Tuesday, April 22, 2014

ክርስትና በኢትዮጵያ

የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ

Read In PDF

ዐሥራ ሦስተኛ - የፍሬምናጦስ ሌሎች ሥራዎች

በፍሬምናጦስ ትጋት፥ በኢትዮጵያ በተቋቋመችው የእግዚአብሔር መንግሥት ወይም ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ውስጥ በዘመኑ ከተፈጸሙት ድንቅ ሥራዎች መካከል ሳይመዘገቡ የታለፉ፥ ተመዝግበው ከነበሩትም በቅብብሎሽ (በትውፊት) እንኳ ዘመናትን አቋርጠው ከእኛ ዘንድ ሳይደርሱ ከጊዜ ርዝመትም ከሁኔታዎች መለዋወጥም የተነሣ በዘመናት እርከናት ላይ እየወደቁ የተረሱና እንዳልነበሩ የሚቈጠሩ እጅግ ጠቃሚ የሥራ ውጤቶች በብዛት ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ የሚታወሱት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት እንደ ሆኑ ይታመናል፡፡

1.    መካሪ፥ አበ ነፍስ፥ ወይም አበ ንስሓ መመደብ

በኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለው ሕዝብ እንደ ማንኛውም ሌላ ሕዝብ ኑሮው የተመሠረተበትን የዕለት ተዕለት ሥራ የእደ ጥበብ፥ የግብርናና የንግድ ሥራን ለመከታተል ያመቸው ዘንድ ቦታ እየመረጠ ተበታትኖ የሰፈረ በመሆኑ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንደ ነበራቸው እንደዚያ ጊዜ ዲያቆናት፥ ቀሳውስት፥ ጸሐፍት… ትምህርተ እምነታቸውን ለማሳደግ ሁኔታው ያላመቻቸው ክርስቲያኖች፥ ብዙኃን እንደ ነበሩ በእግረ ልቡና ወደ ኋላ ተመልሶ ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደ አኹኑ በየሰው እጅ የሚገቡበት ዕድል አልነበረም፡፡ የማንበብና የመጻፍም ችሎታ የጥቂት ሰዎች መታደል ብቻ ሆኖ ይቈጠር ነበር፡፡ በእነዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ ከምሁራኑ መካከል በየመንደሩና በየቀበሌው መካሪና አስተማሪ አድርጎ መመደብ ጊዜያዊ መፍትሔ ሆኖ ተገኘ፡፡

መካሪና አስተማሪ የሆነው ምሁር ክርስቲያን ከሚፈጽመው የወንጌል ማዳረስ አገልግሎት ሌላ፥ በየቤቱ ለቤተ ሰቡ አባላት፥ በየመንደሩም ለመንደሩ ነዋሪዎች የቀለም ትምህርትና የሃይማኖት ትምህርት እያስተማረ፥ በክርስትና ሕይወታቸው ለሚያጋጥማቸው ችግርም ምክር በማካፈል ምእመናንን ያንጽ ነበር፡፡ ስለ አንዳንድ ጕዳይ ጥያቄ የነበረው ምእመንም ወደ አማካሪው (አስተማሪው) በመኼድ እየተረዳ መንፈሳዊ ሕይወቱን ያሳድግ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

መካሪና አስተማሪ ለመሆን ብቃት ያለው መሆኑ እየታመነበት ሊመደብበት በታቀደው የሥራ መደብ መመደብ የተጀመረው ከመቼ ጀምሮ እንደ ሆነ አልታወቀም፡፡ እያደርም መካሪና አስተማሪ የተባለው ሰው የሰውን ነፍስ በሚመለከት ኀላፊ፥ ዋስ፥ ጠበቃ እንደ ሆነ ያኽል ተቈጠረና አበ ነፍስ አበ ንስሓ ተባለ፡፡ ወንጌልንም የማይሰብክ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ሰውን የማይመክር፥ የማይገሥፅ፥ የማስተማር ችሎታም የሌለው ሆነ፡፡

አኹንማ የግል መካሪና አስተማሪ (አበ ንስሓ፥ አበ ነፍስ) መኖር የክርስቲያን ግዴታ ሆኖ ተቈጠረ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው፥ መምህራንን አሠልጥነው የሚመርቁና የሚያስመርቁ ሊቃውንት ሳይቀሩ ተማሪዎቻቸው ለመሆን እንኳ ብቃት የሌላቸውን የፊደል ሰዎች ለነፍሳቸው ዋስ፥ ጠበቃ አድርገው መቀበል ግዴታቸው ተደረገ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይኑር ከተባለም መካሪና አበ ነፍስ ነን የሚሉት ለራሳቸው አበ ነፍስ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ሊቃውንቱ ለእነዚህም ለሕዝቡም አበ ነፍስ ሆነው ቢያስተምሩና፥ ቢመክሩ፥ ቢገሥፁም ማለት መሪና ተመሪ የሥራ ዝውውር ቢደረግላቸው እንዴት ባማረ?

አበ ንስሓ (አበ ነፍስ) ጾም ሲገባና ሲፈታ በዓመት አንድ ጊዜ ለሻሽና ለልብስ መግዣ ገንዘብ አበ ነፍስ ካደረገው ከእያንዳንዱ ሰው የመቀበል መብት አለው፡፡ አበ ነፍስ (አበ ንስሐ) የሌለው ሰው ቢሞት የመቀበር መብት የለውም፡፡

በአብ ቀኝ ተቀምጦ የሚማልድላቸውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመንፈስ ዐይን የሚመለከቱ ምእመናን ግን፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ አስመ አበ ነፍስየ አንተ፤ በሎሙ ላመላእክት ተፈሥሑ ሊተ፤ ረከብክዎ ለወልድየ በከንቱ ዘሞተ (ኢየሱስ ክርስቶስ! የነፍስ አባቴ አንተ ነህና መላእክትን፥ በከንቱ ሞቶ (ጠፍቶ) የነበረውን ልጄን አግኝቼዋለሁና፤ ተደሰቱልኝ (የደስታዬ ተካፋይ ሁኑ) በላቸው፡፡” (/ሉቃ. 15፥3-24/መልክአ ኢየሱስ) እያሉ ተገልለው በአሠራሩ መበላሸት ሲያዝኑ ኖሩ፡፡ በመሠረቱ መካሪና አስተማሪ መመደብ ማለት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን መንጋን የመጠበቅን ኀላፊነት በቅዱሳት መጻሕፍት የጠለቀ ዕውቀት ላላቸው መምህራን አከፋፍሎ በግልና በቡድን ማሠራት ማለት ነበረ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ በተገለጸበት ቀን ጴጥሮስን እንዲህ አለው፡- የምትወደኝ ከሆነ ግልገሎቼን መግብ፥ ጠቦቶቼን ጠብቅ፥ በጎቼን መግብ እያለ ኀላፊነትን በዐደራ ሰጠው፡፡ ጴጥሮስ የሞተለትን ጌታውን የሚወድ ከሆነ ብቻ የበጎቹን የጠባቂነትና የመጋቢነት አገልግሎት በዐደራ መቀበል ነበረበት (ዮሐ. 21፥15-17)፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጧት የጸጋ ስጦታዎች መከከል አንዱ እረኛነት ነው፡፡ ሥራው በዝርዝር ሲገለጽ፥ አስተዳዳሪነት፥ መሪነት፥ መጋቢነት፥ ጠባቂነት … ነው (ሐ.ሥ. 20፥28፤ ኤፌ. 4፥11)፡፡

በቤተ ክርስቲያን የእረኛነት ሥራ የተሰማራው ጴጥሮስም እንደርሱ መንጋውን የመጠበቅና የመመገብ ዐደራ ለተቀበሉ እረኞች ሲጽፍ፥ የሁሉም እረኞች አለቃ (ሊቀ ኖሎት) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጽበት ጊዜ የክብር አክሊል ለመቀበል እንድትበቁ፥

-   ረብ (ሥጋዊ ጥቅም) ለማግኘት ባለማቀድ
-   በግድ ሳይሆን በፍቅር በማስተዳደር፥
-   ምሳሌ በመሆን፥ መንጋውን ጠብቁ በማለት አሳሰበ (1ጴጥ. 5፥1-4)፡፡

በዘመነ ብሉይ ኪዳን የሥጋ እስራኤል የእግዚአብሔር መንጋ ነበረ (መዝ. 74፥1-2፤ 79፥13፤ 80፥1፤ 95፥7)፡፡ አሁንም በዘመነ ሐዲስ ኪዳን የመንፈስ እስራኤል የእግዚአብሔር መንጋ ነው (ዮሐ. 10፥16፤ ሐ.ሥ. 20፥28)፡፡ ለጥቅም ብሎ ሳይሆን ፍቅር ከሆነው መለኮታዊ ባሕርዩና በፈጣሪነቱ ካለበት ኀላፊነት የተነሣ እግዚአብሔር የመንጋው እረኛ ነው፡፡ ለመንጋው ያስባል፥ ይጠነቀቅለታል (መዝ. 23 እና 121፤ ዮሐ. 10፥1)፡፡

ሊቀ ኖሎቱ በጸጋ ስጦታ እየሸለመ ቅጥረኛ እረኞችን በጥበቃና በመግቦት ሥራ ላይ ይመድባል፡፡ ሆኖም በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ቅጥረኛ እረኞች ለተቀበሉት ዐደራ ብቁ ሆነው ባለመገኘታቸው ሲወቅሣቸው ኖረ፤ አሁንም ቃሉ ሕያው ስለሆነ እየወቀሠ ነው (ኤር. 23፥1-4፤ ሕዝ. 34፥2-31)፡፡

ሀ. ቅጥረኛ እረኞች በበጎች ላይ ያደረሱት በደል
1.      በጎችን በማሰማራት ፈንታ በለመለመው መስክ ራሳቸውን አሰማሩ
2.     በኀላፊነትና በዐደራ ስለ ተሰጧቸው በጎች ራሳቸውን ከሚሰጡላቸው ይልቅ እነርሱው ራሳቸው በጎችን እያረዱ በሉ
3.     በሕይወት ካሉትም ጠጕራቸውን እየሸለቱ ለበሱት፤ ለብርድም አጋለጧቸው፤
4.     ደካማዎቹን በጎች አላጽናኗቸውም፤
5.     ታማሚዎቹን በጎች አላከሟቸውም፤
6.    ሰባራዎቹን አልጠገኗቸውም፤
7.     መንገድ ተሳስተው የጠፉትን በጎች ወደ መንጋው በመመለስ ፈንታ በተኗቸው፤
8.     የጠፉትን ፈልገው አላገኟቸውምና ለምድር አራዊት መብል ሆኑ፤ የተረፉትም ተቅበዘበዙ ፈላጊም አልነበራቸውም፤
9.    የተረፉትንም በኀይል በማስገደድ፥ በጭቈና ገዟቸው፡፡

እረኞች የተጣለባቸውን መንጋውን የመጠበቅና የመንከባከብ ኀላፊነት ከትከሻቸው አውርደው ወረወሩ፡፡ እረኞች ይህን የመሰለውን በደል ሲፈጽሙ የሰቡ፥ የደነደኑ በጎችም በከሱና በገረጡ በጎች ላይ ያልተጠበቀ ጕዳት አደረሱ፡፡ ረብ ፈላጊ ከሆኑ ቅጥረኛ እረኞች ጋር በመመሳጠር ጥቅም ተካፋይም በመሆን ራሳቸውን አድልበዋል፡፡ በየአጥቢያው መንፈስ ቅዱስ ሳይሾማቸው ራሳቸውን የመንጋው እረኞች ላደረጉ አስመሳዮች መንጋውን ለማስገዛትና ለማስበላት እርስ በርስ በመመራረጥ መንጋው የሚበዘበዝበትን ሥርዐት አደራጁ፡፡ አንድ ለእኔ፥ ሁለት ላንተ በማለት መንጋውን ካዱ፡፡ እግዚአብሔር የእነዚህንም በደል ተመልክቶታል፡፡

ለ. የደለቡ በጎች በከሱ በጎች ላይ ያደረሱት በደል
1.      የከሱትን በጎች በአፍንጫቸውና በትከሻቸው እየገፉ ከመንጋው አስወጧቸው፤
2.     በቀንዳቸው እየወጉ ጐዷቸው፤
3.     እየተሸቀዳደሙ ራሳቸውን ሊመግቡ፥ የተረፋቸውን ምግብ ምስኪኖቹ በጎች እንዳይመገቡት በእግራቸው ረጋገጡባቸው፤ አበላሹባቸው፤
4.     ውሃውን በቅድሚያ መጠጣታቸው አንሶ ተራፊውን የተጠሙት ምስኪኖች በጎች እንዳይጠጡት በእግራቸው አደፈረሱባቸው፡፡

እግዚአብሔር ስለ መንጋው የማይገደው መስሏቸው ቅጥረኞቹ እረኞችና ድልቦቹ በጎች በምስኪኖቹ የመንጋው አባላት (በጎች) ላይ ጕዳት አደረሱ፡፡ የመንጋው ባለቤት በቅጥረኛ እረኞችና በደለቡ በጎች ላይ ሊፈርድ ተነሣ፡፡

ሐ. ፍርድ በቅጠረኞች እረኞች ላይ
1.      የጠፉትን (የተጐዱትን) በጎች ከእጃችሁ እፈልጋለሁ፤
2.     በጎቼን ከማሰማራት አስተዋችኋለሁ (ቅጥራችሁን እሠርዛለሁ)፤
3.     በጎቼን ከጕዳት እታደጋቸዋለሁ፤
4.     በጎቼን ከመበላት አድናቸዋለሁ፤
“ጌታ ይመስገን”

መ. ፍርድ በደለቡ በጎች ላይ
1.      የደለበውን በግ ከመንጋዬ እለየዋለሁ፤
2.     አጠፋዋለሁ፤
3.     እፈርድበታለሁ፤

“ጌታ! በግህ ነውና በምሕረትህ እየው፡፡”

ሠ. ተስፋ ለተጐዱ በጐች
1.      በጎቼን እኔ ራሴ እሰበስባለሁ፤
2.     ጨለማንና ጉምን ተገን አድርገው ከሚባሉ አራዊት አድናቸዋለሁ፤
3.     በተራሮች፥ በፈሳሾች፥ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤
4.     ማደሪያቸውን (ጕረኖአቸውን) በተራሮች ላይ አደርጋለሁ፤
5.     የጠፉትን እፈልጋለሁ፤
6.    የባዘነውን እመልሳለሁ፤
7.     የተሰበረውን እጠግናለሁ፤
8.     የደከመውን አበረታለሁ፡፡
              ሃሌ ሉያ!

ረ. ስለ መካሪ (አበ ነፍስ፥ አበ ንስሓ ) የተሳሳተ ትምህርት

በብሉይ ኪዳን ለምጽ በሽታ ይዞኛል ብሎ የተጠራጠረው ሰው ወደ ካህን ቀርቦ መታየት ነበረበት፡፡ ካህኑ በታማሚው ሰው ቆዳ ላይ የታየውን ነገር በምልክት ይከበውና ከኅብረተ ሰቡ ተገልሎ እንዲቈይ፥ ከተወሰኑ ቀናት በኋላም እንዲመለስ ያዘው ነበር፡፡ በየቀጠሮውም ምልክት የተደረገበትን ቆዳ እየተመለከተ ታይቶ የነበረው ነገር ጠፍቶ፥ ወይም ሰፍቶ እንደ ሆነ ይመረምራል፡፡ በምልክት የተከበበው ነገር ከጠፋ፥ ለምጽ አይደለምና ወይም ድኗልና ወደ ኅብረተ ሰቡ የመመለስ ፈቃድ ይሰጠዋል፤ በቅድሚያ ግን በሕግ የታዘዘውን ቊርባንና መሥዋዕት ለእግዚአብሔር እንዲያቀርብ ያደርጋል፡፡ ዳሩ ግን በቆዳው ላይ የወጣው ነገር ከተደረገበት ምልክት ውጪ እየሰፋ መኼዱን ካህኑ ከተረዳ፤ ሰውየውም ለምጻም ነውና እስኪድን ወይም እስኪሞት ድረስ ከኅብረተ ሰብ ተለይቶ እንዲቀመጥ ያዘዋል (ዘሌ. 13 እና 14 ይመልከቱ)፡፡

በእንደዚህ ያለ የለምጽ ደዌ ምክንያት ከኅብረተ ሰብ ተለይቶ የነበረ ሰው አንድ ቀን በመንገድ ላይ ጌታ ኢየሱስን ተገናኝቶ ያነጻው ዘንድ እንደ ለመነው ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ለምጻሙን በቃሉ አነጻው፤ ወደ ኅብረተ ሰቡ ይቀላቀል ዘንድም ካህኑ መርምሮ እስኪያረጋግጥ ቊርባንና መሥዋዕቱን ያቀርብ ዘንድ ነገረው፡፡ “ኺድና ራስህን በካህን አስመርምርና ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ (ሑር ወአፍትን ርእሰከ ለካህን ወአብዕ መባዐከ)” አለው (ማቴ. 8፥1-4፤ ማር. 1፥40-44፤ ሉቃ. 5፥12-14)፡፡ ስለ አበ ንስሓ የሚናገር ክፍል አይደለም፡፡

      ሰ. ስለ ኑዛዜና ቅጣት

ኑዛዜ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ነው (ምሳ. 28፥13፤ 1ዮሐ. 1፥7-10፤ ያዕ. 5፥16)፡፡ እርስ በርስ ተናዘዙ አንዱ ለሌላው ይጸልይለት ሲባል እኔ አናዛዥ ነኝ እንጂ ተናዛዥ አይደለሁም የሚል እንዳይኖር ቃሉ፥ “ኀጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ስለሚል ኑዛዜው ሁሉንም የሚመለከት ነው፡፡

እጅጉን የሚያሳዝነው አሠራር ለእያንዳንዱ የኀጢአት ዐይነት በመጽሐፈ ቀኖናና በሌሎቹም ተመሳሳይ መጽሐፎች ቅጣት መወሰኑ ነው፡፡ ተናዛዡ ኀጢአቱ ሊያስከፍለው የሚችለውን ቅጣት በመጽሐፈ ቀኖና እንደ ታዘዘው ራሱ በመቀጣት እንዲከፍል የሚደረግበት ሥርዐት ኢ ክርስቲያናዊ ነው፡፡

እግዚአብሔር የሁላችንን ኀጢአት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጭኖአል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ በግ ሆኖ ተሠውቷል፡፡ በዚህ መሥዋዕት ያልተሸፈነ ኀጢአተኛ የለም፡፡ በዚህም መሥዋዕት ያልተሰረየ ኀጢአት የለም (ኢሳ. 53 እና ዮሐ. 1፥29)፡፡

ሰው ሁሉ የራሱን ኀጢአት እየተሸከመ ቅጣቱን ይክፈል ከተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሠቃየ? ለምንስ ሞተ? አንድ መዝሙር እንዲህ ይላል፡-
“ኀጢአትህ ባንተ ላይ የቀረ ቢሆን (ኖሮ)
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተገረፈ?
የተቀደሰ ደሙም ባይከፍል ዕዳህን
ከጐኑስ ለምን ጐረፈ?
(ይልቅስ) እይ፥ እይ፥ እይና ዳን
የተሰቀለውን ኢየሱስን፥
በእምነት ብታይ ይሆንልሃል ሙሉ መዳን፡፡”

ደግሞም ሰው የኀጢአቴን ቅጣት ራሴ እቀበላለሁ ካለ፥ የጊዜውንና የዘላለሙን ፍርድ ከእግዚአብሔር ይቀበላል እንጂ የምን መቀለድ ነው? (ዳን. 12፥2፤ ማቴ. 25፥46፤ ዮሐ. 5፥29)፡፡

በለበቅ፥ በቅጠል በቸብቸብ የኀጢአት ቅጣት ሊከፈል? ስግደት በአምልኮት ሥርዐት ውስጥ ለእግዚአብሔር መገዛታችንን መዋረዳችንን እንገልጽበታለን እንጂ የኀጢአት ዕዳ የሚከፈልበት ቅጣት አይሆንም፡፡ የጦም መዋል ማደር ዐላማ ሌላ ነው እንጂ የኀጢአትን ዕዳ አይከፍልም፡፡ በገንዘብ መቀጫም የኀጢአት ዕዳ አይከፈልም፡፡ ለመሆኑ ስርየትን ይቸረችር ዘንድ በጅምላ የገዛ ነጋዴ የትኛው ነው? እግዚአብሔር ይገሥጽህ! በክርስቶስ ደም አትቀልድ አንተ ሰይጣን፡፡

የንስሓን ጕዳይ በቦታው መናገር ያስፈልጋል እንጂ፣ ንስሓ ባለፈው መጸጸትና ያለፈውን ነገር ትቶ ወደ ነበሩበት የእግዚብሔር ጸጋ መመለስ ነው፡፡ የኀጢአትን ዕዳ በራስ ድካም፥ በራስ ገንዘብ ለመክፈል ከእግዚአብሔር ጸጋ የሚወጣበት ሥርዐት አይደለም፡፡ “ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፥ ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፤ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናልና” (1ዮሐ. 1፥7-10)፡፡


እንግዲህ ወደ ታሪኩ ስንመለስ፥ በአባ ሰላማ ዘመን እንደ ተደነባ ከሚቈጠረው የመካሪና አስተማሪ (አበ ነፍስ፥ አበ ንስሓ) ሥርዐት መልካም፥ መልካም የሆነው ሁሉ ከዘመን ብዛት ጠፍቶ ለዐይነት የተረፈው ተናዛዡን፥ “እግዚአብሔር ይፍታህ” የሚለው ብቻ ነው፡፡ “ወዳጄ እኔ አልችልም፥ ዐይንህን ከአገልጋዮች ላይ አንሣና ወደ እግዚአብሔር አቅና፥ እግዚአብሔር ይፍታህ” ይባላል (ዕብ. 3፥1)፡፡

በጮራ ቊጥር 8 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment