የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
ከነቅዐ ጥበብ
ፍሬምናጦስ በሐዋርያዊ ስብከቱ ለመሠረታት ለማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ካከናወናቸው ዐበይት
ሥራዎች ጥቂቱን ባለፉት ዕትሞች ተመልክተናል፡፡ በረጅም ዓመታት ጕዞ ውስጥ የሚታዩና የማይታዩ መሰናክሎችን ዐልፋ ከእኛ ዘንድ በደረሰችው
የእግዚአብሔር መንግሥት ምክንያት ባለውለታችን የሆነው ሐዋርያ በአሁኑ ጊዜ ስንት የሥራው መታሰቢያዎች በስሙ ተመዝግበው እንደሚገኙ
በተጠየቅን ጊዜ እኛም ጠይቀን የተሰጠንን መልስ ለጠያቂዎቻችን ነግረናል፡፡ ሆኖም አላረካቸውም፡፡ ጠያቂዎቹ ከትምህርት ተቋማት፥
ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፥ ከመሰብሰቢያዎች (አደባባዮች) ከሐውልቶች፥ ከመንገዶች… ጥቂቱ ስሙ የሚጠራባቸውና ሥራው የሚታሰብባቸው
ቢሆኑ አይበዛበትም ባዮች ናቸው፡፡ አሁን ግን የዚህኑ የደገኛውን ሐዋርያ ሥራ መግለጹን እንቀጥላለን፡፡
ስምንተኛ - ኤጲስ ቆጶስ መሾም
የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነቱንና ጌትነቱን ለአይሁድም ለአረማውያንም
ከሰበከ በኋላ፥ አማኞችን አሰባስቦ “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በሚል መጠሪያ ክርስቲያናዊ ድርጅቱን እንዳቋቋመ፥ በኋላም ከምእመናን
መካከል በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በመሠረተው ትምህርተ ሃይማኖት የላቀ ዕውቀት ያላቸውን እንደየጸጋ ስጦታቸው ዲያቆናት፥ ጸሐፍት፥ ቀሳውስት
በሚል የሥራ ደረጃ እንደ መደበ ተመልክተን ነበር፡፡
ፍሬምናጦስ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የበሰለ
ዕውቀት የነበረውን እንበረምን ክርስቲያን ሲያደርገው ሕዝበ - ቀድስ ብሎት እንደ ነበረ በኋላም ኤጲስ ቆጶስ አድርጎ እንደ ሾመው
በታሪከ ነገሥትና በገድለ ተክለ ሃይማኖት ተርኳል፡፡ ሕዝበ ቀድስም በሀገሪቱ ውስጥ እየተዘዋወረ፥ የኖባና ሳባን፥ የናግራንና የትግሬን፥
የአማራና የአንጎትን የቀጣን፥ የዝበግዱርን ሕዝብ እንዳስተማረም ተጽፏል፡፡
የወንጌልን ስርጭት እንደዚህ ካስፋፋና የማኅበረ ጽዮን ሰማያዊትን
የሥራ አመራር አማክሎና አጠናክሮ ካቋቋመ በኋላ የአንዲት ሀገራዊት ቤተ ክርስቲያንን ህልውና እውን አደረገ፡፡ ለክርስትና መሠረት
የሆኑትን ቅዱሳት መጻሕፍት ከሀገሪቱ ሊቃውንት ጋር ወደ ግእዝ ተረጐመ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ሥራዎች በመላዋ ኢትዮጵያ ለማስፋፋትና
ለመዘርጋት ላቀደው የክርስትና እምነትና ትምህርት የተጠናከሩ የመሠረት ድንጋዮችን በጥልቀት እንደ መትከል የሚቈጠሩ ነበሩ፡፡
ዘጠነኛ- ትምህርተ እምነትን ግልጽና ጥልቅ ማድረግ
ፍሬምናጦስ እስከዚህ ድረስ የተገለጸውንና ያልተገለጸውን ሁሉ
በትጋት በማጠናቀቅ ሳይወሰን የክርስትና መሠረተ እምነት ወደ ምእመናን ልብ ጠልቆ ይገባ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ የግሪኮችን
ፍልስፍና ተከታታይ የነበሩት አረማውያንና የብሉይ ኪዳን ዕውቀት የነበራቸው አይሁድ የጌታ ኢየሱስን መሲሕነቱንና (ከርስቶስነቱን)
የእግዚአብሔር ልጅነቱን ከመረዳት ያግዷቸዋል ወይም ያሰናክሏቸዋል የተባሉት ዐጥሮች ሁሉ ተወግደው፥ ወደ ሙሉ መረዳት እንዲደርሱ
ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ከተከታታይ ክሥተቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
የክርስትና መነሻውም መድረሻውም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ
ግልጽ ነው (ዕብ. 12፥2)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን የተሰጡ ተስፋዎችንና የተነገሩ ትንቢቶችን አሟልቶ ለመፈጸም
በመሲሕነት በሥጋ የተገለጸ ወልደ እግዚአብሔር ነውና፡፡ መሲሕ በብሉይ ኪዳን እንዴት ያሉ ተስፋዎችና ትንቢቶች ማእከል ሆኖና የሰዎችን
ልብና ናፍቆት አገናኝቶ በመያዝ እንዴት እንደ ቈየ ማወቅና መገለጡንም ከሐዲስ ኪዳን አስተምህሮት ጋር አገናዝቦ የእውነቱን መጀመሪያና
መጨረሻ መጨበጥ እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡ ወደዚህም እውነት ለመድረስ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተነሥቶ ወደ ሐዲስ ኪዳን መዝለቅ
ያስፈልጋል፡፡ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡
1. በትንቢተ ኢሳይያስ 7፥14 “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች” ከሚለው
ቢነሡ፥ ትንቢቱ የተፈጸመበትን ታሪክ ከማቴዎስ 1፥18-25 ማንበብ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት የምትፀንሰው ድንግል ናትና ያለ ዘርዐ
ብእሲ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚወለደውም ወንድ ልጅ ነውና ኢየሱስ ሲወለድ እንደ ትንቢቱ ተፈጽሟል ወደ ምስጢሩ ሲገባም፡-
- “ዐማኑኤል” መባሉ “አምላክ ከሰው ጋር” ወይም “አምላክ ሰው” ማለትን ለመግለጽ ከሆነ ከድንግል የሚወለደው ሰውን የሚወክል
ሰው መሆን ያለበትን ያኽል፥ በመለኮታዊ አካልና ህላዌ የሚታወቅ አምላክ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ በመሆኑም ከድንግል
የተወለደው ኢየሱስ እንደ አምላክ አምላክ፥ እንደ እኛ እንደ ሰዎችም ሰው ሆኖ በአንድ አካላዊ ህላዌ ስለ ተገለጸ ዐማኑኤል ለመባል
ብቃትና ተገቢነት ኖረው ማለት ነው፡፡ አባቶችም ኅቡረ ህላዌ ምስለ አብ በመለኮቱ፥ ወኅቡረ ህላዌ ምስሌነ በትስብእቱ “ከአብ ጋር
በመለኮቱ፥ ሰው በመሆኑም ከእኛ ጋር የአኗኗርና ባሕርይ አንድነት አለው” ያሉት ይህንኑ ለመግለጽ ነው፡፡
- የተወለደው ፍጡር መልአክ ቢሆን ኖሮ ትንቢቱ ተፈጸመ ማለት በተቻለ ነበር፡፡ እንዲሁም መልአክ ሰው “መባል ነበረበት
እንጂ ዐማኑኤል ሊባል ባልተገባ ነበር፡፡ ግን ዐማኑኤል ስለ ተባለ “አምላክ - ሰው መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ የዚህም እውነት በኢሳይያስ
9፥6 ከተለጹት ሌሎች ስሞቹ ጋር ሲገናዘብ ይበልጥ ጐልቶ ይገኛል፡፡
- “ኀያል አምላክ” የተፈጠረ ያይደለ እውነተኛ ባሕርያዊ አምላክ 1ዮሐንስ 5፥20 “የዘላለም አባት” አወጣጡ ከጥንት ከዘላለም
ነው (ሚክ. 5፥2) በሚለው የተረጋጠጠና፥ ወልደ አብ ዋሕድ ሆኖ እያለ በአብ ህልው ስለሆነ እንዲሁም የአብ የሆነው ሁሉ የእርሱም
ነውና (ዮሐ. 16፥15) በዘላለም አባትነት የመጠራት መብት ያለው ነው፡፡
- “የሰላም አለቃ” ይሆዋ ሻሎም - የሰላም ጌታ የሰላም ምንጭ በራሱ ሰላም ነውና ሰዎችን ከራሱ ጋር ከእርስ በርስም ጋር
የሚያስታርቅ የሚያስተራርቅ ነው (መሳ. 6፥23-24፤ ኤፌ. 2፥13-15)፡፡
- እንግዲህ መሲሕ (ክርስቶስ) ሲባል፥ ከዚህ በላይ ለምሳሌ የተገለጹትን የሚመስሉ ብዙ መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት
በብሉይ ኪዳን እውነተኛ አማኞች ዘንድ ሲጠበቅ የነበረ መሆኑ እሙን ነው (ዮሐ. 7፥31፡40-46)፡፡
2.
አሁንም አንድ ሌላ ምሳሌ እናክልበት፤ ፊልጶስ ስለ ኢየሱስ
ከርስቶስ ለናትናኤል መሰከረለት (ዮሐ. 1፥46-50)፡፡ ሙሴና ነቢያት የጻፉለትን “አግኝተነዋል” ብሎ ናትናኤልም ቢጠራጠር፥ አንተው
ራስህ ወደርሱ መጥተህ አረጋገግጥ አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደርሱ የመጣውን ናትናኤልን “ፊልጰስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች
ሳለህ አየሁህ” በማለት ጥርጣሬውን የሚያስወግድበት የብርሃን ጮራ በልቡ
ላይ ፈነጠቀበት፡፡ ከዚያ በኋላ፡-
- “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” አለው፡፡ አወጣጡ ከጥንት ከዘላለም ነው በተባለው መሠረት ልደቱ ተብሎ በሚተረጐመውና
በቃልነቱ ከዊን ከልብ በሚወጣ ፀአቱ (አወጣጡ) ምክንያት የእግዚአብሔር ልጅ ሊባል ተገቢው መሆኑን መሰከረ፡፡
- “የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው፡፡ በሥጋና በመንፈስ እስራኤል ላይ ሥልጣነ መንግሥቱን ያሰፍን ዘንድ በሥጋ ከነገደ ይሁዳ
ከዳዊት ቤት እንዲወለድ ሲጠበቅ የቈየ ፍጹም ሰው እንደ ሆነ ተናገረ (ዘፍ. 49፥8-10፤ ኢሳ. 11፥1-2፤ ኤር. 23፥5-6፤
ሉቃ. 1፥31-33)፡፡
እንግዲህ የተስፋውንና የትንቢቱን
ቃል በመንፈስ ያስተዋሉና ስለ ፍጻሜው ተግተው ይጠባበቁ የነበሩት ሁሉ ስለ መሲሕ የነበራቸው ግንዛቤ ይህን ይመስል ነበር ማለት
ይቻላል፡፡ አዎን መሲሕ ለመባል የእግዚአብሔር ልጅ፥ ኀያል አምላክ፥ እንደ ገና የሰው ልጅ መሆንን የሟሟላት ትንቢታዊ ግዴታ ሆኖ
በነቢያት የተነገረው የምስጢሩ ቍልፍ መክፈቻ ነው፡፡
በማኅበረ ጽዮን ሰማያዊትም የታቀፉት የፍሬምናጦስ ደቀ መዛሙርት
(ከአይሁድም ከአሕዛብም በስብከቱ የተጠሩት ማለት ነው) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን፥ በትንቢትና በተስፋው ቃል አስቀድሞ
የተነገረውንና ከተፈጸመ በኋላ በሐዲስ ኪዳን የተሰበከውን በማገናዘብ የቀሠሙት ዕውቀት ወደ ጐንና ወደ ላይ በማደግ፥ ስፋቱንና ቁመቱን
ያሳየ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁን ሥርንና መሠረትን ለማጥበቅ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጠ - ምስጢር ጠልቆ በመግባትና በማስተዋል
የተደገፈ የማይናወጥ መሠረተ እምነት ነበረው፡፡ ይህን የተባለበትን ምክንያት በሚቀጥሉት ክፍሎች ከተገለጸው መገንዘብ ይቻላል፡፡
ዐሥረኛ - ዓለም ዐቀፋዊ የእምነት እንቅስቃሴዎችን መከታተል
ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ያቋቋማትን የእግዚአብሔር መንግሥት ዙሪያዋን
በባሕር እንደ ተከበበች ደሴት አላስመሰላትም፡፡ ከክልሏ ውጪ የሚካሄደውን የወንጌል አገልግሎትና በተቃዋሚነት እንደ ዐውሎ ነፋስ
(አውራቂስ ሐ.ሥ. 27፥14) እየሆነ ይነሣ የነበረውን ኑፋቄና ክሕደት የማትከታተል በዋሻ ውስጥ ያለች ዝግ ቤት አላደረጋትም፡፡
ቀደም ሲል ክርስትና በተስፋፋባቸውና የነገረ መለኮት ትምህርት
ቤቶች በነበሯቸው በእስክንድርያና በአንጾኪያ፥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ይታዩባቸው በነበሩት በሌሎች ከተሞች፥ ማለት በቍስጥንጥንያ፥
በኤፌሶን፥ በሮም ይነፍስ የነበረውን ሽውታ ማኅበረ ጽዮን በንቃትና በጥንቃቄ ትከታተል ነበር፡፡ በየከተማው የታዩትን ዐረሞች አበቃቀል፥
ዐረሞቹን ለመንቀል የተደረጉትን ጥረቶች እየተከታተሉ በማጥናትና ለምእመናን በማስጠናት ለማናቸውም ተጋድሎና ለሚከፈለው መሥዋዕት
ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ይደረግ ነበር፡፡
ከሣቴ ብርሃን ፍሬምናጦስ ስብከተ ወንጌልን በኢትዮጵያ አውራጃዎች
እንዲሠራጭ በሚያደርግበት፥ የማኅበረ ጽዮን ሰማያዊትን ሥርዐት ባለው ሁኔታ በሚያደራጅበት፥ ለድርጅታዊ ሥራዋና ለወንጌል አገልግሎቷ
በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን በመደልደል፥ በየአቅጣጨው የሚካኼደውን የሥራ እንቅስቃሴ ኺደት በሚከታተልበት ጊዜ በአርዮስ
ትምህርት መወገዝ ምክንያት የእስክንድርያና የባሕር ማዶ አብያተ ክርስቲያናት ሁከት ደርሶባቸው እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲል
318 አባቶች በኒቅያ ተሰብስበውና የግራ ቀኙን ሐሳቦች፥ ክርክሮችና ያቀረቧቸውን ማስረጃዎች በእግዚአብሔር ቃል መርምረው አርዮስን
ከነትምህርቱ ከቤተ ክርስቲያን እንዲገለል ካደረጉ በኋላ፥ የተስማሙበትን የእምነት መግለጫ በዚያው ጊዜ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ዐሥራ አንደኛ - ማኅበረ ጽዮን በአርዮስ ትምህርት ላይ
የወሰደቸው ቈራጥ የውሳኔ ርምጃ
በኒቅያ ጉባኤ የተቀመጡት አባቶች ያወጡትን የእምነት መግለጫ ይዘት የኢትዮጵያ
ምእመናን ተቀብለው፥ እግዚአብሔር በሰጣቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ ነጻነት እግዚአብሔርን እያመለኩና እያከበሩ ክርስቲያናዊ ሕይወትን እያጣጣሙ
ይኖሩ በነበረበት ጊዜ ማኅበረ ጽዮንን በሚመለከት አንድ ሁኔታ በድንገት ተከሠተ፡፡ መደቡ በቍስጥንጥንያ ሆኖ መላውን የሮምን የቄሣርን
መንግሥት በተደላደለ ሁኔታ ሲመራ የነበረው ቈስጠንጢኖስ (324-337) ሲሞትና ልጁ ቍንስጣ በሥልጣነ መንግሥቱ ተተክቶ ሲገዛ
(337-361) በኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ ተቀባዮች ላይ ድንገተኛ ችግር ተፈጠረ፡፡
ቍንስጣ (ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ ይባላል) በሥልጣኑ ከተደላደለ በኋላ ቀደም
ሲል አርዮስን ለማስታረቅና ወደ ሥራው እንዲመለስ ለማድረግ አባቱ ጀምሮት የነበረውን ሙከራ በሥልጣኑ ከግብ ለማድረስ ወስኖ ተነሣ፡፡
ከአርዮስ ጋር ባለው የግል ወዳጅነትና ራሱም አርዮሳዊ በመሆኑ አርዮስ ወደ ቀድሞ ሥራው እንዲመለስ ወስኖ ለእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት
ለአትናቴዎስ አስታወቀ፡፡ በማያገባው የሥልጣን ክልል (ማለት በሃይማኖት አባቶች ጉባኤ) የተወሰነውን በመሻሩ አትናቴዎስ ዐዝኖ ውሳኔውን
አልቀበልም፤ አሻፈረኝ አለ፡፡
ቄሣር ቍንስጣ የሊቀ ጳጳሱ አልታዘዝም ባይነት ሥልጣኑን እንደ መቃወም ሆኖ
ስለ ተሰማው አትናቴዎስን ከሥልጣን አግልሎ በምትኩ አርዮሳዊውን አባ ጊዮርጊስን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሾመው፡፡ ዐዲሱን
ተሿሚም ምእመናኑ አንቀበልም ሲሉ በወታደር ኀይል በመንበሩ አስቀመጠው፡፡
ጉዳዩ በዚህ ቢወሰን ኖሮ የኢትዮጵያ ምእመናንን የሚመለከት ነገር ባልኖረ
ነበር፡፡ በቀጣይ ዓመታት ሁሉ የተለያየ እምነትን በተከተሉ የሮማ ቄሣሮች መለዋወጥና እነርሱም ሃይማኖትን በተመለከተ በሚፈጽሙት
ጣልቃ ገብነት ምክንያት ይፈጠር የነበረ ችግር በማይደርስባት የራሷ ሉዓላዊ መንግሥት በነበራት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመችውን ቤተ
ክርስቲያን ፈታኝ ሁኔታ አጋጠመ፡፡ በቍስጥንጥንያ የነበሩ የመንግሥት መሪዎች ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር የነበራቸው የንግድና የባህል
መለዋወጥ የፈጠረውን ወዳጅነት ምርኵዝ በማድረግ በአባ አትናቴዎስ የተሾመው ፍሬምናጦስ ከሥልጣኑ እንዲወርድና አርዮሳዊ ቴዎፍሎስ
በመንበሩ እንዲቀመጥ ቍንስጣ በደብዳቤ አብርሃና አጽብሓን ጠየቀ፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ቃልም ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
“ቪክቶሪዩስ ኮንስታንስዮስ ማክሲሙስ አውግስጦስ ለአይዛናና
ለሳይዛና (አብርሃና አጽብሓ)
እግዚአብሔር
የሰጠን ትምህርትና ማስተዋል ለሁሉም እውነትንና ጽድቅን ለሚፈልግ ሁሉ እንዲዳረስ ስመኝ በናንተና በሮማውያንም ቤተ ክርስቲያን መካከል
አንድነት እንዲኖር ይገባል፡፡
ከሹመቱ
የተሻረው ብዙ ሺሕ ክስ ቀርቦበት መመለስ ያቃተው አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን ሾሞ ልኳልና በቶሎ ፍሬምናጦስን መልሳችሁ ለተከበረው ጳጳስ
ለጊዮርጊስ በዚያም ላሉ ቀሳውስት ላኩትና የርሱን ነገር እነሱ ይጨርሱት፡፡ የአባ አትናቴዎስን ሥራ ግን ከናንተ በቀር አገር ሁሉ
ዐውቆ አላስጠጋ ስላለው በናንተ ዘንድ መጠጊያ ይፈልጋል፡፡
ፍሬምናጦስ
ከልቡ ጳጳስ መሆን ከፈለገ የሕይወቱን ታሪክ ለቀሳውስቱ ገልጾ የቤተ ክህነትን ሕግና ሥርዐት በደንብ ፈጻሚ መሆኑ በነዚያ ዘንድ
ከታወቀ ተመልሶ እንደ ሕጉ ጳጳስ መሆን ይችላል፡፡ ያለዚያ እንደ አትናቴዎስ እንደ ለፍላፊው … ከሕግ የሚሸሽ ሆኖ ወደ አክሱም
የመጣና ሹመቱን የያዘ እንደ ሆነ እናንተንም ቤተ ክርስቲያናችሁንም እንዳያበላሽና ሁከት እንዳይፈጥር ያስፈራል፡፡ … እኔ ግን እንደሚመስለኝ
ፍሬምናጦስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ በጣም ከከበረው ጳጳስ ከጊዮርጊስና ከፍ ካሉት ሊቃውንት ተገናኝቶ የቤተ ክህነትን ሕግና ትምህርት
ከተረዳ በኋላ ወደ ጵጵስና ስፍራው ሊመለስ ይችላል፡፡
በጣም
የተከበራችሁ ወንድሞቼ ሆይ እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ፡፡”
ደብዳቤው የተጻፈበት ቀን አልተለየም፡፡ ከ360 ዓ.ም. ትንሽ ቀደም ብሎ
መሆኑን ኮንቲሮሲኒ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚባለው መጽሐፍ 150 ገጽ ላይ ይጽፋል፡፡ እስከዚህ ያለው ከኢትዮጵያ ታሪክ 1ኛ መጽሐፍ
(ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኵሪያ ከጻፉት) ገጽ 310 የተወሰደ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 24 እና 25 ይህንኑ አውጥተዉታል፡፡
የደብዳቤው ይዘት ሲታይ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሮም ቄሣሮች ተጽዕኖ
የማይደርስባት ሀገር ስለ ነበረች ደብዳቤው የሚያባብልና የሚያግባባ መልእክት ወይም ማሳሰቢያ የያዘ ነበረ፡፡ ስለ አርዮስና ትምህርቱ
ቀደም ብሎ በተረዱት በኢትዮጵያ ነገሥታትና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘንድ የቄሣሩ ደብዳቤ ተቀባይነትን አላገኝም፡፡ በማኅበረ ጽዮን
ትምህርት ላይም አንዳች ለውጥ ከቶ አላመጣም፡፡
ገና በማደግና በመጠንከር ላይ በነበረችበት በዚያን ጊዜ ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት
ለአርዮስ የኑፋቄ ትምህርትና ለቄሣሩ የማግባቢያ ደብዳቤ እጅ ሳትሰጥ የመቅረትዋ ታሪክ የእግዚአብሔር የጥበቃ ሥራ እንዳለበት የሚያሳምን
ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የአርዮስን አተላ ትምህርት ብትቀበል ኖሮ እስከ አሁን ድረስ የሚያሳዝን ዕድል በገጠማትና በምስጢረ ሥሳሴና
በምስጢረ ሥጋዌ ከእውነተኛ ትምህርት ውጪ በሆነ መንገድ እየባዘነች ለመኖር ትገደድ ነበር፡፡
ለምሳሌ፥ በሮም ቄሣር ውስጥ የነበሩት
አብያተ ክርስቲያናት ታላቁ ቈስጠንጢኖስ (324-337) ከሞተ በኋላ የአርዮሳውያን ደጋፊ የነበረው ልጁ ቍንስጣ በዙፋኑ ሲተካ እነ
አትናቴዎስ ሐዋርያዊውን የመሳሰሉ አበው ከመንበራቸው ተሰደዱ፡፡ የኒቅያን እምነት መግለጫ የተቀበሉ የቤተ ክርስቲያን አበው ትምህርተ
እምነታቸው ሙሉ በሙሉ የተደገፈላቸውና መብታቸው የተመለሰላቸው በታላቁ ቴዎዶስዮስ (379-395) ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡
ከቍንስጣ እስከ ታላቁ ቴዎዶስዮስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ብዙ
አብያተ ክርስቲያናት በሮም ቄሣር ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው፥ ትምህርተ እምነታቸው ከቄሣሮች መለዋወጥ ጋር ዐብሮ ሲወድቅና ሲነሣ
ታየ፡፡ ኢትዮጵያ ግን የራሷ ሉዓላዊ መንግሥት ስለ ነበራት የሮም ቄሣሮች ተጽዕኖ አያሠጋትም ነበርና የአርዮስ ትምህርት አንድ ጊዜ
ገብቶ ቢሆን ኖሮ በሚቀጥለው ቄሣር ተጽዕኖ የመውጣት ዕድል ሊያጋጥመው አይችልም ነበረ፡፡ ማኅበረ ጽዮን በመሪዎችዋና ክርስቲያኖች
በነበሩት ነገሥታቷ ብርታት ከቄሣር ቍንስጣ የተላከውን መልእክት ያልተቀበለችበትና በፍሬምናጦስ ምትክ መንፈሳዊ መሪዋ እንዲሆን ተልኮ
የመጣውን ሕንዳዊ ቴዎፍሎስን አሳፍራ የመለሰችበት ዐይነተኛ ምክንያት ከሮማ ቄሣሮች ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መንግሥት ጥላ ሥር ስለ ነበረች
መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በዚያን ጊዜ አርዮሳዊውን ትምህርት አለመቀበልዋ
ጠቀማት እንጂ፥ ተቀብላው ቢሆን ኖሮ በነጻ መንግሥት ሥር መገኘቷ ሊጐዳት በቻለ ነበር የሚያሰኝ ምክንያት አለ፡፡ ይኸውም በኋላ
እንደ ገና በታላቁ ቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግሥት ፈጽሞ የተወገዘውን
ኑፋቄ አርዮስን ከምእመናኗ አእምሮ አስለቅቆ በምትኩ ታድሶ የጸናውን የኒቅያን የእምነት መግለጫ ማኅበረ ጽዮን እንድትቀበል ለማድረግ
ዕድሉ የመነመነ በሆነ ነበር፡፡ የቄሣሮችን ተጽዕኖ በማትፈራበት ሁኔታ በነበረችበት ጊዜ ኑፋቄ አርዮስ አንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ቢገባ
ኖሮ፥ ከሮም ቄሣር አገዛዝ በታች በነበሩት ሀገሮች እንደ ሆነው ሁሉ በሮም ቄሣሮች ኀይል ማስወጣት ባልተቻለ ነበር፡፡
ስለዚህ በደገኛው ሐዋርያዋና መሪዋ በፍሬምናጦስ ብርታትና አርቆ
አስተዋይነት ቀደም ብላ የኒቅያን የእምነት መግለጫ መቀበልዋ፥ በኋላም በለሰለሰ መንገድ በአታላይነት ሊገባ የሞከረውን አርዮሳዊ
ኑፋቄና መልእክተኛውን ቴዎፍሎስ ሕንዳዊ በመጡበት እግራቸው መመለሷ፥ ትምህርተ መለኮቷን ወደ ፊት በመልካም ጐዳና ለመምራት ያስቻላትን
ዕድልና ጸጋ እግዚአብሔር በቸርነቱ እንደ ሰጣት ያረጋግጣልና ታላቁን የእግዚአብሔርን ስም ደግመን ደጋግመን እንባርካለን፡፡
በዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በቅዱሳት መጻሕፍት
አተረጓጐም የታዩትን ክሥተቶች፥ ጠንካራና ደካማ ጐኖቻቸውን፥ ገንቢና አፍራሽ ተልእኮዎቻቸውን
ለመከታተል የማኅበረ ጽዮን መሪዎችና ምእመናን የተከፈቱ ጆሮዎች ስለ ነበሯቸው፥ በአርዮስ ትምህርት ላይ የተወሰደውን የማግለል ርምጃም
በቅድሚያ ተረድተዉትና ደግፈዉት ነበረ፡፡ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም የተሰጣቸውና የተቀበሉት የቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት በእምነታቸው
የሚያጸና፥ በማናቸውም የኑፋቄ ነፋሳትና ማዕበላት ከመናወጥና ከመወሰድ የሚጠብቅ ስለ ሆነ (ኤፌ. 4፥14-16) ኑፋቄ አርዮስን
መርምረው እነርሱም በበኩላቸው ከልባቸው ወግደዉት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይህን መንፈሳዊ ቅንዐት የሚያነሣሣ የአባቶችን ታሪክ የተመለከተ
ማንኛውም ሰው ጥንታውያን አባቶች ገና በሽታው ክርፋቱንና ኰምጣጣነቱን ዐውቀው ወደ ሀገር ሳያስገቡ ከውጪ የደፉትን የአርዮስ አተላ
ዘመነኛው ሰው ዶሮ ማታ፥ ዶሮ ማታ እየተባለ ዐይኑን ጨፍኖ ሲጋተው በሚታይበት ጊዜ በእውነት የእነዚያ አባቶች ዝርያ መሆኑን ለማመን
ይከብዳል፡፡ የደፉትን አተላ የሚልስ ትውልድ መፈጠሩን እነዚያ አባቶች ቀና ብለው ቢያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን?
ዐሥራ ኹለተኛ - ማኅበረ ጽዮን በመለኮት አሐድነት ታምናለች
በፍሬምናጦስ ሐዋርያነት የሚመሩትና በማኅበረ ጽዮን የታቀፉት ምእመናን የአርዮስን
ኑፋቄ የተጸየፉበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር በአካላት ሦስት፥ በመለኮት ግን አንድ ነው
የሚለው የምስጢረ ሥላሴ ቊልፍ መግለጫ ባልተማረውም በተማረውም መነገሩ በምእመናን ልብ በጥልቀት የሠረጸ መሆኑን ይጠቍማል፡፡ በአካላትና
በኩነታት፥ ለእነዚህም ተገቢ በሆኑ ስሞች በመጠራት ምክንያት መለያያት ሳይኖር የሥላሴ በመለኮት አንድ መሆን መሠረቱ ኩነት እንደ
ሆነ በአብዛኛው አማኝ ይታወቃል፡፡ ሦስት ልብ፤ ሦስት ቃል ሦስት ሕይወት ቢኖር ኖሮ፥ አንዱ በሌላው ህልው የመሆን መብትና ግዴታ
ባልኖረ፥ አንድ ህላዌ መለኮትም ባልተገኘ ነበር፡፡ የመለኮት አሐድነት አለ ቢባል እንኳ የስምምነት አንድነት እንጂ ባሕርያዊና ዘላለማዊ ሆኖ ባልተገኘ ነበር፡፡ አንዱ በሌሎቹ ህልው እንዲሆን የባሕርያዊና የመለኮታዊ መብትን መኖር ያስገኘ
“ኩነት” ነውና፡፡ ለሥላሴ መለኮት አሐድነት፥ መሠረቱ፥ እንዲሁም በጊዜና በክብር ላለመቀዳደምና ላለመበላለጥ ምንጩ ኩነት ነው፡፡
እግዚአብሔር በጊዜና በክብር መቀዳደምና መበላለጥ በማይኖራቸው
በለባዊነት፥ በነባቢነት፥ በሕያውነት በሚታወቁት ሦስት ኩነቶች ለኩነቶቹም ባለቤቶች በሆኑት በሦስት አካላት ራሱን ገልጿል፡፡ በኩነታትና
በአካላት እኩልነት (እሪና) መኖሩንም እያመለከተ በመለኮት አሐድነት ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን አባቶች ቀደም ብሎ የተቀበሉትን
የኒቅያን እምነት መግለጫ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሲያገናዝቡት “ወልድ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ (ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ)”
የመባልን ተገቢነት ተቀብለዉት ቈዩ፡፡
አርዮስ ግን ቀደም ብሎ የአብ ባሕርያዊ ቃል ወልድን የተፈጠረ
ቃል አስመስሎ አስተማረ፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ፍጥረታትን ፈጠረ ሲባል እየተናገረበት ያልነበሩትን ፍጥረታት በትእዛዝ ወደ መሆንና
መኖር ማምጣቱን ማስተዋል ተሳነው፡፡ ቃልን ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕርይ ውጪ የሆነ በእግዚአብሔር እንደ ተሠራ የፍጥረታት ማምረቻ
መሣሪያ ገመተው፡፡ “እርሱ ተናገረ፤ እነርሱም ሆኑ፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ የለም፡፡” የተባሉትንና
የመሳሰሉትን ጥቅሶች አጣጥሞ ለመረዳት ፈቃደኛነቱን አላሳየም፡፡ አብ ከባሕርያዊ ቃሉ ከወልድ እንዲሁም ከባሕርያዊ ሕይወቱ ከመንፈስ
ቅዱስ ይበልጣል ማለት ለባዊነት ከነባቢነትና ከሕያውነት ይበልጣል፤ ሕያውነትም ከለባዊነትና ከነባቢነት ያንሳል እንደ ማለት ነው፡፡
ለመሆኑ ሕያውነት የሌለበት ለባዊነትና ነባቢነት አለን? የለባዊነትስ መኖር ያለነባቢነትና ሕያውነት ሊኖርም ሊታወቅም ይችላልን?
ለሰላማ ደቀ መዛሙት ይህ አባባል በቀላሉ የሚስተዋል ስለ ነበረ፥
የአርዮስን ትምህርት ይዞ የመጣውን ዐዲሱን ተሿሚ አባ ቴዎፍሎስን በመጣበት እግሩ መለሱት፡፡ የ20ኛው ምእተ ዓመት ትውልድ እስኪነሣለት
ድረስ አርዮስ በኢትዮጵያ ስሙን የሚያስጠራለት እንኳን ሰው ውሻም አልነበረውም፡፡ የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን እንባርከዋለን፡፡
ለስሙም ለመንግሥቱም ታላቅነትና ገናናነት ውዳሴን እናቀርባለን፡፡
የኒቅያን የእምነት መግለጫ ያዘጋጁት አባቶች ስለ ወልድ በሚናገሩበት
ክፍል፥ “ወልድ ከአብ ጋር በመለኮቱ አንድ ነው” ያሉትን በሀገራችን ጸሎተ ሃይማኖት በተባለው እምነት መግለጫ ላይ “በመለኮቱ ከአብ
ጋር እኩል ነው ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ” ብለዉታል፡፡ እንዲህ የተባለውም ከመቼ ጀምሮ እንደ ሆነ አይታወቅም፡፡ በኒቅያ ጉባኤ
የአብ፥ የወልድ፥ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት አንድ ነው ተባለ እንጂ እኩል ነው አልተባለም፡፡ ሦስት መለኮት ቢኖር “እኩል ነው” ማለት
በተቻለ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የአካል ሦስትነት ሲኖር የመለኮት ሦስትነት ፈጽሞ የለም፡፡ እኩልነት በሦስትነት ለሚታወቁ አካላት ቢነገር
ይስማማል እንጂ በቍጥር አንድ (አሐዱ) ነው ለተባለው የሥላሴ መለኮት ግን ዋሕድ መባል እንጂ ዕሩይ መባል ተስማሚው አይደለም፡፡
በሀገራችን ሦስት መለኮት፥ ማለት የአብ መለኮት፥ የወልድ መለኮት፥
የመንፈስ ቅዱስ መለኮት እያሉ መለኮትን እንደ አካላት ሦስት አድርገው ለሚያስተምሩ “የ3 መለኮት ባህል አስተማሪዎች” ሁኔታዎችን
ለማመቻቸት በማቀድ “ወልድ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ነው (ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ)” በሚል አገላለጽ ተዘጋጅቶ የወጣውን
መግለጫ በመለወጥ “ወልድ በመለኮቱ ከአብ ጋር እኩል ነው፤ (ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ) ብለዉት ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡
የኒቅያን በመለወጥ የወጣው የዐዲስ ባህለ ሃይማኖት መግለጫ ነው፡፡ የሚገርመው ግን በአሁኑ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ የሚደገመው ይኸው
የ3 መለኮት ባህል እምነት መግለጫ መሆኑ ነው፡፡
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment