Sunday, February 3, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተ ሰባቸው
 (በጮራ ቊጥር 5 የቀረበ)
የአለቃ እልፍኝ እንደ ተለመደው በሰዎች ተሞልታለች፡፡ ልዕልት፥ አንተነህና ግሩም እንግዶቹን በማስተናበር ከቈዩ በኋላ፥ ወደ በሩ አጠገብ ተቀምጠዋል፡፡ የዐይን መነጽራቸውን እንደ ሰኩ፥ በፊታቸው ትልቅ መጽሐፍ በአትሮንስ ላይ ዘርግተው ከፍ ባለ በርጩማ ላይ በእንግዶቹ መሐል የተቀመጡት አለቃ ነቅዐ ጥበብ ጉባኤውን በጸሎት አሳልፈው ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ ቀጥለውም ወደ ሰዎቹ ቀና ብለው አንድ በአንድ ተመለከቷቸውና “የዛሬው ውይይት በምን ርእስ እንዲሆን ወስናችኋል?” አሉና ጠየቁ፡፡

ዲያቆን ምስግና መስቀልኛ ያደገደገውን ኩታውን ከአመቻቸ በኋላ፥ “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት ቢያስረዱን? አንብቡ የተባልነውን ኦሪት ዘሌዋውያን ከም. 4-6 ያለውንና ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈውን መልእክት ደጋግመን አንብበናል፡፡ በዚህ ርእስ የሚሰጡንን ማብራሪያ ለመከታተል ተዘጋጅተናል፡፡” ሲል ሁሉም ዲያቆን ምስግና በተናገረው መስማማታቸውን ለመግለጽ ራሳቸውን ወደ ላይና ወደ ታች ነቀነቁ፡፡


አለቃ ነቅዐ ጥበብ ጒረሮአቸውን አጠሩ፤ እእእ-እእእ-እእ … “ለዕብራውያን ከተጻፈው መልእክት ከመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ቊጥሮች አንብብ” አሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ አነበበ፡፡ ሲያብራሩም እንዲህ አሉ፤ “በቀድሞ ዘመናት እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ለአባቶቻችን ብዙ ጊዜ ተናግሮ እንደ ነበረ ጸሓፊው ከአስረዳ በኋላ በመጨረሻ ዘመን ግን በልጁ በኩል ተናገረን ይላል፡፡ እኛን የተናገረበት ልጁን፥
§  ዓለማትን የፈጠረበት ባሕርያዊ ቃሉ፣
§   የክብሩ ነጸብራቅ፣
§  የባሕርዩ ምሳሌ፣
§  የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ የወረሰ፣
§  ዓለማትን አጽንቶ የያዘ፣
§  ኀጢአታችንን በራሱ ያነጻ፣
§  በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠ ነው በማለት ያስረዳናል፡፡

በእነዚህ ቊጥሮችና በተከታታይ ምዕራፎች እግዚአብሔር ቀደም ሲል ከሰዎች ጋር የመሠረተው ግንኙነት ፍጹም እንዳልነበረ ካሳየን በኋላ፥ አሁን ያን ግንኙነት በፍጹምነት ወደሚገኝ ደረጃ በማድረስ እንዳሳደገው ይነግረናል፡፡ ሰዎች ነንና ስለ ግንኙነት ብዙ እናውቃለን፡፡ በጉርብትና፥ በሥራ፥ በጋብቻ፥ በሌላም ምክንያት ግንኙነት በሰዎች መካከል ይፈጠራል፡፡ ሀገሮች ወይም መንግሥታት የሚያገናኛቸው ጒዳይ ከሌለ የግንኙነት መሥመር አይዘረጉ ይሆናል፡፡ የጋራ ጒዳዮች ሲወለዱ ግን ግንኙነቱን ደረጃ በደረጃ ማለት በደብዳቤ፥ በመልእክተኛ፥ በጒዳይ ፈጻሚ፥ በቆንሲል ደረጃ ይመሠርቱት ይሆናል፡፡ የጋራ ጒዳዮቻቸው መብዛት ግፊት እያመጣ ሲሄድ ግንኙነታቸውን በማዳበር በአምባሳደር ደረጃ ያሳድጉታል እንበል፡፡ በመንግሥታቱ መካከል እየዳበረ የመጣው ይህ ዐይነቱ ግንኙነት ጤናማ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ደረጃው እንደማያዘቀዝቅ፥ ወደ ቆንሲል ወይም ወደ ጒዳይ ፈጻሚ ደረጃ እንደማይወርድ የታወቀ ነው፡፡” አሉና አለቃ መነጽራቸውን አስተካካሉ፡፡

በመቀጠልም “እግዚአብሔር ከሰው ጋር ቀድሞ የመሠረተው ግንኙነት በተለያየ መንገድ በነቢያት አማካይነት እንደ ነበረ ከቃሉ ተረዳን፡፡ በዚያ አላቆመም፤ በዘመን መጨረሻ ማዕርጉና ክብሩ ከፍ ብሎ በተገለጸው በልጁ በኩል ሰውን ሲገናኝ የእግዚአብሔርና የሰው የግንኙነት ደረጃ እስከ ፍጹምነት ማደጉን ያበሥረናል፡፡ በልጁ በኩል፥ የሆነው የግንኙነቱ ደረጃ ወደ ፍጹምነት ደርሷል፤ ከዚያ በላይ የሚያድግበት ደረጃ ከቶ አልተተወም፡፡ በተጨማሪም ለመጨረሻ ዘመን በእግዚአብሔር የተወሰነ የእድገት ጣሪያ ስለሆነ ለፍጻሜ ዘመን የተመደበው ከተገኘ ሌላ ምንም አይጠበቅም፡፡ እንዲህ ስለሆነ የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት በደረሰበት የእድገት ፍጹምነት ላይ ይቈያል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ ደረጃውን ከልጁ አንሥቶ ወደ ነቢያት፥ ጊዜውንም ከመጨረሻው ዘመን ወደ መጀመሪያ ዘመን ማለት ወደ ኋላ አይመልሰውም፤ ዲያብሎስ ይፈር፡፡ ታዳምጡኛላችሁ?” አሉና በረጅሙ ተነፈሱ፡፡

አለቃ ነቅዐ ጥበብ ሁሉንም በየተራ በመመልከት መነጽራቸውንም ከፍ ዝቅ በማድረግ እያስተካካሉ አድማጮቻቸው እየተከተሏቸው መሆኑን ከየግንባራቸው ለማረጋገጥ ሞከሩ፡፡ ቀጠሉናም “የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ በመጨረሻ ዘመን እኛን ይገናኝበት ዘንድ እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከው የልጁ ውክልና (አምባሳደርነቱ) ለእግዚአብሔር ብቻ እንዳልሆነ እንድናውቅ መንገድ ከፍቶልናል፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ ፍጹም ሰው ሆኖአል፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ ፍጹም ሰው ሆኖአልና የሰዎች ወንድም ነው (ዮሐ. 1፥1-15፤ ዕብ. 2፥14)፡፡ አስተውሉ! ፍጹም ሰው በመሆኑም እግዚአብሔርና እኛ ሰዎች፥ በአንድ አካል ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ እኩል ዝምድና አለንና በግንኙነቱ መሥመር ከተመለከትነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የእግዚአብሔር አምባሳደር፥ ለእግዚአብሔርም የሰው አምባሳደር ሆኗል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርና ሰው ለመሠረቱት፥ ላዳበሩትና ወደ ፍጹምነት ደረጃ ላደረሱት ግንኙነት ለየራሳቸው ሁለት የተለያዩ ወኪሎችን (አምባሳደሮችን) መሰየም አላስፈለጋቸውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ መካከለኛ ሆኖአልና፡፡ እየተከታተላችሁኝ ነው?” አሉና አለቃ ግንባራቸውን ቋጠር ፈታ መነጽራቸውንም ከፍ-ዝቅ እያደረጉ ቈዩና ቀጠሉ፡፡

“እንግዲህ ቀድሞ ማለት በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔር በኩል የመካከለኛነት ማዕርግ ከተሰጣቸው ከሙሴ፥ ከአሮን፥ ከኢያሱና ከመሳሰሉት ሁሉ ይልቅ የኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ብልጫው እንዴትና ምን ያህል እንደ ሆነ በዕብራውያን መልእክት ከም. 3-10 በዝርዝር ተገልጿል፡፡ የእነ ሙሴ መካከለኛነት በደረጃው ዝቅተኛ ነበር፤ የሰውን ዘር ብቻ የሚወክሉ ሰዎች ብቻ መሆናቸው ሲታወቅ፥ በእርሱ ዘመን እግዚአብሔር የወከለው እግዚአብሔርነት የሌላቸውን ሰዎችን (ዕሩቅ ብእሲ የሚባሉትን) ነበርና፡፡ እንዲሁም ውክልናቸው ለተለያየ የግንኙነት መሥመር እንጂ ለአጠቃላይ ጒዳይ አልነበረም ማለት፥
ሙሴ ለነቢይነት፥ ለአስተዳዳሪነት
አሮን ለክህነት
ኢያሱ ለጦር መሪነትና ሕዝብን ለማስፈር
የዛሬ ጥያቄአችሁ የሆነው የአማላጅነት ጒዳይ በክህነት የተመደበውን አሮንንና ልጆቹን ይመለከት ነበር፡፡ ዐልፎ ዐልፎ ሌሎቹም እየደረቡ የምልጃን ሥራ ሲያከናውኑ ቢታይም የማማለድ ኀላፊነትና ተግባር የአሮንና ልጆቹ የሥራ መደብ ነበር፡፡ የክህነት ሥራ በምልጃ ላይ የተመሠረተ የማስታረቅ አገልግሎት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ማስታረቅ የሚባለው በሁለት ሰዎች በኩል የሚቀርበውን አቤቱታ አዳምጦና ጥፋተኛው ማን እንደ ሆነ መርምሮ የዝምድና ውሳኔ የሚሰጥበትና በዕርቅ እንዲፈጸም የሚደረግበት ተግባር ሲሆን፥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ሁኔታ የተስተዋለ እንደ ሆነ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ምን ጊዜም ዐጥፊው ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ሁል ጊዜም ዕርቁ የሚፈጸመው፥ እግዚአብሔርን በመማለድ ነው፡፡ ሰዎችን የማስታረቅ ሥርዐት አሁን ባለንበት ዘመን እንዴት እንደ ሆነ ማን ይነግረኛል?” አሉና አለቃ ለአድማጮቻቸው የተሳትፎ ዕድል ሰጡ፤ ከግራ ወደ ቀኝ እያማተሩ ሳለ አቶ ሀብቴ አእምሮ እጃቸውን አወጡ፥ ተነሥተውም ሲያስረዱ፥

“ሁለት የተጣሉ ቡድኖች ወይም ግለ ሰቦች ባልና ሚስትም ቢሆኑ ለየራሳቸው የሚመርጧቸውን ሰዎች በማቅረብ አንድ አስታራቂ ኮሚቴ ወይም የቤተ ዘመድ የሽምግልና ጉባኤ ይሰይማሉ፡፡ የተሰየመው ጉባኤ እንደ አንድ አካል ሆኖ የሁለቱን ቡድኖች ወይም ግለ ሰቦች ጒዳይ ይመረምራል፤ አንዱ በደለኛ ሆኖ ከተገኘ ለተበደለው እንዲክስ ይወስናል፡፡ ተበዳዩ ለበደለኛው ይቅርታ እንዲያደርግ ይማልዳል፤ ያስታርቃል፡፡” አሉና ተቀመጡ፡፡

አለቃ ነቅዐ ጥበብ ለጥያቄያቸው ተገቢ መልስ ሲሰጥ “መልካም መልካም” ማለት ይቀናቸዋል፡፡ አሁንም “መልካም” አሉ፡፡ “በቀድሞ ዘመን በአስታራቂነት የተመደቡት አሮንና ልጆቹ ሰውንና እግዚአብሔርን የማስታረቁን ኀላፊነትና ተግባር በፍጹምነት ደረጃ ለመወጣት ያልቻሉበት ጒድለት በግልጽ ሊታየን ይገባል፡፡ ሰዎች ብቻ እንደ መሆናቸው መጠን ለሰው ዘር ወኪሎች መሆን ቢችሉም እግዚአብሔርነት አልነበራቸውምና በአስታራቂው አካል የእግዚአብሔር ውክልና አልነበረበትም ማለት ነው፡፡ ስለ ሆነም የዚህን የሥራ መደብ ደረጃ በዚህ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ወደ ፍጹምነት አሳደገው፡፡ ፍጹም እግዚአብሔር የሆነው ቃል ፍጹም ሰው ሆኖአልና በሊቀ ካህናትነትም ተመድቦአልና፡፡ እግዚአብሔርና ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም የማስታረቁን ሥራ በፍጹምነት አከናወነው፤ ኀላፊነቱንም በብቃት ተሸከመው፡፡ ይህ በእግዚአብሔር ቃል የተደገፈው እውነት ለአውጣኬ ልጆች አይዋጥላቸውም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ሰዎች ይከናወኑ የነበሩትን የነቢይነትን፥ የንጉሥነትን ሥራዎች ከክህነት ጋር አዋሕዶ ተሾሞባቸዋል፡፡ አሁን የጀመርነው የክህነት ጒዳይ ስለ ሆነ ወደዚያው ተመልሰን ለክህነቱ ሥራ እነ አሮን ያላሟሏቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የተገኙትን መስፈርቶች እንዘርዝራቸው፤ መስፈርቶቹን ብትጽፏቸው ለወደ ፊቱ ለማስታወስና ለመከለስ አትቸገሩም” አሉ፡፡ ወዲያው ዲያቆን ምስግና ድግድጋቱን እያስተካከለ ተነሣና “የኔታ በምንጽፍበት ጊዜ አንዳንድ ተፈላጊ ነጥብ እያመለጠን ስለ ተቸገርን መቅረጸ ድምፅ አዘጋጅተናል በዚህ እመካከል በተቀመጠው መቅረጸ ድምፅ ትምህርቱ በሙሉ እየተቀዳ ስለ ሆነ፥ በመጨረሻ እያባዛን ድርሻ ድርሻችንን እንወስዳለን” ሲል አስረዳቸው፡፡

“መልካም” አሉ መነጽራቸውን እያስተካከሉ “መልካም በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ተሟልተው በፍጹምነት ደረጃ የተገኙት መስፈርቶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.     አሮንና ልጆቹ ካህናት የሆኑት ከሌዊ በሥጋ በመወለድ ብቻ እንጂ ሌላ የብቃት መለኪያ አልነበራቸውም፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሌዊ ነገድ ሳይወለድ በማያልፍ ሕይወት ኀይል ተሾመ (ዕብ. 7፥11-16)፡፡
2.    አሮንና ልጆቹ በተወሰኑ የዕድሜ ክልል በተገኙበት ጊዜ በክህነት እንዲያገለግሉ ተወስኖ ነበር፡፡ ያንን የዕድሜ ክልል ከመጨረሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ በሞት ይቀጩ ነበር፡፡ እንዲህ ስለ ሆነ በዘመናት ውስጥ ብዙ ካህናት ሞቱ፤ ብዙ ካህናትም ተተኩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለተወሰነ የዕድሜ ወይም የዘመን ክልል ሳይሆን ለዘላለም ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ በመሐላ ተሾመ (ዕብ. 7፥17-22)፡፡
3.    አሮንም ሆነ ካህናት የሆኑት ልጆቹ ሲሞቱ ሌላ ካህን ይተካ የነበረበት ምክንያት ሲሞቱ የምልጃና የማስታረቁን አገልግሎት ሊቀጥሉ ስለማይችሉ ነበር፡፡ የማማለድና የማስታረቅ ሥራ የሚከናወነው ነፍስ በአካለ ሥጋ በምትገኝበት ጊዜ ብቻ ሲሆን ከሞቱ በኋላ ወደ መቃብር በገባው ሥጋቸው ወይም እግዚአብሔር በወሰነላት ስፍራ በተሰየመችው ነፍሳቸው የምልጃንና የማስታረቅን ሥራ ሊሠሩ ስለማይችሉ ሌላ በሕይወተ ሥጋ ያለ ካህን ለሥራው መተካት ነበረበት፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ስለ ተነሣ፥ ነፍሱ በሲዖል አልተተወችም፤ ሥጋውም በመቃብር ውስጥ አልቀረም፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ በአርባኛው ቀን ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀምጦአል (ሐ.ሥ. 2፥23-36)፡፡ እንዲህ በመሆኑም የማይለወጠው ክህነቱ ለዘላለም ስለሚኖር ያማልዳል፤ በእርሱ በኩል የሚመጡትንም ያድናቸዋል (ዕብ. 7፥23-28)፡፡

ከዚህም በላይ እነ አሮን እንደ ማንኛውም ሰው ኀጢአተኞች ነበሩና ለሌላው ሰው ስርየት ከመጠየቃቸው በፊት ስለ ራሳቸው መሥዋዕት ማቅረብ ይገደዱ የነበረ ሲሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ያለ ነውር የተወለደና የኖረ ስለ ሆነ ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡

እነ አሮን ለራሳቸውም ሆነ ለሕዝቡ የእርድና የእህል መሥዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን በመሥዋዕትነት አቀረበ፡፡

አሮንና ልጆቹ የማያቋርጥ መሥዋዕት ዕለት ዕለት ማቅረብ የተገባቸው ሲሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን አንድ ጊዜ ብቻ በማቅረብ ዘላለማዊ ስርየትን አስገኘልን፡፡ ይህ ሁሉ ከዕብራውያን ምዕራፍ 7፥26-28 ሳንወጣ የምናገኘው ማስረጃ ነው፡፡ በያንዳንዱ ምዕራፍም ሰፊ ማነጻጸሪያ ጸሓፊው አቅርቧል፡፡ በየግላችሁም በኅብረትም አንብቡት” በማለት አለቃ በረጅሙ ተነፈሱና ዝም አሉ፡፡ መነጽራቸውንም ያመቻቻሉ፤ ግንባራቸውን ቋጠር ፈታ ያደርጋሉ፤ አድማጮቻቸውን አንድ በአንድ ይመለከታሉ፡፡ ልጃቸው አንተነህ ንግግራቸውን የጨረሱ መሰለውና እጁን በማውጣት ቆመና “አባባ ጥያቄው ገና በሙሉ ምላሽ አላገኘም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነትና አስታራቂነት በመስቀል ላይ ነፍሱን እስከ ሰጠበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን እርሱ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ይማልዳል እንጂ አማላጅ አይሆንም የሚሉ ሰዎች አጋጥመውናል፡፡ በማስረጃነትም የሚጠቅሱት በዮሐ. 16፥26 ያለውን ነው፡፡ አሟልተው መልስ ቢሰጡበት” አለና ተቀመጠ፡፡

“አዎን ስለ ዮሐንስ 16፥26 በኋላ ተመልሰን እንነጋገራለን” አሉ አለቃ፤ “በቅድሚያ ግን እነዚህን ጥያቄዎች እንመልስ፡፡ አንደኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ዘላለማዊ ነው? ወይስ እንደ እነ አሮን ጊዜያዊ ነው? ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይነቱን፥ ንጉሥነቱን፥ ካህንነቱን በፍጹምነት ደረጃ ያስገኘለትን ፍጹም እግዚአብሔር ፍጹም ሰው የሆነበትን የመካከለኛነት ሥራ መደብ (ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ የተሰኘበትን) ማዕርግና ክብር ከትንሣኤው በኋላ ተነጥቆአልን? ሦስተኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በመካከለኛነት፥ በአማላጅነትና በአስታራቂነት ላይ መሆኑን የሚገልጹ ጥቅሶች የሉምን? ለመጀመሪያ ጥያቄ የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ዘላለማዊ ነው፤ እግዚአብሔር አብ አንተ ለዘላለም ካህን ትሆን ዘንድ ማለ፤ በመማሉም አይጸጸትም የሚለውን እስኪ አንድ ሰው ያንብብ” ሲሉ ልዕልት መዝ. (110)፥4፤ ዕብ. 7፥20-25ን አነበበች፡፡ “የማይለወጥ፥ የማይሻር ለዘላለም የሚኖር ክህነት አለው፡፡” ሲባል ከመስቀል ሞት በኋላ ካህን አይደለም ማለት እልከኛነት ነው፡፡

ሁለተኛ ክህነቱ የተመሠረተበት መካከለኛነቱ፥ እግዚአብሔርና ሰው በመዋሐድ ክርስቶስ ከሆነበት ምስጢር ጋር የተቈራኘ ነው፡፡ ብቃት ባልነበራቸው በፍጹምነት ደረጃ አገልግሎት ሊሰጡ ባልቻሉ ብዙ ሰዎች ተይዞ የነበረውን መካከለኛነት ወደ ፍጹምነት ደረጃ አደገ ማለት የተቻለው እግዚአብሔርና ሰው በአንድ አካል ተዋሕደው ለሁለቱም እኩል ዝምድና ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማስገኘታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ማእከላዊነት በተዋሕዶ የጸና ዘላለማዊ እንጂ በጊዜያዊነት እንደ ተሰየመ ኮሚቴ የሚፈርስ አይደለም፡፡ በ1ጢሞ. 2፥5 እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛም አንድ እንደ ሆነ ይነግረናል፡፡ ይህም መካከለኛ ራሱን ለሁሉ ቤዛ የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ቃል አለ፡፡ ይህን ቃል ብናስተውለው (ሀ) የተጻፈው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ እጅግ ዘግይቶ በግምት ከ60 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ (ለ) ይህ መልእክት በተጻፈበት ጊዜ  በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ ያው ራሱን በቤዛነት የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ ይነግረናል፡፡ ከዚሁ ጋርም በዕብራውያን መልእክት 8፥6 እና 12፥24 የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ ይነበባል፡፡ የዕብራውያን መልእክትም ከ60 ዓ.ም. በኋላ እንደ ተጻፈ የሚገመት ሲሆን ኀላፊ ጊዜን ሳይሆን የአሁን ጊዜን ያመለክታል፤ ማለት ነበረ፥ አይልም ነው ይላል እንጂ! የመናፍቃን ክፍሎች “ተዋሕዶ” እስከ መስቀል ድረስ ይመስላቸዋል፤ ይህ የእነሱ ብሂል መሆኑን ዐውቀን ከመርዛቸው ራሳችንን እንጠብቅ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የቀረበውን ጥያቄ እንመልሰው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ጊዜ አማላጅ እንደ ሆነ የሚናገሩትን ጥቅሶች እንይ፤
ሀ) በሮሜ 8፥34 የእኛ አማላጅ ከሙታን የተነሣው በአብ ቀኝ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው አይልምን?
ለ) በዕብ. 7፥23-35 ባሉት ቊጥሮች “ለዘላለም ካህን ትሆን ዘንድ ሾሜሃለሁ” ስለ ተባለ የማይለወጥ ክህነትን ይዞ እያማለደ ለዘላለም እንደሚኖር አይናገርምን?
ሐ) እንዲያውም በዕብ. 7፥26 ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጡ ይልቁን ተገቢ ሊቀ ካህናት እንደሚያደርገው ይገልጻል” አሉና አለቃ ጥቂት ዐሰብ አደረጉ፡፡ ቀጠሉናም፥ “በአራተኛ ደረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በተናገራቸው ቃሎችና በመረጣቸው በሐዋርያቱ ምስክርነት የመካከለኛነቱ ሥራ ጊዜያዊና ከመስቀል በኋላ የሚከስም መሆኑ ተጠቊሞአልን? እንመርምር፡፡
1.     ዮሐ. 10፥9 የበጎች በር እኔ ነኝ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤
2.    ዮሐ. 14፥6 እኔ መንገድ ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚደርስ የለም፤
3.    ዕብ. 7፥25 በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ያድናቸዋል፡፡

እንግዲህ በእነዚህ ክፍሎች አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ሲሰጥ ዘላለማዊ ስርየት በማስገኘቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም መባሉ መሥዋዕቱ ኀጢአትን ለዘላለም ለማስተስረይ ብቃት ስላለው ነው (ዕብ. 9፥23-28፤ 10፥11-18)፡፡ ዕለት ዕለት መሥዋዕት አለማቅረቡ በሊቀ ካህናትነት ሥራው የተሻረ መስሎአቸው ይሆን? እናንተ ግን በአብ ቀኝ የተቀመጠውን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ ዕብ. 3፥1” አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ተከዝ ብለው፡፡

ቀጥለውም “እንግዲህ ወደ ዮሐንስ 16፥26 እንመለስ አሉ ጥቅሱን አንብቡ አንዳችሁ!” ተነበበ፡፡ “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይምሰላችሁ” ይላል ጥቅሱ፡፡ ኰስተር ባለ አነጋገር አለቃ ማብራሪያቸውን ቀጠሉ፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ከእነርሱ የሚለይበት ጊዜ መድረሱን ርእስ በማድረግ በሚናገርበት ጊዜ የደቀ መዛሙርት ልብ በሐዘን ተሞልቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ሐዘን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ተናገረ፡፡ ስለ ሆነም ወቅትን የሚያመለክቱ ቃላትን ደጋግሞ ተጠቀመ፡፡ ከቊጥር 16  ጀምሮ ያሉትን ጥቅሶች ብንመረምራቸው ቊጥር 16-20 “ጥቂት ጊዜ አለ እኔን የማታዩበት፤ ቀጥሎ ለጥቂት ጊዜ ታዩኛላችሁ፤ ከዚያም ወደ አብ እሄዳለሁ” ይላል፡፡ እንደዚሁም ሌሎቹን ቊጥሮች ብናነብ ቊ. 21 የምጥ ወራት፥ ቊ. 22 አሁን፥ እንደ ገና፥ ቊ. 23 በዚያን ቀን፥ ቊ. 24 እስከ አሁን፥ የምናገርበትና የማልናገርበት ሰዓት ቊ. 26 በዚያ ቀን (እንደ ቊጥር 23) እንግዲህ ክሥተቶችና ድርጊቶች የሚፈጸሙበት በየወቅቶቹ ውስጥ ስለ ሆነ የንግግሩን መሠረታዊ ሐሳብ ለመረዳት ወቅቶችን ከየተገቢ ክሥተቶችና ድርጊቶች ጋር በአግባቡ ማገናኘት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ በሰዋስዋዊ አገባብ መሠረት የቃላትን ትርጉም ትንተናና ሙያ መረዳትም ይቻላል፡፡
 ከቊ. 22 ብንጀምር
§  “እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል” መቼ? ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለ3 ቀናት፤
§  “እንደ ገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል” መቼ? ከትንሣኤው በኋላ፤
§ ቊ. 23 “በዚያ ቀን ከእኔ አንዳች አትለምኑም፤ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አብ ይሰጣችኋል፤ በተመሳሳይም፥
§ ቊ. 26 “በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለም፤ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና” መቼ?

የአንዳንድ ሰዎች ችግር ይህን “በዚያ ቀን የተባለ ውሱን ወቅት የቱ እንደ ሆነ ከመረዳቱ ላይ ነው፡፡ የችግራቸውም ምንጭ አንድ ጥቅስን ከፊትና ከኋላ ካሉ ጥቅሶች ጋር አዛምዶና በሰዋስዋዊ አገባባቸውም ተጠቅሞ የመረዳትን ችሎታና ፍላጎት ከማጣት የተነሣ ነው፡፡

በቊጥር 23 በተመሳሳይም በቊ. 26 በዚያን ቀን የተባለው ውሱን ወቅትን የሚገልጸው ቃል ተያይዞ የተነገረው ከቊ. 22 በኋላ ስለ ሆነ፥ የቱ ቀን? በማለት መጠየቅና በቊጥር 22 ከተነገሩት የድርጊት መግለጫ ቃላቶች ጋር አዛምዶ መተርጐም ይጠበቅብናል፡፡ በቊጥር 22 እናንተ የምታለቅሱበትና ዓለም የሚደሰትበት ወቅት አለ ይላል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዞ ማለት ከሐዘኑ በኋላ እንደ ገና የምትደሰቱበት ወቅት አለ ይላል፡፡ ቀጥሎም በቊጥር 23 “በዚያ ቀን” ሲል በቊጥር 22 ከተነገሩት ሁለት ተቃራኒ ድርጊቶች የትኛው ድርጊት የሚፈጸምበት ወቅት ነው በዚያን ቀን ተብሎ በቊጥር 23 የተነገረው? ብለን ስንጠይቅና ወደ ሰዋስዋዊው አገባብ ስንመጣ፥ “በዚያ ቀን የሚለው አጠገቡ ያለውን የደስታ ጊዜ አያመለክትም፡፡ ከትንሣኤው በኋላ ያለውን የደስታ ጊዜ ለማመላከት ቢፈልግ ኖሮ ተያይዞ የተነገረ ነውና “በዚህ ቀን” መባል ነበረበት፡፡ ይህም  ማለት እንደ ገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፡፡ በዚህ ቀን ከእኔ አንዳች አትለምኑም ወይም እኔ አብን አልለምንም ተብሎ በተናገረ ነበር፡፡

እንዲህ ስላልተባለ ግን “በዚያ ቀን” የተባለው ወቅትን የሚገልጸው ቃል የሚያመለክተው ከደስታው ቀን በፊት የነበረውን የልቅሶና የሐዘን ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለው ወቅት ነው፡፡ ሐሳቡ ሲጠቃለልም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ያልተለመነበት ጊዜ አለ ቢባል ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለው የዝምታ ወቅት ነው፡፡

የአንድን ጥቅስ ምስጢር ለመረዳት ቢያንስ 4 መንገዶችን መጠቀም ይቻላል፡፡
ሀ) ከጥቅሱ በፊትና በኋላ ካሉት ዐረፍተ ነገሮች ጋር አያይዞ በመተርጐም
ለ) በሰዋሰዋዊው አገባብ መሠረት በጥቅሱ ውስጥ ያለውን የእያንዳንዱን ቃል ሙያ በመመርመር፥
ሐ) ጥቅሱ የሚገኝበት መጽሐፍ ለተጻፈበት ዐላማ ጥቅሱን በማስገዛት፥
መ) ጥቅሱ የያዘውን ዐይነት ሐሳብ ከያዙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በማገናዘብና በማስማማት ለመረዳት መሞከር ይገባል እንጂ፥ አንድን ጥቅስ ለብቻው መዞ በማውጣት ለአንድ ዶክትሪን መሠረት ማድረግ ማለት፥ ከአንድ ጋቢ አንድ ክር በመምዘዝ ለመልበስ እንደ መሞከር ማለት ነው፤ ከብርድ አይከላከል፥ ራቊትነትንም አይሸፍን፥ ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ይህን እዚህ ላይ እናቁምና ስለ “ይህና ያ” አንድ ምሳሌ እንይ ታሪኩ ከዘፀ. 3፥2 የተወሰደ ነው፡፡

ነበልባል መጣና እንዳበል አለው የዋሁን ቊጥቋጦ፥
ይህም ሳይሸነፍ በዚያኛው ተላምጦ፥
ያኛውም ሳይጠፋ በዚህ ተሰልቅጦ፥
ተዋሕደው ኖሩ በኢተዋውጦ፡፡

በግጥሙ ውስጥ ሁለት በቅደም ተከተል የተጠሩ ስሞች አሉ፡፡ ቀድሞ የተነገረው ስም ነበልባል ሲሆን፥ በሁለተኛነት የተነገረው ስም ቊጥቋጦ ነው፡፡ “ይህና ያ” የተባሉት ቅጽሎች ከሁለተኛ ግጥሙ ቤት ጀምሮ ሁለቱን ስሞች ተክተው ገብተዋል፡፡ የሰዋስውን ሀ ሁ የቈጠረ ሰው “ይህና ያ” እንማንን እንደሚገልጹ ለማወቅ አይቸገርም፡፡ “ይህ” በአጠገቡ፥ በአቅራቢያው ያለውን ቊጥቋጦን ሲወክል ነበልባል ግን ሩቅ ቅጽል በሆነው “ያ ያኛው” ይወከላል፡፡ እንግዲህ የምልጃን ጒዳይ በአንድ ቀን ስለማንጨርሰው በሌላ ቀን ካቋረጥንበት ነጥብ በመነሣት እንቀጥላለን” አሉና የዕለቱን ውይይት ጨረሱ፡፡ አለቃ ነቅዐ ጥበብ አስጀምሮ ያስጨረሳቸውን አምላክ በማመስገን ጸሎትን ምዕራገ ጸሎት በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲያሳርጉ፤ አድማጮቻቸውንም ወደ እውነት ሁሉ ለሚመራቸው መንፈስ ቅዱስ አደራ ሰጡ፡፡

No comments:

Post a Comment