Monday, March 12, 2012

አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው


ከቊርስ በኋላ፥ ጊዜው በግምት ሦስት ሰዓት ይሆናል፡፡
“እነዚህ ልጆች ዛሬም ወደ ዕርሻ ሄደው አይሠሩም ማለት ነው?” አሉ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ ጦቢያው፡፡
“ነገ ይሰማራሉ፤ ዛሬ እኔ የትም ስለማልሄድ እነርሱም እቤት ውለው ቢያጠኑ ይሻላል፡፡” አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ የምሩ፡፡ ወዲያውም በማከታተል ተጣሩ፡፡ “ግሩም፣ አንተነህ፣ ልዕልት!” አሉ፡፡

“አቤት፥ አቤት!” አሉ፥ ሁሉም በየተራ፡፡

“ኑ፥ ወንበራችሁን ዘርጉና ቀጽሉ፡፡ እስካሁን ምን እየሠራችሁ ነው?” በጥያቄ የተዘጋ፥ ግን መልስ የማይሻ ኮስታራ ትእዛዝ ነበረ፡፡
እነግሩም እየተቻኰሉ ወደ አባታቸው ሲሄዱ፥

“የወንዶቹስ ይሁን፥ መቼም አሁን የሴቷ ልጅ ትምህርት ምን ይባላል? ዳዊት ከደገመች መቼ አነሳትና ነው፤ አትቀድስ፥ አትሠልስ፤ መጣፍ፥ ቅኔ እያሉ ሥራ እሚያስፈቷት፡፡” አጒረመረሙ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ፡፡ ልጆቻቸው እንጂ አለቃ የባለቤታቸውን ንግግር አልሰሙትም፤ ቢሰሙትም አይመልሱላቸው እንደ ነበረ ከልማድ የታወቀ ነው፡፡

ሦስቱም ልጆች መጣፍ መጣፋቸውን ይዘው ተቀመጡ፡፡ እግዚአብሔር ትምህርቱን እንዲባርክላቸው አለቃ ጸሎት
አደረሱ፡፡


ትምህርት ለመጀመር እንደ ተዘጋጁ “አባባ” አለ ግሩም፡፡ “አቤት! የሚል ድምፅም ሳይጠብቅ “አበባ! ትናንትና ያጋጠመኝ ነገር” አለ፤ “ከትምህርት በፊት ልናገርና የምጠይቀውን ያስረዱኝ፡፡” አለ፡፡ አሁንም ፈቃድ ሳይሰጡት ንግግሩን ቀጠለ፡፡

“ትናንት ሁለት የከተማ ልጆች እንጃ! የአስኳላ ተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ከመምሬ በሻህ ውረድ ጋር ሲነጋገሩ ቆሜ አዳምጥ ነበር፡፡ ታዲያ እየቈየ ንግግራቸው ከውይይት ወደ ክርክር ተሻገረ፡፡ መምሬም ተቈጡ፤ በመቋሚያቸው አንደኛውን ልጅ ሊዠልጡት ሠንዝረው ነበር ተወርውሬ መቋሚያቸውን ባልይዝ፡፡ ከገላገልኳቸው በኋላ ልጆቹ እኔንም መምሬንም <ጌታ እግዚአብሔር ይባርካችሁ> በማለት መረቁንና በፈገግታ ተሰናብተው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ የሁለቱም ወገኖች ሁኔታና አነጋገር ገረመኝ፡፡ ሌሊቱን ሲያብሰለስለኝ ሲያባዝተኝ ዐደረ፡፡”

“ስለ ምን ነበር ክርክራቸው ወይም ውይይታቸው” አሉ አለቃ? ግሩም ከየት መጀመር እንዳለበት ዐሰብ አደረገና በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ “ልጆቹ እፊት እፊቴ ይሄዱ ነበር፡፡ መምሬ ግን ከቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ሲመጡ እመሳለሚያው አጠገብ ከመስቀለኛው መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ ልጆቹ ቆም እንዳሉ ለጠቅኋቸው፡፡ ሁለቱም ለመምሬ ቅድሚያ ለመስጠት መንገዱን ለቀቅ አደረጉ፡፡ ከአንገታቸውም ጐንበስ በማለት ሰላምታ ሰጧቸው፡፡ መምሬም አጸፋውን ይሰጣሉ ብዬ ስጠብቅ ለምን እንደ ሆነ ሳላውቅ ፊታቸውን ክስክስ አደረጉት፡፡ እኔም ለሁሉም ሰላምታ ሳልሰጥ በመገረምም በመደንገጥም ከልጆቹ አጠገብ ቆምኩ፡፡”
“የአያት የቅድም አያቶቻችሁን ሃይማኖት ትታችሁ የባዕድ ሃይማኖት መከተላችሁን ሰምቼ ነበር፤ ይኸውና በዐይኔ አሳየኝ፡፡ እናንተ ከሓዲዎች ርጉሞች ናችሁ፡፡” አሉ በመቋሚቸው እየጠቈሙ፡፡ ዐይኔ መቋሚያቸውን ቢከተል የመቋሚያቸው ጫፍ ልጆቹ በእጃቸው ወደ ያዙት መጽሐፍ ቅዱስ ማመልከቱን ተረዳሁ፡፡

ከሁለቱ አንደኛው ልጅ ለስለስ ባለ ድምፅ

“ሃይማኖት እኮ!” አለ፡፡ “ሃይማኖት እኮ የአያቴ የቅድም አያቴ ነው ተብሎ አይታመንበትም የኔታ፡፡ መጽሐፍ ተመርምሮ የሚያድን፥ ለነፍስ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ በመጽሐፍ ቃልና በኅሊና ሲረጋገጥ ብቻ “የኔ ሃይማኖት ነው” ተብሎ ይያዛል እንጂ፡፡ እንዲህማ ባይሆን ኖሮ በአቡነ ሰላማ የተሰበከውን  ወንጌል በዚያ ዘመን የነበሩት አባቶቻችን ባልተቀበሉት፤ የአያት የቅድም አያቶቻችን ሃይማኖት አይደለም ብለው በተቃወሙት ነበር፡፡”

“አቡነ ሰላማ ወንጌልን በሀገራችን በሰበኩበት ጊዜ ሰዎቹ የዘር ሃይማኖት ነበራቸውኮ! በኦሪት ሃይማኖት የነበሩ ጨረቃ የሚያመልኩ ለልዩ ልዩ ፍጥረት የሚሰግዱ ነበሩ ከታሪክ እንደምናነበው፡፡ ታዲያ ቢሆንም ወንጌል ሲሰበክላቸው የቃሉን እውነት በመረዳታቸው እኩሌቶቹ ተቀበሉ፤ ያልተቀበሉትም በቀድሞው ሃይማኖታቸው ጸኑ፡፡ የኔታ! በእርስዎ አባባል ከተሄደ ከዘር የወረደላቸውን የጨረቃ አምልኮ አንተውም ያሉት መመስገን፤ ዐዲሱን የወንጌል ሃይማኖት የተቀበሉት መነቀፍ ነበረባቸው ማለት ነው” አለ፡፡

“ወዴት ወዴት ነገር ታጠማዝዛለህ? እኔ የተናገርሁት ስለ ክርስትና ሃማኖታችን ብቻ ነው፡፡” አሉ መምሬ እንደ ተቈጡ ሆነው፡፡ ሐሳባቸውንም ሳይቋጩ አቋረጡት፡፡

“የክርስትና ሃይማኖትንም ቢሆን” አለ ሁለተኛው ልጅ በወንድሙ ተተክቶ መልስ ሲሰጥ፤ “የክርስትና ሃይማኖትንም ቢሆን የወላጆች በመሆኑ ብቻ እንደ ባህል እንደ ወግ ዕቃ እንደ ቋንቋ እንደ ሀብት በውርስ ሊቀበሉት አይገባም፡፡ ክርስቲያን መሆን ለምን እንደሚያስፈልግ በቅደሚያ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምሮ ማንን እንዴት ማመን እንደሚገባ መረዳት ያሻል ማለታችን ነውኮ! መምሩ” አለ፡፡

“በዚህን ጊዜ ነበር ቄሱ መቋሚቸውን የሠነዘሩት” አለና ግሩም ንግግሩን ደመደመ፡፡ ቦዘዝ ብሎም አባቱን ዐይን ዐይናቸውን ይመለከት ጀመር፡፡

“ታዲያ ምን መረዳት ፈልገህ ነው ይህን ገጠመኝህን የነገርከን?” አሉ አባት፡፡

“የልጆቹ ጥቄዎች መልስ አላገኙምኮ! አበባ፡፡” በአጋጣሚውም የተከሠቱ ሁኔታዎች መልስ የሚያሻው ጥያቄ ቀስቅሰዋል፡፡ ሁሉንም መልሶች መረዳት እፈልጋለሁ ነበር የልጃቸው መልስ፡፡ “እስኪ ጥያቄዎችህን አንድ ባንድ እንስማቸው፡፡” አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ፡፡
“አንደኛ” አለ ግሩም፡፡ “አንደኛ አዘውትራችሁ እንደምትነግሩን የእናንተ የወላጆቻችን የዘር ሐረግ ሲሳብ በአቡነ ሰላማ ስብከት ክርስቲያን ከሆኑ የዘር ግንዶች የበቀለ ነው፡፡ እኛም ልጆቻችሁ ከክርስቲያን ቤተ ሰብ በመወለዳችን ክርስቲያን ተደርገናል፡፡”
“ክርስቲያን ተደርገናል?” ሲሉ አለቃ የልጃቸውን ንግግር በድንገት አቋረጡት፡፡

“አዎና!   ” አለ ግሩም፡፡
"እኛ መጻሕፍትን መርምረን ክርስቲያን መሆን አለብን በማለት በውሳኔያችንና በምርጫችን ክርስቲያን አልሆንም፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ እናንተ የምትሉትን እንድንል፤ የምትሠሩትን እንድንሠራ አዘዛችሁን፡፡ እናንተን መምሰልና መከተል ሥነ ሥርዐት ሆነና የምትሉትን አልን የምትሠሩትን ሠራን፡፡ ይኸው የመምሰል ሁኔታ ክርስቲያን ሊያሰኘን ይበቃል ካልተባለ በስተቀር ለምን ክርስቲያን መሆን አስፈለገን? ክርስቲያን በሆኑትና ባልሆኑት መካከል ቀኖናዊ ሥነ ሥርዐትን ሲፈጽሙ መታየት ነው ወይስ በልዩነት የሚታወቅና የሚታይ የሕይወት ለውጥ አለ? ካለስ ምንድር ነው? የሚለውን ዐስበነውም አናውቅ፡፡ እንድናስብበትም ዕድል አልተሰጠንም ማለቴ ነው” አለና ግሩም ወደ አባቱ ተመለከተ፡፡

አለቃ ግንባራቸውን ቋጠር-ፈታ፤ ጨፍገግ-ፈገግ፤ እያደረጉ በመደመም እያዳመጡ ሳለ የልጃቸው ንግግር ቢቋረጥባቸው፥ አንዴ ተናጋሪውን፥ አንዴ አንተነህና ልዕልትን በእይታቸው ዳሰሱና “ቀጥል እንጂ!” አሉ፡፡
አስተያያታቸውና አነጋገራቸው ያለ መቈጣት ምልክት መሆኑን የተረዳው ግሩም አየር ሳበና - “ታዲያ እኔ የምለው ልቤ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት ምስክርነት ያልተለኰሰና ያልበራ መሆኑን እያወቅሁ የዓለም መብራት ክርስቲያን ነኝ ማለቴ በእሳት ያልተቀጣጠለ፥ ነገር ግን በመቅረዝ ላይ በመቀመጡ ብቻ መብራት ነኝ የሚል ሻማን አስመስሎኛልና ላፍር ይገባኛል፡፡ ከእኛ ይልቅ በአቡነ ሰላማ ዘመን የነበሩ ሰዎች እውነተኞች ነበሩ፡፡ በተለያየ ሃይማኖት በነበሩበት ጊዜ ክርስትና ሲሰበክላቸው ምርጫና ውሳኔ አደረጉ፡፡ በነባር ሃይማኖታቸው ሳይገበዙ በጊዜው መጤ የነበረውን ክርስትና ያለ ይሉኝታና ያለ ፍርሀት አንዳንዶቹ ተቀበሉ፡፡ በመቀበላቸውም ከኅብረተሰብ ችግር አልደረሰባቸውም፡፡”

“እኛ ግን የእነርሱ ዐይነት መረዳትና ውሳኔ ከማድረግ ውጪ ነን፡፡ ቀኖናዊ ሥነ ሥርዐትን መፈጸም ብቻ በተለምዶ ክርስቲያን ያሰኛል እንጂ አያደርገንም እላለሁ፡፡ አይደለም እንዴ! ሳይደከምበት በውርስ እንደ መጣ ቅርስ የአባቴ፥ የአያቴ፥ የምለው ሃይማኖት አያስመካኝም፡፡ የኔ የምለው እምነት ሊኖረኝ ይገባል፡፡ መምሬ በሻህ ውረድ በልጆቹ ተጠይቀው ያልመለሱት ይህን ነበር፡፡”

“ሁለተኛው ጥያቄ” አለ ግሩም በመቀጠል፡፡ “ለማመን መረዳት አስፈላጊ አይሆንም፤ ሲያያዝ የመጣውንና ከወላጆች በውርስ የተገኘውን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት እንደ እምነት በመቊጠር ለእርሱም ታማኝ ሆኖ መኖር ይገባል የሚባል ከሆነ ማን ማንን ሊሰብክ ይችላል? ሁሉም በውርስ የተቀበለው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት አለውና፡፡”

“አባባ! በአቡነ ሰላማ ዘመን ነባር ሃማኖታቸውን በመተው መጤ የነበረውን ክርስትና የተቀበሉትን የዘር ሃይማኖታቸውን ለመተው ፈቃደኞች ያልነበሩትን ሰዎች ይደግፋሉ? አይሁድ ስለ ሃይማኖታቸው ቀናተኞች በመሆናቸው ክርስቶስንና ትምህርቱን ተቃወሙ፡፡ በልዩ ልዩ አምልኮ ተይዘው የነበሩትም በውርስ ለተላለፈላቸው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት ታማኝ መሆንን ወደው ወንጌልን አልተቀበሉም፡፡ ሊመሰገኑ ይገባቸዋልን?”

“ሦስተኛው የኔ ጥያቄ”  አለ ግሩም ንግግሩን በማራዘም  “ክርስቲያን ነኝ ባዩም፥ አይሁዳዊውም፥ ሌላ ሌላውም ሃይማኖቱን ያልተቀበለለትን ወይም ስለ ሃይማኖቱ እንዲያስረዳው የጠየቀውን፥ ወይም የተከራከረውን ሰው ማሳደድ፥ መደብደብ፥ መግደል፥ ንብረቱን መዝረፍ፥ የቀበረውን አስከሬን ከተቀበረበት አውጥቶ ለአውሬ መስጠት … ይገባዋልን? ይህን ማድረግ ላንድ ሃይማኖት ትክክለኛነት መለኪያ ነውን? የሃይማኖት መሥራቾች ተከታዮቻቸው እንዲህ እንዲሠሩ ደንግገዋልን? ለኔ እንደሚመስለኝ በሃይማኖት የማይመሳሰሏቸውን የሚያሳድዱና ሲሰብኩት ባልተቀበሏቸው ሰው ላይ ጥቃት የሚያደርሱ የሃይማኖት ክፍሎች ሁሉ በሃይማኖታቸው ትክክለኛነት የማይተማመኑና በትምህርተ ሃይማኖታቸው የሚያፍሩ ሰዎች ይመስሉኛል፡፡ እርስዎስ አባባ?” አለና ግሩም ንግግሩን ጨረሰ፡፡

በልጃቸው ጥያቄ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ወዳልጠበቁት ተመስጦ ጠልቀዋል፡፡ ልጃቸው ነገረ ሃይማኖትን ይህን ያህል የመመራመር ፍላጎትም ብቃትም ይኖረዋል ብለው ዐስበውም አያውቁ ኖሮአል፡፡ አለቃ ብቻ አልነበሩም የተደነቁት፤ አንተነህና ልዕልትም እጅግ አስገርሟቸዋል፤ መልሱ ምን ሊሆን ይችላልን እያሰላሰሉ፥ እየጓጉም በሐሳብ ካንዱ ጥያቄ ወደ ሦስተኛው፤ እንደ ገናም ከሁለተኛው ወደ አንደኛው በመዝለል ይመላለሱ ነበር፡፡

ወ/ሮ ትደነቂያለሽም ሥራቸውን በመከወን ላይ እያሉ፥ አንዳንድ ጊዜ እንደሚያደርጉት፥ ሲያልፉ፥ ሲያገድሙ ጆሮዎቻቸውን ወደ ባላቸውና ወደ ልጆቻቸው ንግግር ጣል አድርገው ነበር፡፡ ከንግግሩ አብዛኛው አላመለጣቸውም፡፡ ታዲያ በመጀመሪያ ልጃቸው ከሓዲ የሆነ መሰላቸውና በልባቸውም በአፋቸውም ረገሙት፡፡ ይበልጡን እያዳመጡ ሲሄዱ ግን የልጃቸው ንግግር ፍሬ ሐሳብ እንደ ፍላጻ ሆኖ ልብ ልባቸውን ወጋጋቸው፡፡ አለቃ የሚመልሱትንም ሲጠባበቁ ነበር፡፡

አለቃ ነቅዐ ጥበብ የምሩ - እእ- እእ- እእ- በማለት ጒረሮአቸውን አጣሩ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ልጆቻቸውን ከተመስጦ ሰመመን በመቀስቀስ በድምፃቸው አነቋቸው፡፡ እእ-እእ-እእ - በማለት “ጥያቄዎቹ በቀላሉ የሚመለሱ አይደሉም፡፡ ከእግዚአብሔር ቃልና ከመንፈስ ቅዱስ የጥያቄዎቹን መልሶች እናደምጣለን” አሉ፡፡ ወዲያውም የዕለቱን ትምህርታዊ ውይይት በጸሎት ዘጉ፡፡ መልሳቸው ምን ይመስል ይሆን?

No comments:

Post a Comment