐ ያዕቆብ! አንተ ልጄ ነህ የቃል ኪዳን ልጄ! ብዙ ውለታ ዋልኩልህ፤ አንተን ግን እስካሁን ድረስ አላዘዝሁህም፡፡ የበርጤሜዎስ ወዳጅነት በቅቶኛል፤ እርሱን ላስወግደው ወስኛለሁ፡፡ በእርሱ ቦታ ተተክተህ ሰዎችን እየመለመልህ ከኔ ጋር የምታወራርሳቸው አንተ ነህ” አለው ድምፁ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ ግን ደነገጠ፡፡ ሰውነቱ ተብረከረከ፤ ነፍሱ የከዳችው መሰለው፡፡ የማን ድምፅ እንደ ሆነም ዐውቆታል፡፡ በበርጤሜዎስ አማካይት ተለማምዶታልና፡፡ እያደርም ንግግሩ ጠበቅ፥ ቃሉ ከረር እያለና ወደ ጆሮው እየተወረወረ ገባ፡፡

“በበርጤሜዎስ ቦታ ተተክትህ የምትሠራልኝ አንተ ነህ፡፡ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ አደርግልሃለሁ፡፡” ሲለው “ሁሉን እንዴት ሁሉን” አለ ዘርዐ ያዕቆብ በልቡ፤ ቃል ግን ከአፉ አልወጣም፡፡ “አዎን ሁሉን” አለ ሳጥናኤል፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ ይበልጥ ተደናገጠ፤ የልቡን ሐሳብ ሁሉ የሚቈጣጠረው መሰለው፡፡ “የምትጠይቀኝን ሁሉ አደርግልሃልሁ የተባለውን ሳያስበው በልቡ ደጋገመው፡፡

በልጅነቱ የሞተችበትን እኅቱን መርሳት አቅቶት ነበር፡፡ ሁል ጊዜ ያሰላስላት፥ እንደ ዳዊት ይደግማት ነበር፥ ዕቃ ዕቃ እያሉ ሲጫወቱ፥ በቍርስ፥ በምሳና በእራት ላይ እንደ ጋባዥና እንደ እንግዳ ራሳቸውን በማስመሰል ሲጐራረሱ፥ “ኧረ በሞቴ! አልመለስም ይቺን ብቻ! ዐፈር ስሆንልህ! ስሆንልሽ” ይባባሉ የነበረው ትዝ ይለው ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሳይታወቀው በጕንጮቹ ላይ መንታ መንታ ቦይ  እየሠሩ የሚንከባለሉት እንባዎቹ መጽሐፉን ያበላሹበት ነበር፡፡ ያሁኑ አነጋጋሪና ተስፋ ሰጪ ድምፅ ወደ ጆሮው ከመምጣቱ በፊት በድግምት ጸሎቱ መካከል የርሷ ትዝታ ጣልቃ በመግባት ያስቸግረውና ልቡን በሐዘን ይሞላው ነበር፡፡ “የጠየቅኸኝን ሁሉ አደርግልሃልሁ ካልከኝ የሞተችውንና ትዝታዋና ናፍቆቷ የሚረብሸኝን እኅቴን ብታመጣልኝ” ጠየቀው ሲፈራ ሲተባ፡፡

“አዬ ዘርዐ ያዕቆብ አንተኮ ለኔ ገና የምታደርግልኝ ብዙ ሥራ ስላለ እኔም ሁሉን አደርግልሃለሁ፡፡ ከነገ ጀምሮ እኅትህ ጧት ጧት እየመጣች እንድታጫውትህ ከዚያ ዕፀ ከርከዴን ስር ሂድ፡፡” አለና ሳጥናኤል ተሰናበተው፡፡
“ጥያቄ አለኝ፤ በርጤሜዎስን ለምን ታስወግደዋለህ? ከልቡ አገልግሎህ የለም እንዴ?” ዘርዐ ያዕቆብ ጠየቀ፡፡
“ልክ ነህ አገልግሎኛል ያረጀ፥ አገልግሎቱን የጨረሰ ዕቃ ወደ ቈሻሻ መጣያ ይጣላል፤ ቈሻሻውም ይቃጠላል ይኸ ነው መልሱ”
“ኧረ ገና ብዙ አገልግሎት ላይ የሚውል ነውኮ!”
“አይምሰልህ አንድ ቀን ንስሓ ቢገባኮ አመለጠኝ ማለት ነው” አለና ሳጥናኤል ደመደመ፡፡

