ትረካ፡- ከነቅዐ ጥበብ
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪካቸው የተመዘገበው ኒቆዲሞስና ዮሴፍ ዘአርማትያስ (ዮሐ. 3፥2፤
19፥38) ያደርጉት እንደ ነበረው፥ መሪጌታ ብርሃነ መስቀልም ጨለምለም ሲል ራሳቸውን ለወጥ አድርገው ወደ አለቃ ነቅዐ ጥበብ
እየሄዱ ከሚማሩ ስውር ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ነው፡፡ በሚያገለግልበት ደብር ውስጥ እርሱ ከሚኖርበት የመቃብር ቤት ጥቂት
ዕልፍ ብሎ በሚገኘው በሌላው መቃበር ቤት ውስጥ ለሚኖረው ባልንጀራው ለመሪጌታ በትረ ጽዮን ግን ወዴት እንደሚሄድ አይነግረውም
ነበር፡፡ ምክንያቱም ካሁን ቀደም በወንጌል ስለ ተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ሊያስረዳው ቢሞክር፥ ፍጹም ተቃዋሚና እርሱንም
አሳልፎ ሊሰጠው የሚችል ዐይነት ሰው ሆኖ ስለ ተመለከው፥ በሌላው ጕዳይ ካልሆነ በቀር ለጊዜው በዚህ ነገር ዳግም ላያነጋግረው
ወስኖ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ እንደ ነገ የሚቆሙትን የማሕሌት ቀለም እንደ ዛሬ ዐብረው ሲመለከቱ፥ የወንጌልን
እውነት ለመግለጥ በር የሚከፍት ቃል ካጋጠመው፥ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ስሕተት ካገኘ አያልፍም፤ በዚያ
መነሻነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ክርክር ያደርጉ ነበር፡፡ ባለማቋረጥ የሚንጠባጠብ የውሃ ጠብታ ከታች ያለውን
ዐለት እንደሚቦረቡረው፥ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል በመሪጌታ በትረ ጽዮን ጆሮ የሚያንቈረቊረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ከጊዜ ወደ
ጊዜ ልቡን እየሸረሸረው መምጣቱ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ የያዘውን ነገር በቀላሉ ለመልቀቅ ስለሚቸገርና ሽንፈትም ስለሚመስለው በቶሎ
እጅ አይሰጥም፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ ጊዜያት አልፈዋል፡፡
አሁን፥ አሁን በእርሱ ፊት የተሸነፈ አይምሰል እንጂ፥ ተቃዋሚ መሆኑን ተወት እያደረገው መጥቷል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ሥራዬ ብሎ ስለማያነብና እርሱ በሚገኝበት ደብር በሠርክ መርሐ ግብር ላይ የሚሰጡ ትምህርቶች ብዙ ጊዜ በተቃውሞ
የተሞሉና ፀረ ወንጌል ዐቋም የሚንጸባረቅባቸው ስለሚሆኑ፥ ልቡ፥ በዝናም ዕጥረት የተዘራውን ዘር ለፍሬ ማብቃት እንደ ተሣነው
መሬት፥ ተገልብጦ ሌላ ዘር የሚቀበል ይሆንና እንደ ገና ያስቸግራል፡፡ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ግን ተስፋ ባለ መቊረጥ አንድ
ቀን እንደሚበቅል በማመን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቃሉን ይዘራል፡፡
መስከረም 16 ቀን ነው፡፡ ሁለቱ መሪጌቶች የደመራን በዓል አክብረው ወደ መኖሪያቸው
እየተመለሱ ነበር፡፡ መሪጌታ በትረ ጽዮን በበዓሉ ስፍራ ስለ ተገኘው የሕዝብ ብዛት፣ በመዘምራን ስለ ቀረቡ ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣
ከተለያየ ሰንበት ትምህርት ቤት የመጡ ወጣቶች ስላቀረቧቸው መዝሙሮችና አስደናቂ ትርኢቶች፣ ወዘተ. እያነሣና እየጣለ በዓሉ
የፈጠረለትን ደስታ (ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም) በሰፊው ይተርክለት ጀመር፡፡ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል የባልንጀራው ልብ ስለ ዕፀ
መስቀሉ ሲዘራበት የዋለውን ዘር መቀበሉን ስላስተዋለ፥ እርሱም የልቡን መሬት በቶሎ ገልብጦ የክርስቶስን መከራ መስቀል ይዘራበት
ዘንድ የክርስቶስ ፍቅር ግድ አለው፡፡
"ሰማህ ጓዴ" አለ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ሲያደምጠው ቈይቶ፡፡
"የዛሬው በዓል በርግጥ የደመቀ ነው፡፡ በትውፊት ሲተረክ እንደ ቈየውና በየዓመቱ እንደሚከበረው፥ ይህ ቀን ክርስቶስ
የተሰቀለበትና አይሁድ ቀብረዉታል የተባለው ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት የወጣበት ቀን ነው፡፡ በዓሉ በሃይማኖታዊ ቅጽር መወሰኑ
ቀርቶ ወደ አገራችን ብሔረ ሰቦች ባህል ውስጥም ሠርጿል፡፡ ሃይማኖታዊ ገጽታውን ስንመለከት፥ ዕፀ መስቀሉን ከተቀበረበት እሌኒ
አስቈፍራ አስወጣችው ተባለ፡፡ በኋላ ላይ ከዐምስት ቦታ ተካፍለዉት፣ ወደ አገራችን መጣ የተባለውን የዚያን መስቀል አንድ ግማድ
(ጕማጅ) ምን አደረግነው? ያው በድጋሚ ቀበርነውም አይደል? ከዚያ ይልቅ ግማደ መስቀሉን በቅርስነቱ ሰው ሁሉ እንዲያየው ቢደረግ
መልካም ነበር፡፡ በቱሪስት መስሕብነትም ለአገራችን የገቢ ምንጭ በሆነ ነበር፡፡ የሆነው ሁሉ ሆኖ ለእኔ ግን ይህ ቀን ዕፀ
መስቀሉ የተገኘበትና መከበር የጀመረበት ቀን ነው ቢባልም፥ መዳኛችን የሆነው መስቀል፥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን
የተቀበለው መከራና ሥቃይ (መከራ መስቀሉ) ከሰው ልብ መጥፋት የጀመረበትና በዕፀ መስቀሉ የተተካበት ቀን ነው ማለት
እችላለሁ፡፡"
"እንዴት? … ደግሞ መስቀሉ በተገኘበት ቀን የጠፋ ሌላ መስቀል አለ ብለህ ዐዲስ
ታሪክ ትፈጥራለህ እንዴ?" ሲል በመገረም መሪጌታ በትረ ጽዮን አቋረጠው፡፡
ጥያቄውን ሲገታ፥ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ቀጠለ፤ "እንደ ተባለው ዕፀ መስቀሉ
ከ300 ዓመታት በላይ ተቀብሮ ከቈየ በኋላ ተገኘ ተብሎ እስካሁን በዚህ ቀን ታሪኩ ይዘከራል፡፡ የክርስቶስ መከራ መስቀል ግን ከዚያ
ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ማለት ይቻላል፥ በተለይም ለዕፀ መስቀሉ የተለየ ክብር እንሰጣለን ለሚሉ ወገኖች ተሰውሮ ነው
ያለው፡፡ ዕፀ መስቀሉን ንግሥት እሌኒ አስቈፍራ አስወጣችው፡፡ ይህን በሚያምኑ መካከል መከራ መስቀሉን ከተሰወረበት የሚያወጣው ግን
አልተገኘም፡፡ ቈፍሮ ለማውጣት ጥረት የሚያደርግ ቢኖር እንኳ አይበረታታም፡፡ የዕፀ መስቀሉ ጠላት ተደርጎ ይፈረጃል እንጂ፡፡
እንዲህ ስል ዐዲስ ታሪክ የፈጠርሁ እንዳይመስልህ፡፡ የምነግርህ ያለውን ግን ያላስተዋልነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው፡፡"
"ለመሆኑ አንተ እየነገርኸኝ ስላለኸው መስቀል መጥፋት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል
ብለሃል፤ ነገር ግን ማስረጃ አለህ? ይህን መስቀል የደበቁትስ እነማን ናቸው?" በማለት ጥያቄዎቹን አቀረበ፡፡
መሪጌታ ብርሃነ መስቀል፥ "በቅድሚያ" አለ፤ "በቅድሚያ እኔ
እየተናገርሁ ያለሁት ቊሳዊ ስለ ሆነ መስቀል አይደለም፡፡ በዐይን ስለማይታየውና በልብ ስለሚታሰበው የክርስቶስ መከራ መስቀል
ነው" አለና ከትእምርተ ኅቡአት በግእዝ፥ "አኮ ከመ ይትረኣይ አላ ከመ ይትኀለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወቦቱ
ንትመካሕ ከመ ንሰብሖ" የሚለውን በዜማ ዘለቀው፡፡ መሪጌታ በትረ ጽዮን ባልንጀራው ያዜመውን የትእምርተ ኅቡአት ቃል፥
ሲደግመውና ሲያዜመው የኖረ ቢሆንም ምስጢሩ እንዲህ ይሆናል ብሎ ዐስቦ አያውቅም፡፡ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል እየነገረው ያለው
ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መንፈሳውያን መጻሕፍትም የሚገኝ መሆኑ ገርሞታል፡፡ ዜማውን እንደ ጨረሰ፥
"ይህ ምን ማለት ነው? … የምንመካበት መስቀል በልብ የሚታሰብ እንጂ በዐይን የሚታይ እንዳልሆነ ያስረዳል አይደል? …
የዚህ መስቀል ስፍራ የምእመናን ልብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መስቀል ጠፍቷል ወይም ተሰውሯል ስልህ፥ ልባቸውን ለዕፀ መስቀሉ
መኖሪያ ያደረጉ ሰዎች ለመከራ መስቀሉ በልባቸው ውስጥ ስፍራ አልሰጡም ለማለት ነው፡፡
"ይህን መስቀል በመደበቅ ግንባር ቀደሞቹ አፅራረ መስቀል የሆኑት አይሁድ ናቸው፡፡
አይሁድ የክርስቶስን መከራና ሞት ከንቱ ሊያደርጉ የሚችሉ አይሁዳዊ ሥርዐቶችን በመስበክና ወደ ክርስትና የገቡ ወገኖችን ወደ
ኦሪት ሥርዐት በመጐተት የተሰቀለውን ክርስቶስን እንዳይመለከቱ አዚማም ስብከታቸውን ይሰብኩ ነበር፡፡ የገላትያ አብያተ
ክርስቲያናትም የዚህ ችግር ሰለባ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ፥ "የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዐይናችሁ
ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማነው?" (ገላ.
3፥1)፡፡ ልብ በል፥ በዚህ ስፍራ ስለ ተሰቀለው ኢየሱስ እንጂ እርሱ ስለ ተሰቀለበት መስቀል አልተወሳም፡፡ ዛሬም የክርስቶስን
መከራ መስቀል ተክቶ የሚሰበክ ማንኛውም ነገር (ዕፀ መስቀሉም ጭምር) መከራ መስቀሉ ከሰዎች ልብ እንዲጠፋ የሚያደርግ አደገኛ
አዚም ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከእውነት መንገድ የወጡትን ለመመለስና ለክርስቶስ መከራ መስቀል በልባቸው ውስጥ ስፍራ ለማግኘት
የምጥ ያህል ያስጨንቃል፡፡ "ልጆቼ ሆይ! ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል"
የሚለው የጳውሎስ ጭንቀትም ይህን ያስረዳል (ገላ. 4፥19)፡፡
"እንዴ መሪጌታ ምን ማለትህ ነው? ዕፀ መስቀሉና መከራ መስቀሉ እኮ የአንድ
ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው! ዕፀ መስቀሉን ስንመለከትም የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው የምናስበው፤ ታዲያ ችግሩ ያለው ከምኑ
ላይ ነው?" አለ መሪጌታ በትረ ጽዮን ነገሩ ተምታቶበት፡፡
"ክርስቲያኖች ሁሉ የመስቀልን ምልክት ዐርማቸው ማድረጋቸው የሚነግረን አንድን
እውነት ነው፤ የክርስትና ማእከል የኢየሱስ መሰቀል፣ መሞትና መነሣት መሆኑን፡፡ ክርስትና ከዚህ ውጪ ሌላ መሠረት የለውም፡፡
በዚህ መሠረት ክርስቲያኖች የመስቀልን ምልክት ዐርማቸው ያደረጉት፥ እርሱን በዐይናቸው ሲመለከቱት የክርስቶስን መከራ በልባቸው
ለማሰብ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ዐላማ አልነበራቸውም፡፡ በእኛ ዘንድ ያለው ሁኔታ እንዲህ ቢሆን እኔ ምን ቸግሮኝ! ነገር ግን
እየሆነ ያለው ሌላ መሆኑ አሳዘነኝ እንጂ፡፡ በርግጥ ካስተዋልኸው ጉዳያችን ከተሰቀለው ኢየሱስ እንጂ እርሱ ከተሰቀለበት መስቀል
አይደለም እኮ!! እስኪ ነገሩን በምሳሌ እንየው፤ የተዘለዘለ ሥጋ የሚሰቀለው በገመድ ላይ ነው፡፡ መቼም እኛ ጕዳያችን ከሥጋው
እንጂ ከገመዱ አይደለም፤ ገመዱ ሥጋውን ከመሸከም ያለፈ ተግባርም ሆነ ለሰውነታችን የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ በገመዱ
ከመገልገል በቀር ስለ ሥጋው ለማሰብ ወደ ገመዱ የምንመለከትበት አንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ ዕፀ መስቀሉም ከዚህ በተለየ
መንገድ ሊታይ የሚችልበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤" ሲል መሪጌታ ብርሃነ መስቀል፥ እርሱ
ላቀረበው ጥያቄ እየሰጠው ያለውን መልስ ማዳመጥ ትቶ ሌላ ጥያቄ እያሰናዳ ከነበረበት የሐሳብ ዓለም እንደ መባነን ብሎ፥
"እ … እሺ" አለ፡፡
መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ቀጠለ፤ "ዛሬ በደመራ በዓል ላይ የሆነውን ሁሉ አይተሃል፤
ሰምተሃል፡፡ የተዘመረው፣ የተሰበከው፣ የተጸለየው፣ በትርኢት መልክ የቀረበው፣ ወዘተ. ሁሉ የተሰቀለውን ክርስቶስን ሊያሳይህ
ቸሏል? ወይስ እርሱ የተሰቀለበትን መስቀል ብቻ ነው ያመለከተህ?"
መሪጌታ በትረ ጽዮን፥ "እ … እ … " እያለ ምን መመለስ እንዳለበት እያሰበና
ቃላቱን እያማረጠ ሳለ ከእርሱ ምላሽ ሳይጠብቅ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል፥ "እኔ በበኩሌ በዚህ ሁሉ ውስጥ የተሰቀለውን
ክርስቶስን ማየት አልቻልሁም ብልህ ምንም አላጋነንሁም፡፡ ዕፀ መስቀሉ የተሰቀለውን ክርስቶስን በማሳየት ፈንታ ሸፍኖብኝ ራሱን
ነው ያሳየኝ ማለት እችላለሁ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አማካይነት በልባችን ውስጥ መከራ መስቀሉን ሲስልልን፥
ሰዓልያንም በቀለም በወረቀት ላይ ክርስቶስን እንደ ተሰቀለ አድርገው ሲስሉት ክርስቶስን ከፊት፥ የተሰቀለበትን መስቀል ደግሞ
ከጀርባ በኩል አድርገው ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ትኲረት የሚሰጠው የተሰቀለው ክርስቶስ እንጂ የተሰቀለበት መስቀል አይደለም
ማለት ነው፡፡ ዛሬ የሆነውን ስታይ ግን በተነገረውና በተደረገው ሁሉ በምእመናን ልብ ውስጥ የተሳለው ማነው? ክርስቶስ
የተሰቀለበት መስቀል እንጂ የተሰቀለው ክርስቶስ ነውን? ታዲያ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና እርሱ የተሰቀለበት መስቀል እንዴት
የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሊሆኑ ይችላሉ? በእውነቱ ሁለቱም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡
"እሺ ያልኸው ሁሉ ልክ ነው ልበል፤ ስለ መስቀል የተጻፉትን ጥቅሶች ግን ምን
ልታደርጋቸው ነው?" አለ መሪጌታ በትረ ጽዮን፡፡ "የትኞቹን ጥቅሶች?" ሲል መሪጌታ ብርሃነ መስቀል
መልሶ ጠየቀው፡፡ እርሱም በደመራው ስፍራ ከተበተኑት ትራክቶች በእጁ የገባውን ትራክት ከኪሱ አውጥቶ በዐይኑ ጥቅስ ፈለገና
ሲያገኝ "ለምሳሌ፦ 1ቆሮ. 1፥18፤ … ይኸው ደግሞ ገላ. 4፥16፤ ፊል. 3፥18"
መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ለጥያቄው መልስ ወደ መስጠት ተሸጋገረ፡፡ "ወደ ጥቅሶቹ ሐሳብ
ከመሄዴ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ክርስቶስን በሰቀሉት አይሁድ ዘንድ በጊዜው ትልቅ ጕዳይ የነበረው
ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ነው ወይስ ሰቅለው የገደሉት ኢየሱስ የመነሣቱ ነገር? የሚለውን መመልከት አለብን፡፡ ኢየሱስን
ሰቅለው ከገደሉት በኋላ ወደ ጲላጦስ መጥተው ያመለከቱት ምን ነበር?" ብሎ ጥቂት ቆም አለ፡፡ "መቼም ያሉትን
ታስታውሳለህ" አለና ቀጠለ፡፡ "'ያ አሳች (ሎቱ ስብሐት) በሕይወቱ ገና ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ
እንዳለ ትዝ አለን' ብለው ደቀ መዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና ከሙታን ተነሣ ብለው እንዳያወሩ መቃብሩ ይጠበቅ ዘንድ ለመኑ
(ማቴ. 27፥63-64)፡፡ በተፈቀደላቸው ጊዜም መቃብሩን አትመው በወታደሮች አስጠበቁ፡፡ የእኛ ጌታ ግን መግነዝ ፍቱልኝ
መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ አይሁድ የፈሩት ደረሰ፡፡ ከጠባቆቹ አንዳንዶች ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን
ሁሉ በማውራታቸው አይሁድ ተደናግጠው ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ በመስጠት፥ ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ወሰዱት ብለው አስወሩ፡፡ እስካሁንም
በአይሁድ ዘንድ ይኸው እንደሚወራ ይታወቃል፡፡
"አይሁድ ኢየሱስን ሰቅለው በመግደል የእርሱን ጕዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጉ
ቢመስላቸውም፥ እርሱ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱና በስሙ ታላላቅ ተኣምራት መደረጋቸው፥ ሌላ ራስ ምታት ሆነባቸው፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ
ላይ የጀመሩትን ተቃውሞ በተከታዮቹ ላይ ቀጠሉ፡፡ ትልቁ ተቃውሟቸውም 'በኢየሱስ ስም ለምን ታስተምራላችሁ?' የሚል ነበር
(ሐ.ሥ. 4፥2፤ 5፥28፡40)፡፡
"በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደምናነበው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ድውይ
ስለ መፈወሱ፣ ሙት ስለ ማስነሣቱና ስለ መሳሰለው የተጻፈ ነገር የለም፡፡ ይህ ትረካ ያለው በትውፊት ነው፡፡ በርግጥ ዕፀ
መስቀሉ እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ የጊዜው ዋና ጕዳይ ይሆን ነበረና ሐዋርያትም በመዘገቡልን ነበር፡፡ ነገር ግን የጊዜው ዋና ጕዳይ
ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱና በስሙ የሚደረጉት ድንቅና ተኣምራት ነበሩ፡፡ አይሁድ የተሯሯጡትም ይህን እውነት ለመቅበር ነበር፡፡
በአጠቃላይ እነርሱን አስቸግሯቸው የነበረው የስሙ ኀይል እንጂ የተሰቀለበት የዕንጨት መስቀል አልነበረም፡፡ ክርስቶስን
የሰቀሉበት መስቀልማ ራሳቸው ያዘጋጁት የቅጣት መሣሪያ አልነበረምን?
"እንዴ ቢሆንስ በኢየሱስ ደም ተቀድሷል እኮ!" አለና አቋረጠው፡፡
"አይ ባልንጀሬ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደሙን ያፈሰሰው ዕፀ መስቀሉን
ሊቀድስ ነው ብለህ ታስባለህን? በእውነት እንዲህ ካሰብህ፥ የጌታን ደም ዝቅ አድርጎ መመልከትና ዋጋ ቢስ ማድረግ ይሆንብሃል፡፡
በርግጥ የጌታ ደም በዕፀ መስቀሉ ላይ ፈሷል፡፡ እርሱን ብቻም ሳይሆን፦ የተገረፈበትን ጅራፍ፣ የተወጋበትን ጦር፣ በራሱ ላይ የተደፋውን
አክሊለ ሦክ፣ የተቸነከረባቸውን ችንካሮች፣ የነጠበበትን ምድርም ነክቶታል፡፡ ነገር ግን የጌታ ደም በግዘፍ የነካቸውን ቈሳቊሶች
ሳይሆን በእምነት የተቀበሉትን ኀጢአተኞች ለመዋጀት፣ ለማንጻትና ለመቀደስ ነው የፈሰሰው (1ጴጥ. 1፥2፡18፤ 1ዮሐ. 1፥7)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረው ይህን ነው፡፡ ዕፀ መስቀሉን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን ቈሳቊሶች ለመቀደስ ደሙን አፈሰሰ የሚል
እንኳ ጥቅስ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ካገኘህ እኔ ተሳስቻለሁ ማለት ነው፡፡" አለው፡፡
"እርሱማ ልክ ነህ፤ እንዲህ የሚል ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አናገኝም፡፡ ድጓው ግን
ይህን ይሠራዋል፡፡" ሲል መሪጌታ በትረ ጽዮን፥ "ምን ብሎ?" አለ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ከአፉ
ነጥቆ፡፡ "ያው የምታውቀው ነው፤ ሀለዉ እለ ይቤሉ ለዕፅኑ ታመልኩ ወለዕፅኑ በዓለ ትገብሩ ኢቀደሶኑ ደሙ በደሙ ክቡር
ለዕፀ መስቀሉ ወበእንተዝ ንሕነ ና..መ..ል..ኮ.. (ዕፀ መስቀልን ታመልካላችሁ በዓልም ታደርጉለታላችሁ የሚሉ አሉ፡፡ ዕፀ
መስቀልን ደሙ አልቀደሰውምን? ስለዚህ ነውኮ የምናመልከው)" ሲል ቀዝቀዝ ባለና "መጀመሪያውኑ ለምን ይህን
ጠቀስሁ?" በሚል ስሜት መለሰ፡፡ በተለይም የመጨረሻውን ቃል ከአፉ ሲያወጣው ለራሱ ስቅጥጥ እያለው ነበር፡፡
"አይ አንተ!" አለ መሪጌታ ብርሃነ መስቀል ጓደኛው የጠቀሰውን በማጣጣል
ዐይነት፡፡ "ለመሆኑ የሃይማኖታችን መመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ድጓ? ደግሞስ 'ኢቀደሶኑ ደሙ' (ደሙ አልቀደሰውምን?)
በሚለው ላይ አተኰርህ እንጂ ቀደም ብሎ ዕፀ መስቀልን እንደሚያመልከው ተናግሯል እኮ! የሚያመልክበትን ምክንያት አስረዳለሁ ብሎ
ነው 'ኢቀደሶኑ' (አልቀደሰውምን?) ያለው፡፡ መቼም ይህ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ምናልባት
አምልኮተ ዕፀ መስቀል እንደ ተስፋፋ በሚነገርበት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በንጹሑ ዘር ላይ የተጨመረ እንክርዳድ ይሆናል፡፡ በነገራችን
ላይ ይህን ስትጠቅስ ሌላው ድርሰት ትዝ አለኝ፡፡" ሲል "ምን የሚለው?" አለ መሪጌታ በትረ ጽዮን፡፡
"መስተብቊዕ ዘመስቀል፥ … ያው እንደምታውቀው በዚህ ድርሰት ዕፀ መስቀል በአምላክ ስፍራ ተቀምጦ እንደ አምላክ
ይለመናል፤ ይመሰገናል፤ ይመለካል፡፡ ቅድም ቄሱና ዲያቆኑ እየተቀባበሉ በዜማ ሲሉት መንፈሴ እንዴት ተበሳጨ መሰለህ? እነርሱ
የዜማውን ማማር እንጂ የቃላቱን ምስጢር መች ልብ አሉት ብለህ ነው?" አለ በሐዘኔታ፡፡
ወደ ደብራቸው እየተቃረቡ ሲመጡ መሪጌታ በትረ ጽዮን ጠይቆ ያልተመለሰለት ጥያቄው ትዝ
አለውና፥ "በነገራችን ላይ የጥቅሱን ነገር አረሳሳኸኝ እኮ?" አለው፡፡ ምን እኔ አረሳሳሃለሁ? አንተ ነህ
እንጂ ከጥያቄ ወደ ጥያቄ እየዘለልህ ያዘናጋኸኝ? … ለማንኛውም እስኪ የጠቀስሃቸውን ጥቅሶች እንመልከታቸው" አለና
የመጀመሪያውን ጥቅስ 1ቆሮ. 1፥18ን በቃሉ አነበበለት፡፡ "ልብ በል! 'የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ
ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነውና' ነው የሚለው፡፡ በነገራችን ላይ ይህና ሌሎቹም ከጳውሎስ መልእክታት ውስጥ ስለ ዕፀ
መስቀል ተብለው የተጠቀሱት ሁሉ የሚናገሩት ስለ መከራ መስቀሉ ነው፡፡ ትራክቱን ያዘጋጁት ክፍሎች ግን ገና ለገና 'መስቀል'
የሚል ቃል ይዟል ብለው ስለ ዕፀ መስቀሉ እንደ ተነገረ አድርገው አቀረቡት፡፡ ለምሳሌ 1ቆሮ. 1፥18 'የመስቀሉ ቃል' ነው
የሚለው፡፡ ይህም ኢየሱስ በመስቀል ተሰቅሎ የመሞቱ ነገር ለሚጠፉ ሰዎች እንደ ሞኝነት የሚቈጠር ሲሆን፥ ለምንድነው ግን
የእግዚአብሔር ኀይል እንደ ሆነ የሚናገር ነው፡፡ አባቶቻችን ባዘጋጁት የአንድምታ ትርጓሜ ላይ ለዚህ ጥቅስ የሰጡት ፍቺ ይኸው
ነው፤ ከዚህ ውጪ 'አንድም' ብለው ስለ ዕፀ መስቀሉም ይናገራል ብለው የጨመሩት ነገር የለም፡፡
"ሌሎቹም ሁሉ ስለ መከራ መስቀሉ የተነገሩ ናቸው፡፡ በተለይ ግን 'ብዙዎች
ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ' የሚለው በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ የሰፈረው ቃል መጠቀስና መብራራት አለበት፡፡
ምክንያቱም አንዳንዶች ለመከራ መስቀሉ የተነገረውን ይህን ቃል ለዕፀ መስቀሉ ጠቅሰው፥ ዕፀ መስቀሉ ያልተሰጠውን ስፍራ
እንዲያገኝ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ፥ ይህ ስሕተት መሆኑ ሲነገራቸው፥ እንዲህ ያለውን ሰው 'የመስቀል ጠላት' ብለው
ይፈርጃሉ፡፡ ቃሉን በተነገረበት ዐውድ መተርጐም ትክክለኛ አንድ ነገር ነው፤ ለራስ ሐሳብ ደጋፊ አድርጎ መጥቀስ ግን ሌላ ነገር
ነው፡፡
"ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ እንዲናገር ያስገደደው ምንድን ነው? የሚለውን
ለመመለስ፥ ቢያንስ ከፊልጵስዩስ መልእክት ምዕራፍ ሦስትን ከመጀመሪያው አንሥቶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ጳውሎስ የክርስቶስ
መስቀል ጠላቶች ያላቸው፥ በአይሁዳዊ ማንነታቸውና በመገረዛቸው እየተመኩ፥ ለሚድኑት የእግዚአብሔር ኀይል የሆነውን የክርስቶስን
መከራ መስቀል ከንቱ የሚያደርጉትን ትምክሕተኞች ነው፡፡ እርሱ ራሱ እነርሱ በሚመኩበት ነገር ልመካ ቢል ከእነርሱ በበለጠ
ሊያስመካው የሚችል ነገር እንዳለው በዚህ ክፍል ይዘረዝራል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ጕዳይ ጌታው ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቁ ጋር
ሲያነጻጽረው ያን ሌሎች የሚመኩበትን ነገር እንደ ጕድፍ ሆኖ ነው ያገኘው፡፡ ስለዚህ ወደ ተጠራበት ግብ ለመድረስ መገሥገሡን
እንደሚቀጥል ይናገራል፡፡ መልእክቱን የጻፈላቸው የፊልጵስዩስ ሰዎችም ይህን ምሳሌነት እንዲከተሉ ሲያሳስባቸው፥ ሌሎችም በዚሁ
ምሳሌነት የሚኖሩ መሆናቸውን እንዲመረምሩ ያሳስባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው የሚመላለሱ
መሆናቸው ስለ ታወቀ ነው፡፡ እነዚህም በምዕራፉ መነሻ ላይ የጠቀሳቸው በሥጋ አለን በሚሉት ነገር የሚመኩትንና የክርስቶስን መከራ
መስቀል ከንቱ የሚያደርጉትን ወገኖች የሚመለከት ነው፡፡ ዛሬም መከራ መስቀሉን በዕፀ መስቀሉም ሆነ በሌላ ነገር ለመተካት
የሚሯሯጡ ሁሉ ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች መሆናቸው ነው፡፡"
"ጓዴ ታዲያ ምን እየሆንን ነው? ወዴትስ እያመራን ነው? መፍትሔውስ ከቶ ምን
ይሆን? ደግሞስ ይህን ለዘመናት የቈየ ባህል እንዴት ማሻሻልና ማስተካከል ይቻላል? በዕፀ መስቀሉና በመከራ መስቀሉ መካከል
ያለው ልዩነት ሳይገባን እያደነጋገረን እስከ መቼ ነው የምንቀጥለው?" እያለ መፍትሔ የሚሹ ጥያቄዎችን አዥጐደጐደ፡፡
መሪጌታ በትረ ጽዮን እነዚህን ጥያቄዎች ሲያቀርብ፥ በዕፀ መስቀሉና በመከራ መስቀሉ መካከል ያለው ልዩነት ፍንትው እያለለት
መጥቷል፡፡ ውስጡም እስካሁን ሲኖርበት ባላስተዋለውና ስሕተት መሆኑ እየታየው በመጣው ትምህርት፥ እንዲሁም አሁን ባሸነፈው
እውነት መካከል እየታመሰ ነበር፡፡
ወደ መኖሪያቸው እየደረሱ ሳለ፥ "ልክ ነህ ባልንጀሬ" አለ መሪጌታ ብርሃነ
መስቀል፥ "ልክ ነህ ባልንጀሬ፥ ችግርን መዘርዘር ቀላል ነው፡፡ መፍትሔውን መፈለግ ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ መፍትሔው እንዲህ
እንዳወራነው ቀላልና በጥቂት ጊዜ የሚመጣ አይደለም፡፡ በእኔ በኩል የሚታዩኝ መፍትሔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
·
ቤተ ክርስቲያናችን
የመስቀልን በዓል ስታከብር፥ በዋናነት ዕፀ መስቀሉን ሳይሆን መከራ መስቀሉን ብቻ ልትሰብክ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በክቡር ደሙ
የዋጃትና ሙሽራዋ የሆነላት የተሰቀለው ኢየሱስ ብቻ ነው እንጂ እርሱ የተሰቀለበት መስቀል፥ ወይም ሌሎች ነገሮች አይደሉም፡፡
ስለዚህ በምንም ምክንያት በዓል ታድርግ ወይም ትሰብሰብ መስበክ ያለባት አዳኟን ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ
ይላልና፤ "መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን
እንሰብካለን፡፡" (1ቆሮ. 1፥22-23)፡፡
"በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ
በቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቈርጬ ነበርና፡፡" (1ቆሮ. 2፥2)፡፡
·
ይህን በወንጌል የተገለጸውን
መልካም ዜና፥ ላልሰሙት ወይም ላላስተዋሉት መንገር ይህን እውነት ከተረዳ ከያንዳንዱ ክርስቲያን ይጠበቃል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ
ተጻፈ፥ "እናንተ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ
ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ" (1ጴጥ. 2፥9)፡፡ በእውነቱ ኢየሱስ ስለ ኀጢአታችን ተሰቅሎ
ከመሞቱና ዕዳችንን ከመክፈሉ የበለጠ የእርሱ በጎነት ምን አለ?
·
በጨለማ ውስጥ ያሉ ብዙዎች
ወደሚደነቀው ብርሃን እንዲወጡና በክርስቶስ የተፈጸመላቸውን ድኅነተ ነፍስ በእምነት እንዲቀበሉ ስለ እነርሱ ዘወትር ምልጃና
ጸሎት ልናቀርብ ይገባል፤ "የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው" (ሮሜ
10፥1)
"ልመናና ጸሎት፥ ምልጃም ምስጋናም ስለ
ሰዎች ሁሉ፥ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፡፡ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ
ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኀኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው፡፡" (1ጢሞ. 1፥1-4)፡፡
እስኪ ለማንኛውም ወደ ማደሪያችን እንግባና የጀመርነውን ሐሳብ በውል እንቋጨው፡፡"
አለውና ተያይዘው ወደ እርሱ መኖሪያ ገቡና በሩን ከውስጥ ቈለፉትና ተቀመጡ፡፡
መሪጌታ ብርሃነ መስቀል፥ "መቼም ርምጃው የሚጀምረው ከራስ ነው፡፡" በማለት
ንግግሩን ጀመረ፡፡ "ስለ እኔ ጥቂት ነገር ልንገርህ፡፡ እንደምታውቀው እኔም እስካሁን ስሕተት ነው እያልሁ እናገረው
በነበረው ትምህርትና ሥርዐተ አምልኮት ውስጥ ነው ያለፍሁት፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት ትምህርት የኖርሁበትን ሃይማኖት ስመዝነው
ግን በአንዳንድ ሁኔታ በተሳሳተ ነገር ውስጥ እንዳለሁ ተረዳሁ፡፡ በዋናነት፥ ስለ ኀጢአቴ የሞተልኝንና ዕዳዬን የከፈለልኝን ጌታ
ለይቼ ሳላውቀውና ለእርሱ ብቻ ራሴን ሳላስረክብ፥ ለእርሱም ብቻ ሳልገዛ ባሳለፍኋቸው ዓመታት ተጸጸትሁና፥ ኀጢአተኛነቴን
በመቀበልና በመናዘዝ ስለ እኔ መዳን በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ኀጢአቴ ሁሉ እንዲታጠብ ጸለይሁ፡፡ እግዚአብሔርም በሕያው ቃሉ
እንዳረጋገጠልኝ ኀጢአቴ እንደ ተሰረየ አመንሁ (1ዮሐ. 1፥7)፡፡ ያን ጊዜ እንዲህ ነው የማይባል ሰላምና ዕረፍት በውስጤ
ሲያልፍ ይታወቀኛል፡፡ ከዚያ በኋላም በዚያው ዕረፍት ውስጥ ነው ያለሁት፡፡
"ስለዚህ አንተም የተነጋገርንበት ሐሳብ እውነት መሆኑን ከተረዳህ ወደ ውሳኔ
መምጣትና ከእግዚአብሔር ጋር መኖር መጀመር ትችላለህ፡፡ ስላለፈው ኀጢአትህና በደልህ አንድ ጊዜ ለዘላለም የፈሰሰው የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ዛሬም ሕያው ነው፤ ኀጢአትህንና በደልህን ያጥብልሃል 'ወደሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያነጽሐነ እምኲሉ
ኀጣውኢነ (የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል)' የሚለው ቃሉ ዛሬም ሕያው ነው" በመሪጌታ በትረ
ጽዮን ጕንጮች ላይ እንባው መንታ መንታ እየሆነ ይወርድ ነበር፡፡
ድንገትም ማንም ሳያዘው ከተቀመጠበት ሸርተት ብሎ ወለሉ ላይ ተንበረከከና እጆቹን ወደ ላይ
ዘርግቶ፥ "ጌታ ሆይ እባክህን ይቅር በለኝ፤ እኔ ኀጢአተኛ ነኝ፤ ሲተረክ ብሰማም የሞትኸው ዕዳዬን ለመክፈል መሆኑ
እስከ ዛሬ አልገባኝም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ገብቶኛል፡፡ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና እንደ ምሕረትህ መጠን ኀጢአቴን ሁሉ
ይቅር በል፡፡ የወንጌልህን ብርሃን እንዳላይ ዐይነ ልቡናዬን ከልሎት የነበረው ጨለማ ስለ ተገፈፈልኝና መከራ መስቀልህን ማየት
ስለቻልሁኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ የተሰቀልህልኝን አንተን ዐልፌ የተሰቀልህበትን የዕንጨት መስቀል ሳመሰግንና ሳመልክ የኖርሁባቸውን
ዓመታት ሳስብ እጅግ ዐፍራለሁ፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ሳደርግ የኖርሁት ማን አዚም አድርጎብኝ ይሆን እያልሁም እደነቃለሁ፡፡ አሁን
ግን ዐይኖቼ ተገልጠዋል፡፡ ጥያቄዎቼ ሁሉ ተመልሰዋል፡፡ ፍጹም ሰላምና ዕረፍት አግኝቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ እኔ በውድና በክቡር
ደምህ የዋጀኸኝ ያንተ ገንዘብ ነኝ፤ የሞትህላትና የተቤዠሃት ነፍሴ ከዚህ በኋላ ላንተ ብቻ እንጂ ለሌላ አትገዛም፡፡ ጌታዬ ሆይ
ኀጢአቴን ይቅር ብለህ፥ በደሌንም ደምስሰህ ስለ ተቀበልኸኝና ልጅህ ስላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ …" እያለ ከእንባ ጋር ለደቂቃዎች
ከጸለየ በኋላ ከተንበረከከበት ተነሣ፡፡ በተፈጠረው ሁኔታ መሪጌታ ብርሃነ መስቀልም በደስታ እያነባ በለኆሳስ (በሹክሹክታ) እግዚአብሔርን
ያመሰግን ነበር፡፡
በጮራ
ቍጥር 40 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment