Tuesday, June 25, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ



 የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው ቀጠለ

በፍሬምናጦስ አገልግሎት ክርስትና በኢትዮጵያ ፍሬ ማፍራት ጀምሮ እንደ ነበረ ባለፈው ዕትም አንብበን ነበር፡፡ በአዳኝነቱ ኢየሱስ፥ ሰውንና እግዚአብሔርን በአንድ አካል በማገናኘቱና ለፍጹምና ዘላቂ ኅብረት በማብቃቱ ዐማኑኤል፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በተመሠረተ ኅብረት ላይ ለሚከናወነው የንጉሥነት፣ የነቢይነትና የክህነት አገልግሎት በመሠየሙ ክርስቶስ የተባለው፥ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል በተሰበከባት በሳባ ኢትዮጵያ መዲና በአክሱም ከተማ “ጽዮን” ወይም “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” የተባለችው ቤተ ክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን) ተቋቁማ እንደ ነበረ ተመልክቶ የነበረውን እናስታውሳለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃልም በዕብራ ይስጡ ኳሃል፥ በግሪክኛው አቅሌስያ ምስጢርና ዘይቤ ሲፈታ ጉባኤ ምእመናንን እንደሚያመለክት ተገልጾ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከሁለት ቍጥር ጀምሮ ብዛት ያላቸውን ያቀፈ፥ ከዚያም በላይ በመላው ዓለም የነበሩትን፣ ያሉትንና ገናም የሚኖሩት በክርስቶስ ደም የተዋጁትን ምእመናን ሁሉ ያቀፈች ለክርስቶስ አካልነት፣ ለክርስቶስ ሙሽሪትነት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ የበቃችውን የቦታ ክልል የማይጋርዳትን፣ ከጾታ፣ ከዕድሜ፣ ከወገን ሁሉ የተጠራችውንና የተመረጠችውን አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደሚገልጽ አንብበን የነበረውን እናስታውሳለን፡፡


በተለይም በግእዝ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል “ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ይሁዳ፣ ቤተ ዳዊት” በተባለው ዐይነት የክርስቲያን ወገን በሚል ትርጕሙ ልንጠቀምበት እንደምንችል በሦስተኛ ደረጃ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፥ ክርስቲያኖች ለአምልኮተ እግዚአብሔር የሚሰበሰቡበትን ቤት “ቤተ ክርስቲያን” ብንለው ግን የቤቱ ባለቤቶች (ባለንብረቶች) ክርስቲያኖች እንደ ሆኑ የሚያስረዳ ተራ ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ ካልሆነ በቀር የአቅሌስያን ትርጕም ለማስያዝ እንደማያስኬድ አስገንዝበን ነበር፡፡

እንግዲህ እንደ ፍሬምናጦስና ተከታዮቹ አስተሳሰብ የማኅበራቸውንና የክርስቲያናዊ ድርጅታቸውን ስም “ጽዮን” ወይም “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” ለማለት ያነሣሣቸው በክርስቶስ ደም ታጥባ የነጻችውና የምእመናንን ስብስብ ለመግለጽ አመቺነቱንና የምስጢራዊ ሀብት ክምችት የተሞላበት ቃልነቱን በመምረጥ መሆኑንም ለማየት ሞክረን ነበር፡፡

በዛሬው ዕትምም ከዚሁ በማያያዝ የፍሬምናጦስን ታሪካዊ የሥራ ፍሬ ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡

ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትን መንፈሳዊ ድርጅት መመሥረቱ

ፍሬምናጦስ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሲከናወን ለሚኖረው ቃሉን የመዝራትና የመሰብሰብ ዑደት አንቀሳቃሽ ኀይሎችን፥ ዕቅዶችንና መርሐ ግብሮችን ዘርግቷል ብለናል፡፡

የወንጌልን ቃል የተቀበሉትን፥ በተቀበሉት ጸንተው ይኖሩና እርስ በርስ ይተናነጹ ዘንድ ማስተዋወቅና ማሰባሰብ፥ በአንድ ሀገራዊት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥርም እንዲታቀፉ ማድረግ ከቻለ በኋላ የሚቀጥለውና ፍሬምናጦስን ይጠብቀው የነበረ ታላቅ ሥራ የቤተ ክርስቲያኑን ድርጅታዊ ሥራ የሚመሩትን በመምረጥና በማስመረጥ የተጠናከረ ድርጅት ማቋቋም ነበር፡፡ ፍሬምናጦስ ከአይሁድ እምነትና ከአረማዊነት የተጠሩትን ክርስቲያኖች አሰባስባ ከያዘች ማኅበረ ጽዮን አባላት መካከል በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመራ ለየሥራ ዘርፉ አስፈላጊ የሆኑትን በመመደብ ኀላፊነቱን አከፋፈለ፡፡

1. የዲያቆናት ምርጫና ሹመት

በመዲናዋ በአክሱም ተማክላ የተቋቋመችውን የማኅበረ ጽዮንን ድርጅታዊ ሥራ በየመልኩ መመደብና ማዋቀር ኀላፊነትንም በየፈርጁ ማከፋፈል ሲጀምር፥ የምርጫው ቅድሚያ ከይሁዲነት (ከተይህዶ) ወደ ክርስትና በተመለሱት ምእመናን ላይ ማረፉ አስገራሚነት አለው፡፡ ምንም ነገሥታቱ ጭምር ከአረማዊነት የመጡ ቢሆኑም፥ ምንም በማኅበረ ጽዮን ውስጥ አረማዊነትን በመተው ወደ ክርስትና የገቡት ብዛት የነበራቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገመት ቢሆንም፥ ምርጫው የሰው ፊትን በመመልከት አድልዎ ያልነበረበት ሆነና አይሁድ ክርስቲያኖች በምርጫው ከፍተኛውንና ብዙውን የአመራር ቦታ ሊይዙ በቁ፡፡

አይሁድ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት በጥልቀት ያጠኑ፥ የመረመሩ፥ ሊመጣ ያለውን መሲሕ እንደ እግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሲጠባበቁ የቈዩ ነበሩና የጠበቁት መሲሕ መምጣቱንና በኢሳ. 53 እንደ ተነገረውና በሌሎቹም ነቢያት እንደ ተተነበየው የሰውን ኀጢአት ተሸክሞ ከተሠዋ በኋላ፥ ከሞት ተነሥቶና ዐርጎ በአባቱ ቀኝ መቀመጡን በማብሠር በተስፋ ላይ ተመሥርቶ ለነበረው እምነታቸው ፍጻሜውን መስበክ ማለት ነው፡፡ ለአረማውያን ወንጌልን ማስተማር ግን ከዚህ የተለየ መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ መጀመሪያ ከጣዖት አምልኮ እንዲለዩ፥ በሰው ያልተሠራውንና ሁሉን የፈጠረውን የአንድ አምላክ መኖርን እንዲቀበሉ በማስተማር ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም የሁሉ ፈጣሪ የሆነው አምላክ በፍጥረቱ መታወቁን፥ በቃሉም ራሱን መግለጹን፥ ሰው በኀጢአት ከወደቀ በኋላ ከአምላኩ መለየቱን፥ አምላኩ ፍቅር ስለ ሆነ ሰውን ለማዳን በቃሉ ተስፋ መስጠቱን፥ ቃል የገባውንም ተስፋ በክርስቶስ መፈጸሙን ማስተማር ያሻል፡፡ ለአንድ አይሁዳዊ ወንጌል ከመስበክ በብዙ ሁኔታ ይለያያል ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ መሠረቱና ግድግዳው ተጠናቆ ለተሠራው ቤት ጣሪያ ማልበስ፥ በርና መስኮቶችን መግጠምና ቀለም ቀባብቶ ቤቱን ማጠናቀቅ የሚቻል ሲሆን፥ ዐዲስ ቤት ለመሥራት ግን ከዚህ የበለጠ ድካምን፥ ጊዜንና ገንዘብን ይጠይቃል፡፡ ቤቱ የሚቆምበትን ቦታ መመንጠር ለመሠረት የሚሆነን ጉድጓድ መቆፈር፤ ለመሠረት፥ ለግድግዳውና ለጣሪያው የሚያስፈልጉትን የሕንጻ መሣሪዎች ሁሉ ማቅረብና ሥራውን አስጀምሮ ማስጨረስ ይኖራል ማለት ነው፡፡

እንደዚሁም ፍሬምናጦስ በሰበከው ወንጌል ያመኑ አይሁድም አረማውንም በተቋቋመችው ማኅበራቸው “ማኅበረ ጽዮን” የታቀፉ ቢሆኑም አይሁድ ክርስቲያኖች ቃሉን በመቀበልና በጸጋ ስጦታዎች ከሌሎቹ ክርስቲያኖች ልቀውና ቀድመው ተገኙ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፍሬምናጦስ ከማኅበረ ጽዮን የሚከተሉትን ለአገልግሎት መረጠና ሾመ፡፡

ፊንሐስ ይባል የነበረውን - ተንሥአ ክርስቶስ
አሮን ይባል የነበረውን - ስምዖን
አዛርያስ ይባል የነበረውን - ማቴዎስ
አቤሜሌክ ይባል የነበረውን - ስብሐት ለአብ
ሄኖክ ይባል የነበረውን - ዐማኑኤል
መልከ ጼዴቅ ይባል የነበረውን - አሐዱ አምላክ
ሳዶቅ ይባል የነበረውን - ማዕቀበ እግዚእ በማለት ዐዲስ ስምና ዐዲስ ሥራ ሰጣቸው፡፡

የስማቸው መለወጥ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምናልባት ከነበሩበት ማኅበረሰብ የሚያገናኛቸው ስም እንኳ እንዳይኖርና ፈጽሞ እንዲለዩ ለማድረግ ታስቦ ይሆናል፡፡ ወይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ሲመርጥ የአንዳንዶቹን ስም ለውጦ የነበረውን መሠረት በማድረግና አርኣያውን በመከተል ሊሆን ይችላል (ማር. 3፥16-17)፡፡ ስለ ዲያቆናቱም አሿሿም የተገኘው ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡

“መቅድመ ኵሉ ሤሞሙ ለሰብዐቱ ደቂቅ ዘነበሩ ውስተ ደብተራ ከመ ይኩኑ ልኡካነ ወይትራድእዎ በጊዜ ቅዳሴ ወቍርባን ወወሰዶሙ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ወሰመዮ ለፊንሐስ ተንሥአ ክርስቶስ፤ ወለአሮን ስምዖን፤ ወለአዛርያስ ማቴዎስ፤ ወለአቤሜሌክ ስብሐት ለአብ፤ ወለሄኖክ ዐማኑኤል፤ ወለመልከ ጼዴቅ አሐዱ አምላክ፣ ወለሳዶቅ ማዕቀበ እግዚእ ወረሰዮሙ ዲያቆናተ፡፡” ከሁሉ አስቀድሞ እነዚህም በስም የተጠቀሱትን አይሁድ ክርስቲያኖች ዐዲስ ስም በማውጣት፥ ፍንሐስን ተንሥአ ክርስቶስ፣ ወዘተርፈ እያለ ከሠየማቸው በኋላ ዲያቆናት አድርጎ እንደ ሾማቸው ይተርካል፡፡

የዚያን ጊዜ የዲቁና ማዕርግ ከአሁኑ ምን ያህል የተለየና የከበረም እንደ ነበር በ1ጢሞ. 3፥8-13 የተጻፈውን መመልከት ይጠቅማል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጥበብንና እምነትን አብዝቶ የሞላባቸው ብቻ ለዲቁና ይመረጡ ነበር (ሐ.ሥ. 6፥3፤ 6፥10፤ 21፥8-9)፡፡ ፍሬምናጦስና ማኅበሩ የዲያቆናቱን ቊጥር በሰባት የወሰኑት፥ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ካደረጉት ጋር ለማመሳሰል ይሆን?

እነዚህን ዲያቆናት “ዘነበሩ ውስተ ደብተራ - በድንኳን ውስጥ የነበሩ” ሲል ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት በአይሁዳዊነታቸው እንደ ምኵራብ ይገለገሉበት የነበረውን፥ ወይም ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ የመሰብሰቢያ ሕንጻ ባልተሠራበት ጊዜ ለአምልኮ ይሰበሰቡበት የነበረውን ድንኳን ለማመልከት እንደ ሆነ ግልጽ አይደለም፡

2.  ጸሓፊዎችን መሾም
ፍሬምናጦስ በአክሱም የተመሠረተውን ማኅበረ ጽዮንን ሥርዐት ባለው መንገድ ለማጠናከርና ኀላፊነቱ የሚጠይቀውን ሁሉ አሟልቶ ፈር ለማስያዝ፣ የተወጠነውንም ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ ሁለት ጸሓፊዎችን እንደ ሾመ በታሪኩ ተመዝግቧል፡፡ “ወኀረየ እምላእካነ ጽዮን ክልኤ፣ አሐደ ተክለ ሃይማኖትሃ፣ ወካልኦ ገብረ መስቀልሃ፣ ወሤሞሙ ጸሐፍተ - ከጽዮን አገልጋዮችም አንደኛ ተክለ ሃይማኖትን፣ ሁለተኛ ገብረ መስቀልን፣ (እነዚህን ሁለቱን) መረጠና ጸሓፊዎች አድርጎ ሾማቸው፡፡” በማለት ከዲያቆናት ቀጥሎ የተሾሙት ጸሓፊዎች እንደ ነበሩ ይናገራል፡፡ እነዚህ ተሿሚዎች አይሁዳዊ ስማቸው ባለ መገለጹ፣ ምናልባት ወደ ማኅበረ ጽዮን ከገቡት አረማውያን ከነበሩ ምእመናን መካከል የተመረጡም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፍሬምናጦስ የማኅበረ ጽዮን ጸሓፊዎች እንዲሆኑ ያስመረጣቸውና የመረጣቸው ሁለት ምእመናን የቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀታቸውን ጥልቀትና የመንፈሳዊ ሕይወታቸውን መብሰል፣ ትጋታቸውን፣ በጎ ፈቃዳቸውንና ብርታታቸውን ጭምር በማጥናት ከመረመረ በኋላ ብልጫ የነበራቸው መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ይችላል፡፡ ለጸሓፊነት የተመረጡት ምእመናን ቀደም ሲል፣ “ከመ ይኩኑ ልኡካነ” ተብለው ለዲቁና ተመርጠው ከነበሩት መካካል እንደ ሆነ ለማመልከት “ወኀረየ እምላእካነ ጽዮን - ከጽዮን አገልጋዮች (ዲያቆናት) መካከል ሁለት ጸሓፊዎችን ሾመ” አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከፍ ብሎ ስማቸው የተጠራው ሰባት ዲያቆናት ዋነኞቹ እንደ ሆኑና ስማቸው ያልተጠራ ሌሎች ረዳት ዲያቆናት እንደ ነበሩ ያስገነዝባል፡፡

ሰባቱ ዲያቆናት በአምልኮ ጊዜ ከነበራቸው የሥራ ድርሻ ሌላ የማኅበረ ጽዮንን ድርጅታዊ ሥራና ያጋጥም የነበረውን ጉዳይ ሁሉ ከፍሬምናጦስ ጋር በመመካከር የሚያጠኑ፣ የሚወስኑና ተግባራዊ እንቅስቃሴውንም የሚከታተሉ ሳይሆኑ አይቀርም ተብሎ ይገመታል፡፡ እንደ እስጢፋኖስና ፊልጶስም ምእመናንን በቃለ እግዚአብሔር በመመገብ ማሳደግ፣ ማጐልመስና ማጐልበትም፣ መምከርና መገሠጽም፣ ክርስቲያን ላልነበሩትም በመመስከር ወደ ጌታና ማኅበሩ ማምጣት በወንጌላዊነት ከሚፈጽሟቸው ተግባራት ጥቂቶቹ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ጸሓፊዎች ግን የማኅበረ ጽዮንን የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ በመመዝገብ እየጻፉ ከመጠበቅ በተጨማሪ ከዲያቆናቱና ከፍሬምናጦስ ጋር አስተዳደራዊውን ጕዳይ ሳይጋሩ አይቀሩም፡፡

ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሥራዎችን እንቅስቃሴ መመዝገብ የተለመደ ነበር ለሚለው ትረካ፣ አራቱ ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ በቂ ማስረጃዎች ናቸው (ሉቃ. 1፥1-4፤ ሐ.ሥ. 1፥1-2)፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለዘመኑና ለሚቀጥለው ትውልድ ላዘጋጀው የማነጽ ዕቅድ ይውሉ ዘንድ መመሪያዎች፣ የጥያቄ መልሶች፣ ተግሣጾችና ምክሮች ጭምር ተመዝግበው የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሰነዶች ሆነዋል፡፡ የጳውሎስና የሌሎቹም ሐዋርያት መልእክታት፣ የሚያስረዱት ይህንኑ ነው (ሐ.ሥ. 15፥23-31፤ 1ቆሮ. 7፥1፤ ቈላ. 4፥18፤ 1ተሰ. 5፥27፤ 2ተሰ. 3፥17፤ 1ጴጥ. 5፥12፤ 2ጴጥ. 3፥1-2፡15-16፤ 1ዮሐ. 2፥12-14፤ ይሁዳ 3)፡፡ ምእመናን በየሥራ ምድባቸው ተለይተው የሚመዘገቡበት፣ ድንጋጌዎችና የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ጭምር ተመዝግበው የሚያልፉበት ሥርዐት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የተለመደ ነበር ማለት ተችሏል (1ጢሞ. 5፥9፤ 2ቆሮ. 2፥5-11፤ 7፥8-13)፡፡

