Read PDF
በም. 1፥3-4 በሞሪያ ተራራ በጽዮን አምባ ላይ ንጉሥ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ “የእግዚአብሔር ሕግ ማደሪያ ታቦተ ጽዮን” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን እንደ ነበረች ይናገራል፡፡ በአገላለጹ ከዜና መዋዕል ካልእ 35፥3 ጋር ይስማማል፡፡ ጊዜው የኢዮስያስ 18ኛ የግዛት ዓመት ስለ ሆነ (2ዜና. 35፥19) ሰሎሞን ከሞተ 359 ዓመት ዐልፎአል ማለት ነው፡፡
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
ካለፈው የቀጠለ
ም. 1፥54-55 ከለዳውያን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ታቦት ማርከው ወደ ባቢሎን እንደ ወሰዱ ይናገራል፤ ትረካው ግን፡-
1. ታቦተ ጽዮን በሰሎሞን ዘመን ተሰርቃ ተወስዳ ነበር ባዮችን የሚደግፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡ መሰረቋን ማወቅ ያልቻለ እንደ ዕዝራ ሱቱኤል ያለ ሰው ነው ካልተባለ በቀር፤ ዕዝራ ሱቱኤል 9፥21-22፡፡
2. የተረፈ ኤርምያስ ጸሓፊ ቤተ መቅደሱ በውስጡ ካለው ዕቃ ጋር ተሰወረ በሚለው ሐሳብ አልተስማማም፤ ተረፈ ኤር. 8፥13፡፡
ም. 3፥4-24፤ 4፥1-13 ዘሩባቤል ከንጉሥ ዳርዮስ ጋሻ ጃግሬዎች አንዱ እንደ ነበረ ያስረዳል፡፡ ከሁለት ጓደኞቹ ይልቅ ዐዋቂ ያሰኘውን የጥበብ ነገር ለንጉሥ ዳርዮስ ተንትኖ በመናገሩ ንጉሡ ደስ እንደ ተሰኘበት ይተርካል፡፡ ቀጥሎም ዘሩባቤልና ጓደኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ በናቡከደናጾር ጊዜ የተቃጠለውን ቤተ መቅደስ እንዲሠሩ ንጉሥ ዳርዮስ የፈቀደላቸው መሆኑን ያብራራል፡፡ ዘሩባቤልም ምርኮኞቹን አይሁድ ይዞ በመመለስ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደ ጀመረ ይተርክልናል፤ የጅምሩ ቤተ መቅደስ ሥራም በቂሮስ ዘመን እንዲቋረጥ መደረጉንና እስከ ዳርዮስ ሁለተኛ ዓመት ድረስ ሥራው መተጓጐሉን ከም. 4፥13 እስከ ም. 5፥73 አክሎ ያስነብበናል፡፡
የዕዝራ ካልእ ትረካ ከ2ዜና መዋዕል ቀጥሎ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱሱን መጽሐፈ ዕዝራና የዓለምን ታሪክ ይቃረናል፡፡
1. በናቡከደናጾር የፈረሰው ቤተ መቅደስ እንደ ገና እንዲሠራ የፈቀደው አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት የባቢሎንን መንግሥት ያፈረሰው ፋርሳዊው ቂሮስ ነውና፤ (2ዜና. 36፥22-23፤ ዕዝ. 1፥1-4፤ ኢሳ. 44፥24-28) ዕዝራ ካልዕ በም. 2፥1-14 እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ዕዝራ የተረከውንም አፍርሶታል፡፡
2. የባቢሎኑን ብልጣሶር ያስወገደው ፋርሳዊ ቂሮስ በፈቀደው መሠረት ብዙ አይሁድን አሰባስቦ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው የመጀመሪያው ቡድን መሪዎች እነ ዘሩባቤል እንደ ነበሩ የመጽሐፍ ቅዱሱ መጽሐፈ ዕዝራ ሲተርክ (ዕዝ. 2፥1-70)፤
እነ ዘሩባቤል ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ በሁለተኛው ዓመት የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደ ጀመሩ ሲገልጽ (ዕዝራ 3፥8-13)፥
የይሁዳ ጠላቶች ሥራውን ለማሰናከል በቂሮስ፥ በተከታዩም በዳርዮስ ዘመን እየታገሏቸው ከቈዩ በኋላ ቀጥሎ ለነገሠው ለአርጤክስስ ደብዳቤ በመጻፍ የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ሲያስረዳ፥ (ዕዝ.4፥1-24)፥
ከአርጤክስስ ቀጥሎ በነገሠው በሜዶናዊው ዳርዮስ ዘመን እነ ዘሩባቤል ሥራውን በመቀጠልና በማጠናቀቅ የቅዳሴ ቤቱን ሥርዐት ማድረሳቸውን ሲናገር ዕዝራ 5፥1-5፤ 6፥15-18፥
ከዳርዮስ ቀጥሎ በዙፋኑ የተተካው አንታርክሲስ (አርጤክስስ) በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ዕዝራ ሁለተኛውን ቡድን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሰ በታሪክ ሲያስከትል (ዕዝራ 7፥1-9)፥
በአንታርክሲስ 20ኛ ዓመተ መንግሥት 3ኛው ቡድን በእነ ነህምያ መሪነት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ተጓዘ (ነህ. 2፥1-12) ከምርኮ የተመለሱትንም ሁሉ በማስተባበር የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደ ታደሰ (ነህ. 2፥17፤ 6፥15፤ 12፥27) በማስከተል ታሪኩን ሲደመድም፥
ቀኖናዊውም መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ ግን የመጽሐፍ ቅዱሱን ዕዝራ የታሪክ ሕንጻ እየናደ ከካልእ መጽሐፍነት የማይጠበቅ ያልነበረ የታሪክ ምስልን ሊተካ ይሞክራል፡፡
“ካልእ” የተባሉትን መጽሐፈ ሳሙኤልን፥ መጽሐፈ ነገሥትን፥ መጽሐፈ ዜና መዋዕልን መላልሰን ብናነባቸው የቀዳማዊውን መጽሐፍ ታሪክ ሲያፈርሱ አናገኛቸውም፡፡ የመጀመሪያው ካቆመበት በመነሣት ይቀጥላሉ እንጂ፡፡ ይህም ይዞታቸው የቀዳማዊና ካልእነትን (1ኛና 2ኛነትን) ደረጃና መብት፥ ሕጋዊነትንና ትክክለኛነትን ለመጻሕፍቶቹ ይጠብቅላቸዋል፡፡ በመጽሐፈ ዕዝራ ካልእ ግን ይህ አይታይም፡፡
ም. 7፥3 በሐጌና በዘካርያስ የትንቢት ቅስቀሳ የተለየ “ቤተ ክርስቲያን” መሠራቱን ይተርካል፡፡ በዘመነ ብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አልነበረም የተርጓሚ፥ የጻፊ፥ የዐታሚ ስሕተት ይሆን? ወይስ ቤተ መቅደስና ቤተ ክርስቲያን አንድ ናቸው ለማለት ይሆን?
No comments:
Post a Comment