Wednesday, December 26, 2012

ክርስትና በኢትዮጵያ

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 (ካለፈው የቀጠለ)

አምልኮት በኢትዮጵያ

ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን አምልኮት በተመሳሳይ ጊዜ በሌላው የዓለም ክፍል ከነበረበት የአምልኮት ታሪክ መሠረታዊ ልዩነት የለውም፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም በሌላው የዓለም ክፍል እንደ ነበረው ሁሉ ዐይነቱ ብዙ ቢሆንም አያስደንቅም፡፡ የአምልኮቱ ዐይነት መብዛትና መለያየት ከነገዶቹ ዝርያ ጐሣዎች መብዛት፥ ከገቡበትም አቅጣጫና ጊዜ መለያየት የተነሣ ነው ቢባል ለእውነት የቀረበ ይሆናል፡፡

በቤት እንስሳት፥ በአራዊት፥ በአዕዋፍ፥ በኰረብታ፥ በሐይቅ በወራጅ ውሃ፥ በሚሳቡ ፍጥረታት (የእባብ ዐይነቶች)፥ በዛፎች፥ በድንጋዮች… የማምለክ ልምድ የነገደ ካም ዝርያዎች ትውፊት ነበር ይባላል፡፡ የነገደ ካም ዝርያዎች በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያዩዋቸውን፥ ለኑሮአቸው ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸውንና እንደ ብርቅ ድንቅም የቈጠሯቸውን፥ ማለት ወይ በጠቃሚነታቸው፥ ወይ በእንቅስቃሴአቸው፥ ወይ በአቋማቸው ወዘተ. ስሜታቸውን የማረኳቸውን ተንቀሳቃሽና ኢተንቀሳቃሽ ፍጥረታትን ያመልኩ ነበረ የሚለውን ትረካ ከተቀበልን፥ በዚያን ጊዜ ሐሳባቸው ገና በአካባቢያቸው ውሱንና ትኲረታቸውም ካፍንጫቸው ሥር ብዙ ያልራቀ እንደ ነበረ የግምት ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡


በዚሁ ትይዩ፥ የፀሓይ፥ የጨረቃ፥ ከዋክብት… አምልኮት ከነገደ ሴም ዝርያዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሳባውያን ትውፊት (ውርስ) ነበረ የሚል ትረካ ይቀርባል፡፡ ይህም ዐይነት አምልኮት በደቡብ ዐረቢያ ከተገኘው የአምልኮት ቅርስ ጋር ስለሚመሳሰል ሳባውያን እንደ ፊደላቸው ሁሉ ሥርዐተ አምልኮአቸውን ይዘው ገብተው ነበር ቢባል ያስኬዳል፡፡

ይህንም አባባል በእውነትነቱ ለተቀበሉ ተራኪዎች በቀዳሚነት ወደ ኢትዮጵያ የገቡና ሀገሪቱን ኩሽ ወይም ኢትዮጵያ ያሰኙ እነዚያው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሰፈሩ የነገደ ካም ዝርያዎች ነበሩ የሚለውን እምነታቸውን ያጐለብትላቸዋል፡፡ እንዲህ ከሆነም ሳባውያን ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት ጊዜ የሰው ልጆች ከከበቧቸው ፍጥረታት ላይ ዐይንና ልባቸውን በማንሣት፥ ራቅና ከፍ ብለው ማሰብ፥ ማየት፥ መመራመር የጀመሩበትና በሥልጣኔ ጥቂት የእድገት እመርታ ያሳዩበት የዘመን አካባቢ እንደ ሆነ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ አባባሉ ሲጠቃለልም የሰው ሥልጣኔ ገና በአካባቢ የነበሩትን ፍጥረታትን በማድነቅ የተወሰነ በነበረበት ጊዜ የነገደ ካም ዝርያዎች የአካባቢ ፍጥረታትን የማምለክ ልምድ ይዘው በመጀመሪያ ሲገቡ፥ ሳባውያን ግን ሰው ከማጐንበስ ቀና ብሎ ጠፈርን ከማየትና ከማድነቅ፥ ከመመራመርም በመነሣት የጠፈር አካላትን ማምለክ ሲጀምር ይህን ዐይነቱን ሥልጣኔና አምልኮ ይዘው ዘግይተው የገቡ ናቸው ማለት ነው፡፡

አምልኮተ እግዚአብሔር
ከነገደ ሴም ዝርያዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሳባውያን ብቻ አልነበሩም፤ እስራኤላውያንም ከሰሜን አስከ መኻል ኢትዮጵያ ገብተው ሰፍረዋል ተብሎ የሚተረከው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በብሉይ ኪዳን ትምህርት መሠረት የአምልኮተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ መገኘት ይህንኑ ስለሚጠቁም ነው፡፡ የአምልኮተ እግዚአብሔር ዘርፍና የእስራኤላዊነት መታወቂያ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ከነገደ እስራኤል ውጪ ርቀው ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህልም የሃይማኖትም ዘርፎች ሆነው አሁን ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፥
v ግዝረት (ዘፀ. 12፥48)
v የሚበሉና የማይበሉ እንስሳትን መለየት (ዘሌ. 11 እና ዘዳ. 14)
v ቀዳሚትን እንደ ሰንበት ማክበር (ዘፀ. 12)
v ለአራስ ሴቶች የመንጻት ወራትን መወሰን (ዘሌ. 12) የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከጥፋት ውሃ በኋላ በየአቅጣጫው ተበታትነው መስፈርንና ኑሮን በግልና በማኅበር መምራት የጀመሩት የኖኅ ተወላጆች ዓመታት ዐልፈው ዓመታት ሲተኩ እግዚአብሔርን ከማምለክ እየራቁ ሄዱ፡፡ የኖኅ ዐሥረኛ ትውልድ የነበረው አብራም ግን ከከለዳውያን አገር ከዑር ከተማ በእግዚአብሔር እንደ ተጠራና የዝርያ አማልክቱን በመተው ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ ጀመረ መጽሐፍ ቅዱስ ይተርክልናል (ዘፍ. 12፥1-9፤ ኢያ. 24፥2-3)፡፡

የአብርሃም ልጅ ይሥሐቅና የይሥሐቅ ልጅ ያዕቆብ እንደ አብርሃም እግዚአብሔርን ማምለክ ቀጠሉ (ዘፍ. 35፥2-4)፡፡

አብርሃም ከዑር ሲጠራ መኖሪያ እንድትሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጠችው፥ ዛሬ መካከለኛው ምሥራቅ እያልን በምንጠራው ክልል ውስጥ ከካም ልጆች የአንደኛው የከነዓን ተወላጆች የሰፈሩባት አገር ነበረች (ዘፍ. 10፥6፤ 15-20 1ዜና. 1፥8-16)፡፡

በከነዓን አገር ተከታትሎ ከደረሰው የድርቅና የረኃብ መቅሠፍት ለመሸሽ ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ተሰደዱ፡፡ ከዚያ ቀደም ሲል ተሽጦ የነበረና በይለፍ ይለፍ ለግብጽ ንጉሥ ያደረው የንጉሡ ባለሟልና የመንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን እስከ መሆን የደረሰው ዮሴፍ አባቱንና ወንድሞቹን ከነቤተሰባቸው አስተናገዳቸው፤ ማረፊያ የሚሆናቸውንም ለምና ሰፊ መሬት አስመራቸው (ዘፍ. 46፥29-34፤ 47፥1-6)፡፡

ዓመታት በዓመታት እየተተኩ ሲሄዱ የእስራኤል ልጆች በግብጻውያን ተጠሉ፤ ጭቆናም ደረሰባቸው፤ የባርነት ቀንበርም ተጫነባቸው፡፡ ስለ ወደቀባቸው የግፍና የባርነት ቀንበር ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ እግዚአብሔርም በሙሴ በኩል ረድኤቱን ላከላቸውና ከግብጽ አወጣቸው፡፡ የእስራኤል ልጆችም ከ40 ዓመት የበረሓ ጒዞ ከኋላ ለአብርሃም ተሰጥታ ወደ ነበረችው ምድረ ከነን ተመልሰው ገቡ፡፡

በአርባ ዓመት የምድረ በዳ ጒዞአቸው እስራኤላውያን ስለ አምልኮተ እግዚብሔር ሰፊና ጠለቅ ያለ ትምህርት ተሰጣቸው፤ ሕጎች ወጡላቸው፤  ደንቦች ተደነቡላቸው፡፡ ከዚያ ጊዜ በፊት ግን አብርሃምም፥ ይሥሐቅም፥ ያዕቆብም በመጽሐፍ የተዉላቸው ትምህርትና ሕግ አልነበረም፡፡ ይሥሐቅና ያዕቆብ ከአብርሃም በቃል የተላለፈላቸውን መመሪያና ከእግዚአብሔር ይሰጣቸው የነበረውን ወቅታዊ ራእይ በመከተል ያመልኩ ነበር፡፡

ሙሴ ከእግዚአብሔር የተነገረውን ሁሉ እየጻፈ ለወገኖቹ አስተማረ፡፡ ሙሴ ከፍጥረት አጀማመር አንሥቶ እርሱ እስከ ተጠራበት ጊዜ ድረስ ያለውን አያይዞ በመጻፍ የተሟላ የሃይማኖት መጽሐፍን በክፍል በክፍሉ አከታትሎ ጽፎአል፤ ኦሪት ዘፍጥረት፥ ኦሪት ዘፀአት፣ ኦሪት ዘሌዋውያን፣ ኦሪት ዘኊልቊ፥ ኦሪት ዘዳግም በማለት፡፡

በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት፥ ሥርዐት ባለው ሁኔታ አምልኮተ እግዚአብሔር የተሰበከበት ብቸኛ ሃይማኖት ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጽሐፍ ተጽፎ የተገኘው ይኸው የእስራኤል ልጆች እምነት ነው፡፡ ሥርዐተ አምልኮው በእስራኤል ልጆች እንዴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ እንደ ወረደ የሚገልጹ የታሪክና የመዝሙራት መጻሕፍት በተከታታይ ትውልዶች ታክለውበት በእስራኤል ልጆችና በጎረ ቤት አገሮች ላይ ስለሚደርሰው የወደ ፊት ሁኔታና ስለ መሲሕ መወለድም ስለ ዓለም ፍጻሜም ትንቢቶች ተጨምረውበት አሁን በእጃችን የሚገኘውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን አስገኝተዋል፡፡

እንግዲህ ይህን ዐይነቱን ሃይማኖት የያዙ የነገደ እስራኤል ዝርያዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ሲረጋገጥ፥ መቼና እንዴት እንደ ገቡ በማስረጃ የተደገፈ ታሪክን ማቅረብ አልተቻለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ሊሆን ከሚችል ግምት በመነሣት ነገደ እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ሊዘልቁና ሊሰፍሩ የቻሉት በሚከተሉት ሁኔታዎችና ጊዜያት እንደ ሆነ ይገልጻሉ፡፡
1.   ዐሥሩን ነገደ እስራኤል ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት በአሦር መንግሥት ሲደመሰስና ሀገሩ ሲወረር (ከክርስቶስ ልደት በፊት በ722/721) ከጦርነቱና በኋላም ከአገዛዙ ጫና ለመሸሽ ወደ ሌላው የዓለም ክፍል ሲበተኑ በኢትዮጵያ ገብተው ይሆናል፡፡
2.  የይሁዳ መንግሥት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነዖር ሲደመሰስ (587/586 ከክ.ል.በ.) ሕዝቡ እየሸሹ ወደ የሀገሩ ሲበታተኑ ወደ ኢትዮጵያም ሳይገቡ አልቀሩም፡፡ የኢትዮጵያ ስም በዚያ ስፍራ በግልጽ ባይጠቀስም፥ የዚያን ጊዜው ጦርነት በባቢሎናውያን ድል አድርጊነት ካበቃ በኋላ ለባቢሎናውያን አንገዛም ያለ ቡድን ኤርምያስንና ባሮክን ይዞ ወደ ግብጽ እንደ ሸሸ ተረጋግጧል (ኤር. 43፥1-7)፡፡
ምናልባትም ናቡከደነፆር በማከታተል ወደ ግብጽ በዘመተ ጊዜ ወደ ግብጽ ሸሽቶ ከነበረው ቡድን መካከል ጥቂቱ ሽሽቱን ወደ ደቡብ በመቀጠል እስከ ኢትዮጵያ የመድረስና በተራ. ቊ. 1 ከተገለጸው ቡድን ጋር የመቀላቀል እድል አጋጥሞት ይሆናል፡፡
3.  በዘመነ ቄሳር አስባሳያኖስ ሮማዊው ጄኔራል ጥጦስ አይሁድ ያነሣሡትን የአንገዛም ባይ ጦርነት ለመደምሰስ ወደ ምድረ እስራኤል በዘመተበት ጊዜ (ከ67-70 ዓ.ም) ወደየሀገሩ መሸሻቸው ይታወቃል፡፡ ወደ ኢትዮጵያም የገቡና ቀደም ሲል በሀገሪቱ ውስጥ ከሰፈሩ ወገኖቻቸው ጋር የተደባለቁ ኖረው ይሆናል፡፡

ለነገደ እስራኤል እነዚህ ዋና ዋናዎቹ የፍልሰታቸው ምክንያቶችና ጊዜዎች ይሁኑ እንጂ በፊትም ሆነ በኋላ በልዩ ልዩ ምክንያት የገቡና በኢትዮጵያ ውስጥ በነዋሪነት የሰፈሩ አይታጡም ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

እንግዲህ ይህን በመሳሰለ ብዙ መንገድ ነገደ እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ በአክሱም፥ በሽሬ፥ በላስታ፥ በሰሜን በጭልጋ፥ በቋራ ... በመስፈር ኖሩ፡፡ ስለ ሆነም እነዚህ ነገደ እስራኤል ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በብሉይ ኪዳን ላይ በተመሠረተ አምልኮተ እግዚአብሔር ጸንተው ከቈዩ በኋላ ክርስትና በኢትዮጵያ በተሰበከበት ጊዜና በኋላ ከመካከላቸው ክርስትናን የተቀበሉ እንደ ነበሩ ይተረካል፡፡ ስለ ሆነም እንደ ግዝረት ያሉትን የእስራኤላዊነት መታወቂያዎቻቸውን ባለመተው ከክርስትና እምነት ጋር ይዘው ኖሩ፡፡ እንዲያውም ከራሳቸው ነገድ ውጪ ከአረማውያን መካከል ክርስቲያን ለሆኑት ምእመናን የራሳቸውን ባህል በማውረሳቸው አይሁድ ባልሆኑትም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የእስራኤላዊነት መታወቂያ ምልክቶቹ ሊታዩ ችለዋል፡፡

ሌላ ዓይነት ትረካ
በ13ኛው ምእት ዓመት መደቡ በላስታ የነበረውን የዛጔን መንግሥት ለማስገልበጥ የመዘዙትን ሐረገ ትውልድ ተንተርሶ የሚጻፈው ትውፊታዊ ታሪክ ከላይ የተገለጸውን እንዳልነበረ ያደርገዋል፡፡ የነገደ እስራኤል በኢትዮጵያ መገኘትንም በሌላ በተቀባባ መልክ ያቀርበዋል፡፡
1.     ከነገደ ዛጔ የመንግሥትን ሥልጣን እንዲረከብ የታጨውን ይኩኖ አምላክን በነገደ ዛጔ ሥልጣነ መንግሥትን ከተነጠቀው ከአክሱማዊ ድልነአድ፤ ድልነአድን ከእብነ መለክ (ቀዳማዊ ምኒልክ) እብነ መለክን ከንጉሠ እስራኤል ሰሎሞን ጋር በማያያዝ ዘር ተቈጠረ፡፡
2.    ሰሎሞንን የጐበኘችው ንግሥተ ሳባ ከሰሎሞን አርግዛ ተመለሰችና ቀዳማዊ ምኒልክን (እብነ መለክን) ወለደች፤ ቀዳማዊ ምኒልክም 20 ዓመት ሲሞላው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደና አባቱን ተዋወቀ፤ በዚያም ለ3 ዓመት ሥርዐተ መንግሥትንና ሥርዐተ አምልኮትን ተማረ፡፡ ወደ ሀገሩ ሊመለስ ሲዘጋጅም ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ፥ ሌሎች ካህናትና ሌዋውያን፤ ከየነገዱም የጐሣ አለቆች ዐብረት እንዲሄዱ ከአባቱ ተሰጡት፡፡ በተለይ አዛርያስ ከካህናቱ ጋር ባደረገው መመሳጠር ሊሆን ይችላል፡፡ የቃል ኪዳኑን ታቦት ሰርቆ እንደ መጣና ሕገ ኦሪትን ኢትዮጵያ እንደ ተቀበለች ይተርካሉ፡፡
3.    በትውፊታዊ የታሪክ ድርሳናቱ የቀዳማዊ ምኒልክ ዘር እስከ አብርሃ ወአጽብሐ (ዒዛናና ሳይዘናስ) ድረስ፤ የአዛርያስም ዘር እስከ እንበረም ድረስ (ሊቀ ካህናት ነበረ የተባለ) ወደ ታች ይቈጠራል፡፡ በዚሁ ዘመን ላይ ንጉሡና ቤተ ሰቡ ሊቀ ካህናቱ እንበረምና ሌሎች ካህናትና ሕዝብ በአቡነ ሰላማ ስብከት ክርስቲያን እንደ ሆኑ ከተተረከ በኋላ ሥልጣነ መንግሥት ለይኩኖ አምላክ መሰጠቱን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በላይ የተገለጸውን የነጋሢነት ዘር አወራረድ መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ በቀዳማዊ ምኒልክ የጀመረው ሰሎሞናዊ ሥልጣነ መንግሥት እስከ ድልነአድ እንደ ቀጠለ፤ በነገደ ዛጔ ጣልቃ ገብነት ቢቋረጥም በይኩኖ አምላክ እንደ ገና ተያይዞና ተቀጥሎ እስከ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ እንደ ደረሰ ባለታሪኮች ያትታሉ፡፡

እንግዲህ ታሪኩ በዐጭሩ እንዲህ ሲሆን በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ግን ከክርስትና በፊት በኢትዮጵያ በሕገ ኦሪት የተመራ አምልኮተ እግዚአብሔር ነበር ስለሚባለው ታሪክ መጠነኛ ግንዛቤ ለማግኘት ነው፡፡

አባባሉ እውነት ይሆን?
ከዚህ የታሪክ አቀራረብ መንፈሳዊውን ይዘት ብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛን ብንመዝነው ውጤቱ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

