Friday, February 1, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት

ከሁሉን መርምር
(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ)
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት 18 ናቸው፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐዶሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡መጠሪያቸው እንደሚያስረዳው እነዚህ ተጨማሪ መጻሕፍት ቀደም ሲል ከቅዱሳት መጻሕፍት ቊጥር ውጪ እንዲሆኑና በአዋልድነት እንዲጠሩ ያደረጋቸው አያሌ ታዋቂ ምክንያቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ከአዋልድ መጻሕፍቱ ጋር ታትመው ቢሆኑ ኑሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ባላደናገሩ ነበር፡፡

የብሉይ ኪዳን መምህራን ስለ እያንዳንዱ ዲዮትሮካኖኒካል መጽሐፍ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙባቸውን ነጥቦች በመጠቈም ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡

መጽሐፈ ዮዲት

ም. 1፥1 “በባጥና ለሜዶን በነገሠ በአርፋክሳድ ዘመን ከፍ ባለች በነነዌ አገር ለፋርስ የነገሠ ናቡከደነፆር በነገሠ ባሥራ ሁለተኛው ዓመት” ይላል፡፡

በናቡከደነፆር ዘመን ትይዩ አርፋክሳድ የተባለ የሜዶን ንጉሥ ነግሦ ነበርን? ፍራአርቲስ ወይም ሲያክስሬስ ለማለት ይሆን?

ናቡከደነፆርም በነነዌ አልነገሠም በባቢሎን እንጂ፡፡ የአሦር መናገሻ ከተማ የነበረችው ነነዌ በናቡከደነፆር አባት በናቦፓላዛር ዘመነ መንግሥት (612 ከክ.ል.በ) ተደምስሳ ነበር፤ በትንቢተ ናሆም 3፥1-7 እንደ ተተነበየው፡፡

የናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት ግን (605-562 ከክ.ል.በ.) እንደ ነበረ ታውቋል፡፡

ም. 2፥21 ጀምሮ እስከ ም. 4 ድረስ ያለው ምንባብ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት በሆሎፎርኒስ የተመራው የባቢሎናውያን ጦር ከነነዌ በመነሣት ወደ በቂጤሊት ከዚያ ሎድ ፌድ፥ ፌስላ፥ ኤሊም፥ ኤፍራጥስንም በመሻገር ሜስፖታሚያ ኪልቅያ፥ ምድያም፥ ደማስቆ፥ ጢሮስ፥ ሲዶና፥ አቴና፥ አስቀሎና፥ አዛጦን የተባሉትን አገሮች በቅደም ተከተል እየወረረ ወደ ምድረ ይሁዳ ተጓዘ ይላል፡፡ ከዚህ ትረካ በመነሣት ጂኦግራፊያዊ መሥመሩን ለመከተልና አባባሉን ለመረዳት አስቸጋሪም የማይቻልም ነው፡፡

ም. 5፥5-19 የአሞን ልጆች ሹም የነበረው አክዮር ወደ ባቢሎን ጦር ሠራዊት አለቃ ወደ ሆሎፎርኒስ ቀርቦ ስለ እስራኤል ልጆች አነሣሥና አወዳደቅ እንደ ተረከለት ይናገራል፡፡ የእስራኤል ልጆች አባቶች ከከለዳውያን ምድር በመነሣት ወደ ካራን ከዚያም ወደ ምድረ ከነዓን እንደ መጡ ቀጥሎም ወደ ግብጽ እንደ ወረዱ ከዚያም ተመልሰው ምድረ ከነዓንን እንደ ወረሱ አክዮር ከተረከ በኋላ፥ “… ያዘዛቸውን ሥርዐት ባፈረሱ ጊዜ ግን ፈጽሞ ብዙ በሆነ ጦር አጠፋቸው ቤተ መቅደስ ፈረሰ ምድረ በዳም ሆነ … ዛሬ ግን ወደ ፈጣሪያቸው ተመለሱ ከተበተኑበትም አገር ተሰበሰቡ፤ ቤተ መቅደስ ባለበት በኢየሩሳሌም ኖሩ” ይላል፡፡

ይህ ድርጊት እየተፈጸመ ያለበት ጊዜ የናቡከደነፆር 18ኛ ዓመተ መንግሥት እንደ ሆነ በም. 2፥21 የተረከው እውነት ከሆነ ከዚያ ጊዜ በፊት የእስራኤል ቤተ መቅደስ አልፈረሰም፡፡ እንደ ገናም አልተሠራም፡፡ ሰሎሞን የሠራው ቤተ መቅደስ ሊፈርስ ነገደ ይሁዳም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ባዕድ ሀገር ሊማረክ ናቡከደናፆርም በዚህ በ18ኛ ዓመተ መንግሥቱ ከበባ ጦርነት ገና እያስደረገ ነበርና (2ነገ. 25፥1-21፤ 2ዜና. 36፥13-21)፡፡

ቤተ መቅደስ ከፈረሰና ሕዝበ አይሁድ ወደ ባቢሎን ከፈለሱ በኋላ እንዲሁም 70 ዓመታትን በምርኮ አሳልፈው ወደ አገራቸው ከተመለሱና ቤተ መቅደስን እንደ ገና አንጸው አምላካቸውን እያመለኩ መኖር ከጀመሩ በኋላ የተደረሰ መሆኑን ከደራሲው አተራረክ መረዳት አያዳግትም፡፡ ደራሲው ድርሰቱን ከጻፈበት ጊዜ ወደ ኋላ ራሱን መልሶ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረ ለማስመሰል ሲል የጋረደውን ሰው ሠራሽ መጋረጃ የአንባቢ ትዝብት ሲገልጥበት ከትዝብቱ ፍላፃ አያመልጥም ማለት ነው፡፡

ም. 6፥1-2 አሞናዊው አክዮር ቤተ መቅደሳቸውን እንደ ገና ሠርተውና ከተበተኑበት አገር ተሰብስበው አምላካቸውን እያመለኩ ያሉትን ሕዝብ ቢወጋ ድል እንደማያደርግ በም. 5 ያደረገለትን ገለጻ ሲያዳምጥ የቈየው የባቢሎናውያን ጦር አለቃ ሆሎፎርኒስ ተራኪውን አክዮርን የእስራኤልን ልጆች አትውጉ የምትለን የዐሥሩ ነገድ ጠንቋይ ነህን? ሲለው ይነበባል፡፡

የዐሥሩ ነገድ መንግሥት ከፈረሰ፤ ሕዝቡ ከተማረከ በዚህ ጊዜ ከ 130 ዓመት በላይ ሆኖት ነበር፡፡ ከሕዝቅያስ ንጉሠ ይሁዳ 6ኛ ዓመት ጀምሮ ሲቈጠር ማለት ነው (2ነገ. 13፥9-12)፡፡ የአሁኑ የናቡከደነፆር ከበባ ነገደ ይሁዳን ብቻ የሚመለከት ነበር፡፡

ም. 9፥6 ጀምሮ ዮዲት ስትጸልይ፥ “ከዚህ አስቀድሞ ለግብጻውያን ታምራት አድርገሃልና ፈጣሪዬ እግዚአብሔር እኔን ድኻዪቱን ልመናዬን ስማኝ በነሰናክሬም፥ በነብልጣሶር፥ በነሆሎፎርኒስ፥ በጽርአውያንም የተደረገውን አንተ ዐውቀህ ተደረገ” ከማለት ተነሥታ አሁንም የዚያን ዐይነቱን ድል እንዲሰጣት ከጸለየች በኋላ እግዚአብሔር ወገኗን የምትታደግበትን ድል እንደ ሰጣት ይተርካል (ም. 13፥14-15)፡፡

እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ በተኣምራት ማውጣቱ ያለፈ ታሪክ ስለ ነበረ በኀላፊ ጊዜ መጠቀሱ ተገቢ ነበር፡፡

የሰናክሬምም ወረራ መክሸፍ ያለፈ ጊዜ ታሪክ ስለ ነበረ እንደዚሁ በኀላፊ ጊዜ መነገሩ ተቀባይነት አለው፡፡ ነገር ግን፡-
1.     ብልጣሶር ከናቡደነፆር በኋላ ከሚነግሠው ከኤዊልማሮዴቅ ቀጥሎ ገና ወደ ፊት የሚነሣ ንጉሠ ባቢሎን ስለ ሆነ፤ 2ነገ. 25÷27፡፡
2.    ሆሎፎርኒስ በዚህ በመጽሐፈ ዮዲት ታሪኩ የቀረበውን የአሁኑን ውጊያ በመምራት ላይ የነበረ የባቢሎን ጦር ሠራዊት አለቃ ስለሆነ፤ ም. 2፥4-6፡፡
3.    ጽርአውያን በሚል ቃል የተገለጸው ቡድን መንግሥተ ባቢሎንና መንግሥተ ፋርስ ተራ በተራ እየገዙ ካለፉ በኋላ ማለት በታላቁ እስክንድር መሪነት የሚነሣ የግሪክ መንግሥት በመሆኑ ዳን. 8፥20-22 በኀላፊ ጊዜ ሊቀርብ የሚገባው ታሪክ አልነበረም፡፡

የመጽሐፈ ዮዲት ደራሲ በመንግሥተ ዮናናውያን ዘመን እንዲያውም በመቃብያን የትግል ዘመን የተነሣና እነዚህን ደምስሶ የሚቋቋም መንግሥተ አይሁድን የሚመኝና ይህንኑ በአእምሮው እየሣለ በቃላት መግለጽ የሞከረ ተምኔታዊ ጸሐፊ ይሆን? ታዲያ ከአይሁድ ምርኮ በፊት የነበረ መስሎ ለምን ቀረበ?

ም. 16፥23-30 ዮዲት በሆሎፎርኒስ የተመራውን የናቡከደነፆርን ሠራዊት ድል ካደረገች በኋላ ተከብራ መኖርዋን ይገልጽና በ105 ዓመት ዕድሜ መሞቷን ያስረዳል፡፡ ይቀጥልናም “የእስራኤልን ልጆች በዮዲት ዘመን ያስፈራቸው የለም፡፡ ዳግመኛ ከሞተች በኋላ ብዙ ዘመን ያስፈራቸው የለም” ይላል፡፡

በመጽሐፈ ዮዲት ከዚህ በላይ የተገለጸው የጦርነት ታሪክ መነሻ ደራሲው እንዳለው የናቡከደነፆር 18ኛው ዓመተ መንግሥት ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት የኢየሩሳሌም ከተማና ቤተ መቅደሱ ተደመሰሱ፤ ነገደ ይሁዳም ወደ ባቢሎን ፈለሱ ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተገልጾ የለምን? 2ነገ. 25፥8-12፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ይሁዳ ከዚህ ከናቡከደነፆር ወረራ በኋላ
1.     የመንግሥተ ባቢሎን
2.    የመንግሥተ ፋርስ
3.    የመንግሥተ ዮናናውያን (የግሪክና የእርሱ ተቀጥላ) መንግሥታት ቅኝ ግዛት ተደረገች፡፡ በመቃብያን ዘመን በትግል ነፃነቷን አውጃ ለጥቂት ዓመታት ብትቈይም ወዲያው በመንግሥተ ሮም ሥር ወደቀች፡፡ ባዕዳን ገዥዎችም ሲፈራረቁባት ኖረች፡፡ ከ1948 ዓ.ም. በፊት ነጻ መንግሥት አልነበረችም፡፡
ስለዚህ በመጽሐፈ ዮዲት የሰፈረው ትረካ በታሪካዊነቱም እሙን አልሆነም፡፡ ልባዊ ምኞት ነው ቢባልም ከምኞትነቱ አላላፈም፡፡

No comments:

Post a Comment