Sunday, December 9, 2012

ጋብቻ

የጋብቻ መሥዋዕትነት
በዝግጅት ክፍሉ
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

መግቢያ

ጋብቻ እግዚአብሔር በባልና በሚስት መካከል የሚገኝበት ቅንጅት ሲሆን፥ በቅንጅቱም ባልና ሚስት ፊት ለፊት ተያይተው ልባዊ መግባባት እንደሚኖራቸው በመጀመሪያው ጹሑፋችን ገልጸናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የጋብቻ ቅንጅት እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆን፥ በጋብቻ ውስጥ ያለውን አባወራነትና የሁለቱንም የተለያየ ኀላፊነት እንዴት እንደሚያብራራ ተመልክተናል፡፡ ይኸውም “የሴት ራስ ወንድ እንደ ሆነ” በእግዚአብሔር አብና በክርስቶስ መካከል ባለው አባወራነት ላይ ማለትም “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” በሚለው የተመሠረተ መሆኑን አይተናል፡፡ ይህም ለባልና ለሚስት ምን ማለት እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ገልጸናል፡፡ በመጨረሻም ጋብቻችን እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆንና በሕይወታችን እንዲገለጽ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቀናል፡፡

በዚህ በሦስተኛው ጽሑፋችን ጋብቻን በተመለከተ ስለ ሌላ መሠረታዊ ሐቅ እግዚአብሔር ወደሚያስተምረን ወደ ዔደን ገነት እንመለስ፥ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡” በጋብቻ ውስጥ የእርስ በርስ መቈራኘት መኖሩ (ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ)፤ ጥቅሱም ቊርኝቱ መሥዋዕትነትን እንደሚጠይቅ (ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል) ያስተምረናል፡፡ ሁኔታው በሴት አፈጣጠር ይታያል፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከአዳም ጐን አንድ አጥንት ወስዶ ሴቲቱን ፈጠረ፤ ሴት የተገኘችው በአዳም “መሥዋዕትነት” ነበረ፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ሙሉ ሰው ሊሆን የሚችለው ከሚስቱ ጋር አንድ ሲሆን ብቻ ነበር፡፡ አዳምም “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለቱ በጋብቻ ውስጥ ያለውን የርክክብና የመሥዋዕትነት ሁኔታ እንደ ተረዳ እናስተውላለን፡፡ የጋብቻ ቅንጅት የተቀደሰ ነውና በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ቅዱስ ግንኙነት እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳናል፡፡ ጋብቻ የትርፍ ወይም የፌዝ ነገር ሳይሆን መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ የርስ በርስ ርክክብ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡


ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ስለ ዋጃት ቤተ ክርስቲያን ራሷን ለእርሱ አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ በዚህ ዐይነት ባል እግዚአብሔር ለሰጠው ሚስት ራሱን አሳልፎ እንደሚሰጥ ሁሉ ሚስትም ለባልዋ ትታዘዛለች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው “የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች፡፡” በዚህ በዙሪያችን ካለው ከፍጥረታት ሕግ የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ ሕይወት ከሞቱ ነገሮች እንደሚነሣ ነው፡፡ ጌታችን ይህን ሲል መንፈሳዊ ሕይወትን ለማስተማር የተፈጥሮን ምሳሌ እንደ ተጠቀመ እናስታውሳለን፡፡ ምክንያቱም በምድራዊ ዓለም ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ዓለምም እውነተኛ ሕይወት ከሞት፥ እውነተኛ ትርፍም ከኪሳራ እንደሚነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፥ ለምሳሌ “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል”  የሚለውን የክርስቶስን ቃል እናገኛለን፡፡ ጌታ በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ይህን በአካሄዱ ገለጠ፡፡ ይኸውም በቊርጥ ሐሳብ ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ በሄደ ቊጥር የመስቀል ሞት በዚያ ይጠብቀው እንደ ነበር ዐወቀ፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ አስተውሎ ነበርና “ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበልና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ደቀ መዝሙርም የጌታን ፈለግ እንዲከተል ተጠርቷል፤ ክርስቶስ እንደ አስተማረ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉን ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡”

ሐዋርያው ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር መኖር” እና “ከክርስቶስ ጋር መሞት” ጐን ለጐን እንደሚሄድ ያሳያል፡፡

እንግዲህ ጋብቻ በሰዎች መካከል ከሁሉም ግንኙነት በላይ የተቀደሰ ስለ ሆነ በጋብቻም ውስጥ ሕይወት ከሞት ይነሣል ብንልም አስገራሚ አይሆንም፡፡ በጋብቻ ምክንያት ሰው ወላጆቹን ሲተው መሥዋዕትነት እንደሚጠይቀው “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል” በሚል ሐረግ ውስጥ መሠረታዊ የጋብቻን ሐቅ አይተናል፡፡ ይህም ወንዱ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ከወላጆቹ ጋር የነበረውን የቅርብ ግንኙነት ትቶ ለአንዲት ሴት ራሱን በፍጹም እምነት አስረክቦ ዐዲሱን ኑሮ ይጀምራል፡፡

አባቱ ለወደ ፊት ለእርሱ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ችግሮቹን ለማቃለል በቅርብ አይገኝም፡፡ እናቱም ለልጅዋ የተለመደውን እንክብካቤ ለማድረግ በአጠገቡ አትገኝም፡፡ አሁን ከእግዚአብሔርና ከሚስቱ ጋር ዐዲሱን ቤተ ሰብ ይመሠርታል፡፡ በመሥዋዕትነት ጐዳና ላይ የሚጓዝ ባል ብቻ አይደለም፤ ሚስትም በዚህ ጐዳና ላይ ዐብራው ለመጓዝ ፈቃደኛ ሆና ካልተዘጋጀች ጋብቻ ቅንጅታቸው አይዳብርም፡፡
እግዚአብሔር ሔዋንን ወደ አዳም ሲያመጣና በጐኑ ሲያስቀምጣት አዳም ለሚስቱ ኀላፊነት እንዳለበት ገለጠለት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርአት ይህ እውነት ሲፈጸም ይታያል፡፡ ቄሱ እግዚአብሔርን ወክሎ የሙሽራዪቱን እጅ ከአባቷ ወስዶ ከሙሽራው እጅ ጋር ያጨባብጣል፡፡ ይህም የሚያሳየው ለወደ ፊት እርሷ ከአባቷ ጥበቃና ኀላፊነት ወጥታ በባልዋ ሥር እንደምትሆን ነው፡፡ እርሷ ደግሞ አዳጋችነቱን ሳትመለከት ከባልዋ ጋር ተያይዛ በዐዲስ መንገድ በእምነት መራመድ አለባት፡፡

ብዙ ሰዎች ጋብቻቸውን ሲጀምሩ ከሚስት ቤተ ሰብ ጋር ወይም ከባል ቤተ ሰብ ጋር ዐብረው ይኖራሉ፡፡ ምናልባት የዚህ ዐይነቱ የኑሮ ምሥረታ ዘዴ የቀለለ መንገድ መስሎ ይታያቸዋል፤ ምክንያቱም ከወላጆች የመለየትን ሥቃይና ከሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ወጪም የሚያድን ይመስላቸዋልና፡፡ ዘዴው በርግጥ ከኪሣራ የሚያድን ሊመስል ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ግን ለዐዲስ ቤተ ሰብ መቋቋም በአመዛኙ ጥሩ መሠረት አይሆንም፡፡ እንዲያውም መተማመን ከመጥፋቱ የተነሣ በወላጆችና በልጆች፥ በሚስትና በባልም መካከል ለልዩ ልዩ ችግሮች መፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፥
v  እናትየዋ ልጅዋን ለመልቀቅ ችግር ይሆንባታል፡፡
v  አማትየዋ ለልጇ ሚስት የዐዲሱን ቤተ ሰብ አስተዳደር ኀላፊነት መውሰድ ያስቸግራታል፡፡
v  ዐዲሱ ባል ያለ አባቱ ፈቃድ ውሳኔ መስጠት ይፈራ ይሆናል፡፡
v  ዐዲሷ ሚስትም ምክርን ከባሏ ከመጠየቅ ይልቅ ወደ አባቷ ዘንድ መሄድ ትፈልጋለች፡፡

ስለ ሆነም ትዳር የሚመሠርቱ የኑሮ ተጓዳኞች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዕቅድ ወላጆቻቸውን ቢተዉ፥ በወላጆቻቸውና በእነርሱ መካከል ያለው ፍቅርና አክብሮት በይበልጥ ጤናማና ጽኑ ይሆናል፡፡ ይህ ቀላል መንገድ አይደለም፡፡ አብርሃምና ሣራ የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰምተው ከአገራቸው ሲወጡ ቀላል ሆኖ አላገኙትም ነበር፡፡

እግዚአብሔር ወደሚያሳያቸው አገር ለመሄድ አገራቸውን፥ ሕዝባቸውንና ቤተ ሰባቸውን ትተው እንዲወጡ ተናገራቸው፡፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለመውጣት ተነሡ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ጋር የአብርሃም አባት ታራና የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ እንደ ነበሩ እናያለን፡፡ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በፍጹም ለመከተል የቻሉት ግን መጀመሪያ ከታራ፥ በኋላም ከሎጥ ሲለዩ ነበር፡፡

እንደዚሁም የአብርሃም የልጅ ልጅ ያዕቆብ በቤተ ሰቡ፥ በተደጋጋሚም በአማቱ በላባ ጕዳይ ጣልቃ በመግባቱ ብዙ ችግር ደረሰበት፡፡ ያዕቆብ ከአማቱ ነጻ ለመሆን ኻያ ዓመታት አስፈለጉት፡፡ ይህ ሁሉ መከራ ያዕቆብ በፊት ስላደረገው ክፋትና ተንኰል የደረሰበት የእግዚአብሔር ተግሣጽ ይመስላል፡፡ ቢሆንም ጋብቻው እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ አላደገም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ያልነበረ በአሁኑ ጊዜ ግን የተጨመረ ሌላ ዐይነት “መተው” አለ፡፡ በዚያን ጊዜ እንደ ተለመደው ወንድ በሥራው አስፈላጊውን ሁሉ ለቤተ ሰቡ ያቀርብ ነበር፡፡ ሥራውም ከጋብቻ በኋላ ይቀጥል ነበር፡፡ ያገባች ሴት ግን ለቤትዋ ታታሪ ነበረች፡፡ ያላገቡ ልጃገረዶች ለጋብቻ ዝግጁዎች እንዲሆኑ ከእናቶቻቸው የቤት ሥራና ባልትና ሁሉ ይማሩ ነበር፡፡ አንዳንድ ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ሥራ እንደ ነበራቸው እናያለን፡፡ ለምሳሌ፥ ራሔል እረኛ ነበረች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያላገቡ ሴቶች ከቤተ ሰብ ሥራ ይልቅ ሌላ ሥራ ሲይዙ እናያለን፡፡ አንዳንዶቹ ጥሪት ያላቸውና በሙያው የሠለጠኑ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዕቅድ ለመመለስ፥ የሰውዮው ጥሪ ሥራውን፥ የሴትዮዋም ጥሪ ባሏን ለመከተል ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ አንዲት ሴት ስታገባ የቀደመውን ጥሪ “መተው” አለባትና የባልዋ ረዳት እንድትሆን ዐዲስ ጥሪን ትቀበላለች። ከእንግዲህ ወዲህ የመጀመሪያ ጥሪዋ ሚስት መሆንና ብዙ ጊዜ ደግሞ እናት መሆን ነው፡፡ እንግዲህ ከባልዋ ጋር ያለው ኅብረት ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲደርስ አፍላ ጒልበቷን ጊዜዋን የተፈጥሮ ስጦታዋን ችሎታዋን ሁሉ እንደ ሚስትም እንደ እናትም ሆና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስረከብ አለባት፡፡

ይህም መሥዋዕትነትን ሊጠቅ ይችላል፡፡ ብዙ ሴቶች ይህን ሊቀበሉ ፈቃደኞች አይደሉምና ሚስቲቱ ሁለት ጥሪዎች በአንድነት ለመፈጸም ስለምትሞክር በጋብቻ ውስጥ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ ሴቲቱ ሙሉ ቀን በሥራ ላይ ከዋለች በኋላ ደክማ ወደ ቤት ስትገባ ለባልዋና ለልጆችዋ የሚኖራት ጊዜና ኀይል አነስተኛ ነው፡፡ ልጆችዋም በቀን ውስጥ በአመቺ ሰዓት የሚጠበቁት በሌላ ሰው ነው፡፡ አንዳንድ ሴቶች ደመወዙ አስፈላጊ መሆኑን ስለሚገምቱ ከጋብቻ በፊት የነበራቸውን ሥራ ሳይተዉ ከባሎቻቸው ተለይተው ይኖራሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሳይከተሉ ጋብቻቸው እንደ ተፈለገው ካላደገ አስደሳች ይሆናልን? ሴትየዋ ሥራዋን በመተው “ክብርዋ” ቢቀንስ ምን ይሆናል? እግዚአብሔር የሚስትነትንና የእናትነትን ጥሪ ከፍ ከፍ ማድረጉ አይበቃትምን? ጌታዋ ክብሩን ትቶ ወደ መስቀሉ በሚወስደው መንገድ አልሄደምን? ለባልዋ ስትታዘዝ፥ በፊት እንዳየነው ጌታ ላገባች ሴት የአዳኝዋን ፈለግ እንድትከተል ልዩ ዕድልን እንደ ገና ሰጥቶአል፡፡ አንዳንዶች ገንዘብ ያስፈልገናል እያሉ ይናገራሉ፡፡ እግዚአብሔር ለልጆቹ አስፈላጊውን ሁሉ ሊያዘጋጅላቸው መንገድ የለውምን?  እውነት ነው ይህ ወደ ዝቅተኛ አኗኗር ሊያደርስ ይችላል፤ ነገር ግን የጥበቡ ቃል “የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል” የሚል ነው፡፡

አንዳንድ ሴቶች ልዩ ሙያ ከሌላቸው ሕይወታቸው እንዳልተሟላ አድርገው ይቈጥራሉ፡፡ ይህ ግን ዓለማዊ አመለካከት ነው፡፡ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በምሳሌ 31፥10-31 ከምትገኘው ከጥሩ ሚስት አርኣያ ጋር አይስማማም፡፡

በአንቀጹ ውስጥ ሚስት ሙሉ በሙሉ ለባልዋ እንደ ተሰጠችና ረዳት እንደ ሆነች እናያለን፡፡ ሚስት የፈጠራና የንግድ ችሎታዎችዋ ከቤትዋ ጋር ባለው ግንኙነት ይንጸባረቃሉ፡፡ የእርስዋ ቤት ለሌሎች በረከት ይሆንላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለሴትየዋ የሰጣትን ስጦታና ችሎታ በብዙ መንገድ ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ቀደም ሲል በተቀበለችው ሥልጠና ላይ በአሁኑ ሰዓት በጥሪዋ ውስጥ ባልታሰበ መንገድ ሊጠቀም ይችላል፡፡ ሴትየዋ ራስዋን አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ ስትሆን እግዚአብሔር ለአገልግሎት መንገዶችን ለመክፈትና አስፈላጊውን ሁሉ ለማዘጋጀት እርስዋና ባልዋ ካሰቡት በላይ ይሰጣቸዋል፡፡

ብዙ ሰዎች እንኳ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለጋብቻ ሲተዉ፥ ጋብቻቸው በሐዘን በመለያየትና አንዳንድ ጊዜ በፍቺም ቢያልቅ አያስገርምም፡፡ ሆኖም ሰው የጋብቻን ትክክለኛ ሁኔታና ዐላማ ከተረዳ ስለ ፍቺ ፈጽሞ ማሰብ አይችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የፍቺን ምክንያት ክርስቶስን ሳይጠይቁ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሎ መልስ ከሰጠ በኋላ ኢየሱስ የኦሪት ዘፍጥረትን አንቀጽ ዐትቶ፥ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየውም” ብሎ ሥልጣኑን በመጠቀም ውሳኔ ሰጠ፡፡ የጋብቻ አንድነት አንዱ ከሌላው በሞት አስኪለይ ድረስ ሲሆን በሌላ በምንም መንገድ ቢቋረጥ ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ ይበላሻል፡፡

ጥሩ ጋብቻ እንደ መልካም ተክል ነው፡፡ እንዲያድግ ትክክለኛ ክብካቤና ምቹ አካባቢ ያስፈልገዋል፡፡ አለዚያ ግን አያድግም፡፡ በሌላ አባባል የምንዘራውን እናጭዳለን፡፡ የክርስቲያን ጋብቻም በረከትና መልካም ፍሬ ከመጀመሪያ ጀምሮ በምናደርገው ጥንቃቄና መሥዋዕትነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ መጠየቅ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡

ማግባት ለሚያስቡ ሰዎች
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ላለው የርስ በርስ ርክክብ ራሳችንን አሳልፈን ለመስጠት ዝግጁዎች ነን? የፈለገውን ያህል መሥዋዕትነት ቢጠይቅ ቤተ ሰብን ልተውና በእምነት ከሚስቴ ጋር ልጣበቅ ፈቃደኛ ነኝን? ቤተ ሰቤንና ሙያዬን (ሥራዬን) ልተውና ለባለቤቴ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ረዳት ጓደኛ ልሆን ፈቃደኛ ነኝን? ጋብቻን ከሥራዬ በቀር እንደ “ትርፍ” ነገር ዐስበዋለሁ? ወይስ እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ በማይነቃነቅና በሚጸና ጋብቻ ፍሬ እንዲገኝ አስፈላጊውን መሥዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝን? ለክርስቲያኖች ፍቺ ማምለጫ መንገድ አለመሆኑን እንገነዘባለን? በእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረት ብንመራ (ብንጓዝ) አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያዘጋጅልን እናምናለን? እግዚአብሔር ለጋብቻ አስፈላጊ የሆነ ልዩ ጸጋ እንደ ሰጠን እናምናለን?

አማኝ ለሆኑ ባልና ሚስት
ጋብቻችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያድጋልን? ወይስ የዓለምን ፈቃድ ይከተላል? ጋብቻችን እንዲበለጽግና ለእግዚአብሔር ክብር ውጤታማ እንዲሆን የማያቋርጥ መሥዋዕትነት እንከፍላለን? ጋብቻችን የማይነቃነቅ ስለ ሆነ ልጆቻችን ዋስትና እንዳላቸው ይሰማቸዋልን? የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ እንሰጣቸዋለን?

ከሁለት አንዳቸው አማኝ ላልሆኑ ባልና ሚስት
ይህ ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ዘመን ብዙ ጊዜ ይፈጸም እንደ ነበርና ልዩ ልዩ ችግሮችን እንደ ፈጠረ ተረድቻለሁን? በዐዲስ ኪዳን አጽናኝ የሆነ ቃል በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፥12-16 ላይ ልብ አድርጌዋለሁን? ባሌ አማኝ ባይሆንም እንድታዘዝለት በሐዋርያው ጴጥሮስ  ትምህርት የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑንና በዚህም እግዚአብሔር ወደ እምነት ሊያደርሰው እንደሚችል አስተውላለሁን?

ለተፋቱት ዐጭር መልእክት
ይህን ጽሑፍ ከምታነቡት መካከል ጋብቻችሁ ስለ ተበላሸ ለወደ ፊት ተስፋ የለንም በማለት የምታዝኑ ትኖሩ ይሆናል፡፡ በሁኔታችሁ ወደ ጌታ ስትመለሱ የተስፋ ቃላት አሉላችሁ፡፡ አንደኛ ኀጢአትን ለሚናዘዙ ሁሉ በይቅርታ ስለሚገኘው ንጽሕና አለኝታን የሚሰጠው ቃል አለ፤ ይኸውም “በኀጢአታችን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡” ሁለተኛ አምላካችን በምሕረቱ አስደናቂ “አንበጣና ደጐብያ ኲብኲባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ” ይላል፡፡ ሦስተኛም በሕይወታችን የሚሆነውን ሁሉ ክፉና ሥቃይ ያለባቸውን እንኳ እግዚአብሔር ለዘላለም በረከታችን ያጠቃልላቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ዐላማ መንፈሳችሁም፥ ነፍሳችሁም፥ ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ፤ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ በሰፊው ስንመለከተው እግዚአብሔር አሳዛኝ በሆነው በጋብቻ ፍቺህ ለሕይወትህ በፍቅር የተሞላውን ዕቅዱን ሊፈጽምልህ ይችላል፡፡

ማጠቃለያ
በኦሪት ዘፍጥረት 2፥24 ላይ የተመሠረተውንና የጋብቻ ግንኙነት ሊፈርስ እንደማይገባ የሚገልጸውን የጌታ የኢየሱስን ትምህርት ሲሰሙ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዱ፥ “የባልና የሚስት ሥርአት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም” ብለው ተናገሩ፡፡ ኢየሱስ ግን፥ “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉም አይደለም” ብሎ መለሰላቸው፡፡ ጋብቻ በሁለት ሰዎች መካከል የተቀደሰ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ቢሆን ሳይጸልይና በጕዳዩ በጥልቀት ሳያስብበት በድንገት በሚፈጠር ስሜታዊ ውሳኔ ተገፋፍቶ ማግባት አይገባውም፡፡ ጋብቻ የእግዚአብሔር ጥሪ ከሌለበት አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ሲሆን ግን በዚህ ዓለም ከደኅንነት ቀጥሎ ከሁሉ በላይ አስገራሚና የሚያበለጽግ ስጦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ያለንን ሁሉ ማስረከብ ይገባናል፡፡ “እያንዳንዱ ለሌላው፤ ሁለቱም ለእግዚአብሔር” የሚለው ሐረግ እግዚአብሔር እውነተኛ ዐላማ ላለው ከፍተኛ ጒዳይ እንደ ጠራን ሊያሳስበን ይችላል፡፡

ከላይ ለቀረበው ትምህርት ጥቅሶች
ዘፍ. 2፥21-23፤24፤ 11፥31-32፤ 12፥1፤ 13፥8፤9፤ 14-18፤ 29፥9፤ 31፥38-42፤55
ምሳ. 15፥17፤ ኢዮ. 2፥25
ማቴ. 2፥13፤ 19-23፤ 19፥3-6፤ 10፤11
ሉቃ. 2፥4-7፤ 9፥23፥24፥ 24፥26፤
ዮሐ. 12፥24፤ ሮሜ 8፥28 ኤፌ. 5፥32
1ተሰ. 5፥23-24 2ጢሞ. 2፥11 1ዮሐ. 1፥9፡፡

1 comment:

  1. በጣም ጥሩ ትምህርት ነው። "የሺህ ጋብቻ"ን በሚመለከት ይህን ጽሑፍ አግኝቼ ላክሁላችሁ። በርቱ።http://www.ethiopianchurch.org/editorial2/147-%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B5-%E1%8C%8B%E1%89%A5%E1%89%BB-%E1%8B%88%E1%8B%AD%E1%88%B5-%E1%8C%85%E1%88%9D%E1%88%8B-%E1%8C%8B%E1%89%A5%E1%89%BB.html

    ReplyDelete