Friday, October 4, 2013

ርእሰ አንቀጽ


እስከ መቼ?

የሰው ልጅ በኑሮው ውስጥ እውነተኛ ፍርድን ይፈልጋል፡፡ የክፉዎች ተራ ሲያበቃና እውነት ስፍራዋን ስትይዝ ማየት ይናፍቃል፡፡ እውነትን ሁሉም ጥቁር ካባ ሲያለብሳት፥ እውነተኞች ጥላሸት ሲቀቡ ማየት ለእውነተኞች ሕመም አለው፡፡ እውነት በሌለበት ፍርድ የለምና እውነትና ፍርድ በጠፋበት ዓለም ላይ እውነተኞች ፍርድን ከሰማይ ይናፍቃሉ፡፡ የሰማዩ ፍርድ የዘገየ ሲመስልም እስከ መቼ? ይላሉ፡፡ ዐልፎ ዐልፎ የእውነት ጊዜ ብልጭ ይልና ብዙ ሳያጣጥሙት ቶሎ ድርግም ይልባቸዋል፡፡ የሐሰት ዘመን ሲረዝምባቸውም በሐዘን ድምፅ እስከ መቼ? ይላሉ፡፡

ሰው ስለ እውነት ከእግዚአብሔር ካልተማረ÷ ኑሮው የሚያስተምረው ጥቂቱን ነው፡፡ የእድሜ ርዝማኔም በራሱ የእውነትን ዕውቀት ለመግለጽ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ብዙ አይደለም፡፡ የታሪክ ክምርም ወደ እውነት አያደርስም፡፡ ወደ እውነት ለመድረስ እግዚአብሔር የዘመን ደወል ያደረጋቸውን እውነተኞቹን መምህራን ማድመጥ ይጠይቃል፡፡


ዕውቀት ክብር ባላገኝበት አገር ሊቃውንት ተጨንቀውና ፈርተው ይኖራሉ፡፡ ጆሮ ጠገቦች ደግሞ ይፋንናሉ፡፡ ዕውቀታቸውን ለሥጋ ማደሪያ የሸጡ ሰዎች ደግሞ የነፍሰ ገዳዮች አዝማች ይሆናሉ፡፡ አለማወቅ እንደ ሃይማኖተኛ፥ ማወቅ እንደ መናፍቅ የሚቈጠርበት አገር ይልታደለ አገር ነው፡፡ የሃይማኖት ማእከል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ተከድኖ ወግና ልማድ መጽሐፉን ተክቶ የሚመራበት አገር ትውልድን ለዘላለማዊ ሞት ይወልዳል፡፡ ባለፈው ታሪክ እየተዝናኑ የሚኖሩ መምህራን ባሉበት አገር “ጉረኛ” እንጂ እውነተኛ ትውልድ አይፈጠርም፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ለእውነተኞች ስፋራ ዐጥታ ኖራለች፡፡ እንደ ድመት ወልዳ የምትበላ አገር እንደ ሆነች ታሪካቸውን በደም የጻፉት ሊቃውንትና ጳጳሳት ይመሰክራሉ፡፡ ባለማወቁ ዘመን ያከበረችውን ልጇን ሲያውቅ መናፍቅ፥ ከሓዲ ትለዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ባለው ታሪክ የበለፀገች ናት፡፡ ጦርነትን የሚባርኩት ካህናት ሲከበሩባት፥ የሚበጀውን የሚመክሩት ግን ይዋረዱባታል፡፡

በጣልያን ወረራ ጊዜ በአዲስ አበባ ላይ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በከበሮና በጽናጽል እየዘመሩ ጣሊያንን እንደ ተቀበሉ ይነገራል፡፡ ጣልያንን የተቃወሙ ሊቃውንት ደግሞ በኢትዮጵያና በጣልያን አገር እስር ቤቶች ማቀዋል፡፡ ነጻነት ሲመለስ እነዚያ ከዘመን ጋር ሲመሳሰሉ የኖሩት ሲከበሩ፥ ለአገራቸው ዋጋ የከፈሉት ግን ተግዘዋል፡፡ ለዘመናትም በካህናት ከሳሽነት በነገሥታት ፈራጅነት የስንቶች ደም ፈሷል?

ነገሥታቱ ቤተ ክርስቲያንን የሥልጣናቸው ሞግዚት አድርገዋት ኖረዋል፡፡ ካህናትና ነገሥታት እንደ ሰምና ወርቅ እየተናበቡ፥ እንደ ወንድና ሴት እያበሩ፥ እንደ ሰይፍና ሰገባ በአንድ እያደሩ ሊቃውንትን የሚፈጁበት ዘመን በማብቃቱ የዛሬ መሪዎች ሲወደሱ÷ ካህናት ግን ለክፋት ብቻችንንም በቂ ነን ብለው ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው ዳኛ ሆነው ብዙዎችን ዛሬም ይገፋሉ፡፡ ግፈኛ አስተዳዳሪዎችን የሚቀጣ፣ ለተገፉት የሚፈርድ ዳኛ፣ በሃይማኖት ስም የተቀመጡ ሰዎች የሚያደርጉትን ግፍ ሊመለከት፥ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሚገፉት ወገኖቻችንም እንደ ዜጋ ሊሟገትላቸው ይገባል፡፡ አሊያ ሃይማኖት ያለ መከሰስ መብት እየመሰለና የግፈኞች ዋሻ እየሆነ ይመጣል፡፡

ባሳለፍነው የብዙ ዘመናት ታሪካችን ችግራችን በአብዛኛው የውጪ ሳይሆን የውስጥ ነው፡፡ አስታራቂ መሆን የሚገባት ቤተ ክርስቲያንም የግፉ ተዋናይና በግልግል ኗሪ ሆና ታሪኩን አክፍታዋለች፡፡ ሌላውን ወይም ባዕዱን የምታከብረው አገር የገዛ ልጆቿን መውደድና ማክበር ተስኗት ሊቃውንቷ ለዘመናት ያነቡባታል፡፡ ማወቅ ዕዳ ሆኖባቸው ዕዳ ይከፍሉበታል፡፡ የሠለጠነው ሕዝብ በዐዋቆቹ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የመውጫ በሩን በማሳየት በመከራ ጅራፍ ማባረሯ በጣም ያሳዝናል፡፡

የአገራችን ሊቃውንት ከትላንት እስከ ዛሬ ስደት ዕጣቸው ሆኗል፡፡ ባዕድን እያወደሱ የገዛ ልጅን መናቅ ምን ዐይነት የማይድን በሽታ ነው! በቅንአትና በምቀኝነት የታወሩ፣ ሥልጣን እንጀራቸው የሆነ አላዋቂ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚያን ሁሉ ሊቃውንት ሲያሳድዱ፥ ለምን? የሚል መጥፋቱ ያስገርማል፡፡ በድንቊርና ጨለማ ጋርደው፥ ማንነታቸው እንዳይታይ የወንጌልን መብራት አጥፍተው በጨለማ የሚመሩ ሰዎች፥ በከባድ የወሬ ነፋስ መብራቱን ለማጥፋት ቢሞክሩም፥ እውነት ግን ይበልጥ ትንቦገቦጋለች እንጂ አትጠፋም፡፡

ለ1600 ዓመታት የግብጻውያን ጥገኛ ሆና የኖረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን÷ ከተማሩት ልጆቿ ይልቅ እንደ ሥዕል ተከናንበው ከመቀመጥ በቀር ቋንቋቸው የማይታወቀውን ግብጻውያን ጳጳሳትን እያከበረች ኖራለች፡፡ ሊቃውንቱም ለግብጻውያኑ ስለማይገዙላቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ነጻነት ስለሚሟገቱ፥ ጳጳሳቱ ካልተማሩት ሰዎች ጋር በማበር ሊቃውንቱን ሲያወግዙ ኖረዋል፡፡

የግብጻውያን መንፈሳዊ ቀንበር ተወግዶ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን ብናይም፥ ያው የማስተማር ችግራችን እንደ ገና ወድቆብን፥ ከዕውቀት ገበታችን ከዐዲስ ኪዳን ምግባችን ርቀን እንኖራለን፡፡ የሕዝቡን ቋንቋ ብናውቅም አላስተማርነውም የሚሉ አንዳንድ ሊቃውንት ቢነሡም÷ የተለመዱት፡- ከሓዲ፣ መናፍቅ፣ ፀረ ማርያምና የመሳሰሉት “ታፔላዎች” እየተለጠፉባቸው ተሰደዋል፤ ተግዘዋል፡፡ ይህ ዕጣ ከደረሳቸው ውስጥ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሊቅ ይጠየቃል እንጂ ይጋዛል ወይ? የሚል ጥያቄ ዛሬም ማንሣት አስፈልጓል፡፡ ቋንቋቸውን የማናውቀውን ቋንቋችንን የማያውቁትን ግብጻውያን ጳጳሳትን በብዙ ወቄት ወርቅ ገዝቶ፥ የተማሩትንና ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የነበሩትን አበው በነጻ ማባረር አሳዛኝ ተግባር ነው፡፡  
    
የአገራችን ሊቃውንት ከትናንት እስከ ዛሬ ዕጣቸው መሰደድ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከሥጋቸው ምቾት ይልቅ የነፍሳቸውን መዳን የመረጡቱ፥ በመከራ ውስጥ ዐልፈው ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ ስለ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ብዙ ደክመዋል፡፡ ሌሎቹ ግን ስም ፈርተው፥ ዐውቀው እንዳላወቁ፣ አፍ እያላቸው እንደ ዲዳ ኖረዋል፤ ዛሬም እየኖሩ ነው፡፡


ከሞተና ከተረሳ ሰው በላይ ከሰው ኅሊና ውስጥ እንዲወጡና እንዲዘነጉ የተደረጉ ሊቃውንት ብዙ ናቸው፡፡ የመልካም ሥራቸውና የተጋድሎአቸው መታሰቢያ ግን ከእግዚአብሔር ቤት አይጠፋምና እንደ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ያሉ አበው ዛሬም እንደ ገና ያበራሉ፡፡ ተጋድሎአቸው ለተጋድሎአችን፥ ከእውነት ጋር መወገናቸው ክርስቶስን ለመምረጣችን አጋዥ ነው፡፡

(በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment