Monday, May 22, 2017

የዘመን ምስክር



 READ PDF
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ትግራይ (1887 - 1983 ..)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከሥተውና በርካታ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተው ካለፉ ታላላቅና ስመ ጥር አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ተጠቃሽ ናቸው። እኒህ አባት በእምነታቸው የጸኑ፣ በመልካም ሥራቸው የተመሰከረላቸው፣ በትምህርታቸው ብሉያትንና ሐዲሳትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን በሚገባ የተረዱ፣ በስብከታቸው፣ በተደማጭነታቸው የሚታወቁ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ላመኑበት እውነት ብቻቸውንም ቢኾን የሚቆሙ፣ በፈሊጥና በጥበበ ቃል የማይረሳና ጠንካራ መልእክት ማስተላለፍ የቻሉ፣ ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ የተረዱትን እውነት በሚገባ በመስበክ የኖሩ መምህር ወመገሥጽ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትሻሻልና ትውልዱን ልትታደግ የምትችለው በትምህርት ብቻ መኾኑን ያመኑ፣ አምነውም በትምህርት ላይ ብዙ የሠሩ ታላቅ አባት ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸውና ሕያው ሥራዎቻቸው እነሆ፣  


ልደት እድገት እና ትምህርት
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከቄስ ገብረ ኢየሱስ ፈቃዱና ከወ/ሮ (በኋላ እማሆይ) ወለተ ኢየሱስ ምሕረተ አብ ሐምሌ 12 ቀን 1887 ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ በአካለ ጕዛይ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ኩርባርያ በተባለ አጥቢያ ተወለዱ። በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሲጠመቁም ገብረ መስቀል ተባሉ። በዚህ ስመ ክርስትና ጳጳስ እስከ ሆኑ ድረስ ተጠርተዉበታል። ወላጆቻቸው የወለዷቸው በስእለት ስለ ነበር፣ በተወለዱ በሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜያቸው በአካባቢያቸው ወደሚገኝ የአቡነ ብፁዕ አምላክ ሥላሴ ገዳም ወስደው ለማኅበረ መነኮሳቱ ሰጧቸው። ማኅበረ መነኮሳቱም ወላጆቻቸው በእምነታቸው መሠረት የገቡትን ቃል መፈጸማቸውን በማድነቅና በማመስገን፣ እስከ ስድስት ዓመት ድረስ እዚያው በቤታቸው እንዲያሳድጓቸው በመምከር አሰናበቷቸው። ስድስት ዓመት ሲሞላቸውም አምጥተው አስረከቧቸውና ከንባብ ትምህርት እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ተምረው በዘጠኝ ዓመታቸው የዲቁና ማዕርግ ተቀበሉ።

በ1903 ዓ.ም. በተንቤን አውራጃ በጭኽ ደብረ ገነት ገዳም ጾመ ድጓ ጀምረው አንድ ጊዜ ከዘለቁት በኋላ ወደ እንደርታ ተዘዋውረው በደብረ ኀይላ ገዳም ጸዋትወ ዜማ፣ ማለትም ድጓ ከመሪጌታ ወልደ እግዚእ፣ ቅዳሴ ከየኔታ ሀብተ ሥላሴ፣ ቅኔ ከመምህር ገብረ ሕይወት ተምረዋል። ኾኖም የቅኔን ትምህርት በደንብ አጠናቆ ለማወቅ በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ ዐድዋ በሚገኘው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ከመምህር ስብሐቱ ዘንድ የቅኔን ትምህርት ከእነ አገባቡና ከእነ እርባ ቅምሩ አጠናክረዋል።
በ1910 ዓ.ም. ወደ ጐንደር ሄደው የድጓ ትምህርት የከለሱ ሲኾን፣ አቋቋምና ዝማሬ መዋስእት በማንኮ ቅዱስ ሚካኤል ደብር ተምረዋል። ከዚያ ወደ ዙር አምባ አቅንተው ከየኔታ ኮከብ ዝማሬ መዋስእት አስመስክረዋል (በዝማሬ መዋስእት ተመርቀዋል)። በኋላም ወደ ሴይኮ ገዳም ሄደው የሰለልኩላን ቅዳሴ ተምረዋል። እንደ ገናም ወደ ጐንደር ተመልሰው አቋቋም አስመስክረዋል። በዜማ፣ በአቋቋምና በቅኔ በኩል የተሟሉ ከሆኑ በኋላ ዋና ዐላማቸውና ፍላጎታቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን መማርና መመርመር በመሆኑ፣ በጊዜው ስመ ጥር ከነበሩት ከመምህር አካለ ወልድ መጻሕፍትን ለመማር ምኞት ነበራቸው። ይኹንና ምኞታቸው ሳይፈጸም የመምህር አካለ ወልድን ዜና ዕረፍት ሰምተው እጅግ ዐዘኑ። በአካል የሚያውቋቸው ያኽልም ስቅስቅ ብለው አለቀሱ። በዚህ ጊዜ የእርሳቸው ደቀ መዝሙር የነበሩት መምህር ደስታ (በኋላ ብፅዕ አቡነ አብርሃም) አዲስ አበባ ነበሩና በእርሳቸው ተጽናንተው ከእሳቸው ዘንድ ለመማር በ1914 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወደሚገኘው መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል (ግቢ ገብርኤል) ገቡ።
በግቢ ገብርኤል ከመምህር ደስታ (ከብፅዕ አቡነ አብርሃም) የመጻሕፍትን ትርጓሜ ሲማሩ ተወዳጅ ተማሪ ኾነው ነበር። በጉባኤ ጊዜ በሚያቀርቧቸው ጥልቅ ጥያቄዎች፣ ከሌሎቹ ለሚቀርቡት ጥያቄዎች በሚሰጡት ፈጣን ምላሽ ይደነቁ የነበሩት መምህራቸው “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” ይሉ ነበር ይባላል። ይህን የብፁዕነታቸውን ብልህነትና ልዩ ተሰጥኦ ከመምህራቸው የሰሙትና ያዩት ንግሥተ ንግሥታት ዘውዲቱ፣ በቤተ መንግሥታቸው ተቀምጠው እንዲማሩ አደረጉ። በዚያም መጻሕፍተ ሐዲሳትን መጻሕፍተ ሊቃውንትንና መጻሕፍተ መነኮሳትን አጠናቀው ተምረዋል። በኋላም ከመምህር ፊላታዎስ መጻሕፍተ ብሉያትን ተምረዋል። አራቱንም ጉባኤ ተምረዋል ማለት ነው።

ለሀገር ምን አበረከቱ?
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በሀገር ወዳድነታቸው ይታወቃሉ። የሕይወት ታሪካቸውን የጻፉት ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሳ፣ “ከኹሉ በላይ ሀገርን መውደድ ለብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ልዩ መታወቂያቸው ነበር።” ይላሉ (ሕያው ስም፣ ገጽ 90)። ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በእንባ ጭምር ሲገልጹ እንደ ታዩም ጽፈዋል። “በአካልም በታሪክም ብዙ ሀገር አይተናል፤ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ኹሉን አሟልቶ የፈጠራት የተባረከች የተቀደሰች ሀገር የለችም። ስለዚህ ስትተኙም ስትነቁም ኢትዮጵያን አስቧት። በረከተ እግዚአብሔር እንዳይለያት ጸልዩላት። ክፉ ነገር እንዳይደርስባት አንዳንድ የእንባ ዘለላ አፍስሱላት።” ይሉ ነበር (ዝኒ ከማሁ ገጽ 90)። ከዚህ በመነጨ ስሜት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሀገራቸውን በብዙ ኹኔታ አገልግለዋል። ከሚጠቀሱላቸው መካከል አንዱ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ነው።    
ጣሊያን አገራችንን በወረረች ጊዜ ከዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጋር ጣሊያንን ለመግጠም ወደማይጨው ዐብረው የዘመቱ ሲኾን፣ የማይጨው ጦር ሲበታተን፣ ደሴ ላይ የወሎን ዐርበኞች እንዲያስተባብሩ የደሴ መድኀኔ ዓለም አስተዳዳሪ ኾነው ተሾሙ። ጦርነቱ ሳይሳካ ቀርቶ አገራችን በጣሊያን እጅ በወደቀች ጊዜ “ንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጄኔቫ ይሂዱ አይሂዱ?” የሚለው ሐሳብ ቀርቦ ሳለ፣ መምህር ገብረ መስቀል “እኛ ግርማዊነታቸው ሕዝባቸው የኾነውን ይኹኑ እንጂ ሕዝባቸውን ጥለው ወደ ውጭ ሀገር ይሂዱ ብለን አንደግፍም። ምክንያቱም የግርማዊነታቸው ከሀገር መውጣት የሕዝቡን ሞራል ዝቅ ያደርጋል፤ ለታሪክም የሚመች አይደለም፤ ጠባሳ ታሪክ ትቶ ያልፋል።” ሲሉ ምክር ሰጥተው ነበር። ኾኖም ንጉሡ ይሂዱ የሚለው ድምፅ ስለ በረታ ወደ ውጪ ሄዱ።
መምህር ገብረ መስቀልም በወረራው ዓመታት ዐርበኞችን በማበረታታት፣ ሕዝቡን ለድጋፍ ሲቀሰቅሱ በጣሊያኖች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር ችለው ነበር። ከዚህ የተነሣ ጣሊያኖች በጥብቅ ይፈልጓቸው ነበር። እንዲያውም “መምህር ገብረ መስቀልን ይዞ ላመጣልን 5 ሺሕ ብር እንከፍለዋለን” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈው ነበር። ኾኖም እርሳቸውን አሳልፎ የሰጠ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ይልቁንም እርሳቸው እንደ መሰከሩት “የአዲስ አበባ ሕዝብ ለራሱ ሳይሳሳ የርሳቸውን ሕይወት ለማትረፍ ያደረገው ተጋድሎ የሚረሳ አይደለም።”
ከዚያ በኋላ ጣሊያኖች የሚመክረንና እውነቱን በትክክል የሚነግረን እንፈልጋለን ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፣ ይህን ለክፉ እንዳላሉ ከተረጋገጠ በኋላ መምህር ገብረ መስቀል (ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ) ዱካደአውስታ፣ ዶክተር ፍራንኮ ጀነራል ግራዚያኒ ባሉበት ቀረቡ። ከዚያ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠላናል? ወይስ ይወደናል? ሰላም እንዲገኝስ ምን ብናደርግ ይሻላል? እውነቱን ይንገሩን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እርሳቸውም ወደ ኋላ ሳይሉ እውነቱን እንዲህ ሲሉ ነገሯቸው። “አዎን የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን የሚወር፣ ነጻነቱን የሚደፍር አይወድምና ይጠላችኋል፤ መራችሁታል። ስትጨፈጭፉት ስትወሩት እንዴት ሊወዳችሁ ይችላል?” በማለት መለሱ።
በዚህ ንግግራቸው የተደናገጡት የጎጃሙ ራስ ኀይሉ “አንቱ እንዴት እንደዚህ ደፍረው ይናገራሉ? መቼም ይህች ምላስዎ አታከርምዎትም ቢሏቸው፣ እሳቸውም “እውነቱን ተናግራ ትቈረጥ” ማለታቸው ይነገራል። ለኢጣሊያ ባለሥልጣኖችም ያገኙትን መረሸን እንዲያቆሙ፣ ሕዝብን በመደዳ መጨፍጨፍ እንዲተዉ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ከማቃጠል ሀብቱንና ንብረቱን ከመዝረፍ እንዲታቀቡ በጅምላ ያሰሯቸውን ኢትዮጵያውያንን በተለይም ሕፃናትን ሴቶችንና ሽማግሌዎችን እንዲለቁና ይህን የመሳሰለው የተካተተበት ሰባት ነጥብ የያዘ ጽሑፍ ሰጧቸው። በዚህ መሠረት በናኩራ በሞቃዲሾና በሌሎችም እስከ ሮም ድረስ ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ተፈቱ። ይህም ለመምህር ገብረ መስቀል ትልቅ አክብሮት አስገኝቶላቸዋል (ገጽ 30)።

ለቤተ ክርስቲያን ምን አበረከቱ
1. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስና እንዲኖራት ታግለዋል
በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሥርዐተ ቀብር ላይ ተገኝተው ቃለ ቡራኬ ያሰሙት የቀድሞው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲን የነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ስለ እርሳቸው በሰጡት ምስክርነት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብጻውያን የጵጵስና አስተዳደር ተላቃ ራሷን ችላ እንድትተዳደርና ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዲሾሙ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉት ኢትዮጵያውያን አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አንዱና ዋነኛው መሥራች የነበሩ…” ናቸው ብለዋል። በርግጥም ይህ ምስክርነት እውነት መኾኑን የሚያረጋጥልን ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ገና ጳጳስ ሳይኾኑ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለ1600 ዓመታት ከዘለቀው የግብጻውያን አመራር ነጻ ለማውጣትና ራሷን ለማስቻል የተደረገው ሰፊ እንቅስቃሴና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፍጻሜን እንዲያገኝ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን ነው።
ከብዙ ወጣ ውረድና ትግል በኋላ ግብጻውያኑ የምንሾማቸውን አባቶች መርጣችሁ ላኩልን ብለው ወደ ኢትዮጵያ መልእክት ባስተላለፉት መሠረት የሚከተሉት አባቶች ተላኩ። እነርሱም፦
መ/ር ደስታ (አቡነ አብርሃም)
መ/ር ወልደ ኪዳን (አቡነ ይስሐቅ)
መ/ር ኀይለ ማርያም (አቡነ ጴጥሮስ)
መ/ር ኀይለ ሚካኤል (ብፁዕ አቡነ ሚካኤል)
ሲኾኑ፣ ከእነዚህ ጵጵስናን ሊቀበሉ ከሄዱት አባቶች ጋር መልእክተኞች ኾነው ወደ ግብጽ ከሄዱት መልእክተኞች መካከል መምህር ገብረ መስቀል አንዱ ነበሩ። ግብጽ ከደረሱ በኋላ ግን ያልተጠበቀ ነገር አጋጠማቸው። ይኸውም ግብጻውያኑ “ጳጳስ እንዳይናቅ ለኢትዮጵያውን ጳጳሳት ሙሉ ሥልጣን አንሰጥም” የሚል ምክር በመምከርና በጽሑፍ በማዘጋጀት፣ ጵጵስና ለመቀበል ለሄዱትና ዐብረዋቸው በመልእክተኛነት ለተጓዙት አባቶች ወረቀት በተኑ። የተበተነው ጽሑፍ የሚሾሙትን ኢትዮጵያውን ጳጳሳትን ሥልጣን የሚገድብ ነበርና፣ መልእክቱን አንብበው የተረዱት መምህር ገብረ መስቀል ዕጩዎቹ በወረቀቱ ላይ ፈርመው ሌላ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በሚል ወረቀቱ እንዲሰበሰብ አደረጉና በበነጋው ውይይቱ ቀጠለ። ግብጻውያኑም በግልጽ “ልንሾማችሁ ከፈለጋችሁ ውል ግቡልን፣ ፈርሙልን” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ይህ ኹኔታ እጅግ ያሳዘናቸው መምህር ገብረ መስቀል ሐሳቡን በመቃወም ቀጥሎ ያለውን ታሪካዊ ንግግር አደረጉ።
“እኛ ወደዚህ የመጣነው እንሾማለን ሥልጣን እንጨምራለን ብለን እንጂ ውል ልንገባ፣ የነበረንንም ሥልጣን ለማስቀረት አይደለም፤ እናንተም የሚሾሙትን  አባቶች መርጣችሁ ስደዱ ባላችሁት መሠረት መጥተናል። እናንተ ግን በሀገራችን ሳለን ያልሰማነውን ያላሰብነውን ሌላ ምክንያት ይዛችሁ ጠበቃችሁን። በመሠረቱ መዋዋል መፈራረም ሥጋዊ ነው፤ በመንፈሳዊ መዋዋል መፈራረም የለም። ሐዋርያት ሲሾሙ ውል ነበራቸውን? እስኪ ማርቆስ የተዋዋለውን ውል ፊርማውን አሳዩን? እኛኮ ጥንታውያን አባቶቻችንን እንዳናስቀይም ግንኙነታችን እንደ ነበረው በፍቅር እንዲቀጥል ብለን ነው እንጂ እናንተ አባትነታችሁን ብትነሡን ከሌሎች እንደምናገኘው ልባችሁ ያውቀዋል። እንደ ሥርዐቱ እኮ ጳጳስ ኤጲስ ቆጶስ ሊሾም የሚችለው ሕዝብ የመረጠው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም በሃይማኖት የሚመራውን ጳጳስ ኤጲስ ቆጶስ መርጦ ለመሾም ይችላል። ደግሞም ትዝ ይበላችሁ፤ ሀገራችሁ አሸዋ በረሓ ነው። ቆማችሁ የምትሄዱበት ከሀገራችን በሚፈልቀው በዐባይ ውሃ ነው። እናንተ መንፈሳዊ ምግባችንን መብታችንን ብትገድቡብን እኛም አባቶቻችን ይሉት እንደ ነበር ሥጋዊ ምግባችሁን  የአባይ ወንዝን መገደብ (መከልከል) እንችላለን። ውል ግቡልን የምትሉ ከኾነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተዋዋሉ እንጂ ከእኛ ጋር አይደለም። አኹንም ትሾሙ እንደሁ ሾማችሁ ስደዱን፤ እማትሾሙን ከኾነ ደኅና ኹኑ ብላችሁ አሰናብቱንና ወደ ሀገራችን እንመለስ” አሉ።
በስፍራው የተገኙና በግብጽ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ነገሩን ለመስማት ተሰብስበው ስለ ነበር፣ የመምህር ገብረ መስቀልን (ብፁዕ አቡነ ዮሐንስን) ታሪካዊ ንግግር በሰሙ ጊዜ  ድጋፋቸውን በጭብጨባ ገለጹ። ግብጻውያኑም በኾነው ነገር መደናገጥና መከፋፈል ውስጥ ገቡ። እኩሎቹ “ይፈርሙልን” በሚለው ዐቋማቸው ሲጸኑ፣ እኩሌቶቹ ግን “እንሾማችኋለን ብለን ጠርተን እንዴት ፈርሙ እንላቸዋለን?” ወደ ማለት ገቡ። የነገሩ አካሄድ ያላማራቸው ፓትርያርኩም መልሱን ከሰዓት እንነግራችኋለን ብለው ስበስባው እንዲበተን አደረጉ። ስብሰባው ከሰዓት በኋላ ቀጥሎ ወደ ስምምነቱ ከተመጣ በኋላ፣ ኢትዮጵያውያን አባቶችን “ነገ ትሾማላችሁ፤ ተዘጋጅታችሁ ዕደሩ” አሏቸው። በማግስቱ ግንቦት 25/1921 ዓ.ም. ከላይ ስማቸው የተዘረዘረው አባቶች ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዚህ የተነሣ ግብጻውያኑ መምህር ገብረ መስቀልን “ገብረ መስቀል ነቀለ” በማለት ይጠሯቸው እንደ ነበርና እንዲህ ያሏቸውም፣ “ከኢትዮጵያ ነቀሉን” ለማለት ነው። መምህር ገብረ መስቀልም በዚያው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ምንኩስናን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላም የጎጃምና የበጌምድር ጳጳስ ኾነው የተሾሙትን መምህራቸውን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ተከትለው በመሄድም ትምህርታቸውን ያጠናከሩ ሲኾን፣ መምህራቸው ሥራ ይበዛባቸው ስለ ነበር እርሳቸውን ተክተው ያስተምሩ የነበሩት መምህር ገብረ መስቀል ነበሩ። በ1923 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ለጕዳይ መጥተው ሳለ መምህር ገብረ መስቀልም ዐብረዋቸው መጥተው ነበርና፣ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ጎጃም ሊመለሱ ሲሉ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ መምህር ገብረ መስቀልን እንዲቀሩ አድርገው በቤተ መንግሥታቸው በማስመቀጥ የዘውድ አማካሪ አደረጓቸው። እውነት ነው ብለው ያመኑበትን ነገር ሳይፈሩ ከመናገር የማይቈጠቡ አባት ስለ ነበሩም፣ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ያደንቋቸውና ያከብሯቸው ነበር። በመኳንንቱ ዘንድም ተደማጭነታቸው ከፍተኛ ነበር።

1. አብያተ ክርስቲያናትን አስተዳድረዋል 
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ጳጳስ ከመኾናቸውም በፊት ለሀገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ያበረከቷቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦዎች አሉ። ከ1928 – 1934 ዓ.ም. የደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው የሠሩ ሲኾን፣ የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ቅዳሜና እሑድ ካህናቱን እየሰበሰቡ ማስተማርንና ማሠልጠንን ነበር። ትኵረታቸውም መምህራነ ንስሓ የሆኑት ቀሳውስት ኀላፊነታቸውን ዐውቀው የንስሓ ልጆቻቸውን በሚገባ እንዲመክሩና እንዲያስተምሩ፣ በቃላቸው የሚያስተምሩትን በተግባርም ኾነው እንዲገኙ ማድረግ ነበር። ካህናቱንና ምእመናኑን በማስተባበርም ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች የሚስፋፉበትንና ስብከተ ወንጌል የሚጠናከርበትን ሥራ ሠርተዋል (ሕያው ስም ገጽ 31)።
በቀጨኔ መድኀኔ ዓለም የጀመሩት የስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው እጅግ ሰፊና ከሩቅም ከቅርብም ብዙዎችን የሳበ እንደ ነበር የሚመሰክሩ አሉ። ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰጡት ምስክርነት አቡነ ዮሐንስ “ጥልቀት ባለው ትምህርታቸው ጉባኤ በጣም ሰፍቶላቸው ነበር። ጉባኤው የቀጨኔ ነዋሪዎች ብቻ የሚሰበሰቡበት ጉባኤ ሳይኾን፣ ከሩቅም ከቅርብም የሚመጣ ብዙ ሕዝብ ነበራቸው። እንዲያውም በካዛንችስ ነዋሪ የነበሩ አንዲት እናት በጣዕመ ትምህርታቸው ስለ ተማረኩ የሳቸውን ትምህርት ላለማጣት ሲሉ መኖሪያ ቤታቸውን ለሌላ ሰው አከራይተው እሳቸው ግን ቀጨኔ አካባቢ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር።” ብለዋል (ዝኒ ከማሁ 131)። 
ከቀጨኔ ተዛውረው የበአታ ገዳም አስተዳዳሪ ኾነው ሳለ፣ ከዚህ ሹመት ጋር የዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (የአቡነ ባስልዮስ) እንደ ራሴና በወቅቱ የመንፈሳዊ ጉባኤ ም/ፕሬዚደንት በመኾን አገልግለዋል። በዚህ ሹመት ላይ ኾነው በነበራቸው የአስተዳደር ችሎታና ሥራ፣ የአመራር ስልታቸውም በዘመኑ ቤተ ክህነቱ የተሻለ መልክና ሥርዐት እንዲኖረው ሠርተዋል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 33)።
በ1940 ዓ.ም. የርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ንቡረ እድ ኾነው የተሾሙ ሲኾን፣ በጊዜው የአክሱም ንቡረ እድ የአውራጃው አስተዳዳሪም ስለ ነበር ሕዝባዊ አስተዳደርና አመራር መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ ወቅት ከመንፈሳዊው አገልግሎት ባሻገር የፍርድና የዳኛነት ችሎታቸው ይበልጥ የታየበት ነበር። በሳምንት አንድ ቀን ችሎት ላይ እየተገኙ ይግባኝ ይሰሙ፣ ውሳኔም ይሰጡ ነበር። ጸሓፊዎቻቸው ባለጕዳዮችን ዛሬ ነገ እያሉ እንዳያጕላሉ “ውሳኔ ሰጥታችሁ በቶሎ አሰናብቷቸው” የሚል ትእዛዝ ይሰጡ ነበር። ይህን ተላልፈው የተገኙና ባለ ጕዳዮችን ያጕላሉትን ጸሓፊዎች የተጕላሉ ባለ ጕዳዮችን ወጪ እንዲከፍሉ ያደርጉ ነበር። ከበታች ያሉ ዳኞችና አስተዳዳሪዎች ድኻ እንዳይበድሉ፣ ፍርድ እንዳያጓድሉ፣ መማለጃ እንዳይበሉ ምክርና ማስጠንቀቂያ ይሰጡ ነበር (ዝኒ ከማሁ ገጽ 35)።
በዚህ ዘመን ሀገር ያስጨነቀ አንድ ሽፍታ ተይዞ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለና ከእስር ተፈትቶ ሊለቀቅ ሲል ንቡረ እድ ገብረ መስቀል አስጠሩትና “ምነው ሙሉ አካል፣ ጕልበት እያለህ ሠርተህ እንዳትበላ አንተን የመሰለ ጐበዝ የሰውን ገንዘብ መቀማት መዝረፍ እንዴት መረጥህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም ሲመልስ “ይህን እንድፈጽም ያስገደደኝ ድኽነቴ፣ ማጣቴ ነው” አላቸው። በዚህ ጊዜ አንድ ጥማድ በሬ የሚገዛበትን ብር ከኪሳቸው አውጥተው በመስጠት “እንግዲህ ወዲህ በሬዎችን ገዝተህ እያረስህ ራስህንና ቤተ ሰቦችህን እየረዳህ ኑር። ለሌላውም መልካም አርኣያ ሁን” ብለው ባልደረባ ሰጥተው አሰናበቱት። ያም ሰው በኑሮውም በሕይወቱም ተለውጦ ከራሱ ዐልፎ ሌላውን እስከ መርዳት ደርሶ የነበረ ሲኾን እየመጣ ይጠይቃቸውም ነበር። ሲምል እንኳ፣ “ገብረ መስቀል ይሙት” ይል ነበር ይባላል። እንዲሁም “ኹለተኛ የወለዱኝ በሕይወት እንድኖር ከሰው ብቻ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋራ በገንዘባቸው ያስታረቁኝ ፍጹም አባቴ ናቸው” እያለ ይናገር ነበር (ዝኒ ከማሁ ገጽ 37)።

. ጵጵስና
ከግብጻውያን አመራር ነጻ እንድትወጣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መብት የታገሉት መምህር ገብረ መስቀል፣ ኹለት ጊዜ ለጵጵስና ቢታጩም ፈቃደኛ ባለ መሆን አሳልፈዉታል። የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብጻውያን እጅ መንፈሳዊ መብቷን ከተረከበች በኋላ ከተመረጡት አባቶች መካከል አንዱ ኾነው ቢታጩም “ግብጽ ሄጄ በግብጻውያን አልሾምም” ብለው ነው ሳይሾሙ የቀሩት። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ለኹለተኛ  ጊዜ ከተሾሙ አባቶች መካከል እንዲሾሙ ቢመረጡም አኹንም አልፈቀዱም። ጵጵስናውን የተሾሙት በኋላ ላይ “የትግሬ ጠቅላይ ግዛት” ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ካረፉ በኋላ ነው። ይህን የብፁዕነታቸውን ለሹመት አለመሳሳት የታዘቡት የቀድሞው ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ “አቡነ ዮሐንስ ፍቅረ ሢመትም (የሹመት ፍቅር) አልነበረባቸውም” ሲሉ መስክረዉላቸዋል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 130)።
ሊቀ ሊቃውንት ተብለው በአዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ በኋላም በታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ንቡረ እድ ተብለው ደግሞ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ያገለገሉት መምህር ገብረ መስቀል፣ ሐምሌ 18 ቀን 1948 ዓ.ም. በመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ፓትርያርክ፣ በዚያን ጊዜ ሊቀ ጳጳስ ይባሉ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ አንብሮተ እድ “ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ” ተብለው ኹለተኛው የትግራይ ጳጳስ ኾነው ተሾሙ።
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሹመቱን የተቀበሉት በፍጹም ፍርሀትና በታላቅ ትሕትና ነበር። ምክንያቱም ጳጳስ መሆን ለዕረፍት፣ ለመዝናናት፣ ለመደላደልና ለመቀማጠል ሳይኾን ከባድ ኀላፊነትና ተጠያቂነት ያለበትን አገልግሎት ለመፈጸም እንደ ኾነ ተገንዝበዋልና። በዚህ ጊዜ ለብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ለእርሳቸው የነበራቸውን ፍቅር ለመግለጽ 21 ጊዜ መድፍ አስተኵሰዉላቸዋል።

. ትምህርትና ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በአንድ ወቅት አንዱን ወጣት አገኙና ካነጋገሩት በኋላ፣ “ልጄ ለምን አትማርም?” ሲሉ ይጠይቁታል። ወጣቱም ሲመልስ “አባታችን ምን በልቼ እማራለሁ?” አላቸው። እርሳቸውም ታዲያ “ምን በልተህ ትደነቊራለህ?” ሲሉ መለሱለት። በዚህ አነጋገር ውስጥ ብፁዕነታቸው ለትምህርት ያላቸውን ትልቅ ልብ ማየት ይቻላል። 
በዜማ፣ በአቋቋምና በቅኔ ትምህርቶች የበሰሉትና በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት የተደላደሉት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ለትምህርት ይሰጡ የነበረው ስፍራ ትልቅ ነበር። ለዚህም ትምህርት ቤትን መገንባት ብቻ ሳይኾን የተማረ የሰው ኀይል ማፍራትም ወሳኝ መኾኑን ተገንዝበው ኹለቱንም ጐን ለጐን ያካሂዷቸው ነበር። በአንድ በኩል የከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅን በትጋት እያስገነቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሀገረ ስብከታቸው ከሚገኙ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል፣ ከርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮንና ከአብርሃ ወአጽብሐ ገዳም የተወጣጡና የትምህርት ፍላጎትና ንቃተ ኅሊና ያላቸውን ዐምስት ወጣቶችን መርጠው ወደ ግብጽ እስክንድርያ በመላክ፣ እንዲማሩና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ነበር። በዚህም መሠረት ወጣቶቹ ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በማጠናቀቅ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን በማገልገል ላይ ናቸው (ገጽ 52፡53)። በጠቅላይ ቤተ ክህነት እንጂ በሀገረ ስብከት ደረጃ ወጣቶችን ወደ ውጭ ሀገር ልኮ ማስተማር እስካኹን ያልታየና በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የግል ጥረት የተከናወነ ተግባር ነበር። ይህም ብፁዕነታቸው ለትምህርት ይሰጡ የነበውን ስፍራና ዋጋ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውንም ወደ ተሻለ ነገር ለማምጣት ከትምህርት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው።
ብፁዕነታቸው ትምህርት ቤት ለመክፈትና ትምህርትን ለማስፋፋት ጠንካራ ዐላማና ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው። ስለ ትምህርትና ትምህርት ቤት ሲናገሩ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፤ “ብዙ [ሕንጻ] አብያተ ክርስቲያናት ከመሥራት ይልቅ ጥቂት ትምህርት ቤቶችን መሥራት ይበልጣል” ይሉ ነበር። ለምን? ተብለው ሲጠየቁ መልሳቸው፣ “በትምህርት የበለጸጉ መምህራን የሚገኙባቸው ጥቂት ትምህርት ቤቶች ብዙ ምሁራንን፣ ብዙ ሊቃውንትን ያስገኛሉ፤ ያፈራሉ። እነዚያም ሊቃውንት በበኩላቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን በእምነት በመልካም ምግባር ሊያንጹ ይችላሉ። ምሁራን የማይገኙባቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ግን፣ ብዙ ምርት አያሌ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል አዝመራ በሚገባ አፍርቶ ላጨዳ ደርሶ ሳለ፣ የሚያጭደው የሚሰበስበው ዐጥቶ፣ መሬት ላይ ረግፎ ባክኖ የአዕዋፍ፣ የእንስሳት ቀለብ ኾኖ የሚቀር አዝመራን ይመስላል።” የሚል ነበር (ገጽ 52)።
በብፁዕነታቸው ትጋት የተገነባውና አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመቀሌው ከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዘመናዊው ትምህርት ከመንፈሳዊው ትምህርት ጋር ተዋሕዶ ዕውቀት እንዲገበይበት ታቅዶ የተከፈተ ነው (ገጽ 53)። በኮሌጁ ይሰጣሉ ተብለው የታቀዱ በርካታ የትምህርት ዐይነቶች የነበሩ ሲኾን፣ ቅድሚያ የተሰጣቸው ግን የሚከተሉት ናቸው።
መደበኛው የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው መሠረታውያን ቋንቋዎች ማለትም በመጀመሪያ ብሉይ ኪዳን የተጻፈበት ዕብራይስጥና ዐዲስ ኪዳን የተጻፈበት ግሪክ፣
ነገረ መለኮት /ቲኦሎጂ/፣
የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነትና ልዩነት የሚያስረዳ በየጊዜው የተፈጸመ ታሪክ፣
መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ያጠናን ዘዴ ማስጠናትና ማስጨበጥ፣
በአጠቃላይ ዕቅዳቸው የነበረው ዘመናዊውን ትምህርት ከመንፈሳዊው ትምህርት ጋር አዋሕዶና አስማምቶ መስጠት ነበር። ከእነዚህ በተጨማሪ ብሔራውያቱ የአብነት ትምህርቶችም እንዲሰጡ ነበር። በመጀመሪያው ዙር ይማሩ ዘንድ ከየገዳማቱና አድባራቱ የሚመረጡ 200 ካህናት እንዲኾኑ ታስቦ የነበረ ሲኾን፣ ሲመረቁ ኀምሳዎቹ በአብነት ትምህርት እየተመረቁ የጉባኤ መምህራን እንዲኾኑ፣ ኀምሳዎቹ በአስተዳደር ትምህርት ተመርቀው አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያስተዳድሩ፣ ኀምሳዎቹ ደግሞ ወደ ውጪ ተልከው ጥንታውያን ቋንቋዎችን በብቃት በማጥናት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መጻሕፍትን እንዲተረጒሙና በኮሌጁ እንዲያስተምሩ፣ የቀሩት ኀምሳዎቹም በዘመናዊ የስብከት ዘዴ ተመርቀው ሕዝብን በጥራትና በብቃት እንዲያገለግሉ ለማድረግ እንደ ነበር ሰነዶች ይጠቍማሉ (62፡63)። ይህም ዕቅዳቸው ቤተ ክርስቲያን ያላትን ብሔራዊ ትምህርትና አሠራርን ከዘመናዊው ትምህርትና አሠራር ጋር አዋሕዳ፣ ከዘመኑ ጋር መራመድ እንድትችል ለማድረግ ምን ያኽል ይጥሩ እንደ ነበር የሚያሳይ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ አጠናን ዘዴ እንዲማሩ የተደረጉት ተማሪዎችም በመጨረሻ ሕዝቡን በማገልግል ላይ ማተኰር እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። አንድ ቀን በአክሱም ቅዱስ ያሬድ ትምህርት ቤት የመጽሐፍ ተማሪዎች የግል ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሱ ማመልከቻ ጽፈው ሰጡዋቸው። ማመልከቻቸውን ከተመለከቱት በኋላ “እኛ ሕዝቡን ቁም ነገር ታስተምሩበታላችሁ ብለን መጽሐፍ ተማሩ ብንላችሁ እናንተ ግን ክርስቶስ እንደ ተናገረው፣ ጳውሎስ እንደ መሰከረው እያላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል የማመልከቻ ማዳበሪያ የገንዘብ ሹመት መለመኛ አደረጋችሁ” አሏቸው።
ብፁዕነታቸው በትምህርቱ ውስጥ ሴቶችንም ያሳትፉ ነበር። ስለዚህ ጕዳይ የዐይን ምስክር የነበሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ሲናገሩ “ብፁዕነታቸው ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀኖናው በሚፈቅደው መሠረት የአገልግሎት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚፈቅዱ አበው አንዱ ስለ ነበሩ ከላይ በተጠቀሰው [በከሣቴ ብርሃን ሰላማ] ትምህርት ቤትና ጊዜ [1964 ዓ.ም.] ሴቶች ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር መንፈሳዊውን ትምህርት ሲማሩ እኔ ራሴ ከመምህራኑ አንዱ ስለ ነበርሁ አይቻለሁ” ብለዋል (ገጽ 136)።     
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አንድ ጕዳይ አለ። ጣሊያን ከአገራችን ከወጣ በኋላ የነበረው ጊዜ ዘመናዊ ትምህርት ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ በእንግድነት የሚገባበት ወቅት ስለ ነበር፣ ብፁዕነታቸው ስለ እንግዳው ዘመናዊው ትምህርት የሚከተለውን ሐሳብ አቅርበው ነበር። “ቤተ ክርስቲያናችን የፊደል፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የትምህርት ባለቤት ናት። ፊደል እያስቈጠረች የሕዝቡን ዐይን ስትገልጥ፣ የአእምሮ ጓዳውን ስትከፍት ኑራለች። መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ሳይኾን በሥጋው የሚጠቀምበትን ተግባረ እድ ማለት፦ ጽሕፈትን፣ ሥዕልን፣ ቅርጻ ቅርጽን የመሳሰለውን ጠቃሚ ጥበብ ሁሉ አስተምራለች። የሀገሪቱን ታሪክ ሥጋዊውንም መንፈሳዊውንም መዝግባ አቈይታለች። ስለ ኾነም ባላት የትምህርት ልምድ መሠረት ከትምህርት ሚኒስቴርም ጐን ተሰልፋ ዘመናዊውንም መንፈሳዊውንም ትምህርት ማካሄድ አለባት። እንደ ባዕድ ከዳር ኾኖ መመልከቱ የሚያዋጣት አይደለም። ይልቁንም ቀረብ ብላ ከጊዜው ጋራ እየተራመደች የሚሻለውን የሚጠቅመውን በመሥራት፣ የሚጐዳውን መጥፎውን በመከላከል የበኩልዋን ድርሻ ልታበረክት ትችላለች። በቸልተኝነት አርቆ ባለ ማሰብ ይህን ሳናደርግ ቀርተን ዕድሉ ከእጃችን ቢያመልጥ ግን ቤተ ክርስቲያን ለነገሩ ባዕድ ትኾናለች፤ ወደ ኋላ ትቀራለች። ኋላ ከማንወጣው የጸጸት ዐዘቅት ውስጥ እንወድቃለን።” ብለው ነበር። “ነገር ግን በጊዜው የነበሩ መኳንንት፣ ካህናት ነገሩን ከሃይማኖት ጋራ በማያያዝ ሃይማኖትን ይጐዳል የሚል ደካማ ምክንያት እያቀረቡ ስለ ተቃወሙዋቸው ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። እንዳሉትም ዕድሉ አመለጠና ባለቤትዋ ቤተ ክርስቲያን ባዕድ እንግዳ ኾነች፤ እንግዳው ባለቤት ኾነ ‘በሞኝ ቤት እንግዳ ይናኝበት’ እንደሚባለው በቤትዋ በጓዳዋ እንግዳ ሲናኝበት ሲያዝበት ከዳር ኾኖ መመልከት ግድ ኾኖባት ይታያል።” (ሕያው ስም ገጽ 33፡34)
ትምህርት ቤትን በማስፋፋት ረገድ ከከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተጨማሪ በሀገረ ስብከታቸው በተለያዩ ከተሞች ልዩ ልዩ የሚከተሉትን ትምህርት ቤቶች ከፍተዋል።
በአክሱም የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት
የአክሱም ዐዳሪ ቤት
በዐድዋ የዓዲ አቡን ትምህርት ቤት
በዐድዋ የየሐ ትምህርት ቤት
ዐድዋ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በኹለት አውላዕሎ የውቅሮ ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በኹለት አውላዕሎ የአብርሐ ወአጽብሐ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት
በአጋሜ የጉሎ መኸዳ ትምህርት ቤት
በተንቤን የዐቢይ ዓዲ ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በራያና አዘቦ የማይጨው ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በሽሬ የሽራሮ ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በሽሬ የዓዲ አውዓላ ዘመናዊ ትምህርት ቤት
በመቀሌ ማኅበራዊ ኑሮ፣ የካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጻሕፍትና የምንጣፍ ሥራ
የሚጠቀሱ ናቸው (ሕያው ስም ገጽ 75)።

. የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ካስተላለፉት ትምህርት በጥቂቱ
ለትምህርት ከፍተኛ ትኵረት የሰጡት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በየቦታው ትምህርት ቤት ማሠራት ብቻ ሳይኾን፣ ጠንካራ ትምህርቶችን ያስተምሩም የነበሩ አባት ነበሩ። በየተገኙበት አጋጣሚ ትምህርታቸውና ምክራቸው ትምህርት ነክ ነበር። በዚህ መሠረት ቦታ ሳይመርጡ ባገኙት አጋጣሚ ኹሉ ሕዝቡን ከመምከርና ከማስተማር ወደ ኋላ አይሉም ነበር። ሲያስተምሩም እንዲያው በግብር ይወጣ ሳይኾን ትምህርታቸው የሚያዝ፣ የሚጨበጥ፣ የሚሰማና ግልጽ የነበረ ሲኾን፣ ያመኑበትን ነገር ሲናገሩም ብቻቸውን ቢቀሩ እንኳ ይሉኝታና ዐድር ባይነት አይታይባቸውም ነበር። ለምሳሌ በአንድ ወቅት እንዲህ ኾነ፣  አንድ ታላቅ ባለ ሥልጣን ሐሳባቸውን ለባለሟሎቻቸው አቅርበው ሐሳብ ስጡበት አሉ። ኹሉም የባለ ሥልጣኑን ሐሳብ “መልካም ነው” እያሉ ሲደግፉ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ግን ብቻቸውን ኾነው ሐሳቡን ተቃውሙት፣ አይበጅም አሉት። “በዚህ ጊዜ ባለ ሥልጣኑ በክፉ ዐይን ሲያዩአቸው ተሰብሳቢዎቹም ዐይናቸውን ወደ እሳቸው ሲጥሉ ተመልክተው “ብቻዬን እንድጠላና እንድለይ ያደረገኝ መማሬና ማወቄ ነው፤ በሐሳቤ ማለት እውነቱን በመናገሬ አልጸጸትም” ብለው በዐቋማቸው ጸኑ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 106)።
ብፁዕነታቸው ማንንም ሳያፍሩና ሳይፈሩ ከላይ እስከ ታች ኹሉንም የሚነካ ለኹሉም እንደየሙያውና እንደየጠባዩ ተገቢውን መልእክት ያስተላልፉ ነበር። ቀጥሎ የሰፈረው ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ከጻፉት ማስተወሻ የተገኘና የ “ሕያው ስም” ጸሓፊ ብፁዕነታቸው ሲያስተምሩ ከሰሙትና በጽሑፍ ካሰፈሩት የተወሰደ ነው (ዝኒ ከማሁ ገጽ 81)።
 
  1.  ንጉሠ ነገሥቱን ገሥጸዋል
በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እና በዐፄ ኀይለ ሥላሴ መካከል ጥሩ ወዳጅነት እንደ ነበረና ብፁዕነታቸው ዐፄ ኀይለ ሥላሴን እጅግ ይወዷቸው እንደ ነበር ይታወቃል። ንጉሡ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅን ለመመረቅ በመጡ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ያበረከቱት ጉባኤ ቃና ለዚህ ምስክር ነው፡፡
በጺሐ መቃብር እቅድምከ ኀይለ ሥላሴ እንዘ ንረውጽ ክልኤነ
እንዘ ጴጥሮስ አንተ አመጣነ ዮሐንስ አነ፡፡
ኀይለ ሥላሴ ሆይ ሁለታችን ስንሮጥ ወደ መቃብር በመድረስ ልቅደምህ
አንተ ጴጥሮስን ስትኾን እኔ ዮሐንስን ነኝና
የቅኔው ምስጢር፦ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር የተባለው ዮሐንስ ወደ ጌታ መቃብር እንደ ሮጡና ዮሐንስ ግን ከጴጥሮስ ቀድሞ ወደ መቃብሩ እንደ ገባ (ዮሐ. 20፥3-4) እኔ ዮሐንስ እርስዎ ደግሞ እንደ ጴጥሮስ ቢኾኑ ከእርስዎ በፊት ሞቴን ያስቀድመው እንደ ማለት ነው።
ይኹን እንጂ እስከዚህ ድረስ የኾነው ወዳጅነታቸው እንዳይጠፋ፣ በተለየ መንገድ ለመወደድ ብለው አሊያም እኖር ብለው የሚያልፉት ስሕተት አልነበረም። የዚያኑ ያኽል ደግሞ እሺ ባይና ታዛዥ ነበሩ። ዐምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ስለ እርሳቸው ሲናገሩ፣ “ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እሺ ባይ ታዛዥ፣ እንቢ ባይ እልከኛ ነበሩ” ሲሉ ኹለቱንም የማንነታቸውን ገጽታዎች ባጭርና ግልጽ አነጋገር መስክረዋል። ከዚህ የተነሣ ነው፣ ብፁዕነታቸው እውነትን መናገርና መገሠጽ ባለባቸው ጊዜና ኹኔታ ንጉሡን በድፍረት እስከ መናገር የሚደርሱት።
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዐፄ ኀይለ ሥላሴን ቀብተው ካነገሡአቸው ግብጻዊ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ጋር በማንኛውም ነገር አይግባቡም ነበር። አለመግባባታቸውን የተረዱት ዐፄ ኀይለ ሥላሴም፣ “እኒህ ጳጳስ ቀብተው ያነገሡን አባታችን ናቸው’ኮ ለምን ቅር ያሰኟቸዋል?” አሉዋቸው። አቡነ ዮሐንስም ሲመልሱ እንዲህ አሉ፡- “ግርማዊ ሆይ! እኛ እግዚአብሔር አነገሥዎ እንላለን፤ ግርማዊነትዎ ግብጻዊ ጳጳስ አነገሠኝ ይላሉን? እንግዲያስ ሥዩመ እግዚአብሔር ማለቱን እንተዋ!” ሲሉ ንገሡን በነገር ጐነጧቸው።
በሌላም ጊዜ ከጵጵስና በፊት ሊቀ ሊቃውንት እየተባሉ ይጠሩ በነበረ ጊዜ አዲስ አበባ የካ ቅዱስ ሚካኤል ኅዳር 12 ቀን የሚካኤል በዓል በሚከበርበት ዕለት ንጉሡ ከመኳንንቶቻቸው ጋር ተገኝተው ነበር፡፡ በዓሉን በማስመልከት ሊቀ ሊቃውንት ገብረ መስቀል እንዲያስተምሩ ተብሎ ታዘዘ፡፡ እርሳቸውም የበዓሉን ታሪክ ካስረዱ በኋላ የሙሴንና የኢያሱን አመራር አንሥተው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ መሪዎች ሙሴና ኢያሱ ስለ ሕዝባቸው ሕይወት ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡ፣ ከራሳቸው መኖር ይልቅ የሕዝባቸውን መኖር ያስቀደሙ እውነተኞች መሪዎች ነበሩ። የዛሬ መሪዎቻችን ግን በተቃራኒው ናችሁ። እናንተ በሕይወት እንድትኖሩ ሕዝቡ እንዲሞትላችሁ ትወዳላችሁ። ስለ ራሳችሁ ደስታ ስትሉ ሕዝቡ እንዲያዝን ትፈልጋላችሁ፤ እንዲህ ከኾነ ደግሞ ሕዝቡን እየመራችሁት ሳይኾን በኋላው ኹናችው እየነዳችሁት ነው። ስለዚህ አመራራችሁን ካላስተካከላችሁ የእግዚአብሔር ፍርድ ይጠብቃችኋል” ሲሉ በድፍረት አስተምረዋል። በዚህም ምክንያት ከንጉሡ ጋር ለጊዜው ተኰራርፈው ነበር። በኋላ ግን ግርማዊነታቸው አቡነ ዮሐንስ የመሰላቸውን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ቈራጥ አባት መኾናቸውን በመገንዘብ፣ እባካችሁ አትናገርዋቸው ያሉትን ፈጽሙላቸው ደግሞ እንዳታሰድቡን ይሉ ነበር ይባላል።
እንዲህ ካለው ጠባያቸው የተነሣ ጥላቻን ያተረፉትን ያኽል ተወዳጅነትንም አላጡም፡፡ አቡነ ዮሐንስ ከአዲስ አበባ በአታ ቤተ ክርስቲያን ንቡረ እድ ተብለው ወደ አክሱም እንዲሄዱ ሲደረግ፣ በጊዜው በስሕተታቸው ምክንያት ሲገሥጿቸውና በድፍረት ሲናገሯቸው የነበሩ መሳፍንት በጣም ደስ አላቸው። እቴጌ መነን ግን ዐዝነው ግርማዊ ጃንሆይን፣ “ሊቀ ሊቃውንት ገብረ መስቀልን ከአዲስ አበባ አዛውረው እንዴት የሚገሥጸንን መካሪ አስተማሪ ያሳጡናል? ደፍረው ስሕተታችንን የሚነግሩን አንድ እሳቸው ነበሩ” ማለታቸው ይነገራል (ገጽ 134)።
ስለዚህ አመራራችሁን ካላስተካከላችሁ የእግዚአብሔር ፍርድ ይጠብቃችኋል” ሲሉ በድፍረት አስተምረዋል። በዚህም ምክንያት ከንጉሡ ጋር ለጊዜው ተኰራርፈው ነበር። በኋላ ግን ግርማዊነታቸው አቡነ ዮሐንስ የመሰላቸውን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ቈራጥ አባት መኾናቸውን በመገንዘብ፣ እባካችሁ አትናገርዋቸው ያሉትን ፈጽሙላቸው ደግሞ እንዳታሰድቡን ይሉ ነበር ይባላል።
እንዲህ ካለው ጠባያቸው የተነሣ ጥላቻን ያተረፉትን ያኽል ተወዳጅነትንም አላጡም። አቡነ ዮሐንስ ከአዲስ አበባ በአታ ቤተ ክርስቲያን ንቡረ እድ ተብለው ወደ አክሱም እንዲሄዱ ሲደረግ፣ በጊዜው በስሕተታቸው ምክንያት ሲገሥጿቸውና በድፍረት ሲናገሯቸው የነበሩ መሳፍንት በጣም ደስ አላቸው። እቴጌ መነን ግን ዐዝነው ግርማዊ ጃንሆይን፣ “ሊቀ ሊቃውንት ገብረ መስቀልን ከአዲስ አበባ አዛውረው እንዴት የሚገሥጸንን መካሪ አስተማሪ ያሳጡናል? ደፍረው ስሕተታችንን የሚነግሩን አንድ እሳቸው ነበሩ” ማለታቸው ይነገራል (ገጽ 134)።

2. ጳጳሳትን መክረዋል፤ ገሥጸዋል
ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብጻውያን አመራር ነጻ እንድትወጣ የታገሉትን ያኽል፣ ነጻ ከወጣች በኋላ በጵጵስናው የሚጠበቀውን ያኽል አልሠራንበትም ብለው ይናገሩ እንደ ነበር መልአከ ሰላም ዐምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ እንዲህ ሲሉ መስክረዋል፤ “ጵጵስና ከግብጽ ሲመጣ፣ ሥልጣንና ውበት ስናገኝ በነጻነት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ብዙ እንሠራለን ብለን ነበር። ነገር ግን አልሠራንበትም፤ እንዲያውም ጵጵስናን ከከበረበት ሀገር አምጥተን እንዳናዋርደው እፈራለሁ ይሉ ነበር።” (ሕያው ስም ገጽ 132)።  
ራሳቸውን ጨምሮ ጳጳሳት ወንድሞቻቸውን “ጳጳስ ተብሎ ታቦት መባረክ ዲቁና ቅስና መስጠት ብቻ አይበቃም። ነገር ግን ሊቃውንትን እየመረጥን ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሥራ ስንሠራ ነው የጳጳስነት ኀላፊነትን ተወጣን ማለት የሚቻለው፤ ይህ ሕዝብ ይህን ጥቊር ልብሳችንን ለብሰን ሲያየን፣ ሥራችንን አለመሥራታችንን ስለሚያውቅ አንድ ቀን ለፍርድ ያቀርበናል” ሲሉ ለጳጳሳት የሚኾን መልእክት አስተላልፈዋል (ዝኒ ከማሁ 81፡82)።
መነኮሳትን ደግሞ “እናንት መነኮሳት ለምን ልባችሁ ሳይመነኩስ ራሳችሁ ይመነኩሳል?”  ይሉ ነበር።

3. ለዳኞች መልእክት አስተላልፈዋል
ዳኞችና አስተዳዳሪዎች ፍርድን በማጣመምና የቀጠሮ ቀንን በማራዘም ፍርድ እንዳያጓድሉ፣ ድኻ እንዳይበድሉ፣ ጕቦ እንዳይቀበሉ፣ በትክክል ዐይን እያዩ ሕዝቡን እንዲያስተዳድሩ የሰጡት ምክር ደግሞ እንዲህ የሚል ነው። “እናንተ ዳኞች ሥልጣናችሁን መሣሪያ መከታ ጋሻ፣ ሹመታችሁን መደበቂያ ዋሻ አድርጋችሁ በፍርድ ስም የድኻውን ገንዘብ መብላት እጅግ በጣም የበደል በደል ከመኾኑም በላይ፣ የሕግ ሽፍቶች ወንበዴዎች ከመባል አያድናችሁም።” ዝኒ ከማሁ ገጽ 82)።

4. ስለ ልማዳዊ በዓላት ተናግረዋል
ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ሕግ የማያዛቸው የልማድ በዓላትን በመከተል ሥራ በመሥራት ፈንታ ተቀምጠው እንዳይውሉ፣ ካህናትም ኾኑ ጳጳሳት ደግሞ ትክክለኛውን የክርስቶስን ትምህርት ተግተው እንዲያስተምሩ ይመክሩ ነበር። “ቤተ ክርስቲያን ማረፍ ሳይኾን መሥራት የምታስተምራችሁ ኹል ጊዜ ነው። የልማድ በዓላት ከአብዛኛው የወር ቀናት ጋር እየተጋጠሙ መሥራት አልቻላችሁም። በዚህ ምክንያት የዕርሻ የዘር የመኸር ጊዜ ይተላለፋል። በበዓላት ጊዜ [ሥራ ፈትታችሁ] ተንኰል ስታስቡ፣ ክፉ ተግባር ስትፈጽሙ ከመዋል ይልቅ መሬቱን ብታለሙ፣ ዐፈሩ እንዳይሸረሸር መደብ መደብ እየሠራችሁ ዛፍ እየተከላችሁ ብታግዱ ይሻላል። እነዚህ መጻሕፍት የማያዟቸው የልማድ በዓላት መሻር አለባቸው። ለመሻር መፍራት አይገባም፤ ሥራ ፈትነት የስንፍና ፍልስፍናን የሚያመለክት ነው።” ይሉ ነበር።
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከዕለታት በአንዱ ቅዳሜ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ትምህርት ቤት አካባቢ ድንጋይ ሲያነሡ፣ ሲያርሙ አንድ ትልቅ ሰው መጥተው ተመለከቷቸውና፡- “ምነው አባታችን ዛሬ እኮ ጌታ ያረፈበት ቀን ነው፤ እርስዎስ ለምን አያርፉም? አሉዋቸው። ብፁዕነታቸውም ሲመለሱ፣ “ጌታ እኮ ሥራውን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ነው ያረፈው፤ እኛ ምን ሠርተን እናርፋለን? ለማረፍ እኮ መሥራት ያስፈልጋል” አሏቸው።
ከዐቅም በላይ የሚደገስ ድግስም ለድኽነት የሚያጋልጥ ነው በማለት በተጨባጭ የሚያስከትለውን አደጋ እየተነተኑና እያስገነዘቡ ሕዝቡ ከዐቅሙ በላይ ድግስ ከመደገስ እንዲታቀብ ያስተምሩ ነበር (ዝኒ ከማሁ ገጽ 82፡83)።

5. ተዝካርን በሚመለከት
ስለ ተዝካር ቤተ ክርስቲያን ከሠራችው ሥርዐት ውጪ የሚታየውን ውዳሴ ከንቱና ብክነት አስመልከተው ሲናገሩ፣ “ሰዎች … በራሳቸው ፈቃድ ለማይጨበጥ ውዳሴ ከንቱ ዋጋ ለሌለው ምስጋና ለጊዜያዊ ዝና ሲሉ ቤታቸውን አራቍተው ያለ የሌለ ንብረታቸውን ሸጠው ለውጠው ፍሰስ ተፋሰስ ካልተባለ ‘ይበል ተዝካር አቤት ድገስ’ ተብሎ ካልተደነቀ በሚል ዐጕል አስተሳሰብ፣ ብዙ ቀን ያጠራቀሙትን ሀብት፣ በአንድ ቀን ድግስ ብቻ ሲያጠፉት ይታያል። ይህንም ቤተ ክርስቲያን አትደግፈውም፤ አትፈቅደውም” ይሉ ነበር። ካህናቱም ይህ ይቀር ዘንድ በትጋት እንዲያስተምሩ፣ በምእመናን ፊት “እኒህ ካህናት ሰከሩ ወደቁ” ተብለው ትዝብት ላይ እንዳይወድቁም ራሳቸውን ይጠብቁ ዘንድ ያሳስቧቸው ነበር።  ምእመናንንም “ዓመት ሙሉ ጥራችሁ ግራችሁ ያፈራችሁትን እኽል በከንቱ ለዝና ብላችሁ አታጥፉ፤ ቍጠባን ተማሩ። እግዚአብሔር በዝናብ ያበቀለውን እኽል መልሳችሁ በውሃ ታጠፉታላችሁ (በጠላ ማለታቸው ነው)። የጥር ጥጋበኞች የሐምሌ የነሐሴ ረኃብተኞች አትኹኑ” ይሉ ነበር (ዝኒ ከማሁ ገጽ 85)።

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት
በደርግ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ኹለተኛው የኢአተቤክ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስር ቤት እያሉ፣ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾሙ። ኾኖም ሹመቱን በቀላሉ አልተቀበሉትም ነበር። እርሳቸው ለዚህ ሥልጣን ሲታጩ ደርግም ስላመነበት፣ እሳቸውን ይዘው እንዲመጡ የጐንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የካቲት 11 ቀን 1968 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ተላኩ። የመጡበትንም ተናግረው እንሂድ ሲሏቸው፣ “ከአቡነ ቴዎፍሎስ በላይ አስተዋይ፣ ታጋሽ ሰው ማን አለ? እሳቸው አጠፉ ከተባሉ፣ እኔ እንዴት ላላማ እችላለሁ? እኔ ከእሳቸው በምን እሻላለሁ?” ብለው ለመሄድ አቅማምተው የነበረ ቢኾንም፣ አግባብተዋቸው ወደ ዐዲስ አበባ ከመጡ በኋላ፣ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት ከስምንት ወራት በላይ አገልግለዋል።
በእነዚህ ስምንት ወራት ውስጥ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል የደርግ ባለሥልጣናትን አናግረውና አሳምነው፣ ደርግ ካሰራቸው እስረኞች መካከል ብዙ ሴቶችና ጥቂት ወንዶች እንዲፈቱ ማድረጋቸው ይጠቀሳል። በዚህም በጣሊያን ጊዜ የፈጸሙትን ተግባር በደርግ ዘመንም ደግመዉታል ማለት ይቻላል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 76-78)። በዚህ ጊዜ፣ “ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ወደ ደርግ ቤተ መንግሥት ገብተው ኮሚኒስቶችን አሳለሟቸው (ባረኳቸው)” ተብሎ በውጭ ሀገር ጋዜጦች ላይ እንደ ተዘገበ ይነገራል።
በዚሁ ዘመን በሀገሪቱ ሕግ መሠረት የቤተ ክህነት ሠራተኛ በሙሉ የጡረታ ዕድሜው ሲደርስ ጡረታ መውጣት አለበት ተብሎ ተወስኖ ነበር። ውሳኔው የቤተ ክርስቲያን የአብነት መምህራንንም የሚነካ ኾኖ ተገኘ። ይኹን እንጂ በዚህ ውሳኔ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ አልተስማሙም። ምክንያታቸው ደግሞ መምህራኑን ተክቶ የሚያስተምር ደቀ መዝሙር ሳይያዝ፣ እነርሱ ቁጭ ብለው ዐርፈው በሚስተምሩበት ጊዜያቸው ጡረታ ይውጡ ማለት ቤተ ክርስቲያን ትዘጋ፤ ሃይማኖት ይጥፋ ብሎ ዐዋጅ እንደ መንገር ነው የሚል ነበር። በመኾኑም ይህን ውሳኔ ያስተላለፉትን የቤተ ክህነት ኀላፊዎችን በመቈጣት ውሳኔው እንዲለወጥ አደረጉ። ይኸውም “የቤተ ክርስቲያን መምህራን ከተቻለ ማስተማር እስኪሳናቸው እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ካልተቻለ ደግሞ እስከ 75 የዕድሜ ገደብ ድረስ ጡረታው እንዲራዘምላቸው በማለት ቈራጥ መመሪያ ወይም ውሳኔ ሰጡ” (ገጽ 80)። ውሳኔውም በመላው ሀገሪቱ እንዲሠራጭ ተደረገ። መመሪያው አኹን ባለው ቅዱስ ሲኖዶስም ተቀባይነት ስላገኘ ቋሚ ሕግ ኾኖ እየተሠራበት ይገኛል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሦስተኛው ፓትርያርክ ኾነው ከተመረጡና በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እና በሌሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከተሾሙ በኋላ፣ ብፁዕነታቸው ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነታቸውን ፈጽመው ጥቅምት 16 ቀን 1969 ዓ.ም. ወደ ሀገረ ስብከታቸው ተመልሰው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ኾኖም የመምህራንን ጡረታ ለማራዘም በብዙ የደከሙት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በ1970 ዓ.ም. ጡረታ እንዲወጡ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ዕድሜቸው 83 ዓመት ኾኖ ነበር። በዚህ ዕድሜያቸው ግን ሽምግልና ሳያሸንፋቸው ድካም ሳያጠቃቸው ሥራቸውን በትጋት ያለ ዕረፍት በመሥራት ላይ ነበሩ። ኾኖም ጡረታ መውጣታቸው ሥራውን እንዲያቆሙ አደረጋቸው። “ያቀዱት ኹሉ ከእሳቸው ጋር እንቅስቃሴውን አቆመ። በተለይም መንፈሳዊ ትምህርት ተዳከመ። በአክሱም በመቀሌ ያቋቋሙዋቸው የመንፈሳዊ ትምህርት ዐዳሪ ቤቶች ተዘጉ፤ አስታዋሽ ዐጡ።” ምን ጊዜም ቢኾን መሪዎች ተተኪ ማፍራት አለባቸው። ካላፈሩ ግን የሠሯቸው ሥራዎች ቀጣይ አይኾኑም፤ ይቆማሉ። በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የተጀመረው ሥራ መቆሙም በአንድ በኩል ከዚህ የሚመነጭ ይመስለናል።

ብፁዕ አቡነ ዮሐንሰ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የነበራቸው አመለካከት
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ አብያተ ክርስቲያናት በተገቢው መንገድ እንዲቀራረቡ አንድነትም እንዲኖራቸው ዓለማቀፍ አመለካከት ነበራቸው። የመቀሌው ከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲከፈት በኮሌጁ ውስጥ እንዲሰጡ ታቅደው ከነበሩት የትምህርት ዐይነቶች መካከል አንዱ፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነትና ልዩነት የሚያስረዳ በየጊዜው የተፈጸመ ታሪክ” የሚል ነበር። ይህ የኮርስ ርእስ በአብያተ ክርስቲያን መካከል ልዩነት ብቻ ሳይኾን ግንኙነት መኖሩን ለማሳየት የተቀረጸ ይመስላል። ዛሬ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ምንም ግንኙነት እንደሌለ አስመስለው ልዩነትን ብቻ ለሚያራግቡ ክፍሎችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሲኾን፣ በዚህ ሚዛን እንኳ ሲመዘኑ እነዚህ ክፍሎች ከአበው መንገድ ምን ያኽል ርቀው እንደ ነጐዱም የሚያሳይ ነው።
የሊቃውንት ጉባኤ አባልና ሰብሳቢ የነበሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ በብፁዕነታቸው የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ ምስክርነት ሲሰጡ፡- በ1964 ዓ.ም. በቅዱስ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ት/ቤት ለካህናትና ለወጣቶች ሰሚናር አዘጋጅተው በነበረበት ጊዜ መምህራኑ ኢትዮጵያውንና እንግሊዛውያን ነበሩ። በተለይም ከእንግሊዛውያኑ መምህራን አንዱ ዶ/ር ሮጀር ካውሊ በትምህርት ቤቱ ሥራ ለብዙ ጊዜ ረድተዋቸዋል (ገጽ 136)።
በ1981 ዓ.ም. ደርግ መቀሌን ለቅቆ ሲሄድ አቡነ ዮሐንስ ያለ ደሞዝ በመቀሌ ቈይተዋል። ይህን ያወቁ በመቀሌ ከተማ የሚኖሩ የሌላ እምነት ተከታዮች “እኛ ልንረዳቸው እንፈልጋለን ብለው ለቤተ ሰቦቻቸው ነገሩ። አቡነ ዮሐንስም፡- ልጆቼ ይህ ርዳታ ለእኛ መልካም አይደለም፤ ሆዳችንን ለመሙላት የሞላ ታሪካችንን አናጐድለም፤ የትግራይ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተቸግረው ርዳታ አደረግንላቸው ማለት ለእነሱ ከፍተኛ ክብር ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን ግን ሀፍረት ነው” በማለት ርዳታውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል።
ዜና ቤተ ክርስቲያን የተባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ጋዜጣ በ1991 ዓ.ም. የወጣውን የጳጳሳት ሀብትና የውርስ ጕዳይ የተመለከተውን ሕግ በመተቸቱ ምክንያት ለደረሰበት አንዳንድ ተቃውሞ ምላሽ በሰጠበት ርእሰ አንቀጽ ላይ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስን በመልካም ምሳሌነት ጠቅሷቸዋል። ብፁዕነታቸው “እንደ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ያለውን መንፈሳዊ ኮሌጅ መሥርተውና ለትውለደ ትውልድ የሚተላለፍ ዘርፈ ብዙ የኾነ ሐዋርያዊ ተግባር አከናውነው ዐልፈዋል። በሰላመ እግዚአብሔር ባረፉበትም ጊዜ ከራስጌአቸው የተገኘው ገንዘብ ለውርስ የሚበቃ ወይም ለወራሽ የሚተርፍ ሳይኾን፣ ዐሥር ሺሕ ብር ብቻ ነበር የተገኘው። ያም ቢኾን ራሱ ‘ይህ ገንዘብ የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው’ የሚል ተጽፎበት ነበር የተገኘው።” (ዜና ቤተ ክርስቲያን ሠኔ 2004፣ ገጽ 3)።
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራቸውን በትጋትና በታማኝነት ሲያገለግሉ ቈይተው በ96 ዓመታቸው በዚያው በተወለዱበት ቀን ነሐሴ 13/1983 ዓ.ም. አርፈዋል። የተቀበሩትም ራሳቸው ባሳነጹትና መቀሌ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ነው።

No comments:

Post a Comment