Tuesday, March 20, 2012

መሠረተ እምነት

በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
(ካለፈው የቀጠለ)

በአንድ ይሆዋ ከሁለት በላይ የሆኑ አካላት እንዳሉ የሚገልጹትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያውም ከብሉይ ኪዳን የመጀመሪው መጽሐፍ አንድ ባንድ መመልከታችንን እናስታውሳለን፡፡ በዚሁ ሁኔታ ጥናታችንን በመቀጠል የብሉይ ኪዳን አባቶች ይሆዋ በአካል ከሦስት እንደማይበልጥና እንደማያንስ አረጋግጠው እንደ ነበረ የዛሬው ዕትም ያስነብበናል፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሁለት

በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ አባቶች ይሆዋ በአካል ሦስት መሆኑን ተምረው አስተምረዋል፡፡ማስረጃ 1
በኦሪት ዘኊልቊ ም. 6 ሙሴ ከይሆዋ የተማረውንና ያስተማረውን የቡራኬ ትምህርት እንይ፤
ቊ. 24 ይሆዋ ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፡፡
ቊ. 25 ይሆዋ ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፡፡
ቊ. 26 ይሆዋ ፊቱን ወዳንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ፡፡

ይህ ጥቅስ “እኛ” እያለ ራሱን የገለጸውን የአንዱን ይሆዋ ሦስትነት ያስተምራል፡፡

አርዮሳውያን ግን “ይሆዋ፥ ይሆዋ፥ ይሆዋ” በማለት ሦስት ጊዜ መነገሩን አጋጣሚ ወይም አጽንኦተ ነገር (ነገርን ማጠናከር) አድርጎ በመቊጠር፥ በትንቢተ ሕዝቅኤል 21፥27 ካለው ጥቅስ ጋር ለማመሳሰል ይሞክራሉ፡፡ እግዚአብሔር በአጋጣሚ አይሠራም፤ አይናገርም፤ በዕቅድ ለዐላማ እንጂ (ኢያሱ 23፥14-15፡፡ ኢሳ. 55፥10-13)፡፡ ስለዚህ አጋጣሚ የሚሉትን እንለፈው፡፡

ቃላት ለንግግር ማጠናከሪያ (ለአጽንኦተ ነገር) እንዲያገለግሉ በሚደረግበት ጊዜ እያንዳንዱ ቃል የአንድ ዐረፍተ ነገር ባለቤት ሆኖ አልተነገረም፡፡  ለምሳሌ፥ በሕዝ. 21፥27 የተጻፈውን “ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፡፡” የሚለውንና በሌሎቹም ክፍሎች (በዘፍ. 22፥11፤ 1ሳሙ. 3፥10፤ 1ነገ. 13፥2፤ 2ሳሙ. 18፥33፤ ሐ.ሥ. 9፥4) የተጻፉትን እንመልከታቸው፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥቅሶች ከኦሪት ዘኊልቊ 6፥24-26 ጋር ብናነጻጽራቸው ከቶ አይመሳሰሉም፡፡ “ይሆዋ” የሚለው እያንዳንዱ ስም አንድ ቊጥር ተሰጥቶት ራሱን የቻለ አንዳንድ ዐረፍተ ነገር የተሠራለት ስለ ሆነ፥ በአንድ ዐረፍተ ነገር፥ በአንድ ማሰሪያ አንቀጽ ውስጥ ነገርን ለማጠናከር በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ቃል ሊቈጠር አይገባውም፡፡ ይልቁንም ይሆዋ የአካል ሦስትነት እንዳለውና እያንዳንዱም አካል የራሱ ግብር መብት እንዳለው ያስገነዝባል፡፡

በተጨማሪም አሮንና ልጆቹ የይሆዋን ስም ለበረከት በሕዝቡ ላይ የሚጠሩበት መንገድ እንዲሆን በድንጋጌ የወጣው ይኸው ሥሉስ የመለኮታዊ ስም አጠራር ፎርሙላ (ናሙና) መሆኑ ይህን ክፍል የሐሳቡ ቊልፍ መክፈቻ ያደርገዋል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔርም ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን” (2ቆሮ. 13፥14) ለማለት የበቃው ያለ ምክንያት (በአጋጣሚ) ወይም ለአጽንኦተ ነገር አይደለም፡፡ መነሻ ምክንያቱ “ለበረከት ስሜን በእስራኤል ላይ የምትጠሩበት መንገድ ይህ ይሁን፡፡ የሚለውን ድንጋጌና ከድንጋጌው ጋር የተሰጠውን ናሙና ትርጒም ከመረዳቱ የተነሣ እንደ ሆነ ሊያከራክር አይገባውም፡፡ (እንደ ገና ዘኊ. 622-27 ያንብቡ)።

ማስረጃ 2
በኦሪት ዘዳግም 6፥4፡፡ “እስራኤል ሆይ! ስማ፤ የኛ ኤሎሂም የሆነው ይሆዋ አንድ ይሆዋ ነው፡፡ ወይም አምላካችን እግዚአግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” ይላል፡፡

ይሆዋ በአንድ አካላዊ መንፈስ ብቻ የሚታወቅ ነው ለማለት ይህን ጥቅስ እንደ ማስረጃ ማቅረብ አለ ማስተዋል ነው፡፡ በአንድ (በነጠላ) አካላዊነት ስለሚታየውና ስለሚታወቀው ሰው ያ ሰው እኮ አንድ ነው ተብሎ ቢነገር ከሞኝነት ይቈጠራል፡፡ አንድ ነው ተብሎ የመነገሩ አስፈላጊነት፤ የሐሳቡም ውበትና አስገራሚነት ሰዎች ከአንድ ቊጥር በላይ ሆነው ሳለ አንድ ያደረጋቸውን ምስጢራዊ ሰንሰለት እንዲገልጽ ሆኖ በሚነገርበት ጊዜ ነው፡፡

ለምሳሌ፥ በጋብቻ ቃል ኪዳን የተጣመሩ ወይም የተዋሐዱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሁለት ሆነው ሳለ በቃል ኪዳኑ ምክንያት “አንድ ናቸው” ይባላል (ዘፍ. 2፥24፣ ማቴ. 19፥4-6)፡፡

ባልን ለብቻው አንድ ሰው መሆኑን መግለጽ አላስፈላጊ ነው፡፡ ሚስትንም ለብቻዋ አደናጋሪ ያልሆነውን አንድ አካልነትዋን ሥራዬ ብሎ መናገር ማደናገር ነው፡፡ ዳሩ ግን በየራሳቸው ምልአተ አካል፥ ምልአተ ባሕርይ፥ ምልአተ ሕላዌ ያላቸው ወንድና ሴት እግዚአብሔር በፈጠረላቸው የጋብቻ መጣመር ምክንያት የተገኘውን፥ በዐይን እይታ ሳይሆን በማስተዋል ብቻ መረዳት የሚቻለውን ምስጢራዊ አንድነት መናገርና መጻፍ ተገቢም አስፈላጊም ይሆናል፡፡

እንደዚሁም “ኢየሱስ አዳኜና ጌታዬ ነው” በሚል አንድ እምነት የተሰባሰቡና ምስጢረ ጥምቀትና ምስጢረ ቊርባንን የተቋደሱ ምእመናን “አንድ አካል” ናቸው ተብሎ መነገሩ የማይታይና የማይጠበቅ አድርጎ ሥጋዊ አእምሮ ያቆመውን የልዩነት ግድግዳ ለማፍረስ ነው (ሮሜ 12፥3-5፤ 1ቆሮ. 12፥12-13፤ ገላ. 3፥26-28)፡፡

እንግዲህ ሦስቱ የይሆዋ አካላት ብዛታቸው በአንድነታቸው አለ መደምሰሱ አንድነታቸውም በሦስትነታቸው አለ መናጋቱ ሊነገር የሚገባው ዘመናት የማይሽሩት ድንቅ ነገር አይደለምን?

ይሆዋም በኤሎሂምነት ራሱን ቢገልጽም፤ እኛ የማለት መብት ቢኖረውም፤ እንፍጠር፥ እንውረድ እያለ ምክክር ቢያደርግም “አንድ ይሆዋ” እንደ ሆነ ታወጀ (ዘዳ. 6፥4)፤ ዕወጃው አስፈላጊነት ነበረውና፡፡ በነጠላ ቊጥር (አንድ አካልነት) የሚታወቅ ቢሆንማ ኖሮ ዕወጃው እንዴት አስፈላጊ ይሆን ነበር?


ማስረጃ 3
በትንቢተ ኢሳይያስ 6፥1-10 ነቢዩ የይሆዋን ክብር ማየቱ የተገለጸበትን ክፍል እናነባለን፡፡ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ይሆዋ የሠራዊት ጌታ” እያሉ ሱራፌል አመሰገኑ፡፡ አመስጋኞቹ በከበቡት ዙፋንም ላይ ከተቀመጠው ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ይሆዋ “ማን ይሄድልናል? ማንንስ እልካለሁ?” የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡

ይሆዋም ነቢዩን ሲናገረው “ሂድ፥ ይህን ሕዝብ መስማትን ትሰማላችሁ፥ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ፥ አትመለከቱምም፤ በላቸው፡፡ በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቊር፥ ዐይናቸውንም ጨፍን” አለው፡፡

የዚህን ቃል መልእክት በተናጋሪው ይሆዋ መንፈስ የምንመረምርና የምናስተውል ከሆነ ከዚህ ከኢሳይያስ ራእይ የሚከተሉት ትምህርታዊ ነጥቦች ጐልተው ሊታዩን ይገባል፡፡

ሀ. ሱራፌል ያመሰገኑትና ነቢዩ በራእይ የተመለከተው ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ የሆነውን ባለ አንድ ዙፋን ይሆዋ እንደ ሆነ፤
ለ. ሦስት ጊዜ ቅዱስ ተብሎ መጠራቱ “እኛ” በማለት ራሱን የሚያስተዋውቀው ይሆዋ ተገቢ መግለጫ እንጂ አጋጣሚ እንዳልሆነ፤ ከዚያውም ዘንድ ሦስትነቱን እንደሚያስተምር፤
ሐ. ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ በመባል የተመሰገነው ይሆዋ “ማን ይሄድልናል?” ሲል የአካል ሦስትነቱን፤ ማንንስ እልካለሁ? በሚልበት ጊዜ ግን ባለ አንድ ዙፋን ገዥነቱን እንደሚያስረዳ፤
መ. ከዚህም በመነሣት የብሉይ ኪዳን አባቶች የይሆዋን ሦስትነቱንና አንድነቱን በማመንና በመስበክ ከሐዲስ ኪዳን አማኞች የሚስተካከሉ እንደ ነበሩ፤ እናምን ዘንድ የቃሉ መልእክት ያስገድደናል፡፡

ማስረጃ 4 
ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ም. 12፥36-42 የሚያስተምረንን እንቀበል፡፡ ኢሳይያስ በዙፋናዊ ክብር ካያቸው ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ይሆዋ ከተባሉትና “እኛ” በማለት ራሳቸውን ከገለጹት ሦስት ሕያዋን አካላት (ሥላሴ) አንደኛው ሕያው አካል ሰው ሆኖ በምድር የተመላለሰው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ወንጌላዊው ያረጋግጣል፡፡ “ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ቢያደርግም፥ ነቢዩ ኢሳይያስ … የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም፡፡  ኢሳይያስ ደግሞ በዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው ዐይናቸውን አሳወረ፥ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው፡፡ ኢሳይያስ ክብሩን ስላየ፥ ይህን አለ፤ ስለ እርሱም (ስለ ኢየሱስ)ተናገረ፡፡”

ኢሳይያስ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ በመባል ሲመሰገኑ ካያቸው፤ ማንስ ይሄድልናል? ሲሉ ካዳመጣቸው መካከል አንደኛው ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) እንደ ሆነ ወንጌላዊው በግልጽ አልጻፈምን?


ማስረጃ 5
ኢሳይያስ ካያቸው ሦስት ጊዜ ቅዱስ በመባል ከተመሰገኑትና በእኛነት ራሳቸውን ከገለጹት መካከል አሁንም አንደኛው ሕያው መንፈሳዊ አካል መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ወንጌላዊ ሉቃስ ያረጋግጥልናል፡፡ እንዲህ ሲል “… መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፥ መስማትን ትሰማላችሁ፥ አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፥ አትመለከቱም፡፡ በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ደንቊሮአል፤ ዐይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው ሲል መልካም ተናገረ” (ሐ.ሥ. 28፥25-27)፡፡

በሱራፌል እየተመሰገነና እየከበረ በአንድ ዙፋን ላይ ነቢዩ የተመለከተው “ይሆዋን” ነበረ (ኢሳ. 6፥1-3)፡፡ ሆኖም የተመለከተው አንድ ሕያው አካላዊ መንፈስ ብቻ አልነበረም፡፡ ማለት “አብ” ብቻ አልነበረም፡፡ እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ አገላለጽ “ወልድም” የዚያው ክብርና የዚያው ዙፋን ባለቤት ነው፡፡  እንደ ወንጌላዊ ሉቃስም ትምህርትና ገለጻ “መንፈስ ቅዱስ” የዚያው ክብርና የዚያው ዙፋን ባለቤት ነው፡፡ እንዲህ ስለ ሆነም ይሆዋ ራሱን “እኛ” በማለት ለነቢዩ ገለጸ፡፡ ስለዚህም ሱራፌል ሦስት ጊዜ ቅዱስ እያሉ አመሰገኑ፡፡

ከዚያ ክብርና ዙፋን አነስተኛ ድርሻ አለው የሚባል የለም፡፡ ይገርማል! በሐዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ የሚገኙ ሰባልዮሳውያንና አርዮሳውያን የብሉይ ኪዳን ዘመኑ ኢሳይያስ ያየውን ያን ዙፋንና ክብር እነዚህንም ባለ አንድ ዙፋኖች አላዩም፤ የሱራፌልንም ሆነ የባለዙፋኖችን ድምፅ አልሰሙም (የይሆዋንም ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል ማን ይሄድልናል ኢሳ. 6፥8)፡፡

ምናልባት ማየትን አይተው ይሆናል፥ አልተመለከቱም እንጂ፤ መስማትንም ሰምተው ይሆናል አላስተዋሉም እንጂ፡፡ የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት ልክ በአይሁድ እንደ ተፈጸመ በእነርሱም ተፈጽሞባቸዋል ማለት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ግን እንደ ኋለኞቹ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያት ሰምተውት፥ አይተውት፥ ተመልክተውት አስተውለውት ነበር፡፡

ማስረጃ 6

በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል የተላለፈልን ተጨማሪ የሥላሴ ትምህርት አለ፡፡ (ኢሳ. 48፥12-16፤ የ1947 ዓ.ም. የዐማርኛ ትርጒምና ዕትም)፡፡

ሰው ሆኖ ሰውን የማዳን ድርሻን የወሰደው “ወልድ” በነቢዩ ዘመን “… ያዕቆብ ሆይ!  የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ እኔ ፊተኛ ነኝ፤ እኔም ኋለኛ ነኝ፡፡ … አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል፡፡” ሲል ድምፁን አሰማ፡፡ ጥቅሱ የሁለት ላኪዎችና የአንድ ተላኪ መኖርን ያስተምራል፡፡ ላኪዎች እግዚአብሔርና መንፈሱ (አብና መንፈስ ቅዱስ) ሲሆኑ ተላኪው ደግሞ ወልድ ነው፡፡ (ከዮሐ. 17፥3፡18 ጋር ማመሳከር ይጠቅማል)፡፡

ታዲያ ሁለት ላኪዎችና አንድ ተላኪ ሦስት አይባሉምን? ሥላሴ ማለትኮ ይኸው ነው፡፡
-   ሁሉን የፈጠረ ነው (ዮሐ. 1፥1-3)፡፡
-   ከሁሉ በፊት የነበረ፤ ሁሉንም አሳልፎ የሚኖር (አልፋና ዖሜጋ) ነው (ራእ. 1፥17-18፤ 22፥12-13

ማጠቃለያ

ከዚህ በላይ ከማስረጃ 1-6 ያቀረብናቸው ጥቅሶች በማስረጃነት ለቀረቡለት ነጥብ (ጭብጥ) ሁለት በትክክል መመስከር አለመመስከራቸውን ጥቅሶቹን ደጋግመን በማንበብ እናረጋግጥ፡፡

በእኛ ግንዛቤ እነዚህ ማስረጃዎች፡-
ሀ. የሠራዊት ጌታ ይሆዋ በአካል ሦስት (ሥሉስ፤ ሥላሴ) መሆኑ፤
ለ. ከሥላሴ እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በራሱ ይሆዋ የሠራዊት ጌታ ተብሎ የመጠራትና የመመለክ ባለመብት እንደ ሆነ፤
ሐ. የሥላሴ ዙፋንና ክብር የማይከፋፈል ነገር ግን በአንድ መለኮተ ይሆዋ ጽናት መቆሙን ያስጨብጡናል፤

ስለዚህም ለእኛ ሦስቱ (ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ) ማለት አንድ “የሠራዊት ጌታ ይሆዋ” ማለት ነው፡፡ አንዱም ይሆዋ በሦስትነቱ እኛ የማለት መብት ያለው (ሦስት ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ) ማለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment