Sunday, February 16, 2014

መሠረተ እምነት

ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ
ባለፈው ዕትም በዚህ ክፍል ውስጥ የዕብራውያንን መልእክት መሠረት በማድረግ የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ለማሳየት ሞክረናል። በተከታታይ እያቀረብን ያለነው የክርስቶስን መካከለኛነት የተመለከተው ይህ ትምህርት ከክርስቶስ ትምህርነት መጀመር እንደ ነበረበት አልዘነጋነውም፤ ሆኖም በክርስቶስ መካከለኛነት ዙሪያ ዋና መከራከሪያ ሆነው የሚገኙት መጽሐፍ ቅዱሳውያን ክፍሎች መልእክታተ ሐዋርያት በመሆናቸው፥ በዚያ መጀመሩ መልካም መስሎ ስለ ታየን ከዚያ ጀመርን። እስካሁን ያየነውና በሐዋርያት ምስክርነት ላይ የተመሠረተው የክርስቶስ የመካከለኛነቱ ትምህርት ምንጭ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን በዚህ ዕትም ለማሳየት እንሞክራለን። ከኢየሱስ መካከለኛነት ጋር ተያይዞ መካከለኛነቱን ማስቀረት ላይቻል፥  በአንዳንድ ወገኖች ለማምታታት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ መከራከሪያዎችንም እንዳስሳለን።

የክርስቶስን መካከለኛነት ማስተዋል ከስሕተት የሚያድንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያመጣ ዋና እና መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ነው። ይህን የትምህርት መንገድ የሳተ ሰው ፍጻሜው ጥፋትና የዘላለም ሞት ይሆናል። ምክንያቱም ያ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰውን ብቸኛና ቀና መንገድ ስቶ ሌላ አቅጣጫን ተከትሏልና።
ኢየሱስ ስለ መካከለኛነቱ የተናገረው
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመጣበትና ቤዛ ሆኖ የሞተበት ዋና ዐላማ ሌላ አይደለም፤ በኀጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረውን ሰው ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲያስረዳ፥ “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአል …” (1ጴጥ. 3፥18) ይላል። በዚህ ቃል መሠረት ኀጢአተኛ ሰው ወደ እግዚአብሔር ይቀርብ ዘንድ መሄጃ መንገዱ እና መግቢያ በሩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፤ እርሱ፥ ወደ አብ መሄጃ መንገዱ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ መመጣት አይችልም ብሏል (ዮሐ. 14፥6)።  ወደ አብ መግቢያ በሩም እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማርያም ያገኛል (ዮሐ. 10፥9) ሲል፥ ኀጢአተኛ ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ፥ ከእርሱም ጋር ሊታረቅና የዘላለምን ሕይወት ሊያገኝ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ብቻ መሆኑን በማይታበል ቃሉ ተናግሯል።

ኢየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ጊዜ መካከለኛነቱን በቃል አስተምሯል፤ በተግባርም አሳይቷል። ከላይ የጠቀስናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ መካከለኛነቱ ካስተማራቸው ትምህርቶች ዋናዎቹ ናቸው። መጽሐፈ ቅዳሴ እና መጽሐፈ ሰዓታትም በወንጌለ ዮሐንስ የተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ የተጠቀሱት እነዚህ ጥቅሶች አንድን ጕዳይ፥ እርሱም የኢየሱስን መካከለኛነት ለመግለጥ እንደ ተጻፉ በማመን አንድ ላይ በማድረግና በአንድ አረፍተ ነገር በተብራራ መንገድ አስፍረዋቸዋል፤ እንዲህ ሲሉ፥ “ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ - ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ የሚያደርስ ጥርጊያ ጐዳና፥ ወደ ወለደው የሚያገባ በር ነው።” መንገድ እና በር ተብሎ በዘይቤያዊ አነጋገር የተገለጸው የኢየሱስ የመካከለኛነቱ ተግባር እንደ ሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ወደ አብ ለመድረስ የቀናው ጐዳና እርሱ ራሱ ብቻ መሆኑን እየነገረን፥ ወደ አብ ሊያድርሱ የማይችሉ ሌሎች መንገዶችን መጥረግ፥ ወደ አባቱ የሚያገባውም በር እርሱ ሆኖ እያለ ሌሎች ወደ አብ የማያገቡ በሮችን መክፈት ከቶ ከየት የመጣ ትምህርት ይሆን? ጌታችን የሚለውን መስማት ይሻላል? ወይስ እርሱ የሚለውን ወደ ጎን ትቶ በራስ መንገድ መጓዝ? የክርስቶስን መንገድነት እና በርነት ለማስተባበል መሞከርስ ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት?

ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አብ እንደሚለምን በተደጋጋሚ ተናግሯል (ዮሐ. 14፥15-16፤ 17፥9፡20-21)። የሚለምነው ኢየሱስ ነው፤ የሚለምነው ስለ ደቀ መዛሙርቱ ነው፤ የሚለምነው አብን ነው። እግዚአብሔር በሾመው በመካከለኛችን በክርስቶስ ስፍራ የራሳቸውን መካከለኛ ያስቀመጡ ሰዎች፥ “እርሱ (ኢየሱስ) ራሱ እግዚአብሔር ነው ወደ ማን ይለምናል?” ሲሉ ለሚያቀርቡት ጕንጭ አልፋ ክርክር፥ ይህ የጌታችን ንግግር በቂ ምላሽ ነው። ይህን ትምህርት ለማረጋገጥ ከእርሱ በላይ ከቶ ማን ይመጣል?

በዚህ ከንቱ የክርክር ጭብጥ እንደሚረቱ ሲያውቁ፥ “እለምናለሁ ቢልም እንዲህ ያለው እስከ ሞቱ ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን አይለምንም” ሲሉ ከፍለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ጌታ ኢየሱስ በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላም መካከለኛችን ነው። ለምሳሌ፡- ከመሰቀሉ አስቀድሞ፥ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል” ሲል አብን እንደሚለምን ተናግሯል። ወደ ሰማይ ካረገና በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ ደግሞ በእርሱ መካከለኛነት በኩል የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለሐዋርያት ተሰጥቷል። “ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው” (ሐ.ሥ. 2፥33) ሲል ጴጥሮስ ይህንኑ ያረጋግጥልናል። በዚህ ሥዕላዊ መግለጫ በሚመስለው የጴጥሮስ ምስክርነት ውስጥ፥ ኢየሱስን በአብና በሐዋርያት መካከል መካከለኛ ሆኖ እንመለከተዋለን። በዚህ ስፍራ ሲለምን አናየውም፤ ይሁን እንጂ ቀድሞ እለምናለሁ ያለበት ጕዳይ የሚፈጸምበት ጊዜ በመድረሱ፥ በቀደመ ልመናው መሠረት፥ የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሲያፈሰው በግልጽ ይታያል። ከእግዚአብሔር መካከለኛችን በሆነው በኢየሱስ በኩል ሁሉ ነገር እንደሚሰጠንና እንደሚደረግልን ከዚህ ቃል መማር ይቻላል። ይህ የሆነው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ እና በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ መሆኑን ደግሞ ልብ ይሏል።  

እርሱ ጌታችን በስሙ እንድንለምን ያስተማረው ትምህርት፥ በመካከለኛነቱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበትን ሁኔታ ያስረዳል። “በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። … በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና።” (ዮሐ. 16፥23-24፡26-27)። በተለይ ከትንሣኤው በኋላ በኢየሱስ ስም አብን ስንለምን፥ ደስታችን ፍጹም ይሆናል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የምንለምነውን እንቀበላለን፤ በኢየሱስ ስም ስንለምን እርሱ አብን አይለምንም፤ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለምንወደውና በስሙ ስለምናምን አብ ይወደናልና፥ በስሙ ያቀረብነው ልመና ተቀባይነት ይኖረዋል። አንድምታ ወንጌሉ ለዚህ ንባብ የሰጠው ትርጓሜ እንዲህ ይላል፤ “በቅንው ወልድከ /በተቸነከረው ልጅህ/፥ በስቁል ወልድከ /በተሰቀለው ልጅህ/ እያላችሁ አብን ብትለምኑት የለመናችሁትን ሁሉ እንዲያደርግላችሁ በውነት እነግራችኋለሁ።” ኢየሱስ ራሱ በስሙ የምንለምነውን ሁሉ እንደሚያደርግልን ተናግሯል (ዮሐ. 14፥13-14)።

ከዚህ ቃል ጋር የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክትም ይስማማል፤ “እግዚአብሔር አብን በእርሱ [በኢየሱስ] እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቈላ. 3፥17)። ስለዚሀ ምስጋና፣ ጸሎት፣ ልመና ከክርስቲያኖች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው በኢየሱስ ስም አማካይነት ነው (ሮሜ 1፥8፤ 7፥25፤ ኤፌ. 3፥21፤ 5፥20)። እግዚአብሔርም ሕዝቡን የባረከውና የሚባርከውም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው (ሐ.ሥ. 3፥26፡ ኤፌ. 1፥3)።

በቅዳሴ እና በአበው ጥንታውያን ጸሎቶች  ውስጥም ይህን በግልጽ ማስተዋል ይቻላል። ለምሳሌ፡- በቅዳሴ ላይ “ነአኵተከ እግዚኦ በፍቁር ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ - አቤቱ በተወደደው ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ [ስም] እናመሰግንሃለን።” የሚልና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአብ የቀረበ ምስጋና እናገኛለን። ሊጦን፣ መስተብቊዕ፣ ዘይነግሥ፣ የተባሉት ጸሎቶች የሚደመደሙት “በአሐዱ ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ - በአንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ” በሚለው የኢየሱስን ስም ምዕራገ ጸሎት (ጸሎት ማሳረጊያ) አድርገው ነው። ያለ እርሱ ስም ጸሎትም ልመናም ወደ አብ የሚያርግበት መንገድ ከቶ የለምና።

ኢየሱስ በመጸለይ፣ በመለመንና በመማለድ መካከለኛነቱን አሳይቷል
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፥ በእርሱ በኩል በስሙ እንዲጸለይ ማስተማር ብቻ ሳይሆን፥ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ ሲመላለስ በነበረ ጊዜ፥ እርሱ ራሱ ስለ ሌሎች በመጸለይና እግዚአብሔርን በማመስገን ጭምር መካለኛነቱን በተግባር አሳይቷል። ለለምሳሌ፡- ስለ ደቀ መዛሙርቱ (ማቴ. 11፥25)፥ በአልዓዛር መቃብር ላይ (ዮሐ. 11፥41-42) እግዚአብሔርን አመስግኗል። ብቻውን፥ አንዳንድ ጊዜም ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶችን ይዞ ጸልዮአል (ማቴ. 14፥23፤ 26፥36-46፤ ማር. 1፥35፤ ሉቃ. 9፥28፤ ዮሐ. 12፥28፤ 17፥1-26)።     

ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንዳንድ ክፍሎች መጸለዩ ብቻ ሲጠቀስ፥ በአንዳንዶቹ ክፍሎች ደግሞ የጸለየባቸው ርእሰ ጕዳዮችና የጸለያቸው ጸሎቶች ተመዝግበዋል። በዋናነት የሚጠቀሰው ጸሎቱ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ የሰፈረው ጸሎቱ ነው። ይህ የሊቀ ካህናትነቱ ጸሎት በአጠገቡ ለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በእነርሱ ስብከት መሠረት በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ የቀረበ የምልጃ ጸሎት ነው። “እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ … ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤” የሚለው ይህን ያመለክታል (ዮሐ. 17፥9፡20-21) ።

ሰይጣን ሐዋርያትን እንደ ስንዴ ሊያበጥራቸው በወደደ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለይ ለስምዖን ጴጥሮስ አማልዶ ነበር፤ ቃሉም “… እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ” ይላል (ሉቃ. 22፥31)። ጌቴ ሴማኒ በተባለች የአትክልት ስፍራም ተንበርክኮ ሲጸለይ፥ “አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ” (ማቴ. 26፥39-42)። በመጨረሻም ለሰቀሉት ሰዎች አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ሲል ወደ አባቱ ጸልዮላቸዋል (ሉቃ. 23፥34)።

ይህ ትክክል ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ወራት የተደረገ ነው እንጂ ከትንሣኤው በኋላ እርሱ መካከለኛ አይደለም የሚሉ አንዳንዶች ይኖራሉ። የክርክራቸው ግብም የመካከለኛነትን ግብር ከእርሱ ላይ አንሥቶ ለሌሎች መስጠት ነው። ለጊዜው ግን፥ እርሱን መካከለኛ ማለት ክብሩን ዝቅ ማድረግ ነው የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ ያቀርባሉ። ኢየሱስ በሥጋው ወራት የእርሱ ስለ ሆኑት በመጸለዩ ከአምላክነቱ ደረጃ ዝቅ ብሏል አያሰኝም። ‘አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ዛሬም መካከለኛችን እርሱ ብቻ ነው፤ ሌላ የሚተካው መካከለኛ የለም’ ማለትም ከክብሩ ዝቅ የሚያደርገው ሳይሆን፥ ትክክለኛ የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናትነቱን የሚያሳይ ነው። ከዚህ ዕትም በፊት በወጡት ተከታታይ ጽሑፎች ላይ እንደ ተጠቀሰውም፥ ሐዋርያት በመልእክቶቻቸው ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣና በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላም መካከለኛ መሆኑን መጻፋቸውን ገልጸናል።  

እስካሁን ለማስረዳት እንደ ተሞከረው፥ ኢየሱስ ምልጃንና ጸሎትን ያቀረበው በሥጋው ወራት ነው። በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በሥጋው ወራት ያደርግ እንደ ነበረው ይጸልያል ይለምናል ማለት አይቻልም። ነገር ግን በቀደመ ልመናውና ምልጃው ዘወትር በአዳኝነቱ አምነው በስሙ እየጸለዩ የሚመጡትን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርባቸውና የሚያድናቸው ግን እርሱ ብቻ ነው። “… እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” (ዕብ. 7፥25)። አንድን መሥዋዕት ለዘላለም እንዳቀረበና ያ አንድ ጊዜ የቀረበው መሥዋዕት ለዘላለም እንደሚያገለግልና ለኀጢአት ሁሉ የቀረበ መሆኑን ከተረዳን (ዕብ. 10፥12፡14)፥ ስለ ሁላችን አንድ ጊዜ ያቀረበው ምልጃም (ዮሐ. 17፥20-21) ለዘላለም እንደሚሠራ መረዳት አያዳግተንም። ይህን ወደ ጎን ጥለንና ለኢየሱስ ክብር የምንከራከር መስለን በእርሱ ስፍራ ሌሎች መካከለኞችን ለማስቀመጥ በማሰብ የክርስቶስን መካከለኛነት ማስተሐቀር (ማቃለል) ግን ትልቅ ስሕተት ነው። እግዚአብሔር የሾመልንን የታመነ፣ የሚምርና የሚራራ ሊቀ ካህናት ላለመቀበል መወሰናችንንም ያስረዳል።

“ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ ወደ ማን  ይማልዳል?”        
በቃላት መዋጋትን እንደ በሽተኛ የሚናፍቁ ወገኖች፥ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት በግልጽ የሚያስተምሩትን ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማስተባበል ሲያቅታቸው፥ በምስጢረ ሥላሴ ላይ ትልቅ ተፋልሶን የሚያስከትል መሠረተ ቢስ አመክንዮን ያቀርባሉ፤ እንዲህ በማለት፥ ‘ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው ወደ ማን ይማልዳል?’ እንዲህ ባዮቹ፥ ኢየሱስን ከመካከለኛነቱ ስፍራ ለማንሣት ሲሉ ይህን ጥያቄ እንደሚያነሡት ይታወቃል። በጥያቄያቸው ውስጥ ግን የሰባልዮስን ትምህርት ተቀብለው እያስተጋቡ መሆናቸውን የተገነዘቡ አይመስልም። ሰባልዮስ በሥሉስ አካላት እና በዋሕድ መለኮት የሚታወቀውን እግዚአብሔርን፥ አንድ አካል ነው በሚል ሦስትነቱን በአንድነቱ የሚጠቀልል ኑፋቄን ያስተማረ መናፍቅ ነው። ቤተ ክርስቲያን ኑፋቄውንም እርሱንም  በጉባኤ መርምራ አውግዛቸዋለች። ይሁን እንጂ በበር በኩል ያስወጣችው ኑፋቄ፥ ከዘመናት በኋላ በክርክር ሰበብ መልኩን ለውጦ ቅጥር እየጣሰ እና አጥር እያፈረሰ መግባቱ አልቀረም። ‘ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፤ ወደ ማን ይማልዳል?’ ማለት በውስጡ የእግዚአብሔርን ሦስትነት በአንድነት የመጠቅለል ሐሳብ ያለበት አገላለጽ ነው። የክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተባበል ሲባል የሚነሣው ይህ መከራከሪያ የሚያደርሰው ወደ ሰባልዮስ ትምህርት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።      

‘ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው ወደ ማን ይማልዳል?’ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ወደ አብ የሚል ይሆናል። ከፍ ብለን እንደ ተመለከትነው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አብን እለምናለሁ” ሲል ተናግሯል (ዮሐ. 14፥15)።

የክርስቶስን መካከለኛነት በተሳሳቱ ምድራውያን አመለካቶች ላይ መመሥረት የለብንም። አንዱ ምድራዊ አመለካከት የሚለምን የበታች፥ የሚለመን ደግሞ የበላይ ተደርጎ መወሰዱ ነው። ክርስቶስ አብን መለመኑ፥ አብ በክርስቶስ መለመኑ የበታችነትንና የበላይነትን አያሳይም። የእግዚአብሔርና የሰው ዕርቅ የተከናወነው በእግዚአብሔር ፍቅርና በጎ ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ ነው። ሰው እግዚአብሔርን ፈልጎትና ልታረቅህ ብሎት አማላጅም ልኮ ዕርቅ አልጠየቀውም። ወደ ገዛ መንገዱ ያዘነበለውንና በኀጢአቱ ምክንያት ሞት የተፈረደበትን ሰው ከራሱ ጋር ሊያስታርቅ የወደደው ራሱ እግዚአብሔር ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3፥16) በተባለው መሠረትም፥ በእርሱና በሰው መካከል ሊከናወን ስለሚገባው ዕርቅ አስታራቂ አድርጎ የላከውና ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታረቀው በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 5፥10፤ 2ቆሮ. 5፥18-19፤ ኤፌ. 2፥16)። ይህም የእግዚአብሔርና የሰው ዕርቅ በክርስቶስ ሞት ስለ ተከናወነ፥ ከዚህ በኋላ ከሰው የሚጠበቅ ሌላ የመታረቂያ መንገድ የለም፤ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን ተገንዝቦ፥ ንስሓ ገብቶና በክርስቶስ የተከናወነውን ዕርቅ አምኖ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ይችላል፤ “በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኤፌ. 2፥18)።      

አብ አማላጅ ተብሏልና ወደ ማን ይማልዳል?
የዚህ መከራከሪያ መነሻም ከላይ የተመለከትነው ዐይነት ምድራዊ አመለካከት ነው። የእግዚአብሔርና የሰው ዕርቅ በእግዚአብሔር ፍቅርና በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው ብለናል። ሰውን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ሲልም እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ልኳል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ እንደ ነበረም ተጽፏል፤ “ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን … ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤” (2ቆሮ. 5፥18፡19)። በዚህ ክፍል በግልጽ እንደ ተመለከተው፥ እግዚአብሔር ዓለሙን በክርስቶስ ያስታረቀው ከራሱ ጋር ነው። በምድራዊ አመለካከት ተይዘን የግድ ከእግዚአብሔር በላይ የሆነ ሌላ ታራቂ አካል መኖር አለበት ልንል አይገባም። በሰው ልምምድ ውስጥ በአብዛኛው እንደሚታየው አስታራቂ ሁለት የተጣሉ አካላትን ለማስታረቅ ጣልቃ የሚገባ ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን ከፍቅር የተነሣ፥ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆችም ከአባታቸው እንደ ተማሩት፥ ተበድለው ሳለ ራሳቸውን ከበደላቸው ሰው ጋር ያስታርቃሉ። እግዚአብሔርም የተበደለ እርሱ ሆኖ ሳለ ራሱ ክሶ ሰውን ከራሱ ጋር አስታርቆታል።

እነዚሁ ወገኖች “አብ አማላጅ ተብሏልና ወደ ማን ይማልዳል?” ሲሉ ለሚያነሡት ጕንጭ አልፋ ክርክር የሚያቀርቡት ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፥ “አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር” የሚለውን ነው (ኤር. 7፥25)።  በዚህ የእግዚአብሔር ንግግር ውስጥ “እየማለድሁ” የሚለው ቃል አብ አማላጅ መሆኑን ያሳያል የሚል ነው ክርክሩ። ይሁን እንጂ በዐማርኛ ማለደ የሚለው ቃል መለመንን ብቻ ሳይሆን በጥዋት መነሣትንም የሚያመለክት ቃል ነው (መዝ. 57፥8፤ መዝ. 108፥2፤ ማር. 1፥35፤ ሉቃ. 21፥38)። በትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 7 ቊጥር 25 ላይ የተጠቀሰው ቃል የሚናገረውም በማለዳ መነሣትን (ከጥንቱ ከጥዋቱ ጀምሮ መናገሩን) እንጂ ምልጃ ማቅረብን አይደለም። ከሚከተሉት የትንቢተ ኤርምያስ ክፍሎች ጋር ይህን ክፍል ብናስተያየውም ጕዳዩ በጥዋት መነሣትን እንጂ ምልጃን (ልመናን) ፈጽሞ አያሳይም (ኤር. 7፥3፤ 11፥3፤ 26፥5፤ 29፥19፤ 32፥33፤ 35፥14፡15፤ 44፥4)። ዐማርኛው “ማለደ” አሻሚነት ቢኖረው እንኳ፥ ሳያጣሩ “አብ አማላጅ ተብሏል” ከማለት በፊት ቃሉ በሌሎች ቋንቋዎች ምን እንደ ተባለ ማመሳከር ይገባ ነበር። ለምሳሌ፡- እንግሊዝኛው “… daily rising up early…” (KJV) ይላል። የግእዙም ትርጕም እንዲህ ነው የሚለው “አባቶቻቸው ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፤ በቀንና በሌሊት ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባቸው ነበር፤” (የ2000 ሺህ ዕትም) ሁለቱም በጥዋት መነሣትን ወይም ጊዜን እንጂ ምልጃን ወይም ልመናን አያሳዩም።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውን የራስን ሐሳብ በእግዚአብሔር ቃል ከማረም ከማስተካከል ይልቅ ቃሉን ለማጣመም መሞከር የእግዚአብሔር ሳይሆን የሰው አገልጋይ መሆን ነው፤ እውነተኛ ሰባኪ ግን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ ለማሰኘት አይሰብክም (ገላ. 1፥10)። አለአግባብ ተጠቅሶ በተሳሳተ መንገድ የተተረጐመው ይህ ጥቅስ ለተከራካሪዎቹ የማስተዛዘኛ ውጤት እንኳ እንዳላስገኘላቸው ግልጽ ነው።

“መንፈስ ቅዱስም ይማልዳል ተብሏልና ወደማን ይማልዳል?” 
“እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” (ሮሜ 8፥26-27)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን “ሌላ አጽናኝ” ሲል ጠርቶታል (ዮሐ. 14፥15-16፤ እንዲሁም ቊጥር 26፤ 15፥26፤ 16፥7ን ይመለከቷል)። ሌላ አጽናኝ ያለውም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገና በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ፥ እርሱን ተክቶ የሚሠራ፥ ማለትም፦ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚኖር፣ ሁሉን የሚያስተምርና ኢየሱስ የተናገረውን የሚያሳስብ፣ ስለ ኢየሱስ የሚመሰክር፣ ስለ ኀጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ዓለምን የሚወቅሥ ሌላው የሥላሴ አካል ነው።  ኢየሱስ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ አይመጣም ሲል፥ የሚመጣው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ፥ ከአብ የሚወጣ የሥላሴ አንዱ አካል መሆኑን ያስረዳል። ኢየሱስን ሊተካ የሚችል፥ እንደ እርሱ ያለ መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ ሌላ ፍጡር ሊሆን በፍጹም አይችልም።

ስለ ሌላ አጽናኝ የተናገረውም፥ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን ሲነግራቸው የደቀ መዛሙርቱ ልብ በሐዘን መታወኩን ተከትሎ ነው። በጊዜው በሥጋ ዐብሮአቸው የነበረውና ስፍራን ሊያዘጋጅላቸው ወደ ሰማይ የሚሄደው መምህራቸው ኢየሱስ በሥጋ ከእነርሱ ተለይቶ ከሄደ በኋላ ተመልሶ መጥቶ ወደ እርሱ እስኪወስዳቸው ድረስ፥ እንደ እርሱ ያለ ሌላ አጽናኝ እንደሚመጣ ነው የነገራቸው (ዮሐ. 14፥1-3፡13-17)። እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት የዮሐንስ ወንጌል ክፍሎች (ዮሐ. 14፥15-16፡26፤ 15፥26፤ 16፥7) “አጽናኝ” ተብሎ የተተረጐመው ቃል በግሪኩ “ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ነው። ጰራቅሊጦስ ማለትም፦ አማላጅ፣ ጠበቃ፣ አጽናኝ ማለት ነው። ቃሉ ለመንፈስ ቅዱስ ተቀጽሎ ስለሚገኝ መንፈስ ቅዱስ ስለ ቅዱሳን ይማልዳል የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን ዝቅ ማድረግ አይሆንም። ከላይ ስለ አብ በተናገርንበት ክፍል የተሰጠው ማብራሪያ እዚህ ላይ ለመንፈስ ቅዱስም ይሠራል።  ኢየሱስ በሥጋው ወራት ለደቀ መዛሙርቱ ይማልድ እንደ ነበረ፥ እርሱ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የወረደውና ከላይ የተዘረዘሩትን ታላላቅ መንፈሳውያን ተግባራትን ለቤተ ክርስቲያን እያከናወነ ያለው መንፈስ ቅዱስ፥ ቅዱሳንን (ምእመናንን) በድካማቸው ጊዜ ያግዛቸዋል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም ይማልድላቸዋል። ይህ እንዴት ባለ ሁኔታ ይከናወናል? ቢባል በቃላት መግለጽ በማይቻል መቃተት መሆኑን ቃሉ ያስረዳል።

ይሁን እንጂ የ200 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ፥ ይህን ሐሳብ ለውጦ ይማልዳል የሚለውን ይፈርዳል ሲል ጽፏል፡፡ ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣ የአንድ ወገን የአተረጓጐም ባህል ነው። የግእዙ ንባብ ከሚለው ውጪም የተሰጠ ትርጓሜ ነው። በቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት አንድምታ ትርጓሜ ላይ ግን “ይከራከራል” ተባለ እንጂ “ይፈርዳል” አልተባለም። እነዚህ ክፍሎች ግን ከእግዚአብሔር ሐሳብ ይልቅ ለትርጓሜ ባህላቸው ሲሉ፥ “ወባሕቱ መንፈስ ለሊሁ ይትዋቀሥ ለነ በእንተ ሕማምነ ወምንዳቤነ - ነገር ግን ራሱ መንፈስ ቅዱስ ራሱ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይከራከርልናል” (ሮሜ 8፥26) የሚለውን “ይፈርዳል” ሲሉ ተርጕመዉታል። ይሁን እንጂ በዚህ የጳውሎስ መልእክት ላይ ተመሥትረው ሌሎች መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ እንደሚጸልይ መስክረዋል። አረጋዊ መንፈሳዊ በተባለ የመነኮሳት መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተጽፏል፤ “ወባሕቱ አጸምዖ ለመንፈስ ዘኅዱር ላዕሌየ ወአስተሔውዝ ኪያሁ ዝ ውእቱ ዘተብህለ ከመ መንፈሱ ይጼሊ በእንቲኣነ - ነገር ግን በእኔ ዐድሮ የሚኖረውን የመንፈስ ቅዱስን ነገር ብቻ እሰማለሁ፤  በእርሱም አደንቃለሁ፤ ይህ ‘መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ይጸልያል’ የተባለው ነገር ነው።” (አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን 13)።

   ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 42 ላይ የቀረበ

1 comment: