Wednesday, January 30, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ



የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበ

ካለፈው የቀጠለ

በሰሜንም በደቡብም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ነገዶች የየራሳቸውን አምልኮት ይዘው እንደ ገቡ ሁሉ እስራኤላውያንም በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሠረተውን አምልኮተ እግዚአብሔር ይዘው በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ስለ መባሉ ባለፈው ዕትም (ጮራ ቊ. 4) ላይ አስነብበናል፡፡

የአምልኮት መወራረስ የተለመደ ነውና እስራኤላውያንም በጋብቻ፥ በአሰፋፈር፥ በጉርብትና፥ በንግድ ልውውጥና በመሳሰለው አዛማጅ መንገድ ተባባሪና ተጣማሪ ለሆኗቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይሰብኩላቸው ሥርዐተ አምልኮታቸውንም ሳያስተምሯቸው እንዳልቀረ ከማሰብ የሚገታ ምክንያት አይኖርም፡፡



እንደዚህ ከሆነም ለእምነታቸውና ለሥርዐተ አምልኮታቸው መሠረት ያደረጉት የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን እንደ ነበረ ይታሰባል የሚሉ አሉ፡፡ በዚያ ጊዜ ይሠራበት በነበረው የሳባውያን ቋንቋና ፊደል የተጻፈ የብሉይ ኪዳን ሙሉ መጽሐፍም ሆነ ከፊል ጥራዝ አለመገኘቱን ለአባባላቸው እንደ ማረጋገጫ ያቀርቡታል፡፡ ወደ ሀገሬው ቋንቋ የተተረጐመ ብሉይ ኪዳን ያልተገኘው ምናልባት ትምህርተ እምነቱ በመጽሐፍ ሳይሆን በቃል ብቻ ተሰብኮ ኖሮ እንደ ሆነ ወይም እምነቱ ወደ ሀገሬው ተወላጆች ዘልቆ ባለመግባቱ ይሆናል፥ ቢባልም ትክክለኛው ገና አልታወቀም፡፡

የእስራኤል ሁሉ ተስፋ
በየትም ስፍራ የሚኖሩትን እስራኤላውያን ከአካባቢያቸው የሚለዩአቸው እነርሱን ግን አንድ ሕዝብ እንደ ሆኑ የሚያሳውቋቸው ከባህል በላይ የሆኑ ብዙ ምልክቶች ነበሯቸው፡፡ እምነታቸው በፈጠራ የመጣ ልብ ወለድ ላለመሆኑ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተጻፈው በትውፊት የተላለፈልን መጽሐፋቸው (ብሉይ ኪዳን) በታማኝ ምስክርነት ይጠራል፡፡ ስለ ፍጥረት አመጣጥና ስለ ሥርዐተ ተፈጥሮ፥ ስለ አባቶች ዘመን ታሪክ፥ ስለ ኀጢአት ወደ ዓለም መግባት፥ ስለ መዳን አስፈላጊነት የተጣራና አሻሚ ያልሆነ መግለጫ በዚሁ መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል፡፡

ስለ ገናና መንግሥታት በየተራ መነሣትና መውደቅ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ተተንብዮ የነበረው ሁሉ፥ በተነገረበት ሁኔታ መፈጸሙን ታሪክ አረጋግጧል፡፡ ስለ መሲሕ መወለድና ስለ ሐዲስ ኪዳን መተካት የተነገረው ትንቢት ታሪክ ሆኖ መነበብ ከጀመረ 2000 ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ ገናም በሚመጣው ጊዜ ሊሆን ያለውና የሚጠበቀው ማለት የዓለም የታሪክ ምዕራፍ እንዴት እንደሚደመደም በዚሁ መጽሐፍ ሰፍሯል፡፡

ብሉይ ኪዳን የእርሱ ተተኪ ሆኖ ሐዲስ ኪዳን እንደሚመጣ ቀድሞውኑ አሳውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱም ኪዳናት በመስማማትና አንደኛው ጅምሩን ለሁለተኛው በማቀበል በአንድነት የሚነድፉት፥ የሚገነቡት፥ የሚደመድሙትና ለጋራ ዐላማ ወደ አንድ ጣራና ጉልላት የሚያሳድጉት አንድ መንፈሳዊ ሕንጻ መኖሩ በጒልሕ ይታያል፡፡ ይህም በተለያየ ዘመን የኖሩት የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ጸሓፊዎች የዘመናት ዳር ድንበር ሳያግዳቸው በአንድ መንፈስ እየተመሩ እንደ ጻፏቸው አምኖ ይቀበል ዘንድ የሰውን ልብ የሚያስገድድ መስሕብ ነው፡፡

ሕዝበ እስራኤል ከነገደ ይሁዳ ከቤተ ዳዊት ከድንግል በቤተ ልሔም መሲሕ ይወለዳል የተባለውን ተስፋ በትንቢተ ነቢያት እየተቀሰቀሱ በትጋት ሲጠብቁ ኖሩ፡፡ በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት የሚመጣው መሲሕም፤
·        ለአሕዛብ ሁሉ በረከትን የሚያመጣ (ዘፍ. 22፥18፤ ገላ. 3፥16)፤
·        በዳዊት ዙፋን ተቀምጦ ዘላለማዊ መንግሥቱን የሚያቋቁምና ሥልጣኑን የሚያሰፍን ንጉሥ (2ሳሙ. 7፥12፤ 13፥16፤ ኤር. 23፥5፤ ሉቃ. 1፥32)፤
·        በመልከ ጼዴቅ ሥርዐተ ክህነት ለዘላለም የሚሾም ሊቀ ካህናት (መዝ. 110/111፥4፤ ዕብ. 7፥15-21)፤
·        በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚሆን ነቢይ (ዘዳ. 18፥18-19፤ ሐ.ሥ. 3፥22-26)፤
·        የሰውን ኀጢአት በመሸከም በሰው ፈንታ የሚቀጣና የሚሠዋ፥ ለሚታመኑበትም ሁሉ የኀጢአትን ስርየት በነጻ በመስጠት የሚያጸድቅ ነባቢ መሥዋዕት (ኢሳ. 53፥4-11፤ ዕብ. 12፥24፤ 1ጴጥ. 2፥22-24)፤
·        በመካከለኛነቱ ብሉይ ኪዳንን የሚፈጽምና ሐዲስ ኪዳንን የሚያቋቁም መሪ (ኤር. 31፥31-34፤ ዕብ. 8፥6-13፤ 9፥15) እንደሚሆን የተነገራቸው ተስፋና የተገባላቸው ቃል ኪዳን አረጋግጦላቸዋል፡፡ በትንቢት የተቀበሉት ተስፋ ሁሉ በዚሁ ይጠብቁት በነበረው መሲሕ እንደሚፈጸም አጥብቀው ሲናፍቁ ኖረው ነበር፡፡ ነገር ግን ዘመናት በዘመናት ሲተኩ የመሲሕን መንፈሳዊ ተልእኮ የሚያዩበት መንፈሳዊ ዐይን እየጠበበ ሄደና ተልእኮው ምድራዊና ሥጋዊ እንደሚሆን እየገመቱ መጡ፤ ግምታቸውም ሲውል ሲያድር እምነታቸው ሆነ፡፡

የመሲሕን ዐዋጅ ነጋሪና መንገድ ጠራጊ እንዲሆን ይላካል የተባለው ነቢይ መሲሕን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ የሥራ ድርሻ ነበረው (ኢሳ. 40፥3-5፤ ሚል. 3፥1)፡፡ ስለ ሆነም በእግዚአብሔር የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ዐዋጅ ነጋሪው ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ ተወለደና ዮሐንስ ተባለ (ሉቃ. 1፥5-25፡57-80)፡፡ በስድስተኛውም ወር ማርያም በድንግልና የፀነሰችውን ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም ስሙን “ኢየሱስ” አለችው (ሉቃ. 1፥26፤ 2፥1-4)፡፡ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የታዩት ክሥተቶች አጋጣሚዎች አልነበሩም፤ ማንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ እንዲገለጥ ከእግዚአብሔር የተሰጡ በቂ ምልክቶች ነበሩ፡፡ ጥቂቶቹን እንጥቀስ፦

1. ኢየሱስን በድንግልና የፀነሰችው ማርያም በገሊላ አውራጃ በናዝሬት ከተማ ትኖር የነበረ ቢሆንም ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በሕዝብ ቈጠራና ምዝገባ ሰበብ ዮሴፍና ማርያም ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄዱና ኢየሱስ በዚያ እንዲወለድ ሆነ (ሉቃ. 2፥4-7)፡፡
2. በቤተ ልሔም አካባቢ መንጋ በመጠበቅ ያደሩ እረኞች የኢየሱስን መወለድ ከመልአክ አንደበት ሰሙ፡፡ ሌሎች ብዙ መላእክትም የምሥራቹን ቃል በማስተጋባት ሲዘምሩ እረኞች አዩ፤ አደመጡም (ሉቃ. 2፥8-14)፡፡
3.             እረኞቹ በመልአኩ የተነገራቸውን ቃል ለማረጋገጥ ሲሉ ወደ ቤተ ልሔም ሄዱና ሕፃኑ ኢየሱስን በከብቶች ማደሪያ በግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት (ሉቃ. 2፥15-16)፡፡ ያዩትንም ሁሉ ለሌሎች ተናገሩ፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ (ሉቃ. 2፥17-18)፡፡
4.    በሌላ በኩልም ከምድረ እስራኤል በስተ ምሥራቅ የመሲሕን መወለድ ሲጠባበቁ የነበሩ ጠቢባን የጠበቁት መፈጸሙ ተገለጠላቸው፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ኮከብ እየተመሩ ጠቢባኑ ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ፡፡ ኮከቡን ተከትለው ወደ ቤተ ልሔም በቀጥታ መጓዝ ሲችሉ ከእግዚአብሔር በሆነ ዕቅድ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገቡና ለከተማው ነዋሪዎች ለንጉሡ ለሄሮድስ ለቤተ ክህነቱ ሹማምንትና ሊቃውንት ልደተ መሲሕን ሰበኩ (ማቴ. 2፥1-8)፡፡
5.    የኮከቡ ብርሃን ሕፃኑ ኢየሱስ ባለበት ቤት ላይ ሲቆም ጠቢባኑ ወደ ቤት ገብተው “ሕፃኑን” እና እናቱን አገኟቸው፡፡ ያን ጊዜ የጸጋ ስግደት የአክብሮት ስግደት የተባለችዋ ትምህርት አልተፈለሰፈችም ነበርና ስግደት የአምልኮ መግለጫ እንደ ሆነ የተረዱት ጠቢባን እናቱን ማርያምንና ዮሴፍን ከስግደትና ከአምልኮ ክበብ ውጪ አድርገው፥ ስግደትን መቀበል ለሚገባው ለሕፃኑ ለኢየሱስ ብቻ ሰገዱ፡፡ ከሀገራቸውም ሲነሡ ያዘጋጁትን እጅ መንሻ አቀረቡለት (ማቴ. 2፥9-11)፡፡
6.    ኢየሱስ ከሄሮድስ ሰይፍ ያመልጥ ዘንድ በእግዚአብሔር እንደ ታቀደው እናቱና ዮሴፍ ይዘውት ወደ ግብጽ ሸሹ፡፡ እንደ ገናም በእግዚአብሔር የታቀደው ይፈጸም ዘንድ አሳዳጁ ሲሞት ከግብጽ ተመልሰው በናዝሬት ተቀመጡ፡፡ ኢየሱስም በዚያ አደገና የናዝሬት ሰው (ናዝራዊ) ተባለ (ማቴ. 2፥13-23፤ ሉቃ. 2፥51)፡፡
7.    የኤልሳቤጥና የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ የጠበቀው መሲሕ ከእርሱ በኋላ እየመጣ መሆኑን በመስበክ መንገዱን ጠረገ (ሉቃ. 3፥3-18)፡፡
8.    ኢየሱስ እንደ ተጠመቀ ሰዎች ሲያደምጡትና ሲታዘዙት የሚገባ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ (ወልድ ዋሕድ) መሆኑን አብ መሰከረለት፤ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ በርግብ መልክ በማረፉ መሲሕነቱን (ክርስቶስነቱን) አረጋገጠ (ኢሳ. 11፥1-2፤ 42፥1-7፤ ማቴ. 3፥16-17፤ ሉቃ. 4፥16-19)፡፡
9.    በኢየሱስ ክርስቶስ ቃልና አኗኗር የተገለጸው ሁሉ ለማንነቱ ማረጋገጫ ነበር (ሉቃ. 4፥20-24፤ ዮሐ. 3፥1-2)፡፡
10.  በሌሎች ሰዎች ያልተሠሩ ልዩና ድንቅ ምልክቶችን በሰዎች ፊት ሠራ፡፡ ወደ እርሱ የመጡትን በሽተኞች ሁሉ ፈወሰ፡፡ አስታዋሽ ያልነበራቸውንም ወደ እነርሱ በመሄድ ከፈውስ ስጦታው አደላቸው (ማቴ. 14፥34-36፤ ዮሐ. 15፥22-24)፡፡

የመረጣቸውን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ከሦስት ዓመት በላይ በምድረ እስራኤልና በአካባቢው እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቈየ፡፡ የአይሁድ ቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ግን በሚያነቡት መጽሐፍ ስለ እርሱ የተነገረው ሁሉ በዐይናቸው ፊት በግልጽ እየተፈጸመ እንደ ሆነ መረዳት ባያስቸግራቸውም፥ ለሰው ሁሉ ይሞት ዘንድ የመጣበት ፈቃዳዊ ግዳጅ ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስን በመሲሕነት አልተቀበሉትም፡፡ በምቀኝነትም ተነሣሡና እንዲሞት አሳልፈው ሰጡት (ዮሐ. 11፥45-52)፡፡

በኦሪት ዘሌዋውያን 4፥13-20 የማኅበረ እስራኤልን በደል ለማስተስረይ የሚሠዋውን እንስሳ፦
·        ማኅበሩ እንዲያቀርቡት
·        የማኅበሩ አለቆች እጃቸውን እንዲጭኑበት
·        በእግዚአብሔር ፊት እንዲታረድ
·        ሊቀ ካህናቱ ደሙን እንዲረጭ
·        የማኅበሩ ኀጢአት በዚሁ እንዲሰረይ ተጽፎ ነበር፡፡
ስለዚህ ኢየሱስን አስወግደው፥ አስወግደው እያሉ ሕዝቡ ጮኹ፡፡ በቤተ ክህነቱ በኩል የሕዝብ አለቆች የነበሩ እነቀያፋ ሕዝብ ሁሉ ከሚሞት አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ቢሞት ይበጃል አሉ፡፡ የሮም መንግሥት ባለሥልጣን የነበረው ጲላጦስም ይሰቀል ዘንድ ፈረደበት፡፡ እንዲሁም ስለ ሁሉ ይሞት ዘንድ እግዚአብሔር የሁሉን ኀጢአት ጫነበት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ውሳኔ አሰጣጥ ሁሉም ተካፋዮችና ተስማሚዎች ሆኑ፡፡

ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊሞት የመጣ እንደ መሆኑ መጠን በተሰጠው የመከላከል እድል አልተጠቀመም፡፡ አጥቂዎቹን አልተቀየማቸውም፡፡ እንዲያውም ማለደላቸው፡፡ የተላለፈበትንም የሞት ፍርድ በፍጹም ፈቃደኝነት ተቀበለ፡፡ ጌታ ኢየሱስ “ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ፥ ጽብዖሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ፥ አቤቱ በእኔ ላይ ግፍ የፈጸሙትን ሰዎች ፍዳ ግፍዕ ክፈላቸው፡፡ እየተጣሉኝ ያሉትንም ተጣላቸው” ሲል ለአባቱ ክስ አቅርቦ ነበር የሚሉ የሐሰት ምስክሮች ምንም ዛሬ ቢቆሙበትም ቅንጣት ታህል እውነትነት እንደሌለበት የታወቀ ነው (ኢሳ. 53፥7-12፤ ሉቃ. 23፥34፤ 1ጴጥ. 2፥23)፡፡

የክርስትና አመሠራረትና እድገት
ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ ደጋግሞ በተናገረው መሠረት የሞት ባለሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በአርባኛው ቀን ዐረገ፡፡ በኀምሳኛውም ቀን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አፈሰሰ፡፡ ቀደም ሲል የጠራቸውንና የተከተሉትን ደቀ መዛሙርት 12 ሐዋርያትና 70 አርድእት በማለት ለይቶ ከሦስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ አሠልጥኖአቸው ስለ ነበር፥ እንደ ተስፋው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በላከላቸው ጊዜ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር  በመጐዳኘት በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተገኘውን የኀጢአት ስርየትና በትንሣኤውም የተበሠረውን ጽድቅ ሰበኩ፡፡ የአይሁድ ቤተ ክህነት ግን ትንሣኤውን ለማሰተባበል የተቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡

ትንሣኤውን አምነው በተቀበሉት አማኞች (ክርስቲያኖች) ስሙ የሚጠራው ኢየሱስ ሕያው እንደ ሆነ የሚመሰክሩ ድንቅ ሥራዎችን ሠራ፡፡ የትንሣኤውን ምስክሮች በመደብደብ፥ በማሰር፥ በማሳደድ፥ በመግደል፥ ለማጥፋት የአይሁድ ቤተ ክህነት ቢሞክርም የአማኞች ቊጥር ከቀን ወደ ቀን በብዙ እጥፍ ጨመረ፡፡ እንደ ሳውል ያሉትን እልከኛ አሳዳጆችን በጠነከረ ቅንዓትና ሥጋዊ ኀይል አስታጥቆ በቊርጠኝት ቢያሰልፍም፥ በሂደት ተሸነፈ እንጂ አላሸነፈም (ሐ.ሥ. 9፥5)፡፡

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አዳኝነትና ስለ መሲሕነቱ የተሰበከው ወንጌል ምድረ እስራኤልን አዳረሰ፡፡ ከዚያ ውጪ በብዙ ሀገሮች ተስፋፋ፡፡ የአይሁድ ቤተ ክህነትም በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ላይ ያወጀው ስደት ለወንጌል መስፋፋት ታላቅ ድርሻ ነበረው፤ ስደተኞቹ ክርስቲያኖች በየተበተኑበት ሀገር ሁሉ ዐዲስ ክርስቲያኖችን ለማፍራት አስችሎአቸው ነበርና (ሐ.ሥ. 8፥4፤ 11፥19)፡፡

ቀደም ሲልም በዓለ ኀምሳን (ጰንጠቈስጤን) ለማክበር ከብዙ ሀገሮች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበሩት አይሁድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና በተባበሪዎቻቸው ላይ በወረደበት ጊዜ፥ በጴጥሮስ ስብከት ብዙዎች አምነውና ተጠምቀው ወደ የሀገራቸው ሲመለሱ፥ የክርስትናን ችቦ በየቦታው እንዲቀጣጠል አደረጉ፡፡ የሥልጣን ማእከል በነበረችው የሮማ ከተማ እንኳ ሐዋርያ ከመድረሱ በፊት የክርስትና እምነት ቀድሞ ደርሶ ነበረ (ሮሜ 1፥7-8፤ ሐ.ሥ. 2፥10)፡፡

ከኢትዮጵያም የንግሥት ሕንደኬ ባለሟል የነበረ ሰው በ34 ዓ.ም. አካባቢ በሕገ ኦሪት የታዘዘውን ሥርዐተ አምልኮ አድርሶ ከኢየሩሳሌም ወደ ሀገሩ በመመለስ ላይ በነበረበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር መንፈስ የታዘዘው ፊልጶስ በጋዛ ምድረ በዳ ተገናኘው፡፡ ኢትዮጵያዊ ያነበበው ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ቦታ መሠቃየት እንደ ሆነ ፊልጶስ አብራራለትና ኢትዮጵያዊው አመነ፤ ተጠመቀም (ሐ.ስ. 8፥26-39)፡፡ ይህ ሰው ወደ ሀገሩ ከደረሰ በኋላ ክርስትናን ሳያስፋፋ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡ ፊልጶስ በሰማርያ ያካሂደው ከነበረው አገልግሎት በመነሣት ከኢትዮጵያዊው ጋር እንዲገናኝ በእግዚአብሔር መታዘዙን ስናነብ ምድረ እስራኤል እንኳ ገና በወንጌል ስብከት ሳትዳረስ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ መንገድ ያዘጋጀውን እግዚአብሔርን ሳናመሰግን ብናለፍ ውለታ ቢስ መሆን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግሥት የተባለችው ሕንደኬ በመርዊ ከተማ የነገሠች የኑብያ ንግሥት እንደ ነበረችና ከኑብያ ጋር በሃይማኖትም በዘርም፥ በባህልም ግንኙነት ያልነበራትና የአክሱም ንግሥት እንዳልነበረች ሳይገልጹ አያልፉም፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስትና የተስፋፋባቸው አብዛኞቹ ሀገሮች የሮም ግዛቶች ነበሩ፡፡ ሕዝቦቹም ከአያት ቅደም አያት የተረከቧቸውን አማልክት ያመልኩ ስለ ነበረ ክርስትና ከአይሁድ ሃይማኖት አንዱ አንጃ እንደ ሆነ ስለ ቈጠሩት ወደው ክርስትናን ከተቀበሉት በቀር ሌሎቹ አረማውያን ደንታም አልነበራቸው፡፡ አይሁድ በየቦታው ክርስቲያኖችን ይከሷቸው በነበረበት ጊዜም ሮማውያን ባለሥልጣኖች በጒዳዩ መግባት አልፈለጉም (ሐ.ሥ. 18፥12-17፤ 19፥35-41)፡፡

የአይሁድ ቤተ ክህነት ባለሥልጣኖችም ሆኑ ተራው ሕዝብ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ልባቸውን በማጠንከር እልከኛ አደረጉ፤ በፀረ ወንጌል  አቋማቸው ገፉበት፡፡ ለማስረጃም ሰውና እግዚአብሔር በኀጢአት ምክንያት መለያያቱን በማመልከት እንደ ምሳሌ ሆኖ እንዲያገለግል ቅድስተ ቅዱሳንን ከቅድስት ይለይ ዘንድ ተጋርዶ የነበረውን መጋረጃ እናስታውሳለን «ዘፀ. 26፥31-33)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ሰው ሁሉ ኀጢአት ራሱን ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ ያ መጋረጃ በመቀደዱ የሰውና የእግዚአብሔር ኅብረት መታደሱንና ሰማያዊ መቅደስ መከፈቱን አበሠረ፡፡ ሰውን ከእግዚአብሔር የለየው ኀጢአት ከተደመሰሰ የምሳሌው በምድር መኖር አስፈላጊ አልነበረምና (ማቴ. 27፥50-51)፡፡ መቼም የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የእኛ የሞት ዕዳ የተከፈለበትና የኀጢአት ስርየት የተገኘበት መሆኑን አምነው ለሚቀበሉ ሁሉ የዚህ ብሥራት አማናዊነት ለልባቸው በመሰከረው የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚረጋገጥ የታመነ ሆኗል፡፡  

በአይሁድ ቤተ ክህነት በኩል ግን እንዲህ አልሆነም፡፡ እግዚአብሔር ያቀደውን መጋረጃ በመደረትም ሆነ በመለወጥ መልሰው ሲጋርዱ በእግዚአብሔር ልጅ ደም ከተገኘው ስርየት ራሳቸውን አገለሉ፡፡ አማናዊው መሥዋዕት በመስቀል ላይ ከቀረበ በኋላም በምሳሌነት ይቀርብ የነበረውን የእንስሳና የእህል መሥዋዕትና ቊርባንን አናቋርጥም በማለት ከምድራዊው መቅደሳቸውና አገልግሎቱ ጋር በእልከኝነት ተቈራኝተው ቀሩ፡፡ ለንስሓ በተሰጣቸው የ37 ዓመታት የጊዜ ክልል ውስጥ በጒዳዩ ማሰብንና በንስሓ አቅጣጫን መለወጥን አልፈለጉም፡፡ የልጁን ደምና በእርሱም የተገኘውን የኀጢአት ስርየት የሚያናንቀውን ይህን የኋልዮሽ ጒዞ ሥርዐት ከሥር ከመሠረቱ ለመናድና መታሰቢያውን ለማጥፋት በእግዚአብሔር የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለሮማውያን አንገዛም በማለት ዐመፁ፡፡ በዐመፃቸው ቤተ መቅደሳቸው ተደመሰሰ፤ ከባድ የሕዝብ ዕልቂት ደረሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኢየሩሳሌም ከተማና ለነዋሪዎችዋ ያለቀሰላቸው በልባቸው እልከኝነት የሚደርስባቸው ይህ ዕልቂት አስቀድሞ ታይቶት ነበረ (ሉቃ. 19፥41-44፤ 20፥9-19)፡፡ የዚያን ዘመን ቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ክርስትናን ለምን ተቃወሙ? ክርስቲያኖችንስ ለምን አሳደዱ? ክርስትናን ባይቀበሉስ በዝምታ ለምን አያፉልትም ነበር? ጣዖታትን ከሚያመልኩ አረማውያን ጋር ተቀላቅለው በየከተማውና በየገጠሩ ተቻችለው ይኖሩ አልነበረምን? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

አንደኛ፥ በዮሐ. 11፥45-53፤ 12፥9-11 እንደ ተጻፈው ልባቸውን ወደ እውነት ያዘነበሉ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት እያመኑ ስለ ነበረ፥ የአይሁድ ቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች የሚያጅባቸው፥ አባ - አባ የሚላቸው፥ ለጦም ቆሎ፥ ለበዓልም ዶሮ የሚያመጣላቸው እንደማይኖር ስለ ተረዱ ይህ ምቀኝት፥ የጥቅምና ክብር ማጣት ጒዳይ አንገበገባቸው፡፡

ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተሉ ሰዎች ዐመፅ ቢያነሡ፥ ሮማውያን ገዥዎቻቸው መጥተው እናንተ የአመራሩን ኀላፊነት መሸከም አልቻላችሁም በማለት የሰጧቸውን የውስጥ አስተዳዳሪነት ሥልጣን ቢነጥቋቸው፥ በሕዝብ ትከሻ ላይ መቀመጣቸው ይቀርና ለፍቶ ዐዳሪ እንደሚሆኑ ታያቸው፡፡

ሦስተኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነትና በቅንዓት ቢገድሉትም እንደ ፈሩት በሦስተኛው ቀን ተነሣ፡፡ ትንሣኤውን ለማስተባበል የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው እንደ ሆነ የሚመሰክሩ ተኣምራትና መንክራት በስሙ በደቀ መዛሙቱ በኩል ተደጋግመው ታዩ፡፡ ስለ ሆነም ዝክረ ስሙን ለመደምሰስ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱ ከእልህ ወደ ባሰ እልህ አስገባቸው፡፡

አራተኛ፥ ክርስቲያኖችን ቢያሳድዱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንደሚያቀርቡ ያህል የሚቈጠርላቸው አድርገው ያምኑ ዘንድ ሰይጣን ልባቸውን አሳወረው፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ቢቆሙ ኖሮ ከእግዚአብሔር የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስንና ተከታዮቹን ለመቀበል ይፈቅዱ እንደ ነበረ እንዳያስተውሉ አደረጋቸው (ዮሐ. 8፥42-45፤ 16፥1-3፤ 2ቆሮ. 4፥3-4)፡፡

እንግዲህ በዚህ ሁሉ ምክንያት በፀረ ወንጌል አቋማቸው ጸኑ፡፡ ዛሬም የእግዚአብሔር ያልሆኑ ሰዎች በስም የእግዚአብሔር ነን እያሉ እውነተኛውን የወንጌል እምነት እንዳይቀበሉ፥ ወይም የተቀበሉትን እንዲያሳድዱ የሚገፋፋቸው ካላይ የተገለጹት ሳይጣን፥ እልህ፥ ምቀኝነትና ጥቅሜ ይቀርብኛል የሚል ሥጋት ናቸው፡፡

የክርስቲያኖች ስደት

አረማውያን ሁሉ ከአያት ቅድመ አያት በአፈ ታሪክ የወረሷቸው በወንድ፥ በሴት ስም የሚጠሯቸው የየራሳቸው አማልክት ነበሯቸው፡፡ ዛሬም ይኖሯቸው ይሆናል፡፡ ለእያንዳንዱ አስፈላጊ ጒዳይ የተለየ አምላክ ስለሚሰይሙ እያንዳንዱ ብሔር ወይም ነገድ ብዙ አማልክት እንዲኖሩት ይገደዳል፡፡ ለምሳሌ፦ የፀሓይ አምላክ፥ የዝናም አምላክ፥ የጦርነት አምላክ፥ የሰላም አምላክ፥ የፍቅር አምላክ፥ ወዘይመስሎ እያለ መሰየም ነበረበት፡፡ አማልክቱ ለየግብራቸው ጠባይ ተስማሚያቸው ይሆናል ተብሎ በተገመተ ወይም በተለምዶ በተሰጣቸው መልክና ጾታ ምስለ ጣዖት ይቀረጽላቸው ነበር፡፡

የጣዖታቱ ክብር እኩል አልነበረም፡፡ በአንደኛው የገዥ ዘመን ዋንኛውን የክብር ስፍራ ይዞ የነበረው ጣዖት በሚቀጥለው ገዥ ዘመን ዝቅ የሚልበትና ስፍራውን ለሌላ ጣዖት የሚለቅበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ ጣዖታቱ ይበልጥ እንዲከበሩ የካህናተ ጣዖት ዘዴኛነት አንዱና ዋናው ምክንያት ይሆን ነበር፡፡ ገዥው ለጦርነት በሚዘጋጅበት ጊዜ “እገሌ (የገዥውን ስም በመጥቀስ) ድልን ትሰጠው ዘንድ ይማፀንሃል” ተብሎ የገዥው ምስል ከጣዖቱ ሥር አንጋጦ ከተቀረጸ ወይም ከተሣለ፥ አጋጣሚውም ተሳክቶ በጦርነቱ ድል ከተገኘ ይህ የጦርነት አምላክ ክብር ከሌላው ጣዖት በለጠ ማለት ነው፡፡ ወይም ድርቅ ባሠጋበት ዘመን ብልጦች ካህናት የፈጣራ ታሪኮችን በመድረስ ጣዖታቸውንና ገዥዎቹን የሚያጣምር የሙገሳ ግጥምን እንዲደረድሩና እንዲቀኙ የሞያና የመኖር ዘዴ ያስገድዷቸው ነበር፡፡ ምስለ ጣዖቱ ወይም የቤተ መቅደስ መገልገያ መሣሪያ ከሰማይ የወረደ ነው ማለት የተለመደና የየዋህ አምላኪዎቻቸውን ልብ የሚያነሆልል ይሆን ነበር (ሐ. 19፥35)፡፡ ያም ሆነ ይህ በአማልክቱና እነርሱን ለማክበር በሚነገሩት የፈጠራ ታሪኮች በኩል የሚቀርበውን ክብርና አምልኮት የሚቀበለው ያው ሰይጣን ስለ ሆነ የተነገረውን ሆነ፥ እየሆነ ያለውን ተውኔት እውነት የሚያስመስልበትን ተኣምር መሰል ማሳሳቻ ይሠራ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የሮማ መንግሥት የበታች ባለሥልጣኖች ለመወደድ ሲሉ ለቄሣሮች ቤተ መቅደስ እየሠሩ ምስሉንም በውስጡ እያስቀመጡ ለአምልኮት ያቀረቡት፥ ክርስትና በሮም ግዛት እየተስፋፋ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ማንኛውም ዜጋ ወደ አቅራቢያው የቄሣር ቤተ መቅደስ በዓመት አንድ ጊዜ ሄዶ በምስሉ ፊት እንዲሰግድ፥ ቄሣር ጌታ ነው እንዲል፥ በዕጣን መሠውያውም ላይ ዕጣን በማሳረግ የዜግነት ግዴታውን እንዲፈጽም፥ ይህንኑም ለማድረጉ ማስረጃ እንዲቀበል ታወጀ፡፡ የግሪክ አማልክትን የሮማን አማልክትን፥ የሲዶናውያንን፥ የግብጻውያንን፥ የአሦራውያንን አማልክት የሚያመልኩ ቢሆኑም ቄሣርን አናመልክም በማለት አልተቃወሙም፡፡ ክብሩን፥ ስግደቱን፥ አምልኮቱን፥ ውዳሴውን፥ ዝማሬውን የሚቀበለው ያው አንዱ የእግዚአብሔር ተገዳዳሪ መንፈስ እንደ መሆኑ፥ በየነገዱ ለቆሙት የተለያዩ አማልክትም ሆነ ለቄሣሮች ቢሰግዱ፥ በኅሊናቸው የተቃውሞ ችግር አልተፈጠረም ችግሩ ለክርስቲያን ብቻ ሆነ፡፡

እውነተኛ ክርስቲያን ግን “እምቢ አሻፈረኝ፥ ጒልቤቴ የሚንበረከከው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ለእኔ ጌታዬ ኢየሱስ ብቻ ነው፥ አንደበቴም የሚያወድሰው መድኀኒቴን ነው” እንዲል የእግዚአብሔር ሕግም ፍቅሩም አስገደደው፡፡

ለዘር አማልክቶቻችን የምንሰግደው የጸጋ ስግደት ለቄሣር የምንሰግደው የአክብሮት ስግደት፥ ለእግዚአብሔር የምንሰግደው የአምልኮት ስግደት ነውና ለቄሣር ምስል እንስገድ የሚል ክርስቲያን አልነበረም፡፡ ለቄሣር ምስል ለመስገዱ ማስረጃ ማቅረብ ያልቻለውን ክርስቲያን ማንኛውም ዜጋ ንብረቱን ሊቀማው እጁን ለመንግሥት ሊያስረክብ ሥልጣን ተሰጠ፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን አረማውያን አማልክቶቻቸውን የሚያናንቁባቸውን ክርስቲያኖች አጥብቀው ይጠሏቸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይህን መሰል መንግሥታዊ ዐዋጅ ሲታከል ለበቀል ይበልጥ አመቺ ሆነላቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ይህ ነው የማይባል ሥቃይ፥ የግፍ አሟሟትና ስደት በክርስቲያን ደረሰ፡፡ በአንዳንድ የቄሣር የአገዛዝ ዘመንና በአንዳንድ ቦታ ረገብ ያለ ቢመስልም፥ የክርስቲያንን ስደት የሚያደፋፍረው ሕግ ከኔሮን ቄሣር ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ እንደ ቀጠለ ከታሪክ ይነበባል፡፡

የወንጌል ብርሃን በኢትዮጵያ

በኑብያ ኢትዮጵያ በሕንደኬ ባለሥልጣን አማካይነት ክርስትና እንደ ገባ አስታውሰን ዐልፈን ነበር፡፡ በዚህ ክፍል የነበሩት ነገሥታትና ሕዝቡ ክርስትናን ተቀብለውና ግንኙነታቸውን ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማድረግ እስከ 1100 ዓ.ም. ድረስ መቈየታቸው ይተረካል፡፡ በሳባ ኢትዮጵያ ግን ወንጌል የተሰበከው በዒዛና  የግዛት ዘመን በ330 ዓ.ም. እንደ ሆነና የወንጌሉም ብርሃን በሀገራችን እንዲቀጣጠል የተደረገው በግሪካዊው ነጋዴ ልጅ በፍሬምናጦስ እንደ ሆነ የታሪክ ጸሓፊዎች ተስማምተውበታል፡፡ ፍሬምናጦስ የወንጌልን ብርሃን በኢትዮጵያ እንዲበራና የአረማዊነት ጭለማ እንዲገፈፍ በማድረጉ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡ ከአዳም በተወረሰው ኀጢአትና በአምልኮ ባዕድ ልምምድም ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለኖረው ሕዝበ ኢትዮጵያ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በእግዚአብሔር ጸጋ የተገኘውን ዕርቅ በመስበኩ፥ “ሰላማ” የተባለው ተቀጥላ ስም ወጥቶለታል፡፡ ይህንንም በሚቀጥለው ዕትም በዝርዝር እናቀርባለን፡፡

No comments:

Post a Comment