Saturday, March 31, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

                                                             በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
PDF:በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

በቊጥር 2 የጮራ ዕትም እንደ ተገለጸው፥ የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን “ኩሽ” ሲል ከካም ልጆች አንዱ የሆነው የኩሽ ነገድ በባለቤትነት ለሰፈሩባት የመሬት ክልልና ለነዋሪዎችዋ ለራሳቸው የሰጠው ስም እንደ ሆነ አንብበናል። ብሉይ ኪዳንን ወደ ጽርእ የተረጐሙት ሊቃውንት ኩሽ የሚለውን ቃል “ጥቊር” የሚያሰኝ ትርጕም እንዲኖረው “ኢትዮጵያ” በሚለው ጽርኣዊ ቃል መተርጐማቸውን ተረድተናል። ሰባ (ሰብዓ) ሊቃውንት የነገደ ኩሽ ጥቊረት የመጣው በሚኖሩበት ምድረ በዳ ካለው የፀሓይ ሐሩር መሆኑን ለመግለጽ ሲሉ፥ ነዋሪዎቹን ብቻ ሳይሆን መኖሪያ አገራቸውን ጭምር ኢትዮጵያ ማለታቸው፥ እንዲሁም በዕብራይስጡ የምድረ በዳ ትርጕም ያለውን ቃል ኢትዮጵያ እያሉ ወደ ጽርእ መመለሳቸው ለቃሉ የነበራቸውን ፅንሰ ሐሳብ እንደሚያመለክት የተሰጠውን ግምገማ ተረድተናል።

ከዚህም በመነሣትና በማያያዝ ኢትዮጵያ፥ የዛሬዪቱ ሱዳን (የቀድሞዪቱ ኑብያ) እና ግብጽ እርስ-በርስ የተገዛዙበት ጊዜ መኖሩን ከግምት በማስገባት፥
አንደኛ ለስሙ በዋና ባለቤትነት የምትታወቀው የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፥
ሁለተኛ በዐረብኛ ጥቊር የማለትን ትርጕም የያዘችው ሱዳን (የቀድሞ ኑብያ-ኢትዮጵያ)፥
ሦስተኛ የኩሽ ወንድም የሚጽራይም አገር የሆነችው ምስር (ግብጽ)፥

በወልም ሆነ በየግል ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ሲጠሩበት እንደ ነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ጥቅሶችን በየተስማሚ ክፍሉ ማንበባችንን እናስታውሳለን።

ይህን ሐሳብ በአእምሮ እንደ ያዝን ሆነን በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ስለ ሰፈሩት ነገዶች ለታሪክ መዘክርነት ብቃት ያላቸው ማስረጃዎች ወደሚያመለክቱን ጥቈማዎች እናተኩራለን።

ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ነገዶች
መቼም የኢትዮጵያ ቀደምት ነዋሪዎች ከነገደ ካም ኩሽያውያን እንደ ነበሩ ክርክር የማይቀርብበት ሐቅ ሆኗል። እንዲህ ባይሆንማ ኖሮ በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን “ኩሽ” የተባለው በጽርኡ ብሉይ ኪዳን “ኢትዮጵያ” ተሰኝቶ ባልተተረጐመና ስያሜው ሳይዛነፍ እስከ ዘመናችን በቅብብሎሽ ባልደረሰ ነበር።

በሌላው የታሪክ ገጽታ ግን ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በጥንታውያን ሐውልቶች ላይ ተጽፈው የተገኙት የታሪክ ቅርሶች፥ ከነገደ ኩሽ ልዩ የሆነ ዘር ወይም ነገድ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ግልጽ ማስረጃዎች ሆነው ቈይተዋል። ጽሕፈቶቹ በሳባውያን ፊደላት የተጻፉ ጠቃሚ ማስረጃዎች እንደ ሆኑ ተመራማሪ ሊቃውንት ሊደርሱበት ችለዋል። በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተገኙ እነዚህ ጽሕፈቶች ከባሕር ማዶ በደቡብ ዐረቢያ በተመሳሳይ ሁኔታ ከተገኙ ጋር ሲመሳከሩ በአንድ ዐይነት ፊደል የተጻፉ መሆናቸው ተረጋገጠ። በሁለቱም ክፍሎች የነበሩ ሰዎች በሳባዊ ፊደል ይገለገሉ እንደ ነበር መረጋገጡም ከሴም ነገድ የሆነው የዮቅጣን ልጅ ሳባ ዘር (ሳባውያን) ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ተብሎ በክብረ ነገሥት የተጻፈውን ታሪክ በማስረጃ የተደገፈ አድርጎታል።

ከነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ የዘለቁ ሳባውያን ብቻ አልነበሩም። እስራኤላውያንም (የዚህ ነገድ ክፍል) በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ መፍለሳቸው ይተረካል። ትረካውንም እውነተኛ የሚያደርጉ ወደ ፊት የምንገልጻቸው የባህልና የሃይማኖት ቅሪቶች እስከ ዘመናችን በገፍ ይገኛሉ።

ከዚህም በቀር በደቡብ በኩል ከነገደ ካም የሆኑ ልዩ ልዩ ነገዶች በሰሜን በኩልም ከነገደ ሴም የሆኑ የተለያዩ የጐሣ ዝርያዎች ወደ ኢትዮጵያ በየጊዜው እየገቡ፥ በቅድሚያ ቦታ ይዘው ከነበሩ ወገኖቻቸው ጋር  በማኅበራዊ ኑሮ፥ በኢኮኖሚ፥ በፖለቲካም እየተዋሓዱ በመጣመር፥ በመካለስ፥ በመደባለቅ አንድ ሕዝብ ሆነው ለዘመናት በነጻነት የኖሩባትን የዛሬዪቱን ኢትዮጵያን አቈይተውናል፤ ውለታቸውን ልንዘነጋ አይገባም።



No comments:

Post a Comment