ስለዚህ ሀገራዊት ቤተ ክርስቲያናችን “ማኅበረ ጽዮን” የጸሓፊነትን ሥራ አስፈላጊነት በመረዳት ከመነሻው ጀምሮ ያለው የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉ በመዝገብ ላይ እንዲሰፍር ሁለት ጸሓፊዎችን በሹመት ደረጃ ስትመድብ ለዕለታዊው ሥራ ማስታወሻ እንዲሆን በውሱን ሐሳብ ተነሣሥታ ነው አንልም፡፡ የሐዋርያትን ትውፊት በተጠናከረ መልኩ ከመቀበል ጋር በቃል ያለው ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለው ይወረሳል የተባለውን በማስተወስ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ሰነድ እንዲኖር ጭምር ዐስባ እንደ ነበር ያስገነዝባል፡፡ ስማቸው ያልተጠራ ብዙ ዲያቆናት የመኖራቸውን ያህል ከሁለቱ ተሿሚ ጸሐፍት ሌላ ስማቸው ያልተጠራ ብዙ ጸሓፊዎች ኖረው ይሆናል፡፡ የአንዲት ሀገራዊት ቤተ ክርስቲያን የጽሕፈት ሥራ በሁለት ምእመናን አይጠናቀቅምና፡፡

ቅዱሳት መጻሐፍትን ከቋንቋ ወደ ቋንቋ መተርጐም፣ ማራባትና ማሠራጨት በጸሓፊነት ሥራ መደብ የሚጠቃለል እንደ ሆነ አይዘነጋም፡፡ በአይሁድ ታሪክም ጸሐፍት ትልቅ ስፍራና ኀላፊነት ነበራቸው፡፡ በፍሬምናጦስም ጊዜ ወይም ከዚያ ቀጥሎ እስከ 1400 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ተከታታይ ዘመናት ጸሐፍት በሀገራችን ላከናወኑት ሥራ አስረጂ የሚሆኑ ብዛት ያላቸው ሰነዶች ቢገኙ ኖሮ ብዙ ቁም ነገሮችን ሊያስተምሩን በቻሉ ነበር፡፡

3.  ማቅሰስ፣ (ቄስን መሾም)

ቅስና ምንድር ነው? ክህነት ማለት ነውን? እነዚህ ሁለት ቃላት መወራረስ ሳይገባቸው በተለምዶ እየተወራረሱ ተገኙ፡፡ በሥጋቸው ፈቃድ በመገፋፋት ሥልጣን ፈላጊዎች የሆኑት አደባለቋቸው እንጂ፣ በትርጉም ሊገናኙ ይቅርና ባሕርያዊ ዝምድና እንኳ ፈጽሞ የላቸውም፡፡ በሚከተሉትም ነጥቦችና ማስረጃዎች የእያንዳንዳቸውን ሐረገ ትውልድ እንመለከት፡፡

3.1. ቄስ (ቀሲስ) ቀሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን፣ በትርጉሙም ሽማግሌ ማለት ነው፡፡ ከግሪክኛው ፕሬስቢተር ወይም ኤጲስ ቆጶስ፣ ወይም ጳጳስ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በሐ.ሥ. 20፥17 ጳውሎስ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወደ ሚሊጢን እንዳስጠራና እንደ መከራቸው መመሪያም እንደ ሰጣቸው ይናገራል፡፡ ለእነዚህ ሽማግሌዎች ሐዋርያው በሰጣቸው መመሪያ በቍጥር 28 ላይ፣ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጰጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት በቍጥር 17 ሽማግሌዎች ያላቸውን ጳጳሳት (ጠባቂዎች) ብሎ በቍጥር 28 ላይ ጠራቸው፡፡

3.2. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ራሱ ሽማግሌ መሆኑን ገልጾ ሌሎቹን እንደርሱ ሽማግሌዎች የሆኑትን መከረ፤ ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑና እንዲጠብቁ በምክሩ አሳሰበ፡፡ ሽማግሌነቱም ለእረኛነት፣ የእግዚአብሔርን መንጋ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንደ ሆነ ገለጸ (1ጴጥ. 5፥1-4፤ ሐ.ሥ. 20፥28፤ ዮሐ. 21፥15-17፤ ዕብ. 13፥7፡17-24)፡፡

3.3. ሽማግሌዎች መመረጣቸውና በሕዝብ ላይ በበላይነት መሾማቸው በእስራኤላውያን የተለመደ ነበር፡፡ በግብጽ ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ በምድረ በዳው ጕዞ ታሪካቸው ውስጥም የቀጠለ፣ ዘመናትንም ሰንጥቆ እስከ ሐዋርያት ዘመን የደረሰ እንደ ነበረ ማስረጃዎች ይጠቍማሉ (ዘፀ. 3፥16፤ 4፥29፤ 12፥21፤ 18፥13-26፤ ዘኍ. 11፥16-30፤ ኢያ. 8፥10፤ 1ሳሙ. 16፥4፤ ኢሳ. 9፥14-16፤ ሕዝ. 8፥1-13፤ ዕዝ. 5፥5፤ 10፥14፤ ሉቃ. 7፥3፤ 22፥66-67፤ ሐ.ሥ. 4፥5፤ 8፥23)፡፡

3.4. ለሽምግልና (ቅስና፣ ኤጲስ ቆጶስና ጵጵስና) ሥራ የሚያስመርጠው፣ በዕድሜ መሸምገል ብቻም አይመስልም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በማስተዋልና በጸጋ ስጦታዎች መሞላት የመንፈስ ቅዱስንም ድምፅ ለማድመጥና ምሪቱን ለመከተል በመንጋው ውስጥ ልቆ መገኘት መንጋውን ለማሰማራት ለመመገብ ለመጠበቅ፣ ለመምራት፣ ለመገሠጽ፣ ወዘተ. በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆን፣ ለምሳሌነት መብቃት፣ ሌሎቹንም በእግዚአብሔር ቃል የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ማሟላት፣ እንዲሁም ለሥራው የእግዚአብሔር ጥሪ መኖሩን ማረጋገጥ ሲሆን፣ በመንጋውም መመረጥን ይጨምራል (1ጢሞ. 3፥1-7፤ 5፥17፤ ቲቶ 1፥5-11፤ 2፥1-2)፡፡

3.5. ሽማግሌዎችን መሾም በሐዋርያት ዘመን ተጀምሮ እንደ ነበር ሲታወቅ፣ ሽማግሌዎቹም ከሐዋርያት ጋር በመተባበር ውሳኔ ያሳለፉና መንጋውን ያስተዳድሩ እንደ ነበር ተረጋግጧል (ሐ.ሥ. 14፥23፤ 15፥1-29፤ 16፥4፤ ፊል. 1፥1)፡፡

3.6. ቄስ ወይም ሽማግሌ ወይም ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ መሆን ለክህነት መሾም ማለት አይደለም፡፡ ካህንነት በሕገ ኦሪት የታዘዘውን መሥዋዕትንና ቍርባንን ለማቅረብ መሾም ማለት ሲሆን፣ ለዚህ ዐይነቱ አገልግሎት የሚያበቃ ሹመት የተሰጠው በሥጋ ከሌዊ ለተወለደው  ለአሮንና ለልጆቹ፣ ለልጅ ልጆቹም ብቻ ነበር፡፡ (ኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ 28 እና 29ን በሙሉ ይመልከቱ፤ እንዲሁም በተጨማሪ ዘሌዋውያን 16 እና 17፥1-7)፡፡

በሐዲስ ኪዳን ግን የክህነት ሹመት ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷል፤ በእርሱም ተደምድሟል፡፡ የሌዊ አያት የሆነው አብርሃም ዐሥራትን በሰጠው በመልከ ጼዴቅ የሹመት ሥርዐት ለዘላለም ካህን እንዲሆን ከነገደ ሌዊ ያልተወለደው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሐላ ስለ ተሾመ፣ እርሱን የሚሽርና መሐላውን የሚያፈርስ ሌላ የክህነት ሥርዐት ከዚያ በኋላ አልተቋቋመም፤ አይኖርምም (ዕብ. 5፥1 እና ም. 7)፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክህነቱ ዘላለማዊ ስርየትን ይሰጥ ዘንድ መሥዋዕት አድርጎ አንድ ጊዜ ራሱን ስላቀረበ፣ ከዚያ በኋላ ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን መሠዋት አላስፈለገም (ዕብ. 8፥1-4፤ 10፥1-14)፡፡

በአሮን ክህነት መሥዋዕት ይሠዋ የነበረው በምድራዊ መቅደስ ነበር፡፡ ምድራዊውም መቅደስ የእግዚአብሔር መኖሪያ ለሆነው ለሰማያዊ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር መኖሩ ለሆነው ለሰማያዊ መቅደስ ምሳሌ ከመሆኑም በላይ፣ ውስጠኛው ክፍል ሊቀ ካህናቱ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚረጭ ደምን ይዞ እንዲገባበት እንጂ ሌላ ማንም እንዳይገባበት በመጋረጃ ተዘግቶ ቈየ፡፡ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የራሱን ደም ይዞ ወደ ሰማያዊው መቅደስ በገባ ጊዜ ሰውን ከእግዚአብሔር የለየው ኀጢአት ምሳሌ ሆኖ ምድራዊው መቅደስ የነበረው መጋረጃም ተቀደደ፡፡ በሰው ልጆች ላይ የተመዘገበው ኀጢአተኛነትና ኀጢአት በሰማይ ከተደመሰሰ በኋላ የመጋረጃ መኖር ተገቢ ባለመሆኑ ተቀደደ፤ ተወገደ (ዘፀ. 26፥30-33፤ ዘሌ. 16፥2-34፤ ማቴ. 27፥51፤ ማር. 15፥38፤ ሉቃ. 23፥45፤ ዕብ. 8፥5፤ 9፥6-8፡23-28)፡፡

እንዲህ በመሆኑም፣ የእግዚአብሔር መኖሪያ ሰማያዊ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለሚታመኑ ምእመናን  ክፍት ስለ ሆነና ዛሬ ወደ አማናዊው መቅደስ የመግባት መብት ስለ ተሰጠ፣ በሐዲስ ኪዳን ምድራዊ መቅደስ፣ ምድራዊ ክህነት፣ ምድራዊ መሥዋዕት አላስፈለገም (ኤፌ. 2፥18-19፤ 3፥7)፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናቸው የዘላለም ሕይወትን በእምነት የጨበጡ ምእመናን በእግዚአብሔር ልጅነታቸው ሰማያዊውን አባታቸውን በምድር የሚያገለግሉበት የተለያየ የጸጋ ስጦታ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንደ ተሰጣቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም የክህነት ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተፈጸመ ለቤተ ክርስቲያን በተሰጧት የጸጋ ስጦታዎች ዝርዝር ውስጥ ክህነት አንዱ ሆኖ አልተሰጠም (ሮሜ 12፥4-8፤ 1ቆሮ. 12፥4-31፤ ኤፌ. 4፥11-13)፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጧት የጸጋ ስጦታዎች ዝርዝር ውስጥ ክህነት አንዱ ሆኖ ካልተሰጠ፣ በአይሁድ መቅደስም ለማገልገል የሚያበቃ የአሮን ተወላጅነትን መቍጠር ካልተቻለ፣ ኀጢአትም በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት መሆን ለዘለዓለም ከተደመሰሰ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ መሥዋዕትን የማቅረብ ሹመት ያለው ካህን ነኝ ማለት ድፍረት አይሆንምን? (ዕብ. 10፥15-18)፡፡

3.7. በሐዲስ ኪዳን ስለ ኀጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት፣ የኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚቀርብበት ምድራዊ መቅደስና ስለ ኀጢአት ስርየት መሥዋዕት አቅራቢ አሮናዊ ካህን እንደሌለ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ የተለየ የሥራ መደብ ሆኖ ሳይቈጠር፣ የተለየ የሥራ ማዕርግና ደረጃ ሳይመደብለት፣ በተለየ ነገድና ጐሣ ላይ ሳይወድቅ፣ ለሐዲስ ኪዳን ምእመናን ሁሉ የተሰጠ መንፈሳዊ ክህነት መኖሩን የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳል፡፡ ለምእመናን ሁሉ መንፈሳዊ ክህነት መሰጠቱ፣ ለኀጢአት ስርየት የሚሆን መሥዋዕት ያይደለ፣ የመሥዋዕት ማቅረቢያ ምድራዊ መቅደስ ያልተመደበለት ልዩ የሆነ መንፈሳዊ መሥዋዕት በሊቀ ካህናታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ ሆነው ያቀርቡ ዘንድ ነው፡፡

