Thursday, May 1, 2014

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

Read in PDF:- Aleka nekeatebebe
አለቃ ነቅዐ ጥበብና አገልግሎታቸው

ከነቅዐ ጥበብ

የአለቃ ነቅዐ ጥበብ አገልግሎት ከእልፍኛቸው ከወጣ ሰንብቷል፡፡ የወንጌል አገልግሎታቸው ለቤተ ሰብ ብቻ መሆኑ ቀርቶ የአካባቢውን ኅብረተ ሰብ የሚያቅፍ ሆኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን፥ በገበያ፥ በዕድር ስብሰባ፥ በልዩ ልዩ ሸንጎ ሁሉ የአለቃ ነቅዐ ጥበብ አገልግሎት ዜና ተስፋፍቶ ይወራል፡፡ “ጠበል ይረጫሉን?” አይ የለም የሰውን ውስጣዊ አካል ማየ ሕይወት በሆነ በእግዚአብሔር ቃል ይረጫሉ፥ ያጥባሉ እንጂ!” የሚለው ጥያቄና መልስ ከሕዝብ ለሕዝብ ሆኗል፡፡

“ኤጭ! ከአያት፥ ከቅድም አያት የወረስነውን ባህለ ሃይማኖታችንንና አድባራችንን፥ አውሌያችንን፥ ጨሌያችንን… አስማምተን ይዘን እንደ ቈየን መቀጠል ይበጃል እንጂ ከሰልባጅ ጋር የመጣ መጽሐፍ ቅዱስ አያዋጣንም” አለ ተቈርቋሪ መሳዩ የደብተራ ምንተስኖት ልጅ፡፡

“እንዴ! ብለህ፥ ብለህ ፈረንጆች ሳይቀበሉ የተቀበልነው ቅዱሱን መጽሐፍና ክርስቲያናዊ ታሪካችንን ትሸጠው?” ይለዋል ሁለተኛ፡፡
ሦስተኛውም በተራው እንዲህ ይላል፥ “በግእዝ ይነገር የነበረው በዐማርኛ ተተርጕሞ ከመጻፉ በስተቀር መጽሐፉ ያው የነበረው የኛው ነው፡፡” ሲል፣

አራተኛው ሰው “እውነትህን ነው ግእዝ እኮ የአምላክ ቋንቋ ነው እየተባለ ስንት ዘመን ተታለልን? እኛ የአምላክን ቋንቋ አላወቅን፤ ወይ አምላክ የኛን ቋንቋ አላወቀ፤ በሰይጣን መሠሪነት ከአምላካችን ተለይተን፤ እውነትን እንዳናውቅ ተደርገን ስንት ዓመታት አለፉ? አሁን ግን እነሆ! በልባችን ውስጥ ብርሃን ይሁን ያለው ራሱ እግዚአብሔር ነውና የተቀጣጠለው ሰደድ እሳት ኀይሉና ክበቡ እየጨመረ ይኼዳል፤ አንዲት የጨለማ ቁራጭ እንኳን በአካባቢያችን፥ በሀገራችን እንዳትኖር እስኪያደርግ ድረስ ሰደዱ ይቀጥላል፡፡ እኛም ከእንግዲህ ወዲያ በብርሃን እንኖራለን፤ እንመላለሳለን፤ እንሠራልን እንጂ ለጨለማና ለሠራዊቱ ጋት የምታኽል ስፍራ ላለመስጠት በአምላካችን ስም ቃል እንገባለን፡፡” ብሎ ሲናገር አብዛኛዎቹ ሰሚዎች “አሜን፤ እግዚአብሔር ይርዳን” አሉ፡፡ ጥቂቶቹ ግን ቃል ሳይተነፍሱ አቀረቀሩ፡፡

የአምልኮት ጊዜ

በአለቃ ነቅዐ ጥበብ አገልግሎት ዙሪያ የተሰበሰቡ ምእመናን የሚመሯቸውንና የሚያስተባብሯቸውን ከመረጡ በኋላ አዳራሽ አሠርተዋል፡፡ ለመምህራንና ለምእመናን መቀመጫዎች በአዳራሹ ውስጥ በሥነ ሥርዐት ተደርድረዋል፡፡ ለተጋበዙ እንግዶች በማሕሌት ለሚያገለግሉ መዘምራንና ለዜማ መሣሪያዎቻቸው ስፍራዎች ተለይተዋል፡፡

ለዚህ ዕለት የተመደቡ አስተናባሪዎች ምእመናኑንና ተጋባዦችን ሁሉ በየተመደበላቸው ስፍራ ካስቀመጡ በኋላ፥ ዲያቆን ምስግና የፕሮግራሙን ቅደም ተከተል አስታወቀ፡፡
ከመክፈቻው ጸሎት በኋላም መዘምራን ቆመው እግዚአብሔርን በዜማ አመሰገኑ እንዲህም አሉ፤-
ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ፥ ለፈለሰፈ፤
የምድርን ባዶነት ለሞላ፥ በላይዋም ለሰፈፈ፤
ብርሃን ይሁን ብሎ ጨለማን ለገፈፈ፤
ምስጋናዬ ይኸው ከልቤ ተረፈ፤ ሃሌ ሉያ

የታለ ጨለማው ምድርን የሸፈነው?
የታለ ቀላዩ የብሱን የሰወረው?
የታለ ጠፈሩ ብርሃን(ን) የጋረደው?
አምላኬ በቃሉ በኀይሉ አስወገደው፡፡ ሃሌ ሉያ፡፡

ክረምቱ አበቃ ዐለፈ ጭጋጉ፡፡
በምድር ሁሉ ላይ አበቦች ፈገጉ፤
መዐዛው ዐወደ፥ ፍሬዎች ጐመሩ፤
የሰማይ የምድርም ፍጥረታት ዘመሩ፡፡ ሃሌ ሉያ

የታለ ጨለማው …

ዝማሬው በከበሮ፥ በጸናጽል፥ በሌሎችም መሣሪያዎች በእልልታና በሽብሸባ ታጅቦ ሲዘመር፥ አንዱ ሰው ለጓደኛ “በመዝሙር 150 ባልተጠቀሱ መሣሪያዎች ጭምር ማገልገል አልነበረባቸውም እንጂ፤ በዝማሬውስ ልቤ ተነክቷል” አለው፡፡ ጓደኛውም መልሶ “አይ ወዳጄ! በያሬዳዊ ሥርዐተ ማሕሌት ውስጥ ዝማሜ አንዱ እንደሆነ ታውቃለህ፤ ለዚህ መገልገያው መሣሪያ ዘንግ (መቋሚያ) እንደ ሆነ አላስተዋልኸውምን? መሣሪያው በመዝሙር ውስጥ ባይጠቀስም ኢትዮጵያዊው ያሬድ ተጠቅሞበታል፡፡ ታዲያ ተሳስቷል ማለትህ ነውን? በአካባቢው በሚገኙ ማናቸውም መሣሪያዎች ማሕሌተ እግዚአብሔርን ማድረስ ይቻላል፡፡ እባካችሁ! እግዚአብሔርን አንወስነው፡፡” አለው፡፡

ዝማሬው እንዳበቃ ለመልእክት አቅራቢው ለመምህር እንግዳሸት ስፍራው ተለቀቀ፡፡ እርሳቸውም ከ1ኛ ጴጥሮስ 1፥18-21 ያለውን አነበቡ፡፡ “ስለ መዋጀት ወይም ስለ መቤዠት ዛሬ ከእግዚአብሔር ቃል እንማራለን” በማለት ጀመሩና ትምህርቱን ይበልጥ ለመረዳት ወደ ኦሪት ዘሌዋውያን 25፥24-54 በመሻገር ማንበብና ማገናዘብ አስፈላጊ እንደ ሆነ ገለጹ፡፡

“እስራኤላውያን ሲደኸዩ ርስታቸውን ቢሸጡና ኢዮቤልዩ (ከየ49 ዓመት ቀጥሎ የሚከበረው 50ኛው ዓመት) ከመድረሱ በፊት ሻጮች ገንዘብ ቢያገኙ የተሸጠውን ርስታቸውን በመግዛት እንደገና የራሳቸው ማድረግ እንዲችሉ ሕጉ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡ ይህም ርስትን የመቤዠት ወይም ቤዛ በመክፈል መልሶ የራስ የማድረግ ሥርዐት ሊባል ይችላል (ዘሌ. 25፥24-28)” አሉና ቀጠሉ፡፡

“እንዲሁም አንዱ እስራኤላዊ በምድረ እስራኤል ነዋሪ ለሆነ፥ ነገር ግን በዘሩ እስራኤላዊ ላልሆነ ሰው ራሱን ለባርነት ቢሸጥ፥ ከዘመዶቹ አንዱ ቤዛ በመክፈል እንዲቤዠውና የባዕድ ባሪያ ከመሆን ነጻ እንዲያወጣው ታዟል፡፡ ነጻ የወጣው እስራኤላዊም ገንዘብ አግኝቶ ራሱን ፍጹም ነጻ እስከሚያደርግበት ወይም ኢዮቤልዩ አስከሚከበርበት ዓመት ድረስ ብቻ ነጻ ላወጣው እስራኤላዊ ሎሌ ሆኖ ያገልግል” ተብሎ መደንገጉን አስረዱ (ዘሌ. 25፥47-54)፡፡

አያይዘውም እስራኤላዊው ከአሕዛብ ወገን ባሪያ ቢገዛ ባሪያው ለዘላለም ገንዘቡ ሆኖ እንዲኖር፥ ሲሞትም ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ በውርስ እንዲተላለፍ የድንጋጌው ከፍል መፍቀዱን ጠቀሱ (ዘሌ. 25፥44-46)፡፡

በመቀጠልም “ከመቶ ዓመታት በፊት ሲሠራበት የነበረው ሰውን ባሪያ አድርጎ የመግዛትና የመሸጥ ሥርዐት እንዴት እንደ ነበረ የሚተርከውን የዓለማችንን ታሪክ ስናገላብጥ፥ በችግር ምክንያት ራሱን በሸጠው ወይም በጦርነት ተማርኮም ሆኖ ታፍኖ ነጻነቱን ባጣው ሰው በጕልበቱ በዕውቀቱም ሆነ በሀብቱ እንዲያውም በልጆቹና በልጅ ልጆቹ የመጠቀም መብት ያለው የባሪያ ጌታ የነበረው ሰው ነበረ፡፡ ከንብረቱ እንደ አንዱ ሊሸጠው፥ በሌላ ንብረት ሊለውጠው ይችል ነበረ፡፡ ሥርዐቱ በጊዜው የተሠራበት ቢሆንም በአሳፋሪነቱ ወደር የሌለው ዘግናኝ፥ ትውስታው የማይጠፋ የታሪክ ጠባሳ ነው” በማለት ተረኩ፡፡ ባሪያው በራሱ ነጻ ሊወጣ ይችልበት የነበረ መንገድ ጠባብ እንደ ነበረ፥ ቢኰበልል እንኳ የማን ባሪያ ለመሆኑ ታትሞበታልና በማኅተሙ ተይዞ ምን ጊዜም የጌታው ንብረት ወደ መሆን ይመለስ እንደ ነበር አስገነዘቡ፡፡ በመቀጠልም ራሱን በመሸጥ ወይም በግዴታ ባሪያ ስለ ሆነው ሰው ዋጋ ይሆን ዘንድ ማንኛውም ነጻ ሰው ቤዛ (ዎጆ) ለባሪያው የከፈለለት እንደ ሆነ ነጻ ሊወጣ ይችል እንደ ነበረ መምህር እንግዳሸት ጠቈሙ፡፡

የአድማጮቻቸውን ልብ ወደ ዕለቱ ምንባብ ፍሬ ነገር ሲመልሱም እንዲህ አሉ፡፡ በነጻነት ተፈጥረው በዔድን ገነት የነበሩት ወላጆቻችን ሰይጣንን ለመታዘዝ በወሰኑ ጊዜ ነጻነታቸውን ዐጥተው በምርጫቸው የሰይጣን ባሪያዎች ሆኑ፡፡ ፈቃዳቸው፥ ጕልበታቸው፥ ዕውቀታቸው፥ ግዛታቸው፥ የዘር ልጆቻቸው ጭምር በጠቅላላው የሰይጣን ሆኑ፡፡ አንዳንድ ሞገደኛ አልሞት ባይ ተጋዳይ የሆነ ባሪያ እንደሚያጕረመርም፥ እንደሚኰበልልና ባርነቱን በሚገልጸው ማኅተም ጠቋሚነት ወይም ነጻ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥለት ማስረጃ ባለመያዙ ምክንያት ተይዞ ወደ ባርነቱ እንደሚመለስ ሁሉ፥ የአዳምና የሔዋን ልጆች የሆነውም ሁሉ ባርነትን ብንጠላውም፥ ነጻነትን ብንመኝም፥ ብናጕረመርምም ራሳችንን ከሰይጣን ግዛት ክበብ ውጪ ማድረግ ወይም ያስረከብነውን ግዛታችንን ከሰይጣን በማስለቀቅ ራሳችንን ነጻ ማድረግ እንዳልቻልን ተረኩ፡፡

“እኛን የወደደ እግዚአብሔር ግን ነጻ ሊያወጣን ቤዛ (ዎጆ) ለመክፈል በፍቅሩ እንደ ተገደደ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡ (ዮሐ. 3፥16፤ 1ዮሐ. 4፥9-10)” አሉ፡፡ ግን እግዚአብሔር ስለ እኛ የከፈለው ዋጋ (ቤዛ ወይም ዎጆ ዓለም ውድ ነው የምትለውን ብር፥ ወርቅ ዕንቍ ወይም ሌላ ነገር እንዳልነበረ ቅዱስ ጴጥሮስ ዛሬ በተነበበው መልእክቱ እንደ ገለጸልን መምህር እንግዳሸት ጠቀሱ፡፡ አያይዘውም እንኳን በምድር በሰማይም ቢሆን ከሚገኙ ከተፈጠሩ ሕያዋንና ኢ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ለሰው ቤዛ ሆኖ ሊሰጥ የሚችል እንዳልተገኘ አስረግጠው ከገለጹ በኋላ፥ “እግዚአብሔር ቤዛ አድርጎ የሰጠልን አንድያና ባሕርያዊ የሆነውን ልጁን እኮ ነው” አሉ፡፤ “ስለዚህም” አሉ፥ “ስለዚህም ሰው በተከፈለለት ቤዛ ምክንያት የሰይጣንና የኀጢአት ባሪያ መሆኑ ቀርቶ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል፤ የምሥራቹ ይህ ነው” ሲሉ በአዳራሹ የተገኙት በእልልታ፥ በሃሌታና በጭብጨባ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ጸጥታ ሲሰፍን፥ መምህሩ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ “የሐዋርያው መልእክት ከሚያስጨብጡን ብዙ ቁም ነገሮች ጥቂቶቹን ለዛሬ በልባችን ጽላት ላይ እንመዝግባቸው” አሉና ሲዘረዝሩ፡-


1.    “እግዚአብሔር በጸጋው የመደበልንን የክብር ደረጃ እንወቅ”

እግዚአብሔር በእጁ የሠራውንና በእስትንፋሱ ሕያው ነፍስ ያደረገውን ሰው ከባርነት መልሶ የራሱ ሲያደርገው በሰማይ፥ በምድርና በባሕር በእነዚህም ውስጥ በሚገኙ ፍጥረታት አልገዛውም፡፡ በነባቢነቱ እየተናገረበት፥ ዓለማትንና በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ የፈጠረበት ባሕርያዊ ቃሉና አንድያ ልጁ ቤዛ ይሆንልን ዘንድ እንደተሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክርልናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ያከበረው በመፍጠር ብቻ አይደለም፡፡ መልሶ የራሱ ሲያደርገው በከፈለለት ዋጋም ከመጠን በላይ አከበረው፡፡ የተዋጀንበትን ዋጋ ክቡርነት መጠን የምንረዳው ከሆነ እግዚአብሔር በመደበልን የክብር ደረጃ እንኑር (ዮሐ. 17፥22-24)፡፡ የተፈጥሮአችንን ከዚያም የሚበልጠውን የቤዛችንን ክቡርነት ካላወቅን በመዝሙር (49)፥12 የተጻፈው ይደርስብናል” በማለት አስጠነቀቁና ወደሚቀጥለው ነጥብ ተሻገሩ፡፡

2.   ለተገዛንበት ለቤዛችን ክብር እንኑር

ተገዝተናልና ራሱን ቤዛ ክፍሎ ለገዛን ክብር እንኑር፥ ለራሳችን ወይም ለሌላ አንኑር (1ቆሮ. 6፥15-20)፡፡ ሁለንተናችንን የራሱ ያደርግ ዘንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለንተናው ቤዛችን ሆኗል፡፡ ከሥጋችን፥ ከነፍሳችን፥ ከመንፈሳችን ቀንሰን ለራሳችን ማስቀረትም ሆነ ለሌላ መስጠት አንችልም፡፡

3.   እግዚአብሔር ባስቀመጠን ስፍራ እንኑር

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋርና በእርሱም በኩል ከአብ ጋር ያለንን አንድነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ በቅድስት ሥላሴ መለኮት እንድንታቀፍ በጸጋው አብቅቶናል (2ጴጥ. 1፥2-4)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገረችው ነፍሳችን (ዮሐ. 5፥24) በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰውራ እርሱ ባለበት እየኖረች ነውና (ኤፌ. 2፥6-7) እግዚአብሔር ባስቀመጠን ስፍራ እየኖርን መሆኑን እናረጋግጥ (ቈላ. 3፥1-4)፡፡

4.   በጥንቃቄ እንመላለስ

የምንበላውንም ሆነ የምንጠጣውን ሁሉ እንኳ ለእግዚአብሔር ክብር እናድርግ (1ቆሮ. 10፥31)፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ሰውሮ እኛን አሉ ከሚባሉ ቅዱሳን መናፍስት ሁሉ በላይ በሰማይ አስቀምጦን ሳለ (ኤፌ. 1፥19-23) ከዚያ ወርደን በምድር በጭቃና በትቢያ አንነካካ፡፡

እግዚአብሔር ለኔ የተለያችሁ ናችሁና ከመካከላቸው ውጡ ብሎናልና በመንፈስም በሥጋም ከመናፍስት ጋር ላለመቈራኘት እንጠንቀቅ፡፡ በመናፍስት ስም ከሚሠዋ ምግብና መጠጥ ራሳችንን እንለይ፡፡ እንግዲህ አሁን በሰማችሁት የእግዚአብሔር ቃል መሠረት እግዚአብሔር በልጁ የገዛኝ መሆኑን ተረድቻለሁና እለይለታለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ ደረጃዬን ዐውቄአለሁ፥ በክርስቶስ ከተሰጠኝ ስፍራ አልነቃነቅም በማለት የምትወስኑ ቁሙና ዐብረን እንጸልይ” ሲሉ መምህር እንግዳሸት ጠየቁና ለቆሙትና ለጉባኤውም ጸሎት አሳረጉ፡፡

ይቀጥላል

በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment