Monday, October 14, 2013

መሠረተ እምነት


ክርስቶስ ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ

መንደርደሪያ
በሕክምናው ዓለም በሰው ውስጥ ያሉና የተለያዩ በሽታዎችን የሚያመጡ ተሐዋስያን ለምሳሌ፡- ባክቴሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከሚገድላቸው መድኀኒት ጋር የሚላመዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከመድኀኒቱ ጋር ከተላመዱ ደግሞ የመድኀኒቱን የፈዋሽነት ዐቅም ያዳክማሉ፡፡ ሊያጠፉትም ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የበሽተኛው ጤና ይቃወሳል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ጠቢባኑ$ ተሐዋስያኑ ከመድኀኒቱ ጋር የተላመዱበትን ምክንያት በመለየት መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡ ከመፍትሔዎቹ አንዱ ከቀድሞው የተሻለ ፈዋሽነት ያለውና ተሐዋስያኑን ሊያጠፋ የሚችል መድኀኒት መቀመም ወይም ማዘጋጀት ነው፡፡

ስለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያሻማ መንገድ ያስተምራል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውነት ለማስተሐቀር (ለማቃለል) የሚሞክሩ ከሓድያንና መናፍቃን ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ለወደ ፊቱም ይኖራሉ፡፡ በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት በተለያዩ ዕትሞች ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት በልዩ ልዩ መንገድ ትምህርት ሲቀርብ መቈየቱን አንባብያን ያስታውሳሉ ብለን እናምናለን፡፡ ይሁን እንጂ ከመድኀኒቱ ጋር እንደሚላመዱ ተሐዋስያን$ በርእሰ ጕዳዩ ላይ ዛሬም መልካቸውን የቀየሩና የሚያደናግሩ የሚመስሉ ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ትምህርቶች እንዳዲስ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች እየተስተባበለ ያለውን የክርስቶስን መካከለኛነት$ በአሁኑ ጊዜ እየቀረበ ካለበት ስልት አንጻር፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረውና የቤተ ክርስቲያን አበውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው በሚሰጡት ምስክርነት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ማቅረብ አስፈልጓል፡፡


ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት የሚታመነው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ዋና የክርስትና ትምህርት በዘመናችን እንደ አንድ ተራ ሃይማኖታዊ የመከራከሪያ አጀንዳ መታየቱ ያሳዝናል፡፡ ክርክሩ፥ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆኖ እያለ$ የመካከለኛነቱ ስፍራ ለሌሎች መሰጠቱ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው በሚሉ ወገኖችና$ የክርስቶስ መካከለኛነት ስላበቃና ያለፈ ድርጊት ስለ ሆነ አሁን ያሉት መካከለኞች ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ብቻ ናቸው፤ ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ መካከለኛ (አማላጅ) አይደለም በሚሉ ወገኖች መካከል የሚነሣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የክርስቶስ መካከለኛነት ከመዳናችን ጋር የተያያዘ ዋና ትምህርት መሆኑ ፈጽሞ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት ስንናገር ስለ መዳናችን መናገራችን ነው፡፡ ዛሬ የክርስቶስን መካከለኛነት የምንክድ ከሆነ ደግሞ÷ አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያትና በክርስቶስ ተፈጽሞልናል ያልነውን መዳናችንን መካድና ሌላ የመዳኛ መንገድ መቀየስ ይሆናል፡፡    

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?
ይህን ጥያቄ መመለስ የቻለ ሰው የክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተዋል አይቸገርም፡፡ ቃል ሥጋ የሆነው (ዮሐ. 1$14) ለሌላ ዐላማ አይደለም፤ እግዚአብሔርንና ሰው ለማስታረቅ ነው፡፡ ይህ ትምህርት በትምህርተ ሥጋዌ ሊብራራ የሚገባው ቢሆንም$ በተለይ የአገራችን ሊቃውንት ከዚህ ይልቅ በክርስቶስ ማንነት ላይ ለተነሡ ኑፋቄዎች ምላሽ በመስጠቱና ቃልና ሥጋ የተወሐዱበትን ምስጢር በማብራራቱ ላይ ስላተኰሩ÷ የክርስቶስ የማዳን ሥራው በትምህርቶቻቸው ውስጥ ደብዝዟል ማለት ይቻላል፡፡ የክርስቶስን ማንነት በትክክል ተገንዝቦ የማዳን ሥራውን በማመን የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ከሚመጣው ቊጣ ያድናል፤ ጕዳዩ ዕውቀት ብቻ ከሆነ ግን አይጠቅምም፤ እንዲያውም የባሰ ፍርድ ያስከትላል፡፡