ዘርዐ ያዕቆብ ሐዘንና ደስታ ተደበላለቁበት፡፡ ልቡ መታ፡፡ ፍርሀትና ሽብር አንቀጠቀጡት፡፡ የእኅቱ ወደ ሕይወት መመለስና የባለ ውለታው የበርጤሜዎስ ወደ ሞት መነዳት ከፊት ለፊት ተደቀኑ፡፡ አንዱን መርጦ ይህ ይሁን የማይባል ድብልቅ ድብልቅልቅ ሆነበት፡፡ ይህን ሲያወጣና ሲያወርድ ትልቁ ዕፀ ከርከዴን ዘንድ ደረሰ፡፡ አሁን የሆነውን ሁሉ የሆነበት፤ በርጤሜዎስ ለርሱ እንትን ያደረገበት፤ ትውስታው የማይረሳ ስፍራ፡፡
“ዘሩ!” የሚል የሴት ድምፅ ሰማ፤ ወደ ኋላ ፈጥኖ ዞረ፡፡ ወለተ እስራኤል የክርስትና እናቷ ወደ ከተማ ወጥተው የገዙላት ዝንጕርጕር ጕርድ ቀሚስና ቀይ ሹራብ ለብሳለች፡፡ ገደል ገብታ በሞተችበት ዕለት የክርስትና እናቷ ገላዋን ዐጠቧት፤ ፀጕሯን ጐነጐኑላት፤ ቀባቧት፡፡ ዐዲሱን ልብስ አለበሷት፤ ፎቶ አስነሧትና “በይ እንግዲህ ወደ ቤትሽ ተመለሽ፡፡” አሏት፡፡ ዘርዐ ያዕቆብና ጓደኞቹ የርሷም ጓደኞች ተጨምረው አጅበዋት ነበር፡፡ እነርሱም የርሷን ያህል በደስታ ፈንጥዘው ነበር፡፡ እያወሩ በመሯሯጥም እየተጫወቱ ወደ መንደራቸው በመመለስ ላይ እንዳሉ “በዚህ በስርጡ በኩል እንሂድ” ተባባሉ፡፡ “አዎን ኰሽምም እየለቀምን እንበላለን በስርጡ እንውጣ” ሁሉም ተስማማ፡፡

ከትልቁ ስርጥ ቀጥሎ ያለውን አነስተኛ ስርጥ እኩሌቶቹ ጨርሰው፤ ሌሎቹም ከወለተ እስራኤል በስተኋላ አቀርቅረው ገደሉን ለመውጣት ሲቧጥጡ የወለተ እስራኤል እግር ተንሸራተተ፡፡ እሪታና ተከታትሎም የኳኳታና የድምድምታ ድምፅ አጃቢዎችዋን ቀሰቀሳቸው፡፡ ከፊት ለፊቷ ያሉት ወደ ኋላቸው ዞሩ፡፡ ከኋላዋ ያሉትም ቀና ብለው ተመለከቱ፡፡ ወለተ እስራኤል የለችም፡፡ ከገደሉ በታች እቋጥኝ ላይ ዐርፋለች፡፡ ጮኹ ተጯጯኹ ከስምሪት ቦታም ከመንደርም ወንዶችም ሴቶችም ሽማግሌዎችም አሮጊቶችም ወጣቶችም እየሮጡ ደረሱ፡፡ ይህ ከሆነ ግን ዓመታት ዐልፈዋል፤ በዕለቱ የነበሩት ሁሉ ታሪኩን ረስተዉታል፤ ዘርዐ ያዕቆብ ግን የእኅቱ ፍቅርና የአደጋው ትርኢት አሁንም በአእምሮው ዐዲስ ነው ግለቱ አልበረደም፡፡

በዕፀ ከርከዴን ሥር ያለችው ወለተ እስራኤል ቁመቷ አልጨመረ፥ አልቀነሰ፤ ልብሷ አላለቀ፥ አላደፈ፡፡ የተጐነጐነው ፀጉሯም ቢሆን ከገደል በወደቀችበት ዕለት በነበረበት ሁኔታ ነበረ፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ አእምሮውን ጥቂት ሊጠራጠረው ሞከረና “የለም! ያችዋ የኔዋ ወለተ እስራኤል ናት! ግን እንዴት” አለ ራሱ ለራሱ ግራ ቢገባው፡፡ እንባውም በጕንጮቹ ላይ መንታ፥ መንታ ሆነው” እኔ እቀድም፥ እኔ እቀድም አሉ ቍልቍለቱን፡፡

“ዘሩ ለምን ታለቅሳለህ እኔ እኮ ሁል ጊዜ እየመጣሁ አጫውትሃለሁ፤ ነገር ግን እኔና አንተ እንደምንገናኝ ለክርስትና እናቴ እንኳ አትናገር ምስጢር ነው፡፡” ብላ አስጠነቀቀችው፡፡ በልጅነታቸው ከሞቱት ወላጆቻቸው ጋር እንደምትኖርም ነገረችው፡፡ እሷንና እሱን ያሳደጓቸውን አክስቷን የአክስቷን ባልና የልጆቻቸውን ጤንነትና አኗኗራቸውን ጠየቀችው፤ ነገራት፡፡ “በል እንግዲህ ስትፈልገኝ ወደዚህ ብትመጣ እኔም እመጣለሁ፡፡ ከፈለግህ እማማንና አባዬን ይዤልህ እመጣለሁ፡፡” በማለት ተሰናበተችው፡፡

በደነዘዘ ደስታ አእምሮው ቢሞላም ግልጽ ያልሆነለት ብዙ ነገር ነበረ፡፡ በሌላ በኩልም ለዚህ ሁሉ ያበቃው በርጤሜዎስ የሚገደልበት ምክንያት፥ “አንድ ቀን ንስሓ ቢገባኮ አመለጠኝ ማለት ነው” የሚል ስለ ሆነ ይህ የሳጥናኤል ንግግር አሁን የሰማው ያህል ሆኖ አንቀጠቀጠው፤ ልቡን ወግቶ ያልተነቀለ ጦር ሆነበት፡፡ ወደ ቤት ሲመለስም በርጤሜዎስ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመጨዋወት ላይ ሳለ በትንታ መሞቱ ተነገረው፡፡ ሰዎች ያለቅሳሉ፡፡ ይጯጯኻሉ፡፡ “ወይኔ ጓዴ፥ ምስጢረኛዬ፥ እንጀራዬ፥ ትምህርቴ …” ዘርዐ ያዕቆብም ከሚያለቅሱት ጋር ተቀላቀለ፡፡ በርጤሜዎስ ተገነዘ፤ ተከፈነ፤ በሰሌን ተጠቀለለ፤ የቤተ ክርስቲያን ደወል ተደወለ፡፡ የ3 አድባራት ካህናት ለፍትሐት ተሰበሰቡ መዋሥእቱ ተመራ፡፡ ከበሮው ጅው ጅው፥ ድም ድም፡፡ ጽናጽሉ ሿ-ሿ፥ የዕጣኑ ጢስ ቦለል ቦለል፤ የቄስ ዘመድ ሲያለቅስም ሲፈታም እንደ ተባለው ሆነ፡፡ የአቡየን በዓል በመሰለ ደማቅ ማሕሌት፥ ሕዝብንና አሕዛብን ባሳተፈ ክብር በርጤሜዎስ ተሸኘ፡፡

ዘርዐ ያዕቆብ ዕፀ ከርከዴኑ ሥር እየሄደ ከወለተ እስራኤል ጋር ቢጫወትም ደስታው ፍጹም አልሆነለትም፡፡ “በርጤሜዎስ አንድ ቀን ንስሓ ቢገባኮ አመለጠኝ ማለት ነው” የሚለው የሳጥናኤል ንግግር እንደ ውጋት ሆኖ በማናቸውም ሁኔታ ደስታው ፍጹም እንዳይሆን ”ህ-እ” እያሰኘ ድንገት ቍልቍል ይመልሰዋል፤ ይወጋዋል፡፡ ይህም ሆኖ በዚያ ጕደኛ ዕፀ ከርከዴን ሥር ከእኅቱም ከእናቱና ከአባቱም ጋር ብዙ ጊዜ ተገናኘ፡፡ የእነርሱን እንጃ እንጂ እርሱ ናፍቆቱን ተወጣ፡፡ በሌላ በኩልም ወደ ቅኔና መጻሕፍት ቤት በየተራ ተዛውሮ ልቡ የተመኘውን ሁሉ አጠናቀቀ፡፡ አንቱ የተባለ ሰው ወጣው፤ ትዳር ያዘ፤ የልጆችም አባት ሆነ፡፡ ቅርብ ለቅርብ ከሆኑ ከሦስቱ አድባራት በአንደኛው በደብረ ፋይድ ገብርኤል በመሪ ጌታነት ተሾመ፡፡ ይህን ደብር ካቋቋመውና በሀብቱ ከዳበረው ከደብተራ ምንተስኖት ደመቀ ጋር በወዳጅነትና በቃል ኪዳን ተሳሰረ፡፡ የሚታወቅባቸውን ብዙ ብዙ ሥራዎች ሠራ፡፡ በሕዝብ ዘንድ ተከበረ፤ ጌተየ፤ የቀንድና የጋማ ከብቶቹ በጎችና ፍየሎቹ አይቈጠሩም፡፡

ይህን ያህል የታወቀ፥ የተከበረና የተወደደ ቢሆንም፥ ሰዎችን ያበላል፤ ያጠጣል እንጂ ምንም ቢሆን ዘርዐ ያዕቆብ በሳንቲም የሚቈጠር ገንዘብ ለሰው አይሰጥም፡፡ ቢበደር እንኳ ምክንያት እየሰጠ ቀጠሮ ያስተላልፋል እንጂ አይከፍልም፡፡ የቅርብ ጓደኞቹ ዘርዐ ያዕቆብ ስምዖን የሚለውን ስም በመቀየር ያደረበትን ፍቅረ ንዋይ በሚገልጹበት ስም ንዋይ ሲሞን በማለት ስም አወጡለት፡፡ በጥቂት ሰዎች የሚታወቀው ይህ ስም ይፋ ወጣና ከዐሥር ሰዎች ወደ ኻያ ከዚያም ወደ መቶ ሰዎች ደረሰ፡፡ በመጨረሻ መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞንን እንጂ ዘርዐ ያዕቆብ ስምዖንን የሚያውቅ ሰው ጠፋ፡፡ የመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን የመጽሐፍ አስተማሪ የነበሩት ዕውቁ የብሉይና የሐዲስ መምህር አለቃ ዐወቀ ገብረ እግዚአብሔር ሲሆኑ፥ በደብረ ፋይድ ገብርኤል ከሚያስተምሩ ከመምህራን አንዱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሄደው አገልግለው አያውቁም፡፡ ከደለበው የቤተ ክርስቲያን ገቢ የተመደበላቸውን ደመወዝ “አልቀበልም እኔ ሰሌን እየሠራሁ፥ መጽሐፍ እየጻፍሁና እየደጐስሁ የማገኛት ገቢ ለዕለት ሲሳይ ትበቃኛለች” ብለው በእንቢተኛነታቸው ጸኑ፡፡

ከተማሪዎቻቸው መካከል አንዱ የማነ ብርሃን በድርጊታቸው ይገረም ነበርና ሁኔታው ሲመቻችለት ምክንያቱን ጠየቃቸው፡፡ “የተቈረጠልዎትን ቀለብ ለምን አልቀበልም አሉ? በየወሩስ ለሚካኤልና ለገብርኤል ደብተራ ምን ተስኖት ቤት እየሄዱ ለምን ድግሳቸውን አይበሉም?” በማለት ያቀረበላቸው ጥያቄ ከመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን ጆሮ ጥልቅ አለ፡፡ አለቃ ዐወቀም ሲመልሱ፥ “የዋህ፥ ገንዘቡ በምን መንገድ እንደሚሰበሰብ ታውቃለህ? ሌባው የሚሰረቅ ገንዘብ እንዲያጋጥመውና ሳይነቃበት ለመስረቅ እንዲያመቻችለት ለገብርኤል ይሳላል፤ ባለገንዘቡን እንዲያፈዝለት እንዲያደነግዝለት ማለት ነው፡፡ በዝሙት ተዳዳሪዋ ድንግልናውን ያፈረሰውን ወጣት፤ ሀብታም ሀብታሙን ሰው ባለትዳሩን ከሚስቱ አፋትቶ፥ ወይም አጣልቶ እንዲያመጣላትና ከእርሷ ጋር በዝሙት ፍቅር እንዲያስተሳስርላት፤ ይህንም በመሳሰለው መንገድ ወረት እንዲገባላት ትሳላለች፡፡ ነጋዴው በተመሳሳይ ንግድ የተሰማራውን ነጋዴ ወረት ወደ እርሱ እንዲያዞርለት፥ ሌላው በላጋራውን እንዲገድልለት ለሌላ ሌላውም ተመሳሳይ ጕዳይ እየተሳለ ይህን የመሰለ ሥራ ላደረገላቸው ባለውለታቸው የድካሙን ዋጋ ለመክፈል ሲሉ ቃል የገቡትን ብፅዐት ለደብረ ፋይድ ያስገባሉ፡፡ ይህን ታውቃለህ አታውቅም?” አሉት፡፡

“በሚገባ ዐውቃለሁ እንጂ የኔታ” በማለት የማነ ብርሃን ሲመልስ፥ አለቃ ዐወቀ ቀጠሉና “ታዲያ ይህን በመሰለ መንገድ የገባውን ገንዘብ መብላት በዐመፅ ሥራ ከዲያብሎስ ጋር መተባበር ማለት ስለሆነ ከቤተ ክርስቲያኑ ገቢ አልቀምስም ያልሁት በዚህ ምክንያት ነው” አሉት፡፡

መቼም የማነ ብርሃን ያልገባውን ነገር ሁሉ መጠየቅና መረዳት ስለሚያዘወትር በማስረጃ ተደግፎ ያልቀረበለትንና ያልተረዳውን ለመቀበል እሺ የማይል ሞገደኛ በመሆኑ አለቃ ዐወቀ ይወዱታል፡፡ አሁንም እንደ ልማዱ ደገመና ጠየቀ፡፡ “የኔታ ሰዎቹ የሚሳሉት ለገብርኤል ነው፤ አሁን እንዳስረዱኝ ከሆነ መልአክ ይህን የመሰለ ርኵሰት እንደማያደርግ ይታወቃል፡፡ ታዲያ በገብርኤል ስም ይህን ርኵሰት የሚያደርግ ክፉ መንፈስ ከሆነ ይህን መንፈስ እግዚአብሔር እንዴት ችላ አለው?” አለቃ ዐወቀ መለሱ፤ “መጽሐፍ ወበእንተዝ አግብኦሙ ወኀደጎሙ ከመ ያርኵሱ ርእሶሙ ለሊሆሙ ወያኅሥሩ ነፍስቶሙ እስመ ሐሰተ ረሰይዎ ለጽድቀ እግዚአብሔር ወአምለኩ ወተጸአጽኡ ተግባሮ ወኀደግዎ ለፈጣሬ ኵሉ ዘውእቱ አምላክ ቡሩክ ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡ - የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለውጠው ሁሉን የፈጠረውን በእውነት ለዘላለም የተባረከውን አምላክ በመተው፥ በእግዚአብሔር የተፈጠረውን አምልከዋልና እርሱ ደግሞ ራሳቸውን ለሚያረክሱበትና ለሚያጐሳቍሉበት ነውር አሳልፎ ሰጣቸው (ሮሜ 1፥24-25) ሲል እንደ ተናገረው፥ ተፈጽሞባቸዋልና በርኵሰቱ በሚገኘው ገቢ ሆዳቸውን መሙላታቸው ለእነርሱ ከሁሉ በላይ ክብር ነው (ፊል. 3፥18-19” አሉት፡፡ የማነ ብርሃን ግን ነገሩን እስኪያብላላ ድረስ ዐንገቱን ደፍቶና ግንባሩን ቋጥሮ ዝም አለ፡፡

ይህን የተማሪውንና የአስተማሪውን ጥያቄና መልስ እነርሱ ልብ ያላደረጉት መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን ጆሮውን አቁሞ አንድም ሳይቀር አድምጦታል፡፡ የሰማው ትምህርት ወደ ሌሎች ሰዎች  እንዳይተላለፍም ሁለቱንም ሊያስገድላቸው ወሰነ፡፡ ጕዳዩ ቀላል ነው፡፡ በማለዳ ዕፀ ከርከዴኑ ሥር ተቀመጠና መልከአ ሳጥናኤልን ደገመ፤ ባለመልኩ መጣ፤ “አለቃ ዐወቀንና የማነ ብርሃንን ግደልልኝ” አለው፡፡ “አልችልም፤ አንተ ከማሰብህ በፊት እኔው ራሴ ብዙ ጊዜ ሞክሬ አልተሳካልኝም፤ አንተ ከኔ ጋር እንደ ተወራረስክ፥ እነርሱ ደግሞ ከኔ ከሚበልጥ መንፈስ ጋር ተወራርሰዋል፡፡ ዐርፈህ ተቀመጥ” አለው በቍጣ፡፡

“በርጤሜዎስ አንድ ቀን ንስሓ ቢገባኮ አመለጠኝ ማለት ነው፡፡ … ንስሓ የገባ ሰው ከሳጥናኤል አመለጠ ማለት ነው? … ንስሓ የገባው ሰው ሳጥናኤልን ከሚያሸንፍ መንፈስ ጋር ተወራረሰ ማለት ነው? … ስለዚህ በርጤሜዎስን ንስሓ ሳይገባ ላስወግደው ወስኛለሁ፡፡ እኔ ግን ተሸናፊ ለሆነ መንፈስ የምገዛ ባሪያ ነኝ፡፡ በራሴ ነጻ መውጣት ግን አልችልም፡፡” ይህና ከዚህ ጋር የተያያዙት የቋጠሮ ውላቸው ስውር የሆኑ ሐሳቦች በልቡ ተመላለሱ፤ ፈነጩበት፡፡ አእምሮው በጭንቀት ተሞላ፤ ተረበሸ፤ አቅለሸለሸው፡፡ የራሱ አእምሮ የራሱንና የመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞንን ታሪክ እየደጋገመ ተረከለት፤ እንደማያውቀው ያህል ሆኖ በትካዜ እርሱም ደጋግሞ አዳመጠው፡፡

በጉባኤው መካከል መሬት ላይ በተዘረጋው በመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን ግዙፍ ሰውነት ውስጥ ያለ ክፉ መንፈስ ከዚህ በላይ የተነገረውን ሁሉ ባለታሪኩ ሦስተኛ ሰው እንደሆነ አስመስሎ ከተረከ በኋላ በመቀጠል ባለታሪኩ እርሱ ራሱ እንዲህ አለ፡፡ “በርጤሜዎስን እንደ ተጠራጠርሁት ሁሉ መሪ ጌታ ንዋይንም ተጠራጠርሁት፡፡ ቢያመልጠኝስ አልሁና አሳበድሁት፤ ልገድለው ነበር፤ ግን ዕቅዴ ከሸፈና እነሆ የማነ ብርሃንና አለቃ ዐወቀ ወደዚህ ይዘዉት መጡ፡፡ ለዚህ ውርደትም አጋለጡኝ፡፡ ወይኔ ሳተናው! ተዋረድሁ፥ ተቃጠልሁ፥ ኧረ ነደድሁ፡፡ እለቃለሁ፥ እወጣለሁ” በማለት ወተወተ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን አለቃ ደምፀ ቃለ አብና ጉባኤው በጸሎት መንፈስ ቈይተው ነበር፡፡ ኀያሉን አምላካችንንም ስለ ድንቅ ሥራው በመንፈስ ያመሰግኑት ነበር፡፡ እንዲህ እያሉ “አምላካችን ሆይ፥ የኀይልህ ታላቅነት ፍጹምና ድንቅ ነው፡፡ የኀይልህ ምንጩ አንተው ራስህ እንደ ሆንህ ታወቅ ዘንድ ተራራውን የሚንደውን፥ ዘንዶውንና አራዊቱን ሁሉ የሚረጋግጠውን፥ እሳቱን የሚያጠፋውን ታላቁን ኀይልህን በድንጋይ፥ በብረት፥ በዕንጨት፥ ውስጥ አላኖርህም፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ከሁሉም ዘንድ ጥቃት ሊደርስበት ይችል በነበረው ደካማ ሸክላ ውስጥ ዓለምን ማሸነፍ የሚችለውን መለኮታዊ ኀይልህን አስቀመጥህ፡፡ እኛ ምንድር ነን ጌታ! ለዚህ ዓለምን ለሚያድነው ወንጌልህ ሥርጭት እንታጭና እንመደብ ዘንድ የአጋንትንም መንጋ እናሳድድ ዘንድ እኛ ምንድር ነን? አቤቱ ስምህን እናከብራለን!!”

በመጨረሻውም ክፉው መንፈስ እንደ ውሻ ጮኾ እንዲወጣ አለቃ በሰማይና በምድር የሥልጣን ሁሉ ባለቤት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዘዙት፤ መንፈሱም እንደ ታዘዘው አደረገ፡፡ መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን ተንፈራገጡና ተዝለፈለፉ፡፡ ወዲያውም አንቀላፉ፤ ከፊታቸው ላብ ተንጠባጠበ፡፡ ጸሎቱም እንደ ተፈጸመ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ለዕለቱ የተዘጋጀውን ትምህርት ካስተማሩ በኋላ ከምእመናን ለቀረቡ ጥቄዎች መልስ ሰጡ፡፡ የጥያቄና መልሱ ፕሮግራም እየተካሄደ ሳለ መሪ ጌታ ንዋይ ነቁ፡፡ “እ-እ-እ” አሉና ዐይናቸውን ገለጡ፤ ተቀመጡም፡፡ ሁኔታው ግር ያሰኛቸው ቢመስልም ጭንቀት አልነበረባቸውም፡፡ የተሟላ የልብ ሰላም የአእምሮ ዕረፍትና የመንፈስ ደስታ እንደ ሞላባቸው ይታይ ነበር፡፡

እንደ ነቁ ለቀረቡ ጥያቄዎች የሚሰጡትን መልሶች አዳመጡ፡፡ በትምህርቱ መዝጊያ ላይ አለቃ ነቅዐ ጥበብ “ ‘ከዚህ ዕለትና ደቂቃ ጀምሮ ስለ ኀጢአቴ ለሞተልኝና ሊያጸድቀኝም ለተነሣው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ራሴን እሰጣለሁ፤ ሰይጣንንና የእርሱን መሣሪያ የሆነውን ሥርዐት ሁሉ እጥላለሁ፡፡’ በማለት የምትወስኑ ተነሡና በጉባኤው መካከል ፈቃደኛነታችሁንና ውሳኔአችሁን አስታውቁ” ሲሉ ቆመው ጋበዙ፡፡ ተማሪ የማነ ብርሃን፥ ዲያቆን በፈቃዱ፥ ዘርዐ ያዕቆብ (መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን የነበሩ) ሌሎችም ተነሥተው ቆሙ፡፡ “ከዛሬ ጀምሮ ለጌታ መንፈስ ተማርካችኋል፡፡ የጌታ ምርኮኞች ናችሁና እጆቻችሁን ወደ ላይ ዘርጉ” አሉ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የጌታ መንፈስ እንዲረከባቸው በጸሎት አሳልፈው ሰጧቸው፡፡ አገልጋዮቹን በእሳት ወላፈን ያስታጠቀውን ጌታን በማመስገን ጸሎቱን ጨረሱ፡፡

በአካባቢው የሚገኙትን ሁሉ ያስደነቁ ሁለት የለውጥ ክሥተቶች ታዩ፡፡ አንደኛው ዘርዐ ያዕቆብን መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን ያሰኛቸው የቀለም ትምህርት ሁሉ ተወስዶባቸው ነበር፡፡ በርጤሜዎስ እርሳቸውን ከክፉው መንፈስ ጋር ከማወራረሱ በፊት ካጠኑት የቀለም ትምህርት ሌላ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ዜማውን ቅኔውን ትርጓሜ መጻሕፍቱን ምን ወሰደባቸው? በማለት ሕዝቡ ሁሉ ተደነቀ፡፡ የደብረ ፋይድ ገብርኤል መሪ ጌትነት ለሌላ ተሰጠ፡፡ መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን መባላቸው ቀረና በቀድሞ ስማቸው አቶ ዘርዐ ያዕቆብ ስምዖን ተባሉ፡፡ ከደብተራ ምንተስኖት ጋርም ለሁል ጊዜ ተለያዩ፡፡

ሁለተኛው አስደናቂ ነገር ከትምህርታቸው በተጨማሪ አንቱ ያሰኛቸው ሀብታቸው ሁሉ እንደ ጉም በነነ፡፡ የከብት መንጋውም በወረርሽኝ በሽታ ድምጥማጡ ጠፋ፡፡ ከሁሉም በላይ የድንቅ ድንቅ ተብሎ የተወራውና በሰው ልብ ተቀርጾ መነጋገሪያ የሆነው አቶ ዘርዐ ያዕቆብ ከሚስታቸውና ከልጆቻቸው ጋር በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር፡፡ የሰይጣን መሣሪያ ከሆነው ሁሉ አንዱ እንኳ በእነርሱ ዘንድ እንዳይገኝ የእግዚአብሔር መንፈስ እያጸዳቸውና እያነጻቸው እንደ ሆነ በመረዳታቸው እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር እንጂ የእግዚአብሔር ከሆኑ በኋላ የሰይጣን የሆነው ሁሉ ከእነርሱ በመወሰዱ አላዘኑም፡፡ አለቃ ደምፀ ቃለ አብም ከነበራቸው የእርሻ መሬት ከፍለው ሰጧቸውና ዘርዐ ያዕቆብና ቤተ ሰባቸው ኑሮኣቸውን በእርሻ ላይ መሥርተው እግዚአብሔርን እያመለኩ በደስታ ይኖሩ ጀመር፡፡

አንድ ቀን ቄስ በሻህ ውረድና ዲያቆን በረደድ የአቶ ዘርዐ ያዕቆብን ጕዳይ አንሥተው ሲጫወቱ፥ “ሃይማኖታቸውን ለለወጡ ሰዎች ገንዘብ የሚያድል ድርጅት አለ፤ ያን ለመቀበል ሲሉ ነው የኛን ሃይማኖት የሚተዉት ይባል የለምን? ታዲያ አቶ ዘርዐ ያዕቆብን የሚያህል ሰው ሃይማኖታቸውን ሲለውጡ ለምን ገንዘብ አልሰጧቸውም?” አለና ዲያቆኑ ጠየቀ፡፡ “አዬ ሞኝ!! አንተ የተነገረህን ሁሉ እውነት መስሎህ ትቀበላለህ? እንዲሁ ስም ለማጥፋት እንናገረዋን እንጂ ገንዘብ የሚሰጥማ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያዎቹ እኛ በሆንን ነበር፡፡ በትምህርታቸው መስፋፋት የተነሣ እውነቱ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሲታወቅ በተፈጸመው የማታለል ሥራ እንዳንወገር እየፈራን ለመከላከል ስንል የምንጠቀምበት መሣሪያ ስም ማጥፋት ሆነና ተገኘ፡፡ ግን የእውነቱን መግለጽ ማን ማገድ ይችላል (ዮሐ. 1፥5)፡፡

በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment