Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
የተተኪው ቤተ መቅደስ ሥራም የተጀመረው ከዚህ ጊዜ ዐምስት ዓመት ያህል ዘግይቶ ነው፤ ዕዝ. 3፥8-13፡፡
ይቀጥላል
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
ባንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721 እስከ 1037 በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? «ተጨማሪ (ዲዩትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት» በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት ዐሥራ ስምንት ናቸው (በ1980 ዕትም)፡፡
በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ ባንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር፥ እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን ጐደሎ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡
መጠሪያቸው እንደሚያስረዳው እነዚህ ተጨማሪ መጻሕፍት ቀደም ሲል ከቅዱሳት መጻሕፍት ቊጥር ውጪ እንዲሆኑና በአዋልድነት እንዲጠሩ ያደረጓቸው አያሌ ታዋቂ ምክንያቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ከአዋልድ መጻሕፍቱ ጋር ታትመው ቢሆን ኖሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በላደናገሩ ነበር፡፡
የብሉይ ኪዳን መምህራን ስለ እያንዳንዱ ዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስኪዚያው ድረስ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙባቸውን ነጥቦች በመጠቈም እናቀርባለን፡፡
ተረፈ ኤርምያስ
አምስት ምዕራፎች ለያዘው ለሰቈቃወ ኤርምያስ ከስድስተኛ እስከ ዐሥራ አንደኛ ምዕራፍ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡
“ተረፍ” የሚለው ቃል ተርፈ፥ ተረፈ፥ ቀረ፥ ከተባለው የግእዝ ግስ እንደ ወጣ ከተቈጠረ ትራፊ፥ ፍርፋሪ፥ ጭላጭ፥ ቀሪ፥ ቅሬታ… ማለት ነው፡፡ ተረፈ ኤርምያስን “ተረፈ” ያሰኘው ከጥራዝ ስለ ተረፈ፤ ከሰቈቃወ ኤርምያስ ጋር በሐሳብ ስላልተያያዘ፤ በኤርምያስ ስም ቢመዘገብም ማረጋገጫ ባለመገኘቱ፤ በዕብራይስጥ ከተጻፈው ከሰቈቃወ ኤርምያስ ጋር ተጽፎ ባለመተላለፉ፤ ወይም ሌላ ምክንያት ቢኖር መምህራን ጥያቄውን ይመልሱልናል፡፡
ተረፈ ኤርምያስ ለሰቈቃወ ኤርምያስ ከምዕራፍ 6 የሚጀምር ተቀጥላ ሆኖ ቢዘጋጅም እንደ አንድ መጽሐፍ ራሱን የቻለ “ርእስ” ተበጅቶለታል፡፡ ኤርምያስ ለተማረኩት አይሁድ ወደ ባቢሎን የላከው መልእክት እንደ ሆነ ርእሱ ይገልጻል፡፡
ኤርምያስ ወደ ባቢሎን ደብዳቤ ከጻፈ በጠላት አለመማረኩን በመግለጹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተስማማ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል! በም. 8፥21 ኤርምያስ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰደ ይላል እንጂ፡፡
ወደ መጽሐፉ ወስጥም ሲገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተቃርኖ ያላቸው ወይም ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦች አሉ፡፡
1. በም. 6፥1 “እስከ ሰባተኛ ትውልድ ድረስ በዚያ በባቢሎን ብዙ ዘመን ትኖሩ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ በደላችሁበት ኀጢአታችሁ ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዷችሁ” ይላል፡፡
በባቢሎን የሚቈዩት ለሰባ ዓመት እንደሚሆን ኤርምያስ በግልጽ ተንብዮ ነበር፤ ኤር. 29፥10፡፡ አይሁድም ሰባው ዓመት የሚፈጸምበትን ጊዜ ይጠብቁ ነበር፤ ዳን. 9፥1፡2፤ 2ዜና. 36፥21፡፡
ታዲያ ሰባት ትውልድ የሚለው ቃል እያንዳንዱን 10 ዓመት ያንድ ትውልድ ዘመን አድርጎ በመቊጠር ይሆን?
2. በም. 8፥13 “ባሮክና ኤርምያስም ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ የሚያገለግሉበትንም ዕቃ ሁሉ ጌታ እንዳዘዛቸው ለምድር ሰጧት፤ ምድርም ያን ጊዜ ተቀብላ ዋጠችው” ብሏል፡፡
በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የወርቅ የብር የነሐስ ዕቃዎች ሁሉ ወራሪዎቹ የከለዳውያን ሠራዊት ወደ ባቢሎን እንደ ወሰዷቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ 2ነገ. 25፥13-17፤ ኤር. 52፥17-23፡፡
3. ም. 8፥18-20 “… ኤርምያስ የቤተ መቅደሱን መክፈቻ ይዞ ከከተማ ወደ ውጪ ወጣ፡፡ … የቤተ መቅደሱን መክፈቻ ተቀበል ብሎ በፀሓይ ፊት ጣለው፡፡ … እስከ ብዙ ዘመን ድረስ ጠብቀው አለው” ይላል፡፡
ከለዳውያን በውስጡ የነበሩትን የማገልገያ ዕቃዎች ከወሰዱ በኋላ ቤተ መቅደሱን አቃጠሉት እንጂ መቼ ተሰወረ? 2ዜና. 36፥17-19፡፡ እንደ ተባለው ዕቃዎቹና ቤተ መቅደሱ ለብዙ ዘመን ተሰውረው ቈይተው ቢሆን ኖሮ ምርኮኞቹ ከሰባ ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ፡-
ሀ) የተማረኩትን ዕቃዎች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ማጓጓዝ ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ ዕዝራ 1፥7-11
ለ) በቀድሞው ቤተ መቅደስ ፍራሽ ላይ አዲስ ቤተ መቅደስ መሥራት አይደክሙም ነበር፤ ዕዝራ 3፥1-3፤ 6፥14-16፡፡
የተረፈ ኤርምያስ ጸሓፊ ራእየ ዮሐንስን ያነበበ ደራሲ ነው የሚሰኝበት ምክንያት አለ፡፡ ዮሐንስ በራእዩ (11፥19) “በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት ታየ” በማለት በመንፈስ ሆኖ (ራእይ 1፥10) ያየውን በሥጋ ዐይን የተመለከተው ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠራው ምድራዊ ሕንጻ ቤተ መቅደስ ስለ መሰለው ለዚሁ ለራእይ ትርጓሜ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያሰበ ይመስላል፡፡
ዮሐንስ ያየው ያን ጊዜ በኤርምያስ ዘመን የተሰወረውን መቅደስ ነው ለማሰኘት የተጠበበ ሳይሆን አይቀርም፡፡
4. በም. 8፥21 “ኤርምያስም ለወገኖቹ ሲያለቅስ እያዳፉ አወጡት፡፡ ከሕዝቡም ጋር እስከ ባቢሎን ወሰዱት፡፡” የሚል ቃል ተጽፎአል፡፡
ሳይማረኩ በይሁዳ የቀሩ አይሁድ ኤርምያስን አስገድደው ወደ ግብጽ ይዘውት ሸሹ እንጂ፤ ኤርምያስንስ ከለዳውያን አልማረኩትም ነበር፡፡ በፈለገበት ስፍራ እንዲኖር ወይም ወደ ፈለገበት ቦታ እንዲሄድ ነጻነት ሰጥተውት ነበር፤ ኤር. 40፥1-6፤ 43፥5-13፡፡
5. በም. 8፥11-12 እግዚአብሔር ኤርምያስን ወደ ባቢሎን እስክትሄድ ድረስ ወደ ግብጽ ሄደህ ስታስተምር ኑር ሲል አዝዞት እንደ ነበረ ይናገራል፡፡
ኤርምያስ ወደ ግብጽ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም በከለዳውያን ወደ ባቢሎን ተወሰደ ለማለት ይሆን? (8፥21)፡፡
በእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደ ተነገረው ኤርምያስንና ባሮክን አስገድደው ወደ ግብጽ የሸሹት በባቢሎናውያን አገዛዝ ሥር በይሁዳ አንኖርም፤ ወደ ግብጽ መሄድ ይሻለናል በማለት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ያመፁ አይሁድ ነበሩ፤ ኤር. 42 እና 43፡፡
6. በም. 8፥12 እና 10፥2 ባሮክ በኢየሩሳሌም በመቃብር ቤት ሆኖ የምርኮውን ዘመን እንዳሳለፈ ተጽፎአል፡፡ እንዲሁም፥
7. በም. 11፥1-24 ባሮክ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ለኤርምያስ፥ ኤርምያስም ከባቢሎን ለባሮክ ደብዳቤ እንደ ጻፉ ይናገራል፡፡
ይህ በተራ ቊጥር 6 እና 7 የተገለጸው ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ተቃርኖ በተራ ቊጥር 4 እና 5 ተመዝግቧል፡፡
8. በም. 11፥25-34 ባሮክ በደብዳቤ ባሳሰበው መሠረት ኤርምያስ ምርኮኞቹን አይሁድ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እያጓዘ ዮርዳኖስ ሲደርስ፥ ከአቤሜሌክና ከባሮክ ጋር ሆኖ ከባቢሎናውያን ጋር የተጋቡትን አይሁድ በመለየት ወደ ኢየሩሳሌም አትገቡም በማለት እንደ ከለከሏቸው፥ የተከለከሉት ሰዎችም ወደ ባቢሎን ቢመለሱ ባቢሎናውያን ደግሞ አንዴ ካገራችን ወጥታችኋልና አትመለሱም እንዳሏቸው፥ የተከለከሉት ሰዎችም ወደ ምድረ እስራኤል በመጓዝ አገር አቅንተው እንደ ኖሩ፤ አገሩንም “ሰማርያ” ሲሉ እንደ ሰየሙት ይናገራል፡፡
ይህ የተረፈ ኤርምያስ ትረካ በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛን የማይደፋ ሆኖአል፡፡ ለምን? ቢባል፡-
ሀ) ምርኮኞቹ አይሁድ ከባቢሎን በእነ ኤርምያስ መሪነት ወጡ የተባለበት ዘመን 66ኛ ዓመተ ፄዋዌ ነው፤ ም. 11፥15፡፡ ስለ ሆነም ከባቢሎን እንዲወጡ የሚፈቅድ ዐዋጅ ገና አልታወጀም፤ ም. 11፥11፡፡ ዘሩባቤልና ጓደኞቹ ገና አልተነሡም፤ ም. 11፥35፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደ ተመለከተው ሰባኛው የምርኮ ዓመት ሲፈጸም ከሜዶኖዊ ዳርዮስ ቀጥሎ የነገሠው ፋርሳዊ ቂሮስ አይሁድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደ፡፡ የመጀመሪያው ተጓዥ ቡድን መሪዎች እነ ዘሩባቤል እንደ ነበሩ ተመዝግቧል፤ ዕዝራ 1፥1-4፤ 2ዜና. 36፥21-23፡፡
ለ) ሰማርያ ስለ ተመሠረተችበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ከተረፈ ኤርምያስ ትረካ በጣም የተለየ ነው፡፡ በዐሥሩ የእስራኤል ነገድ ላይ በቴርሣ ነግሦ የነበረ ዘንበሪ “ሳምር” ከነበረ ሰው መሬት ገዛና በመሬቱ ላይ የሠራውን ከተማ “ሰማርያ” ሲል ሰየመው፤ 1ነገ. 16፥23-24፡፡ የዐሥሩ ነገደ እስራኤል መንግሥት በአሦር ንጉሥ በሰልምናሶር እስከ ፈረሰበት ጊዜ ድረስ ሰማርያ መናገሻ ከተማ ሆኖ ኖረ፤ 1ነገ. 16፥29፤ 22፥51፤ 2ነገ. 3፥1፤ 10፥36፤ 13፥1፡10፡፡ … ለመጨረሻም 18፥9-12፡፡
እንግዲህ ሰማርያ የተከተመበት ትክክለኛ ዘመን በተረፈ ኤርምያስ ከተጻፈው ዘመን የ385 ዓመት ያህል ቅድሚያ አለው፡፡
9. በም. 11፥40 የመጀመሪያውን የምርኮኞች ቡድን እየመራ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ የተባለው ኤርምያስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ (በ66ኛው ዓመተ ምርኮ መሆኑ ነው) ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ጸለየ ይላል፡፡
ቤተ መቅደሱማ ከተቃጠለ 66 ዓመታት ዐልፈዋል፤ ኤር. 52፥12፡13፡፡
ይቀጥላል
ጮራዎች, please change the bright orange background on the website. አይን ያጠፋል እኮ! የማነበው ጽሁፍ እየጣመኝ ሳነብ አይኔ ግን እየጠፋ ነው። ወደ ሌላ ተስማሚና የተረጋጋ ከለር እንድትለውጡልን እንጠይቃለን።
ReplyDelete