ከናሁ አዳም
ነጥብ (ጭብጥ) ዐምስት
ካለፈው የቀጠለ
አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በመባል የህላዌ ፍጹምነትን ለሚያረጋግጥ የየራሳቸው
ግብር ባለቤት የሆነው በሦስት አካላትና ስሞች የተገለጹት ሥላሴ “በኩነትም” ሦስት መሆናቸውን የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል፡፡
ይህም ማለት አንዱ አካላዊ መንፈስ በሦስት “ኩነታት-ኹነታዎች” አልተገለጸም፡፡ ዳሩ ግን እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በአንዱ መለኮተ
ይሆዋ በተለየ አካሉ የራሱን ህላዌና ባሕርያዊ ግብር መግለጽ በሚችል “ኩነት- ኹነታ” ታውቋል፡፡
ኩነት (ኹነት-ኹነታ)
አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) ሥሉስነታቸው እንደ ተጠበቀ በአሐዳዊው
መለኮተ ይሆዋ እያንዳንዳቸው ምን ሆነው እንደሚገኙ በእግዚአብሔር ቃል የተገለጸው ባሕርያዊ ኹነታቸው በግእዝ “ኩነት” ይባላል፡፡
አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ለሦስት ህልዋን ተገቢ በሆኑ ሦስት ስሞች እንደሚጠሩና እንደሚታወቁ ሁሉ እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ
በራሱ ባሕርያዊ ኹነታ ስለ ታወቀ ለሥላሴ ሦስት ኹነታት አሏቸው ማለት ነው፡፡
ይህም እንደሚከተለው ነው፡-
የአብ “ኩነት-ኹነታ” ልብነት፥ ልብ መሆን
(ከዊነ ልብ)
የወልድ “ኩነት-ኹነታ” ቃልነት፥ ቃል መሆን
(ከዊነ ቃል)
የመንፈስ ቅዱስ “ኩነት-ኹነታ” ሕይወትነት፥
እስትንፋስነት ሕይወት (እስትንፋስ) መሆን (ከዊነ ሕይወት ከዊነ እስትንፋስ)
የኩነት ስም
በአሐዳዊ መለኮተ ይሆዋ ያለው እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ ለባሕርያዊና አካላዊ
ኹነታው ተገቢ ሆኖ የሚጠራበት ስም የ”ኩነት ስም” ይባላል፡፡ ስለ ሆነም ሥላሴ ሦስት ኩነታት እንዳሏቸው ሁሉ ሦስት የኩነታት ስሞችም
አሏቸው ማለት ነው፡፡
ኹነታዎቻቸውና የኹነታዎቸቸው ስሞች ሆነው የተገኙባቸው የአካል ባሕርያዊ ስያሜዎች
ናቸው እንጂ በሥራ ድልድል ምክንያት ወይም በዚህ ኹነታ እንጠራ በማለት ለየራሳቸው ያወጧቸው ስያሜዎች አይደሉም፡፡ ይህም ቀጥሎ
እንደ ተመለከተው ነው፡፡
የአብ የኩነት ስም - ልብ
የወልድ የኩነት ስም - ቃል
የመንፈስ ቅዱስ የኩነት ስም - ሕይወት እስትንፋስ
ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን በእግዚአብሔር ቃል እየተመራን እናጥናው፡፡
ሀ) ወልድ በአካሉ ምሉዕነትና በህላዌው ፍጹምነት
እንደ እርሱ ምሉዕ አካልና ፍጹም ህላዌ በሆነው ይሆዋ ዘንድ የነበረ፥ ያለና የሚኖር ይሆዋ ነው፡፡ ታዲያ በይሆዋ ዘንድ የይሆዋ
ልብ ወይም መንፈስ (ሕይወት) ሆኖ አልኖረም፡፡ የይሆዋ ቃል ሆኖ ይኖራል እንጂ (ዮሐ. 1፥1፤ ራእ. 19፥11-13)፡፡
ለ) መንፈስ ቅዱስ በአካሉ ምሉዕነትና በህላዌው
ፍጹምነት በይሆዋ ዘንድ የኖረ ይሆዋ ሲሆን በአኗኗሩ የይሆዋ መንፈስ (ሕይወት እስትንፋስ) ሆኖ ይኖራል እንጂ ልብ ወይም ቃል ሆኖ
አልኖረም፥ አይኖርምም (1ቆሮ. 2፥10-12፤ ኢዮ. 33፥4፤ ሐ.ሥ. 5፥1-4)፡፡
ሐ) በአካሉ ምሉዕነትና በህላዌው ፍጹምነት
የሚገኘው አብ ቃል ከልብ በሚወጣበት (በሚወለድበት) አወጣጥ ዐይነት በኩነት አጠራር “ቃል” የሆነውን ወልድን ያወጣ ከሆነ (ሚክ.
5፥2፤ ዮሐ. 8፥42) እንደዚሁም የሕይወት መውጪያ ልብ እንደ ሆነው ሁሉ በኩነት አጠራር “መንፈስ ወይም ሕይወት” የሆነውን መንፈስ
ቅዱስን ያወጣ (ያሠረጸ) ከሆነ (ዮሐ. 15፥26)፤ ለቃልና ለሕይወት (መንፈስ) መገኛና መውጪያ (መፍለቂያ) የሆነው የአብ ኩነት
(ኹነታ) ምንድር ነው? የኩነት ስሙስ? የሚለው ጥያቄ ስለሚፈጥር መልሱን የእግዚአብሔር ቃል እንዲሰጠን ብንፈቅድ፥
ቃልን የሚያወጣ ልብ ነው ይለናል (ማቴ. 12፥35)፡፡
የሕይወት መፍለቂያ ልብ እንደ ሆነ ይነግረናል (ምሳ. 4፥23)፡፡
እንግዲህ እስከዚህ ከመጣን “ቃል” የሆነውን ወልድና ሕይወት የሆነውን መንፈስ
ቅዱስን ያወጣ (እና ያሠረጸ) የአብ የኹነታ (የኩነት) ስሙ “ልብ” መባል እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል አላስተማረንምን?
አርዮሳውያን ወልድ “ቃል” መባሉ ከተፈጠሩ መላእክት መካከል ተመርጦ “ቃለ ዐፄ”
ሆኖ በመሾሙ ነው በማለት አስመስለው ቢናገሩም፥ አባባሉ በእግዚአብሔር ቃል ያልተደገፈ እንደ ሆነ ከፍ ብሎ ከተገለጸው ከማስረጃው
አቀራረብ እንረዳዋለን፡፡ ክዋኔውም ሆነ ስመ ክዋኔው ባሕርያዊና አካላዊ ነውና፤ ይህንም ጒዳይ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ ራሱን
አስችለን በተለይ በምናቀርበው ጥናት በሰፊው እንመረምረዋለን፡፡ እስከዚያው ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ጨብጠን እንለፍ፡፡
ሀ. ጌታ እግዚአብሔር አብ በራሱ ልብ መሆን
“ለባዊ (ልበኛ)” በወልድ ቃል መሆን “ነባቢ (ተናጋሪ)” በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት መሆን “ሕያው” ነውና ያስባል፤ ያቅዳል፡፡ ቃሉ
በሆነው ወልድ (በመናገር) ይሠራዋል (ዘፍ 1፥1-31፤ መዝ. 148፥1-5)፡፡ እርሱ አለ እነርሱም ሆኑ ተፈጠሩ፡፡
ለ. ጌታ እግዚአብሔር ወልድ በአብ ልብ መሆን
“ለባዊ (ልበኛ)” በራሱ ቃል መሆን - “ነባቢ (ተናጋሪ)” በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት መሆን “ሕያው” ነውና ቃል እንደ መሆኑ መጠን
በአብ ልብ መሆን የታሰበውን ይሠራዋል (ዮሐ. 1፥1-3፤ ዕብ. 1፥2፤ 3፥3)፡፡ “ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ የሆነ የለም፡፡”
ሐ. ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በራሱ
ሕይወት መሆን “ሕያው” እንደ መሆኑ ለአብና ለወልድ “መንፈስ (ሕይወት)” ነው (ዮሐ. 3፥34-35፤ ሐ.ሥ. 16፥6-7)፡፡ ስለ
ሆነም መንፈስ ቅዱስ፡-
ሐ.1 በአብ ልብ መሆን
ልበኛ በወልድ ቃል መሆን ነባቢ፥ ተናጋሪ ነውና ያስባል፤ ይናገራል፤ ይሠራልም (ሐ.ስ. 20፥23፤ 21፥11፤ 28፥25-27)፡፡
ሐ.2 በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት
መሆን ሕያው የሆነ አብ ቃሉ በሆነው ወልድ “እኔ ሕያው ነኝ” ብሎ ይናገራል (ዘዳ. 32፥39-40፤ ኢሳ. 45፥23)፡፡
ሐ.3 በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት
መሆን ሕያው የሆነ ወልድ በአብ ልብ መሆን ለባዊ ልበኛ ነውና “እኔ ሕያው ነኝ” ሲል በራሱ ቃል መሆን ይናገራል (ሮሜ 14፥9-12)፡፡
ስለዚህ አንዱ ከሌላው በጊዜ እንደማይቀድምና በክብርም እንደማይበልጥ፥ የሥላሴ
የየግላቸው ኹነታዎች ይበልጥ ግልጽ ያደርጉልናል፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁና እናንተ ቃልንና ሕይወትን ከሚያፈልቀው ልባችሁ የሚቀድመውንና
የሚበልጠውን እስኪ አስረዱን? በተጨማሪም በልብ ተምሳሊት የገለጽነው ለሰው ነፍስ የተሰጣትን በእንስሳ የማትገኘውን “የማሰብ ችሎታን”
ነው እንጂ በሥጋ አካል ውስጥ ያለውን ልብ የሚባለውን የሥጋ ብልት እንዳይደለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሰው ከእንስሳ የሚለይበት ልብ
የሥጋ ብልት የሆነው ልብ እኮ አይደለም! ይህንማ እንስሳትም አላቸው፡፡ እንስሳት የሌላቸው “ልብ” የተባለው ግን ሰው ሕያው ነፍስ
የተሰኘበትን፤
ለባዊነት (የማሰብ ችሎታን)፥
ነባቢነትን (የመናገር ችሎታን)፥
ሕያውነትን እንደ ሆነ ማስተዋል አለብን፡፡
መዝ. 49፥12-20
ቢነገርም ባይነገርም ሐሳብን በቃል ቅርጽ የሚያፈልቅ የሚያውጠነጥን ልብ ሕይወት
ያለው ልብ ነው፡፡ በሕያው ልብ የሚታሰቡት፥ የሚብሰለሰሉት፥ የሚውጠነጠኑት፥ የሚታቀዱት ሁሉ በቃል ማለት በመናገር ችሎታ ቀራጺነት
የሐሳብ የንድፍ የሥራ ቅርጽና አካል ይሰጣቸዋል፡፡ ሐሳቡ፥ ንድፉ፥ ሥዕሉ በልብ ውስጥ የሚኖር እንኳ ቢሆንም ትርጉም ያለውና በራሱ
ህላዌ የሚገኝ ቃል ነው፡፡ በይሆዋ ልብ ሐሳብ ሲታሰብ፥ ዕቅድ ሲወጣ፥ ሲነደፍ ይታያል፡፡ ንድፉ የቃል ትርጉም ያለው ነው፡፡
እንግዲህ ማቴዎስ፥ “በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ያለውን (ማቴ.
28፥19-20)፤ ጳውሎስ፥ “የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት” (2ቆሮ. 13፥14)
በማለት በተለየ ተራ አቀማመጥ ሊጽፍ የቻለው የሥላሴ ኹነታት ምስጢር ማንንም ቀዳሚ፥ ማንንም ተከታይ ስለማያደርግ መሆኑ ሊስተዋል
ይገባል፡፡
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 5 ላይ የቀረበ
be mejemeriya Selase woyem trinity yemil qal bible wust yelem. huleteghna egziabher aend endehone enji sost endehone andem bota altegeletsem. Egziabher be seega tegelete woym qal seega hone malet sost akal malet aydelem.
ReplyDelete