Sunday, February 17, 2013

መሠረተ እምነት



ካለፈው የቀጠለ
ነጥብ (ጭብጥ) ስድስት

በሦስት አካላትና በሦስት ኩነታት ራሱን የገለጸው አንዱ ይሆዋ በመሆኑ፥

የማይከፋፈል አንድ መለኮት (አምላክነት)
የማይበተን አንድ ሥልጣን
የማይለያይ አንድ ዘላለማዊ መንግሥት ብቻ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

1.     ስለ አምላክነት
አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) ያንዲት የማትከፋፈል መለኮት እኩል ባለቤቶች ናቸውና፥
1-ሀ. “አብ እውነተኛ አምላክ ነው” እንላለን “እውነተኛ አምላክ የሆንኽ አንተን ብቻ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ናት” ዮሐ. 17፥3፡፡


1-ለ. ወልድ እውነተኛ አምላክ ነው “የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፡፡ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” 1ዮሐ. 5፥20፡፡
1-ሐ. “መንፈስ ቅዱስ እውነተኛ አምላክ ነው” በመዝ. 93/94 “ኑ በይሆዋ ደስ ይበለን ... ይሆዋ ታላቅ አምላክ ነውና በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና፡፡ … ኑ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ በእርሱ ባደረገን በይሆዋ ፊት እንንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና … በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ፤ … አባቶቻችሁ ፈተኑኝ፤ ሥራዬንም አዩ፤ ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር፡፡ ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቍጣዬ ማልሁ” ይላል ከቍ. 1-11 በዚህ መዝሙር እንዲህ ተብሎ የተነገረውን ማስጠንቀቂያ የሰጠ “ይሆዋ ታላቅ አምላክ” የተባለው ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ አብራርቶ አስረድቷል (ዕብ. 3፥7-11)፡፡

2.    ስለ ፈጣሪነት
አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) አንድ ፈጣሪ በመሆን ለአንዲት የመፍጠር ሥልጣን እኩል ባለቤቶች ናቸውና፥
   2-ሀ. አብ ፈጣሪ ነው፤ ዘዳ. 32፥1-18 “የይሆዋን ስም እጠራለሁ፤ እርሱ አምላክ ነው፡፡ ሥራውም ፍጹም ነው፡፡ … ለይሆዋ ይህን ትመልሳለህን? …. የፈጠረህ ያጸናህ እርሱ ነው” ሲል ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያስተማረውን በግእዙ “አኮኑ ዝንቱ አብ ፈጠረከ - የፈጠረህ ይህ አብ አይደለምን?” ይላል፡፡
   2-ለ. ወልድ ፈጣሪ ነው “ከሆነው ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ የለም” ዮሐ. 1፥1-3፡፡
   2-ሐ. መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ ነው “የይሆዋ መንፈስ ፈጠረኝ፤ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ፡፡” ኢዮ. 33፥4፡፡

3.    ስለ ሁሉን ቻይ ሥልጣን
አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) የአንዲት ሁሉን ቻይ (ኤልሻዳይ) ሥልጣን እኩል ባለቤቶች ናቸውና፥

3-ሀ. አብ ወልድን ከሞት አስነሣ ተባለ “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፡፡” ሐ.ሥ. 2፥22-24
3-ለ. ወልድ ራሱን ከሞት አስነሣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው፡፡ ይህን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ አለ፡፡” ዮሐ. 2፥19-21
3-ሐ. መንፈስ ቅዱስ ወልድን ከሞት አስነሣ ተባለ “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን በመነሣት በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” ሮሜ 1፥3-4
4.    ስለ መንግሥትና ክብር
አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) የአንዲት ፍጽምት የማትከፋፈል መንግሥት እኩል ባለቤቶች ናቸውና፥
4-ሀ. አብ የዘላለማዊ መንግሥትና ክብር ባለቤት ነው “ይሆዋ ታላቅ ነው ለሰው ልጆች ኀይልህን፥ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፡፡” መዝ. 144/145፥1-13፤ ከሮሜ 16፥27 ጋር ይመሳከር፡፡
4-ለ. ወልድ የዘላለማዊ መንግሥትና ክብር ባለቤት ነው፡፡ “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለክርስቶስ ሆነች፡፡ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል፡፡” ያለህና የነበርህ ሁሉንም የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ትልቁን ኀይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ ራእ. 11፥15-18፤ ከ1ጢሞ. 1፥15-17 ጋር ይነበብ፡፡
4-ሐ. መንፈስ ቅዱስ የዘላለማዊ መንግሥትና ክብር ባለቤት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታን ልብ ያወቀና አማካሪውስ ማን ነበር” ሲል ከጠየቀ በኋላ “ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን” ብሏል፡፡ ሐዋርያው ይህን ሀሳብ የወሰደው ከትንቢተ ኢሳ. 40፥12-14 “የእግዚአብሔርን መንፈስ ማን መከረው” ከሚለው ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በላይ በተራ ቍጥር 1-3 “ታላቅ ንጉሥ” የተባለው መንፈስ ቅዱስ የዘላለም ክብር ባለቤት ነው፡፡ አሁንም ከዘላለም እስከ ዘላለም ለጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ይሁን፤ አሜን፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሰባት

የሥላሴ አንድነት በመቻቻል ለአንድ ዐላማ በመሥራትና በመኖር የተገኘ ስምምነታዊ አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዱ በሌላው የሚኖርና የሚሠራ (ህልው) በመሆኑ፤ ያለሌላው ግን ያልኖረና የማይኖር፤ ያልሠራና የማይሠራ ከመሆኑ የተነሣ ነው፡፡

የሥላሴ እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በሌሎቹ (ሁለቱ) ሁለቱም በአንዱ የሚኖሩና የሚሠሩ እንደ መሆኑ መጠን ለተሠራው ሥራ እኩል ባለቤቶች ናቸውና በአንድነትም በሦስትነትም ይመሰገኑበታል፡፡

1.   ጌታ እግዚአብሔር አብ ሲመሰገን “ዳዊትም በጉባኤው ፊት ይሆዋን ባረከ፤ ዳዊትም እንዲህ አለ … አቤቱ በሰማይና በምድር ያለው ሁለ ያንተ ነውና ታላቅነትና ኀይል ክብርም ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ መንግሥት የአንተ ነው አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ፡፡ ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው… ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነው፡፡” 1ዜና. 29፥10-19፡፡

2.   ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሲመሰገን “የይሆዋን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? … ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፡፡ ኢሳ. 40፥12-14 ከሮሜ 11፥33-36 ጋር ይነበብ፡፡

3.   ጌታ እግዚአብሔር ወልድ ሲወደስ “ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ፥ በእርሱም ሁሉ ለሆነ ለእርሱ ተገብቶታልና፡፡” ዕብ. 2፥9-12፡፡ “የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም÷ በረከትም ሊቀበል ይገባዋል፡፡” ራእ. 5፥12፡፡

ማጠቃለያ

በጣም ዐጭር በሆነና በተጠቃለለ አገላለጥ ውቅያኖስን በጭልፋ የሚባለውን ያህል የምስጢረ ሥላሴን ትምህርት መፈጸማችን ነው፡፡ ከትምህርቱ የተገነዘብነውን እንደሚከተለው አጠቃለን እንደመድማለን፡፡

1.     የብሉይና የዐዲስ ኪዳናት ምእመናን “ይሆዋ አንድ ነው” ሲሉ አንድ አካላዊ መንፈስ ነው ብለው ያምኑ እንዳልነበረ ተገልጿል ብለን እንናገራለን፤ ከአንድ አካላዊ መንፈስ በላይ መሆኑን የተረዱትም “ኤሎሂም” በመባሉና ራሱንም “እኛ” እያለ በመግለጹ እንደ ሆነ ይገባናል፡፡
2.    “እስራኤል ሆይ ስማ የእኛ ኤሎሂም የሆነው ይሆዋ አንድ ይሆዋ ነው” የሚለው ማስጠንቀቂያ በሦስት አካላትና በሦስት ኩነታት መገለጹን፤ እንዲሁም በብዙ ቍጥር “እኛ፥ ኤሎሂም” እያለ ራሱን ማስተዋወቁን መነሻ በማድረግ የተለያዩ ባለሥልጣናት መንግሥታት፥ መለኮታት፥ ያሉ እንዳይመስላቸው ለማስገንዘብ ነበረ እንጂ በነጠላ ቍጥር የሚታወቅና የተገለጸ አንድ አካላዊ መንፈስ እንደሆነ የሚታመን ቢሆንማ ኖሮ ይህን ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልግ እንደ ነበረ ወደ መረዳት ባለጠግነት ደርሰናል፡፡
3.    በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ የተባሉ ሐዋርያት “ሥላሴን” አያውቁም ነበር የሚለው የትምህርት መንገድ ዐይነ ልቡናቸው ለበራላቸው ምእምናን የማያስኬዳቸው እንደ ሆነ ተገንዝበናል፡፡
4.    የሥላሴን ስም ለመጥራት ከአብ መጀመር በጊዜና በክብር መቀዳደምን እንደማያመለክት የተረዳው ሐዋርያ “የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት” በማለት ቡራኬ መስጠቱ አብነታዊ ማስረጃ እንደ ሆነ አረጋግጠናል፡፡
5.    የሥላሴ አንድነት በመለኮት በሥልጣን ብቻ አለመሆኑን፥ ይልቁንም የመለኮት፥ የሥልጣን አንድነት የተመሠረተው አንዱ በሁለቱ ሁለቱም በአንዱ ስለሚኖሩና ስለሚሠሩ እንዲሁም አንዱ ያለ ሁለቱ ሁለቱም ያለ አንዱ ስለማይኖሩና ስለማይሠሩ እንደ ሆነም ተረድተናል፡፡ ለዚሁም እንደ ማስረጃ “እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑብኝ” ዮሐ. 10፥38፤ 14፥8-11 እና “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር፡፡” 2ቆሮ. 5፥19፤ ቈላ. 1፥19-20፤ ሐ.ሥ. 3፥26 የተባሉትን ጥቅሶች መመልከታችን ስለ ጕዳዩ ማስተዋልን ሰጥተውናል፡፡
6.    በመጨረሻም ለነፍሳችን ከለባዊነቷ፥ ከነባቢነቷና ከሕያውነቷ ውጪ የሆነ የምትታወቅበት ሌላ ህላዌ ከየትም እንደማናመጣላት ይገባናል፡፡ ማንነቷ ወይም እኔነቷ የሚታወቀው በእነዚሁ ኹነታዎችዋ ስለሆነ ለባዊነቷ በነባቢነቷና በሕያውነቷ፥ ነባቢነቷም በለባዊነቷና በሕያውነቷ፥ እንደዚሁም ሕያውነቷ በለባዊነቷና በነባቢነቷ ይታወቃሉ፤ ይገለጻሉም፤ ይታወቃሉና ይገላጻሉ ብቻም ሳይሆን ይኖራሉና ይገኛሉም፡፡ ከዚህም በመነሣት በአካላትና በኩነታት ሦስት ለሆነ ይሆዋ አሐዳዊ መለኮት መሠረቱ ህልውና ማለት አንዱ በሌሎቹ የመኖሩና የመሥራቱ ባሕርያዊ መብት እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ ለምሳሌ ዘማሪው “ይሆዋ እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል … ይመራኛል፡፡” እያለ ይሆዋን ጥበቃውን ምሪቱን እንክብካቤውን ተናገረ፤ መዝ. 21/22፡፡

የይሆዋ እረኛነት ነፍሱን ስለ በጐቹ ቤዛ በሚሰጥ ቸር እረኛ በሆነው በይሆዋ ባሕርያዊ ቃል በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸ፡፡ አዎን ፍቅር ለሆነው ይሆዋ ራስን ከመስጠት ያነሰ ችሮታ አያረካውምና (ዮሐ. 10፥11)፡፡

እንደ ገናም የይሆዋ እረኛነት በምድረ በዳ መንጋውን ሲመራ በነበረው ባሕርያዊ ሕይወቱ በሆነው በጌታ መንፈስ ቅዱስ ጥበቃና እንክብካቤ ተረጋገጠ (ኢሳ. 63፥14፤ መዝ. 78፥52)፡፡ እንግዲህ ጌታ ቢፈቅድ በሚቀጥለው ዕትም ስለ ጌታ እግዚአብሔር ወልድ ማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆዋ እንደ ሆነ ተከታታይ ትምህርት ይቀርባል፡፡

በጮራ ቍጥር 5 ላይ የቀረበ

1 comment:

  1. Bibel wust Egziabher Ab yemil ale Egziabher wold Egziabhe menfes kidus yemil geen yelem. Ye Egziabher lij weyem ye Egziabher menfes yelal. tadiya wendeme keyet amtetewu newu yeminagerut?

    ReplyDelete