Sunday, June 1, 2014

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

የጥያቄና መልስ ጊዜ

ሥርዐተ አምልኮው እንደ ተፈጸመ፥ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት ጊዜ መሆኑን ዲያቆን ምስግና እንዳስታወቀ፥ አለቃ ነቅዐ ጥበብ የተመደበላቸውን ስፍራ ያዙ፡፡ የዛሬው ጥያቄና መልስ በምን ርእስ ላይ እንደሚያተኵር አለቃ ሲጠይቁ፥ ከሳምንታት በፊት ስለ ምልጃ ከተማርን በኋላ ቀሪውን በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ተብሎ እንደ ነበረ ዲያቆን ምስግና አስታወሳቸው፡፡ አለቃም መነጽራቸውን ካስተካከሉና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ካመቻቹ በኋላ “መልካም” አሉ፡፡ “መልካም ባለፈው ጊዜ በሐዲስ ኪዳን ተገቢ ሊቀ ካህናት፥ ነቢይ፥ ንጉሥ፥ መካከለኛ ሆኖ የተሾመው፤ ሰውም እግዚአብሔርም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ የሚናገሩትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣን ተመልክተን ነበር፡፡ በጥቅሶቹም አስረጅነት በመሐላ የተሾመው፥ ክህነቱ የማይሻረው ዘላለማዊው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሥዋዕት ማቅረቡን ሥራ ጨርሶ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ጊዜም እያማለደን መሆኑን የሚያስጨብጥ ግንዛቤ አግኝተን እንደ ነበረ ይታወሳል” በማለት ጀመሩ (ጮራ ቍ. 4 እና 5)፡፡

ለሚቀጥለው ሐሳብ መግቢያ የሚሆነውን ሲያብራሩም እንዲህ አሉ፤ “የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የቃል ኪዳን ማኅተም ይሆን ዘንድ የእንስሳ ደም ተረጭቶባቸው ነበር (ዘፀ. 24፥6-8)፡፡ ደም ሕዝቡ የእግዚአብሔር፥ እግዚአብሔርም የሕዝቡ ለመሆናቸው ጽኑዕ የትስስርና የውርርስ ቃል ኪዳን ማረጋገጫ ነው፡፡ ሆኖም ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች ቢበድሉ በመቅሠፍት እንዳይቀጡና የእግዚአብሔር ሕዝብነታቸውን ዐድሰው እንዲኖሩ የመሥዋዕት ሕግ ተደነገገላቸው፡፡ እስራኤላዊው የእግዚአብሔርን ሕግ ቢተላለፍ የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና ሞት የሚያስፈርድበትን ኀጢአቱን የሚሸከምለትንና በምትኩ ይሞትለት ዘንድ የሚሠዋለትን እንስሳ ወደ መገናኛው ድንኳን መውሰድ ነበረበት፡፡ ሊቀ ካህናቱ ቢበድል (ዘሌ. 4፥1-12)፥ ማኅበሩ ቢበድል (ዘሌ. 4፥13-21)፥ የማኅበሩ መሪ ቢበድል (ዘሌ. 4፥22-26)፥ የማኅበሩ አባል ቢበድል (ዘሌ. 4፥27-35) እንደ ታዘዘው መፈጸም ነበረባቸው፡፡

ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና (ዕብ. 9፥22) ኀጢአተኛ የሆነ ሁሉ በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበትን ስርየት እየተቀበለ ኅብረቱን ያድስ ነበር፡፡ በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 4 ውስጥ የየክፍሉ መጨረሻዎች ማለት ቍጥር 20፡26፡31፡35 መሥዋዕት በቀረበበት ኀጢአት በደለኛው እንደማይጠየቅ ያረጋግጣሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን ለስርየት ማግኛ የፈሰሰው ደም በምሳሌነቱ ያመለክት የነበረው ዘላለማዊውን ስርየት ሊሰጠን አንድ ጊዜ የፈሰሰልንን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ነው፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ለተሠራው ኀጢአት ሁሉ በእግዚአብሔር የተዘጋጀው አማናዊ ማስተስረያና መታረቂያ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው (1ዮሐ. 1፥1-10፤ ኤፌ. 1፥7፤ ራእ. 1፥5-7፤ 13-14)፡፡

ወንጌላዊ ዮሐንስ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል ሲል፡-
ሀ. የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም የማያነጻው ኀጢአት አለመኖሩን፤
ለ. ማንኛውም ኀጢአት የሚነጻበት ሌላ መንገድ በእግዚአብሔር እንዳልተዘጋጀ አረጋግጦ ይመሰክርልናል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር የልጁን ደም ለኀጢአት ማስተስረያ አድርጎ በዘመን ፍጻሜ ሲያቆመው
-    በፊት የነበረውን ኀጢአትና
-    አሁን በዚህ ዘመን የተሠራውን ኀጢአት
በማስተሰረይ ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው (ሮሜ 3፥25-26) አሉና አለቃ አየር ሳቡ፡፡ መነጽራቸውንም እያስተካከሉ አድማጮች እየተከተሏቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ግራ ቀኙን ማተሩ፡፡

ከዚያም “መልካም” አሉና ቀጠሉ “የልጁ የኢሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል የሚለውንና ለኀጢአት ስርየት የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው (ማቴ. 26፥28) የሚለውን የምሥራች በእምነት የተቀበለ ክርስቲያን ደምህ ባይፈስልኝ ኖሮ ሞት የተገባኝ ኀጢአተኛ ነበርሁ፤ ለኔ የፈሰሰው ደምህ ኀጢአቴን ለመደምሰስ ኀይልና ብቃት እንዳለው አምናለሁ በሚል ልብ ሲታመንበት ታጥቧል፥ ነጽቷል (1ቆሮ. 6፥11)፡፡ ሁል ጊዜ ጥያቄ የሚያስነሣው ጉዳይ ግን ከዚያ በኋላስ ክርስቲያን ኀጢአት ቢሠራ በምን መንገድ ስርየት ያገኛል? የሚለው ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ አንጽቶ ወደ ሥራ ላሰማራቸው ደቀ መዛሙርት እግራቸውን ሁል ጊዜ መታጠብ እንደሚያስፈልጋቸው አስተማራቸው፡፡ አይሁዳዊ ወጣ ብሎ ወደ ቤቱ በተመለሰ ቍጥር መላ አካሉን መታጠብ ባያስፈልገውም፥ ከቤቱ በራፍ ካስቀመጣቸው ማድጋዎች ውሃ በመቅዳት በአቧራና በከባቢ ነገሮች በመነካካት በቀላሉ የሚያድፉትን እግሮቹን በመታጠብ እንደሚያነጻ ሁሉ (ዮሐ. 2፥6) አንድ ጊዜ ጌታ ያነጻው ክርስቲያን ከዓለም ጋር በመነካካት የሚያድፈውን እግረ ልቡናውን ሁል ጊዜ እየታጠበ መንጻት እንዳለበት እግርን በመታጠብ ምሳሌ አስተማራቸው (ዮሐ. 13፥10)፡፡

የቈሸሸ እግረ ልቡናን ለማን ይሰጧል? በምንስ ይነጿል

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ካላጠብሁህ ከኔ ጋር ኅብረት አይኖርህም” (ዮሐ. 13፥8) ሲል ምስጢሩ የተሸፈነ አይደለም፡፡ የትሕትናውን ሥራ ሁላቸው እንዲሠሩ ቢያዛቸውም (ዮሐ. 13፥12-17) እኔ ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ኅብረት አይኖርህም በማለቱ የቈሸሸውን እግረ ልቡና ማጠብና ማንጻት የሚችለው ራሱ እንደሆነ ማመልከቱ ነበር፡፡ በአባባሉ ኀጢአትን የማንጻት ኀይልም ሥልጣንም ያለው ራሱ መሆኑን በማያወላውል ሁኔታ አስረድቷል (መዝ. (32)፥5፤ ኢሳ. 1፥18፤ 43፥25-26፤ ማር. 2፥5-12)፡፡ የቈሸሸ እግረ ልቡና የሚነጻው ያው አንድ ጊዜ በፈሰሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ ውድ አባቱ ጌታ እግዚአብሔር አብ ‘ከእንግዲህ ኀጢአትን በሰው ላይ እስከማልቈጥር ድረስ የተቀበልኸውን መከራ፥ ሥቃይና ሞት የፈሰሰውንም ደምህን ለኀጢአት ዕዳ ክፍያ በቂ ነው ብያለሁ፥ ይህም በትንሣኤህ ተረጋግጧል፤’ ሲል ያወጀበትን ሕጋዊ ሰነድ በማሳየት፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናዛዡን ኀጢአተኛ ተቀብሎ በማማለድ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በዚህ ረገድ የሚያስጨብጠን ምስጢር ጥልቅ ቢሆንም በእምነት ለሚቀበሉት ሁሉ ሽፍን አይደለም፡፡ እስኪ እንደሚከተለው ዘርዘር አድርገን እንከልሰው” አሉና አለቃ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልበጥ ገልበጥ፥ የእልባት ምልክቶችን ሰካ - ሰካ እያደረጉ፥ ለሰከንዶች ጸጥ አሉ፡፡ እንደገናም “መልካም” በማለት ጀመሩ፡፡

ሀ. ኀጢአታችንንም ለማስተሰረይ፤ እኛንም ለማማለድና ለማስታረቅ ለሐዲስ ኪዳን ተገቢ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት የማይሻርና ዘለዓለማዊ ነው፡፡ (ወውእቱሰ ይነብር ለዓለም እስመ ኢይሰዓር ክህነቱ፤ ዕብ. 7፥22-24) የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ክህነት እንደነቀያፋ ክህነት ጊዜያዊ የምታደርገውና ሌላ ሊቀ ካህናት የምትሾም አንተ ነህ እንጂ እግዚአብሔርስ ለዘላለም ሾሞታል (መዝ. (110)፥4፤ ዕብ. 7፥28)፡፡
ለ. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀ ካህናትነቱ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ኀጢአትን ለዘላለም በማስተስረይ ለሚያምኑት ሁሉ የዘላለም መዳን ሆነ (ዕብ. 5፥5-10፤ 9፥25-26)፡፡ (ኮነ ዐሳዬ ሕይወት … ወመድኅነ ዘለዓለም)፡፡
ሐ. ዛሬ ዐዲስ አማኞችም ሆኑ የቈሸሸ እግረ ልቡናቸውን በማሳጠብ ኅብረታቸውን የሚያድሱ ክርስቲያኖች ወደ እግዚአብሔር ሊቀርቡ የሚገባው እነርሱንና እግዚአብሔርን በአንድ አካል (በራሱ አካል) ያገናኝ ዘንድ መካከለኛና ሊቀ ካህናት በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው (ወይክል አድኅኖቶሙ ለዝሉፉ ለእለ ይቀርቡ ኀበ እግዚአብሔር እንተ መንገሌሁ፡፡ ዕብ. 7፥25)፡፡ ጌታችንም በኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ አይመጣም (ወአልቦ ዘይመፅእ ኀበ አብ ዘእንበለ እንተ ኀቤየ ዮሐ. 14፥6) ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ለመግባት ብትሞክር፥ በሌብነት ተይዘህ እጥፍ ፍርድህን ትቀበላለህ እንጂ አይሳካልህም (ዮሐ. 10፥1-7)፡፡
መ. ሞትን ድል አድርጎ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን ሁሉ እተቀበለ በማይሻረው ዘላለማዊ ክህነቱ ያማልዳቸዋል፥ ያስታርቃቸዋል፡፡ (እስመ ለግሙራ ሕያው ውእቱ፥ ወይተነብል ሎሙ፡፡) ዛሬ አያማልድም የምትል ካለህ ከሓዲነትህን ታሳውቃለህ እንጅ መጽሐፍ ቅዱስስ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል ይልብሃል ዕብ. 7፥25)፡፡
ሠ. በየጊዜው መሥዋዕት የማይቀርብ ከሆነ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ መሥዋዕት ዛሬ እንዴት ስርየትን ይሰጣል፥ ያማልዳል፥ ያስታርቃል ቢባል ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡
ሠ.1. ጌታችን ራሱን አንዴና ለመጨረሻው መሥዋዕትና ቊርባን አድርጎ ባቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ከእንግዲህ ኀጢአትን ለዘላለም አላስብም እስኪል ድረስ አርክቶታል፡፡ አልቦ እንከ መሥዋዕት በእንተ ኀጢአት (ዕብ. 9፥24-28፤ 10፥14-18)፡፡
ሠ.2. ጌታችን ዛሬ ስለ እኛ የሚማልደውና የሚያስታርቀን በየጊዜው መሥዋዕትን በማቅረብ ሳይሆን፥ አሁን በላዩ ተጭኖ የማይታየውን፤ አንድ ጊዜ ግን ተሸክሞት የተሠዋበትን ኀጢአት ለዘላለም ማስወገዱን በሚያረጋግጥና ድልን ለሚያበሥር መገለጥ እየታየልን እንደ ሆነ ቃሉ ያበሥረናል (ዕብ. 9፥28)፡፡ ለምን እንዲታይልን አስፈለገ? የኀጢአት ዕዳችን የተከፈለበትን ሕጋዊ ሰነድ ለማሳየት ነዋ፡፡ አባባ! ስለ ሰው ልጆች ኀጢአት ሁሉ የከፈልሁትን ዋጋ ምንነትና መጠኑን የሚያስረዱትን በምስማር የተቦደሱትን እጆቼንና እግሮቼን፥ በጦር የተነደለውን ጐኔን፥ በጅራፍ የተተለተለውን ጀርባዬን ተመልከት! አባት ሆይ! በእሾህ የተወጋውን ራሴንና ግምባሬን፥ በፈጠርሁት እጅ የተጸፋውን ጕንጬን እየው እስኪ! የእርሱን ኀጢአት ለማስወገድ ይህን ሁሉ መቀበሌን አምኖ ይህ ኀጢአተኛ በእኔ በኩል፥ ወደ እኔ መጥቷልና በእኔ ያመነ ሁሉ ይቀበለው ዘንድ ለተገባው የኀጢአት ስርየትና የዘላለም ሕይወት ባለመብት አድርገው እንደ ማለት ነው፡፡
ሠ.3  ያ ስለ ሰው ኀጢአት ከጲላጦስ አደባባይ ጀምሮ አስከ ቀራንዮ ኰረብታ የፈሰሰው የልጁ ደም ድምፅ ከጆሮው ትዝታው ከልቡ ሳይጠፋ ምን ጊዜም በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረ ስፍራውን እንደ ያዘ ይኖራል፡፡ ይኖራልና ዐዲስ አማንያንና እግረ ልቡናቸው የቆሸሸባቸው ክርስቲያኖች ይነጹ ዘንድ ሰው ሠራሽ መሥዋዕት ሳያስፈልጋቸው በእምነት በዚሁ ቅዱስ ደም ይረጫሉ፤ ይነጻሉም፡፡ የዕብራውያን መልእክት ፀሓፊ በምድር ገና እየኖሩ ሳሉ በሰማያት ወደ ተጻፈ የበኵራት ማኅበር የተጨመሩትን - ወደ ሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከአቤል ደም ይልቅ የተሻለ ወደሚናገር ወደ መረጨት ደም ደርሳችኋል ይላል (ዕብ. 12፥18-24)፡፡
       
        የአቤል ደም የጮኸው፥ ቃኤልን ለመክሰስ ነበረ (ዘፍ. 4፥10)፡፡ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ግን የሚያሰማው ድምፅና የሚፈጥረው ትዝታ ኀጢአትን ለማስተሰረይና ስለ ሰዎች ለመማለድ ነው፡፡ በቅዳሴ ሐዋርያት በመሲሕነት የላክኸው የልጅህ ደም እነሆ ስለ እኔ ይጮኻል (ወናሁ ደመ መሲሕከ ይኬልሕ በእንቲአየ) ሲል ቀዳሹ በመማፀን ያቀረበው ልመና ከዚህ ጋር የሚስማማ ነው፡፡

ረ. ወንጌላዊ ዮሐንስ ምዕመናን ኀጢአትን እንዳይሠሩ ከመከረ በኋላ ኀጢአትን ሠርተው ቢገኙ ግን፡- የኀጢአታችን ማስተስረያ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ዘንድ ጠበቃ ሆኖ እንዳለልን ያስረዳናል (1ዮሐ. 2፥1-2)፡፡ ጠበቃችን ተከራካሪና ተሟጋች ወይም አማላጅ ብቻም አይደለም፤ የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው እንጂ (ሮሜ 3፥25)፡፡ በእርሱ በኩል ለሚቀርብ ተናዛዥ ይህማ እኔ የተወጋሁለት፤ የደማሁለት፥ የቈሰልሁለት፥ በመስቀል ጐዳና ሞትን የተቀበልሁለት መሆኑን ያመነ ኀጢአተኛ ነው፡፡ ስርየት በተሰጠበት ኀጢአት ሊጠየቅ አይገባውም በማለት የኀጢአት ማስተስረያ የሆነበትን ማስረጃ በማሳየት ይለፍ ያሰኛል ማለት ነው፡፡ ከኀጢአተኛ ምእመን የሚጠበቀው መናዘዝ ነው፡፡ እንደ ተናዘዘ የኀጢአቱ ማስተስረያ ሆኖ ከአብ ዘንድ በሚገኘው ጠበቃው አማካይነት የስርየት ማረጋገጫና የይለፍ ፈቃድ ይሰጠዋል (1ዮሐ. 1፥7-10)፡፡ እግዚአብሔር አሁንም ለዘላለም ይመስገን፡፡

እንግዲህ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይኖረን ዘንድ ተገቢም አስፈላጊም ሆኖ የተገኘበት ምስጢር ከዚህ የተነሣ ነው (ዕብ. 7፥26-28)፡፡ ሁሉ በራሱ ፍጻሜ የሚያገኝበት ምስጢር በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አለ፡፡ እንደ ሙሴ ነቢይና መካከለኛ፥ እንደ አሮን በመልከ ጼዴቅ የሹመት ሥርዐት ሊቀ ካህናት እንደሚሠዋ እንስሳ በደሙ ኀጢአትን የሚያስወግድ መሥዋዕት፥ እንደ መገናኛው ድንኳን በሥጋው ሰውንና እግዚአብሔርን ያገናኘ መቅደስ (ዮሐ. 2፥19-22) … ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ የተደመደመበት ፍጻሜ ነው (ቈላ. 1፥19-22፤ 2፥1-3፤ 9-15) አሉና አለቃ መነጽራቸውን አንሥተው እየወለወሉ ከግራ ወደ ቀኝ ከላይ ወደ ታች እይታቸውን በማዛዋወር ጉባኤውን በመመልከት ላይ እያሉ ተማሪ የማነ ብርሃን እጆቹን ከፍ አደርጎ ዘረጋና ተነሣ፡፡

“የኔታ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት ከየት አስከ የት እንደ ሆነ አስረድተዉናል፡፡ የሚታከል ነገር ቢኖር በሕይወት ያሉና የሌሉ ቅዱሳን በአማላጅነት ሥራ ተካፋይነት ቢኖራቸው እንዲያስረዱን ፈቃድዎን እንጠይቃለን” አላቸው፡፡

በአዳራሹ ውስጥ ያሉ ሁሉ በጥያቄው መስማማታቸውንና መልሱን ለማወቅ መጓጓታቸውን በምልክትም በቃልም አስረዱ፡፡ አለቃም መነጽራቸውን እያስተካከሉ ቆዩና እንደ ተለመደው “መልካም” አሉና “በሉቃስ ወንጌል 16፥19-31 የተጻፈውን የራሱን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት መላልሰን ብናነብ ይህን የተጠየቀውን ርእስ በሚመለከት በተለያየ አቅጣጫ ለሚነሡት ጥያቄዎች ሁሉ አጥጋቢ መልሶችን እናገኛለን፡፡ ባለጸጋው በሀብቱ እግዚአብሔርን ሊያከብርበት ይገባው የነበረውን ችላ በማለት እግዚአብሔር በሰጠው ሀብት ራሱን ብቻ አገለገለበት፤ ምድራዊ ሩጫውን ፈጸመ፤ ሞተ፡፡ ሞት ማለት ብዙዎቹ ይሆንልናል ብለው እንደ ተመኙት ወደ አለመኖር መለወጥ ሳይሆን ቀረና፥ የሥጋና የነፍስ መለያየት ሆነ፡፡ ስለዚህም ሥጋው ሲቀበር ነፍስ ወደሚገባት ሥፍራ ተወሰደች፡፡ በሲኦል የነበረችው የባለጸጋው ነፍስም ቀጥሎ የተመለከቱትን ነገሮች መረዳት ችላ ነበር፡፡

አንደኛ  ከሥጋ ከተለየች በኋላ በተሰጣት ስፍራ ያጋጠማት ሥቃይ ይሰማት ነበር፡፡
ሁለተኛ በሲኦል ለመሠቃየት ያበቃት በሥጋ በነበረችበት ጊዜ ማድረግ ሳይገባት ያደረገችውና፥ ማድረግ ሲገባት ያላደረገችው ነገር መሆኑን በሚገባ ዐወቀች፡፡
ሦስተኛ ለሥራዋ ውጤት ተገቢ ሆኖ የሚከፈላት ዋጋ ገና እንደ ሆነና አሁን ያለችበት የፍርድ መጠባበቂያ ማረፊያ ሊለወጥ እንደማይችል ያወቀች ቢሆንም ቢሻሻልላት ኖሮ ተመኝታ ነበር፡፡ ከንቱ ፀፀት!
አራተኛ የእርስዋን ዐይነት ሥራ እየሠሩ በነበረበት ጊዜ ወደ ኋላ የተወቻቸው ወገኖችዋ ዕጣ ፈንታ የእርሷ ዐይነት እንደሚሆን ተረድታ ነበር፡፡ የሚቻል ቢሆንማ እነርሱ እንኳ ጐዳናቸውን እንዲለውጡ ከሞት የተነሣ ሐዋርያ ቢላክላቸው ተመኝታ ነበር፡፡
አምስተኛ ትታው የመጣችው ምድራዊ ነገር ትዝታ አልተረሳትም፡፡ ሆኖም እርስዋ ከተወችው በኋላ የተለወጠ ሁኔታ ቢኖር ኖሮ የምትረዳበት መንገድ አልነበረም፡፡ እነዚህን ነጥቦች እንደ ጨበጥን ወደ ቀረበው ጥያቄ ተመልሰን በአምስት ክፍል የተዘጋጁ መልሶችን እሰጣለሁ፡፡ አሉ አለቃ፥

1.     በዐጸደ ነፍስ ያሉ ማለት ምድራዊ ሩጫቸውን ጨርሰው በአካለ ነፍስ ገነት የተወሰዱ ቅዱሳን እንደነርሱ ሩጫቸውን ጨርሰው በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ለገቡ ነፍሳት ይማልዳሉን? ወይም ያማልዳሉን? ቢባል አያማልዱም፤ አይማልዱም የሚል ነው መልሱ፡፡ በሲኦል ያሉ ነፍሳት ከፃዕር የተነሣ በገነት ወደሚገኙ ቅዱሳን ቢጮኹ እንኳ የሚሰጣቸው መልስ ልጄ ሆይ በሕይወትህ ሳለህ የተሰጠህን ዕድል አልተጠቀምህበትም፡፡ ዛሬማ በመከካከላችን ታላቅ ገደል አለ ይባላሉ (ሉቃ. 16፥25-26)፡፡

2.    በዐፀደ ነፍስ ያሉ የቅዱሳን ነፍሳት በዐጸደ ሥጋ ላሉት ይማልዳሉን? ያማልዳሉን? የለም አያማልዱም፤ አይማልዱም፡፡ በሕይወተ ሥጋ ያሉ ሰዎች ዕድል ፈንታ፥ እነርሱ እንዳደረጉት ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚሰጡትን ምሪት መከተልና መዳን እንደ ሆነ ያውቃሉና (ሉቃ. 16፥27-29)፡፡

3.    በሕይወተ ሥጋ ያሉ ቅዱሳን በዐጸደ ነፍስ ለሚገኙት ይማልዳሉን? ያማልዳሉን? ቢባል አሁንም መልሱ አይማልዱም አያማልዱም ነው፡፡ ሰው የሚድነው በሕይወተ ሥጋ በነበረበት ጊዜ መጻሕፍት በሚሰጡት ትምህርት ልቡ ሲነካና ንስሓ ሲገባ እንደ ሆነ አሳምረው ያውቃሉና (ገላ. 6፥7-8) ወልድ ያለው ሕይወት አለው፥ ወልድ የሌለው የእግዚአብሔር ቁጣ ይኖርበታል እንጂ ሕይወትን የሚያይበት ሌላ እድል አልተሰጠውም (ዮሐ. 3፥36)

ማስገንዘቢያ፡- በእግዚአብሔር አመነ፥ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት የተባለው አብርሃም ከቤተ እስራኤልም ከቤተ አሕዛብም በእምነት ለሚጸድቁ ሁሉ አባት ስለ ሆነ (ሮሜ 4፥1-12) የቅዱሳን ነፍሳት ማረፊያ ሕፅነ አብርሃም፡- የአብርሃም ዕቅፍ (አጠገብ) በመባል ይታወቃል (ማቴ. 8፥10-11፤ ሉቃ. 13፥28-29)፡፡ ይህ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን ሁሉ አባት የሆነው አብርሃም ከተማፀነችውና ከወተወተችው ነፍስ ጥያቄዎች አንዱን እንኳ ለመፈጸም ችሎታ እንደሌለው ቢታወቅም፥ ወደ እግዚአብሔር ምልጃ እንኳ አላቀረበላትም፡፡ ወሰኑን ያውቀዋልና፡፡

4.    በሕይወተ ሥጋ ያሉት እንደ እነርሱ በሕይወተ ሥጋ ላሉት ይማልዳሉን ምልጃቸውስ ተቀባይነት አለውን ቢባል አዎን፡፡ እንዴታ!
4.1      ያዕቆብ በመልእክቱ 5፥14-20 አንዱ ለሌላው ይጸልይለት ይማልድለት፥ ከስሕተት ይመልሰው፤ እርስ በርስ ተናዘዙ አለ፡፡ መካሪውና ማላጁ፤ እንዲሁም ተመካሪውና ምልጃ አቅራቢው (መስተብቊዕ -  አድራሹ) ሁለቱም ወገኖች በሕይወተ ሥጋ ያሉ ናቸው፡፡
4.2     ሐዋርያው ጳውሎስ በሥጋ ሕይወት በነበረበት ጊዜ እንደ እርሱ በሥጋ ሕይወት ለነበሩት ማለት፥ ለምእመናን፥ ለአብያተ ክርስቲያናትም ይጸልይ ነበር፡፡ መስተብቊዕ - ምልጃ ያቀርብ ነበር (ሮሜ 1፥9-10፤ ኤፌ. 1፥16፤ ፊል. 1፥4፤ ቈላ. 1፥3-9፤ 2ጢሞ. 1፥2-3፤ ፊልሞና 4-5)፡፡
4.3    ይኸው ሐዋርያ የሚጸልይላቸው ምእመናን፥ አብያተ ክርስቲያናት ስለ እርሱና ስለ አገልግሎቱ እንዲጸልዩ (መስተብቊዕ እንዲያደርሱ) ያሳስብ ነበር (ሮሜ 15፥30፤ 2ቆሮ. 1፥11፤ ኤፌ. 6፥18-19፤ ፊል. 1፥19፤ ቈላ. 4፥3፤ 1ተሰ. 5፥25፤ 2ተሰ. 3፥1፤ ፊልሞና 22፤ ዕብ. 13፥18)፡፡
4.4    ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉትን ሁሉ ተግባራቸውን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲያከናውኑ፥ ይድኑም ዘንድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያስተውሉ ምልጃ ያቀርቡላቸው ዘንድ ክርስቲያኖችን አዟል (1ጢሞ. 2፥1-4)፡፡ እርሱም ይህን ኀላፊነት እንደ ተወጣ ገልጿል (ሐ.ሥ. 26፥29)፡፡

ሐዋርያው ወደ ጌታ መንግሥት ከመጠራቱ በፊት የመጀመሪያው የጌታ ሰማዕት እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶ ነበር፤ ነፍሱን ጌታ ሲቀበላት፥ ሥጋውን ግን ምእመናን ቀብረዉት ነበር (ሐ.ሥ. 7፥59-60፤ 8፥1-3)፡፡ ለዚህም ጳውሎስ ምስክር ነበር (ሐ.ሥ. 7፥58-59፤ 8፥3)፡፡ እንዲሁም ይኸው ሐዋርያ ከተጠራ በኋላ የጴጥሮስ ወንድም ያዕቆብ ተሰይፎ (አንገቱን ተቈርጦ) ነበር (ሐ.ሥ. 12፥1-2) በታሪክም እንደ ተገለጸው ጌታን በሥጋ የወለደችው ድንግል ማርያም፥ ጳውሎስ አብዛኛውን መልእክቶቹን ከመጻፉ በፊት በሞት ከዚህ ዓለም ተለይታ ነበር፡፡ የሐዲስ ኪዳን አማንያንን ጠቀስን እንጂ ጳውሎስ ከላይ የተጠቀሰውን ማሳሰቢያ በጻፈበት ጊዜ የቅዱሳን አባት አብርሃምና ሌሎቹ የብሉይ ኪዳን አማንያን፥ ከሐዲስ ኪዳን መግቢያም መጥምቁ ዮሐንስን ጨምሮ በዐጸደ ነፍስ መኖራቸውን አንዘነጋም፡፡ ሆኖም እነዚህ ቅዱሳን ነፍሳት ይማልዱለት ዘንድ አልጠየቀም፤ በሕይወተ ሥጋ ያሉትን ብቻ ጸልዩልኝ አለ እንጂ፡፡ በሕይወተ ሥጋ ላሉት ራሱ ሲጸልይና ሌሎችም ክርስቲያኖች እንዲጸልዩ ሲያሳስብ ለሞቱት ወገኖቹ ግን አልጸለየም፡፡ ሌሎችንም ይጸልዩ ዘንድ አላዘዘም፡፡

ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ላሉት ቢጸልይ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የመዳን ዕድል በፊታቸው ስላለ ይህን ዕድል ይጠቀሙበት ዘንድ ጌታ እንዲረዳቸው መጸለይ አስፈላጊነት ይኖረዋል፡፡ በዐጸደ ነፍስ ያሉት ግን ቃሉን ሰምተው የመዳን ዕድል ያመለጣቸው በመሆኑ ስለ እነርሱ ለምን መጸለይ ያስፈልጋል? የቅዱሳንም ነፍሳት ቢሆን እንደ ኀጥኣን ነፍሳት ሁሉ ከፀሓይ በታች በሚደረገው ነገር የመካፈልን ዕድልና ችሎታን ያጡ፥ ሊያስተውሉ ይቅርና ከሞት በኋላ ልጆቻቸው ከብረው ወይም ደኽይተው እንደ ነበሩ እንኳ አያውቁም፡፡ ቀድሞ በምድር የነበሩበትን ሁኔታ ከማስታወስና አሁን ራሳቸው ያሉበትን ሁኔታ ከመረዳት በቀር ከሞቱ በኋላ የቤተ ሰባቸው ሁኔታ ተለውጦ እንደ ሆነ፥ ወይም በዚያው ሁኔታ እየቀጠለ እንደ ሆነ አያዩም፥ አያውቁም (ኢዮ. 14፥20-22፤ መክ. 9፥4-6፤ ኢሳ. 63፥16)” አሉና አለቃ በረጅሙ ተነፈሱ፤ ሆኖም የድካም ምልክት አልታየባቸውም፡፡

5.    “በእግዚአብሔር በኩል ሆኖ ሰዎችን መማለድም አለ፡፡” አሉ አለቃ በመቀጠልም “ከዚህ በላይ ከ 4.1 - 4.4 የዘረዘርናቸው ምልጃዎች በሕይወተ ሥጋ ያሉ ሰዎች እንደነርሱ በሕይወተ ሥጋ ባሉ ሰዎች በኩል ሆነው እግዚአብሔርን ሲማልዱ ነው፡፡ በዚህኛው በአሁኑ ክፍል ግን በሕይወተ ሥጋ ያሉ ሰዎች በእግዚአብሔር በኩል ሆነው በሕይወተ ሥጋ ያሉ ሰዎችን ሲማልዱ፥ ሲለምኑ ይታያሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው ያማስታረቅ አገልግሎት ምክንያትና በኩል እግዚአብሔር ሰዎችን ታርቋል፡፡ ሰውን ከእግዚአብሔር ያጣላው ኀጢአት መደምሰሱን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ዕርቅና ሰላም መውረዱን ጌታ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ አብሥሯል (ሉቃ. 24፥36-47፤ ዮሐ. 20፥19-26፤ ኤፌ. 2፥11-18፤ ቈላ. 1፥20-22)፡፡

በጌታ የተበሠረውን የዕርቅና የሰላም ዐዋጅ የሰሙት ሐዋርያት ለተተኪዎች አስተላለፉት፡፡ ተያይዞም እኛ ዘንድ ደርሷል፡፡ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን (ማቴ. 28፥18-20፤ ማር. 16፥8-19፤ 20፤ ሉቃ. 1፥1-4፤ 24-46፤ 53፤ ሐ.ሥ. 1፥1-8፤ ዕብ. 2፥3-4)፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ለ2 ሺሕ ዓመታት ያህል ክርስቶስ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ከእንግዲህስ ሰላምና ደስታ ሆኗል፤ (ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን አግዐዞ ለአዳም፤ አሰሮ ለሰይጣን እም ይእዜሰ ኮነ ፍሥሓ ወሰላም) በማለት እያወጀች አለች፡፡ ጌታ የሰጣቸውን የዕርቅ ዐዋጅ የያዙ አገልጋዮች ከሐዋርያት ጀምሮ በያለበት ይሰብካሉ፡፡ በእግዚአብሔር በኩልም ሆነው ሰዎችን እየማለዱ፥ እየለመኑ ይገኛሉ፡፡ እግዚአብሔርም የዕርቁን ዐዋጅ ይዘው ከወጡ አስታራቂዎች ጋር ሆኖ (በእነርሱ በኩል) እኔ ይቅር ብያለሁ ኑ ታረቁኝ እያለ (በመማለድ) በመለመን ላይ ይገኛል (2ቆሮ. 5፥18-21)፡፡

ማስገንዘቢያ፡-

1.     ኀጢአት የማያውቀውን ልጄን ስለ እናንተ ኀጢአት ያደረግሁት እናንተ በእርሱ የኔ ጽድቅ እንድትሆኑ ነውኮ! በእኔ በኩል ይቅር ብያለሁ፥ የዕርቁን ዐዋጅ ስሙና ኑ ታረቁኝ እያለ እግዚአብሔር በወንጌላውያን በኩል እየማለደ ሳለ፤ አይ ልጅህ በፈጸመው ሥራ አልታረቅም፤ ሌላ አስታራቂ እፈልጋለሁ ለሚል ሰው ኧረ ምን መፍትሔ ይገኛል?

2.    ከእግዚአብሔር ጋር ኑ ታረቁ ይሉ ዘንድ የዕርቁን ዐዋጅ የሚያሰሙት በሕይወተ ሥጋ ላሉት ኃጥኣን ነው እንጂ በዐጸደ ነፍስ ላሉ ኃጥኣን አይደለም፡፡

3.    በሕይወተ ሥጋ ላሉት ኃጥኣንም የዕርቁን ዐዋጅ የሚሰብኩት ያው እንደነርሱ በሕይወተ ሥጋ ያሉ ቅዱሳን ናቸው፡፡

4.    አንዳንድ ሰዎች ለክርክር የሚያመጡትን ሐሳብ እዚሁ እንመልከተው፤ ሐዋርያት በ12ቱ ነገደ እስራኤል ላይ ትፈርዳላችሁ ተብለዋልና እንዴት ማማለድ አይችሉም? ይላሉ፡፡ ይህ የአስተዳዳሪነት ሹመት ሊሰጣቸው የታቀደው በዳግም ምጽአቱ እንደ ሆነ የሚገልጸውንና ተያይዞ የሚነበበውን ካለማስተዋል የሚነሣ ጥያቄ ነው (ማቴ. 19፥28፤ ሉቃ. 22፥30) ለማስረጃና ለማገናዘቢያም፡-

-    የመንግሥትን ሥልጣን ተቀብሎ ለመምጣት የሄደው መኰንን የሰጣቸውን መክሊት ምን ያህል እንዳራቡት አገልጋዮቹን የተቈጣጠራቸው የሾማቸውና የፈረደባቸው ሥልጣነ መንግሥትን ተቀብሎ በተመለሰ ጊዜ ነበር( ማቴ. 25፥14-33፤ ሉቃ. 19፥12-27)፡፡
-    ጳውሎስ የተዘጋጀለትን አክሊል የሚረከበው በዚያን ቀን እንደ ሆነ ይናገራል (2ጢሞ. 4፥6-8)፡፡
-    እያንዳንዱ ክርስቲያን እንደ ሥራው ሽልማት የሚቀበልበት ቀን የጌታ ዳግም ምጽአት ነው (ሐ.ሥ. 17፥30-31፤ 1ቆሮ. 3፥12-13)፡፡
-    ዛሬ ክርስቲያኖች የሚረዱት ነገር ቢኖር ከማንቀላፋታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ሕይወታቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ መሰወሩን ብቻ ነው፡፡
-    የተሰወረውም ሕይወታቸው በጌታ ዳግም ምጽአት ከጌታ ጋር ይገለጣል (2ተሰ. 1፥5-10፤ 1ዮሐ. 3፥1-2)፡፡ በቅዳሴ ሠለስቱ ምእትም “እንክርዳድ የሌለበት ስንዴ (ነጩ፥ ጥቍሩ… በአንድነት) በአንዲት መዝገብ ውስጥ ይጨመራል፡፡ ለሁሉ እንደየሥራው እስከሚከፈልበት ጊዜ ድረስ የጻድቃን ነፍሳት በዚያች ይኖራሉ፥ በዚያም ይጠበቃሉ” ስለሚል ዛሬ ዋጋ እንደ ተከፈለ የሚሰበከው ትምህርት ዘግይቶ የበቀለ ዐረም እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ጻድቁ ሰማዕቱ እንደ ሞተ አክሊልና ሹመት ተሰጠው ማለት ዘበት ነው፡፡
-    በሕይወተ ሥጋ ባሉበት ጊዜ የመጀመሪያውን ርምጃ የሚለውጡና አክሊላቸውን የሚያጡ ይኖራሉ፡፡ ሥራቸውም የሚገመገመው በእግዚአብሔር ዐይን እንጂ በሰው ዐይን አይደለም (1ቆሮ. 9፥24-27፤ 2ቆሮ. 5፥10፤6፥8፤ ራእ. 2፥5፤ 3፥11)፡፡
-    ሁሉን በሚመረምር በእርሱ ዐይን ሥራዎች ተመርምረው ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ራእ. 20፥15)፡፡ ጻድቃን ያን ጊዜ በአባታቸው መንግሥት እንደየሥራቸው ይሸለማሉ፥ ይሾማሉ ማለት ነው፡፡ ካሉ በኋላ አለቃ ደምፀ በዝምታ ውስጥ ሆነው ጉባኤውን ሲመለከቱ ዲያቆን በፈቃዱ ቆመና፥ “መላእክት ያማልዱን ዘንድ ወደ እነርሱ እንድንጸልይ ታዟልን” ሲል ጠየቀ፡፡
-    አለቃም መነጽራቸውን ካሰማመሩና ካስተካከሉ በኋላ “መልካም” አሉና ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ “የተዘነጋውን ጉዳይ ዲያቆን በፈቃዱ በማስታወስህ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ ወደዚህ ጉባኤ መምጣት ከጀመርክ ጊዜው ዐጭር ቢሆንም (ጮራ ቁ. 7) ታስተውል ዘንድ ዐይነ ልቦናህን መንፈስ እንዳበራልህ ለመረዳት ችያለሁ፥ ጌታ ይመስገን፡፡

እሺ፥ ወደ ጥያቄው እንመለስ፥ ክርስቲያን ያማልዱት ዘንድ ወደ መላእክት እንዲጸልይ አልታዘዘም፡፡ በተቃራኒው ያለውን ለመረዳት ግን አራት መግለጫዎች ከእግዚአብሔር ቃል ትመለከቱ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡
አንደኛ፡- መናፍስትንና የሙታንን ነፍሳት አትጥሩ ሲባል፡- የሙታን ነፍሳት የተባሉት አንድ ጊዜ እንደ እኛ ከአዳምና ከሔዋን ዘር በሥጋና በደም ተወልደው በዚህ ምድር  ለዐጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ከታዩ በኋላ ሥጋዎቻቸው በዚህ ምድር ሲቀሩ፥ ነፍሶቻቸው በሲኦልና በገነት ያሉትን ማለቱ እንደ ሆነ ይገባናል፡፡ መናፍስት የተባሉትም አገልጋዮቹን መናፍስት አድርጎ ፈጠራቸው ተብሎ እንደ ተነገረው እግዚአብሔር በትእዛዝ የፈጠራቸውና ከአለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸው መላእክት ናቸው (ዕብ. 1፥14)፡፡ እነዚህንም እንዳንጠራቸው (በጸሎት) ተከልክለናል፡፡ ከላይ የሰጣኋችሁን ጥቅሶች እቤታችሁ ስትገቡ መላልሳችሁ አንብቧቸው፡፡
ሁለተኛ፡- ኢዮብን ለማጽናናት በአጠገቡ ከተገኙት አንዱ ኤልፋዝ - መልስ ታገኝ እንደ ሆነ እስኪ ከቅዱሳን ወደ አንዱ ተጣራ በማለት ተናገረው፡፡ እስኪ መልስ ታገኝ እንደ ሆነ ሲል አታገኝም ለማለት ነው፡፡ ምናልባት በሕይወተ ሥጋ ያሉ ሰዎችን መጪ ዕድል ለመጠየቅ በዐጸደ ነፍስ ያሉትንና መናፍስት የሆኑትን መላእክት ብንጠራ፡- የእግዚአብሔር ሕዝብ በቀጥታ ከእስትንፋሱ ይልቅ የቀረበውን አምላኩን (ኤር. 23፥23) ለምን አይጠራም? በማለት ይመልሱልናል፡፡ ደጋግመን እንደ ገለጽነው መናፍስትንና የሞቱ ሰዎችን ነፍሳት መጥራት ማለት እግዚአብሔር በሚጸየፈውና በከለከለው በሟርት፥ በጥንቆላ፥ በአስማተኛነት ሥራ ላይ መሰማራት ማለት ነው (ኢሳ. 8፥19)፡፡
ሦስተኛ፡- ከኢዮብ አጽናኞች አራተኛው ኤሊሁ ግን ለሰው አማላጅ ሆኖ ሊቆም ስላለው ከአእላፋት ሁሉ ምርጥ ስለሆነው፥ ቤዛ በመክፈልና ሰው የሚከሰስበትን ኀጢአት በማስወገድ ቤዛውን ከፍያለሁና ኀጢአተኛውን ይቅር በለው በማለት ወደ እግዚአብሔር ለመማለድ መካከለኛ ሆኖ ስለሚገለጠው ስለ አንዱ ልዩ መልአክ ተስፋ ለኢዮብ ነገረው፡፡ በመልአከ እግዚአብሔር አምሳያ በብሉይ ኪዳን የተገለጸው ያ መልአክም ለቃልነቱ ከዊን (ቃል ለመሆኑ) እና ለተወላዲነቱ ተስማሚ ሆኖ በተሰጠው በመልእከተኛነት ስም የተገለጸው ወልደ እግዚአብሔር ቃል በሥጋዌ ስሙም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በቤዛነቱ ኀጢአትን ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል በማስወገድ ኹለቱን እርስ በርስም ያስታረቀና ሰላምን ያስገኘ ብቸኛ መካከለኛ ነው (ኢዮ. 33፥23-28፤ ኢሳ. 53፥10-12፤ ሚል. 3፥1፤ ሉቃ. 23፥34፤ ኤፌ. 2፥13-17)፡፡



በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment