Read PDF
አቤቱ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ!! (መዝ. 138(139)፥14)
ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
የመዳን ትምህርት
“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል?” ሮሜ 7፥24 ካለፈው የቀጠለ፡፡
እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲመለከት ጻድቅ የሆነ አንድ ሰው ስንኳ ከመካከላችን እንዳልተገኘ ኀጢአት፥ ያልተመረተበት የሰውነት ክፍልም በእያንዳንዳችን እንደ ሌለ የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባለፈው ዕትም ተመልክተናል (መዝ. 13፥1-3)፡፡
የዛሬው ዕትም ደግሞ የሰው መበላሸት ከመፈጠሩ ጀምሮ እንዳልሆነ ያስነብበናል፡፡
የሰው አፈጣጠር እንዴት ነበር?
መቼም እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በቅድሚያ ያረጋግጥልናል (ዘፍ. 1፥4፡10፡12፡18፡21፡25፡31)፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነበረ ሲባል፥ መልካም ከነበረው ፍጥረት አንዱ ሰው እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንዲያውም “መልካም” የሚል ገደብ የተበጀለትን የየዕለቱን ፍጥረት መመዘኛ በማለፍ “እጅግ መልካም” የሚል እመርታን የሚያሳይ ዐዲስ የመመዘኛ ወሰን የተገኘው ሰው ከተፈጠረና የፍጥረት ገዥ ሆኖ ከተቀመጠ በኋላ ነበር (ዘፍ. 1፥31)፡፡
ስለዚህ ፍጥረት ሁሉ ያለ ሰው መልካም ሲሆን፥ ከሰው ጋር ሲታይ ደግሞ “እጅግ መልካም” ነበረ፡፡ ከሌሎቹ ፍጥረታት ሰውን የሚያልቀው የተፈጥሮ ብልጫው ከምን መጣ ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት የማወቅን ጥማት ያረካል፡፡
ሰው ሌሎቹ ምድራውያን ፍጥረታት ከተፈጠሩባት ምድር ብቻ እንዳልተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያብራራ “… እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር ዐፈር አበጀው” ካለ በኋላ፥ “በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት” ይላል (ዘፍ. 2፥7)፡፡ ሰው ከምድር ብቻ እንደ ተፈጠሩት እንስሳት፥ አራዊት፥ አዕዋፍ ለመብላት፥ ለመጠጣት፥ ለመራባት፥ ሙቀትንና ቅዝቃዜን ለመለየት … በምታስችል ደማዊት ነፍስ እንዲንቀሳቀስ ብቻ አላደረገውም፡፡ እኔ ሕያው ነኝ የሚልበትን የሕይወቱን እስትንፋስ በመስጠትና በደማዊት ነፍስ ሕያዋን ከተባሉ ፍጥረታት በማላቅ አከበረው (ዘዳ. 32፥40፤ ኢዮ. 33፥4-6)፡፡
የእግዚአብሔርም የሕይወት እስትንፋስ ሕያው አድርጎታልና ሰው በዚህ ተፈጥሮኣዊ ባሕርዩ መንፈስ የሆነውን የእግዚአብሔርን መልክ በመያዙ የመንፈሳዊ መልክ ባሕርያዊ መግለጫዎች በሆኑት እውነት፥ ጽድቅና ቅድስና … አምላኩን ይመስላል ሊባል በቃ (ዮሐ. 4፥24፤ ኤፌ.4፥24፤ ቈላ.3፥10)፡፡
በእንስሳት፥ በአራዊት፥ በአዕዋፍ፥ … በማይገኝ ለባዊነቱ፥ ነባቢነቱና ዘላለማዊ ሕያውነቱም የአምላክ ምሳሌ ሆኗል፡፡
ሰው ከሌሎቹ ምድራውያን ፍጥረታት ሁሉ ተለይቶ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማወቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሚዛንነት ክፉ ምን እንደ ሆነ የመረዳት፥ ክፉን የመጥላትና ቅድስናን የመምረጥ ችሎታና ዝንባሌ ሊኖረውም የቻለው አምላኩን በሚመስልበት፥ የእግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ በሆነው ሕያውነቱ ነው፡፡ በዚህም ተፈጥሮኣዊ ባሕርዩ ሰውን ስንመዝነው ከግዙፋን ፍጥረታት ብቻ ሳይሆን ከረቂቃኑ ፍጥረታት መካከልም ቢሆን የሚወዳደረው እንደሌለ እንረዳለን፡፡
መላእክት እንኳ እም ኀበ አልቦ (ካለ መኖር) አምጥቶ የፈጠራቸው መናፍስት ሲሆኑ፥ የሥራ መደባቸውም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን ማገልገልና የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደ ሆነ ከቃሉ እንማራለን (መዝ. (91)፥11፤ (104)፥4፤ ዕብ. 1፥14፤ ራእ. 4፥10-11)፡፡
እንደዚህ ሆኖ የተፈጠረው ሰው የፍጥረት ራስ በመሆን ፍጥረትን እንዲገዛ ሥልጣን ተሰጠው (ዘፍ.1፥26-31)፡፡ የዚህም ምስጢር እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ባኖረው የሕይወት እስትንፋስ አማካይነት በሰው ሆኖ ፍጥረትን እንዲገዛ የተነደፈ ዕቅድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በዚህ ትይዩ መላእክት እንኳ ሰውን ሕያው ካደረገው ከእግዚአብሔር እስትንፋስ አልተፈጠሩም፡፡ ከሰው የበለጡ ሆነው የሚታሰቡበት ሁኔታ ቢኖርም ለሰው የተሰጠው የግዛት ዐይነት አልተሰጣቸውም (መዝ. 8፥4-6፤ ዕብ. 2፥6-9)፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ለሰው ሊያወርሰው ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት መላእክት ከውጪ ሆነው እያዩ ይመኙታል እንጂ በወራሽነት ከቶ አይገቡበትም (ዕብ. 2፥5፤ 1ጴጥ. 1፥10-12)፡፡
ከሚያስደንቀው በላይ አስደናቂ የሆነ የእግዚአብሔር ሥራ ደግሞ አለ፡፡ በራሱ ምርጫ ክብሩን ያጣው ሰው በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ክብር ሲመለስ ራስ ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠው አምላክ ሰው (ዐማኑኤል) በሆነው በጌታችንና በአምላካችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም እንኳ መላእክትን እየገዛ ነው (ኤፌ. 1፥18-23፤ 2፥6-7፤ 1ቆሮ. 6፥3)፡፡
የሰው አፈጣጠር እንደዚህ ያማረና የተዋበ ሆኖ ሳለ ታዲያ እንዴትና መቼ ተበላሸ የሚለው ጥያቄ በሚቀጥለው ዕትም ይመለሳል፡፡
የክፍሉ መታሰቢያ ጥቅስ፡-
No comments:
Post a Comment