3.7.ሀ. ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የተጠሩት ምእመናን የጠራቸውን አምላካቸውን በጎነት ላልሰሙት እየመሰከሩ ወደሚደነቀው ብርሃን ይጋብዟቸው ዘንድ የተመረጠ ትውልድና የንጉሥ ካህናት ሆነዋል (1ጴጥ. 2፥9-10)፡፡
      
       ስለዚህ ኀጢአት የተሰረየበትንና የዘላለም ሕይወት የታወጀበትን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተውን የምሥራች (ወንጌል) ቃል፣ ላልሰሙ ሰዎች በመስበክ ሊጠፉ የነበሩትን ሰዎች በምስክርነታቸው ከመድኅኑ ጋር ማገናኘት መንፈሳዊ ክህነት ይባላል፡፡ በዚህ ቦታ በክህነታቸው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት መንፈሳዊ መሥዋዕት ሰውን መሆኑ ነው (ሮሜ 15፥15-16)፡፡
      
       በእግዚአብሔር ጸጋ የተገኘውንና ሰዎች በእምነት የሚቀበሉትን ደኅንነት መመስከር የሚገባቸው በዕድሜ፣ በጾታ፣ በሥራ መደብ፣ በጐሣ የተለዩ ሰዎች አይደሉም፡፡ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የተጠሩና የጌታን የማዳን ኀይል የቀመሱ ሁሉ ናቸው እንጂ (ሮሜ 10፥8-13)፡፡

3.7.ለ. ምእመናን እገሌና እገሌት የሚባሉ ሳይኖርባቸው ሁሉም እግዚአብሔር አምላካቸው ደስ ይሰኝበት ዘንድ ሰውነታቸውን ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ መንፈሳዊ የክህነት አገልግሎት እንዲፈጽሙ ይለመናሉ (ሮሜ 12፥1-2፤ ኤፌ. 5፥1-2)፡፡

       ሰውነትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ሐዋርያው ጳውሎስ የተቃጠለ መሥዋዕት ሲለው ዳዊት ደግሞ የተሰበረ መንፈስና የተደቈሰ ልብ ይለዋል (መዝ. 50/51፥16-17)፡፡

3.7.ሐ. አንድያ ልጁን በለውጥ የሰጠላቸውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ዘወትር በማመስገን፣ ለስሙ ከሚቀርብ ምስክርነት ጋር ምስጋናን መሠዋት፣ የሐዲስ ኪዳን ምእመናን በመንፈሳዊ ክህነታቸው ከሚያቀርቧቸው መንፈሳውያን መሥዋዕቶች አንዱ ነው (ዕብ. 13፥15)፡፡
      
       በእነ አሳፍ ያደረ የትንቢት መንፈስ ከእርድ ወይም ከእህል መሥዋዕትና ቊርባን ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የላቀ መሥዋዕት ምስጋና እንደ ሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ እንዲህም የተባለው እንደ ሕጉ የእህልና የእርድ መሥዋዕትና ቊርባን ይቀርብ በነበረበት ጊዜ ነው (መዝ. 50/51፥4-14፡23)፡፡

3.7.መ. እግዚአብሔር ከሰጣቸው በረከት ላይ በመክፈል ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሚቸሩ ምእመናን በመንፈሳዊ ክህነታቸው የሚያቀርቡት ሌላው መንፈሳዊ መሥዋዕት ነው (ፊል. 4፥18፤ ዕብ. 13፥16)፡፡

ከዚህ በላይ ከ3.7.ሀ. - 3.7.መ. የተዘረዘሩትና የመሳሰሉት መንፈሳውያን መሥዋዕቶች ጐሣና ጾታ ሳይለይባቸው ከሐዲስ ኪዳን መንፈሳውያን ካህናት ማለት ከምእመናን ሁሉ መቅረብ የሚገባቸው ሲሆኑ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ ያላቁ የመንፈሳዊ ክህነት አገልግሎቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ ፍሬምናጦስ ለማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ዲያቆናትን፣ ጸሓፊዎችን፣ ቀሳውስትን ካላይ በተመለከተው ሁኔታ መርጦ በመሾም ድርጅቱን እንዳጠናከረ ተመልክተናል፡፡ ቀሳውስት ሲባልም ካህናት ማለት እንዳይደለ ከቃሉ ተገንዝበናል፡፡
በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment