Sunday, February 18, 2018

ልዩ ልዩ



የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት 25ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀረበ ጽሑፍ

አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር በእንተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ(ሮሜ 18) በእንዲህ መሰሉ ክርስቲያናዊ ክብረ በዓል ላይ ቃለ አኰቴት መቅደሙ አያስገርምም። ደግሞስ እንደ ክርስቲያን በኹሉና ስለ ኹሉ ማመስገን ይገባን የለምን? ስለ ኾነም ከኹሉ አስቀድመን በነገር ኹሉ የረዳንን ልዑል እግዚአብሔርን በኢየሱስ ክርስቶስ እናመሰግነዋለን።

ቀጥሎስ? እንኳን ደስ አላችሁ። የማኅበረ በኵር አባላትና አገልጋዮች፥ የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት መሥራቾች፥ አዘጋጆች፥ ዐምደኞች፥ የራእዩ ደጋፊዎችና በዚች መጽሔት አገልግሎት የተጠቀማችሁ ኹሉ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ።

መግቢያ

አገራችን ኢትዮጵያ የሚታዩና የሚዳሰሱ ቀደምት የሥልጣኔ አሻራዎች ባለቤት መኾኗ የታወቀ ነው። በአስገራሚ ኪናዊ ጥበብና ውበት የተገነቡ ዘመን ተሻጋሪ የሥነ ሕንጻ ባለቤት ናት። በሥነ ጽሑፋዊ ቅርሶችም ረገድ የራሷ ፊደል ያላት ብቻ ሳይኾን ቀደምት ጽሑፎችን አበርክታለች። ለጽሑፍ ሥራ እንግዳ ኾናም አልኖረችም። በጥንታዊውም፥ በመካከለኛውም ኾነ በዘመናዊው ታሪካችን ወቅት በተከሠቱ ኹነቶችና ባጋጠሙን ውስጣዊም ኾነ ውጫዊ ፈተናዎች የወደሙትን ሳንቈጥር፥ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች አካብተናል። እግዚአብሔር ይመስገን።

የጽሑፍ ማካበቱ ጕዳይ ከተነሣ ቅድመ ክርስትና እና ድኅረ ክርስትና ማዕቀፍ አለው። ቅድመ ክርስትና አገሪቱና ሕዝቦቿ ለጽሑፍ ሥራ ባዕድ ባይኾኑም፥ የክርስትና መግባት ግን የጽሕፈትን፥ የትርጕምን የነገረ መለኮት አስተንትኖትንና ትምህርትን ለማስፋፋት በር ከፍቷል። ይኹን እንጂ፥ በሚፈለገው ልክ፥ ዐይነትና ብዛት አምርተናል ለማለት አስቸጋሪ ነው። የተጻፈውንም ለማንበብ የታደሉት ጥቂት የማኅበረ ሰቡ አካላት ብቻ መኾናቸው አከራካሪ አይደለም። የመጻፍና የማንበብ ባህል ሥር ለመስደድ ሳንካ የገጠመው ከዚህ የተነሣ ሳይኾን አይቀርም።

የጽሑፍ ታሪካችንን ለማስተንተን ዕውቀቱ፥ ጥሪው፥ አዘንብሎቱና ሙያዊ ብቃቱ ያላቸው ወገኖች እንዲሰማሩበት ወደ ጐን በመተው እኛ ዛሬ ወደ ተሰበሰብንበት ዐላማ እናምራ። ያሰባሰበን የጮራ መጽሔት ጉዳይ ነውና እሱኑ እናተኵርበታለን። ያውም በጨረፍታ።

 

የመጽሔት ነገር

መጽሔት ከሥነ ጽሑፍ ድጕሶች አንደኛው ነው። መጽሔት ከመጽሐፍ ዝቅ ብሎ ከጋዜጣም ከፍ ብሎ እናገኘዋለን። ኾኖም መጽሔት በራሱ ዐይነተ ብዙ ነው። እንደ ዐላማው፥ እንደ ይዘቱ፥ እንደ ተደራሲው ዐይነትና ፍላጎት፥ እንደ ትኵረቱ አቅጣጫ የመጽሔት ደረጃና ጥንካሬ ልዩ ልዩ ነው። በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ካለችው አዕምሮ መጽሔት ጀምሮ ዓለማዊ ብቻ ሳይኾኑ ስፍር ቍጥር የሌላቸው መንፈሳዊ የመጽሔት ዐይነቶች ታትመው ለንባብ በቅተዋል። አብዛኞቹ የተወሰነ ጕዟቸውን ድክ ድክ ብለው ካሳዩ በኋላ ጨንግፈው ቀርተዋል። ያው፥ እንደ ተባለው፥ የክሽፈቱ አባዜ በጽሑፋችንም ረገድ መታየቱ አልቀረም።

የመጽሔት ላይ ጽሑፎች በቍጥብነታቸው፣ በቀጥተኛነታቸው፣ በወቅታዊነታቸውና ወጋዊ ይዘትን በመላበሳቸው የበርካታ አንባብያንን ቀልብ በቀላሉ ይስባሉ። ለዚህም ይመስላል በገበያ ውስጥ ለመግባት ብዙ ጊዜ ሲቸገሩ የማይታዩት። በአንጻሩ፣ መጽሔቶች ለሚያነሡት ርእሰ ጕዳይ የሚሰነዝሩት ሐሳብ ወይም ትንታኔ የውስንነት ችግር ይታይበታል። ይህ የሚኾነው ከጸሓፊው ዐቅም ዕጦት ብቻ ሳይኾን፣ ከመጽሔት ጽሑፎች የአጻጻፍ ባሕርይ የተነሣ ጭምር ነው።ዛሬ ትኵረታችን ርእስ የኾነው መጽሔት ጮራ ግን፥ በደምሳሳ እይታ፥ ከእነዚህ ውሱንነቶች በላይ ለመራመድ ሲፍጨረጨር እንደ ቈየ ምስክሮችና ማስረጃዎች አሉ። ቍጥር 1 ዕትሙን ጨምሮ፥ ቀዳሚ ዕትሞቹ ኹሉ፥ እንደ መጽሐፍ በተደጋጋሚነት እየታተመ ለመሠራጨት የበቃውና በብዙዎች ዘንድ ደግሞ እየተደጐሰ (እየተጠረዘ) የሚቀመጠው ከዚህ ተፈላጊነቱ እንዲሁም ከያዘው መልእክት ዘመን ተሻጋሪነት የተነሣ ይመስላል።

 

የ”ጮራ” ምንነት?

ጮራ በማኅበረ በኵር አማካይነት እየታተመች የምትወጣ መንፈሳዊ መጽሔት ነች። ትኵረቷም መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ርቱዕ የክርስትና ነገረ መለኮት ነው። በኢትዮጵያ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ ተአምኖ ላይ መሠረት በማድረግ፥ ሰዎች በጌታችንና በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አማካይነት እግዚአብሔርን በማወቅ የድኅነትን ኀይል እንዲረዱና እንዲለማመዱ፥ በዳኑበት ሕይወትም በጽድቅና የመታዘዝ ኑሮ እንዲመላለሱ የማነጽን ሥራ የምታከናውን መጽሔት ናት። በተለይም፥ እናት ቤተ ክርስቲያን ከከበባት ማንኛውም ዐይነት እንግዳ ትምህርት፥ ተነቃፊ ትውፊት፥ ጐታች ባህል፥ የአሕዛብ ልማድና ሕጹጽ ሥርዐተ አምልኮ በመላቀቅ ወደ ቀደመው የጠራ የእምነትና ተግባራዊ መንገዷ እንድትመለስ ያላሰለሰ ጥረት ስታካኺድ የቈየች መኾኑን ላለፉት 25 ዓመታት ታትመው ከተሠራጩት 48 ዕትሞቿ መረዳት ይቻላል።

በዚህም ምክንያት መጽሔቷ ወዳጅም ባላንጣም ያፈራች ኾና ታይታለች። በአንባቢዎቿ ዘንድ በጕጕት ታስሳ የምትፈለገውን ያህል በዐቋሟና በመልእክቷ ትኵረት በሚጻረሯት ዘንድ ታድና እንድትወገድ ዘመቻ የተከፈተባት፥ ቅስቀሳ የሚካኼድባትና በየሜዳው የተገኘው አቧራ ኹሉ ታፍሶ የሚበተንባት መጽሔት መኾኗ በየአደባባዩ የሚታይ እውነት ነው። በተግባሯ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ “በምድረ በዳ የምትጮኽ” ዐይነት ብትመስልም፥ የንስሓና የእምነት ጥሪዋን ስታከናውን ቈይታ 25 ሻማዎችን ለመለኰስ ብትበቃም፥ ውጣ ውረዶቿን ከመጽሔቶቹ ዕትሞች ቍጥር ብቻ መረዳት አይከብድም። በጮራ አማካይነት ምን ያህል ነፍሳት በወንጌለ መንግሥቱ ኀይልና ጸጋ እንደ ተማረኩ የሚታወቀው በታላቁ ነጭ ዙፋን ፍርድ ወቅት ቢኾንም፥ ከተለያዩ ምስክርነቶች እንደሚታየው ግን አያሌ ወገኖች የሕይወትን ጸጋ ተቀብለዋል።[1]

መጽሔቷ ባለፉት 25 ዓመታት 48 ቅጾችን አበርክታለች። ጮራ እስከ ዛሬ ድረስ በሦስት ዋነኛ አዘጋጆችና በሦስት ም/ አዘጋጆች ተመርታለች። የመጀመሪያው የመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ የነበሩት የማኅበረ በኵር መሥራችና አሰባሳቢ የነበሩት አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ነበሩ። ኮማንደር መላኩ ዳኜ የምክትል አዘጋጅነት ሥራ እንደ ነበራቸው መጽሔቱ ላይ ይታያል። በአለቃ መሠረት አዘጋጅነት ከቍጥር 1 - 13 ያሉት ዕትሞች ተሰናድተዋል። ኾኖም የአለቃ መሠረት ወደ ጌታ ዕረፍት መሰብሰብን ተከትሎ፥ ቍጥር 14 በፊት ሽፋን ገጹ የእርሳቸውን ምስል የሚያሳየውን ፎቶ ግራፍ ይዞና ዜና ዕረፍታቸውን አካቶ ሲታተም ዐዲስ አዘጋጅ እንዳገኘ ይገልጻል፤ አቶ ጸጋዬ ደምሴ ናቸው። በጸጋዬ ደምሴ አዘጋጅነት መጽሔቷ ከቍጥር 14 እስከ 37 ዘለቀች። በዚህ ጊዜ አቶ ሠርፁ እጓለ ጽዮን ምክትል አዘጋጅ ኾነው ቈይተዋል። ከቍጥር 38 ጀምሮ እስከ አኹን በዘለቀው የመጽሔቷ ዕትም ደግሞ በዋና አዘጋጅነት የሚያገለግሉት ዲያቆን አግዛቸው ተፈራ መኾናቸውን መረዳት ይቻላል። ሦስተኛው አዘጋጅ ከመጡ በኋላ ዐዳዲስ ዐምዶች ከመጨመራቸውም በላይ የመጽሔቷ ገጸ ቅንብርና የኅትመት ጥራት ላይ ለውጥ ተደርጓል። በአጠቃላይ ግን ዐበይት የሚባሉትን ዐምዶች በዘላቂነት የመጠበቁ ባህል መቀጠሉ ይታያል። ለምሳሌ ያህል በመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የሚመረጡ አርኣያ የሚኾኑ ጎምቱ አባቶች ታሪክ ቀርቦበታል። ምሳሌ፦ አለቃ ታየ፥ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፥ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፥ …

 

የጮራ አቀራረብ

መጽሔቷ ነሐሴ 1983 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የኅትመት ብርሃን በመቀዳጀት በአደባባይ ታየች። ዋጋዋ ብር 1.50 ነበረ። ትኵረቷን የኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክን፥ የመዳን ትምህርት፥ የትዳር (ጋብቻ) እና መሠረተ እምነትን በማድረግ የየርእሶቹን የመጀመሪያ ክፍል አወጣች። በርግጥ ሌሎች ዐጫጭር ሐሳቦች የያዙ ዐምዶችም ነበሯት። ኾኖም ግን የተጠቀሱት ርእሶች በተከታታይ ዕትሞች የሚዳሰሱ መኾናቸው በራሱ ኹለተኛ ዕትም እንደሚኖራት ከማመልከቱም በላይ ምን ይጻፍ ይኾን? የሚል ጕጕት በአንባቢዎቿ ላይ መጫሩ እንደማይቀር የሚያመለክት ነበር።

የተጠቀሱት ዐምዶች በዋነኛነት የመጽሔቷ መታወቂያዎች ኾነው ዘልቀዋል። ለዚህም ይመስላል ከዐበይት ዐምዶቿ በአንዱ ሲተላለፍ የቈየው ትምህርት በአንድ ተጠርዞ ወደ መጽሐፍነት ሊለወጥ እንደ ኾነ ማኅበሩ ያስታወቀው። መጽሐፉም በዚህ የሩብ ምእት ዓመት ክብረ በዓል ላይ እንደሚመረቅም ይጠበቃል።

ቀዳምያት ዕትሞቿ በአብዛኛው በተጠቀሱት ዋነኛ ዐምዶችና ሐሳቦች ላይ የሚያተኵሩ ሲኾኑ፥ በኋላ ላይ ብቅ ያለውና ለበርካታ ዕትሞች ያለማቋረጥ የቀጠለው የአለቃ ነቅዐ ጥበብና አገልግሎታቸው ምናባዊ ታሪክ የአንባቢዎችን ንቃተ ኅሊና ያዳበረ፥ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መታደስ እምነትና ተስፋ ሠንቀው ለወጡ ኹሉ እንደ ትንቢታዊ መልእክት የተቈጠረ ነበር። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢን ጨምሮ ሌሎች ወገኖች አለቃው በሚገኙበት ደብር ለመኼድና አገልግሎታቸውን ለመካፈል በታላቅ ጕጕት እስኪሞሉ ድረስ የጽሑፉ ተጽዕኖ ጠንካራ እንደ ነበር የሚናገሩ አሉ። ዘግየት ብለው በመጡት ዕትሞች የአለቃ ታሪክ ምናባዊ[2] መኾኑን ብናውቅም እንኳ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታወቁ ቤተኛ ካህን መስለው በትምህርታቸውና በአመራራቸው የሚኖሩ ይመስል ነበር። እኚህ አባት ዛሬ እዚህ መጥተው ከኾነም ሰላምታ እናቀርብላቸዋለን።

 

የጮራ መጽሔትና የተሐድሶ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ  

ለቃለ እግዚአብሔር የበላይነት መገዛት

መጽሔቱ በቻለው መንገድ በሁሉም ነገር ለሚያቀርበው ለአስተንትኖቱም ለሙግቱም ኹሉ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ያደርጋል። ምንም እንኳ ታሪካዊ የኾነውን በርቱዕ የክርስትና ዘርፍ የሚታወቁ ቀዳምያን አበውን ትምህርት አስተሳሰብ ትውፊት ቢያካትትም በእግዚአብሔር ቃል የተገዛ እስካልኾነ ድረስ አይጨምረውም፤ ይተወዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል የበላይ የሚያደርግ መጽሔት ነው። ለትምህርታችንም ለሥርዐተ አምልኮአችንም ለልምምዳችንም የእግዚአብሔር ቃል የበላይ ባለ ሥልጣን ነው የሚል እምነትና ትኵረት እንዳለው መረዳት ይቻላል። ለየትኛውም በውስጡ ለተካተተ ጽሑፍና ሐሳብ የእግዚአብሔር ቃል በማስረጃነት ይቀርብበታል።

ኦርቶዶክሳዊነት

መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱን እንደ ጠበቀ፥ ፍለጋቸውን የምንከተለውን የቀደምት አበውን አስተምህሮ ሳያዛንፍ ጥንታዊው የኦርቶዶክስ ክርስትና የጮራ መታወቂያ ቀለም ነው። ትምህርቱ፥ ቋንቋው፥ ነገረ መለኮታዊ አስተንትኖቱ፥ ታሪካዊ ማስረጃው እና ሌሎችም መሠረታዊ መታወቂያዎቹ በሙሉ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው። በክፋት በጠመዱት ዘንድ እንዲፈራ ብቻ ሳይኾን “የበግ ለምድ እንደ ለበሰ ተኵላ” ፈርጀው እንዲዘልፉት የገፋፋቸው በጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ባህል ላይ ባለው ጥልቅ መረዳትና ዐቋም የተነሣ መኾኑን ማስተዋል ከባድ አይደለም።

ዐውዳዊነት

ከላይኛው ጋር የተዛመደ ነው። ነገረ መለኮታዊ ሐሳቦች በይዘታቸውና በምንነታቸው አይለወጤ ናቸው። ዘመን ተሻጋሪና ባህል ዘለል ናቸው። ቦታና ጊዜ አይሽራቸውም። ይህ እውነታ የተመሠረተው እግዚአብሔር የማይለወጥ ሐሳቡም የጸና ከመኾኑ ላይ ነው። ይኹንና ነገረ መለኮታውያን ሐሳቦች በቅርጽና በመገለጫ ገጽታቸው ዐውዳዊ ናቸው። በሚነገሩበት ዘመንና ኹኔታ ተሠግዎኣዊ ዝምድና ይኖራቸዋል። ስለዚህም ነገረ መለኮት ዐውዳዊ ነው። ክርስትና ዘመን ዘለቅና ዘመን ዘለል ትምህርቱን ይዞ ዐውዳዊ መገለጫ አለው።
ለምሳሌ ወንጌላውያኑ ላይ የተባለውን እንመልከት። በአፍሪካ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ደግሞ በተለይ እየተሰበከ የቈየውና አኹንም እየተሰበከ ያለው ነገረ መለኮት በቀጥታ ከውጭተዝቆ የገባነው። ይህም ሲባል አውሮጳዊ-አሜሪካዊ ነው። የራሱን ሀገራዊ ገጽታና አካባቢያዊ ጠገግ አልተተገነም። ነገረ መለኮታዊ አስተንትኖቱም “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” የመንቀልን ጥበብ አላዳበረም። በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ዘንድ ነገረ መለኮት በጥልቀትና በምጥቀታዊ አስተንትኖቱ አልዳበረም ብቻ ሳይኾን ነገረ መለኮትን የማስተንተኑ ሙከራ ራሱ ቤተኛ አልተደረገም። በርግጥ ችግሩ የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም። አፍሪካን ይመለከታል። ምኒልክ አስፋው ኬኒያዊውን ጆን ሚቢቲን ጠቅሶ እንደ ተናገረው “ክርስትና አፍሪካን ተቈጣጥሯል፤ ጥያቄው አፍሪካ ክርስትናን ተቈጣጥራለች ወይ? የሚለው ነው። ክርስትና አፍሪካን አከርስትኗል፤ ነገር ግን አፍሪካ ክርስትናን አፍሪቃዊ አላደረገችም።
ነገር ግን ነገረ መለኮትን ዐውዳዊ በማድረግ ጥንታዊውና ነባሩ የኢትዮጵያ ክርስትና ዘርፍ በዐውዳዊነት ድክመት የሚወቀሥ አይደለም። የቀደምት ክርስትና ማእከላት የነበሩት የሰሜን አፍሪቃ ቦታዎች በሃይማኖታዊ ስደት ነበልባል ሰበብ ክርስትናቸውን ያጡት ዐውዳዊነት ስላልነበራቸው መኾኑን የሚናገሩ ምሁራን አሉ። በኢትዮጵያ፥ ግብጽና ሶርያ ክርስትና መከራ፥ ስደትና ጦርነትን ተቋቍሞ የሰነበተው ቅዱሳት መጻሕፍትና ነገረ መለኮት በሀገሬው ቋንቋና ባህል በመዛመዳቸው እንደ ኾነ ግልጽ ነው።[4]

ካርል ባርዝ፦ “ማንኛውም ሰባኬ ወንጌል በቀኝ እጁ መጽሐፍ ቅዱሱን በግራ እጁ ደግሞ ጋዜጣ መያዝ አለበት” ይል ነበር። ክርስቲያኖች የወንጌሉን መልእክት ሳይለውጡና ሳይበርዙ በሚኖሩበት ዓለም ውስጥ ማቅረብ መቻል አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንደምናጠና ኹሉ አካባቢያችንን ማጥናት አለብን። “ወፍ እንደ ሀገሯ ትጮኻለችና”። በጮራ ላይ የሚታየው ይኸው ነው።

የተቀበረውን እውነት ፈልፍሎ የማውጣት ጥረት

ሐሰትንና ድንቍርናን በጽናት መታገል

ውሸትን ሲቃወም ፍርጥም ብሎ ነው።

ድንቍርና መንፈሳዊነት አይደለም። ዕውቀት ጠልነት ለክርስትና ባዕድ ነገር ነው። እውነት ለመናገር በምዕራቡ ዓለም ለተከሠተው የዕውቀት መምጠቅ በር ከፋች የነበረው የአይሁዳዊ እና ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ነበር። ቤተ ክርስቲያን ዕውቀትን የምታሳድድ መኾን የለባትም። “በምዕራቡ ዓለም መሃይምነት እንዳይነግሥ ቍልፍ ሚና የተጫወቱት መንፈሳዊ ተቋማት ናቸው፤ ገዳማት የትምህርትና ምርምር ማእከላት ነበሩ፤ በአንድ ወቅት የድንቍርና ጨለማ አውሮጳን ለመዋጥ ተቃርቦ ነበር። ኾኖም ድንቍርና ገዳማት ውስጥ በነበረው ትምህርትና ምርምር ተገታ[5]
በኢትዮጵያ ያለችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም ከዚህ ብዙ መማር ትችላለች። ጥንትም ኾነ በስተኋላ ቤተ ክርስቲያን ለትምህርትና ዕውቀት ብልጭታ አስተዋፅኦ እንደ ነበራት አይካድም። ይኹን እንጂ ዕውቀትን ሊያፍንና ሊከለክል ያለውን ነገር ሁሉ ማስወገድ ይገባል።
ነገረ መለኮት (መንፈሳዊ ትምህርት) እና ክርስቲያናዊ አስተንትኖት ቸል ሊባል አይገባውም። ትክክለኛውን ትምህርት መከተል ከኀጢአት ዐርነት የሚያወጣን ሲኾን፣ (ዐውቀንም ኾነ ሳናውቅ) የተሳሳተ ትምህርት መያዝ በበኩሉ አምልኳችንን ከንቱ ከማድረግም ዐልፎ ተርፎ ከእምነት እንድንወድቅና ከእግዚአብሔር እንድንለይ ሊያደርገን ይችላል። የሚያስቡ፥ የሚጠይቁ፥ የሚያጠኑና የሚመራመሩ መንፈሳዊ መሪዎች ልናፈራ እንደሚገባ የምታሳይ መስታወት ናት።

ለተሐድሶ እንቅስቃሴ ያበረከተው አስተዋጽዖ

በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምጋቤና በኹሉን ቻይነቱ፣ እንዲሁምዘላለማዊ ዕውቀቱ መሠረት ስለ ነበሩን ቀዳሚ ቅርስና ውርሳችን ሁሉ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ታሪክና ቀዳሚነት ግን ብቻቸውን የሚፈይዱት ብዙም አይደለም። ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን ጠቃሚ ሀብታት አንድም በማበላሸት ካቈሸሽናቸው፣ ደግሞም ለእርሱ ክብር ከማድረግ ይልቅ ለሥጋዊ ትምክሕትና ሌላውን ወገን ለማክፋፋት ካዋልናቸው ዐላማቸውን ስተዋልናተሐድሶ ነፋስ ያሻቸዋል። ስም ተሸክሞ ምዉት የመኾን አደጋ እንዳለ ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ከጥንታውያት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለአንዲቱ ጠባቂ እረኛ ኢየሱስ በቀጥታ የተናገረው ይህን ነበር፥ ሥራህን አውቃለሁ። ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ፤ ሞተህማል (ራእ. 31)። ስም እያለው የሞተ ማለት፣ በቁሙ የሞተ ማለት ነው።
በዚህ ዘመን በሀገራችን የሃይማኖት ቀዬ “ተሐድሶ መናፍቅየሚባለውንስድብያህል የገነነ ዘለፋ ያለ አይመስልም። አንዳንድ ወገኖችም ይህን ከመፍራት ይመስላል “የተሐድሶ አካል አይደለሁምበማለት ሲያስተባብሉና ሲማጸኑ ይታያል። ሌሎች (መዘዙን ከመፍራታቸው የተነሣ) ቃሉን እንኳ (አስፈላጊ በኾነበት ስፍራ ሳይቀር) ላለመጠቀም ሲሣቀቁ ይስተዋላል። መጋቤ አእላፍ መክብብ ይህን በታዘቡበት ገጽ እንዲህ ብለው አስፍረዋል፡-
አንዳንዶቹማ ያለችሎታቸው በያዙት የስብከተ ወንጌል መድረክ ስንቱን ሕዝብ በማሳሳት ግራ ሲያጋቡት ይኖራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ትምህርታቸውም ሆነ ስብከታቸው እግዚአብሔርን ማእከል አያደርግም።ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ መናገርም በተሐድሶነት ያስጠረጥረናልብለው በስሙ የሚያፍሩበት ብዙዎች ናቸው።[6]
በዚህ ረገድ ጮራ ተጋፋጭ ናት። ስለ ተሐድሶ ራሱ በግልጽ ጽፋ አስነብባናለች።

 

ጮራ በወንጌላውያን ምእመናን አካባቢ

ለጥናትና ምርምር የሚፈለግ መጽሔት ኾኗል። ጸሓፊው በታዘባቸው በርካታ የኹለተኛ ዲግሪና ጥቂት የዶክተራል ድግሪ ማሟያ ወረቀቶች ላይ በምንጭነት ተጠቅሶ ይገኛል።

ያሉበት ውሱንነቶች

·        ጊዜውን ጠብቆ አይታተምም 25 ዓመት መታተም የነበረበት 100 ቅጾች ነበር።
·        ሊያካትታቸው የሚገባቸውን ተጨማሪ ጕዳዮች አያካትትም።
·        ከተከላካይነት ያለፉ መልእክቶችን መጨመር።
·        የዐቅም ውሱንነትን ለመቅረፍ ማስታወቂያ መጠቀም ያዋጣ ይኾን?
·        አነጋጋሪ ነገረ መለኮታዊ ጭብጦችን መጨመር፦ በጥናት የተደገፈ፥ የበሰለ።

እኛስ ምን እናድርግ

·        አንድም እናንብብ። መጽሐፍትም ይኹኑ ሌሎች ጽሑፎች ከተጻፉ በኋላ መነበብ ካልቻሉ ፋይዳቸው በምን ይታወቃል። ርግጥ ነው፥ለስሟ መጠሪያ ቍና ሰፋችዐይነት ኾኖባቸው የሚጫጭሩ አሉ። ነገር ግን እንደ ጮራ ዐይነት በጥልቅ ጥናትና ምርምር፥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትና በርቱዕ የክርስቲያን ታሪካዊ ነገረ መለኮት መሥመር ለሚጻፉ ሥራዎች የንባብ ትኵረትን አለመስጠት በደል ነው። ጆሴፍ ብሮድስኪ መጻሕፍትን አቃጥሎ ከማውደም የሚከፉ በርካታ ወንጀሎች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል አንደኛው መጻሕፍቱን ያለማንበብ ወንጀል ነው።

ስለዚህ እውነት ወደ ሰው ልብ ዘልቃ እንድትገባ፥ ኀጢአተኞች ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱና እግዚአብሔርን መፍራት በሰው ልጆች መካከል እንዲሰፍን ሰዎች ከመንፈሳዊ ድንቍርና መላቀቅ አለባቸው። የምግባር ልቀትና የማስተዋል ብርታት የጐደለው ሰው በሾላ ፍሬ ውስጥ እየኖረ ውጭውን ዓለም ማየት እንደማይቻለው ትንሽ ፍጥረት ሐሳበ ጠባብና ጥራዝ ነጠቅ ግትር ይኾናል።[7]

ተደጋግሞ ሲነገር እንደሚሰማው፥ ማንበብ ከሚችሉ መካከልብዙዎቹ፥ አዘውትሮ የማንበብ ልማድ የላቸውም ይባላል። ይኹንና ማንበባችን ዕውቀት ለመገብየት፥ ከሌሎች ሰዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሮ ለመማር፥ የጠራና የነጠረ አመለካከት ለማዳበር፥ እንዲሁም በሕይወት የሚገጥሙንን ዐሳሳቢ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሚያግዙንን ሐሳቦች ለማግኘት ወዘተ. እንደሚያስችለን የታወቀ ነው። ድንቍርና አፈር አስግጦ የሚገድል መርዝ ዐዝሎ እንደሚኖር ለማወቅ ከእኛ በላይ መርገምቱን “ያጣጣመው” ማን አለ? ያለ ንባብ የቆመ ሥልጣኔና እድገት የለም። ኤልበርት ሑባርድ ለመጽሐፍ የምናወጣው ገንዘብ ለአንጫቄ (መስቲካ) ከምናወጣው ገንዘብ እስካልበለጠ ድረስ ሥልጡን አገር ልንኾን አንችልም።ይላል። ስለዚህ የንባባችን አንዱ ምርጫ ጮራ ቢኾንስ?
·        እናስተላልፍ። ስለ ጮራ ለሌሎች እናስተዋውቅ። መግዛት ለማይችሉም እናውስ። ዐቅማችን ከፈቀደ ደግሞ ጨምረን በመግዛት ለሌሎች እንለግስ። በማኅበራዊ የዜና አውታሮች እናሠራጭ።
·        በመጽሔቷ ላይ የውይይት ቡድኖች እናደራጅ
- በአነስተኛ ቡድኖች መጽሔቷ በምታነሣቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ መለኮታዊ ሐሳቦች ላይ
- ከኦርቶዶክሳዊ ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን ጋር ለሚኖረን ግንኙነት ድልድይ ይፈጥራል
·        የመጽሔቱ ቋሚ ዓመታዊ ደንበኛነትን ማዳበር
·        የመጽሔቱን የኅትመትና የሥርጭት ወጭ መሸፈን
·        ጽሑፎችን ማበርከት፦ ለድካማችን ተመጣጣኝ “የላብ መተኪያ” ባይገኝበትም እንኳ ወዛችንን ቀርቶ በምድር ላይ አንዲቱ የፀጕራችን ቅንጣት በከንቱ እንዳትወድቅ ከሚጠብቀን ቸር ጌታ ወሮታችንን እየጠበቅን።
·        ጸሎት፦ በግልም በጋራም ለምሳሌ የጮራ የጸሎት ማኅበር
·        በየንባብ ቤቶቹ ማስገባት
·        አማካሪነት

ማጠቃለያ

እንግዲህ ጮራ ለሩብ ምእት ዓመት ተጕዛ ምስክር ኾነናልና እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ጌታችን በመጪዎቹ ዘመናት ካልተመለሰ ሌላ 25 ጨምራ የወርቅ ኢዩቤሊዩዋን ስታከብር በብዙ ድልና ስንቅ ተሞልታ ይኾናል የሚል ተስፋ አለኝ። የተሐድሶ እንቅስቃሴውም በጋመ የጸጋ ነበልባል ተመልቶ የነፍሳት መከር ይበዛለታል ብዬ ዐልማለሁ። ያ እውን እንዲኾን መንፈሳዊ ድንቍርናን ለመዋጋት የጽሑፍ ሥራ ታላቅ አስተዋፅኦ አለው። የአውሮጳዊውን ተሐድሶ ለመምራት የማተሚያ ማሽን ጥቅም ላይ መዋል መጀመሩ የፈጠረው የጽሑፍ አብዮት ታላቂቱን የሮም ቤተ ክርስቲያን ቀድሟት ስለ ሮጠ በሜዳው ላይ የተሐድሶው ንቅናቄ ሊገታ አልቻለም።

ዘነብ ኢትዮጵያዊ በመጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ እንዲህ ሲል ይጮኻል፤እናንተ ሰነፎች [ሆይ] ድንቍርናን ከማይመለስበት ሽጡት፤ የሰነበተ እንደ ኾነ ይገድላችኋል።[8] ድንቍርና ላይመለስርቆ የሚሸጠውበቃለ እግዚአብሔር ዕውቀት፥ በማንበብ ገበያ፥ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በአሰላስሎ አይደለምን? “ሩቅ አስቦ ሩቅ ለማደርመጽሐፍ ምርኵዝ ነው፤ መጽሐፍ አርቆ ማያ ነው። አለቃ ዘነብ እንደሚል፥መጽሐፍ መነጽር ነው፤ ለሚመለከተው ሰው ሩቅ ያሳያል።[9]

እውነቱን ነው፥ ዘነብ፤ አርቆ በማያይ ካህን ስንት ሕይወት መከነ? የቅርቡን ብቻ በሚያይ መምህር ስንት እንቦቃቅላ ተቀጨ? አርቆ በማያይ ሐኪም ስንት ሕሙም ደከመ? አርቆ በማያይ ፖለቲከኛ ስንት ዜጋ ተፈጀ? አርቆ በማያይ ሰባኪና ነቢይ ምን ያኽል ጎጆዎች አዘነበሉ? የቅርቡን ብቻ በሚመለከት ስግብግብ ነጋዴ ስንት ነፍሳት ታጨዱ? … መጻሕፍት በሚሰጡት ዕውቀትና ጥበብ ባልበረታ ድውይ አስተሳሰብ ምን ያህል ወደ ኋላ ተጓዝን? ሩቅ ያላየ ስንቱን አጋየ! አኹን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሚታየው ግልብነትና ጥራዝ ነጠቅነት መድኀኒቱ ጥራዝ ጠለቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ መለኮታዊ ጽሑፎች ናቸው። ጮራ ይህን ክፍተት በመሙላት ረገድ የራሷን ሚና እንደምትጫወት አልጠራጠርም።

ጀሴ ሊ ቤኔት ከአለቃ ዘነብ ሐሳብ ጋር የቀረበ አባባል አለው፤ “መጻሕፍት አደገኛ የኾነውን የሰው ልጅ የሕይወት ባሕር በአግባቡ ለመቅዘፍና ለመሻገር እንዲያስችሉን በሌሎች የተዘጋጁልን አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓሶች፥ የርቀት መመልከቻ አጕሊ መነጽሮችና የመዳረሻ ቦታውን የሚያመላክቱን መልክአ ምድራዊ ሰንጠረዦቻችን ናቸው”[10] ብሏል። ከግለ ሰብ ጀምሮ አንድ ማኅበረ ሰብ በንባብ መበርታት ያለበት ለዚህ ነው፤ አርቆ እንዲያይ፥ ረቅቆ እንዲያስብና ርቆም እንዲጓዝ።



[1] ለዚህ ዋቢ የሚኾኑ በርካታ ወገኖች ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲኾን፥ ማኅበረ በኵር ራሱ በተለያዩ ጊዜያት ያቀረበው ዘገባ ተጠቃሽ ነው።
[2] ተወዳጅ የምናባዊ ባለ ታሪኮች (ገጸ-ባሕርያት) በአንድ ግለ ሰብ ወይም ማኅበረ ሰብ ለይ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ጠንካራ ነው። ሼርሎክ ኾምስ የዝነኛው የምርመራ ልቦለዶችና ዐጫጭር ጽሑፎች ደራሲ የሰር አርተር ካነን ዶይልፍጡርየኾነ ገጸ ባሕርይ ነበር። ገጸ ባሕርዩን በኹሉም ጽሑፎች ውስጥ የወንጀል መርማሪ ኾኖ እናገኘዋለን። በአንዱ መጽሐፉ ላይ ኾልምስ በመሞቱ ምክንያት የደራሲው ቤት በሕዝብ ተከቦ እንደ ነበር ይነገራል። ስለዚህ፥ ያለውዴታው (ወይም በውዴታው) በቀጣዩ መጽሐፍ ገጸ ባሕርዩን የታሪኩ አካል በማድረግ እንደ ገና ተከታይ መጽሐፍ ለመድረስ ተገዷል። በኢትዮጵያም፥ የማዕበል ዋናተኞች በሚባለው ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ መደምደሚያ ላይ የደረሲው ኀይሉ ጸጋዬ ቤት ተመሳሳይ ዕጣ እንደ ደረሰበት ጄቴቪ ኢትዮጵያ ላይ ቃለ ምልልስ በሰጠ ቀን ሲናገር ተደምጧል። 
[4] አገር በቀል አመራርን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያንና - የቤተ መንግሥት ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች የተጫወቱትን ሚና ባንዘነጋም ቅዱሳት መጻሕፍት በሀገሬው ቋንቋ መተርጐማቸውና ክርስትናው በሕዝቡ ባህል ውስጥ ሥር መስደዱ ያበረከተው አስተዋፅኦ ጕልሕ ነበር። See Calvin E. Shenk, “The Demise of the Church in North Africa and Nubia and Its Survival in Egypt and Ethiopia: A Question of Contextualization?” Missiology: An International Review, Vol. XXI, No.2. 1993.
[5] ማቴቴስ፥ 21
[6] መክብብ አጥናው (መጋቤ አእለፍ) አምስተኛው ጉባኤ፦ ዕድሜ-ቀጥል፣ ትምህርት ዐዘል የአባቶች ጨዋታ፣ ክፍል አንድ  (ዐዲስ አበባ፡- አልቦ አሳታሚ፣ 2004 ..) 12
[7] መክብብ አጥናው (መጋቤ አእላፍ) ኹለገብ ትምህርት ሰጭ የአዕምሮ ማዝናኛ  (ዐዲስ አበባ፦ አሳታሚ አልተጠቀሰም፥ 2005 ..) 121
[8] ዘነብ ኢትዮጵያዊ [አለቃ] (ዳንኤል ወርቁ ቀድቶ እንዳሳተመው) መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ 19
[9] ዘነብ፥ ጨዋታ 25
[10] Johnny Ong, Don’t Live Your Life in One Day: 100 Effective Rules to Live a Meaningful Life (Singapore: Armour Pub. Ltd: 2008), 11.

1 comment:

  1. ጮራወች አባ ሰላማ ከአይናችን ከጠፋች በኋላ እናንተም ጠፋችሁብንኮ።

    ReplyDelete