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ወዳጄ ልቤ” በተሰኘው ድርሰታቸው በገጽ 42 ላይ$ ሊቃውንት በክርስቶስ ልደት ዙሪያ ሲከራከሩ ዋናውን ቁም ነገር ቸል ማለታቸውን በሚከተሉት ስንኞች ገልጸዋል፡፡
“አባቶች ሁሉ በልደቱ[1]
ምን አጣላቸው በከንቱ
የኔንስ ልቤን ያስጨነቀው
የኋላው ምጽአቱ ነው፡፡”

እንደ እውነቱ ከሆነ የክርስቶስን ትክክለኛ ማንነት (አንዱ ክርስቶስ አምላክም ሰውም መሆኑን) ማብራራት ተገቢ ነው፡፡ ማብራሪያው ግን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ግብረ አድኅኖ (የማዳን ሥራ) ለማድረስ ያለመ መሆን አለበት፡፡ በአገራችን ሊቃውንት ዘንድ ግን በአብዛኛው በሥጋዌ ትምህርት ውስጥ ቃልና ሥጋ ስለ ተወሐዱበት ሁኔታ ለማብራራት የተሰጠውን ትኵረት ያህል የማዳን ሥራው አልተተኰረበትም ቢባል ምንም ስሕተት የለበትም፡፡ ብዙው ሰው ከመዳን መንገድ ወጥቶ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የነጐደውም$ የክርስቶስን የማዳን ሥራ በሚገባ የሚነግረውና የሚያሳርፈው ስለ ጠፋ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡

ርግጥ የቀደሙት አበው ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ (ቃል ሥጋ ስለ ሆነበት ምሥጢር) ሲያስተምሩ ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ነጥለው አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፡- አትናቴዎስና እርሱን የመሰሉ ጥንታውያን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በምስጢረ ሥጋዌ ትምህርታቸው ለመዳን ትምህርት ሰፊ ትኵረት እንደ ሰጡ ጽሑፎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡[2]

የክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚባለው እግዚአብሔርና ሰው የታረቁበት የመካከለኛነቱ ሥራ ነው፡፡ አዳም ሕግ አፍርሶ በሠራውና ወደ ዓለም ባስገባው ወይም ለዘሩ ባወረሰው ኀጢአት ምክንያት$ ኀጢአተኛ ባሕርይን ወርሶ የተወለደው የሰው ዘር በሙሉ ኀጢአተኛ ነውና (ሮሜ 5$12) የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል (ሮሜ 5$10)፡፡ የሰው ዘር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቷል ማለት ነው፡፡ ታዲያ በኀጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላውን ሰውን ከፈጣሪው ጋር ማን ያስታርቀው?

ከሰው መካከል “ከደሙ ንጹሕ ነኝ!” የሚል አስታራቂ ሊገኝ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ ሌላውን የሚያስታርቅ ቢያንስ$ እርሱ ራሱ ንጹሕና ከታራቂው ወገን ጋር ያልተጣላ$ ሁለቱን የሚታረቁትን ወገኖችም የሚወክል ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቅዱሳን የተባሉ ሰዎች እነዚህን መስፈርቶች ሊያሟሉ አልቻሉም፡፡ ምንም እንኳ ቅዱሳን ተብለው ቢጠሩም$ ኀጢአትን ፈጽሞ አልሠሩም ማለት አይደለምና በኀጢአት ዕዳ ተጠያቂ ሆነዋል (2ዜና. 6$36፤ ኢዮ. 4$17፤ 14$4፤ 15$14-16፤ ምሳ. 20$9፤ ኢሳ. 64$6፤ ሮሜ 3$11-12:22-24)፡፡ በሌላም በኩል ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) ስለ ሆኑ እግዚአብሔርን ሊወክሉ የሚችሉበት ማንነት የላቸውምና እግዚአብሔርንና ሰውን ለማስታረቅ አልቻሉም፡፡ 

አቡሊዲስ እንዲህ ብሏል፡- “ብእሲ (ሰው) ዓለምን ለማዳን አይችልም፡፡ ... የሰው መሞትም ከኀጢአት አያነጻም፡፡ ... ዳዊት ‘ሕያው ሆኖ የሚኖር ሞትንም የማያይ ሰው ማነው? ከሲኦል እጅስ ነፍሱን የሚያድን ማነው?’ ሲል እንደ ተናገረ ሞትን ያጠፋ ዘንድ$ ሕይወትንም ያበራ ዘንድ የሚቻለው ከሰዎች ይገኛልን? ነፍሱን ለማዳን ካልቻለስ መላውን ዓለም እንዴት ሊያድን ይችላል? ኀጢአት በሰው ውስጥ ዐድሯልና፡፡ ሞትም ይከተለዋል፡፡ ... ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም የያዘው ገዛው እንጂ፡፡ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ እርሱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ገጽ 145 ቊጥር 5፡7፡8፡11፡12)

በተፈጥሮአቸው ከእግዚአብሔርም ከሰውም ጋር የማይዛመዱት ቅዱሳን መላእክትም ቢሆኑ በአስታራቂነት ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉበት ምክንያት የለም፡፡ እነርሱ ረቂቃን መናፍስት ናቸው እንጂ መለኮትነት ስለሌላቸውና ሥጋንም ስላለበሱ$ እግዚአብሔርንም ሰውንም የሚወክሉበት ማንነት የላቸውምና ለማስታረቅ አልበቁም፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅና ጵርቅሎስ የሰጡትን ምስክርነት ቀጥሎ እንመልከት፡፡

“እስመ ለሊሁ ነጸረነ ወናሁ ኮነ አፅራረ ለእግዚአብሔር ወአልብነ ምንተኒ ግሙራ ዘይክል ያቅርበነ ኀቤሁ ለዐቂበ ሀብቱ ... ወኢያንሥአ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢእምኀይላት እለ እሙንቱ ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ፡፡ - እርሱ ተመልክቶን እነሆ ለእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነን ተገኘን፡፡ ሀብቱን ለማግኘት ... ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ የሚችል ፈጽሞ አልነበረንም፤ ዙፋኑን ከበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) አልሾመልንም፡፡” (ሃይማኖተ አበው ገጽ 222፣ ቊጥር 15)

“ብእሲሰ ትሑት አድኅኖ እምኢክህለ እስመ ውእቱሂ ይፈዲ ምስሌነ ዕዳ ወመልአክሂ ኢክህለ ተሣይጦተነ እስመ አልቦቱ ቤዛ ሥጋ በዘይትቤዘወነ፡፡ - ወራዳው ሰው የገዛ ራሱ ከእኛ ጋር ዕዳን ስለሚከፍል ሊያድነን ባልቻለም፤ መልአክም ቢሆን ስለ እኛ ቤዛ የሚሆንበት ሥጋ ስለማይኖረው ሊዋጀው አልቻለም፡፡” (ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ ገጽ 150)፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ የነበረው ቃል ሥጋ ሆነ፤ ማለትም እግዚአብሔርንም ሰውንም በሚወክልበት ማንነት ተገለጠ፡፡ በእርሱ በኩልም እግዚአብሔርና ሰው መታረቅ ቻሉ፡፡

በመጽሐፈ ምዕላድ ደግሞ የሚከተለው ተጽፏል፡፡ “እምቅድመ ይሠጎ ተኀጥኣ ንጹሕ ዐራቂ እምክልኤ ጾታ እምይእዜሰ ይደልዎ ይስረይ ኀጢአተ ምስለ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ በመለኮቱ እስመ ተረክበ ንጹሓ ዐራቄ ወመተንብለ በትስብእቱ፡፡ - ሥጋ ከመልበሱ በፊት በሁለቱም ወገን ንጹሕ የሆነ አስታራቂ ታጥቶ ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በመለኮቱ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ ኀጢአትን ይሰርይ (ይቅር ይል) ዘንድ ተገብቶታል፤ በሰውነቱ ንጹሕ አስታራቂና የሚጸልይ ሆኖአልና” (ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ  ገጽ 112)፡፡ አምላክ ሰው የሆነው እግዚአብሔርንና ሰውን ለማስታረቅ እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ ስለዚህ “ኀጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው” (1ጢሞ. 1÷15)፡፡

ቃል ሥጋ የመሆኑ አስፈላጊነት
ሰው መዳንን እንደ መብት መጠየቅ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በጽድቅ መንገድ ከታየ ሰው አስቀድሞ እንዳይበላ በእግዚአብሔር ከተከለከለውና ቢበላ ደግሞ ሞትን ከሚያስከትልበት የዛፍ ፍሬ ወስዶ በልቷል፡፡ የበላውም እንዳይበላ እየተመከረና ቢበላ የሚከተለው ሞት እንደ ሆነ እየተነገረው ነበር፡፡ እርሱ ግን ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ መብላትንና መሞትን መርጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ሞት ለሰው ተገቢ ዋጋው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው መዳንን እንደ መብት የሚጠይቅበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ በኀጢአት ከወደቀበት እንዲነሣና መዳንን እንዲያገኝ የእግዚአብሔር ምሕረት ያስፈልገዋል፡፡ የሰው መዳን የሚገኘው በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ዮና. 2$10) ይላል፤ (እንዲሁም ኢሳ. 45$21፤ ሆሴ. 13$4፤ ማቴ. 1$21፤ ዮሐ. 4$42፤ ሐ.ሥ. 4$12፤ 1ጢሞ. 1$1፤ 4$10፤ ቲቶ 1$3፤ ይሁ. 25ን ይመልከቱ)፡፡

የሰው መዳን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ያለ ቢሆንም$ እግዚአብሔር መዳንን ለባሕርዩ በማይስማማ መንገድ ለኀጢአተኛው ሰው ይሰጣል ማለት ግን አይደለም፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ቅን ፍርድ የኀጢአቱን ፍዳ መቀበል ነበረበት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ኀጢአተኛው ሰው እንዲሞት አልፈቀደምና$ ምትክ ሆኖ የሚሞትለትንና የኀጢአቱን ፍዳ የሚቀበልለትን አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጠለት፡፡ በዚህ አሠራሩ እግዚአብሔር ጻድቅ$ መሓሪ አምላክም መሆኑን አሳየ፡፡

ቃል ሥጋ መሆኑ, አንዱ ክርስቶስ በሰውነቱ ቤዛ ሆኖ እንዲሰጥልን, በአምላክነቱ ደግሞ እንዲያድነን አድርጓል፡፡ እርሱ ኀጢአትን ከቶ ያልሠራ ፍጹም ሰው በመሆኑ በእኛ ምትክ ሞቶ የኀጢአታችንን ዕዳ ከፈለልን፡፡ በአምላክነቱ ደግሞ መዳንን ሰጠን፡፡ ቄርሎስ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል “ወውእቱ መዋዔ ኵሉ ኀጢአት በመለኮቱ$ ኮነነ ሊቀ ካህናት በትስብእቱ፡፡ - በመለኮቱ (በአምላክነቱ) ኀጢአትን ሁሉ የሚያጠፋው እርሱ ሰው በመሆኑ አስታራቂ ሆነን፡፡” (ሃይማኖተ አበው ገጽ 330 ቊጥር 68)

እነ አትናቴዎስ “ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው” ካለው ከአርዮስ ጋር በኢየሱስ አምላክነት ላይ ሲከራከሩ ያቀረቡት አንዱ ነጥብ$ “ኢየሱስ ክርስቶስ መድኀኒት ነው፤ አዳኝ ነው፤ ማዳኑን ካመንህ$ የባሕርይ አምላክነቱንም ማመን አለብህ፤ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ መስክሯልና” የሚል እንደ ነበር$ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ጽፈዋል፡፡[3] አክለውም በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከሰው ልጆች የመዳን ምስጢር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እርሱ አምላክ ካልሆነ ግን እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ በሱ መዳናችንን ካመን ግን ያዳነን እሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፤ ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልምና፡፡ ራሱ መዳን የሚያስፈልገው ስለ ሆነ፡፡[4] በማለት የአትናቴዎስን ሐሳብ ያብራራሉ፡፡

የክርስቶስ አዳኝነትና መካከለኛነት
አንዳንዶች የክርስቶስ አዳኝነት ሌላ$ የክርስቶስ መካከለኛነት ደግሞ ሌላ ይመስላቸዋል፡፡ በተጨማሪም አዳኝነቱና መካከለኛነቱ አንድ ጊዜ ተፈጽሞ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ እየሠራ የሚቀጥል አገልግሎቱ መሆኑን ለመቀበል ይቸገራሉና ያለፈ ድርጊት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህም ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው$ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም መካከለኛ ከተባለ ከአምላክነቱ ደረጃ ዝቅ ይላል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ክርስቶስ ዛሬም መካከለኛ ነው ከተባለ$ በልዩ ልዩ መንገድ በእርሱ ስፍራ መካከለኛ አድርገው ያቆሟቸው መካከለኞች ተግባረ ፈት ይሆናሉና ያንቀላፉ ቅዱሳንንና መላእክትን ምን እናደርጋቸዋለን የሚል ይመስላል፡፡ እነዚህን ክፍተቶች መሙላት ስለሚቸግራቸውም ክርስቶስ ዛሬም አዳኝ ነው፤ መካከለኛም ነው የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ይቃወማሉ፡፡

ስለ ክርስቶስ አዳኝነት ስንናገር አዳኝነቱ ስለ ተከናወነበት መካከለኛነቱ መናገራችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ” ይለዋል (ዕብ. 12$24)፡፡ ዐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ደም የተመሠረተና እርሱ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ አንድ ጊዜ በተከናወነው ቤዛነት የሚያምኑ ሁሉ መዳንን የሚቀበሉበት፣ በኀጢአት ቢወድቁ የሚነሡበት ኪዳን ነው፡፡ የዚህ ኪዳን ብቸኛው መካከለኛ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መካከለኛነቱና አዳኝነቱ የተያያዙ መሆናቸውንም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡፡ “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግም አንድ አለ፡፡ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ብሎ መካከለኛነቱን$ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፡፡” ብሎ ደግሞ አዳኝነቱን ተናገረ (1ጢሞ. 2$5-6)፡፡

ብዙዎች አንድ ጊዜ የተፈጸመውን የክርስቶስን የማዳንና የማስታረቅ ሥራ ያምናሉ፡፡ በተግባር ግን ያ አንድ ጊዜ የተፈጸመው ለዘላለም የሚያድንና የሚያስታርቅ መሆኑን ከፍ ብለው በተገለጹት ሁለት ዋና ምክንያቶች የተነሣ አይቀበሉም፡፡ እንዲያውም ያስተባብላሉ፡፡ ብዙዎቹ ማስተባበያዎች ግን ከመዘመናቸው በቀር በይዘታቸው ብዙም ዐዲስነት አይታይባቸውም፡፡ ዐዲስ መስለው የሚታዩትም ቢሆኑ$ በምድር ላይ ያለውን የሕይወት ተመክሮ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ለሰማያዊው ነገር መገለጫ አድርገው የሚያቀርቡ ናቸውና አመክንዮኣዊነት ይጐድላቸዋል፡፡ ከሚቀርቡት ማስተባበያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

*    ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም፤
ጊዜውን በትክክል መጥቀስ ባይቻልም$ ይህ አመለካከት የክርስቶስን የመካከለኛነት ስፍራ ለቅዱሳን መላእክትና ላንቀላፉ ቅዱሳን ሰዎች መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እየተስፋፋ የመጣ$ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት እንደ ሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ የአመለካከቱ አቀንቃኞች ለኢየሱስ አምላክነት በመቅናት$ ትስብእቱን (ሰው መሆኑን) በንግግር ያመኑት መስለው በተግባር ግን ይክዱታል፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ መካከለኛ፣ አስታራቂ፣ አማላጅ፣ ጠበቃ፣ ... ከተባለ እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል ይላሉ፡፡ ካጤ ቃል በላይ፣ ዕውቅ አታላይ ይሏል ይህን ጊዜ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተጻፈው$ ቃል ሥጋ ሆኖ$ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እኛን ለማዳን የመጣው ራሱን ዝቅ አድርጎ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ መሰከረው$ “እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፡፡” (ፊል. 2$6-8 ዐ.መ.ት.)፡፡ ጌታ እስከዚህ ድረስ ራሱን ዝቅ ያደረገው በፈቃዱ ስለ ሆነ$ ድርጊቱ ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር ያሳያል እንጂ ክብሩ መዋረዱን ፈጽሞ አያመለክትም፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነውና፡፡

እርሱ በዘላለም ሐሳቡና በፈቃዱ ዝቅ ቢል$ እኛ በጴጥሮስ መንገድ ሄደን$ አይሁንብህ ጌታ ሆይ ይህ ከቶ አይደርስብህም” (ማቴ. 16$22) ብንለው$ ለእኔ ቀንተው ነው በሚል አያመሰግነንም፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስቡም ብሎ ይነቅፈናል እንጂ፡፡ ስለዚህ እኛ እንዲሆንልን የምንፈልገነውን ዐይነት ኢየሱስ ለመፍጠር መሞከር ኑፋቄ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለቤዛ ዓለም አሳልፎ የሰጠውንና በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተጻፈው ማመን ግን ትክክለኛ እምነት ነው፡፡    

በርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጓል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊል. 2$9-11)፡፡ አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ሳይሆን እጅግ ከፍ ብሎ ነው ያለው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራ$ አምነው በእርሱ በኩል የሚመጡትን ሁሉ የሚያስታርቃቸውና የሚያድናቸው እርሱ ብቻ ነው (ዕብ. 7$25)፡፡ ምክንያቱም ስለ ኀጢአታችን ያቀረበው መሥዋዕት$ አንድ፣ ፍጹም፣ የማይደጋገምና ዘላለማዊ ነው (ዕብ. 10$12-18)፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት የኀጢአታቸውን ስርየት ለመቀበል አምነው በእርሱ በኩል ለሚመጡትና ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆኖላቸዋል (ዕብ. 5$9-10)፡፡ ይህም ማለት ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው$ እስከ መስቀል ሞት ደረስ እንደ ነበረው ዐይነት እየወደቀ$ እየተነሣ ይለምናል፤ ይማልዳል ማለት አይደለም፡፡ በእርሱ አዳኝነት በኩል አምነው ለሚመጡት በቀደመው ልመናውና መሥዋዕቱ ይታይላቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል ማለት ነው እንጂ (ዮሐ. 16$23-24፤ ዕብ. 5$7-10፤ 9$24፡28)፡፡

ለአንድ በሽታ ፈዋሽ መድኀኒት ስለ ተገኘና መድኀኒቱ በየፋርማሲው ስለሚሸጥ በሽታው ጠፍቷል፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎችም ድነዋል ማለት አይደለም፡፡ ለመዳን በሽተኞቹ መድኀኒቱን መውሰድና በተገቢው መንገድ መጠቀም አለባቸው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ስለ ተሰቀለና በሞቱ የኀጢአትን ዕዳ ስለ ከፈለ ወይም ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ መሥዋዕትን (ራሱን) ስላቀረበ ሰዎች ሁሉ ድነዋል ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመው የማዳን ሥራ ለእነርሱ እንደ ተከናወነ በማመን በኢየሱስ መካከለኛነት በኩል መቅረብ$ በእርሱ ሥራም ድኅነትን እንዳገኙ ማመን አለባቸው፡፡

በዚህ ሁኔታ ሲቀርቡ መካከለኛቸው ኢየሱስ በዕለተ አርብ የፈጸመው ግብረ አድኅኖ (የማዳን ሥራ) ለእነርሱ በማስቈጠር በማድረግ የዘላለም ሕይወት ባለቤት ያደርጋቸዋል (ሮሜ 4$23-25)፡፡ ምክንያቱም የማዳኑ ተስፋ ጌታ ከመምጣቱ በፊት ባለው ዘመን አምነዉት ለሞቱትና በተሰቀለበት ጊዜ ለነበሩት ብቻ አይደለም፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ$ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው ... (ሐ.ሥ. 2$39) ተብሎ እንደ ተጻፈ$ ጌታ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ላሉ የሰው ልጆች ሁሉ ነው፡፡ በሩቅ ካሉቱ መካከል የምንቈጠር እኛም$ የማዳን ሥራውን አምነን ድኅነተ ነፍሳችንን የተቀበልነው$ በዚህ የተስፋ ቃል መሠረት በክርስቶስ መካከለኛነት በኩል ቀርበን ነው፡፡

በክርስቶስ ሥራ ሲያምኑ የዘላለምን ሕይወት ያገኙ ክርስቲያኖች ወዲያው ፍጹም አይሆኑምና$ ኀጢአት መሥራታቸው አይቀርም (1ዮሐ. 1$8፡10)፡፡ ስለሚሠሩት ኀጢአት ግን ያው አንድ ጊዜ በቀረበው የክርስቶስ መሥዋዕትነት በኩል ስርየትን ያገኛሉ እንጂ ሌላ መሥዋዕት አይቀርብላቸውም (ዕብ. 7$27፤ 9$25-26፤ 10$18፡26)፡፡ አንድ ጊዜ ለዘላለም የቀረበው መሥዋዕት (የክርስቶስ ሞት) ፍጹምና ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ በመሆኑ$ ይህን ኀጢአታቸውንም ይሰርያል (ሮሜ 3$25፤ 1ዮሐ. 1$7-9፤ 2$2)፡፡

ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው የሚባለው ስለዚህ ነው፡፡ እርሱ እጅግ ከፍ ብሎ ባለበት ሁኔታ የሚያከናውነው ይህ የመካከለኛነት ተግባሩ ከከፍታው ዝቅ የሚያደርገው አይሆንም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን አዳኝ$ ዳግመኛ ሲመጣ ደግሞ ፈራጅ ማለት ነው፡፡

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን መካከለኛ አይደለም፤ ፈራጅ ነው የሚሉ ወገኖች$ የኢየሱስን ግብር (ሥራ) መግለጽ የሚፈልጉት ስለ እርሱ ከተጻፈው ሁሉ በመነሣት ሳይሆን$ የራሳቸውን አመለካከት ሊደግፍ ይችላል ያሉትን ግብሩን ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስ አለአግባብ በመጥቀስ ነው፡፡ ይህ ደግም ምንፍቅና (ከፍሎ ማመን) ነው የሚሆነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ሞቶ የኀጢአታችንን ዕዳ ከከፈለልን በኋላና እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ባለው ጊዜ ሁሉ ፈራጅ ነው ብሎ በአንድም ስፍራ አይናገርም፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አዳኝ፣ መካከለኛ፣ አማላጅ፣ ጠበቃ መሆኑን ነው የሚመሰክረው፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር በቀዳማዊ ምጽአቱ (ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ) አንድ ልጁን የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አላከውም ... (ዮሐ. 3$17) ተብሎ ተጽፏል፡፡

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ፈራጅ ነው የሚሉት ወገኖች ተሳስተዋል የሚባሉት$ ኢየሱስ ፈራጅ ነው በማለታቸው አይደለም፡፡ በአዳኝነቱ ዘመን እርሱን ፈራጅ ብለው በመሠየማቸው ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ዓለምን እንዲያድን የላከውን መድኀኒታችንን ኢየሱስን$ በዓለም ፍጻሜ ደግሞ ፈራጅ አድርጎ ሾሞታል (ዮሐ. 5$22-23፤ የሐዋ. 10$42፤ 17$31፤ 2ቆሮ. 5$10፤ 2ጢሞ. 4$1)፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅነት የሚናገሩ ናቸው፡፡ ራሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱም ፈራጅነቱን የጠቀሱት ወደ ፊት በዳግም ምጽአቱ ከሚሆነው ፍርድ ጋር አያይዘው ነው፡፡ እንዲያውም ለአዳኝነቱ አጽንዖት ለመስጠት ሲሉ ፈራጅነቱን እንደ ጠቀሱት ግልጽ ነው፡፡ ወደ ፊት ሊፈርድ የተዘጋጀው እርሱ ስለ ሆነ ከሚመጣው ፍርድ ለማምለጥ ዛሬ በአዳኝነቱ እመኑ የሚል ነበር መልእክታቸው፡፡

ለምሳሌ፡- ጌታ ፍርድ ሁሉ ለእርሱ እንደ ተሰጠው ከገለጸ በኋላ$ “ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው$ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም፡፡” ሲል አሁን በእርሱ ስለሚገኘው መዳን ነው የተናገረው፡፡ ከሐዋርያትም ጴጥሮስ ወደ ፊት ይፈርድ ዘንድ በእግዚአብሔር የተወሰነው እርሱ መሆኑን ከገለጸ በኋላ$ ዛሬ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል” (የሐዋ. 10$42-43) በማለት ባላመኑበት ላይ ወደ ፊት የሚፈርደው ኢየሱስ÷ ለሚያምኑበት ዛሬ አዳኝና መድኀኒት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ትምህርቱ ይኸው ብቻ ነው፤ አይለወጥም፡፡ ኢየሱስ ፈራጅ መሆኑ የሚነገረውና የወንጌሉን ብሥራት ሰዎች ሰምተው አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ያለባቸው$ ዓለምን ለማዳን በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ካላመኑ$ በመጨረሻው ቀን የሚፈርድባቸው እርሱ ስለ ሆነ ነው፡፡

በርግጥ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ያላመኑ ሁሉ ወደ ፊት ሳይሆን ከአሁን ጀምሮ ተፈርዶባቸዋል (ዮሐ. 3$18)፡፡ በፍርድ ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸው በእርሱ አለማመናቸው ነው እንጂ÷ ጌታ አሁን በፍርድ ወንበር ላይ ተሰይሞ ፍርድ የሰጠ ሆኖ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች በሕይወተ ሥጋ እስካሉ ድረስ ከፍርድ ለማምለጥ ዕድሉ አላቸው፡፡ በተሰጣቸው የንስሓ ዕድል ተጠቅመው ወደ ማመን ካልመጡና ባለ ማመን ከጸኑ$ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉም ከሞቱ ግን ከፍርድ በቀር በይግባኝ የሚታይ ሌላ የመዳን ተስፋ ፈጽሞ የላቸውም (ዕብ. 9$27)፡፡       

*    ሮሜ 8$34 ምን ይላል?
ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን መካከለኛ አይደለም ፈራጅ ነው የሚለው አመለካከት$ ምንም ዐይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንደሌለው ከላይ ለመመልከት ሞክረናል፡፡ ይሁን እንጂ አመለካከቱ መሬት እንዲይዝ ለማድረግ በአመለካከቱ አቀንቃኞች በኩል ያልተፈነቀለ ድንጋይ ያልተቈፈረ ጕድጓድ አለ ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ነገሩ ጦዞ ለአመለካከቱ ድጋፍ እንዲሆን በሚል የእግዚአብሔርን ቃል እስከ መቀየር የደረሰ ርምጃ ተወስዷል፡፡ በዚህ ረገድ ሮሜ 8$34 ይጠቀሳል፡፡

የ1953 ዓ.ም. ትርጕም መጽሐፍ ቅዱስ የሮሜ 8$33-34 ቃል እንዲህ ይላል፡፡ “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኰንንስ ማነው? የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡” ይሁን እንጂ በ2000 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ባሳተመችውና የግእዙን ትርጕም መሠረት አድርጎ በተዘጋጀው ሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ$ስለ እኛ የሚማልደው” የሚለው ሐረግ “ስለ እኛ የሚፈርደው” በሚለው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ግን እንደ 1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ “ግሪኩ ‘የሚማልደው’ ይላል” በሚል ተቀምጧል፡፡ ታዲያ የትኛው ቅጂ ነው ታማኝ? ዐዲስ ኪዳን በመጀመሪያ የተጻፈበት የግሪኩ ቅጂ ወይስ የቅጂ ቅጂ የሆነው ግእዙ?  

የተደረገው ለውጥ በምን ላይ የተመሠረተ እንደ ሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የሐረጉ ግእዛዊ ንባብ “ይትዋቀሥ በእንቲኣነ” የሚል ሲሆን$ ወደ ዐማርኛ ሲመለስ “ስለ እኛ ይሟገታል  ወይም ይከራከራል” የሚል ፍቺ ይሰጣል፡፡ “ተዋቀሠ” የሚለው ግስም$ በቁሙ (ተዋቀሠ)፣ ተሟገተ፣ ተከራከረ የሚሉ ፍቺዎችን ይሰጣል እንጂ$ “ይፈርዳል” ተብሎ ሊተረጐም አይችልም (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ 401)፡፡ ታዲያ ግሱን አለ ፍቺው መተርጐም ለምን አስፈለገ? አለ ንባቡ በተሳሳተ መንገድ በተተረጐመ ቃልስ እውነተኛ መሆን እንዴት ይቻላል?

“ስለ እኛ ይፈርዳል” ተብሎ የተተረጐመው ስሕተት የሆነው አለ ንባቡ በመተርጐሙ ብቻ አይደለም፤ በሕገ ሰዋስው መሠረት ሲታይ ሐረጉ በአረፍተ ነገሩ ውስጥ እንዲገልጽ የተፈለገውን ሐሳብ ስለማይገልጽና ሌላ ትርጕም ስለሚሰጥም ጭምር ነው እንጂ፡፡ በዐማርኛ ሰዋስው “ስለ እኛ ይፈርዳል” የሚል ንባብ “ለእኛ ይፈርዳል” የሚል ትርጕም ሊሰጥ አይችልም፡፡ የሚሰጠው ፍቺ በእኛ ምትክ፣ እኛን ወክሎ ይፈርዳል የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቃሉን የለወጡት ወገኖች ቃሉ እንዲናገርላቸው የፈለጉትን “ለእኛ ይፈርዳል” የሚለውን ሐሳብ አይጠራላቸውም፡፡ እንዲያውም ያልጠበቁትን ትርጕም ይሰጥባቸዋል፡፡ የተፈለገውን ትርጕም ይሰጥ ዘንድ “ስለ” የሚለው መስተዋድድ ይፈርዳል ከሚለው ግስ ጋር ሳይሆን ይማልዳል ወይም ይከራከራል ከሚለው ግስ ጋር ነው ሊሄድ የሚችለው፡፡

ዐውደ ምንባቡ የሚናገረው ስለ መፍረድ ነው? ወይስ ስለ መማለድ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ የጥቅሱ መነሻ ሐሳብ «እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?» የሚለው ሲሆን$ ምላሹ ማንም! የሚል ነው፤ እግዚአብሔር ያጸደቃቸውን ማንም ሊኰንናቸው አይችልምና፡፡ ከሳሽ ቢነሣ ግን በኀጢአት ከመጠየቅ በሞቱ$ ፍዳ ሞታቸውን የከፈለላቸውና በትንሣኤው ያጸደቃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ$ በእግዚአብሔር ቀኝ ስለ እነርሱ ይሟገታልና (በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተከፈለው ቤዛ ይታይላቸዋል ማለት ነው) ክሱ ውድቅ ይሆናል፡፡ የመጨረሻ ብይን በተሰጠበት ጕዳይ ላይ ከሳሽ ተቃውሞ ቢያሰማ$ ቀድሞ የተወሰነውን ውሳኔ ከማስታወስና ከማሳወቅ በቀር ዳግም ፍርድ ሊሰጥ እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በትክክለኛ ፍርድ አንድ ጊዜ ያጸደቃቸውን ከሳሽ ቢቃወማቸው$ የሚያስፈልገው ዳግም የሚፈርድላቸው ዳኛ ሳይሆን የኀጢአታቸውን ዕዳ ከፍዬላቸዋለሁ እኮ! የሚል ተሟጋች ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሳሽ ቢነሣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነውየተባለው፡፡              

ይቀጥላል

(በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ)
[1] ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፤ ሦስት ልደታት አሉት በሚሉ ነጥቦች ላይ የሚነሡትን ክርክሮች  የተመለከተ ነው፡፡
[2] የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 101-104
[3] የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ 1974፣ 111-112
[4] ዝኒ ከማሁ ገጽ 112

No comments:

Post a Comment