Wednesday, February 6, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
 በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ
ኦሪት ዘፍጥረት 3፥14-25

የእግዚአብሔር ፍርድና የደኅንነት መንገድ

መግቢያ፤ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎና ማስጠንቀቂያውን ጥሶ በኀጢአት እንደ ወደቀ ባለፈው ጥናት ተመልክተናል፡፡ አማኞች ይህን አንቀጽ ሲያነቡ ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍርድ ላይ ያተኲራሉ፡፡ እግዚአብሔር በፍርድ ሰውን መቅጣት ብቻ ሳይሆን ሰውን የማዳን ዐላማ ያለው በመሆኑ በዚህ አንቀጽ የደኅንነትን መንገድ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ከፈተ እንመረምራለን፡፡ በርግጥ ይህ ምዕራፍ ስለ ክርስቶስ በግልጽ አይናገርም፡፡ ነገር ግን ወደ ዐዲስ ኪዳን ሐሳብ የሚመሩን ልዩ ልዩ ፍንጮች አሉ፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳንም ሆነ በዐዲስ ኪዳን ዘመን ሰው የሚድንባቸው መሠረታውያን ነገሮች አንድ ዐይነት ስለ ሆኑ ነው፡፡

ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት ከመሞከርህ በፊት የሚከተሉት ማስታወሻዎች ሊረዱህ ይችላሉ፡፡

ቊ. 14 በሆድህም ትሄዳለህ፤ እባብ በፊት ቀጥ ብሎ በክብር የሄደ ይመስላል፡፡
ቊ. 15 በዘርህ፥ የእባብ ዘር የሰይጣንን ተከታዮች ያሳስባል፡፡
በዘርዋም፥ የሴቲቱን ዘር በሥጋዊና በመንፈሳዊ አቅጣጫ መተርጐም የሚቻል በመሆኑ ቃሉ ሰዎችን ሁሉ በእምነት የሚኖሩትን ብቻ ወይም ክርስቶስን ሊያመለክት ይችላል፤ ዘፍ. 17-18፤ ሮሜ 16፥20፤ ገላ. 3፥16፡፡


እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ የሴት ዘር ፍጹም ያሸንፈዋል፡፡

አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ፤ ከጠላትነቱ የተነሣ በውጊያው የሴቲቱ ዘር ከእባብ ዘር መከራን ይቀበላል፡፡

ቊ. 20 የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና፥ አዳም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደበት ቢያውቅም በእግዚአብሔር ቃል መሠረት (ቊ. 15) ዘር እንደሚኖረው ዐውቆ ይህን ስም ለሚስቱ በመስጠቱ እምነቱን ገለጠ፡፡

ቊ. 21 የቈርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ አንባቢዎች የነበሩት የሙሴ ተከታዮች “የቈርበት ልብስ” ከመሥዋዕት የተገኘ ሊመስላቸው ይችል ነበር፡፡

የሰዎች ነውር እንዲሸፈን እግዚአብሔር አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አደረገ፤ ከቊ. 7 ጋር ያነጻጽሩ፡፡

ቊ. 22 ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፥ የምጸት አገላለጥ ይመስላል (ከቊ. 5 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ ሰው ባለመታዘዙ ከሕይወት ዛፍ መብላት መብት አልነበረውምና ሳይገባው ቢበላም ኖሮ የባሰውን ፍርድ በራሱ ላይ ያመጣ ነበር 1ቆሮ. 11፥27-30፡፡

ወደ ሕይወት ዛፍ፥ ዛፉ ገና አለ፥ አልተቈረጠምና፥ ሆኖም ሰው አሁን መብላት የሚችለው የሞትን መንገድ ከተሻገረ በኋላ ብቻ ነው ራእ. 2፥7፤ 2፥2-14፡፡

ቊ. 24 ኪሩቤል፥ የብዙ መጠሪያ ቃል፡፡ ኪሩቤል የተገኙ በታቦት ላይ ነበርና የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ አንባቢዎች ከዚህ ጥቅስ እግዚአብሔር ለሰው የመሠዊያ ቦታ እንደ ደነገገ፥ ደግሞም የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ የእግዚአብሔር የመገኛ ምልክት መሆኗን ማስተዋል ይችሉ ነበር፡፡ በዚህ ቦታ የአዳም ልጆች መሥዋዕታቸውን አቀረቡ፤ እግዚአብሔርም አነጋገራቸው (4፥3-6፤ ዘፀ. 25፥22)፡፡

የእግዚአብሔር ፍርድ (ቊ.14-19)፥
1. የእግዚአብሔር ፍርድ ሀ)በእባቡ፥ ለ)በሴቲቱ፥ ሐ)በአዳም ላይ ከክፋታቸውና ከተፈጥሮአቸው ጋር እንዴት ተዋሐደ?
2. ከቊ. 15 ስለሴት ዘር ታሪክ ምን አራት መሠረታውን ነገሮችን እናገኛለን?
3. አዳም ከቊ. 15 ስለ ትንቢት አፈጻጸም ምን ሊያስተውል ይችል ነበር?
4. ለአዳምና ለሔዋን ከነውር መሸፈን የሚቀጥሉት ነገሮች ምሳሌዎች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ?
ሀ) ኀጢአተኛ በእምነት መጽደቁ (ሮሜ 3፥28)
ለ) ኀጢአተኛ በደም መጽደቁ (ሮሜ 5፥9)
ሐ) ኀጢአተኛ በጸጋ መጽደቁ (ሮሜ 3፥24)
መ) አማኝ በሌላው ጽድቅ መኖሩ (1ቆሮ. 1፥30-31፤ 2ቆሮ. 5፥21)

የቅድስና ኑሮ ቊ. 22-24
5. እግዚአብሔር
ሀ) ሰው በማይገባው መንገድ ሕይወትን እንዳይፈልግ
ለ) የልቡን ክፋት እንዲገታ
ሐ) በትክክል እርሱን እንዲያመልክ
መ) ተስፋ እንዳይቈርጥ ምን አደረገ?

No comments:

Post a Comment