1)     ሰሎሞን በነገሠ በ4ኛ ዓመት ከሁለት ወር ቤተ መቅደስ ለመሥራት መሠረት አኖረ (1ነገ. 6፥11 2ዜና. 3፥1-2)፡፡ ይህን መነሻ አድርገን ብንይዝ 4 ዓመት ከ2 ወር፡፡
2)    የቤተ መቅደሱ ሥራ ሰሎሞን በነገሠ በ11 ዓመት ከ8 ወር ተጠናቀቀ (1ነገ. 6፥36-37) ሥራው የወሰደው ጊዜ  7 ዓመት ከ6 ወር፡፡
3)   ከዚያ በኋላ ሰሎሞን የራሱን ቤተ መንግሥት አሳነጸና በነገሠ በ20 ዓመት አጠናቀቀ (1ነገ. 9፥10፤ 2ዜና. 8፥1-2) ሥራው የወሰደው ጊዜ 13 ዓመት፡፡
4)   ሰሎሞን ከዚህ በማከታተል ለሀገርና ለመንግሥት የሚጠቅሙ ሥራዎች አሠርቷል (2ዜና. 8፥1-18፤ 1ነገ. 9፥10-28) ሆኖም ሥራዎቹ በምን ያህል ጊዜ እንደ ተጠናቀቁ አልታወቀም፡፡
5)   የሳባ ንግሥት ወደ ሰሎሞን የሄደችው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር፡፡ የቤተ መቅደሱን ሥራና የአገልግሎቱን ሥርዐት አድንቃለች፡፡ የቤተ መንግሥቱን የውስጥና የውጭ ድርጅት ጐበኝታለች (1ነገ. 10፥1-13፤ 2ዜና. 9፥1-12)፡፡

ንግሥቷ ኢየሩሳሌምንና አካባቢውን ከተሞችንና ድርጅቶችን በመጐብኘት ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፈች አይታወቅም፡፡

ኢየሩሳሌም በገባችበት ዕለት እንደ ፀነሰች እንኳ ቢታሰብና የእብነ መለክ መወለጃ ጊዜ ቢደመር 9 ወር፥

6)   እብነ መለክ (ቀዳማዊ ምኒልክ) በ20 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ ከ3 ዓመት በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሰ ስለሚባል 23 ዓመት ድምር 48 ዓመት ከ5 ወር ይሆናል፡፡

የሰሎሞን የግዛት ዘመን ግን 40 ዓመት ብቻ ነበር (1ነገ. 11፥41-43፤ 2ዜና. 9፥30-31)፡፡

እብነ መለክ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ ከአባቱ ጋር ተዋወቀ በተባለበት ጊዜ ሰሎሞን ከሞተ 5 ዓመታት አልፈው ነበር፡፡ መንግሥቱም ከሁለት ከተከፈለ በኋላ የይሁዳ መንግሥት በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም እየተመራ ነበር፡፡ ስለ ሆነም እብነ መለክ ከሰሎሞን ጋር ተዋወቀ፡፡ 3 ዓመት ሥርዐተ መንግሥትና ሥርዐተ አምልኮ አስጠናው፡፡ የቃል ኪዳኑን ታቦት ሰጠው፤ ወይም አሰረቀው የተባለበት ጊዜ አለመገጣጠም ታሪኩን ከጊዜ በኋላ በፈጠራ የተዘጋጀ ድርሰት ያስመስለዋል፡፡

ስለ ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ
በመመሳጠርና በውስጠ አዋቂነት ታቦቱን ይዞ መጣ የተባለው ሊቀ ካህናት አዛርያስ በዚያው በኢየሩሳሌም ቤተ ክህነት ትውልዱ ሲቈጠር ይገኛል እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኢትዮጵያ ስለመፍለሱ አልተነገረም፡፡ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ያገለግል የነበረው አዛርያስ በዚያው በኢየሩሳሌም ትውልዱን አስከፍልሰተ ባቢሎን አስቈጥሯል (1ዜና. 6፥10-15)፡፡ የአይሁድ ምርኮኞች ከባቢሎን በተመለሱ ጊዜም ከካህናት በኩል ዋና ሆኖ የተመለሰው ዕዝራ የዚሁ የአዛርያስ ተወላጅ ነበር (ዕዝ. 7፥1-10)፡፡

ታቦት ምንድር ነው?
እግዚአብሔር በላዩ ሆኖ ለሕዝቡ መመሪያ የሚሰጥበት ክዳን ያለውና ለጽላት መኖሪያ የሚያገለግል ትልቅ ሳጥን ነው (ዘፀ. 25፥16-22)፡፡

በታቦቱ ውስጥ የሚቀመጡት ዐሥሩ የሕግ አንቀጾች የተጻፈባቸው ሁለት ጽላት ነበሩ (ዘፀ. 34፥28፤ ዘዳ. 5፥5-22፤ 10፥1-5፤ 2ዜና. 5፥10)፡፡

ሕዝበ እስራኤል በጽላቱ ላይ የተጻፈውን ቃል ቢጠብቁ ከእግዚአብሔር የሚሰጣቸውን በረከት ባይጠብቁ ግን የሚወርድባቸውን መቅሠፍት ስለ ያዙ አንዳንድ ጊዜ የምስክር ሌላ ጊዜም የቃል ኪዳን ጽላት (የውል ሰነድ) ይባሉ ነበር (ዘፀ. 31፥18፤ ዘዳ. 4፥13)፡፡

በስርቆሽም ይሁን በስጦታ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢትዮጵያ መጣ ሲባል፥ ጽላቱን የያዘው ታቦት እንደ ሆነ፥ ወይም ጽላቱ ብቻ እንደ ሆነ በትውፊታዊ ታሪኮቹ ተገልጾ አያውቅም፡፡

ቃል ኪዳኑ ለማን ነው? (ውለታው ከማን ጋር ነው?)
እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን በቃልም በጽላትም በመጻፍ የተዋዋለውና የተካየደው (ቃል ኪዳን የገባው) ከእስራኤል ልጆች ጋር ነበር (ዘፀ. 4፥6-8፤ 34፥27-28፤ ዘሌ. 25፥55፤ 26፥1-46፤ ዘዳ.5፥1-3፤ 6፥6-11፤ ዘፀ. 24፥4-8)፡፡

በእግዚአብሔር አምላክና የተለዩ፥ ሕዝቤ ባላቸው በእስራኤል መካከል ለተደረገው ቃል ኪዳን ምስክር የሆነው የኪዳኑ ታቦት (የውል ሰነድ) በሌላ ሕዝብ ቢሰረቅ ምን ይጠቅማል? በሌብነት ያስጠይቃል፤ ያልሰረቁ ሰዎችንም ስም ማጥፋት ወንጀል ነው በሰነዱም ላይ በነበረው ቃል ኪዳን ከእስራኤል ነገድ ውጪ የሆኑት አይሸፈኑበትም፤ አይጠቀሙበትም (መዝ.147፥8-9) በኢትዮጵያውን የሚገኝ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያውን እስራኤሎች ንብረት ሊሆን በተገባው ነበር፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ምን ይላል?
ታቦት ለእስራኤል ልጆች ለአምልኮአቸውና ለቤተ መንግሥታቸው ትርፍና ዝርዝር ጒዳይ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን የያዘ (የውል ሰነድ) ስለ ሆነና የሁሉ ነገራቸው ማእከል (እንብርት) ስለ ነበረ፥ ለይኩኖ አምላክ ሥልጣነ መንግሥት ማስጨበጫ እንዲሆን የተጻፈው የታሪክ ድርሰት እንደሚገልጸው እግዚአብሔር ከወሰነው ስፍራ ተሰርቆ ቢሆን ኖሮ በፍልስጥኤማውያን ላይ የደረሰው የመቅሠፍት ዐይነት በሰራቂዎቹ ላይ በወረደ ነበር (1ሳሙ. 4፥10 እንደገናም ምዕ. 5፥ እና 6 ያንብቡ)፡፡

ለእግዚአብሔርና ለእስራኤል ልጆች የቃል ኪዳን ታቦት ማደሪያ የሚሆን መቅደስ እንዲሠራበት በእግዚአብሔር የተመረጠው ቦታ ኢየሩሳሌም ስለ ነበረ ከዚያ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ቢደረግ ቅሥፈትን ባስከተለ ነበር (ዘዳ. 14፥22-25፤ 26፥1-2፤ 1ነገ. 8፥15-21፤ 2ዜና. 3፥1፤ 1ዜና. 21፥18-30፤ 22፥1-2)፡፡

በድፍረትም ሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ታቦቱ ከኢየሩሳሌም እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ ኖሮ ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ በተሰጠው ነበር፡፡

እስኪ እንመልከት ከሴሎ ወደ አቤንኤዜር ከዚያም ወደ አዛጦን ጌት፥ አስቀሎና ሲወሰድ፥ እንደ ገናም ለእስራኤል ልጆች ተመልሶ ወደ ቤት ሳሚስ፤ ከዚያም አሚናዳብ ቤት ሲቀመጥ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ይተርካል (1ሳሙ. 4፥3 እስከ ም. 7፥2 ቀጥሎም ከአሚናዳብ ቤት ወደ ወደ አቢዳራ ቤት ሲዛወር፥ ከዚያም ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ጸዮን አምባ ሲመጣ ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል (1ሳሙ. 6፥1-17)፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታቦቱ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ሠርቶ ወደዚያ እንዲገባ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ በድንኳን ውስጥ ይቀመጥ ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በስጦታ ወይም በስርቆሽ ወደ ሌላ በእግዚአብሔር ወዳልተፈቀደው ቦታ ቢሄድማ ኖሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚያ የበለጠ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ሌላ ታሪክ ባልተገኘ ነበር፡፡

ይልቁንም ታቦቱ ተወሰደ ከተባለበት ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኋላ 359 ዓመት ዘግይቶ ማለት በኢዮስያስ ንጉሠ ይሁዳ 18ኛ የግዛት ዘመን ታቦቱ በኢየሩሌም ቤተ መቅደስ እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል (2ዜና. 35፥3)፡፡ መቼም የታቦቱ በቤተ መቅደስ አለመኖር ከሰው ተሰውሮ ኖረ ቢባል እንጂ ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰወር ባልሆነ ነበር (ኤር. 3፥23-24)፡፡

የቀኖና መጻሕፍትስ ምን ይላሉ?
1. መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል
ታቦተ ጽዮን በባቢሎናውያን ተማርካለች ይላል (9፥22-23)፡፡ እንዲህ ከሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በኢየሩሳሌም ሰሎሞን ከሞተ በኋላ እስከ 391 ዓመት የታቦትን መኖር ይገልጻል፡፡

2.   መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ
 ሀ) በም. 1፥3-4 ታቦተ ጽዮን በኢዮስያስ ዘመን ሰሎሞን ባሠራላት ቤተ መቅደስ እንደ ነበረች ይገልጻል (ተሰረቀች ከተባለበት ጊዜ 359 ዓመት ዘግይቶ መሆኑን ያስተውሏል)፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በዚህ ጒዳይ ይስማማል፡፡
 ለ) በም. 1፥59 ታቦተ ጽዮን ከቤተ መቅደሱና ከቤቱ መንግሥቱ ዕቃ ጋር ወደ ባቢሎን ተማረከች ይላል ከዕዝራ ሱቱኤል ጋር ይስማማል፡፡

3.   ተረፈ ኤርምያስ
ባሮክና ኤርምያስ ቤተ መቅደሱን ከነሙሉ ዕቃው ምድር እንድትውጠው አደረጉ ይላል (8፥13-19) ከሁሉም ጋር አይስማማም፡፡

ማስገንዘቢያ
የቀኖና መጻሕፍት እርስ በርሳቸው እንኳ እንደሚቃረኑ፥ የእኛንም የትውፊት ታሪክ እንደማይደግፉ፥ ከአተራረካቸውም በመነሣት ስለ ቃል ኪዳኑ ቦታ አስተማማኝ የታሪክ ማስረጃ ግኝት እንደሌለ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ታዲያ ታቦቱ የት ደረሰ?
ወደ ኢትዮጵያ መጣ ከተባለ በኋላ 359 ዓመት ዘግይቶ ታቦቱ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የነበረ መሆኑ ከተረጋገጠ፥ ወደ ባቢሎንም ካልተማረከ፥ በአንድ ሌላ ቦታም ካልተደበቀ፥ የት ደረሰ? የሚለው ጥያቄ መመለስ እንዳለበት የታመነ ቢሆንም፥ ለጥያቄው የሚሰጠው መልስ ግምታዊ ይሆናል፡፡ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚጠቅሟቸውን ዕቃዎች ባቢሎናውያን ከወሰዱ በኋላ ቤተ መቅደሱን እንዳቃጠሉት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (2ነገ. 25፥8-9፤ ኤር. 52፥12-13፤ 2ዜና. 36፥17-19)፡፡

ባቢሎናዊው ወታደር በድፍረት ታቦቱን ከቤተ መቅደሱ ለማውጣት ቢሞክር ኖሮ እንደ ዖዛ በተቀሠፈ ነበር (2ሳሙ. 6፥6-7)፡፡ ስለ ሆነም ታቦቱ ከቤተ መቅደሱ ጋር ሳይቃጠል አልቀረም የሚል ግምታዊ መልስ አለ፡፡

መቼም ወደ ባቢሎን ቢማረክ ኖሮ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የተማረከው ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ለአይሁድ እንዲመለስላቸው ሲያደርግ የቃል ኪዳኑንም ታቦት በመለሰላቸው ነበር (ዕዝ. 1፥1-11)፡፡ ወይም ናቡከደነጾር ገና ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ላይ በነበረበት ጊዜ ካህናቱ በምስጢር ደብቀውት ቢሆን ኖሮ ከባቢሎን ምርኮ በተመለሱበት ጊዜ ከመካከላቸው የዕድሜ ባለጸጎች ስለ ነበሩ (ዕዝ. 3፥12) ከተደበቀበት እንዲወጣ ጥቈማ ባደረጉ ነበር፡፡ የደበቁት ሰዎች ሁሉ ቢሞቱ እንኳ የቃል ኪዳኑ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር በነቢያቱ በነሐጌ በኩል ይጠቊማቸው ነበር ተብሎ ይታመናል፡፡ እንግዲያውስ ከቤተ መቅደሱ ጋር ተቃጥሎ ይሆናል፡፡

ታቦት እንደ ገና አልተቀረጸምን?
ከባቢሎን የተመለሱ አይሁድ ከመማረካቸው በፊት በተነገረው ትንቢት መሠረት በኢየሩሳሌም አዲስ ቤተ መቅደስን ሠሩ (ኢሳ. 44፥24-28፤ ዕዝ. 1፥1-4 ፤ 6፥14-18)፡፡

ይህ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ የተከናወነ ሲሆን ታቦት እንደ ገና እንዲሠራ ግን እግዚአብሔር አላዘዛቸውም ነበር፡፡ ይልቁንም የይሁዳና የብንያም ልጆች ገና ወደ ባቢሎን ከመማረካቸው በፊት ዐሥሩ ነገደ እስራኤል ወደ አሦር ከፈለሱ በኋላ በነቢዩ በኤርምያስ በኩል እግዚአብሔር ባስተላለፈው መልእክት፥ የዐሥሩን ነገድ ልጆች ከአሦር፤ የሁለቱን ነገድ ልጆች ከሌላ ከተማ ወደ ጽዮን እንደሚመልሳቸው ተናገረ፡፡ ዳሩ ግን ወደ ጽዮን ቢመለሱም፥ ዐዲስ ቤተ መቅደስ ቢሠሩም፥ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትን መቅረጽ እንደማያስፈልጋቸው ገልጾላቸው ነበር፡፡  “... ወደ ጽዮን አመጣችኋለሁ፡፡ ... በዚያ ዘመን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፡፡ ልብ አያደርጉትም አያስቡትምም፡፡ አይሹትምም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም፡፡” በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል …” ይላል (ኤር 3፥6-18) ይህ ትንቢት የተናገረው ታቦቱ በኢየሩሳሌም በነበረበት በኢዮስያስ ዘመን ነበር፡፡

ስለዚህ ቊርጥ ባለ አነጋገር የተላለፈላቸው የትንቢት ቃል ለእነርሱ ግልጽ ነበርና እንደ ገና በሠሩት ቤተ መቅደስ ታቦት ቀርጾ ማስገባት አላስፈለጋቸውም፡፡

ቤተ መቅደስ በሕጉ መሠረት መታነጽ የነበረበት በኢየሩሳሌም ብቻ ቢሆንም ለእግዚአብሔር ቃል ጥናትና እርስ በርስ ለመተናነጽ ለመጽናናት፥ ለመወያየት የሚገለገሉበትን ምኲራብ ዐሥር ወንዶች አይሁድ ባሉበት ቦታ ያቋቁሙ ነበር፡፡ መሥዋዕት ግን አይቀርብበትም፡፡

እንግዲህ አምልኮተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ነበረ ስንል፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የነበሯቸው በእነርሱም በመመራት እግዚአብሔርን እያመለኩ የእስራኤላዊነትን ወግና ሥርዐት ይዘው የኖሩ ከመካከላቸውም ክርስትናን የተቀበሉ አይሁድ ነበሩ ከማለት የሚዘል አይደለም፡፡

ከክርስትና በፊት የኢትዮጵያ አብያተ መንግሥት በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሠረተ አምልኮተ እግዚአብሔር ነበራቸው የሚለው የቃል ታሪክ ወደ ፊት በሚገኘው የታሪክ ቅርስ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ በብፁዕ አቡነ ሰላማ ወንጌል እስከ ተሰበከበት ዘመን ድረስ በኑብያም በሳባም የጣዖት አምልኮ እንደ ነበረ ከማረጋገጥ የሚያልፍ የታሪክ ቅርስ እስካሁን አልተገኘም፡፡

እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ የተዘጋጀውን ታቦት ማለት የጽላቱን ማደሪያ ሳጥን ስለ አሠራሩ የተሰጠውን መመሪያ በመከተል ሠርቶ ማቅረብ ይቻል ይሆናል፡፡

ጽላቱን በተመለከተ ግን በተሰበሩት ዐይነት እንደ ገና ሠርተህ አቅርብ የተባለው ሙሴ፥ ጽላቱን ጠረበና እግዚአብሔር ሕጉን ጻፈባቸው፡፡ በኋላም በታቦቱ ውስጥ አስቀመጣቸው እንጂ ስለ ርዝመታቸው፥ ወርዳቸውና ውፍረታቸው መጠን የተሰጠ መመሪያ አልነበረም፡፡

እንደ እውነቱማ፤ በዐይን የማይታየው፥ በጆሮ ብቻ የሚደመጠው ከእግዚአብሔር አፍ የወጣው ቃል የተጻፈበት ጽላት የእግዚአብሔር ቃል ወልድ በሥጋ ተገልጾ የሚታይ እንደሚሆን የሚያመለክት ተምሳሊት ስለ ነበረ፥ በሥጋ የተገለጸውን ቃለ እግዚአብሔር ወልድን (ቃል ሥጋ ሆነ የሚል እምነትን) የተቀበሉ ክርስቲያኖች በምሳሌ ለማምለክ ወደ ኋላ አይመለሱም፡፡ ከደራሲው ጋር “ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኲለሄ ዘግቡር እም ዕፅ ዘኢይነቅዝ፥ ይትሜሰል ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ ዘኮነ ሰብአ ... ኹለንተናው በወርቅ የተለበጠ ከማይነቅዝ ዕንጨት የተሠራው ታቦት ሰው በሆነው ቃል እግዚአብሔር ወልድ ይመሰልልናል” ይላሉና፡፡

1 comment: