Tuesday, January 8, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


ጭውውት
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)


ከየትና ከየት ተገናኛችሁ? እንደ ምን ሰነበታችሁ? ግቡ፥ ግቡ እንጂ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ሁላችንም ከተለያየ አቅጣጫ ስንመጣ በርቀት ብንተያይም መድረሻችን አንድ መሆኑን የተረዳነው አሁን ነው፡፡ እንደ ምን ሰነበቱ? … እግዚአብሔር ይመስገን - አለቃ ነቅዐ ጥበብና እንግዶቹ የተለዋወጡት ሰላምታ፥

የአለቃ እልፍኝ በውስጡ ዙሪያውን መደብ የተሠራለትና አጐዛና ሰሌን የተነጠፈበት ስለ ነበረ ሁሉም እንዳገባባቸው ተቀመጡ፡፡ ሥራ በሌለበት የበዓል ቀን ብዙ ሰው ወደ ቤታቸው እየመጣ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ነገረ ሃይማኖት ያልገባውን በመጠየቅ የሚያጠግብና የሚያረካ መልስ ስለሚያገኝ አለቃ ሰዎቹን ለምን መጣችሁ? አላሏቸውም፡፡



አለቃ ከልጆቻቸው ጋር ጀምረውት የነበረውን ውይይት በይደር አቋረጡና የእንግዶቹን ለማስቀደም ወሰኑ፡፡ ከእነዚሁ ሰዎች ጋር ቀደም ሲል ተጀምሮ ሳያልቅ በጊዜ ዕጥረት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የውይይት ርእስ ምን እንደ ነበረ ለማስታወስ እንደ ልማዳቸው ግንባራቸውን ቋጠር (ሽብሽብ) ፈታ አደረጉ፤ አስታወሱት፡፡

ዲያቆን ምስግና፡- እስኪ ባለፈው ጊዜ እንጃ፥ ሳምንት ሆነው እንዴ የተጀመረውን ጥያቄህን ድገመውና እንወያይበት፤ በቅድሚያ ግን አለቃ ደምፀ ቃለ አብ በመካከላችን ስላሉ ጌታ በመንፈሱ እንዲመራን ይጸልዩልን አሉ፡፡

ከጸሎት በኋላ ዲያቆን ምስግና ጥያቄውን ቀጠለ፥ አንዳንድ የክርስቲያን ክፍሎች ያማረ ሕንጻ በቤተ ክርስቲያን ስም ይሠሩና ለጸሎት ይሰበሰቡበታል፤ ይዘምሩበታል፤ አምልኮተ እግዚብሔር ይፈጽሙበታል በውስጡ ግን ታቦት ወይም ጽላት የለበትም ምክንያቱም ሲጠየቁ በአዲስ ኪዳን ታቦት ወይም ጽላት እንዲኖር አልታዘዘም ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን ታቦት የዘላለም ቃል ኪዳን ሥርዐት ሆኖ እንደ ተሰጠ በኦሪት ዘፀአት ም. 27 ተጽፎ እናነባለን፡፡ ስለዚህ ጒዳይ ነበረ ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይት አለ፡፡ አለቃ ጊዜ ሳይወስዱ፣ ማብራሪያውን መናገር ቀጠሉ፡፡

-  የዘላለም ቃል ኪዳን ሥርዐት አልከኝ? አዎን የዘላለም ሥርዐት አሉ፡፡ አለቃ ትኲረት ሊደረግበት የሚገባውን ነጥብ በመደጋገም በሰው ልብ ውስጥ ይቀርጻሉ፡፡
-  የዘላለም ቃል ኪዳን ሥርዐት አዎን የዘላለም ሥርዐት ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ምኑ ነው የዘላለም ሥርዐት? አሉና አዎን! እግዚአብሔር ከእስራኤል ዘሥጋ ጋር የተዋዋለው ኪዳን የተጻፈባቸው ሁለት ጽላት፤ ለጽላቱ ማደሪያ እንዲሆን የተዘጋጀው ታቦት፤ - ታቦቱ የሚቀመጥበት የመገናኛው ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ሦስት ክፍሎች እንዲኖሩት መደረጉ፤
-  እያንዳንዱ ክፍል በመጋረጃ መከፈሉ፤ በሦስቱም ክፍሎች ለአገልግሎት የተመደቡት ዕቃዎችና ክፍሎች ለአገልግሎት የተመደቡት ዕቃዎችና አቀማመጣቸው፤ በዚህም ውስጥ እንዲያገለግሉ የተመደቡት የአሮንና የልጆቹ ክህነት፤ የካህናቱ አለባበስ፤ ይህ ሁሉ ተዘርዝሮና ተደምሮ የዘላለም ሥርዐት እንዲሆንላቸው አዟቸዋል አሉና በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ቀጥለውም
-  ከኦሪት ዘፀአት ከም. 28፥ ቊ. 1 ጀምሮ እስከ ም. 27፥ ቍ. 21 ድረስ ያለውን እስኪ አንተነህ አንብበው አሉት፡፡
-  እርሱ ሲጨርስ ምስግና ቀጥልና ከም. 28 ቊ. 1-43 ያለውን አንብብ አሉት፡፡ እርሱም የተሰጠውን ክፍል አነበበው፡፡ ሁሉም በጥሞና ቃሉን አዳመጡ፡፡

እንግዲህ አሉ አለቃ ሁሉንም ሰማችሁት፤ አስተዋላችሁት አይደል? ስለ ታቦት ብቻ አልተነገረም፡፡ ከእርሱ ጋር በማያያዝ ታቦቱ ስለሚቀመጥበት ስፍራ ስለ ካህናቱ ማንነት ስለ አለባበሳቸውና ስለሚያገለግሉባቸው ዕቃዎች (ንዋያተ ቅድሳት) ሁሉ ከተናገረ በኋላ ማጠቃለያው “ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሁንላችሁ” የሚል ነው፡፡

-  አለቃ ማብራሪያቸውን በመቀጠል ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጠው ትእዛዝ እስራኤል ዘመንፈስን ማለት ከቤተ እስራኤልና ከቤተ አሕዛብ በወንጌል በኩል ለክርስቶስ የተለዩትን ክርስቲያኖችን ይመለከታል ለማለት ነው ጥያቄው? አሉ፡፡ አንድን ነገር ለመረዳት አንድ ጥቅስ ከመጽሐፍ መቀንጠብና ለመከራከሪያ ማዋሉ ቁም ነገር አይደለም፡፡ ሙሉውን የመጽሐፉን ሐሳብ መረዳትና እርስ በርሱ አዛምዶና አዋሕዶ መተርጐም ይበጃል ከስሕተትም ይጠብቃል፡፡ ለምሳሌ አሉና መዘርዘር ጀመሩ፡፡

አንደኛ፥ ግዝረት የተሰጠው ለእስራኤል ዘሥጋ ነው፡፡ እርሱም “የዘላለም ቃል ኪዳን ይሁንላችሁ” ተብሏል፡፡ አንብቢዋ ልዕልት ኦሪት ዘፍጥረት ም. 17 ከቊ. 1-14 አነበበችው፡፡

እዩት እንግዲህ ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ “የዘላለም ቃል ኪዳን ነው” የተባለው ግዝረት ከቤተ አሕዛብ ክርስቲያን ለሆኑት ምእመናን ይቅርና ክርስቲያን ለሆኑ እስራኤላውያንም ቢሆን በእምነት ጠቀሜታ እንደሌለው በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በግልጽ ተነግሯል፡፡ ማነህ ባለተራ እስኪ ተከፋፈሉና አንብቡ፤ ግብረ ሐዋርያት 15፥1-5፤ 28፥29፤ 1ቆሮ. 7፥18-19፤ ገላ. 5፥6፡፡

ሁለተኛ፥ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የወጡበትን የፋሲካ በዓል ለማክበር በየዓመቱ በአቢብ ወር በ14ኛው ቀን የፋሲካ ጠቦት ማረድን በዓሉንም በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ማክበርን በማግስቱ ቂጣ መብላትን፥ የዘላለም ሥርዐት አድርገው እንዲጠብቁት ታዘዋል (ኦሪት ዘፀአት 12፥17-24፤ ኦሪት ዘሌዋውያን 23፥5-8፤ ኦሪት ዘዳግም 16፥1-8 አንብብ ማነህ? ግሩም አሉ፤ አነበበ፡፡

ለእስራኤል ዘመንፈስ ግን የምሥራች ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናል! 1ቆሮ. 5፥7 ተመልከቱ፡፡ ስለዚህ በግ እየነዳን ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድ ነጻ ወጥተናል!!

ሦስተኛ፥ የእህልና የዕርድ መሥዋዕትን በቤተ መቅደስ ማቅረባቸው፤ ተረፉን የአሮን ልጆች መብላታቸው “የዘላለም ሥርዐት ይሁን” ተብሏል (ዘሌ.10፥12-15)፡፡

አራተኛ፥ በየዓመቱ በዓለ ሲዊትን በዓለ መጸለትን፥ በዓለ ስርየትን በቤተ መቅደስ ተገኝተው እንዲያከብሩ ይህም “የዘላለም ሥርዐት” እንዲሆንላቸው እስራኤል ዘሥጋ ታዘዋል፤ ኦሪት ዘሌዋውያን 23 እና ኦሪት ዘዳግም 16ን በሙሉ አንብቡ፡፡

አለቃ እንደ ገና ተመቻችተው ተቀመጡና አየር ሳቡ፡፡ ንግግራቸውን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ፡፡ አስተውሉ እስራኤል ዘሥጋ “ዘሥጋ” ነበርና የሚታይ የሚዳሰስ ምድራዊ ወይም ሥጋዊ አገልግሎት ተሰጠው፡፡

ለእስራኤል ዘመንፈስ ግን
1)     በአሮንና በልጆቹ ክህነት ፈንታ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ተተካ (ዕብ. ም. 7 በሙሉ፤ 8፥1፤ 9፥11-28)፡፡
2)    በዕርድና በእህል መሥዋዕትና ቍርባን ፈንታ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠልን (ዕብ. 8፥2-8፤ 9፥6-14)፡፡
3)   ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የምድራዊ ቤተመቅደስ አገልጋይ አይደለምና መሥዋዕትና ቍርባን የሆነውን ራሱን ያቀረበው በሰው እጅ በተሠራው የሰማያዊው መቅደስ ምሳሌ በነበረው በኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ ውስጥ አልነበረም፡፡

ተገቢው ሊቀ ካህናት እስኪመጣና በአማናዊው መሥዋዕት እግዚአብሔርንና ሰውን እስኪያስታርቅ ድረስ ለሰው ዝግ ሆኖ በቈየው በሰማያዊው መቅደስ (የእግዚአብሔር ዙፋን ባለበት) ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ ስለ ሆነም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና መሥዋዕትነት ሰማያዊ መቅደስ ተከፈተና እስራኤል ዘመንፈስ በእምነት ገቡበት (ኤፌ. 2፥14-18፤ ዕብ. 7፥19-20፤ 9፥23-28) ሃሌ ሉያ!!

እነዚህን ጥቅሶች አንብቡና መርምሩናም እውነቱን ተረዱት፡፡ ይህ ዛሬ የሚሠራው ቤት ለመሰብሰቢያ ለመጠለያ የሚያገለግል ነው (ዕብ. 10፥19-25)፡፡ ቤተ መቅደስ እኮ አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ስንል ሕንጻውን ቤቱን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን የክርስቶስ መንጋ፥ ወይም ጉባኤ ምእመናንን ነው፤ ግብረ ሐዋርያት 20፥ 17-28 አንብቡ፡፡

ቤተ ክርስቲያን የምታይ የምትሰማ የምትመክር፥ የምትገሥጽ የሕያዋን ምእመናን ጉባኤ (መንጋ) ናት እንጂ ግዑዝ ሕንጻ አይደለችም (ማቴ. 18፥17)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን ኹኔታዋን የሚያስረዱላት ብዙ ምሳሌዎች በእግዚአብሔር ቃል ተሰጥተዋታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሕንጻ፤ ወይም በቤተ መቅደስ ስትመስል ምእመናን የሕንጻው ተገጣጣሚ ድንጋዮች ሆነው መሠረቷና የማእዘኗ ራስ ጌታ ኢየሱስ ከርስቶስ ነው (1ቆሮ. 3፥11፤ ኤፌ. 2፥20-22)፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአካል ስትመሰል ምእመናን የአካሏ ብልቶች ሆነው የአካሉ ራስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ቆሮ. 12፥27-31፤ ኤፌ. 4፥11-17)፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሙሽሪት ስትመሰል ሙሽራዋ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ኤፌ. 5፥23-32)፡፡

ሐሳቡንና ጥቅሱን እያዛመዳችሁ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ጋር እያመሳከራችሁ እውነቱን ተረዱ እንጂ የሰዎችን ባህል እንደ እውነት አትቀበሉት አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ፡፡ ከዚያም ሰዎቹ የሚያቀርቡት ሌላ ወይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ቢኖር ዕድል ለመስጠት ዝም አሉ፡፡

ጠያቂው ምስግናና ሌሎቹም አድማጮች በነጥቡ ላይ እርስ በርስ ተነጋገሩበት፡፡ ለወደ ፊቱም የአለቃን ድካም ለመቀነስ ለየግላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራቸው ወሰኑ፡፡

አለቃ ደምፀ ቃለ አብም በሚከተለው ሁኔታ ውይይቱን አጠቃለሉት፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እግዚአብሔርና ሰው አልታረቁም፤ ሰማያዊ መቅደስም ለምእመናን አልተከፈተም፤ እኛም በክርስቶስ ኢየሱስ በሊቀ ካህናታችን መሪነት በእምነት ወደ ሰማያዊ መቅደስ አልገባንም፤ የሚሉ ካሉ በርግጥ እንደ እስራኤል ዘሥጋ ምድራዊ መቅደስ፤ ምድራዊ አገልግሎት፥ ሥጋዊ ክህነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ውሳኔያቸው ከጸኑ መቼም ገና ወደ አዲስ ኪዳን አልገቡምና ወደ ይሁዲነት ገብተው፥
1)     ምድራዊ መቅደስን በኢየሩሳሌም
2)    የአሮንን ክህነት፤
3)   የዕርድንና የእህል መሥዕትና ቊርባን አገልግሎትን ማቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ ያለበለዚያ አይሁዳዊነትንና ክርስትናን መደራረት ሁለቱንም አለመሆን ፤ ወይም በሁለቱም አለመገልገል ማለት ነው አሉ (ማቴ. 9፥16-7)፡፡

ዲያቆን በፈቃዱ ጥያቄ አለኝ የኔታ አለ፡፡ ፊቱን ወደ አለቃ ደምፀ አዙሮ በፈገግታና በጥቅሻ ሲፈቅዱለት፥ “እኔ ኦሪትንና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም፤ ላድሳቸው ነው እንጂ ብሎ የለም እንዴ፤ ጌታ” አለና በዐጭሩ ጠየቀ፡፡

ጥቅሱን በአግባቡ አልጠቀስከውም ዲያቆን በፈቃዱ አሉ አለቃ፡፡ እየው ልሽራቸው አልመጣሁም ልፈጽማቸው ነው እንጂ የሚል ነው ትክክለኛ ሐሳቡ፡፡ ማቴ. 5፥17-18 ላይ ይገኛል አንብበው አንተው፡፡

ታዲያ መሻርስ ምንድነው? መፈጸምስ? አሉ ጠየቁና ራሳቸው ሲመልሱ፥ መሻር ከሹመት ጊዜ ፍጻሜ በፊት በጥፋት ወይም በሌላ ምክንያት ከሥልጣን መውረድ ነው እንደ አሜሪካዊው ኒክስን፡፡

መፈጸም ማለት የሹመትን ጊዜ ፈጽሞ ከሥልጣን መገለል ማለት ነው፡፡ በዐጭር አነጋገር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግንና ነቢያትን አልሻራቸውም፤ ነገር ግን ፈጸማቸው፡፡ እንዴት እንደ ፈጸማቸው እስኪ ጠለቅ ብለን እንመልከት፡፡
1)     በክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት የኦሪት የሹመት ጊዜ ተፈጸመ፡፡ በገላ. 3፥15-29 ያለውን ልዕልት አንብቢ እንደ ገና በገላ. 4፥1-7 ያለውን ምስግና ቀጥልና አንብብ አሉ፡፡ ሁሉም አዳመጡ አለቃ ሲያብራሩ ለአብርሃም በዘርህ የምድርን አሕዛብ እባርካለሁ ሲል እግዚአብሔር ቃል ገባ፡፡ ይህ ኪዳን ከተነገረ ከ430 ዓመታት በኋላ ኦሪት ከነሥርዐቷ ለእስራኤል ሕዝብ ተሰጠች፡፡

አሕዛብ ጭምር የሚባረኩበት ዘር እንደሚመጣ ኪዳን ከተሰጠ በኋላ ኦሪት በጣልቃ ገብነት ለምን መጣች? ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ ይጠይቅና መልሱን ራሱ ይሰጣል፡፡ በረከትን የሚሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡን በሞግዚትነት እየመራች ወደ ክርስቶስ እንድታደርስ የመጣች መሆኗን ይናገርና አሕዛብን የሚባርከው የአብርሃም ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ የሞግዚትነቷ የሹመት ጊዜ ዐለቀ፤ ተፈጸመ ይለናል፡፡

ኦሪት መርታ መርታ ክርስቶስ ዘንድ ስትደርስ ትቆማለች፤ ትፈጸማለች፡፡ የኦሪት ፍጻሜውም ወይም መደምደሚያዋ ቊንጮዋ ክርስቶስ ነው፡፡ ከዚያ ማለፍ አትችልም (ሮሜ 10፥4)፡፡

2)    ከሰው ዘር ኦሪትን (ሕግን) የፈጸመ አንድም ሰው አልተገኘም፤ ወደ ፊትም አይኖርም፡፡ በሌላ አነጋገር ሰው ሁሉ ኦሪትን ሽሯታል ማለት ነው፡፡ ሮሜ 3፥9-20 አንደኛችሁ አንብቡ አሉና ተነበበ፡፡ ከድንግል በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ያለአንዳች እንከን ነቊጣው እንኳ ሳይቀር ኦሪትን በማድረግ ፈጸማት (ማቴ. 5፥18፤ 1ጴጥ. 2፥22-23)፡፡

3)   በሰው ዘር ያልተፈጸመችው ኦሪት ኀጢአተኛ የሆነውን ያልፈጸማትን የሰው ዘር ማሳጣት መክሰስና እንዲፈረድበት ማድረግ መብቷ ነው፡፡ የኀጢአተኛነታችን ቅጣት ሞት ነው (ሮሜ 6፥23)፡፡ እንግዲያውስ በኦሪት አፍራሽነታችን ሞት ያስፈረደብንን ኀጢአት እግዚአብሔር ኀጢአትን ባላደረገው ኦሪትን በማድረግ በፈጸመው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አኖረውና በኀጢአታችን ልንሞተው የሚገባንን ሞት ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተልን፡፡ ኢሳ. 53፥4-9 በጥንቃቄ አንብቡ አንዳችሁ አሉና እስኪነበብ ጸጥ አሉ፡፡

አለቃ ደምፀ ጒረሮአቸውን አጠሩና ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ አያችሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቦታችን ተተክቶ ስለ ሞተልን፥ እርሱ የተቀበለው ፍርድና የሞት ቅጣት በኛ ላይ እንደ ተፈጸመ ይቈጠራል 2ቆሮ 5፥14-15፡፡

በሰው ዘር የተሻረው ኦሪት በደለኛውን የሰው ዘር ከመክሰስና ከማስገደል በላይ ሌላ የሚፈጸምበት መንገድ የለም፡፡ የኀጢአተኛው የሰው ዘር ምትክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው የተሻረውን ኦሪትን ስለ ሰው በመሞቱ አልፈጸመውንም? እኛ በክርስቶስ ሥጋ ተገድለናልና የኦሪት ፍርድ ጸንቶአል ሮሜ 3፥21-31፤ 7፥1-4፡፡

4)   ነቢያትስ? አሉ አለቃ፡፡ ነቢያትማ ከሙሴ ጀምሮ ስለ መሲሕ ተናገሩ፡፡ ታዲያ መሲሑ ኢየሱስ በመምጣቱ ነቢያትን አልፈጸማቸውምን? ዮሐ. 1፥42-46 ፤ ሐ.ሥ. 3፥17-26፡፡

እንግዲህ እናጠቃልለው አሉ አለቃ፡፡ ኦሪትና ሥርዐቱ ሁሉ ነቢያትም በዚያ ጊዜ ወደ ፊት ሊመጣ ያለውን ለአሕዛቡ ጭምር በረከትን የሚያመጣውን የአብርሃምን ዘር ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክቱ ነበሩ፡፡
        ስለ መቅደሱ
        ስለ መሥዋዕቱ
        ስለ ክህነቱ
የተጻፈው ሁሉ ስለ ሌላ ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ነው ሉቃ. 24፥44፤ ዮሐ. 5፥39፡47፡48፡፡

ትንተናውን ከቃሉ ጋር እየተዛመደ አዳመጣችሁ፡፡ ኦሪትና ነቢያት ጸኑ? ተፈጸሙ? ወይስ ተሻሩ? ጥሩ ነው፡፡ በዚሁ ጥናታችሁን ቀጥሉ ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አጠናን አንድ አጠቃላይ ዘዴ ልንገራችሁ፡፡

አንዳንድ ሰዎች እምነታቸው ምንም የተሳሳተ ቢሆንም፥ ከማረምና ከማስተካከል ይልቅ፥ እምነታቸውን ላለመልቀቅ የሚደግፏቸውን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይፈልጋሉ፡፡ አንዲት ጥቅስ ከመጽሐፍ ሐሳብና ዐላማ ውጪ መዘውና ገንጥለው በመውሰድ ድጋፍ ሊያደርጓት ይሞክራሉ፡፡ ይህ በድቡሽት ላይ ቤት እንደ መሥራት ይቈጠራል፡፡ ይህን ዘዴ አትከተሉ፡፡

ልትከተሉት የሚገባውን የአጠናን ዘዴ ልንገራችሁ፤ በዘመኑ አነጋገር ልጠቀም፡፡ አቋም ከመውሰዳችሁ ወይም ከመያዛችሁ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግማችሁ አንብቡ፤ እርስ በርስ አመሰካክሩትና መርምሩት፤ ስትረዱ በእርሱ ላይ ተመሥረቱ፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ አሉና ጨረሱ፡፡

አለቃ ነቅዐ ጥበብም አከሉበት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያረካውን ማየ ሕይወትን የሚሰጠው ለተጠማው ነው እንጂ በሌላ መጠጥ ተሞልቶ እያገሣ ለሚቀርብ አይደለምና መሞላት ብትሹ ወደ እርሱ በባዶነት ቅረቡ፤ ያጠጣችኋል፤ ያረካችኋል ዮሐ. 7፥37-38፡፡ አሉና በጸሎት ሕዝቡን አሰናበቱ፡፡






1 comment:

  1. በጣም ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ እናመሰግናለን
    ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete