Saturday, August 31, 2019

የዘመን ምስክር

READ PDF

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
ካለፈው የቀጠለ
መዝገበ ቃላት
ኪ.ወ.ክ. ሲነሡ ከስማቸው ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚነሣው ዕውቅ ሥራቸው “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” ነው። የዚህ ንባቡ በግእዝ፣ ፍቺው በዐማርኛ የኾነ መዝገበ ቃላት ሥራ ጀማሪ በእርሳቸው ብርዕ፣ “በሮማውያን ዘንድ የከበሩ ትምህርት ከጥፈት ያስተባበሩ፥ በትምርታቸውም የተደነቁና የታወቁ፥ በሀገራቸው ግን እንደ ነቢያት የተናቁ እንደ ሐዋርያት የተጠቁ፥ እንደ ዮሴፍም ወንድሞቻቸው ጠልተው ተመቅኝተው ለማይረባ ዋጋ የሸጧቸው የአንኮበሩ ሊቅ” በማለት የተገለጡት መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ወልደ አባ ተክሌ ሲኾኑ፣ ፈጻሚው ደግሞ ኪ.ወ.ክ. መኾናቸው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል።

“ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃል ብቻ መንቀፍ አይበቃም” የሚል ዐቋም የነበራቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ይህን የግስ (የመዝገበ ቃላት) መጽሐፍ ለማዘጋጀት የተነሣሡት፣ ዲልማን የተባለው የውጭ አገር ሊቅ ያዘጋጀውን የግእዝ ግስ ከተመለከቱ በኋላ፣ በተለይ በሞክሼ ፊደላት (ሀሐኀ፣ ዐአ፣ ሠሰ እና ጸፀ) አጠቃቀም ላይ የታየውን ጕድለት በሥራቸው ለመንቀፍ (ትክክለኛውን ለማሳየት) ነው። ኾኖም ዲልማን የውጭ ዜጋ ኾኖ ግእዝን አጥንቶ መዝገበ ቃላት በማዘጋጀቱ ከፍ ያለ አክብሮትና አድናቆት እንደ ቸሩትም በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ እናነባለን። ሞክሼዎቹ ፊደላት እንደ ቀድሞው የድምፅ ልዩነት ባይኖራቸውም የመልክ ልዩነት ስላላቸውና ምስጢራቸውና ስማቸውም እንደ መልካቸው የተለያየ ስለ ኾነ ያ ተጠብቆ መጻፍ አለበት ይላሉ።


መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግሱን ያዘጋጁት በሃይማኖት ጉዳይ ተሰደው በምጽዋ ደሴት ሳሉ ነው። ዝግጅቱን አጠናቀው ወደ ከረን ሲልኩት በጻፉት ማስታወሻ ላይ የግሱ ሥራ የቀሩት ነገሮች እንዳሉና እንዳልተጨረሰ፣ ወደፊት ጊዜ ሲገኝ እንደሚጨረስ ጠቍመው ነበር። ይኹን እንጂ እንዳሰቡት ለማረምና ለማሳተም ዕረፍትና ጊዜ ስላላገኙ፣ ሥራውን የማጠናቀቅና የማሳተም ዐደራውን ለተማሪያቸው ለኪ.ወ.ክ. አስተላለፉ፤ እንዲህ በማለት፦ “ልጄ ሆይ ይህነን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደ ገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፤ የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን ፩ መክሊት ለማባዛትና ለማበርከት ትጋ፤ ዘር ኹን ዘር ያድርግኽ፤ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለሀገርኽ ያብቃኽ።”

ይኹን እንጂ በዚህ መካከል ዐፄ ኀይለ ሥላሴ “ያገራችንን የቋንቋ ድኽነት መቼም የምታውቀው ነው፤ ስለዚህ ዲክሲዎኔር እንዲዘጋጅ አዝዣለኹና ለዚሁ ሥራ ላቶ ብሩ ረዳት ኾነኽ የተቻለኽን ያኽል ዐብራችኹ እንድትሠሩ ይኹን።” ብለው የዐማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲያዘጋጁ የካቲት 27 ቀን 1921 ዓ.ም. ለኪ.ወ.ክ. ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር። ሊሠራ የታሰበውም “ላሩስ ያሳተመውን ትልቁን የፈረንሳይ መዝገበ ቃላት ወደ ዐማርኛ ተርጕሞ ዐማርኛን ከዚያ ለመልቀምና ለመሰብሰብ ነበር።” ነገር ግን በዚህ መንገድ መሥራት አስቸጋሪ ኾኖ ስለ ተገኘ የዐማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሥራ በውጥን ቀረ። ኪ.ወ.ክ.ም ለደስታ ተክለ ወልድ የግእዝ መዝገበ ቃላት ዝግጅታቸውን ትተው የዐማርኛን መዝገበ ቃላት መጻፍ እንደማይገባቸው በመግለጥ እርሳቸው ዐማርኛውን በአበገደ ተራ እንዲሰበስቡና ጊዜ ከተገኘ ወደፊት እርሳቸው (ኪ.ወ.ክ.) እንደሚተረጕሙት፣ ካልኾነ ግን እንደ ጀመሩ እንዲጨርሱት በማሳሰብ ንጉሣዊ ደብዳቤውን ለደስታ በታላቅ ዐደራ አስረከቧቸው።[1]

ኪ.ወ.ክ. በግእዙ መዝገበ ቃላት ሥራ ላይ በማተኰር ሥራውን ቀጥለው የተቀበሉትን ዐደራ ከዳር ለማድረስ ብዙ ደክመዋል። እንዴት ባለ ሸክምና መሰጠት የመዝገበ ቃላቱን ሥራ እንዳከናወኑ ሲገልጡ ደቀ መዝሙራቸው ደስታ ተክለ ወልድ እንዲህ ብለዋል፤ “በሥራ ውለው ማታ ነፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሐሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመጻፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ። በምሳ ወይም በእራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ። ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነሥተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ።” ይኹን እንጂ መጽሐፉን ማሳተም አልቻሉም። ኾኖም ይህን ታላቅ ሥራ ከግቡ የሚያደርስ የግእዝ ችሎታ ያለውን ደስታ ተክለ ወልድን ቀደም ብለው ስላገኙ፣ እርሳቸውም ዐደራቸውን ለደስታ በማስተላለፍ፣ ከእርሳቸው ኅልፈት ከ12 ዓመታት በኋላ፣ በ1948 ዓ.ም. መጽሐፉ የኅትመት ብርሃን አየ።

መዝገበ ቃላቱ እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ከተሠሩ መዛግብተ ቃላት እጅግ ላቅ ያለ፣ የግእዝ ቃላትን በመጠቀም ለሚሠራ ሥራ በማንኛውም ወገን በዋቢነት ሳይጠቀስ የማይታለፍ ሥራ ነው። ከፊደል አንሥቶ በቋንቋው ውስጥ ስላሉ ልዩ ልዩ ሰዋስዋዊ ሙያዎች ሰፊ ትንታኔ በማቅረብ የሚያስተምር፣ የቃላትን ፍቺ ብቻ ሳይኾን ቃላቱ በግእዝ በተጻፉ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙበት ሐረግ ወይም ዐረፍተ ነገር በተወሰዱ ጥቅሶች አስረጂ የሚያቀርብ፣ ብዙ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ነገረ መለኮታዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊና የመሳሰሉት ጉዳዮችም በበቂ ኹኔታ የተከማቹበት የዕውቀት ጎተራ፣ በብዙ ነገር የበለጸገ ከመዝገበ ቃላት ያለፈ ታላቅ መጽሐፍ ነው።

ከመዝገበ ቃላቱ ቀደም ብሎ “አበገደ” እና “መዝገበ ፊደል የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ” የተሰኙና በኅትመት ረገድ ለዋናው መዝገበ ቃላት እንደ መንገድ ጠራጊ የሚቈጠሩ ኹለት መጻሕፍትን በ1926 ዓ.ም. አሳትመዋል። “ሃይማኖተ አበው ቀደምት” የተባለ መጽሐፍም ጽፈዋል። (ከዓለመ መጻሕፍት በተሰኘው ዐምዳችን ላይ ይህን መጽሐፍና ይዘቱን የተመለከተ ጽሑፍ ቀርቧል)።

ይኹን እንጂ በሃይማኖት ዐቋማቸውና (ሦስት ልደት በማለታቸው)፣ አንዳንድ ተድበስብሰውና ተቀብረው እንዲቀሩ የተደረጉ ታሪኮችን፣ በተለይም ስለ ዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት እውነቱን ገላልጠው በመጻፋቸው ምክንያት አንዳንድ ደፋሮች እንዲህ ሲሉ ለመተቸት ሞክረዋል፤ “አለቃ ኪዳነ ወልድ አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስ ያዘጋጁትን የግእዝ ግስ መዝገበ ቃላት፤ ከሚያውቋቸው የግእዝ፣ የዕብራይስጥ ዐረብኛና ላቲን ቋንቋዎች ጋር አገናዝበውና አስፋፍተው ማሳተማቸው ብዙ የሚጋነን ነገር አይደለም። አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስም ኾኑ አለቃ ኪዳነ ወልድ፤ የግእዙን ሰዋስውና ቋንቋውን ያገኙት፥ ወይም የተማሩት እኮ ከጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነው። በመኾኑም የአእምሮኣዊ ንብረት ባለቤት፥ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መኾንዋ መዘንጋት የለበትም። ሌሎቹ ቋንቋዎችም ቢኾኑ ባለቤት አላቸው።”[2] ይህ ተራና ማስተዋል የጐደለው፣ ለትችት የተጋለጠና ብዙ ምላሽ ሊሰጥበት የሚችል ቢኾንም፣ ጊዜና ወረቀት ከመፍጀት ፍርዱን ለአንባቢ መተው ሳይሻል አይቀርም ብለን በዚሁ ዐልፈነዋል።
    
ስለ ግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመጀመሪያ ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ እንደ ተጻፈ ይታወቃል። ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው እናት ቋንቋዎች ወደ ሌሎች አያሌ ቋንቋዎችም ተተርጕሟል። ሲተረጐም ግን ለእናት ቋንቋዎች ታማኝ መኾን የግድ አስፈላጊ ነው። አሊያ የእግዚአብሔርን መልእክት ማዛባትና የራስን ሐሳብ ማራመድ ይኾናል። አለቃም ከዕብራይስጥ ወደ ጽርእ ከተተረጐመው የሰባ ሊቃናት ትርጕም የተመለሰውን የግእዙን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ችግሮች አሉባቸው ያሉት በአንዳንድ ኹኔታ ከእናት ቋንቋዎች ጋር ሲነጻጸሩ ስምምነት ስለማይታይባቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዐይነት ችግር ካለበት በቃሉ በኩል የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልእክት ያዛባል።
      
ኪ.ወ.ክ. መጻሕፍተ ብሉያትንና መጻሕፍተ ሐዲሳትን እንደ ተማሩ ቀደም ሲል ጠቅሰናል። በኢየሩሳሌም ዕብራይስጥና ግሪክን ጨምሮ ሌሎችንም ቋንቋዎች በሚገባ አጥንተዋል። በተለይ ዕብራይስጥና ግሪክ ማጥናታቸው የሰባ ሊቃናት ቅጂ በኾነው የግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብሉዩ ከዕብራይስጡ፣ ሐዲሱ ከግሪኩ ምንባብ የሚለዩባቸው ምንባባት እንዳሉ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ጠቍመዋል። ብሉዩ በዕብራይስጥ ሐዲሱ ደግሞ በግሪኩ መታረም እንዳለበትም ሞግተዋል።

ከጽርእ የተመለሰው የግእዙ ብሉይ ኪዳን፣ “በዕብራይስጥ ስላልታረመና የቅጂ ቅጂ ስለ ኾነ ከናቱ ከምንጩ ከጽርእ ብቻ እንጂ ካያቱና ከቅድም አያቱ ከዕብራይስጥ አይስማማም፤ ዐልፎ ዐልፎ መሥመር ይጥላል (ይረሳል/ይዘላል)፥ ቃል ይለውጣል። ይህነንም ዕብራይስጥና ጽርእ የሚያውቁ ግእዝ የተማሩ እንደነመዐልም ዮሐንስ፥ እንደነዲልማን፥ እንደነጕይዲ ያሉ ብዙ ዐዋቆች ይመሰክራሉ። ጀርመናዊው ሊቅ ሲዲ ጳውሎስም ለጎንደር ሊቃውንት ትፈቅዱ እንደ ኾነ ብሉያችሁን ከዕብራይስጥ ሐዲሳችሁን ከጽርእ እያስማማሁ ዐርሜ ንባቡን ከነትርጓሜው አሳትሜ ብዙ መጻሕፍት ላምጣላችሁ ቢላቸው አንፈልግም ብለው በምቀኝነት እንዳስቀሩት፥ ቅነነት ያላቸው ብዙ ሰዎች ይተርኩታል፤ ርሱም በታሪኩ ውስጥ ጥፎታል ይባላል።” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ብሉዩ ከዕብራይስጥ ሐዲሱ ደግሞ ከግሪኩ ምንባብ ልዩነት እንዳላቸው ከላይ የተጠቀሱት ሊቃውንት ብቻ ሳይኾኑ ራሷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2000 ዓ.ም. ለራሷ ያሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስም በግልጥ መስክሯል። መጽሐፍ ቅዱሱ በእግርጌ ማስታወሻዎቹ “ዕብራይስጡ እንዲህ ይላል”፣ “ግሪኩ እንዲህ ይላል” በሚሉ ማብራሪያዎች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ለሮሜ 8፥34 የተሰጠው ትርጕም “ይፈርዳል” የሚል ቢኾንም፣ በእግርጌ ማስታወሻ ላይ ግን “ግሪኩ ስለ እኛ የሚማልደው ይላል” ይላል። (ይኹን እንጂ ግእዙም “ይፈርዳል” ሳይኾን “ይከራከራል” ነው የሚለው።) የግእዙ ምንባብ ከዕብራይስጡና ከግሪኩ አንዳንድ ልዩነት እንዳለው ቢታወቅም፣ በዕብራይስጡና በግሪኩ ማረም ሲገባ ከነልዩነቱ እንዲቀጥል ነው የተደረገው። አንዳንድ ከጊዜ በኋላ የተነሡ ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ትምህርቶችም በልዩነቱ ብቻ ሳይኾን ከዚያም ዐልፎ ቃሉን ለራስ አስተምህሮ እንዲስማማ ተደርጎ በተለወጠው ንባብ ላይ ጭምር እንደ ተመሠረቱ ማየት ይቻላል።

ሐሰተኛ ታሪክና ትምህርት ስለ ያዙ መጻሕፍት
መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ “አዋልድ” ብሎ የሚጠራቸው መጻሕፍት በኹለት የሚከፈሉ ናቸው። በአንድ በኩል በስድሳ ስድስቱ ላይ ተጨማሪ የኾኑትን መጻሕፍት የብሉይ ኪዳን አዋልድ ብለው ይጠሯቸዋል (ገጽ 19)። “የሊቃውንት መጽሐፍ፥ ድርሳናት፥ ተግሣጻት፥ ንባባቸውና ምስጢራቸው እንደ ዐጽቅ ኹኖ ከብሉይ ከሐዲስ” (ገጽ 391) የተወጣጡትን መጻሕፍትም አዋልድ ይሏቸዋል። በይዘታቸው ከእነዚህ ውጪ የኾኑትንና ልዩ ልዩ ስሕተቶችን የያዙ መጻሕፍትን ደግሞ በመተቸት ዋሾዎች መኾናቸውን ገልጠዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ክብረ ነገሥት ነው።

ክብረ ነገሥት በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቢኾንም፣ ውስጡን በመረመሩት ዘንድ ግን ሐሰተኛና የፈጠራ ታሪክ በማቅረቡ ይተቻል። ኪ.ወ.ክ.ም ስለ ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት የዘር ሐረግ የሚተርከውን ክብረ ነገሥትን በዘወርዋራ መንገድ ክፉኛ ተችተውታል፤ እንዲህ በማለት፦ “ያልጠራ ያልበራ እንቶ ፈንቶ ታሪክ ባዋቆችና በመርማሮች ዘንድ ያሳፍራል እንጂ አያኰራም። ኢትዮጵያንም እንደ ርጎ የሚያረካትና የሚያስመካት ጃንሆይና እቴጌም የሚያሰኛት ምንጯ ሲማስና ዱሯ ሲጣስ ከጥንት ዠምሮ የነበረው የነገደ ኵሽ ልብሰ መንግሥት አርድ አንቀጥቅጥ (ሲያዩት የሚያንቀጠቅጥ፣ የዱሮ ነገሥታት የሞት ፍርድ በሚፈርዱበት ቀን የሚለብሱት) የዘውዳቸውም ፈርጥ የነጻነቷ ሽልማትና ጌጥ መንግሥተ ሳባዋ አሮጌው ካባዋ ነው እንጂ፥ በኋላ ዘመን እንደ እጅ መንሻ ኹኖ የመጣላት የሰሎሞን ድርብ (ሰፊ ጥበብ ያለው ዋጋው ውድ የኾነ ጌጠኛ የማዕርግ ልብስ) ምኒልክ የዘውዱ ቀጸላ (ሻሽ፣ የራስ የፊት መሸፈኛ፣ መደረቢያ) የንግሥተ አዜብ የወርቅ ድባብ የየመን ጃንጥላ አይደለም። የሰሎሞኑና የየመኑስ በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት እንዲሉ፥ ዕለተ በዓል የገጠመው የስንክሳር ታሪክ ወበዛቲ ነው።”

የዚሁ የክብረ ነገሥት ትምህርት ውላጅ የኾነው “ገድለ ቀውስጦስ” የተሰኘው መጽሐፍም፣ “ኦሪት ነቢያት በሰሎሞን ጊዜ ከዕብራይስጥ [ወደ ግእዝ] እንደ ተመለሱ ተናግሮ ፪ኛ ደግሞ ከዕብራይስጥ በፄዋዌ (በባቢሎን ምርኮ ጊዜ) ጠፍተው በሚጠት (ከምርኮ ሲመለሱ) በኋላ ዘሩባቤል አይዙር ከሚባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ለምኖ አሶስዶ ከግእዝ ወደ ዕብራይስጥ እንዳስተረጐመው ይናገራል። ‘አይዙርሰ ዘነግሠ መንፈቀ መዓልት በሰብዐቱ ምእት ሰብዓ ወክልኤቱ (በ፯፻፸፪/772) ዓ.ም. - በ772 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን የነገሠው አይዙር’ [ስለሚል] (ታሪከ ነገሥት)። ይህነንስ ወዲያ እንተወውና ብሉያችን በዘመነ ብሉይ ከዕብራይስጥ ተመልሷል ማለት፥ በነብሪድ (ንቡረ እድ - በራሱ ላይ እጅ የተጫነበት የአክሱም ጳጳስ የማዕርግ ስም) ይሥሐቅ እጅ ሳይከካና ሳይቦካ ሳይጋገር ምጣድ ሳይነካ እም ኀበ አልቦ (ከባዶ) የተገኘ የምኞት የሕልም እንጀራ ነው።” በማለት የክብረ ነገሥት ውላጅና ዋሾ መጽሐፍ መኾኑን ገልጠዋል።

አክለውም ብሉያት ከጽርእ ወደ ግእዝ የተመለሱት ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በ4ኛው ምእት ዓመት ነው እንጂ፣ “ሱቱኤል ዕዝራን ያላየ ያልሰማ ስለ ጣፈው ዐጥፎ ደርቦ እየዋሸ ታሪክ ያበላሸ የቀውስጦስ መጽሐፈ ገድልና መጽሐፈ ምስጢር እንደሚሉት በዘመነ ብሉይ አይደለም።” እነዚህንም የገድለ ቀውስጦስና የመጽሐፈ ምስጢር ጽሑፎች “ፍሬ ቢስ ወሬ፣… ልቦለድ ፈጠራ፣ ዋሾ ታሪክ” ሲሉ፣ ከገድለ ቀውስጦስ ጋር የአባ ጊዮርጊስ ድርሰት የኾነውን መጽሐፈ ምስጢርን ደርበው ሐሰተኛ ምስክርነትን የያዘ መጽሐፍ መኾኑን መስክረዋል።

“አርድእት” የተባለ የጸሎት መጽሐፍ ደግሞ “ዐሥራ ኹለቱ አርድእት (ደቀ መዛሙርት) ወይም ሐዋርያት ሰዶም ገሞራ ገብተው ወንጌልን ሲሰብኩ የሰዶም ሰዎች አናምንም አንቀበልም ቢሏቸው አርድእት ወደግዜር ጸልየው እሳትና ዲን አዘነሙባቸው፤ ሎጥ ግን ከነልጆቹ በወንጌል በአርድእት ቃል ስላመነ ከእሳት ዳነ ብሎ ገና ኦሪት ሳትጻፍ በአብርሃም ዘመን የኾነውን ለወንጌልና ለአርድእት ሰጥቶ ይተርካል፤” ካሉ በኋላ፣ “ጣፊ ለጣፊ ዋሾ ቀጣፊ የሚያሰኝ እንደዚህ ያለው ነው” ሲሉ በልኩ የተሰፋ ትችት ሰንዝረውበታል።

በተክለ ሃይማኖት ገድል የተጻፈውና ተክለ ሃይማኖት ስድስት ክንፍ አበቀሉ የሚለው ታሪክም ሙያዊ ግዴታቸውን በታማኝነት መወጣት በተሳናቸው ታሪክና ገድል ጸሓፊዎች የተፈጠረ ሐሰት መኾኑን ሲገልጡ እንዲህ ብለዋል፤ “ታሪክና ገድል የሚጥፍ ሰው ምሎ ተገዝቶ እንደሚመሰክር ወይም የሰውን መልክ በፎቶ ግራፍ እንደሚያነሣና እንደሚሥል እንደዚያ መኾን ሲገባው፤ እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት ከማለት ወጥቶ የማይገባውን እንዳዝማሪ እንደ ሐሚና ቢያቈላምጥ፤ አለስሙና አለመልኩ ሌላ ስምና መልክ ቢሰጥ፤  ወይም እንደ ባለቅኔ እውነቱን እያሳበለ ሐሰቱን እያሰባቀለ (እያቀላጠፈ)ለአዳም ሥጋ ያልተሰጠ ሕዋስ ፮ ክንፍ ፲፮ ክንፍ እያለ የኵሸትና የምጸት ቃል ቢጥፍ ታላቅ ዕዳ አለበት።”

ይህም ብቻ አይደለም፤ ከዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተያይዞ ከሰማይ ወረደ ስለ ተባለው መስቀል “ምድራዊ አንጥረኛ የሠራውን መስቀል ግብዞችና አታላዮች ከሰማይ ወርዷል” ብለው የማይመስል ነገር እየተናገሩ እንዳለ ጠቅሰዋል። ማን እንደ ተቀኘው ለጊዜው ማወቅ ባይቻልም ቀጥሎ የቀረበው “ዘአምላኪየ” ቅኔም ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል ከሰማይ አለመውረዱንና ከምድር የተገኘ መኾኑን ይገልጣል።  
“እፎኑ መስቀል ዘደብረ ሊባኖስ ጽርሑ
ወረድኩ እምነ ሰማይ ይቤለነ ናሁ
እንዘ ነአምሮ ለሊነ ከመ ሊቀ ጸረብት አቡሁ”
ትርጕም፦ “አባቱ የጠራቢዎች አለቃ መኾኑን እያወቅነው እንዴት መኖሪያው ደብረ ሊባኖስ የኾነ መስቀል እነሆ ከሰማይ ወረድኩ ይላል?”

የኪ.ወ.ክ. ደቀ መዝሙር የኾኑት ደስታ ተክለ ወልድም ዐማርኛ በላስቶች ዘመን በጣም የሠለጠነ መኾኑን ለማመልከት በዐማርኛ የተጻፈ የዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ በደብረ ሊባኖስ (ቀጠባ ማርያም ዋሻ) መኖሩን ገልጠዋል። መጽሐፉን በጥልቀት ያዩትና የመረመሩት በ1928 ዓ.ም. ሐምሌ 22 ቀን በፋሺስት ኢጣሊያ ስለ አገራቸውና ስለ ሃይማኖታቸው ሰማዕት የኾኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ይህ ታሪክ “ከሰማይ ወረደ የሚባለውን መስቀል ከውጭ አገር እንደ መጣ ይመሰክራል። በመስቀሉም ላይ የፈረንጅ ፊደል የእጅ ጽፈትና ዓመተ ምሕረት ጭምር ተቀርጾበት ይታያል።” ማለታቸውን ጽፈዋል። ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተ ተክለ ሃይማኖት ናቸው።

ስለ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖትና ዕጨጌው ተክለ ሃይማኖት
ኪ.ወ.ክ. ቤተ ተክለ ሃይማኖት መኾናቸው ይታወቃል። በስማቸውም ላይ “ወልደ አባ ተክሌ” የሚል ቅጽል ይጠቀማሉ። ይህም የጻድቁና በሰባተኛው ምእት ዓመት የኖሩትና ከአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቀጥሎ በኦርቶዶክሳዊው ባህለ ትምህርት ውስጥ የሚጠቀሱት ኹለተኛው አባት መኾናቸው በተደጋጋሚ ተጠቅሶአል። ይኹን እንጂ የእኒህ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ በ13ኛው ምእት ዓመት ለተነሡት ለደብረ ሊባኖሱ ዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት ተሰጥቶ፣ የታሪክ መፋለስ እንዳጋጠመ ኪ.ወክ. ይናገራሉ። ይህን ታሪክ የያዘው ገድል በአንዳንድ ደብርና ገዳም፣ ይበልጥ ደግሞ በወይንጌ ዘብሔረ ወግዳ፣ ዳግመኛም በግራርያ ዘበጌምድር እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በሮማውያን ስንክሳርና በ1042 ዓ.ም. በላስቶች ዘመን ተጽፎ ከደብረ ሊባኖስ ወደ ኤውሮፓ የሄደው ጥንታዊው ገድለ ተክለ ሃይማኖት የዕጨጌውን ታሪክ ሳይጨምር ስለ መጀመሪያው ተክለ ሃይማኖት እንደሚተርክ፣ ይህንንም ገድል አንድ ባለታሪክ ዲልማንና አንጧን ዳባዲ የተባሉ ግእዝ ዐዋቂዎች የኾኑ አውሮፓውያን ሊቃውንት በእንግሊዝ አገር እንዳዩትና እንደ መረመሩት፣ በመጽሐፋቸውም እንደ ጠቀሱት፣ ዛሬም በሎንዶን እንደሚገኝ ይናገራል ይላሉ።

ዳንኤል ክብረት ግን “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በብዙ ሥራዎቻቸው የተከበሩና የተመሰገኑ ሊቅ ናቸው። አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ላነሡት ሐሳብ ግን ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም።” እርሳቸው አለ የሚሉት ሌላ ገድል አልተገኘም። “አለቃም ያነበቡት ከኾነ ያነበቡትን፣ ያገኙት ከኾነም ያገኙበትን አልነገሩንም። ምንጭ የላቸውምና ለታሪክ ክርክር ሊጠቀሱ አይችሉም።” ሲል ለማጣጣል ይሞክራል።[3] ይኹን እንጂ አለቃ ስለዚህ ጉዳይ የጠቀሷቸው ምንጮች መኖራቸው እላይ ተጠቅሷልና፣ ዝቅ ብለን እንደምናየው ሌሎች ጸሐፍትም ይህን የሚያዳብር ሐሳብ አስፍረዋልና እንዲሁ ማጣጣል የሚቻል አይደለም። እርሳቸውን በድፍረት ለማጣጣል ከመሞከር ይልቅ አንዳንድ ጊዜ በሐሰት የተካበ ታሪክ ተደጋግሞ ስለ ተጻፈና ኹሉም ተቀባብሎ ስለ ተረከው እውነተኛ ሊኾን እንደማይችል መገንዘብ፣ አንዳንድ የአገራችን ታሪክ ጸሓፊዎችም፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እንዳሉት ተመልካች ልቡናቸውን በማሳወርና የማያደላ አእምሮአቸውን አድሎኣዊ በማድረግ እውነተኛ ታሪክን በመዘገብ ላይ ኀጢአት እንደሚሠሩ የተናገሩትን ማስተዋል ይበጃል።

ለዕጨጌው ተክለ ሃይማኖት ገድሉ የተጻፈላቸው እርሳቸው በሞቱ በ254 ዓመት በነአባ ዮሐንስ ከማ አማካይነት ሲኾን፣ የጻድቁን ሥራ ለዕጨጌው በመስጠት የቀረበ መኾኑን ይናገራሉ። በጻድቁና በዕጨጌው መካከልም የ550 ዓመት ርቀት መኖሩን ኪ.ወ.ክ. ያክላሉ።  

ዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት በናታቸው የነገሥታት ወገን የይኩኖ አምላክ ያክስት ልጅ ወይም የናት ወንድም አጎት ወዲህም የደብረ ሊባኖስ አበምኔት (የገዳሙ አባት) ነበሩ ይባላል። ፊት በሕግ ቀሰው ሚስታቸው ከሞተች በኋላ መንኵሰው አቡን ስለ ኾኑ ያልተማሩ ሰዎች የማይገባ መስሏቸው “አቦ ብልኀት ዕጨግነት ከሚስት” ሲሉ ተርተውባቸዋል። እርሳቸው በዚህ ሐዲስ ስም ተክለ ሃይማኖት ተብለው በመጀመሪያ ለተጠሩት ለጻድቁና ቅዱሱ ታላቁ ሐዋርያ ኹለተኛ በመኾናቸው ዳግማይ (ኹለተኛ) ተክለ ሃይማኖት ይባላሉ።

የዕጨጌውን ታሪክ በተመለከተም “ሀሎ ጽሑፈ ማእከለ ገድል ከመሰ ኢይርአዮ ሰብእ ወኢያንብቦ ከመ ኢይበል ላዕሌሁ ቃለ መሐደምት ከመ ሰብአ ጎንደር ደኀርት ‘አቦ በልኀት ዕጨግነት ከሚስት’ ሀሎ ስፉየ ወልጹቀ ጥቁበ ወድርጉሐ ኅቱመ ወዝጉሐ እስከ ዮም።” ትርጕም፦ “በገድሉ መካከል ሰው እንዳያየው እንዳያነበውም፣ እንደ ኋለኞች የጎንደር ሰዎችም ‘አቦ ብልኀት ዕጨግነት ከሚስት’ የሚል የቧልት ንግግር እንዳይናገሩ እስከ ዛሬ ድረስ ተሰፍቶ፣ ተገጥሞ፣ ታስሮ፣ ተደርቶ፣ ታትሞና ተዘግቶ ይገኛል።” በማለት ምስጢር እንዳይወጣ የተሠራውን እውነትን የማዳፈን ሥራ አብራርተዋል። ምናልባት የመጀመሪያውን ተክለ ሃይማኖትን ታሪክ ለዳግማዩ (ዕጨጌው) ተክለ ሃይማኖት የሰጡ ክፍሎች ስለ ዕጨጌው ትክክለኛ ማንነት የተጻፈውን አጥፍተውት ይኾናል።

ይህን የኪ.ወ.ክ.ን ትረካ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስም የሚጋሩበት ኹኔታ ያለ ይመስላል፤ “መርሐ ልቡና” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የቅዱሳንን የገድላት መጻሕፍት ቍጥር በዘረዘሩበት ክፍል ውስጥ ኹለት ዐይነት ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንዳለ ጠቅሰዋል። እነርሱም፦ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ እና ገድለ ተክለ ሃይማኖት ዘተንቤን ናቸው (1945፣ 78)። እዚህ ላይ የተንቤኑ ገድል የቀዳማይ ተክለ ሃይማኖት ገድል እንደ ኾነ ይታመናል።

“የደብረ ሊባኖስ ገዳም አመሠራረት ታሪክና ዜና” በሚል ርእስ በግንቦት 12/1989 ዓ.ም. የታተመች ትንሽ መጽሐፍ “አንዳንድ በአለ ታሪኮችን የሚያወዛግቡ ልዩ ልዩ ተክለ ሃይማኖቶች እንዳሉ ይነገራል። አንዱ በዘመነ አክሱም ፍጻሜ ላይ ትግራይ ውስጥ በብሕትውና ኖረው ከዐለፉ በኋላ ቤተ ክርስቲያን የታነጸላቸው፤ ገድል የተጻፈላቸው ጻድቅ አባ ተክለ ሃይማኖት የተባሉ መንፈሳዊ አባት ናቸው።” (ገጽ 6)። መጽሐፉ አክሎም ስለ ዕጨጌ ተክለ ሃይማኖት ሲተርክ “የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ ከአደጉ በኋላ በማዕርገ ድቁናና ቅስና፤ በኋላም በምንኵስና ሳሉ …” እያለ ይተርካል። በዚህ ውስጥ “ቅስና” የያዙት ከምንኵስና አስቀድሞ መኾኑ ተጠቍሟልና ምናልባት በመጀመሪያ ባለ ትዳር ቄስ እንደ ነበሩ ሊያመለክት ይችላል፤ ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዐት መሠረት አንድ ዲያቆን ሊቀስስ (ቄስ ሊኾን) የሚችለው ሚስት አግብቶ ወይም መንኵሶ ነው። በዚህ ንባብ ውስጥ ግን ከምንኵስናው ቅስናው ስለ ቀደመ ያገቡ ቄስ መሆናቸው በግልጥ ይታያልና፣ ከምንኵስና በፊት አስቀድመው መቅሰሳቸውም ተጠቅሷልና የቀሰሱት አግብተው መኾን አለበት። ስለዚህ በትዳር ውስጥ ያለፉና በኋላ መንኵሰው የጰጰሱ ሰው ነበሩ ማለት ነው ከሚለው ከኪ.ወ.ክ. ትረካ ጋር ይስማማል።

ዶ/ር ሐዲስ የሻነውም “ፍንጭ ፍተሻ” በኋላም “ምዕላደ ትምህርት”[4] በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ዕጨጌውን  ተክለ ሃይማኖት “አባ ተክለ ሃይማኖት ዳግማዊ” ብለው ጠርተዋቸዋል። ለምን ዳግማይ አሏቸው? ቀዳማይ ተክለ ሃይማኖት በመኖራቸው አይደለምን?

ይኹን እንጂ ኪ.ወ.ክ. ስለ ዕጨጌው ተክለ ሃይማኖት ምንጭ ጠቅሰው የጻፉትን ታሪክ እርሳቸውን ለመተቸት ብቃቱ የሌላቸው አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች፣ “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ በጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ላይ ጽርፈት በመሰንዘር ከጸጎቹ መካከል ዋነኛው ናቸው”[5] እስከ ማለት ደርሰዋል።
      
ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ታግለዋል
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ በመጽሐፋቸው “ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ በዲሰርቴሽኑ ውስጥ እንደ ጠቀሰው ለራስ መቻል ከሚሟገቱት አንዱ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነበሩ።”[6] ብለዋል። ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ በግብጽ ለአንድ ዓመት የቈዩት ኪ.ወ.ክ.፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የበላይ ኾና በቈየችባቸው ዓመታት ያሳደረችውን አሉታዊ ተጽዕኖ በቅርበት ሳይገነዘቡ አልቀሩም። በእርሳቸው ዘመን እንደ ነበሩት እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያን ጳጳሳት መመራቷ ያደረሰባትን ዘርፈ ብዙ ችግር በማጤን ይቈጩም ነበር። መቈጨት ብቻም ሳይኾን ከጥገኛነት እንድትላቀቅና ራሷን እንድትችል የበኩላቸውን ትግል አድርገዋል።

በኢየሩሳሌም ሲኖሩ ያስተዋሉትና ይቈጩበት የነበረው አንዱ ነገር፣ ግብጻውያን በፍትሐ ነገሥቱ ውስጥ በሥርዋፅ ያስገቡትንና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሊቃውንት ጳጳሳት አድርገው እንዳይሾሙ የሚከለክለውን አንቀጽ[7] መሠረት አድርገው ግብጾች የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ይዞታ እስከ መቀማት የደረሱበትን ሕገወጥ አሠራር ነው። የሚከተሉት ስንኞች ይህን ቍጭታቸውን የገለጡባቸው ናቸው።
“ያገር ልጅ የማር እጅ የሚሉት ተረት
ከመምር ከጳጳስ አለው መስማማት
ንጉሥና ጳጳስ ግራና ቀኝ ዐይን
አንድ ዐይነት ሊኾኑ አይገባምን
ንጉሥ እያላችሁ ጳጳስ መበደር
ይኸ ነው የዘጋው የትምርቱን በር
ከሕዝብ ተመርጦ በትምህርቱ ተስፋ
ልቅና የሚሾም ያገር ልጅ ሳይጠፋ
ክብርን አሳልፎ ለባዕድ መስጠት
ስንፍና እንደ ኾነ ዛሬም ዕወቁት
...
የባዕድነትንም ሥራ እንድትረዱት
ሳሌም ተሻግራችሁ ዴር ሡልጣን እዩት
ዴር ሡልጣንም ማለት ገዳመ ንጉሥ
የኢትዮጵያ ቦታና መቅደስ
ይገባናል ብሎ እንደ ልቅናው
በቱርኮች ትከሻ ግብጥ የወሰደው
ዋሽቼም እንደ ኾን በግብጥ በቱርክ
ይታዘቡኝ አርመን ሶርያ ግሬክ

ይህ ብቻ አይደለም፤ ግብጻውያን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በአመራራቸው ሥር ለማቈየት የተጠቀሙበት አንዱ ፖለቲካቸው፣ “ጳጳስ የሚኾን ሰው ጥንቱን ሲፀነስ በናቱ ራስ ላይ፥ ኋላም ሲወለድ በሕፃኑ ላይ ነጭ ርግብ ከሰማይ ወርዶ ያርፍበታል፤ ይህ ምልክት ያልታየበት ሰው፥ ስንኳን ጥቍሩ ኢትዮጵያዊ ቀዩ ግብጽ ቢኾን ጳጳስ ለመኾን አይበቃም እያሉ የጻፉት” እንደ ኾነ ኪ.ወ.ክ. ጠቅሰዋል።

በዚያ ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብጻውያን አመራር ነጻ እንዳትወጣ ግብጻውያን ካደረጉት በላይ ግን ኢትዮጵያና ልጆቿም ከሊቃውንታቸው ይልቅ ለባዕዳን የሚሰጡት ግምት ከፍተኛ መኾኑ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ፣ በተለይ ከግራኝ ወዲህ በጎንደር ዘመነ መንግሥት ሐሰተኞች፣ ጳጳሳት ሳይኾኑ ጳጳሳት ነን ብለው እንደ መጡና ብዙ ጥፋት እንደ ደረሰ እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል።

“ከልጆቿ ይልቅ ባዕድ የንጀራ ልጅ የምቶድ ወረተኛ ባልቴት ስለ ኾነች ኢትዮጵያን በየዘመኑና በየጊዜው እንደዚህ ያለ ይህን የመሰለ ልክ የሌለው ሐዘን ጥቃትና ውርደት የሰው መሣቂያነት አግኝቷታል። መቸም መች ቢኾን በንጀራ ልጆቿ በግብጦች ከኀሳር በቀር ክብር አላገኘችም። የባሕርይ ልጆቿም ታላላቆቹና ብዙዎቹ በመምህር በሞግዚት በቤተ ክሲያን ትምርት ያላደጉ ጽልሙታነ ልብ (ልበ ጨለማዎች) ስለ ኾኑ ብሩሃነ አልባብ (ልበ ብርሃኖች) በሊኀነ ንባብ (አንደበተ ርቱዖች) ከኾኑት ከወንድሞቻቸው መርጦ መሾምና በጥቍር ጳጳስ እጅ መባረክ ውርደትና ርግማን መስሏቸው አላስተርጓሚ የማይሰሙትና የማይሰማ፣ ቋንቋውና መልኩ የተለየ የውጭ አገር ጳጳስ አባ ቀዮ በመጣ ቍጥር በሃይማኖት ነገር ጢስ እንደ ገባው ንብ ሲታወኩና ሲታመሱ ሲተራመሱ ሲሟገቱና ሲፋለሱ ሲካሰሱ ይኖራሉ።”

በዚያ ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረችበትን ኹኔታ ጎጆ ባልወጣና ራሱን ባልቻለ ልጅ መስለው ያቀረቡበትም ኹኔታ አለ። እንዲህ ያለው ልጅ እንዳባቱ ባለቤት መኾን አቶ እገሌ መባል የለውም። የኢትዮጵያም ቤተ ክርስቲያን ኹኔታ እንደዚህ ልጅ ነው። ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለ1700 ዓመት ወለተ ግብጽ (የግብጽ ሴት ልጅ) እየተባለች ዲቃላውም ትምህርት ሳይቀርባት ትኖራለች። “ወየው ጳጳሳቷም እንደ ነገሥታቱ የላሟ ልጆች ያውራዋ ውላጆች ኹነውላት ቢኾን! ሰው ኹሉ ወደ ፊት ሲሮጥ ሲገሠግሥ ርሷ ተለይታ እንዲህ ወደ ኋላ ባልቀረችም።” ሲሉ በግብጻውያን ሥር መቈየቷ ለኋላ ቀርነት እንደ ዳረጋት ቍጭት ዐዘል በኾኑ ቃላት አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያን ጳጳሳት መመራቷ ቀርቶ ራሷን ችላ የተጓዘች ብትኾን ኖሮ በዋናነት ከራሷ ዐልፎ ተርፎ ወንጌልን ለአፍሪካና ለቀረውም ዓለም አብሣሪ ትኾን ነበር የሚልም ሐሳብ አንጸባርቀዋል፤
“መበደሩ ቀርቶ ክህነትና አቡን
ሊቀ ጵጵስናው በእጃችሁ ቢኾን
ኢትዮጵያችሁ እንደ ፀሓይ ሙቃ
ታንዣብቡ ነበር አፍሪቃ ላፍሪቃ
ወደ እስያም ክፍል እንዳፄ ካሌብ
ትሻገሩ ነበር በወንጌል መርከብ።”

የኪዳነ ወልድ ክፍሌ የመጨረሻ ዓመታት
ኪ.ወ.ክ. ፋሺስት ኢጣሊያ አገራችንን መውረሩን በግልጥ ይቃወሙና ኢትዮጵያ በቶሎ ነጻ እንደምትወጣ ዐፄ ኀይለ ሥላሴም ከስደት አገር ተመልሰው እንደሚመጡ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የመላ አፍሪካን ነጻነት በተመለከተ ምንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ ይናገሩ ነበር። በዚህ ምክንያት “በ1929 ዓ.ም. ጠላት ወስዶ በጽኑ እስራት ከጨለማ ቤት አገባቸውና እዚያ ዐይናቸው ጠፋ። እንዳሉትም ኢትዮጵያ ነጻ ወጣች። ሦስት ዓመታትን የነጻነትን ብርሃን በዐይነ ልቡናቸው እያዩ” ኖሩ። ከዚያ “ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ላለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መፍቅድኽን (ለኑሮ የሚያስፈልግኽን ልብስ ምግብ) እየሰጠኹ በምትፈልገው ነገር ኹሉ እረዳኻለሁ (እጦርኻለኹ) ስላገራችንም ጥቅም ብዙ ዘመን የደከሙበትን የግእዝ ሰዋስውና ግስ አሳትምልኻለኹ ብለው ተስፋ ስለ ሰጧቸው በ1936 ዓ.ም. ኅዳር 26 ቀን እሳቸው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ቀበና”[8] ተቀመጡ። ከዚያ በኋላ የቈዩት ለሰባት ወራት ብቻ ነው፤ ሠኔ 24 ቀን 1936 ዓ.ም. ዐረፉና ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።

ምን ተማርን?
ከላይ በጥቂቱ ከቀረበው የኪ.ወ.ክ. ታሪክ የምንማረው ብዙ ነገር እንዳለ ግልጥ ነው።  የመጀመሪያው ነገር ለመማር የነበራቸው ትጋትና በትምህርት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ነው። ተግቶ መማርና ከትልቅ ደረጃ መድረስ አንድ ግብ ቢኾንም፣ በተማሩበት መስክ ፍሬ ማፍራትና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ሠርቶ ማለፍ ግን ከተማሩና ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ብዙዎች መካከል ጥቂቶች የሚጨብጡት ውጤት ነው። የቀለም አባታቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ “ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን ፩ መክሊት ለማባዛትና ለማበርከት ትጋ፤ ዘር ኹን ዘር ያድርግኽ” በማለት የመዝገበ ቃላቱን ሥራ እንዲፈጽሙ የሰጧቸውን ዐደራ በብቃት መወጣታቸው ጥሪያቸውን ጠንቅቀው ያወቁና ለዚያው የኖሩ፣ ከጥሪያቸው የሚያስወጣ የንጉሥ ትእዛዝ እንኳ ሲመጣ “ግእዝን ትቼ ዐማርኛን ልጽፍ አይገባኝም” ብለው የጸኑ፣ መምህራቸው እንዳሉት አንዱን መክሊት ለማባዛትና ለአገር ለማበርከት እጅግ የተጉ ሊቅ ናቸው። የምንኖረው ለእኛ ብቻ ከኾነ የተፈጠርንበትን ዐላማ እንደ ዘነጋንና የተሰጠንን ጸጋና ችሎታ እንዳባከንነው መቍጠር አለብን። ምድራዊ ኑሯችን በላ ጠጣ ለራሱ ኖሮ ሞተ ከሚለው ግለኛነት መውጣትና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ በማበርከትም መገለጥ አለበት።

የሀገር ፍቅርን እንማራለን። አለቃ ኪዳነ ወልድ ብዙ የተማሩና ለአገር እጅግ የሚጠቅሙ ሊቅ ቢኾኑም በሕይወተ ሥጋ ሳሉ አገራቸው ኢትዮጵያም ኾነች የተማሩባትና ያደጉባት ቤተ ክርስቲያን በሥራዎቻቸው እየተጠቀሙ ተገቢውን ክብርና ስፍራ አልሰጧቸውም። ይህ ልብን የሚሰብርና ተስፋ የሚያስቈርጥ ጉዳይ ቢኾንም ለአገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው የነበራቸው ፍቅር ቅንጣት ታኽል አልቀነሰም ነበር።
“ያገር ፍቅር የሚሉት ጌሾና ብቅል
ሆድ ያባውን ዅሉ ያስለፈልፋል።”
 እነዚህ ኹለት ስንኞች ግብጾች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸሙትን ጥፋት ከዘረዘሩ በኋላ ሐሳባቸውን የቋጩባቸው ናቸው። ስንኞቹ አገሪቱም ኾነች ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ ሊቅነታቸው አክብረው ባይዟቸውም፣ ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር ቅንጣት ታኽል እንዳልቀነሰ ያመለክታሉ።
                                                                   
ዘመናቸውን የፈጸሙት ለኢትዮጵያ ነጻነትና እድገት ለቤተ ክርስቲያንም መታደስ ተጋድሎ በማድረግ ነው። ለዚህም ሰፊውንና ጥልቁን ዕውቀታቸውንና ግልጥና ቀጥተኛ የኾነውን በድፍረትም የተሞላውን ሰብእናቸውን በእጅጉ ተጠቅመውበታል።

እውነትን ይዞ ለብቻም ቢኾን መቆምን እንማራለን። በማኅበረሰባችን ውስጥ መማር ፈሪ ያደርጋል የሚል አስተሳሰብ ነበረ፤ አኹንም አለ። ይኹን እንጂ ይህን አስተሳሰብ ጥሰው የተገኙ ሊቃውንት አሉ። አለቃ የሚታወቁበት አንዱ ነገር ያመኑበትን ጉዳይ ለመግለጥ ምንም የማይፈሩ፣ ብቻቸውንም ቢኾኑ ላመኑበት እውነት የሚቆሙ መኾናቸው ነው። ብዙዎች የተስማሙበትን ብቻ መልሰው ከማስተጋባት ይልቅ የሚመረምሩና የሚያጠኑ፣ በተለያየ መንገድ የተደበቀውንና የተጨቈነውን አይነኬም የኾነውን አስተምህሮ እውነትና ታሪክ በብርዓቸው ነጻ በማውጣትና ሰው ኹሉ እንዲያየውና እንዲያስተውለው፣ የኅሊና ፍርድም እንዲሰጥበት ለማድረግ ራሳቸውን አጋልጠው የሰጡ ሊቅ ናቸው። ቤተ ክርስቲያንም ያሉባትን ስሕተቶች እንድታርም ለማድረግ በየጽሑፎቻቻው ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። በዚህ ልዩ ሰብእናቸው ምክንያት አድናቂዎችና ተከታዮች ባያጡም፣ ብዙ ጠላትና ተቃማዊም አፍርተዋል።                                            
                                                   ዋቢ ጽሑፎች
ሐዲስ የሻነው (ዶ/ር)። ምዕላደ ትምህርት። ዐዲስ አበባ፦ አድመንት ፕሪንት፣ 2010 ዓም.።
ሥርግው ሀብለ ሥላሴ። “አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት።” (ያልታተመ) ዐዲስ አበባ፦ 1981 ዓ.ም.።
ሰሎሞን ጥላሁን እና ሥምረት ገብረ ማርያም። ደማቆቹ /ፀሓያተ ሌሊት/። ዐዲስ አበባ፦ ርሆቦት ፕሪንተርስ፣ 2000 ዓ.ም.።
አበበ ተሻለ። አውሎግሶን። ዐዲስ አበባ፦ ያሬድ ፕሪንቲንግ ፕሬስ፣ 2008 ዓ.ም.።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ። መዝገበ ፊደል የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ። ድሬዳዋ፦ ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት 1926 ዓ.ም.።
 አበገደ ፊደልና ፊደላዋርያ የልጆች አፍ መፍቻ። ድሬዳዋ፦ ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት፣ 1926 ዓ.ም.።
  መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ። ዐዲስ አበባ፦ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1948 ዓ.ም.።
 “ሃይማኖተ አበው ቀደምት” (ያልታተመ)
ኮሊን ማንሰል (ቄስ)። ትምህርተ ክርስቶስ። ዐዲስ አበባ፦ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ 1998 ዓ.ም.።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን። ሃይማኖተ አበው። ዐዲስ አበባ፦ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1986 ዓ.ም.።
 መጽሐፈ ቅዳሴ። ዐዲስ አበባ፦ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1984 ዓ.ም.።
ያሬድ ፈንታ (አለቃ)። ባሕረ ሐሳብ። ዐዲስ አበባ፦ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኀ.የተ.የግ. ማ.፣ 2004 ዓ.ም.።
ደስታ ተክለ ወልድ። ርብሐ ስም ወአንቀጽ። ዐዲስ አበባ፦ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1946 ዓ.ም.።
 ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት። ዐዲስ አበባ፦ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1962 ዓ.ም.።
ዳንኤል ክብረት። “የሌለውን ፍለጋ - ክፍል አንድ።”  29th October 2013. Accessed on 12 October 2018, 2.54 PM. www.danielkibret.com
ገብረ ሥላሴ (ጸሓፌ ትእዛዝ)። ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ። ዐዲስ አበባ፦ ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጠ፣ 2008 ዓ.ም.።
ጌታቸው ኃይሌ። አንዳፍታ ላውጋችሁ። ዐዲስ አበባ፦ ግራፊክ ዐታሚዎች፣ 2006 ዓ.ም.።
ጎርጎርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ። ዐዲስ አበባ፦ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ፣ 1974 ዓ.ም.።[1] ደስታ ተክለ ወልድ 1962፣ መግለጫ የሚለውን ይመለከቷል።
[2] አበበ ተሻለ፣ ፳፻፰ ዓ.ም. ገጽ 302።
[3] www.danielkibret.com 29th October 2013.
[4] (2010 ዓ.ም.፣ ገጽ 43።

[5] አበበ ተሻለ፣ ፳፻፰ ዓ.ም. ገጽ 300።

[6] 2006፣  ገጽ 56።

[7] ይህ አንቀጽ ከ1951 ዓ.ም. ጀምሮ በተግባር የቀረ ቢኾንም፣ እስከ ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ድረስ ግን ብዙዎች ድምፃቸውን ቢያሰሙም ከየመጽሐፉ ውስጥ ሳይሠረዝ ይታተም ነበር። በተጠቀሰው ጊዜ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ግን በቀጠይ ጊዜ እንዳይታተም ውሳኔ ተላልፏል። ውሳኔው የተላለፈበት ጊዜ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጋራ ጉዳዮች ከተወያዩና ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የተወሰነ በመኾኑ፣ ውሳኔው ከዚያ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደ ኾነ ታውቋል (አዲስ አድማስ ጋዜጣ የግንቦት 5 2009 ዓ.ም. ዕትምን ይመለከቷል)። 

[8] ደስታ ተክለ ወልድ 1946፣ ገጽ 4።


No comments:

Post a Comment