ባለፈው ዕትም ስለ መካከለኛነቱ
ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን፥ በተግባርም እየጸለየ፣ እየለመነና እየማለደ ያሳየውን፥ በዝርዝር ተመልክተናል። አብም፣
ወልድም፣ መንፈስ ቅዱስም ይማልዳሉ የሚል ንባብ በመጽሐፍ ቅዱስ አለና፥ ሦስቱም ይማልዳሉ ከተባለ ወደ ማን ነው የሚማልዱት? በሚል
አንዳንዶች ለሚያነሧቸው ክርክሮችም መልስ ለመስጠት ተሞክሯል።
የዚህን ትምህርት እውነተኛነት
ለማረጋገጥ ከራሱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ ማንም ሊናገር አይችልም። ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይም ሌላ ምስክር አይኖርም። ይሁን
እንጂ ይህ ጌታችን ያስተማረው፣ ሐዋርያትም ከእርሱ ተቀብለው ያስተላለፉት እውነተኛ ትምህርት፥ ከእነርሱ በኋላ በተነሡ አበው ዘንድም
የታወቀ መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ይህን የምናደርገው የእነዚህ አበው ምስክርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተመዘገበው የጌታችን
ትምህርት፣ ከእርሱ ተቀብለው ሐዋርያት ከሰጡትም ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር ሆኖ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን ብቸኛ
መካከለኛ ነው የሚለው ትምህርት “እንደ ውሃ ፈሳሽ፣ እንደ እንግዳ ደራሽ” በድንገት ብቅ ያለ ዐዲስ ትምህርት ሳይሆን፣ ከጥንት
የነበረ፣ በአበውም ትምህርት ውስጥ በስፋት የተንጸባረቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መሆኑን ለማሳየትም ጭምር ነው።
በዚህ ዕትም ሊቃውንት በክርስቶስ
መካከለኛነት ዙሪያ የሰጧቸውን ምስክርነቶች በጥቂቱ እናቀርባለን። እነዚህ ምስክርነቶች በየመጻሐፍቱ ውስጥ ተበትነው የሚገኙ ናቸው።
እዚህ ላይ ሰበሰብ አድርገንና መልክ ሰጥተን በአንድነት ማቅረባችን የክርስቶስን መካከለኛነት ሊቃውንቱ እንዴት አድርገው እንደ ገለጡት
ለማሳየት ይረዳል ብለን ዐስበናል።
ክርስቶስ መካከለኛ ይሆን ዘንድ ለምን አስፈለገ?
ከሰው ወገን አስታራቂ የሚሆን
ንጹሕ ሰው (ሕግን ሁሉ የፈጸመና በኀጢአት ከቶ የማይጠየቅ ሰው) ስላልተገኘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[እግዚአብሔር] ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ፤
ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኀኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው” ይላል (ኢሳ. 59፥11-16)። እንዲሁም “የምበቀልበት ቀን
በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና። ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም የሚያግዝም አልነበረምና
ተደነቅሁ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኀኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ።” (ኢሳ. 63፥4-5) ይላል።
ይህን መሠረት አድርጎ ሊቁ ቄርሎስ እንዲህ አለ፤ “ወኢሳይያስኒ ነቢይ ይቤ አኮ ውእቱ መተንብል
ወኢመልአክ አላ ለሊሁ እግዚእ ዘመጽአ ወአድኀነነ ወኢያድኀነነ በደም ነኪር ወኢበሞተ ብእሲ አላ በደሙ ባሕቲቱ። - ነቢዩ ኢሳይያስም
ሰው ሆኖ ያዳነን እርሱ ራሱ ጌታ ነው እንጂ ሌላ አማላጅ ወይም መልአክ አይደለም።
በባዕድ ደም በዕሩቅ ብእሲም ሞት አላዳነንም።
ራሱ በደሙ አዳነን እንጂ” ይላል (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 77 ክፍል 46 ቁ 13፤ ኢሳ. 63፥9ን ግእዙን ተመልከት)።
ከሰው ወገን ንጹሕ አስታራቂ መታጣቱ ብቻ
አይደለም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ተገቢ አስታራቂም አልተገኘም ነበር።
በመጽሐፈ ምዕላድ የተጻፈው ይህን ያስረዳል፤ “እምቅድመ ይሠጎ ተኀጥአ ንጹሕ ዐራቂ እምክልኤ ጾታ እምይእዜሰ ይደልዎ ይስረይ ኀጢአተ
ምስለ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ በመለኮቱ እስመ ተረከበ ንጹሐ ዐራቄ ወመተንበለ በትስብእቱ። - ሥጋ ከመልበሱ በፊት በሁለቱም ወገን
ንጹሕ የሆነ አስታራቂ ታጥቶ ነበር።
ከእንግዲህ ወዲህ ግን በመለኮቱ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ ኀጢአትን ይሰርይ ዘንድ ተገብቶታል።
በሰውነቱ ንጹሕ አስታራቂና የሚጸልይ ሆኗልና።”
(ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ ገጽ 112)።
ኤጲፋንዮስም፥ ጌታ አስታራቂ
ሆኖ በመምጣቱ የቀደሙ አስታራቂዎች የነበረባቸውን ጒድለት ያሟላ መካከለኛ ነውና፥ ቤዛ (ምትክ ሆኖ የሚሞት) እና አዳኝ መሆኑን
አስረድቷል። እንዲህ በማለት፥ “ወበእንተ ዝንቱ እግዚእ መጽአ ወተሠገወ እም እጓለ እመ ሕያው፤ ወኮነ እግዚአብሔር ቃል ሰብአ ከመ
የሀበነ መድኀኒተ በመለኮቱ፤ ወይሙት ቤዛነ በትስብእቱ። - ጌታ ከወዲያ
ዓለም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከሰው ወገን ተወለደ፤ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ። አምላክ በመሆኑ ያድነን ዘንድ፣ ሰው በመሆኑም ቤዛ
ሆኖ ይሞትልን ዘንድ” (ሃይ. አበ. ም. 58 ክ.13 ቁ 50)።
ቅዱስ ቄርሎስም እንደዚሁ ክርስቶስ በአምላክነቱ
ኀጢአትን ሁሉ የሚያስተሰርይ ሲሆን፥ በሰውነቱ ደግሞ የዐዲስ ኪዳን አስታራቂ ሆኗል ይላል። “ወውእቱ መዋኤ ኵሉ ኀጢአት በመለኮቱ
ኮነነ ሊቀ ካህናት በትስብእቱ - በመለኮቱም ኀጢአትን ሁሉ የሚያጠፋ እርሱ ሰው በመሆኑ አስታራቂ ሆነን” (ሃይ. አበ ምዕ.
79 ክፍ. 50 ቁ. 68)።
“ክርስቶስ አስታራቂ ሆነ” የሚለው አነጋገር
እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል ብለው ለሚሠጉ ሰዎች፥ አስታራቂ የሆነው በሰውነቱ መሆኑን ሊቃውንቱ ደጋግመው ተናግረዋል። ለምሳሌ፥
ዮሐንስ አፈወርቅ፥ “ወኢተናገረ በዝየ በእንተ ህላዌ መለኮት አላ ተናገረ በእንተ ሥርዐተ ትስብእት እስመ ትስብእቱ ግቡር ውእቱ።
- በዚህ አንቀጽ ስለ ባሕርየ መለኮት አልተናገረም፤ አምላክ ሰው ስለ መሆኑ ሥርዐት ተናገረ እንጂ ሥጋ ፍጡር ነውና።” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 63፣ ከፍል
2፣ ቊጥር 28)።
ቄርሎስም በበኩሉ፥ “ይህ ነገር ፍጡር
የሚል እንደሚመስል ነገሩ ግልጽ ነው። ይህም ሰው ስለ መሆኑ እንጂ ለሌላ አልተነገረም። እርሱ የባሕርይ አምላክ ሲሆን ሰው በመሆኑ
ከአብ ክብርን ይቀበላል” ብሏል (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 79 ከፍል 50 ቊጥር 74)።
ከሰው ወገን ብቻም ሳይሆን ከመላእክትም
ወገን እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ የጠፋ መሆኑን ከነምክንያቱ ሲያስረዳ ጵርቅሎስ የተሰኘ አባት እንዲህ አለ፤ “ብእሲሰ
ትሑት አድኅኖ እምኢክህለ እስመ ውእቱሂ ይፈዲ ምስሌነ ዕዳ ወመልአክሂ ኢክህለ ተሣይጦተነ እስመ አልቦቱ ቤዛ ሥጋ በዘይትቤዘወነ።
- ወራዳው ሰው የገዛ ራሱ ከእኛ ጋር ዕዳን ስለሚከፍል ሊያድነን ባልቻለም፤ መልአክም ቢሆን ስለ እኛ ቤዛ የሚሆንበት ሥጋ ስለማይኖረው
ሊዋጀን አልቻለም” (ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ ገጽ 150)።
ቅዱስ መጽሐፍ መዳን
በኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ በሌላ በማንም የለም ይላል (ሐ.ሥ. 4፥12)። መዳናችን በእርሱ ብቻ የሆነው ተስፋችን በዕሩቅ ብእሲ
(በሰው ብቻ) ሳይሆን፥ ሰው በሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንዲሆን ነው። በፍጡር መታመንና ፍጡርን ተስፋ ማድረግ
ርጉም ያደርጋልና። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ አለ፤ “ወሕይወትነሂ ኢኮነ በሰብእ፤ ወኢእምነትነ በሰብእ፤ እስመ
ይቤ መጽሐፍ ይኩን ርጉመ ዘይትአመን በእጓለ
እመ ሕያው፤ ... ወኢክህለ መኑሂ እም ኲሉ ዘኮነ እም አዳም እስከ ይእዜ ይግበር መድኀኒተ ዘእንበለ እግዚአብሔር ቃል ከመ ኢይኩን
ተስፋነ ሙሱነ። - ድኅነታችንም በዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ እምነታችንም በዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ መጽሐፍ በዕሩቅ ብእሲ የሚያምን
ርጉም ይኹን ብሏልና። ... ከአዳምም ጀምሮ
እስከ ዛሬ ከተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ማንም ማን ሊያድነን አልቻለም፤ ከእግዚአብሔር ቃል (ከኢየሱስ ክርስቶስ) በቀር፤ በሰው
ቢሆን አለኝታችን ከንቱ እንዳይሆን።” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 58፣ ክፍል 13፣ ቊጥር 46፡49፤ መዝ. 59/60፥11፤
ኤር. 17፥5)
በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን
መካከለኛ መሆን ያስፈለገው በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት መካከለኞች ጒድለት ስለ ነበረባቸውና እግዚአብሔርንና ሰውን በፍጹምነት
ማስታረቅ ስላልቻሉ ነው። “… ከአቤል ደም ጀምሮ እስከ በራክዩ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ [በግፍ የፈሰሰው] የቅዱሳን ነቢያት
ደም ዓለምን ለማዳን እንዳልጠቀመ ባየ ጊዜ ቤዛ መድኀኒት የሚሆን ልጁን ሰደደልን። ፈጽሞ ያድን ዘንድ” እንዳለ መጽሐፈ ቅዳሴ (ዘኤጲፋንዮስ
ቊጥር 43)። በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት እግዚአብሔርና ሰው ስለ ታረቁ፥ ከሰው የሚጠበቀው ይህን ዕርቅ መቀበል፥ በቀጣይም
አንድ ጊዜ በተከናወነው በዚህ ዕርቅ መሠረት ስለ ኀጢአቱ ንስሓ እየገባና ዘወትር እየታረቀ መኖር ነው እንጂ ሌላ መካከለኛ መሾም
አይችልም። ልሹም ቢልም የኢየሱስን መካከለኛነት ማቃለሉ ነው። ወደ ፍጻሜው መጓዝ ሲገባው ወደ ቀድሞውና ፍጹም መዳን ወዳልተገኘበት
የኦሪትን ወደ መሰለ ሥርዐት መመለሱ ነው።
ክርስቶስ በመካከለኛነቱ ምን አደረገ?
ሊቁ ቄርሎስ እንዲህ አለ፤ “ዛሬስ በምን
ሁኔታ በእግዚአብሔር ፊት ተገለጠ (ታየ)? አምላክ የሆነ ቃል እንደኛ ሰው ሆኖ በዐዲስ ሥራ ታየ። ዛሬ ስለ እኛ በእግዚአብሔር
ፊት በእኛ ባሕርይ በአስታራቂነት ታየ። ... ዛሬ ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ታየ የምንናገረው ነገር ይህ ነው። በአዳም
ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ተዋርዶ የነበረ የሰውን ባሕርይ ገንዘብ አድርጎ በአባቱ በእግዚአብሔር ፊት ገልጦለታልና በገንዘቡ ግብር
በእግዚአብሔር አብ ፊት አቆመው፤ ቀድሞ እንደ ነበረው አይደለም፤ ሰው ሆኖ ታየ እንጂ፤ ዳግመኛ ወደ አባቱ ያስገባን ዘንድ” (ሃይማኖተ
አበው ምዕራፍ 79፣ ክፍል 50፣ ቊጥር 72-73)።
ከዚህ የቄርሎስ ትምህርት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ
በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ በአስታራቂነት መታየቱን እንገነዘባለን። በእግዚአብሔር ፊት መታየት የሚለው ሐሳብ አስቀድሞ በዕብራውያን
መልእክት ውስጥ ተገልጿል (ዕብ. 9፥24፡28)። ጌታ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ የታየው የእኛን ኀጢአት ተሸክሞ የኀጢአታችንን
ዕዳ መክፈሉንና ወደ እግዚአብሔር ለመግባት ባለ መብቶች ያደረገን መሆኑን ያመለክታል።
ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ
ሆኖ ያከናወናቸው በተለይ ሁለት ተግባራት አሉ። እነርሱም መጸለይና መሥዋዕት ማቅረብ ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ
እነዚህን የመካከለኛ ተግባራት ማከናወኑን አበው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ተናግረዋል። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ
የተጻፈውን የሊቀ ካህናትነቱን ጸሎት መሠረት በማድረግ፥ ጌታችን ኢየሱስ ስለ መጸለዩና ስለ መማለዱ መጽሐፈ ቅዳሴ መስክሯል። “አንቃዕደወ
ሰማየ ኀበ አቡሁ ወአስተምሐረ ወላዲሁ ወአማኅጸነ አርዳኢሁ ከመ ይዕቀቦሙ እምኵሉ እኵይ። - ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ቀና ብሎ አየ፤
ወላጅ አባቱንም ማለደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ከክፉው ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ አደራ አስጠበቀ።” (ቅዳሴ ማርያም ቊ 103)።
አሁንም ቄርሎስ እንዲህ ሲል መስክሯል።
“ወሰአሎ ለአብ ያኅልፍ እምኔነ መዓተ ዘረከበነ እምቅድም ከመ ዘለሊሁ ይኌልቍ ስዕለተ ሎቱ እስመ ውእቱ ነሥአ አምሳሊነ ከመ ይስአሎ
ለአብ በእንቲኣነ ከመ ምዕረ ዳግመ ይዝክረነ ወኢይኅድገነ እምኔሁ። - እርሱ ለራሱ ልመናን የሚሻ መስሎ ከጥንት ጀምሮ ያገኘንን
ፍዳ ከእኛ ያርቅ ዘንድ አብን ማለደው። እንደ ገና ደግሞ እንዲያስበን ከእርሱም እንዳይለየን ስለ እኛ አብን ይማልደው ዘንድ ባሕርያችንን
ነሥቷልና” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 79 ክፍል
50 ቊጥር 38)።
ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ መጸለይ
ብቻ ሳይሆን ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ አንድን መሥዋዕት ለዘለዓለም በማቅረብም መካከለኛነቱን አሳይቷል (ዕብ. 10፥12)።
“… ዝ ውእቱ ዘእግዚአብሔር ቃል ዘተሰብአ
እምኔኪ ዘአዕረገ ለአቡሁ ርእሶ ዕጣነ ወመሥዋዕተ ሥሙረ። ንሰግድ ለከ ክርስቶስ ምስለ አቡከ ኄር ሰማያዊ ወመንፈስከ ቅዱስ ማኅየዊ
እስመ መጻእከ ወአድኀንከነ። - ራሱን ዕጣንና የተወደደ መሥዋዕት
አድርጎ ወደ አባቱ ያሳረገ ከአንቺ (ከድንግል ማርያም) ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። ክርስቶስ ሆይ፥ ከሰማያዊ አባትህና
አዳኝ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንሰግድልሃለን። መጥተህ አድነኸናልና።” (መጽሐፈ ቅዳሴ ገጽ 26፣ ቊጥር 122፣ ውዳሴ ማርያም
ዘእሑድ)።
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀርም የታመነ
አስታራቂ እንደሌለ፥ ኢየሱስም ከራሱ በቀር ያቀረበው ሌላ መሥዋዕት እንደሌለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፤ “መኑ
ውእቱ ሊቀ ካህናት ወምእመን ዘእንበሌሁ ዘይክል ለሊሁ ባሕቲቱ ሰራዬ ኀጢአት ወምንት ውእቱ መሥዋዕት ዘአዕረጎ በእንተ ዝንቱ ሥርዐት
ዘእንበለ ሥጋሁ ባሕቲቱ ዘነሥኦ በእንተ ዝንቱ ግብር። - ከእርሱ በቀር ራሱ ብቻውን ኀጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ
ማነው? ለማስታረቅ ኀጢአትን ለማስተስረይ ያቀረበው መሥዋዕትስ ምንድነው? መሥዋዕት ለመሆን የነሣው ሥጋው ብቻ ነው እንጂ።” (ሃይማኖተ
አበው ምዕራፍ 62 ክፍል 2 ቊጥር 14)።
መካከለኛነቱ ምን አስገኘልን?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛነቱ
ያቀረበው ጸሎትና ያሳረገው መሥዋዕት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ፍጹም ዕርቅን አውርዷል። ከሰው የሚጠበቀው ይህን ዕርቅ መቀበልና
ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው። ኢየሱስ ወደ አብ የሚወስደውን ዐዲስና ሕያው የሆነ መንገድ በከበረ ደሙ መርቆ ከፍቷልና፥ (ዕብ.
10፥19-22) በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ንስሓ በመግባትና እርሱ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት አማካይነት የኀጢአታቸውን ስርየት በመቀበል
የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ይችላሉ። በእርሱ በኩል አምነው ወደ እግዚአብሔር ለሚመጡት የመዳን ምክንያት ሆኖላቸዋል (ዕብ.
5፥9-10)። ጌታ ኢየሱስ በሠራው የቤዛነት ሥራ ያመኑበትን ወደ አብ ለመግባት ድፍረት እንዲያገኙ አድርጓል (ኤፌ. 2፥18፤
3፥12)። በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛነቱ ያመኑበትን ወደ እግዚአብሔር አቅርቧል። መካከለኛነቱ ያስገኘው ዋና ነገርም
ይኸው ነው። ጥንታውያን አበው ከሰጡት ምስክርነት የሚከተሉትን እንመልከት።
“ያጽምእ ዘንተ ውስጡ ለሰብእ ክርስቶስ
ፀመደነ ለኀበ አቡሁ አቅረበነ መጺኦ እም ድኅረ ሐመ ወወሪዶ ውስተ ሲኦል ዘውእቱ ነፍሳተ ምዉታን ጼወዎ ለሕይወት። - ይህን [የምሥራች]
የሰው ውስጣዊ ጆሮ ያድምጥ፤ ክርስቶስ ገዛን ወደ አባቱም አቀረበን። ወደዚህ ዓለም መጥቶ መከራን ከተቀበለ በኋላ ወደ ሲኦል ወርዶ
የሞቱ ነፍሳትን በሕይወት እንዲኖሩ ምርኮ አድርጎ አወጣቸው።” (ትምህርተ ኅቡኣት)።
“ፍቅረ ለነ ኀበ አቡከ ገበርከ ወዐረቀ
ማእከሌነ። - ከአባትህ ዘንድ ፍቅርን አደረግህልን፤ በመካከላችንም (በእግዚአብሔር እና በእኛ መካከል) ሆነህ አስታረቅኸን” (መጽሐፈ
ኪዳን)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛነቱ
ከእግዚአብሔር ርቀን የነበርነውን ወደ እግዚአብሔር አቅርቦናል። ይህን በተመለከተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዲህ ሲል መስክሯል።
“ወዘሰ ይቤ አቅረበነ ሎቱ ያጤይቅ ግብረነ እስመ ህላዌ እጓለ እመሕያው ተፈልጠ እም እግዚአብሔር በኲሉ ዘመን ቅዱሳን አበው ወነቢያት
ወሕግ ኲሎ ዘሀሎ እምቅድሜሆሙ ወእም ዐለወ አዳም ኢክህለ መኑሂ እምእሉ ኲሎሙ ያቅርበነ ሎቱ። - ወደ እርሱ አቀረበን ያለው ርቀን መኖራችንን ያስረዳል። የሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር
ተለይቶ ነበርና በደጋጎች አበው በነቢያት በኦሪት ከእርሱ አስቀድሞ በነበረው ዘመን ሁሉ አዳምም ከበደለ ጀምሮ ከእነዚህ ሁሉ ወደ
እርሱ ሊያቀርበን ማንም ማን አልቻለም ነበር (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 68፣ ቊጥር 17)።
መካከለኛነቱ እስከ መቼ ነው?
ክርስቶስ ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ
ነው። ዐዲስ ኪዳንም በክርስቶስ ደም የተመሠረተና አሁን የምንገኝበት ኪዳን ነው። የዚህ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
መካከለኛነቱ አንድ ጊዜ የተፈጸመና ዛሬም ለወደ ፊቱም እስከ ምጽአት ድረስ የሚሠራ እንደ ሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል። ይሁን
እንጂ ለአንዳንዶች መካከለኛነቱ ያለፈ ድርጊት ብቻ ይመስላቸዋል። የጥንት ጽሑፎች ግን ያለፈ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ወደ ፊትም እስከ
ምጽአቱ ድረስ የሚያገለግል መሆኑን ይመሰክራሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የብሉይ ኪዳንን
ሊቃነ ካህናት ከክርስቶስ ጋር በማነጻጸር የእነርሱ መካከለኛነት በሞት የተገደበ፥ የክርስቶስ ግን ቀጣይነት ያለውና እስከ ምጽአት
ድረስ የሚያገለግል መሆኑን ተናግሯል፤ እንዲህ በማለት፥ “ወበዝየሰ ለእመ ኮነ ሊቀ ካህናት
ዐቢይ ውእቱ እስከ ጊዜሁ፤ ዘአመ ኮነ ሳሙኤል ወእለ ከማሁ። በደኃሪሰ
አልቦ። እስመ እሙንቱ ሞቱ። ወበዝየሰ አኮ ከማሁ። አላ ዘልፈ ያድኅን በኲሉ ጊዜ፤ ... ወከማሁ ውእቱ አኮ ዘያድኅኖሙ ለእለ ይቀርቡ
ኀበ እግዚአብሔር ባሕቲቱ እመንገሌሁ በዝየ አላ ወበከሐከኒ። - በዚህኛው (በብሉይ ኪዳን) ታላቅ ካህናት ቢኖር፣ ታላቅ መባሉ እስከ ጊዜው ድረስ ነው። ሳሙኤል እስከ ጊዜው ድረስ እንደ
ኖረ፣ እንደ እርሱ ያሉትም ካህናት እስከ ጊዜው ድረስ እንደ ኖሩ፣ በኋላ ግን ታላቅ ሊቀ ካህናት መባላቸው የለም፤ ቀርቷል። በዚህኛው
(በዐዲስ ኪዳን) ሊቀ ካህናት በኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ሁል ጊዜ ለዘላለም ያድናል እንጂ። በእርሱ አስታራቂነት
በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን የሚያድናቸውም፣ በዕለተ ዐርብ ብቻ አይደለም፤ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ለዘላለምም ነው እንጂ
(13ኛ ድርሳን ቊጥር 138-144፡147-148)።
ይኸው ሊቅ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የዕብራውያንን
መልእክት በተረጐመበት 13ኛ ድርሳኑ ቊጥር 156 ላይ፥ “ወጊዜ ፈቀደ ይተነብል ሎሙ አኮ በዝንቱ ጊዜ ባሕቲቱ አላ በእንተ ዘትመጽእ
ሕይወት ዘለዓለም - በወደደ ጊዜ ይለምንላቸዋል፤ በዚህ ጊዜ (በዕለተ ዐርብ) ብቻም አይደለም። ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ ለዘላለም
ነው እንጂ” በማለት ከዕለተ አርብ በኋላ እስከ ዘላለም (ዳግም ምጽአት) ድረስ መሆኑን አስረድቷል።
ቅዱስ ቄርሎስም እንዲህ ብሏል፤ “ወሰአሎ
ለአብ ያኅልፍ እምኔነ መዓተ ዘረከበነ እምቅድም ከመ ዘለሊሁ ይኌልቍ ስዕለተ ሎቱ እስመ ውእቱ ነሥአ አምሳሊነ ከመ ይስአሎ ለአብ
በእንቲኣነ ከመ ምዕረ ዳግመ ይዝክረነ ወኢይኅድገነ እምኔሁ። - እርሱ ለራሱ ልመናን የሚሻ መስሎ ከጥንት ጀምሮ ያገኘንን ፍዳ ከእኛ
ያርቅ ዘንድ አብን ማለደው። እንደ ገና ደግሞ እንዲያስበን ከእርሱም እንዳይለየን ስለ እኛ አብን ይማልደው ዘንድ ባሕርያችንን ነሥቷልና”
(ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 79፣ ክፍል 50፣ ቊጥር 38)።
ቅዱስ ያሬድም በድጓው የክርስቶስ አስታራቂነት
እስከ መስቀል ላይ ሞት ድረስ ብቻ ሳይሆን ከትንሣኤውና ከዕርገቱም በኋላ የቀጠለ መሆኑን መስክሯል (ሮሜ 8፥34፤ ዕብ. 7፥25፤
1ዮሐ. 2፥1)።
“ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአርዳኢሁ አዐርግ ኀበ
አቡየ ወእስእሎ በእንቲኣክሙ - ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ አባቱ ዐርጋለሁ ስለ እናንተም አለምነዋለሁ አላቸው”
(የፋሲካ ድጓ ገጽ 291 3ኛው ዐምድ ላይ)።
“ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአርዳኢሁ አዐርግ ሰማየ
ኀበ አቡየ ኀበ እስእል ምሕረተ በእንተ እሊኣየ - ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የኔ ስለ ሆኑት ምሕረትን ወደምለምንበት ወደ አባቴ ወደ
ሰማይ ዐርጋለሁ አላቸው።” (የሠኔ
ሚካኤል ዚቅ (ዓራራይ)
ቅዳሴ አትናቴዎስም፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ዛሬም መካከለኛ እንደ ሆነ ቈጥሮ፥ “ወልድ ሆይ እንደ ታመመ ሰው አሰምተህ ተናገር። ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ በል። በአፋቸውም ውስጥ
ሳለ አባ አባቴም ሆይ፥ ሥጋዬን የበሉትን ደሜን የጠጡትን ማራቸው፤ ይቅር በላቸው በል።” በማለት ይማጸነዋል (መጽሐፈ
ቅዳሴ ገጽ 119፣ ቊጥር 144)።
ክርስቶስን የሚተካ ሌላ መካከለኛ አለን?
ከላይ በተመለከትናቸው የአበው
ምስክርነቶች ውስጥ፥ የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው በመሆኑ እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት መካከለኛነቱ በሞት
የሚገደብ አይደለምና፥ ዛሬም መካከለኛው እርሱ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን ባለማስተዋል የእርሱ መካከለኛነት እንዳበቃ
እና/ወይም በሌሎች ፍጡራን “መካከለኞች” እንደ ተተካ ያምናሉ፤ ያስተምራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሚተካው የሌለ የዐዲስ ኪዳን
ብቸኛው መካከለኛ ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህን አስመልክቶ
የሚከተለውን ብሏል፤ “ወእመሰ ኢኮነ አሐደ ውእቱ እም ኢኮነ ዘኢይመውት ወእልከቱሰ ካህናት ኮኑ ብዙኃነ መዋትያን እሙንቱ ከማሁኬ
ዝንቱ አሐዱ በእንተ ዘኮነ ዘኢይመውት ይቤ እስመ ይክል አድኅኖቶሙ ለዝሉፉ እለ ይቀርቡ ኀበ እግዚአብሔር እንተ መንገሌሁ እስመ
ለግሙራ ሕያው ውእቱ ወይተነብል ሎሙ። ጠየቀኑ ኦ ፍቁር ከመ ብሂሎቱ ኮነ በእንተ ሣጋዌሁ … እመሰኬ ካህን ውእቱ አሜሃ ይተነብል።
… ይቤ እስመ ይክል አድኅኖቶሙ ለዝሉፋ እስመ ሕያው ውእቱ ለዓለም ወአልቦ ተውላጥ እምድኅሬሁ።”
ትርጓሜ፥ “እርሱ አንድ ባይሆን ኖሮ የማይሞት
ባልሆነም ነበር። የኦሪት ካህናት ግን የሚሞቱ ስለ ሆኑ ብዙ ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ ይህ አንድ የሆነው የማይሞት ስለ ሆነ ነው።
ሐዋርያው በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ዘወትር ሊያድናቸው ይችላልና፤ ለዘላለም የማይሞት ሕያው ስለ ሆነ ስለ እነርሱም
ይማልድላቸዋል። ወዳጅ ሆይ ይማልድላቸዋል ብሎ ያለው ሰው ስለ መሆኑ እንደ ሆነ ተረዳህን? ሊቀ ካህናት በመሆኑ ያን ጊዜ ይማልድላቸዋል
አለ … ለዘላለም ሕያው ስለ ሆነ ለዘወትር ያድናቸው ዘንድ ይችላልና አለ። ከእርሱ በኋላም የሚተካ የለም።” (ድርሳን ዘዮሐንስ
አፈ ወርቅ 13ኛ ድርሳን ቊጥር 129-131፡135-136)።
በርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የሐዲስ ኪዳን
መካከለኛ አንድ፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ይናገራል (1ጢሞ. 2፥5-6)። ለምን ይሆን ሰዎች የእርሱን መካከለኛነት
አንቀበልም ብለው ሌሎች መካከለኞችን መሰየም ያስፈለጋቸው? አንዱ
ምክንያት ዛሬም እርሱን መካከለኛ ነው ካልን የእርሱ ክብር ዝቅ ይላል የሚል እንደ ሆነ ይታወቃል። ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን “ለዚህ
ሐሳብ አይግባችሁ” ይላል። “ወዳጅ ሆይ ይማልድላቸዋል ብሎ ያለው ሰው ስለ መሆኑ እንደ ሆነ ተረዳህን? ሊቀ ካህናት በመሆኑ ያን
ጊዜ ይማልድላቸዋል አለ” ሲልም ምላሽ ይሰጣቸዋል።
የኢየሱስ መካከለኛነት ለእኛ ምን አስገኘልን?
እያንዳንዱ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር
ለመቅረብ መካከለኛ እንደሚያስፈልገው ያውቃል። መካከለኛ እንደሚያስፈልገው ብቻ ሳይሆን መካከለኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑንም
መቀበል አለበት። የሊቀ ካህናት ኢየሱስን መካከለኛነት ክዶ በእርሱ ምትክ ሌሎች መካከለኞችን ካቆመ ግን፥ ወደ አብ ከሚወስደው መንገድ
ወጥቶ ወደ አብ በማያደርሱ መንገዶች ላይ እየተጓዘ መሆኑንና ወደ አብ እንደማይደርስም ሊገነዘብ ይገባል። ምክንያቱም፥ ራሱ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም”
ሲል ተናግሯል (ዮሐ. 14፥6)። ከጥንት አበው አንዱ ቄርሎስም ይህንኑ ደግሞ ተናግሯል። “አልቦ መኑሂ ዘይክል በጺሐ ኀበ እግዚአብሔር
ዘእንበለ ወልድ - ያለ ወልድ ወደ እግዚአብሔር መድረስ የሚቻለው ማንም የለም።” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 76፣ ከፍል
36፣ ቊጥር 8)። መጽሐፈ ሰዓታት እና መጽሐፈ ቅዳሴም፥ “ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ።
- ኢየሱስ ክርስቶስ ወደአባቱ የሚያደርስ መንገድ፥ ወደወለደውም የሚያስገባ በር ነው።” ሲሉ መስክረዉለታል።
የዐዲስ ኪዳን ብቸኛው መካከለኛ ሊቀ ካህናት
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሆነ፥ ክርስቲያኖች በእርሱ በኩል ብቻ (በስሙ) እንዲጸልዩ (ዮሐ. 16፥23-24)፣ በእርሱም በኩል ብቻ
(በስሙ) ለእግዚአብሔር ምስጋናን እንዲያቀርቡ (ቈላ. 3፥17፤ ዕብ. 13፥15፤ ያዕ. 3፥9) መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ስለዚህ በመካከለኛነቱ በኩል (በስሙ) ልንጸለይና
እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል፤
“ይቤ ወናቀርብ ናሁ ሎቱ መሥዋዕተ ለእግዚአብሔር
እመንገለ ዐራቅይናሁ መሥዋዕት ዘይቤ ፍሬ ከናፍር ውእቱ እለ ይትአመኑ በስሙ ወእሉሰ አቅረቡ አባግዐ ወአልህምተ ወንሕነኒ ኢናበውእ
ምንተኒ እም እሉ ግብራት አላ አኰቴተ … እስመ እግዚአብሔር ይሠምር በዘከመዝ መሥዋዕት መፍትው ለነ ናብእ ሎቱ ዘከመዝ መሥዋዕተ
ከመ ያብእ ውእቱኒ ለአብ ወኢይትከሀል ያቅርቡ ምንተኒ በእንበለ በዐራቅይናሁ ለወልድ”
ትርጓሜ፥ “በወልድ አስታራቂነት በኩል
ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን እናቅርብ አለ። መሥዋዕት የሚለው ስለ ስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ ነው። እነርሱም (የኦሪት ካህናት)
ላሞችንና በጎችን ሰዉ። እኛ ግን ከእነዚህ መካከል ምንም ምን አናቀርብም፤ ምስጋናን እንሠዋለን እንጂ። እንዲህ ባለው መሥዋዕት
እግዚአብሔር ደስ ይሰኛልና። እንደዚህ ያለውን መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ ይገባናል። እርሱም (ወልድ) ለአብ ያቀርብ ዘንድ፤ ያለ
ወልድ አስታራቂነት ምንም ምን ያቀርቡ ዘንድ አይቻልም።” (33ኛ ድርሳን ከቊጥር 209-218)።
በመሆኑም ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ
የሚገባንና የምንችለው በጌታችን ስም ነው። ያለ እርሱ ስም መጸለይም ሆነ እግዚአብሔርን ማመስገን አንችልም፤ መንገዱ እርሱ፥ በሩም
እርሱ ነውና። በኢየሱስ ስም ስንጸልይ እርሱ መካከለኛችን መሆኑንና ወደ እግዚአብሔር መጸለይም ሆነ እርሱን ማመስገን የቻልነው በኢየሱስ
ክርስቶስ የቤዛነት ሥራ እንጂ በራሳችን ብቃት እንዳልሆነ ማመናችንና መመስከራችን ነው። ይህን እውነት የተረዱ አበውም ጸሎታቸውንና
ምስጋናቸውን ወደ እግዚአብሔር ያሳርጉ የነበረው በኢየሱስ ስም ነው። በጽሑፍ ከተላለፉ የአበው ጸሎቶች መካከል ሊጦን፣ መስተብቊዕ፣
ዘይነግሥ፣ የመሳሰሉት ጸሎቶች የሚደመደሙት “በአሐዱ ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ… - በአንድ ልጅህ በጌታችን ኢየሱስ…” በሚል ተማኅጽኖ
ነው።
በመጽሐፈ ሰዓታት ላይ እግዚአብሔር አብ
በኢየሱስ ስም ይለመናል፤ እንዲህ ተብሎ፥ “ኦ! አብ በእንተ ኢየሱስ ርድአነ ክርስቶስ ኀበ አቡከ ኄር አማኅጽነነ - አብ ሆይ ስለ
ኢየሱስ ብለህ ርዳን፤ ክርስቶስም በቸር አባትህ ዘንድ ዐደራ አስጠብቀን።”
መጽሐፈ ቅዳሴም እግዚአብሔር አብን በኢየሱስ
ስም ያመሰግናል። “ነአኲተከ እግዚኦ በፍቁር ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ - አቤቱ በተወደደው ልጅህ በጌታችን ኢየሱስ [ስም] እናመሰግንሃለን”
(መጽሐፈ ቅዳሴ ገጽ 44፣ ቊጥር 2)።
ይህ በአጋጣሚ የሆነ ወይም እንደ አማራጭ
የቀረበ ስም ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘና አበውም ያስተላለፉት እግዚአብሔርን የምንለምንበትና የምናመሰግንበት፥ ወደ እርሱም
የምንጸልይበት ብቸኛ ስም ነው። ኢየሱስ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው። “እርሱ [ኢየሱስ] በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር
ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ
አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር
እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ
ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊል.
2፥6-11)። ማንኛውም ክርስቲያን የኢየሱስን መካከለኛነት አምኗል፤ ተቀብሏል የሚባለው፥ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ባከናወነው የማዳን
ሥራው ዛሬም መካከለኛዬ ነው ብሎ በቃልም ይሁን በሥራ የሚያደርገውን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም ሲያደርግ ነው (ቈላ. 3፥17)።
በኢየሱስ ስም እንዲጸልይ፥ እንዲንበረከክና እግዚአብሔርንም ስለ ሁሉ ነገር በኢየሱስ ስም እንዲያመሰግን ታዟል።
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 43 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment