ከነቅዐ ጥበብ
ስለ እግዚአብሔር ወልድ በባሕርይ ፍጹምነትና በህላዌ (አኗኗር) ዘላለማዊነት ጸንቶ ያለው
ይሆዋ በመለኮት አሐድነት ላይ በተመሠረተ፥ በህልውናና በኩነት በተሰናሰለ ሦስትነት ራሱን እንደ ገለጸ መጽሐፍ ቅዱስ
ያስተምራል፡፡ ከሥላሴም እያንዳንዱ ህልው (ኗሪ) ለየራሱ እኔ የማለት መብት ያለውና በምልዐተ ህልውና የሚኖር እንደ ሆነ
እኔነቱንም የሚያሳቅውበት ህላዌ ኹነታውና (ኩነቱና) ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ተረጋግጦ መሰበኩ አሌ የማይባል በእምነት በተዘረጋ
እንደ መንፈስ የሚዳሰስና የሚጨበጥ እውነት ነው፡፡ ስለ ሆነም በዚህና በተከታታይ ዕትሞች፥ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ በመባል
ከሚመሰገኑት ሥላሴ በራሱ እኔ የማለት መብት ስላለው ስለ እግዚአብሔር ወልድ ተከታታይ ትምህርት ይቀርባል፡፡
መግቢያ
ክርስትና ከተሰበከበት ጊዜ ጀምሮ እንክርዳድን በመዝራት ንጹሕ የሆነውን የትምህርተ
ክርስትናን ስንዴ ጥራት ለማበላሸት በማቀድ በጠላት የተደረገው ሙከራ ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል (ማቴ. 13፥24-30)፡፡ ጠላት
እንክርዳድን በስንዴ መካከል የመዝራቱ ዐላማ ምን እንደ ሆነ የክርስቶስ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ከተረዳችውና በጥንቃቄ
ከተከታተለችው ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ የጠላት አፈ ሙዝ ምን ጊዜም ከክርስትና ትምህርት በተለይ ጌታ እግዚአብሔር ወልድንና ጌታ
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በሚመለከት ዶክትሪን ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሰዎች የኀጢአታቸውን
ስርየት በመቀበል ከኵነኔ የሚድኑት እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ በሰው ቦታ ተተክቶ የሰውን ኀጢአት በመሸከሙና በመቀጣቱ ነው፡፡
ስለ ሆነም ጌታ የተቀበለው ቅጣት ለኔ ስለ እኔ ነው በማለት የታመኑበት ብቻ እንደሚድኑ የተረጋገጠ ሆኗል (ዮሐ. 3፥14-18)፡፡ ይህን የወንጌል ማእከላዊ ምስክርነት በፍጥረታዊ ሰው ልብ ውስጥ በማስገባት መለኮታዊውንም ብርሃን
በመፈንጠቅ ይታመኑበት ዘንድ የሚረዳቸው ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው (1ቆሮ. 2፥10-13)፡፡ የአባባሉን እውነትነት
የምንቀበል ከሆነ ይዋጀው ዘንድ ቤዛው ሆኖ የሞተለትን ኢየሱስ ክርስቶስንና እንዲያምን የሚረዳውን መንፈስ ቅዱስን የሰደበ፥
የናቀ፥ ያቀለለ፥ ሰው በምን መንገድ ሊድን ይችላል? እንደዚህ ያለው ሰው መውጪያ ወደሌለው ዐዘቅት ውስጥ ወድቆ በጭንቅላቱ
የቆመ ሰውን ይመስላል (ማቴ. 12፥31-32)፡፡ ሰይጣን የራሱን ያህል ብቻ ሰው እግዚአብሔርን በማወቅ እንዲወሰን ቸል ቢልም፥
ሰው ከሰይጣን ተለይቶ ለእግዘአብሔር የሚሆንበትን የመዳኛውን መንገድ ሊዘጋበት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ስመ ክርስትና ካላቸው
ወገኖችም እንደዚህ ያሉ የክርስትናን ታሪካዊ ነገር ብቻ እንዲያምኑ ሰይጣን የለቀቃቸው ሰዎች መገኘታቸው ቢያስደንቅም የመኖራቸው
ጕዳይ ግን ርግጠኛ መሆኑ አያከራክርም፡፡
እስኪ ከክርስትና ውጪ የሆኑ ሃይማኖቶችን በአንድ ወገን፥ ስመ ክርስትናን ቢይዙም
በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትን ጌትነት ላይ በተመሠረተው ወንጌል ላይ ያልቆሙትን ሁሉ በሌላ ወገን በማሰለፍ
የትምህርቶቻቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ጐን ለጐን በማድረግ እናነጻጽራቸው፡፡ ይህን ብናደርግ ሁለቱም ወገኖች ስለ ክርስቶስ
የሚሰብኩአቸው ዶክትሪኖች በቅርጽና በመልክ የማይመሳሰሉ ናቸው የሚያሰኝ ፈሊጠኛ አቀራረብ ቢኖራቸውም፥ ከአንድ አባትና እናት
የተወለዱ ልጆችን ያህል የደም ጥልቀት ዝምድናቸው ፍጹም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አንባቢ ሆይ! የእግዚአብሔርን አምላክነትና የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ክዶ የሞተ ሰው
ድኗል ብሎ የሚመሰክረውን ለወደ ፊቱም የእግዚአብሔር ባሮች ልንባል፤ ሕጉንም ልንጠብቅ አይገባንም በማለት ያወጀውን ድርጅት
በምን ይሰይሙታል? ክርስቲያናዊ ወይስ አረማዊ? ክርስቲያናዊ ነኝ የሚል ድርጅት ነው ብንልዎ ምን ፍርድ ይሰጣሉ? ምናልባትም
የሃይማኖት ነጻነት ባይኖር ኖሮ እንደዚህ የሚል ሰው ምላሱ፥ እጁ፥ እግሩ፥ መቈረጥ፥ አፍንጫው መፎነን፥ አንገቱን መሰየፍ
አለበት በማለት በችኰላ እንደ ዳዊት ቢፈርዱ “ያ ሰው እኮ አንተ ነህ” የተባሉ እንደ ሆነ ያሳፍርዎታል (2ሳሙ. 12፥1-7)፡፡
ከዚህ ለመዳን የሚጠሩበትን ስመ ሃይማኖትዎን ሳይሆን ትምህርተ እምነትዎን በቅድሚያ በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈሱ ይመርምሩት፡፡
ምክራችንን ተቀብለው ቢመረምሩ ከአንድ አስተማማኝ ውጤት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ሰውን የወደደ እግዚአብሔር በኀጢአቱ ሞት
የተፈረደበትን ሰው ለማዳን በመለኮታዊ ጥበቡ ያገኘውና ያዘጋጀው ብቸኛ መንገድ አንድያ ልጁን ቤዛ (ተለዋጭ) አድርጎ መስጠት
እንደ ሆነ የሚመሰክረውን የእግዚአብሔርን ቃል (ዮሐ. 3፥16) በማስተባበል የተሰለፉትን ክርስቲያናዊና ኢክርስቲያናዊ
ሃይማኖቶችን ሁሉ ቀድሞ ምስጢር ከነበረውና ዛሬ ግን ቀስ በቀስ እየተገለጸ ካለው ከዐመፅ ሰውና ከትምህርቱ ጋር (2ተሰ. 2፥5-12)
ገና የስምምነት ውል ባይፈርሙም፥ ከአሁኑ ጀምሮ በአንድ ላይ ለመሥራት መጀመራቸውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም!
አንባቢን የሚያስደንቅ ሌላ ምስጢር ያልሆነና ሁሉ የሚያውቀው እውነተኛ ምልክት መኖሩን እንጠቁም፡፡ የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ በጠላትነት
የሚያዩት ማንን ወይም ምንን እንደ ሆነ አንባቢ ሆይ አስተውለው ይሆን?
ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የአምላክ ልጅ እውነተኛ የሰው ልጅ ነው (ኢሳ. 9፥6፤ ማቴ.
16፥16፤ ዮሐ. 6፥69)፡፡ “እርሱ በሞቱና በትንሣኤው ምንም ጕድለት የሌለበትን ደኅንነት አስገኝቶልናል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ
ካልሆነ የዘላለም ሕይወት የለም (ሮሜ 3፥21-31፤ ዮሐ. 3፥36፤ ሐ.ሥ. 4፥12)፡፡ የአበው ተስፋ፥ የሙሴና የነቢያት ሁሉ
ትንቢት ፍጻሜ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ሉቃ. 24፥44-47፤ ዮሐ. 5፥37-47፤ ሮሜ 10፥4) በማለት የምታምነውንና
የምትሰብከውን የክርስቶስን ጉባኤ (አቅሌስያን) ዓለማውያን ሃይማኖቶች ሁሉ ይጠሏታል፡፡ በዚህ ጕዳይ ሁሉ ለምን ተባበሩ? ብለው
ይጠይቁ፡፡
ለፍጥረታዊው (ዓለማዊ) ሰው ማታለያና መደለያ ይሆን ዘንድ አስቀድሞ በትንቢተ ነቢያት
ያልተቀየሰ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያልተመሠረተ በሐዋርያቱም ያልተሰበከ ልብ ወለድ ወንጌል፥ ወይም ባዕድ የሃይማኖት መጽሐፍ
በስመ ክርስትና ወይም በሌላ ስመ ሃይማኖት እያዘጋጀ የሰጠ ከጥንቱ ያ ጉደኛ ጠላት ዲያብሎስ ነበረ ወደ ማለት ያደርስዎታል፡፡
ለማታለል ሲል እንደማይገናኙ አስመስሎ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን አቋቁሞ በመበተን ሲሠራ ከቈየ በኋላ አሁን በፍጻሜ ዘመን
ሲያሰባስባቸው እናያለን፡፡ የተቀበሉትና የኔ የሚሉት ሃይማኖት ካለ አንባቢ ሆይ የርስዎ ሃይማኖት እስኪ ከዚህ ከዐመፅ ሰው
ምስጢር ጋር በምንና በምን እንደሚገናኝና እንደሚለያይ ይመርምሩ፡፡ ለነገሩማ ሃይማኖት የለንም ባዮችም የሚጠቃለሉት በዚሁ ፀረ
ክርስትና ክፍል መሆኑን አይርሱ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ሦስተኛ ረድፍ የለምና (ማቴ. 25፥31-46)፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት የታተመባቸው ምእመናን ከስሕተት ትምህርቶች ሁሉ
የሚጠበቁበት በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ የሰይጣንን ስውርና ግልጽ ሥራዎቹን የሚመረምሩበትና የሚቃወሙበት ብቸኛ መሣሪያ መጽሐፍ
ቅዱስ ነውና ስለ መሣሪያው ጥራትና ጠቃሚነት እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ባለፉት 2000 ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር ወልድንና
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በሚመለከት ሰይጣን በክርስትና ውስጥ ከበተናቸው እንክርዳዶች መካከል ከዚህ በታች የተጠቀሱትን
በመጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምራቸው በዝርዝር ባይሆንም አጠቃለን አቅርበናል፡፡ ክርስቲያን ካልሆኑ ሃይማኖታዊ ዶክትሪኖች ጋርም
ተመሳሳይነታቸው በምንና በምን እንደ ሆነ አንባቢ እያነጻጸረ እንዲያልፍ እናሳስባለን፡፡
1.
ሰባልዮሳውያን፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሦስት ህልዋን (ዃኞች) ስሞች
አይደሉም፤ አንዱ ህልው (ዃኝ) በተለየ ጊዜ እንደ አብ፥ እንደ ወልድ፥ እንደ መንፈስ ቅዱስ
አድርጎ ራሱን በማቅረብ ትርኢት ያሳየባቸው የመድረክ ስሞቹ ናቸው አሉ፡፡ ከእነዚህ ማሕፀን የወጡ ሌሎችም አሉ፡፡
1.1
በእኛ ዘመን ለየት ያሉ የሰባልዮሳውያን ውርጃዎች (በጭንጋፍነት የተከፈሉ)
ይገኛሉ፡፡ ከሰባልዮስ ትምህርት ወጣ በማለት ወልድ ከአብ በተለየ ምልዐተ ህልውና መታወቅ የጀመረው ከአብ በቃል አወጣጥ ተለይቶ
በድንግል ማሕፀን ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ነው ይላሉ፡፡ ከቀድሞዎቹ ሰባልዮሳውያን ወላጆቻቸው የሚለዩት በአብ ምልዐተ ህልውና በመካተት
የኖረው ወልድ በዘመነ ሥጋዌ ራሱን ችሎ (ጎጆ ወጥቶ) ከአብ የተለየ ምልዐተ ህልውና ገንዘብ ማድረጉን በመስበክ ነው፡፡
(ትምህርታቸው ኢ ክርስቲያናዊ ከሆኑ ሃይማኖቶች መካከል ከነማን ጋር ግንኙት እንዳለው አንባቢ ያነጻጽር)፡፡
1.2 መቅዶንዮስ የመንፈስ ቅዱስን በምልዐተ ህልውና መኖር ሳይክድ ከአብ ወልድ ያንሳል፥ ከወልድ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ያንሳል
ብሎ ነበር፡፡ የዘመኑ ሰባልዮሳውያን ግን መንፈስ ቅዱስ በአብ ምልዐተ ህልውና የተካተተ ራሱ የሆነ ምልዐተ ህልውና የሌለው
መለኮታዊ ኀይል ነው ይላሉ፡፡ (አንባቢ በስመ ክርስትና የሚሰበክ ይህ ባዕድ ወንጌል ኢ ክርስቲያናዊ ከሆኑ ክፍሎች ትምህርት
ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል ያነጻጽር)፡፡
2.
አርዮሳውያን፡- የወልድ አምላክነት እንደ አብ ባሕርያዊ
አይደለም፡፡ ከተፈጠሩ መላእክት አንዱ ሆኖ ሳለ በሹመት ንኡስ አምላክነትነት ተቀበለ በማለት ያስተምራሉ፡፡ ወልድ እውነተኛ
አምላክ ይሆዋ፥ ኤልሻዳይ፥ መነሻና መድረሻ የሌለው … በሚል ስምና ማዕርግ ሊጠራ አይገባውም ማለትንም ያክሉበታል፡፡ (ኢ ክርስቲያናዊ
ለሆኑ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በዚህ አባባል እንደ አባት የሚቈጠሩ መሆናቸውን አንባቢ ያስተውል)፡፡
2.1 ይሆዋ ዓለማትንና በውስጣቸው ያሉትን ፍጥረታት መፍጠር የቻለው ከለባዊነቱ
(ከልብ ከዊኖቱ) በሚያፈልቀው ባሕርያዊ ቃሉ አይደለም፤ እንደ ማምረቻ መሣሪያ የተገለገለበትን ቃሉን ከፈጠረ በኋላ በእርሱ ዓለም
ተፈጠረ ማለት ሌላው የአርዮሳውያን መታወቂያ (መለዮ) ነው፡፡ (ኢ ክርስቲያናዊ ከሆነ ከየትኛው ፍልስፍና የተወሰደ ትምህርት መሆኑን
አንባቢ ያረጋግጥ)፡፡
2.2
የዘመኑ አርዮሳውያን
መንፈስ ቅዱስ የይሆዋ መለኮታዊ ኀይል እንጂ የራሱ የሆነ ምልዐተ ህልውና የለውም ይላሉ፡፡ (ይህን በመስበክ ከዘመኑ ሰባልዮሳውያንና
ከሌሎች ኢ ክርስቲያናዊ ሃይማኖቶች ጋር (ከእነማን ጋር) ይተባበራሉ?
3.
አውጣኪያን፡- የአውጣኪ ተከታዮች አይደለንም የሚሉ ነገር ግን በትምህርታቸው
ይዘት ላይ የአውጣኪን ዐርማና ማኅተም ያተሙ ቡድኖች ዛሬም እንዳሉ ከትምህርታቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል በ19ኛ ምእት ዓመት በሀገራችን
“ካራ” የሚል ስም ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ካራ ማለትም ባህለ ሃይማኖታቸውን የሚያስፋፉት ተቃዋሚዎቻቸውንና ያልተሰበኩላቸውን ሰዎች
ሁሉ ከፍ ብሎ አንገቱን ዝቅ ብሎ ባቱን በመቍረጥ እንጂ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌላቸው
በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ “ቅጠል በጣሽ” የሚባሉ ናቸው፡፡ ቅጠል በጣሽ የተባሉትም እንደ አንድ ዛፍ ከሚቈጠረው ቅዱስ
መጽሐፍ ስለ ሥሩ፥ ስለ ግንዱ፥ ስለ ቅርንጫፎቹ፥ ስለ ፍሬዎቹ፥ ስለ አእላፋት ቅጠሎቹ
የማይገዳቸው፥ ከዛፍ አንድ ቅጠል እንደ መበጠስ ያህል ከቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ አንዲት ቃል ወይም ሐረግ ወይም ዐረፍተ ነገርን በጥሶ
በመውሰድ ተያይዞ ከተነገረበት ዐላማ ውጪ እንደ ሰይጣን የሚጠቅሱና ለባህለ ሃይማኖታቸው ድጋፍ ማድረግ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ዛሬም
የእነዚህ ቡድኖች ባህለ ሃይማኖት የሚጠበቀው “በካራ” ብቻ ነው፡፡
በአምልኮአቸው ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ዐልፎ ዐልፎ ቢጠራም አምልኮታቸው
አብዛኛውና ከፍተኛው ክፍል መናፍስትንና የሙታንን ነፍሳት በመጥራትና በመማጠን የድንጋይ፥ የዕንጨት፥ የብረታ ብረት ሥዕሎችን፥ ምስሎችንና ቅርጾችን በመሳለም፥
ለየተራራዎችና ኰረብታዎች ለቅርሳ ቅርስ ሥራዎችም አምልኮት ስግደትና ልመና በማቅረብ የተያዘ ነው፡፡ ከአረማውያን የተወረሰ
አምልኮ ባዕድን ከክርስትና መሰል ባህለ ሃይማኖት ጋር ቀላቅለው ፍናፍንት ለሆነ የአምልኮ ሥርዐት ይገዛሉ፡፡ ግን ከኛ ወዲያ
ክርስትና የለም ባዮችም እንደ ሆኑ አይዘነጋም፡፡
አስማተኛነት፥ ጥንቈላ፥ ሟርት፥ በጨሌ፥ በአድባር፥ የሚደረግ አምልኮት
ተደባልቆ የሚገኘው በዚሁ በካራ ባህለ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ነው፡፡ በዚህና በመሳሰለው መንገድ ሁሉ ከመናፍስት ጋር በመቈራኘታቸው
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትን የያዘው ወንጌል
በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በሚሰበክበት ቦታ መገኘት አይችሉም፡፡ አይወዱምም፤ የአምልኮትን መልክ ይዘው ኀይሉን የካዱ ናቸውና፡፡
በሰው ደም አፍሳሽነትና በነፍስ ገዳይነት እንዲመኩ የሚያደርጓቸው የተቈራኟቸው መናፍስት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ጥንታዊው ነፍሰ
ገዳይ ዲያብሎስ ነበርና፡፡ በርግጥ በሁለንተናቸው፥ በፈቃዳቸውና በዝንባሌቸው ሁሉ የሚንጸባረቀው ይኸው ስለ ሆነ ዘሩ የጸናባቸው
የዲያብሎስ ልጆች ናቸው ማለት ይቻላል (ዮሐ. 8፥44፤ 1ዮሐ. 3፥8-15)፡፡
3.1 አውጣኪያን
ዱሮ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነት አይክዱም ነበር፡፡ የፍጹም አምላክነትና የፍጹም ሰብእነት መገናዘብ (መወሐድ) ዘለዓለማዊ
እንደ ሆነና ያንደኛው አካላዊና ባሕርያዊ አቋም ወደ ሌላው አለመፍለሱን ለመቀበል ባለመታደል ይቸገሩ ነበር፡፡ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ
ሰብእነት በአምላክነቱ ተዋጠ ስለሚሉ መራቡን፥ መጠማቱን፥ መድከሙን፥ ማዘኑን፥ ማልቀሱን፥ የኀጢአትን ዋጋ
ለመክፈል፥ እየተሰማውና እያመመው የተቀበለውን መከራ ሁሉ ምትሐታዊ ያደርጉታል፡፡ በዚህም አስተሳሰባቸው ኀጢአታችንን በላዩ የጫነበት
እግዚአብሔር እኛ ልንቀጣ ይገባን የነበረውን ቅጣት ሁሉ ሙሉ በሙሉ በአግባቡ እንዲቀጣ አላደረገም ማለታቸው ስለ ሆነ፥ “ኰናኒ
በጽድቅ ፈታሒ በርትዕ የሚፈርድበትን በእውነት የሚፈርድለትንም ባልተዛባ ቅንነት (ቀጥተኛነት) ያለ አድልዎ ያለ ማስመሰል
በሚፈርደው” በእግዚአብሔር ዙፋንና ችሎት ሲቀልዱ ኖሩ፡፡
3.2
አውጣኪያን፡- ብሉይ ኪዳን የወልድ አስተርእዮት አይደለም፤ የአብ ብቻ እንጂ በማለት በስመ ክርስትና ከሚጠሩ
ከአርዮሳውያንና ኢ ክርስቲያናዊ ከሆኑ ሌሎች ሃይማኖታውያን ድርጅቶች ጋር በዚህ ረገድ ተመሳስለዋል፤ በአንድ ላይም
ተሰልፈዋል፡፡
3.3
የጌታ የኢየሱስ
ክርስቶስ መሠቃየትና መሞት በውርስ ከአዳም ለመጣ ኀጠአት ብቻ ነው ይላሉ የአውጣኪ ተከታዮች፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለት ዕለት ስለሚሠሩት
ኀጢአት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ አዳኝ ወይም ከኀጢአት የሚያነጻ ሌላ ኀይል ይፈልጋሉ፤ ያበጃሉ፡፡ “የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ
ደም ከኀጠአት ሁሉ ያነጻናል” የሚለውን ዐዋጅ ያልተቀበሉት ይመስላል፡፡
3.4. የኀጢአት ደመ ወዝ ሞት እንዳልሆነ ያህል በዓለም ላይ ያለ ሁሉ ለሰው ነፍስ
ቤዛ መሆን ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ በዘመነ ሐዲስ ኪዳን እየኖሩ ከኦሪታውያንና ከአረማውያን ጋር በዚህ በኩል ያብራሉ፡፡
3.5. ከኀጢአትና
ኀጢአትን ተከትሎ ከመጣው ኵነኔ መዳንና መጽደቅን እና ለበጎ ሥራ የሚከፈል ዐስብን (ዋጋን) የአውጣኪ ልጆች ያደባልቋቸዋል፡፡ አማኒም
ሆነ ኢአማኒ ለሠራው መልካም ሥራ የሚገባውን ዋጋ መቀበሉ ወይም በሠራው ክፉ ሥራ መቀጣቱ ኀጢአትን የመደምሰስ ወይም የማስኰነን
ኀይል እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ፥ ሙሴና አሮን እነርሱም ይመሯቸው የነበሩት ያ ትውልድ እስራኤል ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሳይደርሱ
ባለመታዘዛቸው ጠንቅ በምድረ በዳ እንዲቀሩ በእግዚአብሔር ውሳኔ ተቀጡ፤ ሆኖም ተኰነኑ ማለት አይደለም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብሎ
ለተቸገረ ድኻ ቢያበላ ቢያጠጣ፥ ቢያለብስ ሌላም የርኅራኄን ሥራ ቢሠራ የማንም ባለዕዳ ያልሆነ እግዚአብሔር ዋጋውን አያስቀርበትም፤
ጸደቀ ማለት ግን አይደለም፡፡ ስለ ሆነም የአውጣኪ ልጆች በጠቅላላው የሰው መጽደቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለሚታመኑ ብቻ
እንደ ሆነ አያምኑም፡፡
3.6. ክርስቲያኖች ሁሉ ለኀጢአት አንድ ጊዜ የሞተውንና ለእግዚአብሔር በሕይወት ይኖር
ዘንድ የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱና በሕይወቱ ለመምሰል በጥምቀት ቃል ኪዳን እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት የክርስቶስን
ሞት ሞቴ ነው ብለው ሞቱን በሚመስል ሞት ለመሞት ወደ ውሃው ጠልቀው፥ ትንሣኤውንም ትንሣኤዬ ነው በማለት ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ
ለመነሣት ከውሃ ወጥተው ከእንግዲህ ወዲህ ለዓለምና ለሥራዋ ከክርስቶስ ጋር ሞቼአለሁ፤ ለጽድቅና ለቅድስናም እኖር ዘንድ ከጌታዬ
ጋር ተነሥቻለሁ ሲሉ ያስታውቃሉ፤ ይመሰክራሉ (ሮሜ 6፥3-10)፡፡
እነዚህ ክርስቲያኖች ከኀጢአታቸው ሊያድናቸው በሞተውና ሊያጸድቃቸውም በተነሣው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ (ሮሜ
4፥23-25) በማመናቸው ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረዋልና (ዮሐ. 5፥24-25) በእምነት በተቀበሉት የትንሣኤ ሕይወት ጌታን እያከበሩ
ይኖራሉ፡፡ ሩጫቸውን ጨርሰው ቢያንቀላፉም ቀደም ሲል ትንሣኤ መንፈስን እንደ ተቀበሉ ሁሉ በጌታ ቀን የሥጋ ትንሣኤን በመቀዳጀት
ጌታን መስለው ይነሣሉ (1ተሰ. 4፥14)፡፡
ከአውጣኪ ተከታዮች መካከል አብዛኛዎቹ ይህን በእግዚአብሔር ፊት በጉባኤውም መካከል የገቡትን ቃል በመናቅና
በማቃለል ከክርስትናቸው ጋር አቀላቅለው በያዙትና በሚገዛቸው (አረማዊ) ባህል ተሸንፈው “ከክርስቶስ ጋር በመሞትና በመነሣት የሚያሳትፈኝ
ጥምቀትና ለዚህም ያበቃኝ እምነት ወደ ፍጹም መዓርገ ጽድቅ አያደርሰኝም” ብለው ይክዳሉ፡፡ አያይዘውም “ራሴን በማስጨነቅ መዳንንና
መጽደቅን ገንዘብ ማድረግ አለብኝ፤ እኔ ለራሴ በራሴ ሞትን በሚመስል ሞት እሞታለሁ” በማለት ለሁለተኛ ሞት ራሳቸውን ይገንዛሉ፤
ያስገንዛሉ፡፡ ትንሣኤና ሕይወት የሌለበት የሞት ሞት መሆኑ ነው!!
በመሠረቱ ጥምቀት አንዲት ብቻ የሆነችበት ምክንያት (ኤፌ. 4፥4-6) በመንፈሳዊ ትርጓሜዋ አንድ ጊዜ መሞትንና
አንድ ጊዜ መነሣትን በማመልከት፥ ኀጢአትን ለማስወገድ የተሠዋው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አንድ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ
መሆኑን ስለምትገልጽ ነውኮ!!
የአውጣኪ ልጆች ይህን ሁሉ ባለማስተዋል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ሁል ጊዜ በሥጋቸው ይገለጥ ዘንድ
አንድ ጊዜ የተፈጸመውን ሞቱን በሥጋቸው ተሸክመው መኖር ሲገባቸው (2ቆሮ. 4፥10-11) እንዲህ ሆኖ ለመኖር በጥምቀት የገቡትን
ቃል ኪዳንና በቃል ኪዳኑም የተሸከሙትን የጌታን ሞት ረግጠው ሁለተኛ ሞትን ለመሞት መረጡ፡፡ በፈቃዳቸውና በምርጫቸው የሁለተኛ ሞት
ወይም የሞት ሞት ሟቾች ሆነዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቃል ከሆነ ክርስቲያን ሊባሉ ባልተገባ ነበር፡፡ ለሌላ ቃል ኪዳን የጥምቀትን
ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና፡፡
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ወልድ ዐማኑኤል እያለ ለየአግባቡ ተስማሚ በሆነ ስም ስለሚጠራው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውን በትክክል እንታመንበትና በመጽናትም እናድግበትና እንኖርበት ዘንድ ከዚህ በላይ
በተገለጹት ኑፋቄዎችና ክሕደቶች ተቃራኒ በሆነ ንጽጽር እንመረምረዋለን፡፡
በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment