Thursday, April 11, 2013

የመዳን ትምህርትከናሁ ሠናይ
ካለፈው የቀጠለ

በኀጢአት ውስጥ የተዘፈቀውን የሰውን ዝርያ ከኀጢአቱና ኀጢአቱ ካመጣበት ፍርድ ለማዳን፥ ለመቀደስና ዓለም ሳይፈጠር ታቅዶለት ወደ ነበረው የክብር ስፍራ ለመመለስ (ማቴ. 25፥34) እግዚአብሔር የተጠቀመበት መንገድ

1.     ጻድቅና ቅዱስ አፍቃሪም በሆነው በአምላካችን ዙፋናዊ ችሎት ኀጢአትን ለመቅጣት ተገቢ የሆነው ፍርድ እንዲፈጸም፡፡
2.    ከምድር ዐፈር ለተሠራው ሰው ለሥጋና ለደሙ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ለመጣች ሕያዊት ነፍሱ በዕሴት የተመጣጠነ ልዋጭ (ቤዛ) መስጠት ተገቢ ሆኖ እንደ ተገኘ ባለፈው ጮራ ቍጥር 5 በዚሁ ርእስ ስር ገልጠን የነበረ መሆኑን አንባቢ ያስታውሳል፡፡

ከዚህ በማያያዝም ከእግዚአብሔር በታደለው የመዓርገ ተፈጥሮ ከፍተኛነት የተነሣ
ሀ. ከዓለምና በውስጡ ካሉት የሀብት ክምችቶች ሁሉ፥
ለ. በሥጋና በደም ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት፥ አራዊት፥ አዕዋፍ፤ በባሕርም ከሚርመሰመሱ ፍጥረታት ሁሉ፥
ሐ. መናፍስት ሆነው ከተፈጠሩት ሠራዊተ መላእክት ሁሉ ለሰው በዕሴት የተመጣጠነ ተውላጥ (ቤዛ) እንዳልተገኘለት፤ ነገር ግን ሰው ለሆነው ወልደ እግዚአብሔር (ሥግው ቃል) ብቻ ይህ ጕዳይ የሚቻልና የሚገባም ሆኖ እንደ ተገኘ (ራእ. 5፥1-14) በዚያው ክፍል መቅረቡ ይታወቃል፡፡


በዛሬው ዕትም ደግሞ ሰውን የማዳን ሥራን ወልድ ሰው ሆኖ እንዲያጠናቅቀው በምክረ ትሥልስት ሲወሰን አምላክ የተጠቀመበትን መለኮታዊ ጥበብና የተገኘውን ውጤት እንገልጻለን፡፡

መግቢያ
ሰውን ለማዳን የሚቻለው ሰው የተከሰሰበትንና ያስፈረደበትን ኀጢአት የሚወስድለትና የሚሸከምለት ተለዋጭ (ቤዛ) በሥጋና በደሙ ብቻ ሳይሆን በነፍሱ ጭምር ፍጹም ሰው መሆን እንዳለበት አያከራክርም፡፡ ስለ ሆነም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ የሰው ቤዛ ለመሆን ፍጹም ሰው ይሆን ዘንድ አስፈላጊነት ነበረው ማለት በሰው የሚገኘውን ኹለንተና ሥጋን ነፍስንና መንፈስን (ከኀጢአት በቀር) ገንዘብ ማድረግ ይገባው ያስፈልገውም ነበረ ማለት ነው (1ተሰ. 5፥23፤ ዕብ. 2፥14-16)፡፡

ለሰው ዝርያ ሁሉ እንደ ምንጭ ሆነው የሚቈጠሩት አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር መልክ እንደ ምሳሌውም የተፈጠሩና በንጽሐ ጠባይዕ በኤድን ገነት የተመላለሱ ቢሆንም በኀጢአት ዐዘቀት ውስጥ ከተዘፈቁበት ጊዜ ጀምሮ ግን የሰው ኹለንተና በኀጢአት የርኵሰት ቀለም በመበከሉ ከእነርሱ የተወለዱት ሁሉ እንደ እነርሱ ኀጢአተኛ ባሕርይን ይዘው ተወለዱ፡፡ የሰውን ዝርያም ኀጢአተኛ ያደረገው የኀጢአት ዘር የመጣው በእባብነት ወደ ሔዋን መጥቶ ከነበረው ከሰይጣን እንደ ሆነ በእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ተጽፎአል (ዘፍ. 3፥1-19፤ ራእ. 12፥9)፡፡

ሰው ሆኖ ከሰው በመወለድም ውስጥ ለሚተላለፍ ኀጢአት በባለቤትነት የሚታወቀው ያው ሰይጣን እንደ መሆኑ መጠን ሰው ከወላጆቹ በሚወርሰው ኀጢአተኛ ባሕርይ ምክንያት የሰይጣን ውላጅነትም አለበት፡፡ የዚህም አባባል እውነተኛ ትርጉም በንጽሐ ጠባይዕ በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥሮ የነበረውን ሰው አይመስልም ማለት ነው፡፡ በተፈጥሮ ጠባይዑ ውስጥ ተጨማሪ ሆኖ ከሰይጣን የመጣ ኀጢአት ተደባልቆበታልና ከሰው ዝርያ የሚወለደው ሰው ሁሉ በኀጢአት ውስጥ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ ንጽሐ ጠባይዕ ያደፈባቸውን አዳምንና ሔዋንን መስሎና አክሎ መወለድ እንደ ተፈጥሮ ባሕርያዊ ግዴታ ሆነበት፡፡ የአዳም ዝርያ የሆነ ሰው በኀጢአት ተፀንሶ በኀጢአት ይወለዳልና (መዝ. 50/51፥5)፡፡

እንግዲያውስ ሰው ኀጢአትን የሚሠራው ከሌላ ሰው በመልመድ ሳይሆን በውስጡ ባለውና ከወላጆቹ በወረሰው ኀጢአተኛ ባሕርይ ግፊት እየተነዳ ነው የሚባለው ትምህርት እውነተኛ እንደ ሆነ የተረጋገጠ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፦ መብላት፥ መጠጣት፥ መራባት ... የመሳሰለውን ሁሉ አስፈላጊነቱንና ከራሱ ውስጥ ለሚነሣ ግፊት የመታዘዙን ግዴታ ከሰው እንደማይለምደው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ፍሬ መራራነት የሚለየው ዛፉ ተተክሎ አድጎና አብቦ ካፈራና ፍሬው ከተቀመሰ በኋላ እንደ ሆነ ቢታወቅም፥ የፍሬው መራራነት ከሌላ ዛፍ ልምድ በመቅሥም ከተገኘ ዕውቀት የመጣ እንዳልሆነ አያከራክርም፡፡ ዛፉ በባሕርዩ ይዞት የኖረውና እንዲህ እንዲያፈራ በውስጡ ካለ ግዴታዊ ግፊት እንጂ፡፡ ይህ ዛፍ መራራነትን ከየት አመጣው ቢባልም ከእርሱ በፊት ከነበረው ለእርሱ እንደ ወላጅ አባት ከሚቈጠረው ዛፍ አንድ ፍሬ ከእርጥብ ዐፈር ላይ ወደቀና በቀለ፤ ችግኝም ሆነ፤ ያም ችግኝ ተተክሎ ከአደገ በኋላ እንደ ወላጅ አባቱ ከሚቈጠረው ዛፍ በዘር የወረሰው መራራ ባሕርይ በፍሬው ታየበት ከማለት የተለየ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ የአዳምና የሔዋን ልጆች የተፈጥሮ ጠባይ መርከስ በዐጭሩ ይህንኑ የሚመስል ሆነ (ኢዮ. 14፥4)፡፡

አዎን! የአዳምና የሔዋን ልጆች ሁሉ እንደዚህ እንደ ምሳሌው በኀጢአት የርኵሰት ቀለም የተበከሉ ከሆነ ሰውን የሚያድነው ወልድም (ቃልም) ትክክለኛ የሰው ተለዋጭ ይሆን ዘንድ የሰውን ኹለንተና ገንዘብ ማድረግ ያለበት ሆኖ ከተገኘ፥ ወልድ በኀጢአት የተበከለውን የሰውን ኹለንተና ገንዘብ ቢያደርግ (ቢወሐድ) ኖሮ በኀጢአት የተበከለውን የሰውን ዝርያ በምን መንገድ ሊያድን ይችል ኖሯል? ያለ ምንም መለኮታዊ ጥበቃና ጥንቃቄ የአዳምና የሔዋን ዝርያ ከሆነ ቤተ ሰብ ቢወለድ ኖሮ እንደ ማንኛውም ሰው ኀጢአትን ወርሶ የሚወለድ፥ እንደዚሁም ኀጢአትን ተከትሎ የመጣውን ሞት የመሞት ግዴታ ከሚወርሰው ኀጠአት ጋር እንደ ማንኛውም ሰው የሚወርስ ይሆን ስለ ነበረ የሚሞተው ሞት ያው በአዳምና በሔዋን ዝርያነቱ መውረስ ለሚገባው የሞት ርስት በተቈጠረ ነበር (ዘፍ. 2፥16-17፤ ሮሜ 5፥12፤ ኤፈ. 2፥1-2)፡፡

ይህ ጕዳይ በግልባጩ ሲታይ የሚሞተው ሞት ሌላው የሚድንበት፥ የመሞት ዕዳ ላለበት ለሌላው የሚቈጠር ሞት አይሆንም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ምን መደረግ ነበረበት?

ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ሊያግባባን የሚችል ነጥብ ግልጽ ሆኖ በቅድሚያ መቀመጥ ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡ ወልድ (ቃል) አዳምና ሔዋን በኀጢአት ውስጥ ከመውደቃቸው በፊት የነበረውን በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩበትን ሥጋና ነፍሳቸውን ገንዘብ አድርጎ (ተዋሕዶ) ቢወለድ ኖሮ፥ ከአዳምና ከሔዋን ሊወረስ ከሚችል ኀጢአት ነጻ በሆነ ነበር እንበል፡፡ ያለ ኀጢአት ሆኖ ከተገኘ በኋላም ቢሞት መሞት ሳይገባው ሞቶአልና የእርሱ ሞት በኀጢአቱ ሞት ለሚገባው የሰው ዝርያ በምትክነት የመቈጠር ተገቢነት ይኖረው ነበር የሚለውንም እናክልበት፡፡ ነገር ግን ባለ መታደል አዳምና ሔዋን በኀጢአት ውስጥ ከመውደቃቸው በፊት ልጅ አልወለዱም ነበርና ከአዳምና ከሔዋን ዝርያ እንዲህ ላለው ጕዳይ የሚውል፥ ኀጢአት ያልነበረበት ቅዱስ ቤተ ሰብ በምድር አልተገኘም (ኢዮ. 15፥14)፡፡ ታዲያ በዚህ ምክንያት በእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆን፥ መከናወን እንዲገባው ከዘላለም ታቅዶ የነበረው ሰውን የማዳን ዕቅድ መሠረዝ ነበረበትን? ዕቅዱ አልተሠረዘም፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!

ሰውን የሚያድነው የእግዚአብሔር ጥበብ እንዴት ተገለጠ?

ኤልሻዳይ ለሆነው አምላካችን የቅድስና ባሕርዩ ሳይለወጥ፥ በኀጢአት ላይ ያለው ቍርጠኛ ፍርድም ሳይዛባ በሰው ዘንድ የማይቻለው፥ ከርኩስ ንጹሕ የማውጣት ችሎታው እንዲህ ሆኖ ተገለጠ፡፡ እግዚአብሔር ወልድ በኀጢአት ርኵሰት ከቀለመው ሰው ዝርያ ኀጢአትን ሳይወርስ የሰውን ኹለንተና ገንዘብ የሚያደርግበትን (የሚዋሐድበትን) ዘዴ ጥልቅ በሆነው ጥበቡ አስቀድሞ ዐቅዶት ነበር፡፡ ስለዚህም ጊዜው ሲደርስ (ገላ. 4፥4) መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል ማርያም ተልኮ በመጣ ጊዜ “… ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላልና መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል” አላት፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ወደ ድንግል ማርያም መምጣት የልዑል ኀይልም መጸለል አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው ከእርሷ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲባል በመታቀዱ መሆኑን አስረዳት፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ወልድ ንጽሐ ጠባይዕ ካደፈባቸው ማለት ከአዳምና ከሔዋን ዝርያ ኀጢአትን ሳይወርስ ያለ ኀጢአት በቅድስና እንዲፀነስና እንዲወለድ የተደረገበት መለኮታዊ ጥበብ በሥራ ላይ ዋለ (ሉቃ. 1፥35)፡፡

ጌታ መንፈስ ቅዱስ ወደ ድንግል ማርያም መጣና ቃል ከእርሷ ሊነሣ ያለውን (ገንዘብ የሚያደርገውን) ሥጋን ከሥጋዋ ነፍስንም ከነፍሷ ከፈለ፤ የተከፈለውንም ሥጋና ነፍስ አነጻና በእግዚአብሔር መልክ ቀድሞ ተፈጥሮ የነበረውን ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈበትን የመጀመሪያውን ሰው አዳምን አስመሰለው፡፡ ከዚያም የተከፈለውንና ያነጻውን ሰብእነትን ከአካለ ቃል ጋር አዋሕዶ ፅንስ አደረገው፡፡ እርሷም ወንድ ሳላውቅ መፅነስ እንዴት ይቻለኛል? ያለችው ጥያቄ ምላሹን በዚሁ አገኘ፡፡

በሰብእነትና በአምላክነት መዋሐድ (መገናዘብ) የታወቀው ፅንስ በድንግል ማርያም ማኅፀን የሚቈይበትን የእድገት ጊዜ እስኪፈጽምና ሰው በሚወለድበት ሥርዐት እስኪወለድ ድረስ የጐደፈው የሰው ባሕርይ በምንም ሁኔታ ወደ እርሱ እንዳይተላለፍ የአብ ኀይል ድንግሊቱን ጸለላት፡፡ ስለ ጸለለ ትርጉም በጮራ ቍጥር 4 ገጽ 18 ይመልከቱ፡፡ ጸለለ በመጋረድ ትርጉሙ ከተወሰደ አቧራውን እያስቀረ ብርሃንን የሚያሳልፍ መጋራጃ ሆነላት፡፡ በማጥለል ትርጉሙ ከተወሰደም የማይፈለገውን ዝቃጭ እያስቀረ ተፈላጊውን የሚያሳልፍ ማጥለያ ሆነላት ማለት ነው፡፡

ወልድ (ቃል) በዚህ ሁኔታ ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደና ዳግማዊ አዳም ተሰኘ፡፡ የመጀመሪው አዳም በኀጢአት ውስጥ ከመውደቁ በፊት በነበረው፥ ከአምላክ በታደለው ተፈጥሮ ንጽሐ ጠባይዑ በኋለኛው ዘመን የተገለጸውን መሲሕን (ኢየሱስ ክርስቶስን) የሚመስል ነበር ማለት ተቻለ (ሮሜ 5፥18፤ 1ቆሮ. 15፥45-47)፡፡

ማስገንዘቢያ
መናፍቃን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጢአትን ሳይወርስ የተወለደበትን ሁኔታ በሚመለከት፥ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ እያስተማሩ፥ ሰዎችን ወደ ስሕተት ዐዘቅት ለመጣል የሚዘረጓቸውን የትምህርት ወጥመዶች እንመርምራቸው፡፡

አንደኛው ቡድን፡- የሚወረስ ኀጢአት የሚባል የለም፤ ሰው ኀጢአትን ሊሠራ የሚነሣሣው ኀጢአትን ከሚሠራ ሌላ ሰው በማየትና በመልመድ ነው ይላል፡፡ ዳዊትም እንኳ “እነሆ በዐመፃ ተፀንስሁ እናቴም በኀጢአት ወለደችኝ” እንዲል ያነሣሣው በሌላ የማይገኝ በራሱ ወላጆች ዘንድ ብቻ የነበረ ኀጢአተኛነት ቢኖር ነው በማለት ሰው ኀጢአተኛ ባሕርይን ወርሶ የሚወለድበትን ሁኔታ ለመካድ ይሞክራል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፈ ኢዮብ 15፥14 ከሴት (ከሔዋን) የተወለደ ሁሉ በራሱ ጻድቅ ይሆን ዘንድ የሚችልበት መንገድ እንደሌለ ተናገረ፡፡ ቀደም ሲልም ኢዮብ 14፥4 ሰው ያለኀጢአት ሆኖ የማይወለድበትን ምክንያት ሲያስረዳ ከርኩስ ነገር የርኩስ ነገር መውጣት ሕጋዊነት እንዳለውና ነገር ግን ከርኩስ ንጹሕ እንዲገኝ ማድረግ እንደማይቻል ካወሳ በኋላ፥ ኢዮብ የራሱም ሁኔታ ከዚህ ሊለይ እንደማይችል በማስተማመን ኀጢአተኛ ባሕርይን ወርሶ በተወለደና በወረሰው ኀጢአተኛነት ግፊት ምክንያት ኀጢአትን በሚሠራ ሰው ላይ እንዴት ትፈርዳለህ? በማለት እግዚአብሔርን ተከራከረ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በምሕረቱ ውስጥ እንዲጠለል ካላደረገ በቀር ሰው በኀጢአቱ ፍርድ እንዳለበት ቢያውቅ እንኳ በወረሰው ኀጢአተኛ ባሕርይ እየተነዳ ኀጢአትን ከመሥራት ራሱን እየተቈጣጠረ ራሱን በራሱ ማንጻት እንደማይሆንለት ከክርክሩ የሚነሣው ትችት ግራ ቀኙን ያስተማምናል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስም ሰው በራሱ ሥራ እንደማይጸድቅ አስገንዝቦ በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት ያለ ሕግ ሥራ የሆነ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንደሚያሻውና ያም በጊዜው በወንጌል መገለጡን ያበሥራል (ሮሜ 3፥21-31)፡፡

በኀጢአት ውስጥ ከወደቁት፥ በዚህም ምክንያት ንጽሐ ጠባያቸው ካደፈባቸው የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች የተወለዱት ሰዎች ሁሉ ኀጢአትን ማፍራታቸው በባሕርዩ የአሜከላ ዝርያ የሆነው ዛፍ የአሜከላን ፍሬ ከማፍራቱ ጋር የተመሳሰለ፥ በመወለድ የሚወረስ ጠባይዓዊ ግዴታ እንደ ሆነ የሚያስረዱትን ጥቅሶች (ማቴ. 7፥16-18፤ 12፥33-35፤ ሉቃ. 6፥43-45፤ ዮሐ. 8፥44፤ ሮሜ 5፥12፤ 7፥14-20) ይህ ቡድን አድበስብሷቸው ያልፋል፡፡

ከዚህም በቀር ይህ ቡድን ሰው ከውሃና ከመንፈስ በመወለድ ከሥጋ ወላጆቹ ሥጋ ሆኖ የተወለደበትን ሥርዐት እንዲሻር ካላስደረገና በዐዲስ ልደት ዐዲስ ፍጥረት ካልሆነ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም የተባለበትን ምስጢራዊና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት በመንፈሳዊ ትርጉሙ አልተረዳውም፡፡ የቡድኑ አባላት በትውፊት ሥነ ሥርዐቶቹን በመቀበላቸው ምክንያት ብቻ በሥነ ሥርዐቶቹ ውስጥ ያልፋሉ እንጂ መለኮታዊው ኀይልና ሥርዐቱ የተመሠረተበት የእግዚአብሔር ቃል በሚሰጡት የመለወጥ ሂደት አይተማመኑበት፤ አይጠቀሙበትምም፡፡ ይህም ማለት በልማድ የሥርዐቱ ወግ አድራሾች ቢሆኑም በሕይወታቸው ከዐዲስ የተፈጥሮ ባሕርይ ሙላት ውስጥ ጭላጭ እንኳ የለባቸውም፤ አይታይባቸውም፡፡

በጣሙን የሚያስደንቅ ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ የተቀበሉት የኒቅያ የእምነት መግለጫ (ጸሎተ ሃይማኖት) “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኀጢአት - ለኀጢአት ስርየት በምትደረግ በአንዲት ጥምቀት እምናለን” ይላል፡፡ የቡድኑ አባላት ይህንኑ መመሪያ ተከትለው የ40ና የ80 ቀን ሕፃናትን እንዲያውም ከታመሙ ከእርሱ ባነሰ ዕድሜ የሚገኙትን በማጥመቅ የኀጢአትን ስርየት ያውጃሉ፡፡ ሕፃናት ኀጢአትን ከወላጆቻቸው ወርሰው ያልተወለዱ ከሆነ ኀጢአትን ለማስተስረያ ያስፈልጋል በተባለ ጥምቀት በድርጊት ኀጢአትን ከመሥራታቸው በፊት ለምን ያጠምቋቸዋል? የቀድሞ አባቶች የውርስ ኀጢአትን ያምኑ እንደ ነበረ ሲታወቅ፥ ይህ ቡድን በአበው ሃይማኖት ድንጋጌም ሆነ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዳልቆመ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ቡድን የነገረ ሃይማኖትን ምስጢራዊ ቤት ሳይገባበት በውጪ ሆኖ፥ በውስጥ ያሉትን የማያያቸውን ዕቃዎች ለመቍጠር የሚሞክር ሰውን ይመስላል፡፡

ሁለተኛው ቡድን፡- ከሰዎች መካከል ድንግል ማርያም ብቻ ከአዳምና ከሔዋን የተላለፈውን ኀጢአተኛ ባሕርይ ሳትወርስ እንደ ተወለደች አድርጎ ይሰብካል፡፡ በፈጠራ ከሚነገሩ ተረቶችና አንዱን ከሌላው በማምታታት ከሚደረግ ገለጻ  በቀር ከእግዚአብሔር ቃል አንድም ድጋፍ ወይም መሠረት ያላገኘ ትምህርት ነው፡፡ ከአዳምና ከሔዋን ወደ ልጆቻቸውና ዝርያዎቻቸው ሲተላለፍ የኖረው ኀጢአተኛ ባሕርይ የትኛው ትውልድ ወይም ቤተ ሰብ ላይ ታገደ? ለሚለው ጥያቄ ይህ ቡድን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ምላሽ መስጠት አይችልም፡፡

ጌታ መንፈስ ቅዱስ በማርያም ወላጆች ወይም አያቶች ላይ መውረድና ልክ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ መፀነስ ጊዜ ያደረገውን ዐይነት የማንጻትና የመቀደስ መለኮታዊና ተኣምራዊ ሥራ ሲያከናውን የታየበት ታሪክ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በግልጽ ተጽፎ መገኘት የነበረበት ሁኔታ አስፈላጊነት ለዚህ ቡድን አባላት አይገባቸውም፡፡ እንኳ በተመርሆ ልቡናና በተኀሥሦ መለኮታዊ ቃል (እንዴት? ለምን? በምን? የት? መቼ? … በሚሉ መጠይቆች ልብን በማነሣሣትና ለመጠይቆቹ መልሱን ከእግዚአብሔር መንፈስና ከቃል ለማግኘት ምርምር በማካሄድ) ወደዚህ ደረጃ በራሳቸው ለመድረስ ፍላጎት ሊኖራቸው ይቅርና ተጠቍመውና ተነግረውም ቢሆን ሊረዱ አለመቻላቸው እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡

ከጥንቱ ከጧቱ ወንጌል በሀገራችን በተሰበከበትና ክርስትና በገባበት ጊዜ ሰዎች በመወለድ በሚወርሱት ኀጢአተኛ ባሕርይ ምክንያት በኀጢአት ውስጥ የወደቁትን አዳምና ሔዋንን መስለው እንደሚወለዱ ትምህርት ሳይሰጥበት እንዳልቀረ እሙን ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት አባቶቻችን ከድንግል ማርያም ሥጋንና ነፍስን በመንሣት አምላክ ሰው የሆነው፥ በመወለድ የሚተላለፈው የውርስ ኀጢአት ወደ እርሱ እንዳይደርስ በማገድ እንደ ሆነ ሲገልጹ “ሥጋዋን አንጽቶና ነፍሷን ቀድሶ በእርሷ አደረ፤ አንጺሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ” በማለት መስከረዋል፡፡ ይህም ትውፊታዊ  የሆነ ትምህርተ ነገረ መለኮት በ6ኛው ምእት ዓመት ውስጥ በተነሣው በዝነኛው ማሕሌታይ ያሬድ የዜማ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ስለ ሆነም የዚህም ቡድን ባህለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ቃልም በጥንታዊ ትውፊታዊ ቴዎሎጂያችንም ያልተደገፈ ልብ ወለድ ነውና የሚጣል ነው፡፡

እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ “ከኀጢአት በቀር እንደኛ ሰው ሆኖ በነቢያት ትንቢት መሠረት በቤተ ልሔም ተወለደ፥ ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኀጢአት በሕቲታ ወተወልደ በቤተ ልሔም በከመ ሰበኩ ነቢያት” ሲባል እኛ የሰው ልጆች ሁሉ ከወላጆቻችን ኀጢአተኛ ባሕርይን ጭምር በመውረስ የምንወለድ ሆኖ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከእኛ ሁሉ በመለየት ኀጢአትን ሳይወርስ፥ ሰው ለመባል የሚያበቃውን ሌላውን ሁሉ ግን ከእናቱ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር በመንሣት መወለዱን የእኛው አባቶች ሲያበሥሩ እንደ ነበረ የታወቀና የማያከራክር ነው፡፡ (ማቴ. 1፥20)፡፡


ይቀጥላል

በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment