Thursday, November 14, 2013

መሠረተ እምነት


ከነቅዐ ጥበብ
ባለፈው ዕትም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት በቀረበው ጽሑፍ፦ አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት፣ ቃል ሥጋ የመሆኑን አስፈላጊነት፣ የክርስቶስ አዳኝነትና መካከለኛነት ተያያዥ መሆናቸውን በማብራራት፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተባበል በዚህ ዘመን የሚነዙ የስሕተት ትምህርቶችን ለመጠቈም ተሞክሯል፡፡ በዚሁ መሠረት ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም የሚለውንና ሮሜ 8፥34 ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት የሚያስተምረውን በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ዕትም ደግሞ ተከታዩ ክፍል ይቀርባል፡፡

ኢየሱስ አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ?
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመድረስ ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመር የግድ ነው፡፡ "ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ መጠጋት" እንደሚባለው ብሂል፥ የራስን አመለካከት ወይም ሌላ ምድራዊ ተመክሮን ይዞ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መጠጋት፥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ሳይሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለራስ ሐሳብ ደጋፊ አድርጎ ለማቅረብ ያለመ አካሄድ ነው፡፡


በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ኢየሱስ መካከለኛነት በብዙ ስፍራ የተጻፈውን እውነት እንዳለ ለመቀበል የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡ የሚቸገሩበት ዋና ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ለራሳቸው አስተምህሮ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው፡፡ ቃሉን እንዳለ ከመቀበልና የእግዚአብሔርን ሐሳብ ከማገልገል ይልቅ ከራሳቸው አስተምህሮ ጋር ለማስማማት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን እውነት በርዘውና ከልሰው ለእነርሱ የሚስማማ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ እንግዳ አስተምህሮን ያስተዋውቃሉ፡፡ በዚህ ሥራ ማስደሰት የሚቻለው ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን ነው?          

በዚህ ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተባበል ከሚሠነዘሩት አስተያየቶች መካከል ምድራዊውን ተመክሮ አብነት በማድረግ፥ ስለ ኢየሱስ ጠበቃነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ለማስተባበል የሚሞከርበት አቀራረብ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጕዳይ ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡት ወገኖች፥ ኢየሱስን ጠበቃ ማድረግ የእርሱን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ እርሱ ዛሬ ዳኛ እንጂ ጠበቃ ሊሆን አይችልም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ከሚያቀርቧቸው የመከራከሪያ ሐሳቦች መካከል አንዱ፥ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ መቀመጡን የተመለከተ ነው፡፡ ‘በአብ ቀኝ መቀመጡ የሚያሳየው ዳኛነቱን ነው፡፡ በምድር ላይ በፍርድ ቤት ቋንቋ ዳኛ ተሠየመ ወይም ተቀመጠ ሲባል፥ ጠበቃ ደግሞ ቆመ ይባላል፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ ተቀመጠ እንጂ ቆመ ተብሎ አልተነገረለትም፡፡ እስጢፋኖስ በተወገረ ጊዜ ግን ለጥብቅና ሳይሆን፥ በአገልጋዩ መወገር ተቈጥቶ ነው የቆመው’ ይላሉ፡፡ መቆም ማለት ማማለድ ማለት ስለ ሆነ፥ የሚቆሙ መላእክትና ቅዱሳን ናቸው ሲሉም የመካከለኛነቱን ስፍራ ለእነርሱ ይሰጣሉ፡፡

1ዮሐ. 2፥1-2 ስለ ማን ይናገራል?
በቅድሚያ ኢየሱስ ጠበቃችን መሆኑን የሚናገረውን ክፍል እንመልከት፡፡ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፡፡ ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" (1ዮሐ. 2፥1-2)፡፡

ይህን ጥቅስ ለማስተባበል ከቀድሞ ጀምሮ ተከፍቶ የነበረው ዋና ዘመቻ ጥቅሱ በትክክል አልተተረጐመም፤ ወይም ተዛብቶ ነው የተተረጐመው የሚል ነበር፡፡ በተለይም ጥቅሱን ከግእዙ ዐዲስ ኪዳን ወደ ዐማርኛ ለመተርጐም የሞከሩ ክፍሎች፥ ከግሪኩ የተተረጐመውን የ1953 ዓ.ም. ዕትም መጽሐፍ ቅዱስን ቃል የተዛባ ትርጕም አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ እነርሱ በግእዙ መሠረት ሰጠን ያሉት ትርጕም ግን የግእዙን ንባብ ያልጠበቀና ለራስ አመለካከት ደጋፊ በሆነ መንገድ የቀረበ ሆኖ ይታያል፡፡

የግእዙ ንባብ፥ "ደቂቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢተአብሱ ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ ውእቱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ ወአኮ በእንቲኣነ ባሕቲቱ አላ በእንተ ዓለምኒ፡፡" ለዚህ ንባብ የተሰጠው ትርጕም እንዲህ የሚል ነው፤ "ልጆቼ ሆይ እንዳትበድሉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኀጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡ ስለ እኛ ብቻ አይደለም፤ ስለ ዓለምም ሁሉ እንጂ" (1ዮሐ. 2፥1-2 የ2 ሺህ ዓ.ም. ዕትም)፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ደግሞ "ግሪኩ ‘ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ እርሱም ጻድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው’" ይላል፡፡

በዚህ ትርጕም ላይ ሁለት ዐይነት ስሕተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የመጀመሪያው የግእዙን የንባብ ሐሳብና የቃላቱን ሰዋስዋዊ አገባብ ጠብቆ አለመተርጐም ወይም ሌላ ትርጕም መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን ቃል ሳይተረጕሙ በማለፍና እንዳለ በማስቀመጥ አንባቢው ክፍሉ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተነገረ ቈጥሮ እንዲቀበለው ማድረግ ነው፡፡

የቃላቱን ሰዋስዋዊ አገባብ በተመለከተ የተፈጸመውን ስሕተት እንመልከት፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውም መቀጸል የነበረበት ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተርጓሚዎቹ ግን ለእርሱ በመቀጸል ፈንታ ስለ ጰራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) እንደ ተነገረ አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ ይህም ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን የሚለው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተነገረና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተደርጎ እንዲታሰብ ሆኗል፡፡ የግእዙ ንባብ "ወኢየሱስ ክርስቶስ" ሳይልም ተርጓሚዎቹ "ኢየሱስ ክርስቶስም" በማለት የ"ወ" ትርጕም ሊሆን የሚችለውን "ም"ን አክለውበታል፡፡ ይህም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የሚናገረውን ዐረፍተ ነገር ከሁለት ከፍሎ ስለ ጰራቅሊጦስም እንደ ተነገረ አድርጎ ለማቅረብ ተፈልጎ ነው፡፡ እንዲህ የሆነውም በዋናነት "ጠበቃ" የሚለውን ቃል ደብዛውን ለማጥፋት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡

"ጰራቅሊጦስ" የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን፥ የሚከተሉት ትርጕሞች አሉት፡፡ በኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ላይ (1948፣ 907) በመጀመሪያ ትርጕሙ፥ "አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ካፉ ማር ጠብ የሚል" ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ፍቺው ደግሞ፥ "ናዛዚ መጽንኢ፤ መስተፍሥሒ፤ መንፈስ ቅዱስ፡፡ በዓለ ኀምሳ፤ የትንሣኤ ዐምሳኛ፣ የዕርገት ዐሥረኛ፤ እሑድ ቀን የሚውል" የሚል ትርጕም ይሰጣል፡፡ ሊቁ፥ "ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ" የሚለውን ጥቅስ አስረጂ አድርገው ያቀረቡት፥ "አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ …" በሚለው በመጀመሪያው ትርጕም ሥር ነው፡፡ ይህም "ጰራቅሊጦስ" የሚለው ቃል በ1ዮሐ. 2፥1-2 ውስጥ የተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት ሳይሆን የኢየሱስን መካከለኛነት ለማሳየት እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለግእዙ ንባብ በተሰጠው ትርጕም ላይ የተፈጸመው ሁለተኛው ስሕተት፥ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን የግሪክ ቃል ሳይተረጕሙ እንዳለ የማስቀመጡ ጕዳይ ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲህ ማድረግ ግን ለምን አስፈለገ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የግእዙ ዐዲስ ኪዳን በዚህ ጥቅስ ውስጥ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን ቃል ወደ ግእዝ ሳይተረጕመው እንዳለ ነው ያስቀመጠው፡፡ ቃሉ በዐማርኛ ውስጥ አቻ ስላለው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ "ጠበቃ" ብሎ ተርጕሞታል፡፡ የ2 ሺሁ ዓ.ም. ዕትምም በተመሳሳይ ሁኔታ ሳይተረጕመው እንዳለ "ጰራቅሊጦስ" ብሎ ነው ያስቀመጠው፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይም እንዲሁ አልተረጐመውም፡፡ ለምን?

ግእዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮ የሚፈጸምበት ዋና ቋንቋ መሆኑ ቢታወቅም፥ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፥ በተለይም ለዐማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት ባይሆንም፥ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን ለመሰወርም አንዳንዶች ሲገለገሉበት ይታያል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን የግሪክ ቃል ሳይተረጕሙ እንዳለ ማስቀመጥ የተፈለገው አቻ ቃል ስለ ጠፋለት አይደለም፡፡ ወይም "ጰራቅሊጦስ" የሚለው ቃል ለዐማርኛ አንባብያን ሐሳቡን ይበልጥ የሚገልጥ ሆኖ ስለ ተገኘም አይደለም፡፡ ነገር ግን "ጠበቃ" ተብሎ ቢተረጐም፥ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ ለፍጡራን የተሰጠውን የመካከለኛነት ስፍራ ለባለቤቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተመላሽ የሚያደርግ በመሆኑ፥ ምስጢሩን ለመሰወር ነው ከማለት በቀር ሌላ ፍቺ አይሰጠውም፡፡

እንዲህ ማድረግ ዐዲስ ነገር አለመሆኑን በሌላ ማስረጃ እናስረዳ፡፡ ሃይማኖተ አበው በተሰኘው መጽሐፍ ላይ በግእዙ ንባብ ውስጥ "ሊቀ ካህናት" የሚለው ማዕርግ ለኢየሱስ ክርስቶስ በተቀጸለባቸው ክፍሎች፥ በዐማርኛው ንባብ ላይ "አስታራቂ" ተብሎ ተተርጕሟል፡፡ ለምሳሌ፦ በገጽ 222 ቊጥር 14 ላይ ያለውን መመልከት ይቻላል፡፡ እንዲህ ይላል፤ "መኑ ውእቱ ሊቀ ካህናት ምእመን ዘእንበሌሁ፤ - ከእርሱ በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ ማነው?" በዚሁ ገጽ ቊጥር 15 ላይ ግን ግእዙ "… ወኢያንሥኣ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢእምኀይላት እለ እሙንቱ ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ" የሚለውን ግን በዐማርኛው ላይ ሳይተረጕሙት "… ዙፋኑን ከበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም" ብለው እንዳለ ነው ያስቀመጡት፡፡ ለምን ሳይተረጕሙት ቀሩ? ቢባል፥ "መላእክትን አስታራቂ አድርጎ አልሾመልንም" እንዳይልባቸው ነው እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ስለዚህ እውነቱን በግእዝ ሸፈኑት ማለት ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ግእዝ እውነትን ለመሰወር አላገለገለምን? እንዴታ!!

እስካሁን የተመለከትናቸው ማስረጃዎች፥ 1ዮሐ. 2፥1-2 የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ጠበቃነት እንጂ ጰራቅሊጦስ ስለ ተባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ያስረዳሉ ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ በላይ ግን የጥቅሱን ዐውዳዊ ፍቺ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስ መልእክት ምዕራፍ 2 የሚጀምረው፥ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፤ ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" በማለት ነው፡፡

ዮሐንስ በዚህ ክፍል ክርስቲያኖች ኀጢአትን ማድረግ እንደሌለባቸው ይናገራል፡፡ ምክንያቱም በዚሁ መልእክት (3፥4-10) ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ የእርሱ ዘር በውስጡ ስላለ ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም፡፡ ደግሞም በክርስቶስ የማዳን ሥራ አምኜ በእርሱ እኖራለሁ የሚል ማንም ቢኖር ኀጢአትን አያደርግም፡፡ በእርሱ እኖራለሁ እያለ ኀጢአትን የሚያደርግ እርሱ ግን ራሱን በከንቱ እየሸነገለ ነው እንጂ ጌታን አላየውም፤ አላወቀውምም፡፡ ለምን ቢባል በጌታ ዘንድ ኀጢአት የለም፡፡ እርሱ በሥጋ የተገለጠውም ኀጢአትን ለማስወገድ ነው እንጂ በኀጢአት እንድንኖር አይደለም፡፡ እንዲያውም የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች የሚለዩት፥ ጽድቅን በማድረግና ባለማድረግ፥ ወይም ኀጢአትን በመሥራትና ባለ መሥራት ነው፡፡

ይህ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባው የጽድቅ ሕይወት ልኩ የት ድረስ እንደ ሆነ ያሳያል፡፡ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ" ሲል በማስጠንቀቅ የጀመረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቲያኖች እንዲህ ሊኖሩ የተጠሩ ቅዱሳን ቢሆኑም፥ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ካመኑበት ቅጽበት ጀምሮ ኀጢአተኛው ባሕርይ ከውስጣቸው በእምነት ተገድሏል እንጂ ከውስጣቸው ተመጥጦ ገና አልተወገደና ኀጢአትን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይኸው ሐዋርያ "ኀጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም" (1ዮሐ.1፥8) ያለውም ስለዚህ ነው፡፡

ክርስቲያኖች ኀጢአት ሠርተው ቢገኙስ? ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? በፍጹም!! ተስፋ አላቸው እንጂ፡፡ ምክንያቱም፥ "ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" ተብሏል፡፡ ከዚህ የምንገነዘበው፥ ኀጢአትን አድርገን ብንገኝ በአብ ዘንድ የሚገኝ የኀጢአታችን ማስተስረያ የሆነው ጠበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላለን እርሱ ነጻ እንደሚያደርገን ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ አንድ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግልና የተወሰኑ ወይም ጥቂቶች ኀጢአቶችን ብቻ የሚያስተሰርይ አይደለም፤ አንድ ጊዜ የቀረበ ፍጹም፣ ሕያውና ዘላለማዊ መሥዋዕት በመሆኑ የክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስ የማዳን ሥራ አምነው፥ አሁንና ወደ ፊት የሚመጡትን ሰዎች ኀጢአት ሁሉ ለማስተስረይ በቂና ችሎታ ያለው መሥዋዕት ነው፡፡ ስለዚህ መበደል የለብንም እንጂ ብንበድል በዚሁ መሥዋዕት እንታረቃለን ማለት ነው፡፡    

የኢየሱስ ጠበቃነት በምድራዊ ጥብቅና ይመዘናልን?
በመነሻችን ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመር ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ያደርሳል ብለናል፡፡ ሌላ ምድራዊ ተመክሮን መነሻ አድርገን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሞከር ግን፥ ይዘን ወደ ተነሣነውና ወደምንፈልገው ነገር እንጂ እግዚአብሔር በቃሉ ወደ ገለጠው እውነት አንደርስም፡፡ ኢየሱስ ጠበቃ መሆኑን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚቃወሙ ሰዎች ችግርም ይኸው ሆኖ ይታያል፡፡

ኢየሱስ ፈራጅ እንጂ ጠበቃ ሊሆን አይችልም የሚለውን አመለካከት የሚያቀነቅኑት ክፍሎች ጥቅሱን ለመቃወም መነሻ የሚያደርጉት ምድራዊውን ተመክሮ ነው፡፡ "ጠበቃ፥ ባለጕዳይን ወክሎ በፍርድ ቤት የሚከራከር፣ የሚሟገት፣ ነገረ ፈጅ" መሆኑ ይታወቃል (የዐማርኛ መዝገበ ቃላት 1993፣ 546)፡፡ ጠበቃ፥ የወከለውን ባለጕዳይ ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ወይም ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሕግ አናቅጽን ጠቅሶ የሚከራከር ባለሙያ ነው፡፡ ሲከራከርም ደንበኛዬ ጥፋት የለበትም ወይም ጥቅሙ ተነክቷል የሚልና በተቃራኒው የቆመውን ወገን ጥፋተኛ የሚያደርግ መሠረት ይዞ ነው፡፡ አንዳንዱ ጠበቃ ደንበኛው ጥፋተኛ ቢሆንም እንኳ ሊረታ የሚችልበት ዕድል ካለው ጥፋተኛ አይደለም ሲል ሊከራከር ይችል ይሆናል፡፡ ትክክለኛ ያለሆነውን ጕዳይ በሚያቀርባቸው መከራከሪያዎችና በሚጠቅሳቸው የሕግ አናቅጽ በችሎት ፊት ቀርቦ ማስረዳት፣ ማሳመንና መርታት ከቻለም ደንበኛውን ነጻ ሊያደርግ፥ ጥቅሙንም ሊያስጠብቅለት ይችላል፡፡

"ኢየሱስ ጠበቃ ነው" የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት፥ ከዚህ ምድራዊ የጥብቅና ሙያ ጋር ካነጻጸርነው በርግጥም ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ የኢየሱስን ጠበቃነት ለመረዳት መነሣት ያለብን ከምድራዊ የጥብቅና ተመክሮ ሳይሆን ቃሉን ከተናገረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ጠበቃ ነው ሲል እንደ ምድራዊ ጠበቃ በአብ ፊት ቆሞ እያንዳንዱን ኀጢአተኛ (ያለማንነቱ) ንጹሕ ነው እያለ ይከራከርለታል፤ ያስምረዋል፤ ከተጠያቂነትም ነጻ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለ ኀጢአተኞች አንድ ጊዜ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት በእርሱ በኩል አምነው የሚቀርቡት ሁሉ በየዕለቱ ይታረቁበታል፤ ስርየትን ያገኙበታል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው በምዕራፍ 1፥7 ላይ፥ "የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል" ብሏል፡፡ በተጨማሪም፥ "እርሱም (ኢየሱስ ክርስቶስ) የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" በማለት፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለኀጢአት ሁሉ በቂ የሆነ መሥዋዕት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት የሚያመለክት ነው፡፡

ሌላው ከምድራዊ ተመክሮ ጋር የተያያዘው የእነዚሁ ወገኖች የመከራከሪያ ነጥብ፥ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ፥ ጠበቃ ሳይሆን ፈራጅ (ዳኛ) እንደ ሆነ ተጽፏልና፥ እርሱ በአንድ ጊዜ ጠበቃም ዳኛም እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ አሁንም ይህ ምድራዊ ተመክሮን መነሻ ያደረገ የእነርሱው አመለካከት እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ነገሩን በዚህ መልክ አላቀረበልንም፡፡ ለዚህ መከራከሪያ በጮራ ቊጥር 39 በገጽ 6 ላይ "ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም" በሚለው ነጥብ ሥር ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ በዚያ መሠረት፥ ኢየሱስ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ለኀጢአተኛውና በእርሱ የማዳን ሥራ አምኖ ለሚመጣ ሁሉ፥ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት መካከለኛው ወይም አዳኙ ነው እንጂ በማንም ላይ አይፈርድም፡፡ የማያምን ቢኖርና ባለማመኑ ቢጸና ግን ከአሁን ጀምሮ ባላመነበት ጊዜ ሁሉ ከፍርድ በታች ነው (ዮሐ. 3፥18)፡፡ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ ፈራጅ ሆኖ ነው የሚገለጠው፡፡ ስለ ሆነም በዚህ መንገድ ኢየሱስ ጠበቃ ነው ቢባል፥ የመካከለኛነቱን ግብር በትክክል ይገልጻል እንጂ የእርሱን ክብር ዝቅ የሚያደርግበት አንድም ምክንያት የለም፡፡

ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ መካከለኛነቱን አስቀርቶታልን?
ብዙዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ እስከ ተሰቀለበት ጊዜ ድረስ መጸለዩንና መማለዱን በአጠቃላይም የመካከለኛነት ሥራውን መፈጸሙን አይክዱም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በግልጽ ያስረዳልና (ኢሳ. 53፥12፤ ማቴ. 11፥25፤ 14፥23፤ 26፥36-44፤ ማር. 1፥35፤ 6፥46፤ ሉቃ. 22፥31-32፤ 23፥34፤ ዮሐ. 17፥9-26፤ ዕብ 5፥7-10)፡፡ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ የእነዚህን ጥቅሶች ግልጽ መልእክት በትርጕሜ እያጠየሙ ደብዛዛ ያደርጉታል፡፡ ጌታችን በፈቃዱ ያደረገውንና ያላፈረበትን፥ ነቢያትና ሐዋርያትም ተቀብለው ሳይቀላቅሉና ሳይሸቃቅጡ ለእኛ ያስተላለፉትን የመካከለኛነቱን ሥራ ለማመን የምንቸገረው ከቶ ለምን ይሆን?

ጌታ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ በክብር ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፡፡ በዚያ የተቀመጠው በክብር እንጂ በዚህ ምድር እንደ ነበረው ዝቅ ብሎ አይደለም፡፡ ቢሆንም ዛሬም ፍጹም አምላክ፥ ፍጹም ሰው ነው፡፡ በዚያ የሚገኘውም አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራው አምነው በእርሱ በኩል ለሚመጡት የመዳናቸው ምክንያት ሆኖ ነው፡፡ ይህን ሲያስረዳ የዕብራውያኑ ጸሓፊ እንዲህ ብሏል፤ "እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት … ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው" (ዕብ. 5፥7-10)፡፡

ዛሬ ሰዎች በስሙ ወይም በእርሱ በኩል ሲጸልዩ፥ እርሱ በአብ ፊት ስለ እነርሱ አይጸልይ አይማልድ እንጂ፥ በቀደመው ልመናውና ምልጃው ምሕረትን እንዲቀበሉ ምክንያቱ እርሱው ብቻ ነው፡፡ ጌታ በሊቀ ካህናትነቱ አንድ ጊዜ ያቀረበው ልመና ለዘላለም የሚያገለግልና በስሙ አምነው በእርሱ በኩል የሚመጡትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሕያው ልመና ነውና፡፡ ጌታ ሲጸልይ፥ የሚለምነው በጊዜው በአጠገቡ ስለ ነበሩት ስለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ እንዳልሆነና የእነርሱን ስብከት ሰምተው በክርስቶስ አዳኝነት ስለሚያምኑና እስከ ኅልፈተ ዓለም ስለሚነሡ ምእመናን ጭምር እንደ ሆነ ገልጧል (ዮሐ. 17፥20-21)፡፡ ኢየሱስ ዛሬም መካከለኛ ነው ሲባል አንድ ጊዜ ያቀረበው ይህ ጸሎቱና መሥዋዕቱ ለሁል ጊዜም ያገለግላል ማለት ነው እንጂ እርሱ በክብር ከሚገኝበት የአብ ቀኝ፥ በዚህ ምድር ወደ ነበረበት ሁኔታው ዝቅ ይላል ማለት እንዳይደለ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡

እውነቱ ይህ ነው፡፡ ብዙዎቹ ስለ ኢየሱስ መካከለኛነት የሚናገሩት ጥቅሶች ኢየሱስን መካከለኛ ነው የሚሉት እስከ መስቀል ሞት ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ኢየሱስ በክብር ወደ ሰማይ ካረገና በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላም ባለው ጊዜ ሁሉ መካከለኛ እንደ ሆነ ይናገራሉ እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር በኀላፊ አንቀጽ (Past Tense) "ነበረ" ብለው ሳይሆን፥ በአሁንና ቀጣይነትን በሚያመለክቱ አናቅጽ (Present and Future Tenses)፦
"ስለ እኛ የሚማልደው" (ሮሜ 8፥34)፣
"ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል" (ዕብ. 7፥25)
"በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው (የነበረው አላለም) መካከለኛው አንድ ነው" (1ጢሞ. 2፥5)፣
"ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን (ነበረን አላለም)" (1ዮሐ. 2፥1-2) እያሉ ነው የሚናገሩት፡፡
   
በተለይም በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ተደጋግሞ እንደ ተገለጸው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው፣ በእጅ ወዳልተሠራችውና በእግዚአብሔር ወደ ተተከለችው መቅደስ የገባውም አንድ ጊዜ ባቀረባቸው ምልጃና መሥዋዕት ስለ እኛ ሊቀ ካህናት ሆኖ በእውነተኛዪቱ መቅደስ ለማገልገል ነው (ዕብ. 6፥17-20፤ 7፥27-28፤ 8፥1-2፤ 9፥10-11፡24 10፥12-14፡19-20)፡፡ ያንቀላፉና በሕይወተ ሥጋ ያሉ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሔር የቀረቡትና የሚቀርቡት፥ በአንድ አካል የተያያዙትም በእርሱ መካከለኛነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ቀኝ መቀመጡ በክብሩ ሆኖ የሚያከናውነውን የመካከለኛነቱን ሥራ አላስቀረውም፡፡ ይህ አገልግሎት የእርሱው ብቻ እንጂ ላንቀላፉ ቅዱሳን ተላልፎ የተሰጠ አይደለም፤ አሁን ባለበት ሁኔታም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ተብሏልና (1ጢሞ. 2፥5፤ ዕብ. 9፥15፤ 12፥24)፡፡

ቅዱሳን መካከለኞች አይደሉምን?   
"ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች" (ያዕ. 5፥16) በተባለው መሠረት፥ ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ ስለ ሌሎች ይጸልዩ ነበር፡፡ ካንቀላፉ በኋላ ግን ስለዚህ ጕዳይ በግልጽ የተጻፈ ነገር የለም፤ ቢያንቀላፉም ሕያዋን ናቸውና ሊጸልዩ ይችላሉ ቢባል እንኳ፥ በምድር ላይ ከሚገኙ ሕያዋን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌላቸው ሕያዋኑ ለእነርሱ የ"ጸልዩልኝ" ርእሰ ጸሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ለክርስቶስ ጥላና ምሳሌ ስለ ነበሩት የብሉይ ኪዳን መካከለኞች የተጻፈውም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

የእነርሱ አገልግሎት በሞት የተገደበና ካንቀላፉ በኋላ የማይቀጥል ነበር፡፡ መካከለኞቹ ብዙዎች የሆኑበት ዋናው ምክንያትም አንዱ ሲሞት በሌላው ይተካ ስለ ነበረ ነው፡፡ "እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው" (ዕብ . 7፥23) የሚለውም ቃል ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን ምንም እንኳ መካከለኞች ተብለው ባይጠሩም፥ ስለ ሌሎች በሚጸልዩት ጸሎትና በሚያቀርቡት ምልጃ ከዚህ የተለየ ማንነት እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡ ጸሎትና ምልጃቸውም ቅድመ እግዚአብሔር የሚያርገው የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል" (ዮሐ. 16፥23) በማለት በእርሱ በኩል እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የክርስቶስን የመካከለኛነት ስፍራ ለቅዱሳን ለመስጠት የሚፈልጉ ክፍሎች፥ ይህን ሐሳባቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ ማስረጃ ይሆነናል ብለው ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ፥ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን" (2ቆሮ. 5፥20) የሚለው ጥቅስ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ስላንቀላፉ ቅዱሳን አማላጅነት ይናገራል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እንደ ማስረጃ የተወሰደው ጥቅሱ ይህን ሐሳብ ስለሚደግፍ አይደለም፤ ነገር ግን "እንደሚማልድ" በሚለው ቃል ውስጥ፥ "ል" ከሌሎቹ ፊደላት ደመቅ ብላ ስለ ተጻፈች፥ በመጀመሪያ "ለ" የነበረውን ደልዘው "ል" አድርገዉት ነው በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ "ለ" ቢሆን ኖሮ ጥቅሱ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" የሚል ፍቺ ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም እግዚአብሔር በቅዱሳን እንደሚለመን ያሳያል፡፡ "ለ" ወደ "ል" ስትለወጥ ግን የቅዱሳንን ማማለድ ያስቀራል የሚል ነው ክርክሩ፡፡

በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ባያከራክርም፥ ከጽሑፍ ሥራው አንጻር በዝግጅትና በኅትመት ሂደት ውስጥ ጥቃቅን የፊደል ስሕተት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ አንዳንዱ ስሕተት በዐረፍተ ነገሩ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ የማያመጣ ሲሆን፥ አንዳንዱ ግን የትርጕም ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፥ በ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢዮ. 33፥14 ላይ "እግዚአብሔር" ማለት የነበረበትን "አግዚአብሔር" ይላል፡፡ ይህ የፊደል ስሕተት ነው፤ መታረም አለበት፡፡ ሆኖም ስሕተቱ የትርጕም ለውጥ አያስከትልም፡፡ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" የሚለው የ2ቆሮ. 5፥20 የፊድል ስሕተት ግን የትርጕም ለውጥ እንደሚያስከትል ከዐውደ ምንባቡ መረዳት ይቻላል፡፡

"… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" ቢባል ስሕተቱ ከምን ላይ ነው? ስሕተቱን ለመረዳት በቅድሚያ ዐውዱ ስለ ምን እንደሚናገር መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከቊጥር 18 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ እንደ ነበረና በሐዋርያቱ ውስጥም የማስታረቅን ቃል እንዳኖረ ይናገራል፡፡ በዚሁ የማስታረቅ ቃል አማካይነት ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የሚገባቸውን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው እንደሚለምኗቸው በክፍሉ ውስጥ እናነባለን፡፡

እግዚአብሔር አስቀድሞ በክርስቶስ አማካይነት ዓለሙን ከራሱ ጋር እንዳስታረቀና በእርሱ የተከናወነውን ዕርቅ ያልሰሙና ያልተቀበሉ ሰዎችን ደግሞ የማስታረቁን ቃል በውስጣቸው ባስቀመጠው አገልጋዮች በኩል ዛሬም እየጠራቸው እንደ ሆነ ነው የምንረዳው፡፡ "ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን" ከሚለው አነጋገርም የምናስተውለው፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር መለመናቸውን ሳይሆን፥ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚፈጽሙት ዕርቅ መጋበዛቸውን ነው፡፡ የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም "ከእግዚአብሔር ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኋለን" ነው የሚለው፡፡ የክፍሉ መልእክት ይህ ሲሆን፥ "እንደሚማልድ" የሚለው ቃል "እንደሚማለድ" በሚለው ቢተካ ግን ትርጕም ያጣል፤ ምክንያቱም በዚህ ክፍል የጌታ አገልጋዮች ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ስለ ማለታቸው እንጂ ጌታን ስለ መማለዳቸው አልተነገረም፡፡ ስለዚህ ይህን ስሕተት ማስተካከል የእግዚአብሔር ቃል በትክክለኛው መንገድ እንዲነበብና እንዲተረጐም ከማድረግ በቀር ሌላ የተለየ ነገር አለው ብሎ ማሰቡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ "ለ" ወደ "ል" መለወጡ ትክክለኛ ዕርማት ነው እንጂ የቅዱሳንን ምልጃ ከማስተባበል ጋር አንዳች ግንኙነት የለውም፡፡

ደግሞም ዕርማቱን ሊሰጥ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱሱን ከዕብራይስጥና ከግሪክ ወደ ዐማርኛ ያስተረጐመው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በመሆኑ፥ የማስተካከል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ ለምን ተስተካከለ ሳይሆን፥ የተስተካከለው የግሪኩ ዐዲስ ኪዳን የሚለውን መሠረት አድርጎ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት? የሚል መሆን ይገባዋል፡፡

ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 40 ላይ የቀረበ

1 comment:

  1. I really appreciate the explanation on 1st John 2 that MK and honestly the EOTC large has been dishonest in making it mean what it is NOT.

    However your explanation on 2nd Cor 5:20 is dishonest as MK is on 1st John. The correct translation is ለ not ል። and it is clearly talking about intercession of Paul and like can play of the intercessory role that God the father gave to Jesus. Now, its clear that you are being dishonest intentionally to highlight your view on intercession.

    Its clear that or not clear in the bible about the intercession role of Saints after they die and its honest debate to argue they do not. The EOTC and orthodox church view on intercession of Saints after they die is not something against the bible. I personally subscribe to the Orthodox view that they do.

    Dont be like MK making the bible yo fit your view.

    Thank you

    ReplyDelete