Saturday, March 16, 2013

መሠረተ እምነት


ካለፈው የቀጠለ
ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው?

ኢ ክርስቲያን ከሆኑ ወይም ስንዴን መስለው ያሳስቱ ዘንድ በስንዴ ዕርሻ ውስጥ እንደ ተዘራ እንክርዳድ ዐይነት የእምነታቸው ሥርና መሠረት አረማዊነት ሆኖ ሳለ ጠላት ወደ ክርስትና አስርጎ ከአስገባቸው ክርስትና መሰል ባህለ ሃይማኖትን ከያዙ ግለ ሰቦች ወይም ቡድኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ለመማር መሞከር የብርሃንን ድምቀት እንዲነግሩን ወይም የቀለም ዐይነቶችን እንዲለዩልን ዓይነ ስውራንን እንደ መጋበዝ ይቈጠራል፡፡

ይልቁንም ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋና በመንፈስ ዐይን ካዩት፥ ሞቱን ሞተው ሕይወቱን ከኖሩት ቅዱሳን ምስክርነት የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት መማር ተገቢና ብቸኛም መንገድ ይሆናል፡፡


የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ለሚጠይቁ ሁሉ በቅንነት የሚስተዋሉ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ ወንጌላዊ ዮሐንስ ይናገራል፥ ይዘረዝራልም (ዮሐ. 5፥31-47)፡፡ የሚሰማና የሚቀበል ካለም ከተዘረዘሩት ማስረጃዎች እጅግ ብልጫ ያላቸውን አስረጅዎች ለይቶ ያቀርባል፤ እነርሱም ጌታ እግዚአብሔር አብና ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ናቸው (ዮሐ. 1፥33-34፤ 5፥37፤ 15፥26-27)፡፡

ዮሐንስ ወንጌሉን ለመጻፍ ሲጀምር፥ “ቃል አስቀድሞ ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሏል፡፡ በወንጌላዊው የተሰበከውና በመጽሐፍም የሰፈረው ይህ ምስክርነት በሦስት ታላላቅ ክፍሎች የተብራራ ትንተናዊ መግለጫ ሊቀርብበት ይችላል፡፡

አንደኛ፡- “ቃል አስቀድሞ ነበረ” ሲል የቃል ህላዌ (አኗኗር) ከጊዜ በፊት እንደ ሆነ ለህላዌውም ጅማሬ እንደሌለው ያስተምራል፡፡ በዐጭሩም የነበረ ያለና የሚኖር (ዘቅድመ ሀሎ ወይሄሉ) የሁሉ መነሻና መድረሻ አልፋና ዖሜጋ) ቀዳሚ ወደኃሪ እንደ ሆነ ተስተውሎ ይታመንበታል (ዘፀ. 3፥14፤ ኢሳ. 43፥13፤ 44፥6፤ ራእ. 1፥17-18)፡፡

ሁለተኛ፡- “ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በማለቱም ቃል ከቀድሞ ጀምሮ የራሱ በሆነ ህላዌና ከዊን ከአብ በተለየ ምልዐተ ህልውና (ፐርሰናሊቲ) በአብ ዘንድ በአብ አጠገብ ከአብ ጋር በአንድ መንበር ከጥንት ጀምሮ እንደ ኖረ ይነግረናል፡፡ በአሐዳዊ መለኮት ይሆዋ በተለየ ምልዐተ ህልውና (ፐርሰናሊቲ) ቃል ሆኖ እንደ ኖረ ለማስረዳት የቃልነት ስምን ገንዘብ ቢያደርግም የራሱ የሆነ ምልዐተ ህልውና (ፐርሰናሊቲ) የሌለው እንዳይመስለን ያስጠነቅቀናል ማለት የሰው ቃል በዚያው ሰው አካል ውስጥ ባልተለየ ህላዌ እንደሚኖር ዐይነት እንዳናስብ በአብ ምልዐተ ህልውና ውስጥ ያልተካተተ እና የማይጠቃለል በራሱ እኔ የማለት መብት ያለው እንደ ሆነ በአጽንዖት ያስገነዝባል (ዮሐ. 1፥1-3፡11፡14-18፤ 17፥6)፡፡

ሦስተኛ፡- “ቃል እግዚአብሔር ነበረ” ሲልም በአጠገቡ ከሚኖረው ከእግዚአብሔር አብ ባነሰ ደረጃ አለመኖሩን እያስተማመነ እንደ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ ሆኖ እግዚአብሔር አብ የሚሠራውን ከእርሱ ጋር እየሠራ ለእግዚአብሔር ሊቀርብ የሚገባውን ክብር ውዳሴ ስግደት አምልኮት በአንድነት እየተቀበለ ለመኖሩ ማረጋገጫ ይሰጠናል (ዮሐ. 17፥5፤ ፊል. 2፥6)፡፡

ሥርዐተ ተፈጥሮና በውስጡ ያለ የሚታየውና የማይታየው ሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ በኖረው በዚህ “ቃል” መፈጠሩን ወንጌላዊ ዮሐንስ አከታትሎ ጽፎአል (ዮሐ. 1፥1-3)፡፡ ይህን ያህል ጠንካራ የትምህርተ እምነት መሠረት በልባችን ውስጥ በጥልቀት ካስቀመጠ በኋላ ይኸው ወንጌላዊ “ቃል” ሰው ሆኖ በሰው መካከል እንደ ተመላለሰ በማብራራት ያስከትላል (ዮሐ. 1፥14)፡፡

ለመሆኑ ወልድ (ቃል) በብሉይ ኪዳን አልተገለጸምን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አጠገብ ያስተምር በነበረበት ጊዜ (ዮሐ. 8፥20) አይሁድ አንተ ማነህ? ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ” ነበረ መልሱ፡፡ ከጥንቱ ከጧቱ ለእናንተ ተናግሬ የነበርሁት እኔ ነኝ እኮ! እንዴት ትጠይቁኛላችሁ? ማለቱ ነበረ፡፡ ይህ አነጋገር በአንዳንድ መተርጕማን በልጅነቱ ወራት በቤተ መቅደስ ለምሳሌ በሉቃስ 2፥42 እንደ ተጻፈው ወይም አርባ ቀን ከጾመ በኋላ ለምሳሌ በናዝሬቱ ምኵራብ በሉቃስ 4፥16-22 እንደ ተገለጠው፤ ወይም ወንጌላት ውስጥ ባልተጠቀሰ ሌላ ጊዜና ስፍራ ራሱን ለአይሁድ ገልጾ የነበረበትን ሁኔታ ሲያስታውሳቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ ይህ ግን አርኪ ትርጓሜ አይደለም፡፡

አነጋገሩ ግልጽ አይደለም ተብሎ እንዳይታለፍም “እኔ እንደ ሆንሁ ባታምኑም በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁ” ብሏቸዋልና ሞትን ወይም ሕይወትን በራስ ላይ የሚያመጣ ቍርጥ ውሳኔ ሊደረግበት የሚገባ የመዳን ወይም ያለመዳን ቍልፍ በዚህ ቃል ውስጥ ስላለበት ሊታለፍ አይገባውም፡፡ አይሁድ አብርሃምን ያህል የሥጋ አባት ቢኖራቸውም የሕግና የሥርዐተ ኦሪት አበጋዞች ቢሆኑም፥ ኢየሱስ ማን እንደ ነበረ አስተውለው እርሱ ያ የጥንቱ ተናጋሪያቸው እንደ ነበረ ባያምኑም አለን ከሚሉት ምድራዊ በረከት ሁሉ ጋር በኀጢአታቸው ምክንያት በሥጋ ወደ መቃብር በነፍስ ወደ ሲዖል መውረድ አይቀርላቸውም፡፡ ኧረ አይሙቱ! ከመሞትስ ያ ጥንት የተናገራቸው እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ቢያስተውሉና ቢቀበሉት ይበጃቸዋል!

የዚህን የወንጌለ ዮሐንስን ምዕራፍ ስምንትን እስከ መጨረሻው ደጋግመን አንብበን ብንመረምረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመናገር የፈለገው፥ “ከመጀመሪው ጀምሮ ሲናገራቸው የነበረው ሌላ እንዳልነበረና ቅድምናው በባሕርዩ ያለ የአብ ባሕርያዊ ቃል የራሱ የሆነ ምልዐተ ህልውና ያለው ወልድ እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ለአይሁድ እያስረዳቸው እንደ ነበረ ከምንባቡ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለእስራኤላዊነታቸው እንደ መነሻ ሆኖ የሚታወቀው የአባታቸው የያዕቆብ (በኋላ እስራኤል የተባለው) አያት የሆነው የአብርሃም ጥሪ ስለ ነበረ እነርሱ በአብርሃም አባትነት ተመኩ፡፡ ቍጥር 33 በሥጋ የአብርሃም ልጆች ቢሆኑም ለአብርሃም መንፈሳዊ ልጆቹ ለመሆን መስፈርቱን እንዳላሟሉ ጌታችን ነገራቸው (ቍጥር 39-40)፡፡

አብርሃም ቀኔን አይቶ ሐሤት አደረገ አላቸው፡፡ ቊጥር 56 እንዲሁም በቊጥር 58 አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ ብሏቸዋል፡፡ የእስራኤላዊነት መነሻ የአብርሃም በይሆዋ መጠራቱ በይሆዋ ቃል መታመኑ እምነቱ በይሆዋ ዘንድ ጽድቅ ሆኖ መቈጠሩ ነውና በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለተነሣው ክርክር አሸናፊ ለመሆን አይሁድ 5 ጊዜ ጌታ ኢየሱስም 6 ጊዜ አብርሃምንና ሥራውን ለምስክርነት ቈጠሩ፡፡

በይሆዋ ለተጠራው አብርሃም ደስ የሚያሰኙ ብዙ ተስፋዎችና ኪዳኖች ተሰጥተውት የነበረ ቢሆንም ሌሎቹ ሁሉ አብርሃም በይሆዋ ታመነ፥ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት ከሚለው ቃል ጋር በደረጃቸው አይመጣጠኑም በሥራው በገንዘቡ፥ መላ ዕድሜውን ዓለምን በመዞር ሊያገኘው አይችል የነበረውን ጽድቅ (መጽደቅ) ይሆዋ ሲሰጠውና ያለምንም ሥራና ክፍያ በይሆዋ ጸጋ የተሰጠውን ጽድቅ የራሴ ነው ብሎ እንዲቈጥረው ማረጋገጫውን በልቡ ሲያትምለት ከሚገኘው ደስታ ጋር የሚወዳደር መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ስጦታ ከቶ የለም፡፡ (ሮሜ 4፥1-5) የጸደቀ ተክል ለመጽደቁ ማረጋገጫ የሚሆነውን የእምነቱን ፍሬ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ማፍራቱ በአብዛኛው በይሆዋ እንደ ተወሰነ እንደ ተፈጥሮ ሥርዐት ሕጋዊነት ሊወሰድ ይችላል፡፡ እንደዚሁም እስማኤልን ከመውለዱ በፊት ጽድቅ የተቈጠረለት አብርሃም እስማኤል በተወለደ በ15 ዓመቱ ይሥሐቅ ከሚስቱ ከሣራ እንደ ተወለደለት ታውቋል፡፡ ይሥሐቅም አድጎና ጐልምሶ የመሥዋዕት ማቃጠያ ዕንጨት ተሸክሞ ወደ ሞሪያ ተራራ ለመውጣት በሚችልበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ማለት አብርሃም ጽድቅ ከተቈጠረለት በኋላ እጅግ ዘግይቶ ይሥሐቅን ለመሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ያጸደቀው እምነቱ ፍሬን አሳየ (ያዕ. 2፥20-24)፡፡ አብርሃም አሻግሮ የተመለከተውና ሐሤትን የሰጠው (በወንጌል “አብርሃም ቀኔን አየ” ተብሎ የተገለጸው) የኢየሱስ ዕለት የቱ ነበር? ቢባል አግባብ ያለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ ያ ዕለት አብርሃም ደካማውን በሚያጸድቀው በይሆዋ የታመነበትና ጽድቅን የተቀበለበት ቀን ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ ለመጽደቅ ደግሞ ሰውን የሚያስኰንነው ኀጢአት ዋጋው ወይም ቅጣቱ መከፈል ነበረበት፤ ይህም ማለት የሰውን ሁሉ ኀጢአት ተሸክሞ ጌታ ኢያሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን የሰጠበትና ለሚታመኑበት ሁሉ ይሆዋ ጽድቃችን የተገለጸበት ዕለት (ኢሳ. 45፥25፤ ኤር. 23፥6)፡፡ ለሰው ሁሉ የሐሤት ማግኛው ምንጭ ስለ ሆነ ያን ዕለት አብርሃም አሻግሮ አየውና ሐሤት በልቡ አፈሰሰለት፡፡

እንግዲህ ከጥንት ጀምሮ ለእስራኤል አባቶች ሲናገር የነበረና ቤዛ ሆኖ ወደሚሠዋበት ዕለት እነርሱንና ልጆቻቸውን እየመራም አሻግረው እንዲያዩትም እያመለከተ በሥጋ ወደሚገለጽበት ወራት ያደረሰ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ ስለ ሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እነርሱ ከመጀመሪው አንሥቶ የሆነውን ሁሉ የመናገርና ባልተቀበሉትም ላይ የመፍረድ መብት ሥልጣንም ችሎታም እንዳለው ሊያውቁ ይገባቸዋል (ዮሐ. 8፥26)፡፡

1. በአርኣያ መልአክ (መልእክተኛ) ተገልጿል

ወልደ እግዚአብሔር በዘመነ አበው ከዚያም በዘመነ ብሉይ ኪዳን በአርኣያ መልአክ ተገልጿል ሲባል፥ ወልድ በዚያን ጊዜ መልአክ የሚባለው ፍጡር ነበረ ማለት አይደለም፤ ተወዳጅ ልጅ ለሚወደው አባቱ እሺ በጄ! ብሎና ፈቃድ ፈጻሚ መልእክተኛ ሆኖ ተገልጾ የነበረ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ “መልአክ” የሚለውን ቃል የሚወልደው አርእስት ወይም ዘር “ልኢክ ልኢኮት” መላክ፥ መስደድ ማለት እንደ ሆነ የግእዝ መዝገበ ቃላት ያብራራል፡፡ ፈንዎ ፈንዎት ለሚባለው የግእዝ ቃልም ተመሳሳይ እንደ ሆነ ከመዝገበ ቃላቱ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ፡-
-   ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “አቡየ ፈነወኒ - አባቴ ላከኝ” አለ፡፡
-   ሊቃውንትም “አብ ፈነዎ ለበኵሩ ውስተ ዓለም” “አብ ቀዳሚና ተከታይ የሌለውን ልጁን ወደ ዓለም ላከው” አሉ፡፡
-   አባቶቻችንም በምስጢረ ሥላሴ አብ ፈናዊ ወልድ ተፈናዊ - አብ ላኪ ነው፤ ወልድም ተላኪ (መልእክተኛ ነው) አሉ፡፡

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ወልድ ሰብእነትን ተገንዝቦ (ገንዘብ አድርጎ) በሰው መካከል በተመላለሰ ጊዜ (በሐዲስ ኪዳን) ተገለጸ ማለት ይቻላል እንጂ ከዚያ በፊት (በዘመነ ብሉይ) አልተገለጸም ይላሉ፡፡ በአርኣያ መልአክ (በመልእክተኛነት) የተገለጸባቸውን የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች እንደ ጦር ከሚፈሯቸው መካከል አርዮሳውያን ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች ናቸው፡፡ በመልእክተኛነት (በአርኣያ መልአክ) የተገለጸውን ማንነት ጥቅሶቹ ሲያብራሩ “እርሱ ራሱ ይሆዋ እንደ ሆነ በመተርጐም ስለሚያቀርቡትና የኢየሱስ ክርስቶስን (የወልድን) ፍጹም አምላክነት ስለሚያረጋግጥባቸው የእነርሱ ዳጎን (ዶክትሪን) በእግዚአብሔር ቃል ማደሪያ (ታቦት) ፊት ሊቆምላቸው አይችልም፡፡

መልአክ፥ ልኡክ፥ ተፈናዊ (የተላከ) መባልና በመልክተኛነት መገለጽ ለተወዳጅ ልጅነቱ (ለወልድነቱ) ብቻ ሳይሆን ለቃልነቱ (ቃል ለመባሉም) ተስማሚ ነው እንጂ “ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም” ይላልና (መዝ. 106/107፥20)፡፡ ስለ ሆነም እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዌ በፊት በአርኣያ መልአክ (በመልእክተኛነት) የተገለጸባቸውን ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣን እንመርምራቸውና ወልድ በብሉይ ኪዳን እንደ ተገለጠ እናረጋግጥ፡፡
1.1     ዘፍ. 16፥7-14፡፡ የሦራ አገልጋይ አጋር ከእመቤቷ ከሦራ ኰብልላ በተሰደደችበት በረሓ መልአከ እግዚአብሔር ተገለጠላትና ወደ እመቤቷ እንድትመለስ አዘዛት፡፡ ያ በአርኣያ መልአክ (በመልክተኛ አምሳያ) ወደ አጋር የተላከውና እርሷም ያየችው ማን እንደ ነበረ ራሷ ታስረዳ ቢባል “ኤል ሮኢ” ትለናለች፡፡ ምን ማለቷም እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያብራራ “የሚያየኝን አየሁትን?” ለማለት የይሆዋን ስም “ኤል ሮኢ” አለች ይለናል፡፡ ያያትና ያየችው እንደ ይሆዋ መልእክተኛ ሆኖ ተገልጾላት ነበር፡፡ ሆኖም ያያት እርሱ ብቻ አልነበረም፤ እርሷም አየችውና የማንነቱንም ውስጠ ምስጢር ተረዳችና ይሆዋ እንደ ሆነ ዐወቀች፡፡ ለይሆዋነቱም ተስማሚ ስም በመስጠት “ኤል ሮኢ” ብላ ጠራችው፡፡ “ይሆዋ” የሚለው ስም ከፈጣሪ በቀር ፍጡራን ሊጠሩበት የማይገባ፥ የነበረ፥ ያለና የሚኖር፤ እንደ ተናገረው የሚሠራ ማለት ስለ ሆነ በዚህ ስም ከፍጡራን መላእክት መካከል ማንኛውም መልአክ አይጠራበትም (ዕብ. 1፥4)፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን መዝገበ ቃላት ገጽ 514 ይመልከቱ፡፡

1.2   ዘፍ. 31፥11-13፡፡ ያዕቆብ በአጎቱ በላባ ቤት በካራን ከኖረ በኋላ ልጆቹንና ሀብቱን ይዞ ወደ ወገኖቹ ለመመለስ ሲዘጋጅና ምክንያቱን ለእኅትማማች ሚስቶቹ ሲያስረዳ፥ ዕቅዱ በይሆዋ መልአክ እንደ ጸደቀ አረጋገጠላቸው፡፡ ያን በአርኣያ መልአክ (በመልአክ አምሳያ) የተገለጠለትን መልእክተኛ ያዕቆብ በሚገባ ተረድቶት ነበረ፤ “በቤቴል የተገናኘሁህና ስለት የተሳልህልኝ አምላክህ ነኝ” ብሎታልና፡፡ በቤቴል ስለ ተገናኘው አምላክ ወደሚተርከው ዘፍ. 28፥10-18 ተመልሰን ስናነብ በቤተል በሕልሙ የተገናኘው አምላክ “እኔ የአባትህ የአብርሃም የይሥሐቅ አምላክ፥ ይሆዋ ነኝ” ብሎት እንደ ነበረ እናነባለን፡፡ በካራን በአርኣያ መልአክ (በመልአክ አምሳያ) ሲገናኘው “የአባቶችህ አምላክ ይሆዋ እኔ ነኝ” ያለውና በቤቴል “እኔ ይሆዋ የአባቶችህ አምላክ ነኝ” ሲል የተዋወቀው ያው አንዱ ይሆዋ እንደ ሆነ ያዕቆብ ተረድቶት ነበረ፡፡ ይህን የይሆዋ አስተርእዮት (መገለጥ) እንደ ሆነ የተረዳበትን ታሪክ ያዕቆብ ለሚስቶቹ ሲመሰክርላቸው ተገላጩ የተገለጸበትን አርኣያ መልአክ (የመልአከ አምሳያ) እያስታወሰ “መልአከ እግዚአብሔር” ብሎታል፡፡ ከዘፍ. 31 በተለይ ቍጥር 3 እና 11 ይመልከቱ፡፡

1.3  ዘፍ. 48፥15-16፡፡ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች ምናሴንና ኤፍሬምን ሲባርክ ቃለ ቡራኬው እንዲህ የሚል ነበረ፡፡

“አባቶቼ አብርሃምና ይሥሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” አለና መረቃቸው፡፡ ያዕቆብ በቃለ ቡራኬው “እግዚአብሔር የእግዚአብሔር መልአክ እያለ ሲጠራ ሁለት የተለያዩ ህልዋንን (ኗሪዎችን፥ ዃኞችን) ማለት ይሆዋንና ፍጡር መልአክን አለማለቱ እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ሁለት ህልዋን ቈጥሮአቸው ቢሆን ኖሮ “እና” የሚል መስተጻምርን በማስገባት ባጫፈራቸው ነበር፡፡ ማሰሪያ አንቀጹንም ለአንድ ህልው (ዃኝ) ተስማሚ የሆነ ግሥን በመጠቀም “ይባርካቸው” በማለት ፈንታ ለብዙ ህልዋን እንዲስማማ “ይባርኳቸው” ባለ ነበር፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር፥ መልአክ እያለ የጠራውን “እርሱ” በማለት አንድ ብቻ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡

ማስገንዘቢያ ከላይ በተራ ቍጥር 1.1 እና 1.2 እንደ ተብራራው ያዕቆብ ባለፈው የሕይወት ጕዞው ከቤቴል እስከ ጌሤም ዐብሮት እየተጓዘ የጠበቀውና የመራው ራሱ ይሆዋ እንደ ሆነ፥ ነገር ግን በይሆዋ መልእከተኛ አምሳል (በአርኣያ መልአከ እግዚአብሔር) እንደ ተገለጸለት ቢረዳም የይሆዋ ሥልጣነ መለኮትና ክብር እንዳለውም በሚገባ አስተውሎታል፡፡

1.4  ዘፀ. ምዕራፍ 3 እስከ ምዕራፍ 6 ከግብጽ በመኰብለል ወደ ምድያም ተሻግሮ አርባ ዓመታትን ያሳለፈው ሙሴ በኮሬብ ተራራ እግርጌ በጎቹን አሰማርቶ በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን በተራራው ላይ አስደናቂ ትርኢት እንደ ተመለከተ በመተረክ ይጀምራል፡፡ ትርኢቱም የእሳት ነበልባልና የእሾህ ቍጥቋጦ መወሐድ እንደ ነበረ ይገልጻል፡፡ በእሳቱ ነበልባል ያልተቃጠለው ቍጥቋጦና በቊጥቋጦው ርጥበት ያልጠፋው የእሳት ነበልባል ሁኔታ ያስደነቀው ሙሴ ምንነቱን ለመመርመር ሲጠጋው ከሚነደው ቍጥቋጦ መካካል የይሆዋን መልአክ አየ፡፡ የሰማው ድምፅ ግን፥ “እኔ የአብርሃም የይሥሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” የሚል ነበር፡፡ በዘላለማዊ ስሙም “ያለና የሚኖር፥ ዘሀሎ ወይሄሉ” እባላለሁ አለና ሙሴን ተዋወቀው ከም. 3፥1-16፡፡

በመቀጠልም ለነአብርሃም “ኤልሻዳይ ሁሉን ቻይ፥ (ዘይክል ኵሎ ወአልቦ ዘይሰአኖ ይሉታል አባቶች) ስሙ ተዋውቋቸው የኖረው ሌላ ሳይሆን እርሱ ራሱ እንደ ነበረም ተረከለት፡፡ በዚህ ጊዜ ለሆነው አስተርእዮቱ (መገለጡ) እና በመገለጡም ለሚፈጸመው ሥራ በባለቤትነት የሚታወቅበት መጠሪያው “ይሆዋ” እንደ ሆነ አክሎ ነገረው ከም. 6፥2-3

ለነአብርሃም በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት ለእስራኤል ልጆች ምድረ ከነዓንን ያወርሳቸው ዘንድ በእርሱ መሪነት በአስደናቂ ተኣምራቱ ከግብጽ እንደሚያወጣቸው ቃሉን በማደስ አጸናለት (6፥4-6)፡፡ “እኔ ከአንተ አፍና ከአሮን አፍ ጋር እሆናለሁ፤ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ” (4፥15) አላቸው፡፡

ማስገንዘቢያ
ይሆዋ በአርኣያ መልአክ ለሙሴ የተገለጸበትን ታሪክ በሐዲስ ኪዳን እስጢፋኖስ ሲተርከው በቍጥቋጦ መካከል ለሙሴ የታየው መልአክ እንደ ነበረ ከተናገረ በኋላ፥ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም የይሥሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው ሲል መስክሮአል (ሐ.ሥ. 7፥30-34)፡፡

1.5  ዘጸ. 33፥1-4 ይሆዋ በሙሴና በኦሮን አማካይነት የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ አውጥቶና ቀይ ባሕርን አሻግሮ በምድረ በዳውም እየመራ በሲና ተራራ እግርጌ እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡ ሙሴንም ወደ ተራራው ጠራውና ሕግን ሰጠው፡፡ ሕዝቡ ግን በአሮን ጥበቃ ሥር ቈዩ፡፡ 40 ቀን በተራራው ላይ የቈየው ሙሴ ሕግ የተጻፈባቸውን ሁለት ጽላትና ሌሎቹንም የመተዳደሪያ ደንቦችን ተቀብሎ ወደ ወገኖቹ ሲመለስ በተራራው ሥር የሰፈሩት ወገኖቹ ላቆሙት የእምቦሳ ምስል በመስገድና እየዘፈኑ በዓል በማድረግ ይሆዋን እያሳዘኑት ሳለ ደረሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር፥ “አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንህ በመንገድህ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ በአንተ መካከል አልወጣምና በፊትህ መልአኬን እሰድዳለሁ” በማለት ይሆዋ ለሙሴ የተናገረው፡፡

ከዚህ ጥቅስ ምን እንረዳለን? እስከዚህ ጊዜ ድረስ በመልአክ አምሳያ (በአርኣያ መልአክ) እየተገለጸ የመራቸው ፍጡር መልአክ እንዳልነበረ ነገር ግን ራሱ ይሆዋ እንደ ነበረ በግልጽ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ግን ይሆዋ በመቈጣቱ ከፍጡራን መላእክት አንዱን ዐብሮአቸው እንዲጓዝ እንዲመራቸውም ለመመደብ መወሰኑ ይታያል፡፡ ራሱ ይሆዋ ሆኖ ሳለ በአርኣያ መልአክ በተገለጸው በእግዚአብሔር በራሱ በመመራትና በፍጡር መልአክ በመመራት መካከል ያለውን ልዩነት የተረዱት ሙሴና ሕዝቡ በሰሙት “ክፉ ወሬ” በፍጡር መልአክ የመመራት ወሬ ዐዘኑ ይላል ቃሉ፡፡

የሙሴንና የሕዝቡን ሐዘንና ጸሎት የተቀበለው እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ራሱ ለመውጣት ተስማማ፡፡ ሙሴም እኔና የምመራው ሕዝብ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? ከሌላው ሕዝብ የተለየን የሚያደርገን እኮ የአንተ ከእኛ ጋር መሆን ነውና አንተ ዐብረኸን ካልወጣህ ከዚህ አታውጣን እዚሁ በበረሓው ተውጠን እንቅር፥ አንተ ግን ከእኛ ጋር ከወጣህ እሰየው! አለውና አምላኩን አመሰገነ (ዘፀ. 33፥14-16)፡፡

ስለዚህ ከዚህ በላይ ከተራ ቍጥር 1.1 እስከ 1.5 የተጠቀሱትን ተደጋጋፊ ጥቅሶችንና በእነርሱም ላይ የተመሠረተውን ሐተታ በሚገባ አጢነነው ከሆነ፥ የእስራኤል ልጆች ቃል የተገባላቸውን ርስት እስኪወርሱ ድረስ ዐብሮአቸው የተጓዘውና የመራቸው “ይሆዋ አምላክህ እኔ ነኝ” የማለት መብት ያለው የይሆዋ መልእክተኛ እንጂ ፍጡር መልአክ እንዳይደለ ሙሴና ሕዝቡ ተረድተው የነበረ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

1.6  ኢያ. 5፥13-15 ለሙሴ የሚሞትበት ቀን መድረሱን ያረዳው እግዚአብሔር እርሱን የሚተካው መሪ ኢያሱ መሆኑን ጨምሮ ነገረው፡፡ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴም ሕዝቡን ሰብስቦ የተባለውን ሁሉ አስተላላፈላቸው፡፡ በተቀኘው መዝሙርም እንዲህ አለ፡፡ “የይሆዋ ዕድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፡፡ ከበበው ተጠነቀቀለት፡፡ … ክንፎቹን ዘርግቶ ዐዘላቸው ይሆዋ ብቻውን መራው፡፡ ከእርሱ ጋር ሌላ (ተባባሪ) አምላክ አልነበረም” (ዘዳ. 32፥9-12)፡፡ ይኸው ሙሴ ለተተኪው ለኢያሱ፥ “ጽና አይዞህ በፊትህ የሚሄድ እርሱ ይሆዋ ነው፥ ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም፡፡ አትፍራ፥ አትደንግጥ” አለው (ዘዳ. 31፥7-9)፡፡

ለሙሴ ሞት የታወጀው የሐዘን ወራት ከተፈጸመ በኋላ ኢያሱ የአመራሩን ሥልጣን ጨበጠ፤ ሕዝቡንም እየመራ ዮርዳኖስን ተሻገረና በጌልጌላ ለሕዝቡ ሥርዐተ ግዝረትን ፈጸመ፡፡ ከዚያ ወደ ኢያሪኮ በማምራት ላይ እንደ ነበረ የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰውን (መልአክን) አየ፡፡ “ከእኛ ወገን ነህ? ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? ሲል ኢያሱ ላቀረበለት ጥያቄ መልአኩ ሲመልስ “ከማንኛችሁም ወገን አይደለሁም፤ የይሆዋ የሰራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ” አለው፡፡ የይሆዋ የሰራዊት አለቃ ነኝ ያለው ይህ መልአክ ባለፉት ተራ ቍጥሮች ከተመለከትነው ራሱ ይሆዋ ሆኖ ሳለ እንደ ይሆዋ መልእክተኛ ከተገለጸውና የእስራኤልን ልጆች እየመራ እዚህ ካደረሳቸው መሪያቸው የተለየ አይደለም፡፡ በዚህ ቦታ ግን እንደ ተለመደው በአርኣያ መልአክ እንዲገለጽ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ፥ አሁንም ከኢያሱ ጋር እንደሚሆን ለማረጋገጥ ነበር፡፡ የዚህን አባባል እውነትነት ከሚያስጨብጡ ማስረጃዎችም የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አንደኛ፡- “አንተ የቆምህበት ስፍራ ቅዱስ ነውና፥ ጫማህን አውልቅ” ተብሎ ለኢያሱ አሁን የተላላፈለት ትእዛዝ ቀደም ሲል ሙሴ ለመሪነት ሲጠራ በኮሬብ ተራራ ከተሰጠው መሪ ትእዛዝ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነው (ዘፀ. 3፥1-5)፡፡

ሁለተኛ፡- ሙሴ የመሪነት ሥልጣኑን ለኢያሱ ሲያስረክበው፥ “ራሱ ይሆዋ ይመራሃል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል” በማለት የነገረው ማበረታቻ ቃልና (ዘዳ. 31፥8) ራሱ ይሆዋም “ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ ካንተም ጋር እሆናለሁ” ብሎ የነገረውን ማረጋገጫ (ኢያሱ 1፥5-9) የሚያጠናክር ነው፡፡

ሦስተኛ፡- ኢያሪኮን ለመውረር በተዘጋጀበት በዚህ ጊዜ ውጊያውን በአዝማችነት የሚመራው የጦር አለቃ ራሱ ይሆዋ እንደ ሆነ ያረጋግጥለት ዘንድ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የተገኘውን የይሆዋ የሰራዊት አለቃ ማንነት ኢያሱ ተረድቶ ነበር፡፡ ይህንም ለማለት የሚያበቃን ሐቀኛ ሚዛን ሆኖ የቀረበው አስተማማኝ ነጥብ በትርኢቱ ትረካ ውስጥ በጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ኢያሱ ለተገለጸለት የይሆዋ የሰራዊት አለቃ ወደ ምድር ተደፍቶ ስግደት ሲያቀርብለት መታየቱ፥ በአርኣያ መልአክ ወደ ኢያሱ የመጣው የይሆዋ የሰራዊት አለቃም እንደ ፍጡር መልአክ “አትስገድልኝ እንዳንተ ፍጡር ነኝ” ሳይለው (ራእ. 19፥9-10፤ 22፥8-9) ስግደቱን በተገቢነት መቀበሉ ነው፡፡

1.7      መሳ. 2፥1-5፡- ኢያሱ ከመሞቱና ሕዝቡን ወደየዕጣ ክፍላቸው እንዲሄዱ ከማሰናበቱ በፊት የይሆዋ መልአክ እንደ ተገለጠ ይተርካል፡፡ “እኔ ከግብጽ አውጥቻችኋለሁ፤ ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳንም ለዘለዓለም አላፈርስም” ካለ በኋላ ሕዝቡ ግን ቃል ኪዳን አፍራሾች ሆነው በመገኘታቸው በወረሱት ምድር ላይ የሚኖሩትን ተረፈ አሕዛብ እንደማያስወጣላቸው፤ እያስጨነቁአቸው እንደሚኖሩም ነገራቸው፡፡ ሕዝቡ ይህን የይሆዋን መልአክ ቃል በሰሙ ጊዜ አለቀሱ፤ በዚያ ስፍራም ለይሆዋ መሠዊያ እንደ ሠሩ ቃሉ ይተርካል፡፡

በአርኣያ መልአክ (በመልአክ አምሳያ) የታየው ፍጡር መልአክ እንዳይደለ፤ ከአነጋገሩና ከአቀራረቡ ይታወቃል፡፡ ይሆዋ እንዲህ አለ በማለት አይናገርም፡፡ ራሱ ይሆዋ ስለ ሆነ “እኔ” በማለት በባለሥልጣንነት ይናገራልና፡፡

1.8  መሳ. 6፥11-24፡፡ በዚህ ክፍል የይሆዋ መልአክ በኦፍራ ለጌዴዎን የተገለጸበትን ታሪክ እናነባለን፡፡ ነገር ግን ይህ የይሆዋ መልእክተኛ ፍጡር መልአክ አልነበረም፤ በአርኣያ መልአክ (በመልአክ አምሳያ) የታየ ይሆዋ እንደ ሆነ የምዕራፉ ቍጥሮች 14፡16፡23 አብራርተውታል፡፡ በቍጥር 22 ላይም ጌዴዎን፥ “አቤቱ አምላኬ ሆይ!” ብሎታል፡፡ የሠራለትንም መሠዊያ “ይሆዋ ሻሎም” እግዚአብሔር ሰላም በማለት ሰየመው (ቍጥር 24)፡፡
    
     በዚያው ሌሊት ስለ ቀጠለውም አስተርእዮት (መገለጥ) ክፍሉ ይተርካል፡፡
ሀ. ከቍጥር 25-32 ጌዴዎን የበዓልን መሠዊያ እንዲያፈርስ በተቃራኒው ለይሆዋ መሠዊያ እንዲሠራ በመሠዊያውም ለይሆዋ መሥዋዕት እንዲያቀርብ ጌዴዎን በይሆዋ ሲታዘዝ ይነበባል፡፡
ለ.  ከቍጥር 36-40 እንዲሁም በምዕራፍ 7 ጌዴዎን ከይሆዋ ጋር ሲነጋገር መመሪያም ሲቀበል የቀጠለ ታሪክ ይገኛል፡፡

1.9 በመሳ. 13፥2-25 ለማኑሄ ሚስት የይሆዋ መልአክ እንደ ተገለጠላትና የሶምሶንን መወለድ እንዳበሠራት ይተርካል፡፡ የይሆዋ መልእክተኛ ሆኖ ወደ እርሷ የመጣው ፍጡር መልአክ እንዳልሆነ ማኑሄ በሚገባ ተረድቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሀ. ማኑሄ የይሆዋን መልአክ ይጋብዘው ዘንድ የፍየል ጠቦት ሊያርድ ሲዘጋጅ፥ “የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበው ዘንድ ስላዘዘውና መሥዋዕት የሚሠዋው ቍርባን የሚቀርበው ለይሆዋ ብቻ በመሆኑ”፥
ለ. ስሙን እንዲነግረው በጠየቀው ጊዜ “ስሜን ለምን ትጠይቀኛለህ?” በማለቱ፥ ያዕቆብ የታገለው ይሆዋ ለያዕቆብ ጥያቄ ከሰጠው መልስ ጋር በፍጹምነት ስለሚመሳሰል (ዘፍ. 32፥29)፡፡
ሐ. “ስሜ ድንቅ ነው” የሚለው ኀይለ ቃል ለፍጡር መልአክ የማይሰጥ ይሆዋ ለሆነው ወልደ እግዚአብሔር የተጠበቀ ስያሜ ስለ ሆነ (ኢሳ. 7፥14፤ 9፥6)፡፡
መ. ለሚስቱ “ይሆዋን አይተናልና ወዮልን እንሞታለን” የሚለው የማኑሄ አነጋገር በእስራኤላውያን ሁሉ ዘንድ ስለ ይሆዋ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ (ዘፀ. 33፥20፤ ኢሳ. 6፥5)፡፡ ከዚህ ሀሉ ማስረጃ ጠቋሚነት በመመራት ማኑሄ በአርአያ መልአክ የተገለጸለት መልእክተኛ ራሱ ይሆዋ እንደሆነ አረጋግጦ ነበር ማለት ተችሏል (ቍጥር 22-23)፡፡

እስከዚህ ድረስ የመረመርናቸውን እነዚህን አስራጂ ጥቅሶችንና የሚያስተላልፏቸውን መልእክቶች ብናጠቃላቸው በዐጭሩ የሚከተሉትን ያስጨብጡናል፡፡
1.     በአርኣያ መልአክ (በመልአክ አምሳል) ለአባቶች የተገለጸው ፍጡር መልአክ እንዳይደለ፤
2.    ራእዩን (መልእክቱን) የተቀበሉት አባቶች አርኣያ መልአክን ገንዘብ በማድረግ (በመላበስ) ራሱን የገለጸላቸው ይሆዋ እንደ ሆነ መረዳታቸውን፡፡
3.    እንዲህ እንደ ሆነ ስለ ተረዱም ለፍጡር መልአክ የማይገባውን ለራሱ ለይሆዋ ብቻ ተገቢ የሆነውን አምላኬ ሆይ መባልን፣ ስግደትን፣ አምልኮትን፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን በመስጠት ያከበሩትና ያመለኩት መሆኑን፥
4.    በአርኣያ መልአክ (በመልእክተኛ አምሳያ) እንዲገለጽ አስፈላጊ የሆነበትም ምክንያት መላክ መልእክተኛ መሆን በተፈናዊነት መታወቅ ለእግዚአብሔር ወልድ አስተርእዮት መግለጫ ተስማሚ ሆኖ በመገኘቱ እንደ ሆነ፥
5.    እግዚአብሔር ወልድ ምንም እንኳ
5.1  ልጅ በመሆኑ ለአባቱ፥ በአባቱ የሚታዘዝ የሚላክ ጻድቅ ባሪያ ቅን አገልጋይ ሥምረት ፈጻሚ (ኢሳ. 42፥1፤ 52፥13-15፤ 53፥11፤ ዮሐ. 17፥1-5፤ ዕብ. 5፥8)፡፡
5.2 ቃል በመሆኑም ተፈነዊነት (ተላኪ መልክተኛ) ፈቃድ ፈጻሚ (መዝ. 147፥7፤ ኢሳ. 55፥10-11) ቢባልም ወልድም ቃልም ለመባሉና ለመሆኑ ተስማሚ ገላጭ ቃል በመሆኑ እንጂ ፍጡራን እንደ ሆኑ ሰዎችና መላእክት የታዛዥነት ባሕርያዊ ግዴታ እንዳልነበረበት የሆነውንም ሁሉ በፈቃዱ የተቀበለ ወልድ፥ በአርዮሳውያንና በአይሁድ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ በሚታወቀው መለኮታዊ ስም ይሆዋ “ኤልሻዳይ” በመባል የመጠራት መብት ያለው ባሕርያዊ አምላክ እንደ ሆነ ያለ ጥርጥር ያስተማምነናል (ፊል. 2፥5-8)፡፡

ማጠቃለያ
1. ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ወልድ በፍጹም አምላክነት ደረጃና ክብር ላይ ያለ ይሆዋ እንደ ሆነ ስለሚገልጽባቸው አርዮሳውያን በጥቅሶቹ ያሉትን አስተርእዮቶች (መገለጦች) ለፍጡር መልአክ ይሰጧቸዋል፡፡ ለወልድ የነፈጉትን የሚገባውን የይሆዋነት ክብር ለማይገባቸው ለመላእክት ሲሰጡ ኅሊና ቢኖራቸው ኖሮ ምን ያህል በተወቀሡ ነበር፡፡
2. መላእክትን የማምለክ ልምድ የተጠናወታቸው ሌሎች መናፍቃንም (ካሮችን ጨምሮ) ለመላእክት የሚያቀርቡትን አምልኮ፥ ስግደት፥ መሥዋዕትና ቍርባን ተገቢ የሚያደርግላቸው ስለሚመስላቸው በጥቅሶቹ ያሉትን አስተርእዮቶች (መገለጦች) ለመላእክት ይሰጧቸዋል፡፡ እነዚህም በፈጣሪ ፈንታ ፍጡራንን በማምለካቸው ለማያስተውል አእምሮ በእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸው (ሮሜ 1፥20-32)፡፡

ዳሩ ግን ከመላእክት አምልኮ ራሳችንን እንድንጠብቅ የእግዚአብሔር ቃል የሚለግሰንን ምክር አንርሳ (ቈላ. 2፥18)፡፡ ሆኖም ወልድ በብሉይ ኪዳን በመልእከተኛነት የተገለጸ ይሆዋ ይመስገን!! አሜን!!!
በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment